
በጥናት ላይ የተመሰረተ ክትትል በዓለም አቀፍ በአደገኛ እፅ አዘዋዋሪነት የተጠረጠሩ 13 ናይጄሪያውያንና አንዲት ብራዝላዊት ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
የኮሚሽኑ ወንጀል መከላከል ዘርፍ የአደገኛ እፅ ቁጥጥር ምክትል ዳይሬክቶሬት አባላት በዛሬው ዕለት በቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ባደረጉት ፍተሻ ነው መነሻቸውን ላቲን አሜሪካ፣ ሳኦፖሎ ከተማ፣ መዳረሻቸውን ደግሞ የተለያዩ ሀገራት ለማድረግ በአውሮፕላን ሲጓዙ የነበሩ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ያዋሏቸው፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ከ14 ኪ.ግ በላይ የሚመዝን ኮኬይን የተሰኘ አደገኛ ዕፅ ይዘው የተገኙ ሲሆን አደገኛ ዕፁ በላቲን አሜሪካ አካባቢ የሚመረትና በአለም አቀፍ ደረጃ የሚዘዋወር መሆኑን የወንጀል መከላከል ዘርፍ የአደገኛ ዕፅ ቁጥጥር ኦፕሬሽን ምክትል ዳይሬክተር ኮማንደር መንግስትአብ በየነ ገልጸዋል፡፡
እስካሁን በተሰሩ ሥራዎች በሶስት ወር ውስጥ ብቻ ወደ 24 የወንጀሉ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር መዋላቸውንና 39 ኪ.ግ ኮኬይንና 36 ኪ.ግ የሚመዝን ካናቢስ የተባለ አደገኛ እፅ መያዙን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡ (ፌደራል ፓሊስ)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply