የዘውግን ፖለቲካ በኢትዮጵያ የጀመረው ማነው?

ጥያቄ አለኝ፥ የዘውግን ፖለቲካ በኢትዮጵያ የጀመረው ማነው?

ዛሬ ያላቅሜ አንድ ጥያቄ ማንሳት ከጅያለሁ። ለነገሩ ዶክተር ያልተጠየቀ ማን ይጠይቃል? እናም ዶክተርን ልጠይቅ ነው። ዶክተር መሳይ በኢትዮጵያ የዘውግን ፖለቲካ የጀመረው ማነው?

ዶ/ር መሳይ ከበደ፥ የኢትዮጵያ ዘውጋዊ ክፍፍሎችና የመፍትሔ ሃሳብ፥ በሚል ርእስ በአንድ መድረክ አቅርቤው ነበር ያሉትን ፅሁፍ በዚህ ድረ-ገፅ ላይ አውጥተው አስነብበውናል። እንደውነቱ ከሆነ በመድረኩ ተገኝተን ፅሁፋቸውን ለመከታተል እድል ላላገኘን ሰዎች በረከቱን ስላሳተፉን አመሰግናለሁ። ግን ጥያቄ አለኝ። ለጥቂቶች ስውር የስልጣን ጥም ማርኪያ፣ ለዛሬይቱ ኢትዮጵያ ደግሞ የህልውና ፈተና የሆነውን የዘውግ ፖለቲካ በዚያች አገር የተከለው ማነው? ህወሃት ወይስ አማራ? ለችግሩ መፍትሄው ክልሎችን ማጥፋት ሳይሆን ራስ ገዝ ማድረግና ስልጣን መስጠት ነው ያሉ መስሎኛል። ይህ ጎሳን መሰረት ያደረገ መፍትሄ የሀገርን  አንድነት ከማስጠበቅ አላማ ጋር እንዴት ሊታረቅ ይችላል? ዘውግ ላይ የተመሰረተ ስርአትን  በማስቀጠል ጠባብ የማንነት ጥያቄ የሀገራዊ አንድነት ፀር እንዳይሆን ማድረጊያው ብልሃት ከየት ይመጣል?

በፅሁፉ ላይ በተነሱት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ እስማማለሁ። ነገር ግን በአንዳንዶቹ ላይ ያለኝ ሀሳብ የተለየ ነው። ምናልባት ላልተረዳኋቸው ነገሮች አጥጋቢ መልስ ካገኘው አስተያየቴን አስተካክል ይሆናል።

ዶክተር መሳይ የፕሬዝደንትነት ምርጫ ዘውድ ወለዱን ችግር እንዴት ሊፈታ እንደሚችል የሰጡት ትንተና በውል ስላልገባኝ በተረዳሁት መጠን ብቻ ትንሽ ሃሳብ ብሰጥ ከመልሱ  ለመማር ይረዳኛል።

የዘውግ ጉዳይ በስልጣን ላይ ላለው መንግስት የፖለቲካ ስልጣን ዋስትና ይሆነው ዘንድ አስልቶ እንደዘረጋው እስማማለሁ። ስሌቱም ጠቅሞታል። ቢያንስ ላለፉት 24 አመታት ተደላድሎ እንዲገዛና የቡድን አጀንዳዎቹን እንዲያስፈፅም ረድቶታል። በተለይ የኢትዮጵያ ህዝብ እንደባቢሎን ዘመን ግንብ ሰሪዎች በቋንቋ እንዳይግባባ በማድረግ የኢትዮጵያዊ አንድነት ጉዳይ ያለፉ ስርአቶች የጭቆና ሃሳብ (ideology) ሆኖ እንዲታይ ቀስቅሷል፤ ቀላል የማይባል ጉዳትም አድርሷል። በተለይ ቅንጥብጣቢ የታሪክ ኩነቶችን አጣምሞ በሌላው ብሄረሰብ ላይ ግፍ የተፈፀመ አድርጎ በማቅረብ የንፁሃን ደም እንዲፈስ ማደረጉ ታሪክ ይቅር የማይለው በደል ነበር። የተበድላችኋል ወሬውን ከህወሃት የሰሙት የስርአቱ አገልጋይ የብሄረሰብ መሪዎችም ህዝቡን ለበቀል በማነሳሳት ከገዛ ወንድሞቹ ጋር ያለአግባብ ደም እንዲቃባ አድርገውታል። በደል ተጋኖ ሲቀርብ ደግሞ ተበደልኩ ባዩ ዘንድ ከፍተኛ ቁጭት መፍጠሩ አይቀርም።

