ያንተ ፈጣሪ (ኢንተለጀንት ዲዛይነር) ማን ነው? – ለጋዜጠኛ አበበ ገላው

ምድራዊ መፍትሄ ማምጣት ያልቻለ፣ ወደ መለኮት ያንጋጥጣል!” መዝገቡ ሊበን

ፕ/ር ተድላ ከጋዜጠኛ አበበ ገላው ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ውስጥ ግልጽነቱ “Intellectual integrity” ያለው ሰው መሆኑን ያሳየበትም ይመስለኛል። ኢትዮጵያ መልካም ሰብዕና ያላቸው ሰዎች አንገታቸውን ደፍተው የሚኖሩባት፣ በየእስር ቤቱ የሚማቅቁባት፣ የሚገደሉባት፣ አገራቸውን ጥለው እንዲሄዱ እየተገፉ የሚወጡባት አገር የመሆኗን ያህል፤ በተቃራኒው መጥፎ ሰብዕና ያላቸው ሰዎች  የሚሾሙ የሚሸለሙባት መሆኗን ሳስብ ነገ የሚሆነው ያስፈራል። የፕ/ር ተድላ አይነት ግልጽነት ያላቸው፣ የአይምሯቸውን የሚናገሩ ሰዎች ወደ አደባባይ መውጣት ግን አንድ ተስፋ ነው። ይህን አይነት “intellectual integrity” ነው በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ምሁራን ውስጥ ያጣነው።

ይህን እንድጽፍ ያነሳሳኝ ዋናው ምክንያት በክፍል ሁለት ቃለ-ምልልሱ ላይ ካነሳቸው በርካታ ጠቃሚ ሃገራዊ ጉዳዩች ውስጥ ዋና የሆነውና “ኢትዮጵያዊያን ብዙ የተማሩ ሰዎች አሉ… በህብረት አንድ ነገር [ለአገራቸው] ለማድረግ እውነተኛ ሰዎች መሆን አለባቸው… እውነትን ማክበር፣ እውነተኛነትን “ቫሉ” ማድረግ፣ ለእውነት መቆም፣ … እውነትን የማያከብር ህብረተሰብ፣ በቀላሉ ይዋሻል … ለማጭበርበር፣ አንዱን አንዱ ለማታለል ቀላል ነው የሚሆነው…” ሲል የተናገረው ነው። ለምሳሌ፣ የሳይንስ ፈተና ላይ፣ “የሰው ልጅ አመጣጥ፣ የኢቮሉሽን (ብቸኛ ዝርያዎች መንስዔ[1]) ውጤት ለመሆኑ የ3.5 ሚሊዩን አመት እድሜ ያላት ሉሲ ምሳሌ ናት” ብለህ መልስ መልሰህ፣ እሁድ ሲነጋ ቤተስኪያን ለጸሎት ከሄድክ፣  ወይም አርብ ዕለት ለሶላት መስጊድ ከተሰለፍክ (በአብርሃማዊዎቹ እምነት መሰረት የሰው ልጅም ሆነ ጠቅላላ ዩኒቨርስ ከተፈጠረ ገና አስር ሺህ አመት አልሆነውም)፣ ለራስህ ታማኝ ያልሆንክ/አስመሳይ ነህ። አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ምሁር “አስመሳይ/hypocrite” ነው። ስለ እውነት እና ውሸት፣ ጥሩ እና መጥፎ፣ ትክክል እና ስህተት.. ወዘተ ስለመሳሰሉት መሰረታዊ የሆኑ የሞራል ጉዳዩች ላይ የምዕራባዊያኑን “Renaissance” ያህል አብዩት ማካሄድ ሳያስፈልገን አይቀርም። “A society deserves the leaders it gets” የሚል ማንበቤን አስታውሳለሁ፤ (በግርድፉ “የመሪዎቹ ማንነት የአንድ ማህበረሰብንም ማንነት ይናገራል”) እንደማለት ነው፣ (በህወሃት ክፋት፣ ጭካኔ፣ መሰሪነት እና ውሸት የባሰ የምራል ውድቀት ውስጥ የመግባታችን ነገር እንዳለ ሆኖ)። ሌላውን ሁሉ ለጊዜው አቆይተን… ሃይማኖትን በተመለከተ በተለይም በምሁሩ ውስጥ ያለው አስመሳይነት (hypocrisy) ለጉድ ነው።

@@@@@@@@@@

ከወራት በፊት ያላገኘሁትና በስራ ጉዳይ እዚሁ አገር ውስጥ የማውቀው አንድ ወዳጄ ጋር በድንገት ተገናኘን። በሙያው የዶክትሬት ዲግሪ አለው። “All about Adam & Eve, how we came to believe in gods, ….” የሚል መጽሃፍ ይዣለሁ። “ምንድነው የምታነበው…” ሲል ጠየቀኝ። ርዕሱን አስነበብኩት። “ኦ…” ብሎ ሲያበቃ “አዳም እና ሄዋን…’ ነው የሚለው?… መቼም ‘የአዳም እና ሄዋንን ታሪክ “Myth” (ተረት ተረት) ነው’ ነው የሚሉት፣ አይደል?… እውነታቸውን’ኮ ነው። ተረት ተረት ነው” አለኝ።

እውነቱን ነው። ይኼን መጽሃፍ አንብቦ እንደገና ተመልሶ “አዳም እና ሄዋን የሰው ዘር የመጀመሪያዎቹ ናቸው…” ብሎ፣ ቢያንስ ትንሽ ሳይጠራጠር አፉን ሞልቶ የሚናገር ሰው ያለ አይመስለኝም። የዚህም ወዳጄ አስመሳይነትም የገረመኝ የዚያኑ ያህል ነው። ሰውየውን በሚገባ አውቀዋለሁ። የሰንበት ቅዳሴ አምልጦት አያውቅም። ታዲያ ምን ቤተስኪያን ያመላልስሃል? የሚል የጅል ጥያቄ አልጠየቅሁትም። መልሱን አውቀዋለሁ።

@@@@@@@@

የዛሬ ሰላሳ አምስት አመት ገደማ፣ በዓሉ ግርማ በአንዱ መጽሃፉ ውስጥ “እግዜር ሰውን በአምሳሉ አልፈጠረም፣ ይልቁንም ሰው ነው በአምሳሉ እግዜሩን የፈጠረው” የሚል ጽሁፉን ያነበብሁ እለት “ጉድ” ነበር ያልኩት። ለካንስ ይኼ የተባለው (በዓሉ እጅግ በጣም ውብ በሆነ አንድ ዓ.ነገር፣ በራሱ ቋንቋ የገለጸው ከመሆኑ በቀር) ገና ክርስቶስ ተወለደ ከተባለበት አመት ስንት እና ስንት መቶ ዘመን በፊት ኖሯል! (“እንዴ! ደሞ ከክርስቶስ እና ከመጽሃፍ ቅዱሱ እግዜር በፊት ሌላ እግዜር ነበር እንዴ?” ብሎ የሚጠይቅ አይጠፋም። ስንት እና ስንቱ እግዜር ሲወለድ፣ ሲሾም እና ሲሻር አንዳንዴም ሲገደል ኖሮ ነው የመጽሃፍ ቅዱሱ እግዜር የተፈጠረው።) … ግሪካዊው ፈላስፋ እና ገዢ “ክሪቲያስ” እንደጻፈው በሚገመተው “ሲሲፈስ” (Sisyphus)  በተሰኘው ስራ ውስጥ የሚከተለው ይገኝበታል። በግርድፉ (እና በጥቂቱ) እንዲህ ወደ አማርኛ መልሼዋለሁ፦

“… አንድ ወቅት ነበር፣ የሰው ልጅ ህይወት ስርዓት አልባ የነገሰበት፣
አውሬያዊ እና ዘግናኝ–አመጻ  የሞላበት፣
በጎ አድራጊ የማይሸለምበት፣ አጥፊም የማይቀጣበት፣
እናም ሲመስለኝ፣ አንድ ብልህ፣ ሊቅ ሰው ህግ ደነገገ፣
አጥፊውን የሚቀጣ፣ ፍትህ ገዢ ልትሆን፣  እያንዳንዱ ወንጀል ካደረገ፣
…… በእኩልነት (ያለ አድልዎ) ሊቀጣ [“ቀ”ን ጠበቅ]፣
ባደባባይ በደል እና አመጻን ማድረግ በወንጀል ሊያስቀጣ፣
እናም… ወንጀልን መከላከል ተቻለ፣
የሠው ልጅ ጥቂት “እፎይ” አለ፣
ግና ግና በስውር (እማኝ በሌለበት)–በደልና አመጻን መስራት ተጀመረ፣
… እናም ያኔ ይመስለኛል፣ ያ ፍትህ-አወቅ ብልህ ሰው ፈሪሃ እግዜርን ፈጠረና፣ በስውር ደባ የሚሰራውን፣ የተናገረውንም ሆነ ያሰበውን ሁሉ…
የሚያይ የሚሰማ እና የሚያውቅ እግዜርን ሰራ/ፈጠረ…”

ይህ ስራው “The Critias Fragment” ተብሎም ይታወቃል። አሁን በዚህ ባለፉት ጥቂት መቶ ክ/ዘመናት ውስጥ ብቻ፣ አብርሃማዊ መጽሃፍቶቹ ብቻ ሳይሆኑ፣ “የመጽሃፍቶቹ ውስጥ እግዜሮች ራሳቸው የሰው ልጅ የፈጠራ ስራ የመሆናቸው…” ጉዳይ ላይ የተጻፉት መጽሃፍት እልፍ ናቸው። ታላላቅ የሚባሉ በርካታ የክርስትና ሃይማኖት ሊቃውንት እና የአጥባቂው ፓርቲዎች የተማሩ እና የተመራመሩ ፈላስፋዎች ሳይቀሩ ዛሬ ዛሬ፣ አብርሃማዊዎቹ መጽሃፍት የሰው ልጅ የፈጠራ ስራ መሆናቸውን በአደባባይ እየተናገሩ፣ ነገር ግን ይሄን ዩኒቨርስ የፈጠረ አንድ “ፈጣሪ/ኢንተለጀንት ዲዛይን አለ…” ማለት ይዘዋል–አብራሃማዊያኑን እግዜሮች እየዘለሉ—ልክ እንደ አበበ ገላው “ኢንተለጀንት ዲዛይን” ማለት ነው። ለመሆኑ ይኼ ኢንተለጀንት ዲዛይነር፣ ምን ያህል ኢንተሌጀንት ነው?

አሁን የጻፍኩትን እያነበብኩ ነው። … ለእኔ ይሄን ጽሁፍ እንዳይ ያደረገኝ “አይን” የተባለው የሰውነቴ ክፍል እንዴት እንደሚሰራ እና ምን ምን አይነት ሌሎች ነገሮች አንድ ላይ ተቀናብረው እና ተዋህደው “ማየት” የተባለውን ማየት የመስራታቸውን ሁኔታ… የአፈጣጠሩ ረቂቅነት ይገርመኛል፤ ይኼን የፈጠረ አንድ አዋቂ ካለ እውነትም በጣም ረቂቅ የሆነ ችሎታ ያለው አዋቂ ነው። ይኼ “አይን” የተባለው የሰውነት ክፍል እንዴት እንደሚያይ አሁን የማስብበት አንጎል (brain) እንዴት እንደሚሰራ እንዴት ለማሰብ እንደቻልኩም ሳስብ…  ይኼን የሰራው አዋቂ እውነትም ሱፐር ረቂቅ የሆነ ጥበብ እና እውቀት ያለው “extremely super intelligent (የአዋቂነቱ ብዛት አማርኛው ብቻውን ያልገልጸልኝ ቢመስለኝ ነው እንግሊዝኛውን የዶልኩት)፣ አሰራሩ ጥበቡ ውስብስብ ነው። ከሰማያዊ ሰማይ በላይ፣ ከክዋክብቱ እና ፕላኔቶቹ ውስጥ እና ዙሪያ ምን እንዳለ፣ የዩኒቨርስን ወርድ እና ስፋት መጠን የለሽነት ወዘተ… ሳስብ፣ ይኼን ዩኒቨርስ የምንለውን መጀመሪያ እና መጨረሻ የሌለውን ነገር (የሰው ልጅ ያልደረሰበት ገና ስንትና ስንት ነገር አለ?”) የፈጠረ ሃይል እውነትም ፍጹም የበቃ፣ የእውቀቱ ልክ የማይደረስበት አዋቂ ነው።

መጽሃፍ ቅዱስንም ሆነ ቁርዓንን ያስጻፈውም በለው የጻፈው፣ የእውቀቱ ልክ የማይደረስበት አዋቂ ያው እግዜር/አላህ እንደሆነ ነው ተጽፎ የምናየው እና የምንሰማው። ይህን አዋቂ “ኢንተለጀንት ዲዛይነር” (እግዜር/አላህ)፣  የሰው ልጅ እንደፈለገ ሲሰፋ እና ሲቀደው በኖረው፣ አብርሃማዊዎቹ መጽሃፍት (መጽሃፍ ቅዱስ፣ ቁርዓን እና ቶራህ”) ውስጥ ያለው እግዜር ነው ማለት ለኔ ይኼን ዩኒቨርስ የፈጠረ ነው የሚባለውን እና ረቂቅ ችሎታ ያለውን ፈጣሪ (ካለ) እውቀት ወይም ኢንተሌጀንስ መናቅ ነው። ሁሉም የአብራሃማዊ ሃይማኖት መሰረት የሆኑት መጽሃፍት የሰው ልጅ እንደፈለገ ሲቀድ እና ሲሰፋቸው የኖሩ መጽሃፍት ናቸው። ይሄ የሚነግረኝ ቢኖር የሰው ልጅ ራሱ የፈጣሪነትን ሚና መውሰዱን ነው። መጽሃፍቶቹ የማይታይ እና የማይዳሰስ መለኮታዊ እጅ እንደሌለባቸው እና የሰው ልጅ ስራዎች መሆናቸውን ነው። ሁሉም የአብርሃማዊ መጽሃፍት ከተጻፉበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ እየታረሙ እና እንዳስፈላጊነቱ እየተለወጡ እዚህ የደረሱ ናቸው—ልክ እንደ በዓሉ ግርማ “ኦሮማይ”፣ሃዲስ አለማየሁ “ፍቅር እስከመቃብር” ወይም እንደ በውቀቱ ስዩም “ከአሜን ባሻገር”። መጽሃፍ ቅዱስ የሰው ልጅ የፈጠራ ስራ መሆኑን ለማወቅ ይረዳ ዘንድ፣ ሃይማኖቱን በከፍተኛ የእምነት ጽናት እና ጥልቅ እምነት አራማጅ (ሰባኪ) ከነበረው ሰው ለመረዳት ይኼን ዶኩመንቴሪ (ከስር የተኮለኮሉትን አስተያየቶችንም ጨዋነት ጭምር ) መከታተል  ይጠቅማል።

በዓሉ ግርማ “መጽሃፍ ቅዱስን የማነብበት ምክንያት ቢኖር በስነ-ጽሁፍነቱ ብቻ ነው” ያለው የትኛው መጽሃፉ ውስጥ ነበር? የምዕራቡ አለም ዛሬ መጽሃፍቶቹ የሰው ልጅ የፈጠራ ስራዎች የመሆናቸውን ጉዳይ እና ሃይማኖቶች ላይመለሱ እየጠፉ እንደሆነ፣ እዚህ ለመድረስ ከሁለት ሺ አመታት በላይ የፈጀባቸው የአብራሃማዊዎቹ ሃይማኖቶች ካሁን በኋላ የሁለት መቶ አመት እንኳን እድሜ እንደማይኖራቸው በስፋት እየተጻፈበት ያለ ጉዳይ ነው

ኢትዮጵያ በጅላጅሎች እጅ እንዴት ያለ ታላቅ ሰው–በዓሉ ግርማን–አጣች? በዓሉ እውነቱን ነበር፣ መጽሃፍ ቅዱስ እንደማንኛውም መጽሃፍ ሁሉ በእውነተኛ ታሪክ እና ባለታሪኮች እና በፈጠራ ገጸ ባህሪያትም ጭምር የተዋቀረ፣ እግዜሩ ራሱ ዋና ገጸ-ባህሪ የሆነበት (አንዳንዴ ደግ እና አዛኝ [Hero]፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ክፉ እና ጨካኝ [villain] ሆኖ የሚጫወትበት) ታሪክ ቀመስ ልብ-ወለድ ድርሰት ነው። ሁሉን የሚያውቀው፣ በሁሉም ቦታ የሚገኘው እና ሁሉን ለማድረግ ሃይል ያለው እግዜር ያሥጻፈውም ሆነ የጻፈው መጽሃፍ ቅዱስ የሰው ልጅ እንደፈለገ በየጊዜው ሲቆርጥ እና ሲቀጥለው የሚኖር መጽሃፍ መሆን ያለበት አይመስለኝም። መጽሃፉ እንደኔ ሰው በሆነ ሰው እየታረመ እና እየተስተካከለ እዚህ የደረሰ የመሆኑን ታሪክ ለመመስከር እኔ ራሴ በህይወት ያለሁ ምስክር ነኝ።

@@@@@@@@

በአንድ ብሩህ የአዲስ አበባ ረፋድ ላይ ፒያሳ እና ጊዎርጊስ አካባቢ እንዲሁ ስራመድ አንድ ከአምስት አመታት በላይ አካባቢ ያላየሁትን እና የት እንዳለ የማላውቀው የነበረውን፣ በጸሃፊነት ትምህርት ከአንዱ ኮሌጅ ተመርቆ፣ በአንድ ስራ አስኪያጃችን ቢሮ ውስጥ፣ የዛሬ ምንትስ አመት አካባቢ፣ በጸሃፊነት ይሰራ የነበረ አንድ የቀድሞ የስራ ባልደረባዬን ድንገት አገኘሁት። ከተለመደው ሰላምታ በኋላ፦

