ህወሓት እንቅጩን ተናገረ!!

ሦስቱ ፓርቲዎችና አጋር ድርጅቶች አቋማቸውን ግልጽ አድርገዋል

ህወሃት “በሁሉም መለኪያዎች አንድ ፓርቲ ለመሆን የሚያስችል መነሻና ምክንያት በሌለበት ኢህአዴግን አፍርሶ ሌላ ፓርቲ ለማቋቋም ማሰብ አገርን የሚበትን ተግባር ነው” ሲል ጉዳዩ የሞት ሽረት መሆኑንን አስታውቋል። አሁን ግጭት እየተባባሰ የሄደውም በዚሁ ምክንያት ነው ሲል አክሏል።

እስከ ዛሬ ከውህደት ተገለው የነበሩ አጋር ድርጅቶች በኢህአዴግ ሥር ተጠቃለው እንዲቀጥሉ ምኞቱን ያኖረው ህወሃት፤ አጋር ፓርቲዎች ስለምን ተገለው እንደቆዩ ቁጭቱንም ሆነ ምክንያቱን በመግለጫው አላካተተም።

ሰሞኑንን አጋር ፓርቲዎች ሙሉ በሙሉ፣ ሶስቱ እህት ድርጅቶች ውህደቱን እንደሚደግፉና እንደሚቀላቀሉ ይፋ ማድረጋቸውን በድጋፍም ሆነ በነቀፌታ ያላስቀመጠው የህወሃት መግለጫ “ውህደቱ አገር ያፈራርሳል፣ ፍፁም ፀረ-ዴሞክራሲያዊ” ከማለት ውጪ እንዴትና በምን መልኩ አገር ልትፈርስ እንደምትችል አላብራራም።

በዛቻ የጀመረው የህወሃት መግለጫ አጋር ፓርቲዎች ውህደቱን እንዲቃወሙ “በህወሃት ስም እማጸናለሁ” ሲል ኢትዮጵያ እንዳትፈርስ መጨነቁን ይፋ አድርጓል። ጭንቀቱ ግን እሱ ያልተቀበለው ውህደት ተግባራዊ ከሆነ ብቻ እንደሆነ መጠቆሙ መግለጫውን ማስፈራሪያ እንዲሰኝ አድርጎታል።

ሟቹ የህወሃት መሪ በ97 ምርጫ ድርጅቱ መሸነፉን ተከትሎ ህዝብ ባነሳው ተቃውሞ ማግስት “ኢትዮጵያ እንደ ሶማሊያ ትበተናለች” በሚል ዛቻ ማሰማቱ፣ እነ በረከት ስምዖን ደግሞ የሩዋንዳውን የኢንተርሃምዌይ ጭፍጨፋ በቴሌቪዥን ማሳየታቸው ለሚያስታውሱ፤ ይህ ስልት የኖረ መሆኑንን የሚያረጋግጥ ነው።
ሰሞኑንን የእህት ድርጅቶችና የአጋር ድርጅት መሪዎች ጉዳዩን ያለቀ ሲሉ ለውህደቱ መዘጋጀታቸውን ይፋ ሲያደርጉ፣ የኢህአዴግ ጽ/ቤት በበኩሉ ህወሃት ውህደቱን የማይቀበለው ከሆነ ሌሎች ውህደቱን እንደሚያከናውኑ ይፋ አድርጓል።

ይህንኑ ተከትሎ ህወሃት ይፋ ካደረገው የማዕከላዊ ኮሚቴ ውሳኔ መግለጫ አስቀድሞ ህወሃት ግንባሩን የማይፈልግ ከሆነ ስለምን ጥሎ አይወጣም በሚል ጭንቀቱ ግራ እንደሚያጋባቸው በርካታ መሁራን ሲናገሩ ከርመዋል።

