
በሁሉም ክልሎች በችሎታቸው የተመረጡ ተማሪዎች የሚማሩባቸው 50 ትምህርት ቤቶች ሊገነቡ መሆናቸውን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በሁሉም ክልሎች በዓይነታቸው ልዩ የሆኑና የልህቀት ማዕከል የሚሆኑ 50 ትምህርት ቤቶች ይገነባሉ ብለዋል።
ትምህርት ቤቶቹ ቀጣይ የአገር መሪ የሚሆኑ ብቁና ተወዳዳሪ ተማሪዎች የሚፈልቁበት በችሎታቸው ብቻ የሚመረጡ ተማሪዎች የሚማሩባቸው መሆናቸውንም ተናግረዋል።
በትምህርት ቤቶቹ የ8ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት መሠረት ባደረገና የትምህርት ሚኒስቴር በሚያወጣውን መመዘኛ የሚያሟሉ ተማሪዎች የሚማሩባቸው እንደሆኑም ተገልጿል።
በሁሉም ክልሎች በሚገነቡት እነዚህ የልህቀት ማዕከላት ከሁሉም የአገሪቱ ክልሎች የሚመለመሉ ተማሪዎችን ተቀብለው የሚያስተምሩ ናቸው።
በተያያዘ ዜና የትምህርት ሚኒስቴር በጦርነቱ የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለመገንባት ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ መመደቡን አስታወቀ።
የትምህርት ሚኒስቴርና የክልል ትምህርት ቢሮዎች በህወሓት የሽብር ቡድን የወደሙ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል።
በውይይቱም የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የትምህርት ቢሮዎቹና ትምህርት ሚኒስቴር የወደሙና የፈረሱ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለመገንባት ከስምምነት ላይ መደረሱን ገልፀዋል።
በስምምነቱም የትምህርት ሚኒስቴር በጦርነቱ ከፍተኛ ጉዳት በደረሰባቸው ሁለቱ ክልሎች ሙሉ በሙሉ የወደሙ 1 ሺህ 93 ትምህርት ቤቶችን እንደሚገንባም መናገራቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል። (አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
እጅግ ግሩም የሆነ ሃሳብ ነዉ፡፡ የልቀት ማእከላቱ ዜጎች ዕዉቀትና ክህሎት የሚያገኙበት ቦታ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊ ማንነትም የሚገነቡበት ማዕከል ይሆን ዘንድ በየማዕከላቱ የሚገቡ ተማሪዎች ስብጥር ኢትዮጵያን በሚያሳይ መልኩ እንዲሆን መደረግ ይኖርበታል፡፡ ወያኔ / ኢሀአዴግ ወደ ስልጣን በመጣ ጊዜ በሀገሪቱ ዉስጥ ከነበሩ 17 የቴክኒክና ሞያ ት/ቤቶች ብዙዎቹ በአፈጻጸም ችግር የተነሳ አብዛኞቹ በመዘጋት ላይ በነበሩበት ዓመታት ወያኔ ባስተላለፈዉ ግብታዊ የፖለቲካ ዉሳኔ ተጨማሪ 25 ማዕከላት (ኦሮሚያ 7፡ አማረ 7፡ ደቡብ 7፡ ትግራይ 5) ማዕከላት በወቅቱ ጠቅላይ ሚንስተር ቀጭን ትዕዛዝና በትምህርት ሚንስትሯ ፊት አዉራርነት በከፍተኛ ወጪ ተሰርተዉ ምንም ሳይፈይዱ እንደቀሩ እንዳይሆን ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲደረግ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ለሚመሩት መሥሪያ ቤት መምከር ‘ልጅ ለናቷ ምጥ አስተማረች’ ስለሚሆን አፌን ሰብሰብ ማድረግ መርጫለሁ፡፡