አንድ ምራቅ መዋጥ የጀመረ የ28 ዓመት ወጣት የኑሮ አጉራ ቢጠናው ጊዜ ወደ ጠንቋይ ቤተ ይሄዳል፡፡ ለአጋፋሪው ሣንቲም ቢቴ ቦጨቅ ያደርግና ወረፋውን አፋጥኖ በተሎ ይደርሰዋል፡፡ በሁሉም ቦታ መቼም ይቺ ሙስና ተንሰራፍታለችና በዚህ አይግረማችሁ፡፡ ሀገራችን በተለይ በዚህ አንደኛ ሳትሆን የምትቀር አይመስለኝም፡፡
ጠንቋይ፤ ምን ፈልገህ መጣህ? አውሊያው ምን እንዲያደርግልህ ትፈልጋለህ አንተ ብላቴና?
አስጠንቋይ፤ የኑሮ ችር ነው ወደዚህ ያመጣኝ፡፡ ሕይወቴ ልፋት ብቻ ሆነ፤ ቀን ከሌት ብለፋ ድካም እንጂ ውጤት የለም፡፡ ጓደኞቼ የትና የት ሲደርሱ እኔ በድህነት እየማቀቅሁ ቀረሁ፡፡…
ጠንቋይ፤ አይዞህ፤ ገና ወጣት እኮ ነህ፡፡ ተስፋ አትቁረጥ…
አስጠንቋይ፤ እሺ! በርስዎው መጀን አባቴ፡፡ ያለርስዎ ማን አለኝ፡፡ እስካሁንም ወደርስዎ ያልመጣሁት በሞኝነቴ ነው፡፡
ጠንቋይ፤ ዋሪዳዬ እንደሚነግረኝ ያንተ ችግር እስከ 30 ዓመት ዕድሜህ ብቻ ነው፤ አይዞህ፡፡
አስጠንቋይ፤ መጀን በእናንተ! ከዚያስ በኋላ አባቴ?
ጠንቋይ፤ ከዚያ በኋላማ ችግሩን ትለምደዋለህ!
የዛሬ 22 ዓመታት ገደማ መለስ ዜናዊና የጭራቅ መንጋው የወያኔ ጉጅሌ አዲስ አበባን እንደተቆጣጠረና የቁምና የሞት ሟቹ መለስ የችግሩ መንግሥት ፕሬዚደንት እንደሆነ አካባቢ በምናቤ ቃለ ምልልስ አድርጌለት ነበር፡፡ ቀንጭቤ ላስታውሳችሁ፡፡
እኔ፤ ክቡር የሽብርተኛው የአፍሪካ ማፊያ ቡድን የሽግግር ፕሬዚደንት መለስ ዜናዊ – የኢትዮጵያ ሕዝብ በእርስዎ ዘረኛ አገዛዝ እንደተሰቃዬ ለስንት ዓመታት የሚቆይ ይመስልዎታል? ችግራችን እስከመቼ ነው? ባጭሩ እስኪ ይግለጹልኝ፡፡
መለስ ዜናዊ፤ እንደምታውቀው የቲምቡክቱና የሆኖሉሉ ሕዝቦች ለዘመናት በደረሰባቸው የብሔር ጭቆና…
እኔ፤ የለም፣ እኔ እምልዎት የኛ የኢትዮጵያውያን ወያኔ ወለድ ሰቆቃ እስከመቼ ይቆያል ነው… ወደዚያ ቢገቡና ቢመልሱልኝ፡፡
መለስ ዜናዊ፤ አልባኒያ በነበርኩበት ጊዜ የዚያች ሀገር ሕዝቦች መሪ ኤንቨር ሆዣ እንደነገረኝ …
እኔ፤ እንዴ? ምን ነካዎት አቶ መለስ – ወደጉዳዩ በቀጥታ ለምን አይገቡልኝም?
መለስ ዜናዊ፤ ጥሩ! የኢትዮጵያ ሕዝቦች ችግር እኛ ሥልጣን ከያዝንበት ዓመት ጀምሮ የሚሰላ እስከ 18 ዓመት ብቻ ነው፡፡
እኔ፤ (በጉጉት) ከዚያስ በኋላ ክቡር ፕሬዚደንት!
