አባዬ – አለው የገበሬው ልጅ
አቤት – አለ አባቱ።
ይሄ የምሰማው ድምጽ ምንድን ነው?
የጃርቶች ድምጽ ነው ልጄ።
ባለፈው ስታርስ ጮኹ። ስትዘራ ጮኹ። ስታጭድ ጮኹ- አለው ልጁ።
ልክ ነህ – መለሰለት አባቱ።
ለምን?- አለ ልጅ።
የጃርት ጠባዩ ነው። ጃርት ይጮኻል እንጂ አይሠራም። ጃርት አያርስም፤ ስታርስ ይጮሃል። ጃርት አይዘራም፤ ስትዘራ ይጮሃል። አያጭድም፤ ስታጭድ ይጮሃል – አለው አባቱ።
ለምን? – ደግሞ ጠየቀ ልጁ።
ጃርት ከጮኸ እየሠራህ ነው ማለት ነው። ፍሬ እያፈራህ ነው ማለት ነው። ጃርት ጠፍ መሬት ላይ አይጮህም። ምርት ያለበት ቦታ ነው የሚጮኸው። ጃርት የራሱ ጉዳይ የለውም፤ የራሱ ሥራ የለውም። የሚችለው በሰው ሥራ ላይ መጮህ፤ እሾህ መርጨት እና ሰብል ማጥፋት ብቻ ነው። ጃርቶች ሲጯጯሁ ከሰማህ ያ ገበሬ እየሠራ ነው ማለት ነው። መሬቱ እያፈራ ነው ማለት ነው። – አለው አባቱ።
እና ምን ይሻላል? አለ ልጅ።
ተዋቸው፧ እኛም እንሠራለን፤ ጃርቶችም ይጩኹ።
እስከ መቼ?
ወጥመድ እስኪገቡ።
ጃርቶች ከጮኹ – በዚያ አካባቢ ምርት አለ ማለት ነው።
ዳንኤል ክብረት
Yemane mergia says
It is very interesting. Thanks a lot.