የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክርቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ በተደጋጋሚ ለመምከር ቀጠሮ የሚይዘውና ስብሰባ የሚቀመጠው የመተዳደሪያ ቻርተሩን በሚፃረር መልኩ የምዕራባውያንን ፍላጎት ለማስፈፀም እንደሆነ የዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር አቶ ፀጋዬ ደመቀ አስታወቁ፡፡
የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክርቤት የትግራይን ጉዳይ ለማየት የጠራውን ስብሰባ አስመልክተው መምህር ፀጋዬ ደመቀ በተለይም ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ ስሙ እንደሚያመላካተው የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክርቤት ስብሰባ ሊጠራ እና ሊመክር የሚችለው የዓለምን ጸጥታና ደህንነት ችግር ላይ የሚጥል ጉዳዮች ላይ ነው፡፡
ምክር ቤቱ በአገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት እንደማያችል በቻርተሩ ላይ በግልጽ ተቀምጣል፡፡ ለዓለም አቀፍ የፀጥታ ስጋት ተብሎ ሊወሰድ የሚችለው ደግሞ በዋነኝነት በሁለት አገራት መካከል ጦርነት ሲካሄድና አስከፊ ደንበር ዘለል ግጭት ሲከሰት ብሎም ግጭቶቹ ከአንድ አገር ቁጥጥር ውጪ ሲሆኑ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
ይህ ማለት ግን አንዳንድ ጊዜ የአገር ውስጥ የፀጥታ ችግሮች ለዓለም አቀፍ ፀጥታ ስጋት አይሆኑም ማለት እንዳልሆኑ ያስገነዘቡት አቶ ፀጋዬ፣ የኢትዮጵያ ያለችበት ወቅታዊ ሁኔታ ግን እንኳን ለዓለም ፀጥታ ለአጎራባች አገራት ስጋት የሚሆን አይደለም፣ ይልቁንስ ወራሪን አሸባሪው ህወሓት የማስወገድ ተግባር ነው ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ በአሁን ወቅት ለዓለም አቀፍ ፀጥታ ስጋት የሚሆን ችግር የለም ፣ወቅታዊ ሁኔታውን ከቁጥጥር ውጪ ያልሆነ እና በራሷ አቅም መፍትሔ ሊሰጠው የሚችል መሆኑን ያመላከቱት አቶ ፀጋዬ፣ይህ እስከሆነም የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክርቤት አጀንዳው ሊሆን እንደማይችል አስገንዝበዋል፡፡ (ኢፕድ)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply