“አትነሳም ወይ” በሚል በሰማያዊ ፓርቲ ድረገጽ አናንያ ሶሪ ባስነበቡት ጽሁፍ ስለ “መነሳት” የተለያዩ ሃሳቦችን በማንሳት እይታቸውን አስፍረዋል። መነሳትን ከህይወት፣ ከህይወት ክንውኖች፣ ከህይወት ስንብትና ከመቃብር እስከመውጣት ባሉ ጉዳዮች በማዋዛት አሳይተዋል።በተለይም “አትነሳም ወይ” በማለት ኢህአዴግንም ፈክረውለታል። ጎልጉል በቀጥታ ከጽሁፉ የወሰደውን በማቃመስ ዋናውን ጽሁፍ በድረገጹ ላይ ታነቡ ዘንድ ይጋብዛል።
“ … አትነሳም ወይ?! ከእንቅልፍ ነው? ከሞት ነው? ከሞት ከበረታ ድንዛዜ ነው? ፎቶ ነው? ራጂ ነው? ክርስትና ነው? … በክፉ ነው የምትነሳው? በደግ ነው የምትነሳው? በትንሳዔ-ሙታን ነው የምትነሳው? በምንድነው የምትነሳው? ለምንድነው የምትነሳው? ወዴት ነው የምትነሳው? መቼ ነው የምትነሳው? እንዴትስ ነው የምትነሳው?…
“… መቼም ኢትዮጵያውያን በባህላችን ብልፅግና የተነሳ አንድ ትልቅ ሰው ወይም አረጋዊ ከውጭ መጥቶ ወደቤት ውስጥ ሲገባ ከተቀመጥንበት ብድግ ብለን ተነስተን “ኖር! ኖር!” እንላለን፡፡ ምላሹም “በእግዜር!” አሊያም “እረ በልጆቻችን!” ይሆናል፡፡ ታዲያ አንተ ወንድሜስ ለእንዲህ ዓይነቱ የትልቅ ሰው አክብሮት የሚገባውን መነሳት ነው የምትነሳው? ማለቴ-ክብር ለሚገባው ክብርን ለመስጠት፡፡ አሊያስ ከወደቅህበት ረግረግ እና ረመጥ ውስጥ ነው የምትነሳው? …
“… ወይ ኪስህ ወይ ቀኑ ጐደሎብህ፣ ወይ ርቦህ አሊያም ታመህ፣ ወይ ደክሞህ ፣ ወይ መሄጃ አጥተህ፣ ወይ ጭንቀትህን ማራገፊያ ወይ ጊዜህን ማሳለፊያ አጥተህ፣ ወይ ድህነትን አሊያም ጭቅጭቅን ሸሽተህ፣ ወይ ሰክረህ ወይ አብደህ ከየአውራ-ጐዳናዎቹ ጥጋጥግ እስከ ጫት ቤቶች ምንጣፍ እንዲሁም ከየካቲካላ ቤቶች ደጃፍ እስከምናምንቴ ‘አልጋ-ቤት’ ተብዬዎች ፍራሽ የተረፈረፍከው ወጣት አወዳደቅህ ምንኛ አሳዛኝ እና ታላቅ ኖሯል?! …
“… ኦ ወንድሜ …. ከዚህ የበለጠ ውድቀትስ ምን አለ? በቁም ከመሞት የበለጠ ሞትስ በወዴት አለ; አደራ-አልሞትኩም ብለህ ራስህን እንዳታታልል …
“… የኢህአዴግ አስተዳደር ድርጅቱ ከወደቀበት የአፍቅሮተ-ሥልጣን ቁልቁለት ሊነሳ ይገባዋል! ከግል-ጥቅመኝነት እና ከፍርሃት ስርቻ ውስጥ ሊነሳ ግድ ይለዋል፡፡ በየቀኑ ከሚለፍፈው ሃሳዊ-ህዳሴ ወደ እውነተኛው ህዳሴ ሊሸጋገርና ሁላችንንም ሊጠቅም በሚችል ፍኖት ጉዞ ሊጀምር ብሎም የመንፈስ-ወኔን ሊያሳይ ጊዜው ደርሶበታል፡፡ ህዳሴ /Renaissance/ የሰዎችን እምቅ-ሃይል በነፃነት እንዲለቀቅ የሚያደርግ የአብርሆት /Enlightenment/ መንገድ እንጂ በሰዎች ውስጥ ያለው ብርሃን እንዲዳፈንና እንዳይገለጥ የሚያደርግ መክሊት-ቀባሪ የአምባገነንነት የጨለማ ድንብርብር አይደለም፡፡ …
“… ኢህአዴግ ሆይ፡- አንተስ አትነሳም ወይ? ራስህን ከማታለል እንቅልፍ! ህዝቡ ከኔ ጋራ ነው ብለህ ስለምን ትኩራራለህ? ህዝብማ እንኳን ከአንተ ጋር ከእውነተኛው አምላክ ከኢየሱስም ጋር አልነበር! ከሙሴም ጋር እንደዚያው! ታዲያ ስለምን በሀሰት ኘሮፖጋንዳህ አቅል እየነሳህ በፍርፋሪ የሰበሰብካቸውን መንፈሰ-ደካማዎች ተማምነህ ረጅም ጉዞ ታስባለህ? ወይንስ 5ቱን እንጀራ እና 2ቱን ዳቦ በተዓምር ቀይረህ ተዓምራዊ ሊባል የሚችል ዕድገት አስመዝግበህ ሁላችንንም ታጠግበናለህ? ለማንኛውም በአሸዋ ላይ የተገነባ ቤት ዝናም ጐርፍና ነፋስ በመጣ ጊዜ እንደሚፈርስ ከቶም አትዘንጋው! …
“… ኢህአዴግ ሆይ፡- ለራስህ ስትል ጣፍጥ አሊያ ድንጋይ ነው ብለን ወደ ደጅ አውጥተን እንጥልሃለን! ከህዝቡ ጫንቃ ላይ እንደመዥገር ተጣብቃችሁ የህዝቡን ደም ስትመጡ እና አጥንቱን ስትግጡ የምትኖሩ ጥገኛ-ተውሳክ ካድሬዎች ሆይ፡- ከኢኮኖሚያችን፣ ከፖለቲካችን፣ እና ከማህበራዊ-ህይወታችን ላይ ተነሱ! አሊያ ግን የህዝብ እንባና ሮሮ ጐርፍ ሆኖ ይጠራርጋችኋል-በጊዜ ንቁ!”
Leave a Reply