
መነሻውን አዲስ አበባ ከተማ ያደረገ አንድ ህገወጥ የገንዘብ አዘዋዋሪ ግለሰብ ዶላር እና ዩሮ በመኪና ጭኖ ወደ ጅቡቲ በጉዞ ላይ እያለ በቁጥጥር ስር ውሏል።
ግለሰቡ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ3-68991 በሆነ ኮንቴነር ተሽከርካሪ ላይ 166 ሺህ 800 የአሜሪካን ዶላር እና 19 ሺህ 850 ዩሮ በመጫንና መዳረሻውን ጅቡቲ በማድረግ በመጓዝ ላይ እያለ በተደረገ ጥብቅ ክትትል መያዙን የኢፕድ ምንጮች ገልጸዋል።
በኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ ላይ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በደረሰው ጥቆማ አዘዋዋሪውን ከነ ገንዘቡ በቁጥጥር ስር እንዲውል ማድረጉንም ነው ምንጮቻችን ጨምረው የገለጹት፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ መነሻቸውን ሀረሪ ክልል ሀረር ከተማ ያደረጉ ሶስት ህገወጥ የጦር መሳሪያ አዘዋዋሪ ግለሰቦችም ከእነጦር መሳሪያቸው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን እነዚሁ የኢፕድ ምንጮች አስታውቀዋል።
ግለሰቦቹ በሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ2B 57711 በሆነ ሎንግ ቤዝ ተሽከርካሪ አንድ ብሬን ከባድ የጦር መሳሪያ ከ732 መሰል ጥይቶች ጋር እና 9130 የክላሽ ጥይቶች በመጫን መዳረሻቸውን ኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን ጊንር ወረዳ በማድረግ ላይ ሳሉ ነው በቁጥጥር የዋሉት።
እንደ ምንጮቻችን ገለጻ፤ የጦር መሳሪያውን ለኦነግ ሸኔ የሽብር ቡድን ለማቀበል በመንቀሳቀስ ላይ እያሉ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ከመነሻው ጥብቅ ክትትል ሲያደርግባቸው ቆይቷል።
በመጨረቻም ሶማሌ ክልል ኢረር ዞን ፊቅ ወረዳ ሲደርሱ ለሶማሌ ልዩ ሃይል ፖሊስ ጥቆማ በመስጠት አዘዋዋሪዎቹ ከነጦር መሳሪያቸው በቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉን ለመረጃው ቅርበት ያላቸው ምንጮቻችን አረጋግጠዋል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Good Job.