“ስራ እንዴት ነው? የት እና ምንድነው የምትሰራው?” አልኩት።
“ቅዱስ ሲኖዶስ” አለኝ። ያገኘሁት ጊዎርጊስ አካባቢ ነበር።
“እንዴ ደ’ሞ እዚያ ምን ትሰራለህ?” አልኩት እየገረመኝ። በዲሲፕሊኑ ይሆን የቀጠሩት? ስል አሰብኩ። በህይወቴ እንደዚህ የስራ ባልደረባዬ ጽዱ “Neat” የሆነ ሰው አጋጥሞኝ አያውቅም። እንኳንስ ሱሪ ሸሚዝ፣ ካልስ እንዲሁ ወንበር ወይም መሬት ላይ ተዝረክርኮ ማየት ቀርቶ፣ ከምኝታ ውጭ ሆኖ፣ የብርድልብሱ አንዱ ጫፍ እንኳን አንዴም ታጥፎ አይቼ የማውቅበትን ጊዜ አላስታውስም።
“ጳጳሱ አሁን ያለው መጽሃፍ ቅዱስ ትክክል አይደለም ብለው ያምናሉ፣ እና እሳቸው የሚተረጉሙትን መ/ቅ መተየብ/መጻፍ ነው ስራዬ” አለኝ።

እኔን ለማመን እና ላለማመን አይምሮሽን ማስጨነቅስ አለብሽ እንዴ? መጽሃፍ ቅዱስ ቤትሽ ውስጥ መደርደሪያ ላይ ከተሰደሩት መጽሃፍት ምንም የተለየ ርቅቀት የሌለው መሆኑ ራሱ ለመጠራጠር በቂ አይደለምን? መጽሃፍ ቅዱስም ሆነ ቁርዓን ምን ያህል ጊዜ ሲቆረጥ እና ሲቀጠል፣ ሲጣፍ እና ሲለጠፍ እንደኖረ ለማወቅ ዛሬ ጉግል ማድረግ ብቻ ይበቃል። … የአጥባቂዎቹ ፓርቲ እጅ ያለበትን አንድ የመጽሃፍ ቅዱስ እርማት ስራ በምሳሌ ልጥቀስ።

ኦሪት ዘጸአት 21፡ 22 ላይ “ሁለት ሰዎች ቢጣሉ፥ ያረገዘችንም ሴት ልጁን እስክትጨነግፍ ቢገፉአት ባትጐዳ ግን፥ የሴቲቱ ባል የጫነበትን ያህል ካሳ ይስጥ፤ ፈራጆቹም እንደ ፈረዱበት ይክፈል” የሚለውን የእንግሊዝኛው የመጽሃፍ ቅዱስ ጥቅስ አሁን በእኔ እድሜ በ1975 ዓ.ም፦ “that she has a miscarriage, yet there is not further injury” የሚለው ተሰረዞ እና ተደልዞ፣ “that she gives birth prematurely, yet there is no injury” በሚል እንደገና ታርሞ ተጽፏል። ነገሩ ያለው፣ “miscarriage (የጽንስ ጭንገፋ/ውርጃ)” የሚለው ቃል በጽንሱ ላይ ሞት የሚያስከትልም ጭምር መሆኑ እና ጉዳቱን ከፍተኛ ስለሚያደርገው፣ “she gives birth prematurely” የሚለው “ልጁ ሳይጠነክርም ቢሆን ተወልዷል”፣ እና ጉዳቱ አነስተኛ ነው ለማስባልም ነው፣ “እና ጽንሱ የጨነገፈው “prematurely (በደንብ ሳይጠነክር)” እና “no further injury የሚለው ደግሞ፣ በእናቲቱ ላይ የደረሰ ጉዳት ከሌለ”(ከውርጃው በተረፈ ሌላ ህመም ከሌለ [ውርጃ ላይ ቀርቶ በዘመናዊ ሳይንስ እየታገዘች እንኳን የሴት ልጅን ምጥ እና መከራ ደም ፍሰት ወዘተ.. ሁሉ ህመም እንዳልሆነ ሁሉ])  በሚል የደረሰውን ጉዳት ወይም፣ የጥቅሱን የአመጻ ድምጸት (violent verse tone) ለማሳነስ ነው።

“ውርጃ” የጽንሱንም ማህጸን ውስጥ እንዳለ መሞትንም ያስከትላል፣ እና ማስወረድን በግልጽ የሚደግፉት የለዘብተኛ አመለካከት ያላቸው ፖለቲከኞች በጣም ተቀባይነት እያገኙ የመሄዳቸው ጉዳይ ያሳሰባቸው እና “… ሆድ ውስጥ የሞተን ወይም እየሞተ ያለን ጽንስ ማስወረድ እንዴት ሃጢያት ሊሆን ይችላል?” የሚለውን፣ የለዘብተኛ ፖለቲከኞችን ጥያቄ መልስ መስጫ ማጣፊያው ያጠረባቸው ቡድኖች ናቸው የጥቅሱን ለውጥ እና እርማት ያስደረጉት። ከዚህ ከዕርማት ስራ በላይ ብዙዎቹን ጸሃፍት የገረማቸው ነገር ቢኖር ግን የተጎዳችው ሴቲቱ ሳትጠየቅ “የሴቲቱ ባል” ብቻውን የመፍረዱ ጉዳይ ነው (አንድ ጸሃፊ፣ “በመጽሃፉ መሰረት ሴት እቃ ነች፣ አይሮፕላን ላይ የጫንከው ሻንጣ ቢጠፋብህ ወይም ቢቀደድብህ፣ ለእቃው ሳይሆን ለአንተ ካሳ እንደሚከፈለው ማለት ነው” ብሎ መጻፉን አስታውሳለሁ)። አብርሃም የገዛ ልጁን ለመሰዋት እንደተጋበዘው አይነትም ነው፣ ዘጠኝ ወር አርግዛ እና አምጣ የወለደችው፣ መከራዋን አይታ ያሳደገችው ሳራ ሳታውቅና ሳትፈቅድ ልጅን ያህል ነገር ለማረድ ማሰብም ሌላው በርካታ የመጽሃፍ ቅዱስ ታሪክ ሃያሲያንን ያስገረመ ጉዳይ ነው። እኔንም ቢሆን “ምንም የማያውቅ ትንሽ ልጁን ከማረድ ራሱን አያርድም ኖሯል?” እንድል አድርጎኛል። አንዳንዶቹ የመጽሃፍ ቅዱስ ሃያስያን ደግሞ፣ አብርሃምን “የሞራል ጭራቅ/መጥፎ ምሳሌ/”moral monster” ያደርጉታል። ሲያንሰው ነው።

በአብዛኛው የዓለም ክፍል ውስጥ በሴቶች እና በዘር አድልዎ ምክንያት እስካሁን ለደረሰው እና አሁንም እየደረሰ ላለው ግፍ እና በደል ከአብራሃማዊ ሃይማኖቶች በላይ ተጠያቂ ሊሆን የሚችል ሌላ አካል/ተቋም ያለ አይመስለኝም። እዚሁ ኦሪት ዘፀአት ላይ “ሰውም ወንድ ባሪያውን ወይም ሴት ባሪያውን በበትር ቢመታ፥ ቢሞትበትም፥ ፈጽሞ ይቀጣ፤ የተመታው ግን አንድ ወይም ሁለት ቀን ቢቈይ ገንዘቡ ነውና አይቀጣ” ይላል። አሁን በዚህ ክ/ዘመን  የአንዳንድ ፓርቲ  ደጋፊ የሆኑ የሃይማኖቱ ሰባኪዎች፣ ባርነት በመጽሃፍ ቅዱስ የተደገፈ ነው…” ማለት ጀምረዋል፤ መጠርጠር ደግ ነው።

ከአብርሃማዊያኑ ሃይማኖቶች መምጣት ጋር ተከትሎ በሴቶችም ላይ የደረሰው በደል የከፋ ነው። ምክንያቱ ደግሞ አሁን አሁን ግልጽ እየሆነ የመጣ ይመስላል። በአንድ ወቅት፣ የሰማያዊው ሰማይ (መለኮታዊው) እግዜር ከመፈጠሩ በፊት፣ ምድራዊ የሴት እግዜራት የገነኑበት፣ ሴቶች ወንዶችን ያስገብሩ እና ያሥሰግዱ የነበረበት ዘመን ነበር–እንደ የኬልቲኳ “ብሪጂድ” እና የግብጾቹ “አይሲስ፣ እናና” የመሳሰሉት። በዚያ ጥንት ዘመን፣ የሴት ልጅ ፈጣሪነት ምክንያት ከሆኑት ክስተቶች አንዱ፣ በግብር አርግዛ፣ አምጣ ወልዳ ሰው ስትፈጥር (ፈጣሪ) የምትታየው ሴቱቱ ከመሆኗ ጋር የተገናኘም ነው (እንዴት ከኛ የተሻሉ ነበሩ?)። ቀስ በቀስ ሴቲቱ እግዜሪት በወንዱ እግዜር እየተሸነፈች፣ የወንድ እግዜሮች (ማድሩክ፣ ዚውስ …ወዘተ) እየገነኑ የመጡበት ሁኔታ ተፈጠረ፣ ነገር ግን ወንዶቹም ምድራዊ እግዜሮች እያደር የግዜርነቱ ነገር አልተሳካላቸውም፣ ያመናቸው እና ያመለካቸው ህዝብ ከጎርፍ እና እሳተ ገሞራ ሳያድናቸው ሲቀር፣ በጎርፍ እና ድርቅ ሰብል ወድሞ የሚልሰው የሚቀምሰው ያጣው ያካባቢው ያመለካቸው ህዝብ ያወግዛቸው ጀመር፣ አንዳንዶቹንም የሰው እግዜሮች ህይወታቸውንም ዋጋ ያስከፍላቸው ጀመር፤ እናም ህዝብ እምነት እያጣባቸው ሲሄድ… ከዚህ ሁሉ በኋላ ነው ምድራዊዎቹ እግዜሮች ቀስ በቀስ እግዜርነቱን ለማይታይ እና ለማይዳሰስ ፈጣሪ፣ ሰማያዊ/መለኮታዊ እግዜር አሳልፈው እየሰጡ…  …እናም… እንዲያ … እንዲያ ነው የአብርሃማዊዎቹ ሃይማኖቶች ውስጥ ያሉት የማይታዩ እና የማይዳሰሱ ሰማያዊዎቹ ወንድ እግዜሮች የተሰሩት።

“የኢትዮጵያን ህዝብ መንፈስ ቅዱስ እየጎበኘው ነው” እያሉ ከበሮ የሚደልቁትን “ነብያት”፣ ሰባኪዎች እና ምዕመናኑም ራሳቸውን በሶስት መክፈል ይቻል ይመስለኛል።

1ኛ) ፍጹም በሆነ ቅንነት እና እምነት፣ እግዜር ተዓምር ይሰራል ብለው የሚያምኑ እና መፍትሄው እሱ ብቻ ነው ብለው የሚያምኑት (Delusion ውስጥ ያሉ ናቸው)።

2ኛ)  በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የህልውና መሰረታቸው ከሃይማኖቱ ጋር የተቆራኘ (ለምሳሌ አብዛኞቹ ሰባኪዎች እዚያው ጭንቅ ያለበት አገር ውስጥ ያሉ በመሆናቸው፣ በሌላውም አለም እየኖሩም ቢሆን…የራሳቸውን ሥራ የፈጠሩ ናቸው። አጀማመራቸው መሰረቱ ከልባቸው አምነው “ዲሉዥን” እንኳን ቢሆን እያደር ግን ጥቅም፣ ህልውና እና ይሉንታ እዚያው ተጣብቀው እንዲቀሩ ያደረጋቸው ናቸው)

3ኛ) ፍጹም የሚያጭበረብሩት ናቸው። …በጥቅሉ ግን እነዚህ “መንፈስ ቅዱስ ጎበኛት” እያሉ ከበሮ የሚደልቁት አብዛኛዎቹ ሰዎች የማህበራዊ ሳይንስ እና ስለ አንድ ማህበረሰብ እድገት እና ውድቀት አመጣጥ እውቀት የጎደላቸው ናቸው። ድህነት፣ መሃይምነት፣ ማህበረሰባዊ/ፖለቲካዊ ውጥረት እና ጭንቀት በበዛበት እና ምድራዊ ተስፋዎች ሁሉ በጨለሙበት ቦታ ሁሉ የሃይማኖት አጥባቂነት/አክራሪነትም ይከሰታል፣ የኢትዪጵያ ህዝብ ምድራዊ ጭንቅ ውስጥ ነው። በአገሩ ላይ ምንም አይነት የመኖር ዋስትና (ምግብ ልብስ እና መጠለያ፣ የጤና አገልግሎት) ያላገኘ ህዝብ እንዲህ እግጅ አሳዛኝ፣ አንዳንዴ አሳፋሪ፣ ዘግናኝ፣ እና አስቂኝም እስኪሆን ድረስ፣ ህጻን ልጅ በሆነ ነገር በማፍዘዝ እና ማደንዘዝ “በጸሎት አዳንኩ” እስከሚባልበት ድረስ ወደ መለኮት ቢያንጋጥጥ የሚገርም አይሆንም። … ምድራዊ መፍትሄ ማምጣት ያልቻለ ወደ መለኮት ያንጋጥጣል እንዲሉ ነው። እናውቅልሃለን የሚሉት ሰባኪዎች እና ነብይ ተብዬዎቹም እንደማህበረሰቡ ሁሉ ጭንቅ ውስጥ ያሉ ናቸው። እናም ለራሳቸው ስራ ፈጠሩ። ከመለኮት ምንም ጠብ ያላለለት ህዝብ ተመልሶ የፖለቲካም ሆነ የሃይማኖት መሪዎቹን፣ ቄስ ደብተራውን እና ፓስተር ነብይ ተብየውን፣ ደረሳ ቃልቻውን ሁላ ይጠይቃል፣ አለያም እርስ በርስ ሊባላ…ሁሉንም ዋጋ ያስከፍል ይሆናል። የፕሮቴስታንት ሃይማኖትን አነሳስ ታሪክ ማወቅ ጠቃሚ ይመስለኛል። ሃይማኖቱ በ”protest/አመጽ/ተቃውሞ” የተጀመረ ነው። “…እግዜር ይቅር እንዲላችሁ እና/ወይም… መንግስተ ሰማያት እንድትገቡ ገንዘብ እዚች ውስጥ አስቀምጡ…” እያሉ እና ሌላም ሌላም ጸያፍ ነገር እያደረጉ ህዝቡን ያሰቃዩ ቄስ እና ደብተራዎች፣ ካርዲናል እና ጳጳሶች የከፈሉትን ዋጋ ማንበብ ነብይ ተብዩዎቹን ይጠቅም ይመስለኛል። የፕሮቴስታንት/ጴንጤ መሪዎችም፣ እንደ ኦርቶዶክስ ክርስትና እና እስልምና መሪዎች ሁሉ የህወሃት መሰሪ ስራ እና

የቁርዓን ጥቅሶች እንደ መ/ቅ ሁሉ የተለያዩ አገላለጾች ቢኖሯቸውም፣ አጠቃላይ ሃሳቡን ግን አይቀይረውም

ማስፈራራት ሰለባ ሆነው በህወሃት መዳፍ ስር መውደቃቸው እውን ይመስላል። አሁን በኛ እድሜ በ”ሜጫ” አንገት እየቆረጠ (ሊብያ ውስጥ፣ ምንም አቅም የሌላቸውንና አንድም መከላከያም ሆነ ተከላካይ የሌላቸውን፣ በገዛ አገራቸው መኖር አቅቷቸው ሄደው የታረዱትን ሰላሳዎቹን ኢትዮጵያዊያን) ያሳየን አይሲስ፣ ክርስቲያን መሆናቸው ብቻ መሆኑ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የተገለጸ ነው። ይህ ኢ-አማኝ የሆኑ ሰዎችን የመውጋቱ ጉዳይ እና ሁሉም የእምነቱን አምላክ (አላህ)ን ብቻ እስኪያመልክ ድረስ የመዋጋቱ ጉዳይ በቁርዓኑም ቢሆነ የተደገፈ ለመሆኑ የተጠቀሰ ቢሆንም (ከጎን የተለጠፈውን ይመልከቱ)፣ የአይሲስ አነሳሱም ሆነ አደረጃጀቱ በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ጉዳዩች ላይ በሺያ ሙስሊሞች አድልዎ ተደርጎብናል ብለው በተነሱ የሱኒ ተከታዮች መሆኑን ቆም ብሎ ማሰብ ለሁሉም አካል ጠቃሚ ይመስለኛል። በዘርና በሃይማኖት ህዝብን መከፋፈል የመጨረሻ ውጤቱ ለሁሉም የከፋ ነው። በተለይ እንደኛ አብዛኛው በአሰቃቂ ድህነት ውስጥ ያለ ህዝብ። እነዚህ ዛሬ እያልተስተማሩ ያሉት (miss-educated) ህጻናት፣ ነገ ምንም ጠብ  የሚል ነገር ሳይኖር ሲቀር፣ በቀላሉ ወዳንዱ የእምነት ቡድን ተስበው ገብተው “ሜጫ” ሊያነሱ የማይችሉበት ምክንያት አይታየኝም።

@@@@@@@

አሁን አሁን ስለዩኒቨርስ አጀማመር የሳይንስ ትንታኔ ለእውነታው እየቀረበ ሲመጣ እና የአብርሃማዊያኑ ሃይማኖቶች እግዜሮች የማያዋጡ መሆናቸውን ሲገነዘብ እና የማያስኬድ ሲመስለው፣ “አንቱ” የተባለው የሃይማኖቱ ሊቅ እና አዋቂው ሁላ፣ ዩኒቨርስን የፈጠረ “ኢንተለጀንት ዲዛይነር አለ” እያለ እየሞተ ያለውን የምዕራቡን አለም እግዜር ማስታመም ይዟል።

