በደቡብ ኦሞ የነዳጅ ፍለጋ ጉድጓድ ቁፋሮ ተጀመረ
በደቡብ ኦሞ ጨው ባህር አካባቢ የነዳጅ ፍለጋ ሥራ በማካሄድ ላይ የሚገኘው ታሎው ኦይል የተሰኘው የእንግሊዝ ኩባንያ የመጀመሪያው የሆነውን የፍለጋ ጉድጓድ ቁፋሮ ከትናንት በስቲያ ጀመረ፡፡ ቁፋሮው የተካሄደው በደቡብ ክልል በደቡብ ኦሞ ዞን በዳሰነች ወረዳ ከኦሞራቴ ከተማ 15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው፡፡ የነዳጅ ፍለጋ ቁፋሮ የተጀመረው 18 ወራት የዘለቀ የሴይስሚክ (በመሬት የድምፅ ሞገድ በሚከናወን) ጥናትና 18,000 ኪሎ ሜትር በሸፈነ የአውሮፕላን የግራቪቲ ጥናት ከተከናወነ በኋላ እንደሆነ ኩባንያው ገልጿል፡፡ የአየር ጥናቱ በዓለም ላይ ከተከናወኑት ሰፊ ጥናቶች ውስጥ ይመደባል ተብሏል፡፡ ጥናቶቹ በደቡብ ኦሞ ዞን የመጀመሪያው የነዳጅ ፍለጋ ጉድጓድ የት አካባቢ መቆፈር እንዳለበት ያመላከቱ እንደሆነ ኩባንያው አስታውቋል ሲል የዘገበው ሪፖርተር ነው።
የመጀመሪያው የፍለጋ ጉድጓድ (Wild Cat Well) ሳቢሳ አንድ በመባል የተሰየመ ሲሆን፣ ሳቢሳ ማለት በደቡብ ኦሞ ዞን ጨው ባህር አካባቢ የምትገኝ የወፍ ዝርያ ናት፡፡ የመጀመሪያው የነዳጅ ፍለጋ ጉድጓድ በወፏ ስም ተሰይሟል፡፡
የታሎው ኦይል ኢትዮጵያ ዋና ኃላፊ አቶ ጴጥሮስ አበበ ኩባንያው ካካሄዳቸው የጂኦሎጂ ጥናቶች የተገኙ መረጃዎችን ከተተነተኑ በኋላ፣ ቦታ ተመርጦ ቁፋሮ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡ ቁፋሮውን እያከናወነ ያለው ኦጄክ የተሰኘ የፖላንድ ኩባንያ መሆኑን ያስረዱት አቶ ጴጥሮስ “አሁን የተጀመረው የነዳጅ ማፈላለግ ቁፋሮ በደቡብ ኦሞ ዞን ነዳጅ ስለመኖሩ የሚፈትሽ ሲሆን ውጤቱንም በወራት ውስጥ ማወቅ ይቻላል” ብለዋል፡፡ አክለውም በተያዘው የአውሮፓውያን ዓመት ሁለት ተጨማሪ የነዳጅ ጉድጓዶችን በዞኑ ለመቆፈር እንደታቀደ ገልጸዋል፡፡
ታሎው ኦይል የነዳጅ ፍለጋ ሥራውን ሲያከናውን ከማዕድን ሚኒስቴርና ከሌሎች የመንግሥት አካላት እንዲሁም አጋሮች ጋር በቅርበት በመሥራት ላይ እንደሆነ ኩባንያው አስታውቋል፡፡ ታሎው ኦይል መቀመጫው ለንደን የሆነ የግል የነዳጅ ፍለጋና ምርት የሚያከናውን ድርጅት ሲሆን በለንደን፣ በአየርላንድና በጋና ስቶክ ኤክስቼንጅ የተመዘገበ ኩባንያ ነው፡፡
ታሎው በጋና ከፍተኛ መጠን ያለው የነዳጅ ዘይት አግኝቷል፡፡ ከአራት ዓመት በፊት በኡጋንዳ አልበርት ቤዚን ተመሳሳይ መጠን ያለው የነዳጅ ከምችት አግኝቷል፡፡ ባለፈው ዓመት ታሎው በኬንያ ቱርካና ቤዚን የነዳጅ ክምችት ማግኘቱም ሪፖርተር አስታውሷል።
ግብጽእያስፈራራችነው
ካርቱምና ግብጽ ፊርማቸውን ያላኖሩበት የናይል ተፋሰስ አገሮች ስምምነት ዋጋ የሌለው መሆኑን አስታወቀች። የህዳሴ ግድብንም መጎነታተል ጀምራለች። የግብጽ የውሃ ሃብትና መስኖ ሚኒስትር ዶ/ር መሐመድ ባሃራ ከቻይና ዜና ወኪል ዡንዋ ጋር 12/2/2013 ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳስታወቁት የናይል ተፋሰስ አገሮች የሚያካሂዱት ማናቸውም ፕሮጀክቶች ግብጽን በአሉታዊ መልኩ የሚነካ ከሆነ አገራቸው ዝም አትልም።
የግብጽ ውሃ ኮታ መቀነሱን ያስታወቁት ሚኒስትሩ ቻይና ለናይል የላይኛው ተፋሰስ አገሮች ከውሃ ፕሮጀክቶች ጋር በተያያዘ የምትሰጠው ርዳታ ግብጽን የሚጎዳ መሆን እንደሌለበት ማረጋገጥ እንዳለበት አሳስበዋል። የአባይ ተፋሰስ አገሮች ሙሉ በሙሉ በውሃው አጠቃቀም ዙሪያ አዲስ በተረቀቀው ስምምነት ላይ ፊረርማቸውን ያኖሩ ሲሆን ግብጽና ካርቱም አልፈረሙም። ካርቱም ለመፈረም መዘጋጀቷን በይፋ አስታውቃ ነበር።የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ በአባይ ወንዝ ጉዳይ መጠቀም መብት ለድርድር እንደማይቀርብ፣ አሁን የተጀመረው ፕሮጀክትም ግብጽን እንደማይጎዳ በባለሙያዎች አስጠንቶ ማቅረቡ አይዘነጋም። ከሶስት ወር በኋላ የሚቀርብ የግብጽ ባለሙያዎች የተካተቱበት ጥናት እንደሚኖር መገለጹም የሚታወስ ነው።
ቴዲ ደቡብ አፍሪካ በኢትዮጵያመለያ
ስለፍቅር ሲባል፣ ስለ ጸብ ካወራን ተሳስተናል፤
አንድ ላይ ሆነን ተለያይተናል፤
አተናል እውነት ነው ተቸግረን ብዙ አይተናል፤
የመጣነው መንገድ ያሳዝናል …፤
ቴዲ በሚሰረስሩት ስንኞቹ መድረክ ላይ ሆኖ ያዜማል፤ ይጠበባል። ስንኝ ቋጥሮ ይፈታል። ስሜትን ያምሳል። ልብ ብለው ሲያዳምጡት የህሊናን በር ዘልቀው የሚገቡ ግጥሞቹ ስሜትን ይፈነቅላሉ። “ … አመመኝ፣ አመመኝ፣ ያኔ ገና ውስጤን አመመኝ፣ ውስጤን አመመኝ” ብሎ ልብ የሚያስለቅሰው ቴዲ ከነሙሉ ባንዱ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ቡድን መለያ ለብሶ በደቡብ አፍሪካ ወገኖቹ ፊት “አሃሃ … ወሬ” ሲል ያድናቆት ጩኸት ወርዶለታል።
የሚያደርገውን የሚያውቀው፣ ሙያውን ያላሻቀጠውና ከወቅት ጋር የሚደወረው ቴዲ የኢትዮጵያችን አምባሳደር ሆኖ
አተናል እውነት ነው ተቸግረን ብዙ አይተናል፤
የመጣነው መንገድ ያሳዝናል … እያለ ጥበብ ፈልፍሎ ስሜትን ሲቆላ ባመሸበት መድረክ የታየው ስሜት ኢትዮጵያን ሰው አያሳጣሽ የሚያሰኝ እንደነበር በስፍራው የተገኙ ተናግረዋል። ቴዲ አፍሮ ስለታሪክ፣ ስለ እምነት፣ ስለ እትብት፣ ስለ ምድራችን በሚያትተው ዜማው “ቀስተደመና ነው የለበስኩት ጥበብ የያዝኩት አርማ” እያለ አገርን አጉልቶ አሳይቷል።
ለዋሊያዎቹ “ኢትዮጵያ ቅደሚ”
ሁለት ዓይነት ባንዲራ ለአንድ አገር?