መለስ ዜናዊ፤ ከዚያ በኋላማ ትለምዱታላችሁ፡፡
ሁሉንም ለመድነው፡፡ እንዲያውም ከወያኔ ሌላ፣ ሌላ አማራጭ የሌለ እስኪመስለን ድረስ ይህን ዘረኛና ከፋፋይ ሥርዓት ለመድነው፡፡ ሕዝቡ በጥቅም፣ በዘረኝነት፣ በወንዘኝነት፣ በሃይማኖትና በመሳሰሉት ወያኔዊ የመከፋፈያ ሥልቶች ተንበርክኮ ራሱን በራሱ በመብላት ላይ ይገኛል፡፡ ወደኅሊናው ተመልሶ ቆም ብሎ ለሚያስበው ሰው የኢትዮጵያ ሁኔታ በእጅጉ ያስደነግጣል፤ ሀገሪቱና ሕዝቧ ተመልሰው ሀገርና ሕዝብ ይሆናሉ ተብሎ መጠበቅ እስከማይቻልበት ድረስ ወርደዋል፡፡ አንድ ሕዝብ ከሃይማኖትና ከባህል ወጥቶ ማተቡን በገንዘብ ከለወጠና እስትንፋሱ ሁሉ በቁሣዊ ነገር ከተቃኘ፣ አንዲት ሀገር በምስጦችና በመዥገሮች ከተገዛችና ሙስና በዐዋጅ የፀደቀ እስኪመስል ሁሉም ነገር ያለሙስና የማይንቀሳቀስ ከሆነ ልዩ ኹነት ተከስቶ ሀገርና ሕዝብ ከነዚህ ወጥመዶች እስካልወጡ ድረስ ሀገርም ሕዝብም የሉም፡፡ የሕዝብ ብዛት መቶ ቀርቶ ሺህ ሚሊዮን ቢደርስ፣ የሀገር የድንበር ግዛት እንደውቅያኖስ የተንጣለለ ቢሆን የሀገርና የሕዝብ ኅልውና መሥፈርቶች እስካልተሟሉ ድረስ ሕዝብም ሀገርም አሉ ማለት አንችልም፡፡ ከሞላ ጎደል ሁሉም ከመሥፈርቱ ተንሸራትቶ ተንቀሳቃሽ ሰው መሳይ አሻንጉሊት እየሆነ ነው፡፡ ይህን ስል አዝናለሁ፡፡ ግን አለማለት ደግሞ አልችልም – ምርጫም የለኝም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ወቅት የሕዝብ አሃዛዊ ብዛት እንጂ ሌላው ቀርቶ ቅጥ ያለው ሰላምታ የሚለዋወጥ ደርዝ ያለው ሰው ማግኘት እንኳን የማይቻልበት ደረጃ እየተደረሰ ነው፡፡ ለገንዘብ የሚሮጥ ሳተና ትውልድ ግን ሞልቷል፡፡ ከላይ አስከታች ሁሉም የተጠመደው ገንዘብ ማግበስበስ ላይ ነው፡፡ በእግርህ ሄደህ የሚፈጸምልህ ጉዳይ ከስንት አንድ ነው፡፡ ዘርህ ከገዢው ወገን ካልሆነ ደግሞ የባሰ መከራ ውስጥ ነህ፤ ዘረኝነቱ ሥር ሰድዶ ሀገሪቱን እንደነቀርሣ በታትኮ ሊጨርሳት ነው፤ እንደኤድስ አመንምኖ ወረደ መቃብሯ እያጣደፈው ነው – አንደበትህ ወይ ግንባርህ ትግሬነትህን አሳብቆ ጉዳይህን ባፋጣኝ ያለመማለጃ ካላስጨረሰልህ በስተቀር የሌላው ዘውግ አባል ከሆንክ ፍዳህን ትቆጥራለህ፡፡ ይሉኝታም ሞቶ ተቀብሯል፡፡ የገዢው ወገን የሆነ ትግሬ ብቻ የሚፈነጭባት ሀገር ተፈጥራልሃለች፡፡ የነጻነትህ ዘመን በቶሎ እንዲመጣ ይልቁናስ ወዳምላክህ አልቅስ፡፡ የተቀረው ተከድኖ ይብሰል፡፡ ሀፍትና ይሉኝታ ያልፈጠረባቸው ወንድሞችህና እህቶችህ ሁሉንም ነገር ለግላቸው ጥቅም ተቆጣጥረው ሀገር ምድሩን እያስለቀሱት ናቸው፡፡ ጥቂት ጥቅም የሚጋሩት በአፋዳሽነትና በአቃጣሪነት ወደነሱ የተጠጉ ናቸው፡፡ የነሱም ኑሮ የሰቀቀን ኑሮ ነው፡፡ ሆድን ቢሞሉት የአእምሮ ነጻነት ከሌለ እንደከብት መሆን ነውና አቃጣሪዎችና አንፋሽ አጎንባሾች ኑሯቸው የተሟላ ነው ማለት አይቻልም፡፡
የሚብለጨለጨው ሁሉ ለጥቂቶች ሲሳይ እንጂ ለአብዛኛው ዜጋ የሚተርፈው ችግርና ሰቆቃ ነው፡፡ ችግርና ሰቆቃ ሲበዛ ደግሞ ከሰውነት ደረጃ እያወጣ ‹ዛሬ ከምሞት ነገ ልሙት› ከሚል የአልሞትባይ ተጋዳይነት ይትበሃል በመነሳት አብዛኛው ሰው አቅልን በሳተ ሕገወጥ የገንዘብ ማግኛ ዘዴ በመሰማራት ወንጀልንና ኃጢያትን ከመጤፍ አለመቁጠሩን ተያይዞታል፡፡ ከዚህ በላይ ሀገራዊ ኪሣራ የለም፡፡ በሞራል፣ በምግባር፣ በሃይማኖት፣ በባህል፣ በፖለቲካ፣ … በሁሉም ከስረንና ልንወጣው የማንችለው ግሽበት ውስጥ ተነክረን ሀገሪቱ የዐይጦችና የፍልፈሎች መፈንጪያ ሆናለች፡፡ ፍትህ የለም፤ ዳኛ የለም፤ ሕግ በወረቀት እንጂ በተግባር ፈጽሞውን የለም፡፡ አትቀደም እንጂ ማንም ቢገድልህ እሰይ የሚል ካልሆነ ደምህን ከራሔላዊ ጩኸት የሚታደግልህ አንድም ሰው የለም፡፡ በስቃይህ የሚደሰት ዜጋ እየበዛ ነው፡፡ እንዴት እንደምጽፋት የሚቸግረኝ ያቺ በከንፈር የምትገለጥ የመጀመሪያ ርዳታ መግለጫ ቃል እንኳ እየጠፋች ነው፡፡ ጭካኔ እየተራባ ነው፡፡ በተለይማ ነጋዴውና ባለሥልጣኑ እየተሻረኩ እነሱ ባንድ አዳር ሽቅብ ሲተኮሱ አብዛኛው ዜጋ ለዕለት ጉርስም መሆን አቅቶታል፡፡ ሀብታሞችና ፖለቲከኞች በገደሏት ሀገር ውስጥ የበይ ተመልካች ሆኖ ከመኖር የዓሣ ነባሪ ሲሳይ ሆኜ ብቀር ይሻለኛል ከሚል ብሶት ሀገሩን እየለቀቀ ባገኘው አቅጣጫ ለስደት የሚነጉደው ሕዝብ የትዬለሌ ነው፡፡ ልማቱና ዕድገቱ በዋሾው የወያኔ ስታትስቲክስ ቢሮ ካልሆነ በተግባር የሚታይ ሁሉን አሳታፊ ዕድገትም ሆነ ልማት የለም፡፡ እየተራቡ ልማት፣ በእሥር እየማቀቁና በሥውር እየተገደሉ ነጻነት፣ በአንድ ዘር የበላይነት የቁም ስቅልን እያዩ ዴሞክራሲ፣ በአንድ ሀገር ውስጥ ልጅና እንጀራ ልጅ ሆነው እየኖሩ የዜጎች እኩልነት፣ የአንድን ብር ዕቃ መቶ ብር እየገዙ የዋጋ መረጋጋት … የወያኔ መሪር ቀልድ እንጂ ሕዝባዊ እውነት አይደለም ……
ሰሞነኞቹ እነተስፋዬ ለማ፣ ታምራት ሞላ፣ ዮናስ አድማሱ … ታድለዋል፡፡ ተገላገሉ፡፡ እኛ ዕዳችን ገና ሆኖ ገና አለን፡፡ ለበጎ ነው ብለን እንኖራለን፡፡ አዎ፣ ሁሉም መጥፎ አጋጣሚ ለበጎ ነው፡፡
ደርግ አንደኛውን ዓመታዊ የልደት በዓሉን ሲያከብር የወቅቱን የኬንያን ፕሬዚደንት ጋብዞ ነበር አሉ፡፡ ያኔ በያኔው አብዮት አደባባይ ላይ ደርግ ያርመሰመሰውን የጦር መሣሪያ የተመለከቱ የኬንያ ፕሬዚደንት ወደፓርላማቸው ተመልሰው ‹ ጎበዝ! እኛ በሩቅ ያለችዋን የሶቭዬት ኅብረትን እንፈራለን፡፡ መፍራትስ እዚሁ አጠገባችን ያለችውን ኢትዮጵያን ነው፡፡ ጉድ ዐይቼላችሁ መጣሁ…› አሏቸው አሉ፡፡ ደርግ ያን ያደረገው ዓላማው ግልጽ ነበር፡፡ የውስጥ ተቃዋሚን ሳይሆን የምዕራቡን ዓለም ጣልቃ ገብነት ተረድቶ በዚያ አቅጣጫ የሚንቀሳቀሱ ‹የአድኅሮት ኃይላት›ን አደብ ለማስገዛት ነበር፡፡
ወያኔ ሰሞኑን ከመሬት ተነስቶ የጦር ትርዒት እያሳዬ ነበር አሉ – ከሚያመልኩባት ወር ከየካቲት 1 እስከ 7/2005 – እኔ ከጤንነት አኳያ ኢቲቪን እንዳልከታተል ሀኪም ስላዘዘኝ አላይም፡፡ ማስፈራራት ጥሩ የሚሆንባቸው አጋጣሚዎች አሉ፡፡ ማንን ማስፈራራት? እንዴት ማስፈራራት? መቼ ማስፈራራት… የሚሉት ጥያቄዎች ግን በአግባቡ መመለስ ይኖርባቸዋል፡፡ በ‹ሀገር አማን› ከመሬት ተነስቶ መሣሪያን ከግምጃ ቤት ማውጣትና ‹እዩልኝ› ማለት ግን የጤና አይመስልም፡፡ አንዱ ለአንዱ ‹ ና አልመታህም› አለው አሉ፡፡ “አሃ! ይሄኔ ነው መሸሽ! ‹ና አልታህም›ን ምን አመጣው?” ብሎ አምርሮ ሸሸ አሉ፡፡ አሁን ወያን ሃሳብ ውስጥ የሚከት ነገር ከየት መጣ? ለምን አሁን? …
ለነገሩ መጽሐፉ ይላል – ‹ንጉሥ በሠራዊቱ ብዛት አይድንም› -ኢይድህን ንጉሥ በብዝኃ ሠራዊቱ፡፡ በመሣሪያና በጦረኞች ብዛት ቢሆን ኖሮ እነደርግም እነሣዳም ሁሴንም እነ‹አሣር› አላሳድም እነሁሉም የጥንትና የአሁን አምባገነኖች በብርሃን ፍጥነት እንደባቢሎን ባልተንኮታኮቱ ነበር፡፡ አምባገነኖች ያሳዝኑናል – ሞኞች ናቸው፤ ከሞኝነት ባለፈም ጅሎች ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ በፋሲካ የገባች ገረድ ሁልጊዜ ፋሲካ ይመስላታል እንደሚባለው ሁሉ እነዚህ ቡልሃዎች ጊዜ የሚከዳቸው፣ ኃይላቸው ማዳኑን አቁሞ የሚዝልባቸውና የሚዝለፈለፍባቸው አይመስላቸውም፡፡ መውደቃቸውንና መሞታቸውን ሳይቀር የማያምኑ ቂላቂል አምባገነኖች ያጋጥማሉ – ልክ እንደጋዳፊ ዓይነቶቹ፡፡ እየወደቁ ሳሉ ደግሞ የውሃ ዋና የከዳው ሟች ዋናተኛ ባህሩ ላይ እየተንሣፈፈ ያለን ፊላና ገለባ – እንዲያድነው – እንደሚጨብጥ ሁሉ እነዚህ አምባገነኖችም ከውድቀታቸው ለመዳን የማይሞክሩት የቀቢፀ ተስፋ ድርጊት የለም፡፡
ምዕመናን፤ ዘጠኝ ሱሪ ፈስ አይቋጥርም፡፡ ቆርጦ ከላይም ይሁን ከታች የሚመጣን ነገር ደግሞ ማስቀረት አይቻልም፡፡ ወደድንም ጠላንም ኢትዮጵያ ነጻ የምትወጣበት ጊዜ እየደረሰ ነው፡፡ ወያኔዎች ኒኩሌር ቢዋሱ እንኳን ያቺን የነጻነት ጊዜ ሊያስቀሯት ይቅርና ሊያዘገዩዋት አይቻላቸውም፡፡ የሁሉም ነገር መሆኛ ጊዜ አለው – አለመሆኛ ጊዜ እንዳለው ሁሉ፤ ፅንስ አለጊዜው ተወለድ ቢሉት አይሆንም፤ ዶሮ እንኳን ከ21 ቀናት ውጪ 20 ወይንም 22 ቀናትን አትታቀፍም ፡፡ ግን ሞት ሲዘገይ የቀረ የሚመስላቸው ዝንጉዎች እንዳሉ ሁሉ የአንድ ነገር የመሆኛ ጊዜም ሲዘገይ የቀረ የሚመስላቸው ሣሞራን መሰል ንፍጥራሶች ባልተገራ አንደበት ከመሳደብ አልፈው አንድን ሕዝብ ከሌላው አነጣጥረው በመለየት ለማጥፋት ይፍጨረጨራሉ፡፡
