በደቡብ ክልል በማር፣ በበርበሬ፣ በጤፍና በቅቤ ምርት ላይ ለጤና ጠንቅ የሆኑ ባዕድ ነገሮች ተቀላቅሎ ሲዘጋጅ መያዙን የደቡብ ክልል ንግድ ቢሮ አስታወቀ።
በክልሉ ከፋ ዞን፣ ቦንጋ ፣ጌዴኦ ዞን ፣ዲላና ሀላባ ዞን ቁሊቶ ከተሞች ላይ ባደረገው የዳሰሳ ጥናት በማር ፤በበርበሬ በጤፍና በቅቤ ምርቶች ላይ ለጤና ጠንቅ የሆኑ ባዕድ ነገሮች ተቀላቅሎ ሲዘጋጅ መያዙን የደቡብ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሽመልስ ዋንጎሬ ተናግረዋል።
የጥራት ደረጃቸውን ያልጠበቁ የምግብ ምርቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱና እየተላመዱ መምጣታቸውን በተደረገው የዳሰሳ ጥናት መረዳት ችለናል ያሉት ኃላፊው ህብረተሰቡ ምግብና ምግብ ነክ የሆኑ ነገሮችን ሲሸምት አጢኖ ሊሆን እደሚገባም አሳስበዋል።
ፎሼ የተሰኘ የጥራት ደረጃውን ያልጠበቀ ለምግብነት የማይሆን በርበሬ ከእርድና ከስንደዶ ማቅለሚያ ኬሚካል ጋር በመደባለቅ ፤ማርን ከሞላሲስ ፣ቅቤን ከጄሶ፣ከአትክልት ተዋፅኦና የእንሰት ምርት ከሆነው ቡላ ጋር እንዲሁም ጤፍን ከካሳቫ ጋር ተከልሶ ለገበያ ሲቀርብ መያዙንም ኃላፊው አረጋግጠዋል።
የደቡብ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሂክማ ከይረዲን በበኩላቸው መጪው ጊዜ በዓል ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ግብይት የሚፈፀም በመሆኑ ሸማቹ ህብረተሰብ ለጤና ጎጂ የሆነ ባዕድ ነገር የተቀላቀለባቸውን የምግብ ምርቶች ሲሸምት በጥንቃቄ ሊሆን እንደሚገባም አሳስበዋል። (ኢብኮ)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply