“የህወሓት ባለሥልጣናትንና አጋሮቻቸውን” መረጃ እየተረከክን ነው – ባለሙያዎቹ

ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብና የኢትዮጵያ ወዳጆች!

የኢትዮጵያን ሕዝብ በአፈና፣ ዝርፊያና ሰብዓዊ ጥሰት ሲገዛ በነበረው ህወሓት እና በሌሎች ጽንፈኛ ብሄረተኞች ትብብርና ቅንጅት የታየውን የለውጥ ተስፋና እየተካሄዱ ያሉ ለውጦችን ለማደናቀፍ በከፍተኛ ሁኔታ እንቅስቃሴ ላይ ይገኛሉ። እነዚህ ቡድኖች በገዥነት ዘመናቸው ከኢትዮጵያ ሕዝብ የዘረፉትን ሀብትና ንብረት በመጠቀም የተለያዩ ቡድኖችን በገንዘብ በመደለል አገርን ከማተራመስ በላይ ወደ ማፍረስ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን በበቂ ሁኔታ ተረድተናል።

በተለይም አሁን አገሪቱን እያስተዳደረ ያለው በጠ/ሚ/ር ዐቢይ የሚመራው ኢህአዴግ ሌሎች አጋር ፓርቲዎችን ጨምሮ በቅርቡ የሚያደርገው ውህደት ያልተዋጠላቸው የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ይኼን የውህደት እንቅስቃሴ በሚዲያ ፕሮፖጋንዳ ከማጣጣል ጀምሮ፣ የተለያዩ የትርምስ እና የሽብር እንቅስቃሴዎችን እስከ ባለስልጣናት ግድያ ድረስ ለማድረግ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑን ከሚያደርጓቸው የመልዕክት ልውውጥ ተረድተናል።

በመሆኑም እኛ በአሜሪካና አውሮፓ የምንገኝ በቁጥር 31 የምንሆን የሶፍትዌርና ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች የአገራችን መጻዒ ዕጣ ፈንታና ሁኔታ ስላሳሰበን አገሪቱን ወደ ሽብር እና ትርምስ ቀጠና ለመውሰድ እየተንቀሳቀሱ ያሉ የህወሓት ባለሥልጣናትን እና አጋሮቻቸውን የኢሜይልና የሶሻል ሚዲያ አድራሻዎች በመስበር ሤራዎቻቸውን ለሕዝብ በማጋለጥ ላይ መሆናችንን የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲያውቅልን እንፈልጋለን።

የአገራችን ወቅታዊ ሁኔታና መጻዒ ዕድል ያሳሰበን ሰዎች ለሕዝባችን በምንችለው አቅማችን የምናደርገው የሙያ ድጋፍ የትኛውንም የፖለቲካ ድርጅት አልያም ንቅናቄ በመደገፍ ሳይሆን አገራችንን ወደ ትርምስና ሽብር ለመውሰድ እየተንቀሳቀሱ ያሉ ቡድኖችን ሤራ በማክሸፍ ሕዝባችንን ለመታደግ እንደሆነ እንዲታወቅልንና የምናወጣቸውን መረጃዎች ሕዝብ በንቃት እንዲከታተል እናሳስባለን።

ድል ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ!
በአሜሪካና አውሮፓ የምንገኝ 31 የሶፍትዌርና ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች

Comments

  1. ለኢትዮጵያ ከመቸዉም ጊዜ የልጆቿን ትብብርና አንድነት ያስፈልጋታል ።

Speak Your Mind

*