ትህነግ ለሌላ አውዳሚ ጦርነት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሀይል እየመለመለ መሆኑን አንድ ዓለም አቀፍ ጋዜጠኛ አጋለጠ። ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጉዳዩን በሚገባ ተገንዝቦ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት መወጣት እንዳለበትም ገልጿል።
በአሸባሪው ትህነግ ጠብ አጫሪነት በተቀሰቀሰው ጦርነት ከፍተኛ ጉዳት በደረሰባቸው የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች ጉብኝት ያደረገው “የስኩፕ ኢንዲፔንደንት ዜና” ዋና ኤዲተር አላስቴየር ቶምሶን፤ የአሸባሪው ትህነግ ዋነኛ ፍላጎት ዳግም ጦርነት መቀስቀስ መሆኑን ከኢዜአ ጋር በነበረው ቆይታ ገልጿል።
የሽብር ቡድኑ ከዚህ ቀደም በርካቶችን በጦርነት በመማገድ ለሞት መዳረጉን አስታውሶ፤ ቡድኑ አሁንም ተመሳሳይ ተግባር ለመድገም እየተዘጋጀ ስለመሆኑ ነው የተናገረው።
ለዚህ ደግሞ በርካታ ቁጥር ያላቸውን ተዋጊዎች እየመለመለና እያሰለጠነ መሆኑን በአስረጂነት አንስቷል።በጦርነቱ እጅግ ከተጎዳው የህብረተሰብ ክፍል ለዳግም ጦርነት ምልመላ ማካሄዱ አሳዛኝ መሆኑንም ጠቁሟል።
በመሆኑም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጉዳዩን በሚገባ ተገንዝቦ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት መወጣት እንዳለበት ጠቅሶ፤ ይህን ማድረግ ካልተቻለ ግን ውጤቱ አደገኛ ሊሆን እንደሚችል ነው የገለጸው።
በጦርነቱ በተጎዱ አካባቢዎች ባደረገው ጉብኝት በተለይ በወልቃይት ጠገዴና ጸለምት አካባቢዎች በሽብር ቡድኑ የተጨፈጨፉ ዜጎችን ጅምላ መቃብር ስለመመልከቱ ተናግሯል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አሸባሪው ትህነግ ባለፉት 40 ዓመታት በአማራ ህዝብ ላይ ሲፈጽም የነበረውን ግፍ በጥናት አስደግፎ ይፋ ማድረጉን አስታውሶ በዚህም ዩኒቨርሲቲው በወልቃይት አካባቢ 20 የጅምላ መቃብሮችን ይፋ ማድረግ መቻሉንና ተጨማሪ ጥናት ማድረግ ከተቻለ ሌሎች የጅምላ መቃብሮች ሊገኙ እንደሚችሉ ገልጿል።
በመሆኑም በዓለም አቀፍ ደረጃ በጅምላ ጭፍጨፋ ላይ ምርምር የሚያደረጉ ባለሙያዎችን በመጋበዝ በስፍራው ተጨማሪ ጥናቶችን መከናወን እንደሚገባም ነው የጠቆመው። (ENA)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply