የኢትዮጵያ አርበኞች ውለታና የባንዳዎች ዕዳ!

ረዥሙ የኢትዮጵያ ታሪክ ከነፍጥ፤ ከሞፈርና ከመስቀል ጋር ተዛማጅነቱ ፍፁም ነው ማለት ይቻላል፡፡ ለዚህ ይመስላል አባ ዳኘው (ዳግማዊ አጤ ምኒልክ) የአድዋ ጦርነት  ዘመቻ ዝግጅት ላይ “… ሀገር የሚያጠፋ፤ ሃይማኖት የሚለዉጥ ጠላት…” መጥቷልና ከርስትህና ከሚስትህ ሳትነቀል የሚል ይዘት ያለው አዋጅ በወቅቱ እንዲነገር ያደረጉት፡፡  በጊዜ ሂደት ሀገሪቱ ከታሪኳ መድረክ “መስቀል”ን ገለል ብታደርግም ነፍጥና ሞፈር (ርስት) የአገሪቱ ህያው አምሳያ የታሪክ አካል ሆነዉ ቀጥለዋል፡፡ ወራሪ ኃይል በመጣ ቁጥርም እነዚህ የአገሬው ማታገያ አብይ አጀንዳዎች ሆነው ሲነሱ ኖረዋል፡፡

የነጮቹ ቅርጫ የሆነችው አፍሪካ በቅኝ ግዛት ክፉ ዕጣ ውልቅልቋ ሲወጣ፤ ኢትዮጵያ አድዋ ላይ በጀግኖች አባቶቻችን ተጋድሎ ሉአላዊነቷን ማስከበር ችላ ነበር፡፡ ፋሺስት ጣሊያንም ሽንፈቷን በእልህና በቁጭት ለመቀበል አርባ ዓመት መጠበቅ ነበረባት፡፡ በአንፃሩ ኢትዮጵያ በቀድሞ ድሏ እየተኩራራች ይህ ነው የሚባል አቅም ሳትገነባ አራት አስርታት ዓመት ተሻገረች፡፡ ያውም እንደ “ሰገሌ”፤ “አንቼም” ባሉ ትልልቅ የርስ በርስ ጦርነቶችና በሥልጣን ሽኩችዎች እየታመሰች ዘመን ተሻጋሪ ጠላቷን ጣሊያንን ዘንግታ፡፡

የፋሺስት መሪ ሙሶሊኒ ኢትዮጵያን ለመውረር የወሰነበትን ወቅት ይህ ነው ብሎ በሙሉ መተማመኝ መናገር ቢያዳግትም ከ1924 በኋላ እንደሆነ ብዙዎቹ የታሪክ ፀሐፊዎች ይስማማሉ፡፡ ሙሶሊኒ በአውሮፓ መድረክ ይከተል የነበረው የመስፋፋት ፖሊስ ከከሸፈበት በኋላ ፊቱን ወደ ኢትዮጵያ ማዞር ግድ ሳይሆንበት እንዳልቀረ የታሪክ ፀሐፍቱ ይስማማሉ፡፡ በህዳር 26/1927 ዓ.ም የተከሰተው የወልወል ግጭት ባንድ መልኩ ኢትዮጵያ ካጎራባች ቅኝ ግዛቶች ጋር ያሏት በቅጡ ያልተከለሉ ድንበሮች ውጤት ነው፡፡ (በይበልጥ ፓንክረስትንና ባህሩ ዘውዴን ያጤኗል)

ከወልወል ግጭት በኋላ መስከረም 22/1928 ዓ.ም የጣሊያን ጦር የመረብ ወንዝን ተሻግሮ በሦስት መስመር በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት ከፍተ፡፡ የጥቃቱ አንዱ ዓላማ ከአርባ ዓመት በፊት የሃፍረት ማቅ የተከናነበበት አድዋ ነበረች፡፡ ሁለቱ ሌሎች የጥቃቱ ዓላማዎች “እንጢቾ” እና “አዲግራት” ነበሩ (በይበልጥ ዘውዴ ረታን፣ ባህሩ ዘውዴንና ፓርክረስትን ያጤኗል)