ህወሃት መንግስትና ፓርቲን በመቀላቀል ድርጅቶቹ ውህደት ከፈጸሙ አገር ለመምራት ኃላፊነት የተሰጠው ኢህአዴግ ስለሆነ መንግሥት ይፈርሳል ሲል የህግ ጥያቄ አመላክቷል። ይህን ያዩ አስተያየት ሰጪ “ዛሬም በጭንቅ ውስጥ ሆኖ ኢህአዴግ በህዝብ የተመረጠ መንግሥት ነው ሲል ይቀጥፋል” ብለው አሽሟጠዋል።

“አሃዳዊ መንግስት ሊቋቋም ነው” በሚል ማደናበሪያ ያልተባለውንና በዕቅድ ውስጥ የሌለ ሃሳብ ወልዶ ሲሰብክ የነበረው ህወሃት በመጨረሻው ሰዓት ብሄር ብሄረሰቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲንና የልብ ፓርቲያችሁ የሆነውን ህወሃትን ታደጉ የሚል ይዘት ያለው ጥሪ አስተላልፏል። መግለጫው የሚከተለው ነው

በውህደት ስም ኢህአዴግን አፍርሶ ሌላ ፓርቲ ለማቋቋም ማሰብ አገርን የሚበትን ተግባር ነው!!!

የህወሓት ማእላዊ ኮሚቴ በስፋት ካያቸው መሰረታዊ ጉዳዮች አንዱ በሀገራችን እየታየ ያለው ፈጣን አደጋና ወዲፊትም ሊኖረው የሚችል አጠቃላይ ሁኔታ የሚመለከት ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ ችግሮች እየተበራከቱ፣ ጥፋት በጥፋት ላይ እየተደራረበ፣ የጥፋቱ ስፋትና መጠን በየቀኑ እየጨመረ ወደ ከፋ አገር የመበተን ደረጀ እየደረሰ ነው፡፡ አደጋው ወደ ከፋ ደረጃ እንዲሄድ እያደረገ ያለው አንዱ ምክንያት የፓርቲ ውህደት ለመፈፀም እየተደረገ ያለው የችኮላ እንቅስቃሴ ነው፡፡ የፓርቲ ውህደት ጥያቄ በኢህአዴግ ውስጥ በተለያየ ጊዚያት እየተነሳ የቆየና ይህንን ለማድረግ ደግሞ ሊሟሉ የሚገባቸው መሰረታዊ ጉዳዮች እንዲታዩና በጥናት ላይ በመመስረት እንዲመለሱ መግባባት ላይ የተደረሰበት ጉዳይ ነው፡፡

ህወሓትም ቢሆን በመሰረተ ሃሳብ ደረጃ የተለየ እምነት አልነበረውም፡፡ ሆኖም ግን ይህን ለማድረግ በሁሉም መሰረታዊ የመስመር ጥያቄዎች፣ ፕሮግራም፣ ስትራቴጂ ወደ አንድ የሚያስተሳስር አመለካካተና እምነት በሁሉም እህት ድርጅቶች ሲፈጠር ብቻ ነው መተግበር የሚችለው፡፡ አንድ ሊያደርግ የሚችል የጋራ የአመለካከትና የተግባር አንድነት በሌለበት ወቅት አንድ ድርጅት እንደ ድርጅት መጠን ህልውና ሊኖረው አይችልም፡፡ ከውህደት በፊት የሚያዋሃህድ አመለካከትና እምነት መለየት አለብን፡፡ ኢህአዴግንና አገርን እየበተኑ ካሉት የተገዙ ደባል አመለካከቶች የሚለይ መስመር እና አጥር በጠራ መልኩ ሳይለይና ሳይቀመጥ ውህደትን ማሰብ አይቻልም፡፡ በደፈረሰ አመለካከትና በአንድነት ሊሰምሩ በማይችሉ እሳትንና ጭድ አስተሳሰቦችን በተሸከመ ኢህአዴግ አይደለም ውህደት ቀርቶ በግምባርነት ለመቀጠል የማይችል የተበተነ ድርጅት ነው አሁን ያለው፡፡ እንደዚህ ያለ የተበተነ ድርጅት ወደ አንድ ፓርቲ ውህደት ይመጣል ብሎ ማሰብ በራሱ ድርጅቱን ከመበተን አልፎ አገርን የሚበትን ተግባር ነው ሊሆን የሚችለው፡፡