@@@@@@@

ለጋዜጠኛ አበበ ገላው፦ ከዶ/ር ተድላ ጋር ባደረግኸው ቃለ ምልልስ ውስጥ “… እኔ የምታወቀው ፈጣሪ የለም በሚለው …ነበር።…የፈጣሪ መኖር እና አለመኖር ሰዎች በአስተሳሰብ ወይም በሪዝን ብቻ ሊያረጋግጡት የሚችሉት ጉዳይ አይደለም፣ እምነት ይፈልጋል … በፈጣሪ አምናለሁ። በተለያዩ ምክንያቶች አመለካከታችን ይቀየራል … ከአካባቢህ ብዙ ነገር ትማራለህ ይኼ ሁሉ ነገር ማን እንደፈጠረው፣ ዲዛይነር ከሌለው… ይኼ ሁሉ ነገር እንዴት ሊሆን ይችላል የሚለውን በቀላሉ መልስ የማታገኝለት  ነገር…” በማለት ” አንድ ኢንተሌጀንት ዲዛይነር …” እንዳለ ነግረኸናል።

“የፈጣሪ መኖር እና አለመኖር ሰዎች … በ”ሪዝን”ብቻ ሊያረጋግጡት የማይችሉት…” መሆኑን ተናገርክ እንጂ አንተም ዲዛይነር እንዳለ “ሪዝን”ህን “ይኼ ሁሉ ነገር ማን እንደፈጠረው፣ ዲዛይነር ከሌለው… ይኼ ሁሉ ነገር እንዴት ሊሆን ይችላል”  በማለት ነገርከን’ኮ። ቀድሞ የምትታወቅበት የ”ፈጣሪ የለም …” እምነትህም  ምክንያት (ሪዝን) የነበረው ይመስለኛል። አሁንም “ይኼ ሁሉ ነገር ማን እንደፈጠረው … ዲዛይነር ከሌለ…” ስትለን፣ ዩኒቨርስን የፈጠረ ሃይል አለ ማለትህም ይመስለኛል። ሁሉም ክርስቲያን የእምነቱ መሰረተ ምክያንቱ (ሪዝን) “መጽሃፍ ቅዱስ የእግዜር ቃል” እንደሆነ ስለሚያምን ይመስለኛል። መጽሃፉ “…ምድርን ፈጠረ፣ ወንድን ከአፈር ሰራ…ሴትን ደሞ…” ይላል። መጽሃፉ ዩኒቨርስ እንዴት እንደተፈጠረ በግልጽ ይናገራል። ለመሆኑ ያንተ ፈጣሪ የመጽሃፍ ቅዱሱ ነው? የቁራኑ አላህ ነው? ወይስ የቶራሁ የህዌ ነው? ከነዚህ ሶስቱ ሁሉ አንዱ ካልሆነ፣ እነዚህ ሶስቱም አብርሃማዊ እግዜሮች የኔ እግዜሮች አይደሉም፣ ግን ሌላ እግዜር ሊኖር ይችል ይሆናል/አለ…” ብለህ በአደባባይ ልትነግረን ትችላለህን?

@@@@@@@@@@

እውነተኛውን “ኢንተሌጀንት ዲዛይነር” እስክደርስበት ድረስ፣ የኔ እግዜር፣ የአብርሃማዊያኑን እግዜሮች የፈጠረው የሰው ልጅ ራሱ ነው! ከሶስት ሚሊዩን አመት በላይ እድሜ ካላት የሰው ልጅ መገኛ ከሆነችው የሉሲ አገር ተፈጥረሽ፣ አስር ሺህ አመት እንኳን እድሜ የሌላቸውን የሜዲቴራንያን አካባቢ ስዎች የፈጠሯቸውን የአብርሃማዊ ሃይማኖቶችን እግዜሮች መከተል ላንቺ አይሆንም። “አንቺ ራስሽ እግዚአብሄሪት ነሽ”