አንድ በግል ተበደልኩ የሚል ግለሰብ ባላንጣውን ሊከስ ፈልጎ ራፖር ፀሃፊ ዘንድ ሄደ ይባላል። ከዚያም ባላንጣው አደረሰብኝ የሚለውን በደል ለራፖር ፀሃፊው ይተርክለታል። ፀሃፊውም ዳኛን ያሳምናል ብሎ በሚገምተው ቋንቋ ታሪኩን አጋኖ ከፃፈ በኋላ ለደንበኛው ሲያነብለት ደንበኛው ስቅስቅ ብሎ ያለቅሳል። ራፖር ፀሃፊውም ምነው ወዳጄ? ምን ሆንክ ቢለው በራፖር ፀሃፊው ቆጥቋጭና ሰርሳሪ ቃላት ልቡ የተነካው ከሳሽ፥ ወይኔ ሰውዬው፣ ለካ ይህን ያህል ተበድዬ ኖሯል፥ አለ ይባላል። የህወሃት መሪዎችም አማራ የሚሉት ህዝብ በአንዳንድ ብሄሮች ላይ ፈፀመ የሚሉትን በደል ትንሿን እውነት በብዙ ውሸት በማባዛት ባነሳሱት የለካስ ተበድያለሁ ቁጭት ሺዎችን በግፍ ማስጨፍጨፋቸው እውነት ነው።

በሌላ በኩል በተለይ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ዘውግ የህዝብ ድምፅ ሳይሆን የልሂቃን ጥቅምና ፍላጎት ማስጠበቂያ ስልት መሆኑም እውነት ነው። በህዝቡ ላይ ሲደርስ የነበረውን የፍትህና የዴሞክራሲ በደል ከልሂቃኑ ስውር አላማ ጋር ይጣጣም ዘንድ የዘውግ ቅርፅ በመስጠት በህዝብ ስሜት ሲጫወቱ ማየት ከልብ ያሳዝናል። እነዚህ ቡድኖች ከዘውግ በላይ የገዘፈ ሀገራዊ አንድነት የግል የስልጣን እድል የሚያገኙ ስለማይመስላቸው እንወክለዋለን ለሚሉት ህዝብ የሚጠቅምም ቢሆን የሀገር አንድነትን ጉዳይ አምረው ይጠሉታል፤ ይታገሉታልም። በመሆኑም ዘውግ የብልጣብልጥ ግለሰቦች ስብስብ የፖለቲካ ስልጣን እርካብ መቆናጠጫ ስልት እንጂ የህዝብ በደል ፈውስ ባለመሆኑ ጉዳይ ላይ ልዩነት የለኝም።

ይልቁንም ዶክተር መሳይ ከበደ በፅሁፋቸው ላይ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት የዘውግን ፖለቲካ የቀየሰው አማራን ከስሩ ለማጥፋት ነው ያሉት ክብደት ያለው ነጥብ ሆኖ አላገኘሁትም። እኔ እስከማውቀው ድረስ የብሄርን ፖለቲካ በዚያች ሀገር እንዲተከል መነሻ ሰበብ የሆነው የወሎው ተወላጅ ዋለልኝ መኮንን ነው። ኢትዮጵያ የብሄር-ብሔረሰቦች እስር ቤት የሚል መርዘኛ ፕሮፓጋንዳ ፈጥሮ የተማሪውን ንቅናቄ ሲያተራምስ የነበረውና ይህን የዘር መርዝ ተክሎብን ያለፈው ይሄው ያማራ ልጅ ይመስለኛል። ታዲያ ጅብ በቀደደው ውሻ እንዲሉ ህወሃት ዘውግን ለቡድን አላማው ተጠቀመበት ከማለት አልፎ አማራን ለማጥፋት የፈለሰፈው ርእዮት-አለም ነው ለማለት እንዴት ይቻላል። የዘውግ ጥያቄ ካማራ ህልውና ጋር ተሳስሮ መቅረቡስ ምን ያህል ምክናያታዊ ሊሆን ይችላል?

ለዘውግ ጥያቄ መፍትሄው ክልሎችን ማስቀጠልና ስልጣን ማካፈል ነው ያሉትም ቢሆን የተሻለ ማብራሪያ ያሻዋል። ማንኛውም ቡድን በሀገሪቱ የፖለቲካ አስተዳደር ውስጥ ተገቢው ተሳትፎ ሊኖረው ይገባል። የዴሞክራሲ አይነተኛ መገለጫውም ይሄው ነው። በዚህ እድል ለመጠቀም ወይም ይህን መብት ለማግኘት በዘውግ መደራጀት የግድ ነው ሊባል ግን የሚችል አይመስለኝም። ባንፃሩ የትኛውም ቡድን በዘውግ እንዳይደራጅ መከልከል ዴሞክራሲያዊ አይሆንም። ግን በዘውግ እንዲደራጅ መገፋፋት ደግሞ ልዩነትን ማበረታታትና አንድነትን ማዳከም ነው። መፍትሄ የሚመስለኝ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት በጀመረው ጎዳና በመቀጠል ህዝብ እንዲበታተን አቅጣጫ ማሳየት ሳይሆን የፍትህና የዴሞክራሲ ጥያቄዎችን ጨምሮ ዘውግ-ነክ መብቶች በሙሉ ባስተማማኝ የሚከበሩበትን ስርአት በመዘርጋት የህዝብ ፍቅርና አንድነት ዘላቂ ዋስትና እንዲኖረው ማድረግ። ይመስለኛል። ይልቁንስ አሳሳቢው ጥያቄ አሁን በየጎራው የተደራጁት የፖለቲካ ሀይሎች በእርግጥም ለሁላችንም የሚመች የተደላደለ የፍትህ ስርአት ለመፍጠር የሚያስችል አቅም፣ ፈቃደኝነትና ቁርጠኝነት አላቸው ይሆን? የሚለው ነው። በመጨረሻም ዘውግና ሀገራዊ አንድነትን ማጣጣም ያስፍልጋል ስላሉ ዶክተር መሳይን አመስግኜ ልሰናበት፤ ጤናይስጥልኝ!

ህሩይ ደምሴ


“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡

Comments

 1. እውነት አሁን ዘውገኝነት ማንን ጠቀመ? እንዲህ ከቀጠለ ግን ጉዳቱ ለሁላችንም ነው። የምር መለያየት ሲመጣ በተለይ ለትግሬ ክልል በጣም እሰጋለሁ። ምክንያቱም አሁን በተገኘው አጋጣሚ ለተደረገው በዝርፈያ ላይ የተመሰረተ የአገር ግንባታ ወደፊት የኢኮኖሚ መሰረቱን ሙሉ ለሙሉ ያጣል። ብዙ ፋብሪካም ቢገነባም በቂ የተፈጥሮ ሪሶርስ እና ሰፊ ህዝብ የግድ ያስፈልጋል። በተጨማሪ ራሳቸውን የቻሉ አገሮች ከተፈጠሩ እንደ ህዝባቸው ብዛትና መሬታቸው ስፋት ቋሚ የጦር ሰራዊት ይኖራቸዋል። ስለዚህ ያኔ ከአላማጣ ወደ ታች ሰተት ብሎ መግባት በፍፁም አዳጋች ይሆናል። መፍትሔው
  1ኛ ፡ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ባስቸኳይ መታረቅ እና ይቅርታን መጠየቅ
  2ኛ ፡ የጎሳ ክልሎችን ማጥፋት
  3ኛ ፡ የጎሳ ፖለቲካ ፓርቲዎችን መከልከል
  4ኛ ፡ በጎሳ ላይ የተመሠረተ የስልጣን እርከን ማስወገድ
  አለበለዚያ እንዲሁ ከቀጠለ አደጋው እየባሰ እና እየከረረ ይመጣል!!

 2. ይዘውግ ፖለቲካ በጥቂት የስልጣን ጥማት የሀገር ላእላዊነትን የህዝብን ታሪካዊ ትስስር በማጣመም የግል ዝናና የሀገር ሃብት ለመዝረፍ የተቀንስጁ የማፊያዎች ሴረኞች የዘውግ ከስርዓት ውርያኔ የተባለ የጥቂት ወገንተኞች ከተለያዩ ለዚህ እኩይ ተግባር የሆድ አደሮች በመመልመል በሀገርና ህዝብን አዋራጅ ስርአት በመዘርጋት ለአፍሪካውያን የነጻነት ማማ የነበረች ታላቂታን የኢትዮጵያ ህዝባን ካደጋላይ ተጠብቆና ታፍሮ የኖረውን ድንበራን የሀገርና የህዝቡን ብስለአቤትነት በመሻር ለባእዳውያን የመሬት ቅርምት ድምበር አሳልፎ እስከ መሸጥ የደረሱ ኃላፊነትን ያልተሸከሙ በሕግና ስርአት የሌላቸው ተር0ራ ሸፍቶች ናቸው።

Speak Your Mind

*