ከዚህም አልፎ በቅርቡ ከግንባሩ እምነትና መተዳደሪያ ደንብ ውጭ የፓርቲ ውህደት ለመፈፀም እየተደረገ ያለው ሩጫ ችግሩ እንዲባባስ የሚያደርግ ፀረ-ዲሞክራሲያዊ አካሄድ እየሰፋ መምጣቱን የሚያሳይ ነው፡፡ የቅርፅ ውህደት ብቻ ሳይሆን በይዘትና በያዘው ፕሮግራሙ በመሰረቱ የተለወጠ አዲስ ፓርቲ ለመመስረት ነው ጥረት እየተደረገ ያለው፡፡ ይህ ሲሆን የኢትዮጵያ ህዝቦች ኢህአዴግ ለያዘው ፕሮግራም መሰረት አድርገው የሰጡት አገርን የመምራት ስልጣን ያከትማል ማለት ነው፡፡ አገርን ለመምራት ሓላፊነት ያልተሰጠው አዲስ ፓርቲ እንዲመሰረት ነው እየተደረገ ያለው፡፡ እንዲህ ያለ አዲስ ፓርቲ በሃገራችን ፖለቲካዊ ድርጅቶች የምዝገባ ህግ ያላለፈ፣ በህዝቦች ፈቃደኝነት በስልጣን ላይ ለመቆየትም ሆነ ስልጣን ለመያዝ ለመወዳደር የማይችል ህገ-ወጥ ድርጅት ነው የሚሆነው፡፡

በመሆኑም በውህደት ስም በፍፁም ፀረ-ዴሞክራሲያዊ መንገድ አዲስ አሃዳዊ ድርጅት ሊመሰረት አይገባም፡፡ በሁሉም መለኪያዎች አንድ ፓርቲ ለመሆን የሚያስችል መነሻና ምክንያት በሌለበት ኢህአዴግን አፍርሶ ሌላ ፓርቲ ለማቋቋም ማሰብ አገርን የሚበትን ተግባር ነው፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግ እንደ ግንባር ተደራጅቶ ችግሮችን በትግል እየፈታ አገር ሊመራ ይገባል፡፡ ከጊዜ አንፃርም ይህ ሊቆይ የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ አጋር ድርጅቶችም በውህደት ስም እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ህልውናችሁን የሚያጠፋ መሆኑን ልትገነዘቡ ይገባል፡፡ ይሁን እንጂ አጋር ድርጅቶች ወደ ኢህአዴግ በሙሉ አባልነት ገብታችሁ በጋራ ትግልና ጥረት አገርን የሚያድን ተግባር ልትፈፅሙ እንደሚገባ ህወሓት በፅናት ያምናል፡፡ ከዚህ ውጭ ህወሓት በእንደዚህ ያለ አገርን የሚበትን ተግባር ውስጥ ገብቶ ሊንቦጫረቅ እንደማይፈልግ ሊታወቅ ይገባል፡፡

መላው የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በውህደት ስም ኢህአዴግን ለማፍረስ የሚደረገው እንቅስቃሴ ሃላፊነት በተሞላበት ተገቢውን ትግል እንድታደርጉ ህወሓት ጥሪውን ያቀርብላችኋል፡፡

የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ ጥቅምት 2012 ዓ/ም ካወጣው መግለጫ የተወሰደ
ህወሃት ፌስቡክ ገጽ

ፎቶ፤ የህወሓት ነፍሰበላ የበረሃ ወንበዴ አዲስ አበባን በተቆጣጠረ ወቅት ሜክሲኮ አደባባይ ላይ አንድ ኢትዮጵዊን በጠራራ ፀሐይ ገድሎ፤ አደባባዩ ፈርሷል

ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ንብረት ናቸው።

Speak Your Mind

*