@@@@@@@@@@
www.segelgazeta.com

ማስታወሻ፡– ይህን ጽሁፍ ጽፌ ከጨረስኩ ወራት አልፈዋል፤ ከነገ ዛሬ እለቀዋለሁ እያልኩ አስረጀሁት መስሎኝ፣ በድረገጾች መልቀቁን ትቼው ነበር፣ እየጻፍኩት ላለሁት መጽሃፍ ግብዓት ለማድረግ ከመወሰን ጋር። (ከዚህ ማስታወሻ ጋር እንዲሄድ በማለት አንዳንድ ለውጥ ያደረግሁ ከመሆኑ በቀር እንዳለ ነው አሁን የለቀቅሁት)። ነገር ግን አሁን በ’ያን ሰሞን፣ ጋዜጠኛ አበበ፣ እርግማን አይሉት ምርቃን፣ … በአንዱ የኢሳት ገንዘብ ማሰባሰቢያ ላይ፣ በሟቹ መለስ ላይ ያደረግኸውን ለአለም የማጋለጥ ስራ አስመልክቶ፦ “… በሰው አይምሮ ልንፈታቸው የማንችላቸው ክስተቶች ይከሰታሉ… ተአምር ብለን እንጠራቸዋለን” ያልከው ትክክል አይመስለኝም። በዚህ ዩኒቨርስ ላይ ተአምር የሆነ ብዙም ነገር የለም፣ የቀን እና ለሊት መፈራረቅ ወዘተ… እንኳን ተአምር አይደለም፤ እንኳን ያንድ አዳራሽ ውስጥ ንግግር። አዳራሹ ውስጥ ከመናገርህ አንድ ወርም ሆነ ደቂቃ በፊት አስበህበታል። አካላዊ/ስሜታዊ ጉዳት አድርሰህበታል? በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ያደረስክበት ይመስለኛል፤ የሰውየው ቅጽበታዊ ስሜቱ እንዴት እንደነበር አይተናል። በፖለቲካው መስክ ለአለም የመለስን ማንነት የማጋለጡ ስራ ተሳክቶልሃል? ይኼም እውን ይመስለኛል–ቀጥታ ወጤቱ የሚለካበት መመዘኛ ባይኖርም “… ይህ ሰው [መለስ] በእግዚአብሄር እጅ ወደቀ… እኔ ነኝ የሚለው አምላክ ኢትዮጵያን ይበቀልላት…” ያልከው ግን …”አዲዎስ!” ጋዜጠኛነትህን ትልቅ ጥያቄ ውስጥ ይዶለው ይመስለኛል።  ለህወሃት የ”እድሜህን ያርዝምልን” endorsement ነው። …  ሟቹ መለስ በእግዜር እጅ አልወደቀም [ቢያንስ እንደ ጋዜጠኛ ስትታይ፤ እንደ ግለ-ሰብ ስትታይ ግን ይህ እምነት የራስህ እና የራስህ ብቻ ነው]። ምነው እግዜር አንድ ላይ ሁሉን አይጥልልን እስታሁን? ዳንግላ ወይም አሰላ ውስጥ ህክምና አጥቶ በሰላሳ አመቱ በኩላሊት ህመም የሞተ ወጣት እና ኖርዌይ ውስጥ በዲያሊሲስ ህመም በየቀኑ ከኩላሊቱ ደም እየተቀየረለት ሲታከም ኖሮ ኖሮ  በ99 አመቱ የሞተ በምዕራቡ አለም ያለ ሰው ሁለቱም እኩል እግዜር ስላዘዘ ነው’ንዴ የሞቱት? እንዲያ ያለ ፍትህ የማያውቅ እግዜር ካለ ያንን እግዜር ለማውገዝ የመጀመሪያው መሆን ያለብህ ይመስለኛል። እውነት ለመናገር፣ የክርስቲያን ክሮኒክል ጋዜጠኛ እንኳን እንዲህ አይነት “እግዜር ይበቀልላት” አይነት እርግማን እና/ወይም ምርቃን የሚያደርግ አይመስለኝም። ሃይማኖት የግል ነው። ጋዜጠኝነትም 100% ያልወገነ (“impartial”) እንደማይሆን ሲ.ኤን ኤን እና ፎክስን ማነጻጸር ይበቃል። ግን የሚያቆሙበት ጥግ/ገደብ አላቸው። በማናቸውም ሁኔታ፣ በማናቸውም የመገናኛ ብዙሃንን በተመለከተ በሚደረግ የስብሰባ ሁነትም ሆነ ሂደት፣ እንዲህ የሚመርቅ እና የሚራገም ጋዜጠኛ በአጼ ሚኒሊክ ጊዜ እንኳን የነበረ አይመስለኝም–የጋዜጣው ዋና አላማ ሃይማኖትን ማራመድ ካልሆነ በስተቀር። ኧረ በየሚዲያው “ከሞት የሚያድኑት” ያሰለቹን መራቂዎች እና ረጋሚዎች አሉን። በመጨረሻ፦ ህወሃት ሃይማኖት የሌለው ሃይማኖተኛ ህዝብ እያበጀልን ነው። የሚገርመው እነዚህ በመላው ኢትዮጵያ እንዲህ ተስፋፍተው ህዝብን “እያላስተማሩ” ያሉ ዘመናዊ ቀሳውስት እና ነብያት፣ ትግራይ ውስጥ የማይፈቀድላቸው መሆኑ ነው። ልክ እንደ ሲጋራ ጫት… ወዘተ። ባጭሩ ከሲጋራ፣ ጫት፣ ሃሺሽ እና መጠጥ ወጥመድ የተረፈውን ዜጋ፣ በ “ሃይማኖት” ውስጥ መክተት ነው። በጣም አስፈሪ ነው። የህወሃት መንግስት እንዴት እንዲህ ያለ ነገር በህጻናት እና በትውልድ ላይ እንዲሆን ይፈቅዳል? የሚል የጅል ጥያቄ ከመጠየቅ ይልቅ “ለምን ያስፈልገዋል?” ብሎ መጠየቅ መልሱን ቅርብ ያደርገው ይመስለኛል። እኔ የሚገርመኝ፣ ህወሃቶች ፍላጎታቸው ተሳክቶለታቸው የትግራይን ነጻነት አውጀው እንኳን ከቀሪው ኢትዮጵያ ቢገነጠሉ፣ እንዲያው በዚህ ብዛት እና ከህጻንነት ጀምሮ እንዲህ፣ “እያላስተማሩት” ያሉት ትውልድ (በተለይ ህጻናቱን እና ታዳጊዎቹን ማለቴ ነው፣ አዋቂውማ “ወደሽ ከተደፋሽ…” እንዲሉ ነው) ጎረቤት አድርጎ ጥሎ መሄድ ራሱ አያስፈራቸውምን? … በመጨረሻ… ጋዜጠኛ አበበ ሆይ! እኔ አንተን ብሆን ኖሮ፣ “ምንትስ ያህል ሰዎች በአጋዚ ተገደሉ” እና መሰል የኢሳት ዜናዎች ስር የሚኮለኮሉትን “ነፍስ ይማር”፣ “ነፍሳችሁን በገነት ያኑር”፣ “RIP” እና በየፌስ ቡኩ እንባ የሚያፈሱትን ሰዎች ብዛት እና አይነት ሌላም ዴታ ሰብስቤ ምንጩን እና መፍትሄውንም አጠና ነበር።…በተረፈ ለኢሳት ጉዳይ ስትመጣ…እባክህ እግዜርህን/አላህህን/የህዌይህን ቤትህ ውስጥ አስቀምጠህልን ምጣ!… አለዚያም ለሙያው ክብር እና ዲሲፕሊን ስትል የኢሳት ስራህን መልቀቅ ይኖርብህ ይመስለኛል…። ኢሳት የኢዲቶሪያል ፖሊሲውን ይመርምርልን።

[1] [ከዶ/ር ሰለሞን ይርጋ መጽሃፍ ላይ የተገኘ የ”ኢቮሉሽን” ትርጉም ነው]

መዝገቡ ሊበን (segelgazeta@gmail.com)


“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ። ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣአቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው።

Speak Your Mind

*