ወያኔዎች በኢትዮጵያና ሕዝቧ ላይ እንዲህ እንዲቀዝኑ የተፈቀደላቸው በኛው ኃጢያት እንጂ በነሱ የፅድቅ ሥራ እንዳልሆነ እናምናለን፡፡ ‹እግዜር ሲቆጣ ሽመል አይቆርጥም ያደርጋል እንጂ ነገር እንዳይጥም› የምንለው ወደን አይደለም፡፡ አሁን በቁማችን የጠፋነው የምናወራርደው የመጥፎ ሥራ ውዝፍ ዕዳ ስላለብን እንጂ ዘመኑ ሲደርስ ወያኔዎች መግቢያ ቀዳዳ ሲያጡና እንደኢዮብ የተፈጠሩባትን ዕለት አምርረው ሲራገሙ የምናይበት ለእኛ ወርቃማ ለእነሱ የጨለማ ጊዜ አለ፡፡ ያም ጊዜ እየደረሰ ነው፡፡ የጠፋው ሕዝብ እንደገና ይፈጠራል፡፡ የባከነው ሕዝብ ልብ ገዝቶ ወደታሪካዊ ሥፍራው ይመለሳል፡፡ ሆዳሞችና ስግብግቦች ግን በጎርፍ ይጠራረጋሉ፡፡ አሁን ምንም እንኳ በተስፋ መቁረጥ ማዕበል ብንናወጥም ተስፋችን እግዚአብሔር ነውና የጨለመው ይበራል፤ የተዘጋው ይከፈታል፡፡ ለዚህ ዓይነቱ አረንቋ የዳረጉን የሃይማኖት ተቋማትና የፖለቲካ አደረጃጀቶችም የየመክሊታቸውን ያገኛሉ፡፡ ከየጥምጣሙና ከየጥንግ ድርቡ ሥር የመሸገው የአጋንንት ሠራዊት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ሲመታ፣ በዬፓርቲውና በዬጎሣ ድርጅቱ የተሰገሰገው የዲያብሎስ መንጋ በመግረሬ ፀር ሲቀጠቀጥ፣ መሀል አዲስ አበባ ላይ ሳይቀር በሣጥናኤል ትዕምርት የአምስት ጫፍ ከዋክብት የተንቆጠቆጡ ሆቴሎችና በሰው ደም ግብር የጠገቡ የንግድና የእምነት ተቋማት ሲፈራርሱ፣ በድግምትና በትብታብ ሰማይ ጠቀስ ፎቅ የገነቡና ባንኮችን ያስጨነቀ ሀብትና ገንዘብ ያከማቹ ውሉዳነ አጋንንት በመስቀሉ ኃይል ሲፍረከረኩ ያኔ ሀገር ‹ሀ› ብላ መፈጠር ትጀምራለች፤ ያኔ ሕዝብ ‹ሀ› ብሎ መፈጠር ይጀምራል – የአሁኑ ግን አይወራ፡፡ ቀባሪ ጠፋ እንጂ በቁማችን ሞተናል፡፡ እንደሞትን እንቀራለን ማለት ግን አይደለም – በፍጹም …
እኔ አንዳንዴ – ስናደድ – እንዲህ እላለሁ፡- ወልደማርያም – የእምዬ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘግይቷል፡፡ ብዙዎችም በዚህ የሚስማሙ ይመስለኛል፡፡ ኃጢያተኛና ወንጀለኛ ለረጂም ጊዜ ሀገር ምድሩን ሲናኝ፣ ወንጀልና ኃጢያት የዘመን መታወቂያ ልዩ ባህል ሲሆን፣ በፈጣሪ ስም ሳይቀር ሲሸቀጥና ሲነገድ፣ እግዚአብሔራውያን በሃይማታቸው ሲያፍሩና መዘባበቻም ሲሆኑ፣ ሰይጣናውያን የላይኛውን የአስተዳደርና የአገዛዝ እርካብ ተቆጣጥረው ክፋት ከጽንፍ እስከ አጽናፍ ሲነግሥ፣ የሞራልና የግብረ ገብ መልካም ዕሴቶች እንደልብ እየተጣሱ ዋልጌነትና መሠሪነት ሀራም(ዕርም) መሆኑ ሲቀር… እንዴት ፈጣሪ ጦሩን አይመዝም? ክርስቶስ እንዴት አስቻለው? ወንድና ወንድ ሲጋባ፣ ሴትና ሴት ግዑዛን ነገሮችን እየቀጣጠሉ የወንዶችን መፈጠር ይሁነኝ ብለው ቸል ሲሉና አልባሌ ሆነው ሕገ ተፈጥሮን ሲጥሱ ፈጣሪና ተፈጥሮ በሶ ጨብጠዋል ወይ? ብለን አንዳንድ ተገራሚያን በአግራሞት ራሳችንን እንጠይቃለን፡፡ ሰው ይህን ያህል አቅሉን ስቶ ለሥልጣንና ለገንዘብ ሲራወጥ ስናይ – በፖለቲካም ይሁን በንግድ ሰበብ ወንድሞቹን ባልተወለ አንጀት በጩቤ ሲያርድ – ግድያና ዝርፊያ፣ ማጭበርበርና ማምታታት የዘመኑ ፋሽን ሲሆኑ ፈጣሪ ወዴት አለ? እንዴትስ ያስችለዋል? ብንል በስህተትነት ሊመዘገብብን የሚችል አይመስለኝም፡፡ አንዳንዴ ደግሞ – ንዴቴ በረድ ሲል- እንዲህ እላለሁ፡- ይህ ሁሉ ነገር እንዲሆን የግድ ነው፡፡ ምክንያቱም በመጻሕፍቱ እነዚህና ሌሎችም ከነዚህ የባሱ የኃጢያትና የወንጀል ዓይነቶች ቀድመው ተጠቅሰዋል፡፡ ችግሩ የፈጣሪና የሰው የጊዜ አለካክና የትዕግስት መጠን መለያየቱ ነው፡፡ ለሁሉም ጊዜ አለውና ይህም ከመስመር የወጣ ሕይወት ይፈጸም ዘንድ የጌታ ፈቃድ መሆን አለበትና ሳይዘናጉ በርትቶ መጸለይ ይገባል እላለሁ፡፡ ለማንኛውም ሁላችንም እንደዬአመለካከታችን ያሻንን እናስብ፣ እንበልም፡፡ ክፋት የለውም፡፡ ግን ግን ጊዜው መቃረቡን ከግምት በላይ በሆነ የትክክለኝነት ደረጃ መናገር እንችላለን፡፡ ‹ጦም ጧሚና ሰው ጠባቂ አንድ ናቸው› እንዲሉ እንዳይሆን ታዲያ የወል ዓለማዊ ወይም የተናጠል ሀገራዊ ነጻነታችንን እስክናገኝ በትጋት በያለንበት እንቁም፡፡ የነጻነታችን መምጣት ጉዳይ የወያኔ ፈቃድ ወይም የኛ ውዴታ አይደለም፤ ተፈጥሯዊ እንጂ ነው፡፡ እርግጥ ነው – ‹እህል የሚደርስ በፍልሰታ እኔ እምሞት ዛሬ ማታ› ልንል እንችላለን – ትክክል ነው፡፡ ቢሆንም አንቸኩል፡፡ ብንቸኩልም ራሳችንን ከማሰቃየት በስተቀር ዋጋ የለውም፡፡ መለስ የአሁኑን አያድርገውና ያ ግማታም ዓላማው እስኪሳካለት ድረስ ከ17 ዓመታት በላይ በጫካ ኖሯል፡፡ በነገራችን ላይ የመለስ መቃብር ሥላሤ ካቴድራል ውስጥ ክላሽን ባነገቡ ወታደሮች እየተጠበቀ እንዳለ ታውቃላችሁ? ማን እንዳይወስደው ይሆን? ዩፎዎች አጥንቱን ወስደው ክፋት አቀፍ ዲ ኤን ኤውን እንዳይመረምሩት ጥንቃቄ እያደረጉ ይሆን? ማፈሪያዎች! ለአፅም ጥበቃ የሀገር ሀብት ይባክን? ሌላኛው መታወቂያችን ኢትዮጵያና ወያ በሙት መንፈስ የሚመሩ መሆናቸው ነው፡፡ ‹የመለስን ራዕይ እውን ለማድረግ› ብሎ ንግግሩን የማይጀምር ባለሥልጣን በግምገማ የሚወገድ እስኪመስል ድረስ በዚህ መጻጉዕ ሰውዬ የሙት መንፈስ እየተጃጃሉ ናቸው፡፡ አሁንስ በጣም አስጠሉ!
በፊዚክስ ትምህርት Inertia የሚባል ነገር እንደተማርክ መቼም አትዘነጋውም፡፡ ይህን ቃል በጊዜያዊነት የውርስ ትርጉም በአማርኛ ‹ደመ ነፍስ› እንበለውና ለተወሰነ ጊዜ ተጨማሪ ወግ እንጠርቅ፡፡ ዛሬ ወግ አምሮኛል፡፡
ኢነርሺያ – Inertia – በፊዚክስ resistance to change: the property of a body by which it remains at rest or continues moving in a straight line unless acted upon by a directional force. በሚል ፍቺ እንደሚታወቅ ማይክሮሶፍት ኢንካርታ የተባለው መዝገበ ቃላት ይገልጣል፡፡ ወዳማርኛ ሲመለስ – በግርድፉ – ‘ለለውጥ አለመገዛት፤ የአንድ ነገር ባለበት የመቆየት ወይም (ውጫዊም ሆነ ውስጣዊ የኃይል ግፊት ሳይኖር) በራሱ ኃይል ብቻ ከአንድ አቅጣጫ የሚመጣ ሌላ ኃይል እስኪያደናቅፈው ድረስ በራሱ ቀጥተኛ መስመር የመንቀሳቀስ ባሕርይ …’ እንደማለት ነው፡፡ ልክ እንደ ኢትዮጵያ!!
ለምሳሌ ቤንዚን የጨረሰች መኪና የእጅ ፍሬን ሳይያዝላትና ታኮ ሳይደረግላት አውላላ ሜዳ ላይ ተተወች እንበል፡፡ ይህች መኪና የቆመችበት ቦታ ውኃ ልኩን የጠበቀ ከሆነ ምልባት ስንመለስ በዚያው ሥፍራ ልናገኛት እንችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን ኢምንት የቦታ ግድለት ካለ በራሷ ጊዜ ያን ሁሉ ሁዳድ አካልላ አንድ ጥጋት ስትደርስ ወይም አንዳች ድንጋይም ሆነ ፈፋ ሲያጋጥማት አይሆኑ ሆና ልናኛት እንችላለን፡፡ በዚህ መልክ ባሉበት ቆመው የሚቀሩ ወይም ተንከባለውና ተንሸራትተው ነባር ሥፍራቸውን በመልቀቅ የሚጎዱ ምናልባትም የማይጎዱ ነገሮች እንዳሉ እንረዳለን – በኔ አረዳድ ኢነርሺያ እንዲህ ይመስለኛል፡፡ አረዳድ የወዩ ቋንቋ ነች፡፡
ከፍ ሲል በጨረፍታ እንደጠቀስኩት የኢትዮጵያም ሁኔታ እንደዚሁ ነው፡፡ መርከቧ ከየቋጥኙ ጋ እየተላተመች ጉዞዋን ቀጥላለች፡፡ የት እንደምታቆም፣ ማን እንደሚነዳት፣ የተሣፋሪዎቹ ማንነት፣ የቀራት የነዳጅ መጠን፣ የምትጓዝበት አቅጣጫ… አይታወቅም፡፡ ጉዞዋን ግን በደመነፍስ እያስነካችው ናት፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ስትኖር በብዙ መልስ የሌላቸው ጥያቄዎች መከበብህን አትርሳ፡፡ እኔ ማን ነኝ? ትልቁ አስጨናቂ ጥያቄ፡፡ የት ነው ያለሁት? ምንድን ነኝ – ሰው ወይንስ እንስሳ? የሰውን እውነተኛ ምንነት የምትረዳ ከሆንክ ሰው ነኝ ብለህ እንደማትገምት ይታወቃልና እንስሳ ነኝ ብለህ ተረዳ፡፡ ምን ዓይነት እንስሳ ነኝ? ምን ዓይነት በረት ወይም ጋጣ ውስጥ ከየትኞቹ እንስሳት ጋር የታሰርኩ እንስሳ እሆን? እሥሩ እስከመቼ ነው? አመክሮስ አለው ወይ? አሣሪዎቼስ እነማን ናቸው? እንደሀገርም ሆነ እንደታሣሪ እንስሳት ለመሆኑ ወዴት እያመራን ነው? … እነዚህን መሰል ጥያቄዎች አንጎልህን ሰንገው የሚይዙ መልስ የለሽ ጥያቄዎች ናቸው – በኢትዮጵያ ውስጥ ስትኖር፡፡
ሀገሪቱ ፍጹም በለየለት ሁኔታ በደመ ነፍስ እየተነዳች ያለች ሀገር ናት፡፡ የሚመራት ወይም የሚገዛት ማን እንደሆነ አታውቅም፡፡ በልማድ ወያኔ እንላለን እንጂ ይህችን ሀገር ወደመቀመቅ እያዳፋት ያለው ከወያኔ ፊታውራነት በተጓዳኝ ቻይና ትሁን፣ ሲአይኤ ይሁን፣ ሞሳድ ይሁን … አይታወቅም፡፡ ብቻ ይመሻል ይነጋል – ይህንንም በፀሐይና በጨለማ መፈራረቅ ምክንያት አንተ ራስህም የምትመሰክረው እውነታ ነው፡፡ ይህ ተፈጥሯዊ ሂደት ብቻ አልተፋለሰም – ይመሻል ይነጋል፡፡ ይርብሃል – ይጠማሃል፡፡ በሀገርህ ላይ ሆነህ ሀገርህ ትናፍቅሃለች፡፡ በሕዝብህ መሃል ሆነህ ሕዝብ ይናፍቅሃል – በወገንና በአለኝታ እጦት ትሰቃያለህ፡፡ በብሔራዊ ስሜት መጥፋት፣ በሆዳምነትና በስግብግብነት መስፋፋት ቅስምህ ተሰብሮ ‹የሰው ያለህ፤ የወገን ያለህ› እያልክ በባዶ ሜዳ ታንቋርራለህ፡፡ ሀገርህ የጆፌዎችና የእስስቶች፣ የዓሣማዎችና የጅቦች መፈንጫ ሆና ስታይ፣ በማንነት ኪሣራና በሕይወት ማግና ድር ውል መጥፋት ውስጥ የተዘፈቀው ብዙ ወገንህ እንደክርስቶስ ኤሎሄውን ሽቅብ ሲያሳርግ ስታይ የምፅዓት ቀን መቃረቡን ልትገምት ትችላለህ፡፡ ኢትዮጵያህ እንደዚህ ያለ አሣዛኝ ሁኔታ ውስጥ ትገኛለች፡፡ ማን ይድረስላት?