በወቅቱ የምስራቅ ትግራይ ገዥ የነበሩት ደጀዛማች ኃይለ ሥላሴ ጉግሳ በግንባር ቀደምነት ለፋሽስት ጣሊያን ጦር ከነ ሰራዊታቸው አደሩ (ባንዳ ሆኑ)፡፡ የኢትዮጵያ የሰሜን ጦር በሦስት ረድፍ የተሰለፈ ነበር፡፡ በስተምዕራብ በራስ እምሩ ኃይለሥላሴ የሚመራው የጎጃምና የበጌምድር ጦር በስተምስራቅ፣ በጦር ሚኒስትሩ በራስ ሙሉጌታ ይገዙ የሚመራው የንጉስ ነገስቱ ጦር፤ በመሀል ደግሞ በራስ ሥዩም መንገሻና በራስ ካሳ ኃይሉ የሚመራ ጦር ነበር፡፡ በዚህ የኃይል አሰላላፍ ለጊዜውም ቢሆን የኢትዮጵያ ጦር ሽንፈትን መቀበል ዕጣዉ ሆነ፡፡

በተለምዶ የማይጨው ጦርነት የሚባለው የ1928ቱ ጦርነት በሽንፈት ለመደምደሙ የፋሽስት ጣሊያን የኃይል አሰላለፍና ወታደራዊ አቅም ከኢትዮጵያ የተሻለ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን በሰሜን ኢትዮጵያ የነበሩ የትግራይ መሳፍንቶች ከነጦር ሠራዊታቸው ለፋሽስቱ ጣሊያን በማዳራቸው እንደሆነ ብዙ የተባለለት ጉዳይ ነው፡፡

በሰሜኑ ግንባር የመጨረሻ ጦርነት የሆነው የማይጨው ጦርነት መጋቢት 24/1928 በሽንፈት ከተደመደመ በኋላ የፋሽስቱ ጦር አዲስ አበባ ለመግባት አርባ ቀናት ያህል እንኳን አልወስደበትም ንጉሠ ነገሥቱ ሚያዚያ 24/1928 ዓ.ም አገር ጥለዉ ሲሰደዱ ጣሊያን ሚያዚያ 27/ 1928 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ ገባ፡፡

ጣሊያኖች የምስራቅ ትግራይን ገዥ ደጃች ኃይለሥላሴን በገንዘብ በገዙበት አኳኋን አንዳንድ ባላባቶችን ከየጁና ከአዘቦ አካባቢ ለማባበል ሞክረዋል፡፡ ይልቁንም እነዚህ ጥቂት ባላባቶች ከጦር ሚኒስትሩ ከራስ ሙሉጌታ ጋር በነበራቸው ቅራኔ ምክንያት አንዳንዶቹ ለፈሽስቱ ጦር ማበር ያዙ፡፡ የቅራኔው ምክንያት “ራስ ሙሉጌታ ቆቦንና አዘቦን አቃጠሉ፤ ሕዝቡን ዘረፉት” በሚል ነበር እንደ የታሪክ መጻሐፍት ይገልፃሉ፡፡ ራስ ሙሉጌታ የራያን፤ የየጁንና የአዘቦን ተወላጅ በውጊው ግንባር ከመሰለፍና ከሞት አንዱን እንዲይዙ ምርጫ ሰጥተዋቸው ነበር ባላባቶቹ ግን ለጣሊያን ማዳርን ምርጫቸው አደረጉ፡፡

የሰሜን ኢትዮጵያ ትግራዋይ ባላባቶች ለጣሊያን ማደርና መተባባር ለፋሽስቶች በፍጥነት ወደ አዲስ አበባ መገስገስና ለአምስት ዓመት ቆይታቸው እገዛ አድርጎላቸዋል፡፡ በወቅቱ  ትግራዋይ ባንዶች በርከት ያሉ ነበር በሚል እንጅ ለባዕድ አገዛዝ ያደሩ ሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢ ተወላጆችም ይገኙ ነበር፡፡ በአንፃሩ ከትግራይ እንደ ራስ መስፍን ረዳ ያለ ጠንካራ አርበኛ እንደነበር መዘንጋት የተገባ አይደለም፡፡ ጎጃም ላይ ዝነኛዉ አርበኛ በላይ ዘለቀና መሰሎቹ በየአዉደ ዉጊያዉ እንዳልተሰለፉ ራስ ኃይሉ ተክለሃይማኖት በተቃራኒዉ ተሰልፈው እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም፡፡ በአምስት ዓመቱ የፋሽስት ጣሊያን ወረራ ወቅት ለባዕድ አገዛዝ አድረው (ባንዳ ሆነው) ከጣሊያን መንግስት ደመወዝ ተቀባዮች የነበሩ መሳፍንቶችና መኳንንቶች ከዚህ እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

ስም ደመወዝ
ራስ ኃይሉ 40,874
ራስ ስዩም 22,900
ራስ ጉግሳ 25,000
ራስ ጌታቸው 7,000
የአውሳሉ መሀመድ አንፋሪ 15,000
ሱልጣን አብዱላሂ አባጅፋር 8,000
ሱልጣን አባጆቢር አብዱላ 8,000
ደጃዝማች ሆሳዕና ጆቴ 15,000
ደጃዝማች ዮሓንስ ጆቴ 15,000
ሼክ ኤል ሆጄሌ 25,000
ደጃዝማች ታየ 1000
ራስ እምሩ 1000
ደጃዝማች አያሌው ብሩ 16000

ምንጭ፡- Alberto  sbacchi (57) (መስፍን ወ.ማሪያም፤ አዳፍኔ ገጽ 152)

ፋሺስት ጣሊያን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጋር የነበራቸው ግንኙነት ጥሩ ሊሆን ስላልቻለ ፓትሪያርኩ አቡነ ቄርሎስ ወደ ሀገራችው ወደ ግብጽ ተመለሱ፡፡ ፋሺስቶች ክርስቲያኑንና እስላሙን ለማጋጨት በነበራችው ፍላጎት የእስልምና ጠባቂና አስፋፊ ነን ማለት ያዙ፡፡ በዚህ ሁኔታ ጥቂት ሰዎችን ብቻ ሲያታልሉ፤ አብዛኛው የእስልምና እምነት ተከታይ ኢትዮጵያዊ በተንኮላቸው መረብ ውስጥ አልገባላቸውም፡፡ ይልቁንም የሃይማኖት አባቶች በጣሊያን ላይ የነበራቸው አቋም እየጠናከረና እየመረረ   ሄደ፡፡ እንደ ብጹዑ አቡነ ጴጥሮስ ያሉት ታላላቅ የሃይማኖት መሪዎች እንደ ደጀዝማች ዑመረ ሰመተር ያሉ ጀግኖች ሰማዕትነትን የተቀበሉት በአምስት ዓመቱ የጨለማ ዘመን ነበር፡፡

ጣሊያኖች በኢትዮጵያ ውስጥ በቆዩባቸው አምስት ዓመታት የፍዳና የጭንቅ ዘመናት ለፓስታሹታ ለማክሮኒ ለፉርኖና ለመሳሰለው ዕለታዊ ጥቅም የወገኖቻቸውንና አርበኞቻችን እንቅስቃሴ እየተከታተሉ የሚጠቁሙና የሚያሳስሩ የሚያስገድሉ ባንዶች ነበሩ፡፡ ከአንዳንድ ከሶላቶዎች ጋር የወሲብ ግንኙነት የፈጠሩ ሴቶች፤ ባሎቻቸውን ሳይቀር አጋልጠው ለመከራ የዳረጉ፤ የቀበሩትን የጦር መሣሪያ እያስቆፈሩ ለጠላት የሰጡ፤ የትዳር ጓደኞቻቸውን ያሳሰሩ ነበሩ፡፡ ጎረቤቶቻቸውን፣ አበልጆቻቸውን ወዘተ በማስያዝ ሽልማት፣ ጉርሻና ደርጎ ሲቀበሉ የነበሩ አልታጡም፡፡ የራስ ካሣ ሦስት ልጆችና የ80 ዓመቱ አዛውንት ደጃች ባልቻ መስዋዕት የሆኑት፤ የደብረ ሊባኖስ መነኮሳት እንደችቦ የነደዱት በዚህ መልክ ነበር፡፡

ግራዚያኒ በወቅቱ በነበሩት ፊውዳል መኳንንትና መሳፍንት ለመቀጠቀም የፈለገው አገሪቱ ውስጥ በእነሱ ተጽዕኖና ርዳታ በደንብ ሰርጎ ለመግባት እንዲመቸው ነበር፡፡ በዚህ መካከል እንዳንዳቹ መሳፍንትና መኳንንት ባንዳዎች በአፄ  ኃይለ ሥላሴ ዘመን ያጡትን ስልጣንና ገናናነት ፋሽሲቱ የጣሊያን መንግስት እንደሚሰጣቸው ገምተው ነበር፡፡ ቀዳሚ ተስፈኞችም የትግራይ መሳፍንቶች ደጃች ኃይለ ሥላሴ ጉግሳና ራስ ሥዮም መንገሻ ቀደም ከነበራቸዉ ማዕረግ ይበልጥ ከፍ የማለትና የንግሥናውን ቦታ የመቆናጠጥ ምኞት ነበራቸው፡፡ የጎጃሙ ራስ ኃይሉ ተክለሃማኖትም አይረሴው ባንዳ ነበሩ፡፡

በአንጻሩ የኢትዮጵያ አርበኞች ውለታ ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም፡፡ በማይጨው፣ በሽሬ፤ በተምቤን… ጦርነት ላይ የዋሉትን በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ አርበኞችን እንኳን ብንተው ጣሊያኖች ከማይጨው ጦርነት በኋላ ወደ መሐል አገር እንደተንቀሳቀሱ “ዱር ቤቴ” ብለው ህዝባዊ ሠራዊት እያስከተሉ የሸፈቱ በርካታ ወገኖች ነበሩ፡፡ ከትግራይ ብቸኛው ፊታውራሪ መስፍን ረዳ፤ ከበጌምድርና አካባቢው ራስ ውብነህ ተሰማና ቢትውደድ አዳነ፤ ከጎጃም ቢትወደድ መንገሻ ጀምበሬ፣ በላይ ዘለቀና ራስ ኃይሉ በለው፤ከሸዋ ራስ አበበ አረጋይ፣ መስፍን ስለሺ ፀሐይ ዕንቁሥላሴ፤ የበሼ ቤተሰቦች ደጃች ተሾመና አበበ  ሽንቁጥ፤ ከደቡብና ምዕራብ እነራስ ደስታ ደምጠው፣ ገረሱ ዱኪ፣ መኮንን ደመሰው፤ ከወሎ እነ ኃይሉ ከበደ፣ ወሰን ኃይሉ፣ ከሐረርጌ እነ ደጃች ዑመረ ሰመተር …. ወዘተ ህልቆ መሳፍርት የሌላቸዉ ጀግና አርበኞችን እያስተባበሩ ጠላትን እንደ ንፍፊት ወጥረውት ቆዩ፡፡ በተለይም በኢትዮጵያ ውድ ልጆች የካቲት 12/1929 ዓ.ም በማርሻል ግራዚኒያ ላይ የቦምብ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ የፋሽስቱ ጭካኔ እየበረታ በመሄዱ የአርበኝነት ተጋድሎም እየተቀጣጠለ  እስከ ድል ጫፍ  ድረስ ቀጠለ፡፡

በአምስት ዓመቱ የአርበኝነት ተጋድሎ ወቅት የ“ጥቁር አንበሳ” አርበኞች ኅብረት የበረታ ትግል የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ በየጊዜው የተነሱባት የውጪ ወራሪ ኃይሎች በህዝብ የተባበረ ክንድ ድባቅ መምታት ችላላች፡፡ የኢትዮጵያ አርበኞች ውለታ ከድል በኋላ በነበሩ ጊዜያት በቅጡ የታሰበና የተከበረ ነበረ/ነው ለማለት ግን አያስደፍርም፡፡

በተለይም አፄ ኃይለ ሥላሴ ከስደት ከተመለሱ በኋላ በዘረጉት የአስተዳደር መዋቅር ግንባር ቀደም አርበኞችን በማግለል ብሎም በማሰርና በመቅጣት በወረራ ጊዜ ለባዕድ አገዛዝ ታዛዥ የነበሩ ባዶችን ወደ ስልጣን ከፍታ ሲስቡ ታይቷል፡፡ በ1937 ዓ.ም  በላይ ዘለቀን በስቅላት፤ በ1953 ራስ አበበ አረጋይን በመረሸን የግንባር ቀደሞችን አርበኞች አሻራ ከአስተዳደራዊ መዋቅራችው እየጠፉ የተጓዙት አፄ ኃይለ ሥላሴ የማታ ማታ መጨረሻቸው አላማረም፡፡

በርግጥ ኢትዮጵያ በአመዘኙ ታሪኳ ለደሙላትና ለቆሰሉላት ውለታ ስትመልስ አትታይም፡፡ ይልቁንስ ለባዕድ አገዛዝ ታማኝ የነበሩ ባንዶችን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ሁነት የኢትዮጵያ ታሪክ አንዱ ገጽታ  ነው፡፡ የአፄ ኃይሌ ሥላሴ የድህረ ነፃነት የሥልጣን ጉዞ የባንድነትን ከፍታ ይበልጥ ያሳያል፡፡ ባንድነት የኢትዮጵያ ህልውና የሚፈታተን ሀገራዊ በሽታ እንደነበርም አይዘነጋም፡፡

በርግጥ ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም እንደሚሉት በየጦር ሜዳው ላይ ያለቀባሪ የቀሩት፣ ጅብና አሞራ የበላቸው የኢትዮጵያ ጀግኖች ድምጽ ተራሮችን እያርበደበደ ወንዞችዋን እያስጋለበ “ብድር መልሱ! ዕዳ ክፈሉ!” እያለ ያስተጋባል፡፡ እነዚህ የኢትዮጵያ ጅግኖች ለኢትዮጵያ አፈር ማዳበሪያ ሆነው በመሞታቸው ሲመግቡን ቆይተዋል፤ በሕይወታቸው ክብርና ኩራት በመሞታቸውም ሕይወት የለገሱንን የአባቶቻችንንና የአናቶቻችንን ድምጽ ማድመጥና ከመንፈሳቸው ጋር መታረቅ አለብን!!

በየዓመቱ ሚያዝያ 27 የሚከበረው የድል ቀን በኢትዮጵያ የቀን መቁጣሪያ (ካሌንደር) ላይ ሥራ ተዘግቶ እንዲከበር ቢደረግም ትውልዱ የቀደሙ እናትና አባቶቹን የተጋድሎ ታሪክ እንዲያወቅ የሚያስችል የበዓል አከባበር አይታይም፡፡ ዕለቱም እንደአንድ ተራ የረፍት ቀን ያልፋል፡፡ በአንጻሩ አንዳች አገራዊ ፋይዳ የሌላቸው የህወሃት፣ የብአዴን፣ የኦህዴድ፣ … የምሥረታ ቀን እየተባለ በብዙ ሚሊዮን ገንዘብ የሚወጣባቸው ለወራት በዕቅድ ተይዘው የሚደገሱ በዓላት በድምቀት እንዲከበሩ ይደረጋል፡፡

አዲስ አበባ አራት ኪሎ አደባባይ ላይ በሚገኘው የድል ኃውልት ላይ የአበባ ጉንጉን በማስቀመጥና በዕለታዊ የዜና ሽፋን የሚታለፈው ይሄው የድል በዓል፤ ትውልዱ የበዓሉን ፋይዳ በቅጡ እንዳይረዳው አድርጎታል፡፡ የፋሽስት ጣሊያን የአምስት ዓመቱ የወረራ  ዘመን በተነሳ ቁጥር የዛሬ ቁንጮ ገዥዎች (የሕወሓት አመራሮች) እንደዘዉጌ ብሄርተኝነታቸው የሚያፍሩበት እንጂ የሚኮሩበት ታሪክ እምብዛም ነው፡፡ ታሪክን በዜግነት ማዕቀፍ ሳይሆን በዘውጋዊ ማንነት ሽንሽኖ ማየት የሚቀላቸው የሕወሓት ሰዎች የኢትዮጵያዊያን የድል ቀን የሆነውን ሚያዝያ 27 በየዓመቱ በደበዘዘ መልኩ እንዲከበር ማድረግ መርጠዋል፡፡

የትግራይ መሳፍንቶች የእነ ደጃች ኃይለ ሥላሴ ጉግሳና ራስ ሥዩም መንገሻ መቼም የማይረሳ የባንዳነት ታሪክ ዕዳ ሆኖባቸው በዓሉን እንደ አንድ ተራ ዕለት ማለፍ ምርጫቸው ሆኗል፡፡ በእኛ በኩል እንደዜጋ የኢትዮጵያ አርበኞች ውለታ በቅጡ እንዳልተዘከረ ይሰማናል፡፡ የአምስት ዓመቱ የወረራ ዘመን በኢትዮጵያዊያን ላይ ያደረሰው የፖሊቲካ፤ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ተጽዕኖዎች በሚገባ እንዳልተዳሰሰም እናምናለን፡፡

የኢትዮጵያ አርበኞች የተጋድሎ ሚና የታሪክ ትምህርት (ሥርዓተ ትምህርት) አንዱ ክፍል እንዲሆን ማደረግ፤ አርበኞችን የሚዘክር ብሔራዊ ቤተመጻሕፍት ማቋቋም፣ የአርበኞች ማህበርን ከፖለቲካ ፍላጎት በፀዳ መልኩ ማጠናከር ወዘተ ተግባራትን በአገር አቀፍ ደረጃ በማከናወን ተተኪ ትውልድ መፍጠር ይቻላል፡፡ አገር ተረካቢ ትውልድ ለማፍራት ኃላፊነት የሚሰማው መንግስት ሊኖር ይገባል፡፡ ይሁንና “መንግስት”ነቱን የዘነጋ የቋሚ  ሽፍታና ወንበዴ ስብስብ የሆነው ህወሓት ሥልጣን ላይ አስካለ ድረስ የኢትዮጵያ አርበኞች ውለታ በተገቢ ሁኔታ ሊታወስም ሆነ ተተኪ ትውልድ ማፍራት የሚቻል አይደለም፡፡

ክብር ለኢትዮጵያ አርበኞች!!!


ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡

 

Comments

 1. ፋሺሽት ኢጣልያ በኢትዮጵያ ላይ ስለ ፈጸመችው የጦር ወንጀል ወቅታዊ የሆነ ጽሑፍ ማቅረባችሁ መልካም ነው። ሚዛናዊ በሆነ መንገድ፤ ባንድ በኩል፤ ለኢትዮጵያ ስለ ታገሉት ጀግኖቻችንና አርበኞች፤ በሌላ በኩል፤ ከፋሺሽቶቹ ጋር ስለ ወገኑት ባንዳዎች የቀረበው ሐተታም ጥልቀት ያለው አቀራረብ ነው። ነገር ግን ከዚህ በታች የተመለከቱት ነጥቦች የሚያሳስቡና መልሳችሁን የሚጠይቁ ናቸው፤
  1ኛ/ ራስ እምሩም እንደ ባንዳ ዝርዝሩ ውስጥ ተካተዋል። ይህ ፍጹም ሐሰት ነው። ማስረጃ የተባለው የሌለ ነው።
  2ኛ/ የሚያዚያ 27 የድል ቀን ሰሞኑን ሲከበርና በናንተም ጽሑፍ የሚያንጸባርቀው ያልተሟላ ውጤት የሚያንጸባርቅ ነው። ኢትዮጵያ የተሟላ ድል አገኘች ሊባል የሚቻለው ለተፈጸመባት የጦር ወንጀል ሁሉ ተገቢውን ፍትሕ ስታገኝ ብቻ ነው። ለመሆኑ፤ በቫቲካን የተደገፉት የኢጣልያን ፋሺሽቶች በኢትዮጵያ ላይ ምን ጉዳት አስከተሉ? ጥያቄውን በመጠኑ ለመመለስ ያህል ብቻ፤
  (ሀ) አንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ተጨፍጭፈዋል። ከነዚሁ ውስጥ የካቲት 12-14 ቀኖች 2029 ዓ/ም በሶስት ቀኖች ውስጥ 30፣000 ኢትዮጵያውያን እንደ ተገደሉ የታወቀ ነው። በተጨማሪም ከ2000 መነኮሳትና ምእመናን በላይ ደብረ ሊባኖስ ገዳም እንደ ተሰዉ የተረጋገጠ ጉዳይ ነው።
  (ለ) 2000 ቤተ ክርስቲያኖች፤ 525000 ቤቶችና 14 ሚሊዮን እንስሶች ወድመዋል።
  (ሐ) እጅግ ብዙ የኢትዮጵያ ንብረት ተዘርፏል። ከዚሁ ውስጥ፤ ባሁኑ ጊዜ፤ ከኢትዮጵያ በፋሺሽቶች የተዘረፉ
  ክ500 ታሪካዊ ሰነዶች በላይ በቫቲካን ቤተ መጻሕፍት እንደሚገኙ የታወቀ ነው።