ጠንካራ ብሄራዊ ቡድን እንዳልገነባች የተነገረላት ደቡብ አፍሪካ በደገሰችው 13ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ የሚሳተፉት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አባላት ተሸልመው፣ ተደራጅተውና ነቅተው “ልማታዊ ተጫዋች ” ተደረገው ሲያበቁ ውድድሩ ከሚካሄድበት አገር ገብተዋል።
ጥር 21 ቀን የመጀመሪያ ጨዋታቸውን የሚያደርጉት ዋሊያዎቹ በደቡብ አፍሪካ በሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ከፍተኛ ድጋፍ ይደረግላቸዋል። ይህም ለጨዋታው ሃይል እንደሚሆን ይገመታል። ከብሄራዊ ቡድኑ መሰረታዊ ተልኮ ውጪ አቶ መለስን ለማስታወስ በሚል ለማከናወን የታሰቡት ጉዳዮች የቡድኑን ስነልቦና እንዳያበላሽው ግን ተፈርቷል።ኢሳት ከደቡብ አፍሪካ በስልክ ያነጋገረቸው ፍርሃቻቸውን በማስጠንቀቂያ አስተላልፈዋል።በደቡብ አፍሪካ ሁለት ብሄራዊ መዝሙር፣ ሁለት ዓይነት ሠንደቅዓላማና ሁለት ዓይነት ደጋፊዎች ለአንድ አገር ብሄራዊ ቡድን በማዘጋጀት ኢትዮጵያ ልዩ ታሪክ ልታስመዘግብ ትችል ይሆናል። ጨዋታውን አስመልክቶ አቶ ሃይለማርያም ደሰለኝ “ማለፋችሁ በራሱ በቂ ነው። የምትችሉትን የኳስ ጥበብ አሳዩና ተመለሱ። ዋንጫ ባንጠላም …” በማለት ከአቅም በላይ ምኞት እንዳይኖር አስቀድመው አሳስበዋል። ኢትዮጵያ በፊፋ ሰንጠረዥ 110ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
የከተራ በዓል ተከበረ፣ ሙስሊሞች ትብብር አደረጉ
በመላው የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ታላቅ ዋጋና ክብር የሚሰጠው የከተራ በዓል ጥር 11 ቀን 2005 ዓ ም ተከብሯል። ምዕመናን በየአጥቢያቸው በሚገኙና ባመቻቸው አድባራት በመገኘት ታቦት በማጀብ በዝምሬና በሽብሸባ በዓሉን ሲያደምቁ ታይተዋል። የቤተክርስቲያን መሪዎች፣ ዲያቆናት፣ ዘማሪዎችና ካህናት በደብር አልባሳት ተውበው ክብረ በዓሉን አድምቀዋል። የእምነቱ ቤተሰቦች ጎዳና ሞልተው፣ ጎዳና አስውበውና አጊጠው በዕልልታ ታቦት በመሸኘትና መልሶ በማስገባት ስርዓተ አምልኳቸውን አከናውነዋል።
በመላው አገሪቱ የሚከበረው የጥምቀት በዓል አስመልክቶ ጥር አስራ አንድ ቀን የአሜሪካ ሬዲዮ አማርኛ ፕሮግራም ባስተላለፈው ዘገባ አንድ የሙስሊም እምነት ተከታይ ሴት አቅርቦ ነበር። በእለቱ የሙስሊሞች “የድምጻችን ይሰማ” ጥያቄ አንደኛ ዓመት የሚታሰብበት ቀን ቢሆንም ለክርስቲያን ወንድምና እህቶች ሲሉ ታላቁን የአንዋር መስጊድ አለመጠቀማቸውን እንግዳዋ ይፋ አድርጋለች። ይህንን ያደረጉት ከአንዋር መስጊድ ጎን ካለው ራጉኤል ቤተክርስቲያን ታቦት ሲወጣ ችግር እንዲፈጠር የታሰበውን ተንኮል ለማምከንና በስፍራው ትርምስ እንዳይፈጠር ለመላው ሙስሊሞች በተላለፈ መልዕክት ምክንያት ነው። እንዲህ ያለው የኖረ መከባበር በርካቶችን አስደስቷል።