ዜጎች እንዴት እንደሚኖሩ ስታይ ታለቅሳለህ፡፡ ኑሮው እንዴት እየተወነጨፈ እንዳለና ያን የሲዖል እሳት ግርፋት ለመወጣት ሲሉ ዜጎች ከሁሉም የሞራልና የሃይማኖት ሰበዞች ወጥተው እንዴት ያለ ኅሊናንና አጠቃላይ ስብዕናን አፍራሽ ተግባራት ውስጥ እንደሚሠማሩ ስታይ መፈጠርህን እስክትጠላ ድረስ ይዘገንንሃል፡፡ የቅዱስ ገብርኤልን ቤተ ክርስቲያን ተሣል የመጣ ምዕመን ነጋዴ ልብሱን ቀይሮ ወደንግድ ሥራው ከመሠማራቱ በደቂቃዎች ውስጥ በመቶ ብር ያመጣውን ዕቃ አምስት መቶ ብር ሊሸጥ ‹ቅዱስ ገብርኤልን በ490 ብር እኔም ከቦታው ያመጣሁት፤ እንዲህ የምለፋው ለ10 ብር ትርፍ ነው!› ሲል ብትሰማው ሃይማኖትም መቅሰፍትም ከሀገራችን ኮብልለው እንደወጡ ትረዳለህ፡፡ ለነገሩ ታቦታቱም ሆኑ ፈጣሪ ስንቱን ውሸታምና አጭበርባሪ ቀንጥሶ ይዘልቀዋል? ዘረኝነት፣ውሸት፣ክህደት፣ሴሰኝነትና አመንዝራነት፣ ጠጭነት፣ ዕብደት፣ ሥራ አጥነት፣ ሥራ ፈትነት፣ ባኖሩት አለመገኘት፣ ማይምነት፣ ጫት ቃሚነት፣ስግብግብነት፣… በሀገራችን ሠፍነው መቆሚያ መቀመጫ እያሳጡን ናቸው፡፡ እንዴት ይነቀቀላሉ? እግዚአብሔር ብቻ ሊመልሰው የሚችለው ትልቅ ጥያቄ ነው፡፡ ስለዚህ እርሱን ለማግኘት መጣር ብቸኛው አዋጭ መንገድ ይመስለኛልና በጠፋ ትውልድ መካከል እንደሎጥ አንድም ፃዲቅ ሰው ካለን ከፈጣሪ ሊያስታርቀን ይሞክርልን፡፡ ባለቀና በአዲስ ሁለት የሚራራቁ ተስፋዎች መካከል ያለ ሰው ብዙ ይናገራልና የዛሬን ቻሉኝ፡፡…
ሀገርህ ውስጥ የምትኖር ከሆንክ፡-
ምነው አምና በሞትኩ እንዲያ እንዳማረብኝ፤
ሰው እንደበርበሬ ሳይለወጥብኝ፡፡
የተባለውን የቀደመ ብሂል እያስታወስክ በሚሆነው ሁሉ ትቆዝማህ፡፡
ዛሬ ሕይወት በኢትዮጵያ እንደዚህ ነች፡፡ መቅኖ ያጣች፣ ባለቤት የሌላት፣ መሪና ተመሪ ተመካክረውና ተስማምተው በሚመስል ሁኔታ የሕይወት ፈተናን ላለማለፍ ቆርጠው የተነሱባት፣ አስተዋይነት ጠፍቶ ለነገና ለነገወዲያ ሳይሆን ለዛሬ ብቻ መጨነቅ የበዛባት፣ የሌባውንና የአጭበርባሪውን ብዛት ከጤነኛው ለመለየት አዳጋች የሆነባት፣ በገንዘብ ብዛት ሰላምና ጤንነት የሚገኝ የሚመስላቸው ተላላ ዜጎች የበረከቱባት፣ ዘረኝነትና ጎጠኝነት ሥር ሰድደው ማኅበራዊ ነቀርሣ የሆኑባት፣… ይህች ኢትዮጵያ ናት አሁን በደመ ነፍስ ወዳልታወቀ አቅጣጫ በውል ተለይቶ ባልታወቀ ኃይል እየተነዳች ያለቸው፡፡
ፈጣሪ መሓሪ ነው፡፡ መዳንም አለመዳንም በርሱ ነው፡፡ ዛሬን እንዲህ ብንሆንም ትናንት እንዲህ እንዳልሆን ሁሉ ነገ ሌላ እንሆናለን፡፡ የወደቀ ይነሳል፡፡ ገናናዎች ይወድቃሉ – ትሑታን ከፍ ከፍ ይላሉ፡፡ ብርሃን ጨለማን ያረግዛል፤ ጨለማም ጊዜው ያልደረሰን ብርሃን ይደብቃል፡፡ በጨለማችን ውስጥ የተረገዘው ብርሃን በቅርብ ይወለዳል፡፡ በብርሃናቸው ውስጥ የተረገዘው ጨለማ ግዘፍ ነስቶ በቅርብ ወደጥልቁ የእሳት ባሕር ያሰምጣቸዋል፡፡ የነበረን መናገር የምሥክርነት እንጂ የነቢይነት ሚናን አያጣቅስም፡፡
ሃሳባችንን እንጠቅልለው፡-
ግፍዖሙ እግዚኦ ለእለ ይገፍኡኒ፣
ጽብኦሙ እግዚኦ ለእለ ይጸብኡኒ፣
ንሣእ ወልታ ወኩዊናተ ወተንስእ ውስተ ረዲኦትየ፣
ምላኅ ሰይፈከ ወዕግቶሙ ለእለ ሮዱኒ፣
በላ ለነፍስየ አነ ውእቱ እረዳኢኪ፣
ለይትኃፈሩ ወይኅሠሩ ኩሎሙ እለ የኀሥሥዋ ለነፍስየ፣
ለይግብኡ ድኅሬሆሙ ወይትሃፈሩ እለመከሩ እኩየ ላእሌየ፣
ለይኩኑ ከመጸበል ዘቅድመ ገጸ ነፋስ፣
ወመልአከ እግዚአብሔር ለይሣቅዮሙ፣ … (በራስህ እማትጨርሰው …)
መዝሙር 34
Leave a Reply