የሕይወት ዋጋ – “አጥንታቸውን እሾህ ያርገው”

በ2009 ዓ.ም. ቆሼ የሚባል ሰፈር ወይም መንደር ተፈጠረ፤ ቆሼ ማለት ቆሻሻን ማቆላመጫ ነው፤ ቆሻሽዬ ማለት ነው፤ ቆሼ የቆሻሻ ተራራ ነው፤ በዚያ የቆሻሻ ተራራ ዙሪያ መሄጃ የሌላቸው ሰፈሩበት፤ ጥንት ሴትዮዋ እንዳለችው፡-

እሾህ ብቻ ሆነ እግሬን ብዳብሰው
እንዴት መራመጃ መሄጃ ያጣል ሰው!

ሴትዮዋ ይህንን ያንጎራጎረችው ከብዙ ትውልዶች በፊት ነው፤ ጉልበተኞች የኢትዮጵያን ሰዓት ሰንገው ስለያዙት አይነቀነቅም! ባለህበት ሂድ! ነው፤ ዛሬም መሄጃ የለም፤ ቆሻሻንም የሙጢኝ ቢሉ ማምለጥ አይቻልም፡፡

እነዚህ አንድ መቶ አሥራ ሦስት ሟቾች በርግጥ ሰዎች ናቸው? በርግጥ ኢትዮጵያን ናቸው? የምናገረው ጠፍቶኛልና ጥያቄዎች ብቻ ልጠይቅ፡– ቤታቸውን ጉልበተኞች አፍርሰውባቸው፣ መሬታቸውን ሰማይ-ጠቀስ ወይም መንገድ ለመሥራት መሬታቸውን ወስደውባቸው የሚደርሱበት አጥተው፣ ባዶ ቦታ ፈልገው የፕላስቲክ መጠለያቸውን እየሠሩ ግፍን አሜን ብለው በሰላም ተቀብለው ኑሮ ካሉት መቃብር ይሞቃል እያሉ ቀኖችን ሲቆጥሩ ቆሻሻ መጣያው ደባል የሆነባቸው መቼ ነው? ወይስ ቆሻሻ መጣያው ቀድሞ እነሱ ደባል ሆነውት ነው? ጥያቄው ማን ቀደመ ሳይሆን ቆሻሻውና መጠለያ ፈላጊዎቹ አብረው አንዲኖሩ ፈቃድ የሰጣቸው ማን ነው የሚል ነው? የመጠለያ ፈላጊዎቹን ቤት ያፈረሰውና የቆሻሻውን ተራራ የሚክበው ጉልበተኛ ወይም ጉልበተኞች የተለያዩ ናቸው? ወይስ አንድ ነው? አንድ ከሆነ እውር-ደንቆሮ ሳይሆን አይቀርም፤ በማን-አለብኝነት ልባቸው ያበጠ ግዴለሾች ሳይሆኑ አይቀርም፡፡

አንድ መቶ አሥራ ሦስቱና ሌሎቹም ዜጎች ቢሆኑ፣ ማለት የአገሩን ባለቤትነት ከጉልበተኞች ጋር በእኩልነት የሚጋሩ ቢሆኑ፣ ሌሎች ዜጎች እነዚህ በቆሻሻ የተበሉት ወገኖቻቸው መሆናቸውን ቢገነዘቡ ቆሻሻና ዜግነት እንደተደባለቁ ማወቃቸው ይቀራል? ዋናው ችግራችንስ ይኸው ሳይሆን ይቀራል?

የሞቱትን ነፍሳቸውን ይማር ማለቱ አጉል ወግ ነው፤ አጥንታቸውን እሾህ ያርገው ማለቱ ሳይሻል አይቀርም!

(ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም)

Comments

 1. dergu temelese says:

  ለወዝቶ አደሮች
  ከአመዳሞች
  ይብላኝ ለእናንተ ምርጥ ለምትበሉት፣
  ይብላኝ ለእናንተ ውስኪ ለምትቀዱት፣
  በአምስት አስራ እንድ በቁምሳ ስሌት፣
  እኛማ እያለቅን በርሀብ እርዛት፣
  በህይወት ከመኖር ይሻለናል ሞት፡፡
  ቁርስ ለንደን በልታችሁ ምሳችሁ ናይሮቢ፣
  እራት አዲስ- አባ በሼራተን ግቢ፣
  ዓለምን ስትቀጩ ብርን ስትገድቡ፣
  ለእኛ ጥፋት እንጂ ልማት አታስቡ፡፡
  ወስኪ ጠጥታችሁ በቀል ስታገሱ፣
  የድሀውን ድርሻ ስታግበሰብሱ፣
  ሞትን ስትሸሹ ምስኪኑን ስትገድሉ፣
  ያጣ ወንድማችሁን በጥይት ስትቆሉ፣
  የህግ እስረኛውን በእሳት ስትቀቅሉ፣
  ዝም ብሎ ሲያይ አይኖር ፈጣሪ ሀያሉ፣
  የዘራችሀትን እናንተም ታጭዳላችሁ፣
  አምላክ ዕድሜ ሰጥቶን ለማየት ያብቃችሁ፡፡
  በአቅላችሁ ሆናችሁ በደሉን አስታውሱ፣
  ድሀ ከመረረው አይሳሳም ለነፍሱ፣
  ምኑ ሊቀርበት የምድሩ ህይወት፣
  ተቆራምዶ አይኖርም ለእናንተ መውዛት፡፡

 2. Prof.Mesfin W/Marian!!! Don’t blame the government!!! They were not pushed to do so!!! They went to the garbage areas!!! Garbage is garbage!!! They went to scavenge garbage!!! To sale garbage!!! It is thrown as a garbage!!! They collect garbage??? They are koshashas!!! Koshasha took them!!! They burried in Koshasha!!!

  • Editor says:

   Mulugeta Andargie

   ማንነትህ እንዲታወቅ ነው “አስተያየት” ብለህ የጻፍከውን ያወጣንልህ። ራስህ በጻፍከው አስተያየት (comment) “ቆሻሻ” ማን እንደሆነ ያውም ደግሞ እጅግ የከፋውና መድኃኒቱ አስቸጋሪ የሆነው የዓዕምሮ “ቆሻሻ”ነት ባለቤት ማን እንደሆነ በሰጠኸው አስተያየት ስለመሰከርህ ይህ አደባባይ ወጥቶ መታወቅ ያስፈልገዋልና አትመነዋል። ብዙ ጊዜ ለአስተያየቶች ምላሽ አንሰጥም። ይህንን ግን ማለፍ አንተ ቆሻሻ ያልካቸው ሟቾች “አጥንታቸው እሾህ” ሆኖ ስለሚወጋን ማለፍ አቻልንም። እንዲሁም ስለራሱ መሟገት የማይችልና በህይወት የሌለን ሰው እንዲህ ባለ ቃል ከመናገር ያለፈ ቆሻሻነት የለም።

   የጎልጉል አርታኢ

Speak Your Mind

*