“ለ3ኛ ጊዜ ጥምቀትን ተከትሎ የሚካሄደው የኢትዮጵያን በጎንደር የባህል ፌስቲቫል ቀዝቀዝ ባለሁኔታ መከበሩን ዘጋቢያችን ከስፍራው ገልጿል” በማለት ኢሣት ዘግቧል፡፡ “በሲምፖዚየሙ ላይ አቶ በረከት ስምኦን ፤የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሩ አቶ አሚን አብዱልቃድር፣ የስነምግባርና ጸረሙስና ኮሚሽነሩ አቶ ዓሊ ሱሌይማን እና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት መገኘታቸው” ኢሣት ጨምሮ አስታውቋል፡፡
ኑሮ እንደተሰቀለ ነው፤ ግሽበት 12.9 በመቶ ደረሰ ተባለ
ባለፈው ታህሳስ ወር የነበረው የዋጋ ግሽበት ባለፈው አመት ከነበረው 35.9 በመቶ ወደ 12.9 በመቶ መውረዱን ፥ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሀጂ ኢብሳ ተናግረዋል። የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር በገንዘብ አቅርቦቱ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር መደረጉ፣ የበጀት ጉድለት አነስተኛ እንዲሆንና ጉድለቱም ከብሄራዊ ባንክ በሚገኝ ብድር ሳይሆን በኢኮኖሚ ወስጥ ከሚንቀሳቀሰው ገንዘብ በመሸፈኑ ለዋጋ ንረቱ መቀነስ እንደ ምክንያትነት ተጠቅሷል።
ቀደም ሲል ወደ ሀገር ውስጥ የገባ 8 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ፣ 2.5 ሚሊዮን ኩንታል ስኳርና 25 ሺህ ቶን ዘይት ለህብረተሰቡ እንዲቀርብና ገበያ እንዲረጋጋ ማስቻሉን፣ 15ሺ ሊትር ዘይትና 2 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ በመጋዝን ላይ እንደሚገኝ፣ እንዲሁም በያዝነው ወር መጨረሻም 4 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴና 252 ሺህ ኩንታል ስኳር ሀገር ውስጥ በማስገባት በቀጣይ እንደሚፋፈል ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። በመንግስት በኩል ይህ መግለጫ ቢሰጥም ኑሮው ባለበት እንደተሰቀለና ህዝብ በኑሮው ያገኘው ለውጥ እንደሌለ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እየተናገሩ ነው። አንዳንዶች አቅርቦቱ መሻሻሉን አሁን ከሚካሄደው የአካባቢ ምርጫ ጋር አያይዘውታል። (ዘገባው የተወሰደው ከፋና ብሮድካስቲንግ የጥር 10 ፣ 2005 ዜና ላይ ነው።)
emamudin akmel says
we found arealy good information in your site,,,thank’s 4 your info.
koster says
What is going on in Ethiopia is not development but looting as was the case in JELZIN Russia. Woyane ethnic fascists and their collaborators are enriching themselves by looting and 10 or 20% inflation is not their problem. It is the poor Ethiopians who are languishing under woyane ethnic fascists looting and terrorizing.