  (መ) ብዙ ኢትዮጵያውያን በእስር፤ በስደትና በሌላም ልዩ ልዩ መንገድ ተሰቃይተዋል።
  3ኛ/ ከላይ ለተዘረዘሩት የጦር ወንጀሎች፤ ኢጣልያ እስካሁን ተገቢውን የፍትሕ ተግባር ሳታከናውን ትገኛለች። እንዲያውም፤ አበው “በእንቅርት ላይ ጆሮ ድገፍ” እንደሚሉት፤ ለኢትዮጵያ ጨፍጫፊው፤ ለሮዶልፎ ግራዚያኒ፤ በቅርቡ እንደ ጀግና መታሰቢያ ሠርተውለት፤ የቫቲካን ተወካይ በተገኙበት አፊሌ በምትባል የኢጣልያ ከተማ ተመርቆለታል።
  4ኛ/ ኢጣልያ እስካሁን የፈጸመችው ኢምንት ተግባር የአክሱም ኃውልትን መመለስና የቆቃ ግድብ ለተሠራበት 25 ሚሊዮን ዶላር የከፈለችው ብቻ ነው። ይኼ ታዲያ በምንም መስፈርት በቂ ነው ሊባል አይችልም!
  5ኛ/ በኢትዮጵያ ላይ ለተፈጸመባት አሰቃቂና ከባድ የጦር ወንጀል ለሐገሩ ሕዝብ በተጨባጭ መንገድ ሊጠቅም በሚችል መንገድ (ማለትም፤ ለሙስና በማይጋለጥ ዘዴ) ተገቢውን ፍትሕ እንድታገኝ ማድረግ የዜግነት ግዴታችን ነው። ይህንን ዓላማ በተመለከተ፤ የሌሎች ሐገሮችን ምሳሌ በመጠኑ ብንመለከት፤ ሊቢያ ለተፈጸመባት የ30000 ሰው እልቂት ከኢጣልያ መንግሥት 5 ቢሊዮን ዶላር ካሣ እንድታገኝ ተስማምተዋል። አርሚኒያ በቱርኮች ለተፈጸመባት የአንድ ሚሊዮን ሕዝብ እልቂት፤ 3 ትሪሊዮን ዶላር ጠይቃለች። ኬንያ በእንግሊዞች፤ ኢንዶኒዚያ በኔዘርላንድስ ለተፈጸሙባቸው ወንጀሎች ይቅርታ ተጠይቀው ካሣ እየተከፈሉ ነው። ኢትዮጵያስ? ለፍትሕ የሚታገሉላት ልጆች የሏትም?!
  6ኛ/ ለኢትዮጵያ ስለሚያሰፈልገው ፍትሕ ጥረት በማድረግ ላይ ለሚገኘው ለዓለም አቀፍ ሕብረት – የኢትዮጵያ ጉዳይ ድርጅት (Global Alliance for Justice – The Ethiopian Cause) (www.globalallianceforethiopia.org) ተገቢውን ድጋፍ ማበርክት በፍትሕ ለሚያምኑ ዜጎችና ወዳጆች ምርጫ የሌለው የሕሊና ግዴታ ነው።

  • ሰላም Wogene

   በቅድሚያ ጊዜ ወስደው ስለጻፉት አሰተያየት ከልብ እናመሰግናለን፡፡ ስለ ጎልጉልም የሰጡትን በአክብሮት ተቀብለናል፡፡
   ወዳነሱት ነጥቦችና ወደጠየቋቸው ጥያቄዎች ስንመለስ፤

   በተራ ቁጥር አንድ እና ሁለት ላይ ያነሱትን ጥያቄ ለመመለስና ከእኛ በኩል ያለንን አስተያየት ለመስጠት እንሞክራለን፡፡ እኛ እንዳስተዋልነው ሌሎቹ ማሳሰቢያዎችና ሌሎች እንዲውያቁት የዘረዘሩት ሃሳብ ስለሆነ በዚህ ላይ የምንለው አይኖርም፡፡

   1. የራስ እምሩን ጉዳይ በተመለከተ፤ “ራስ እምሩም እንደ ባንዳ ዝርዝሩ ውስጥ ተካተዋል። ይህ ፍጹም ሐሰት ነው። ማስረጃ የተባለው የሌለ ነው።” ብለዋል፡፡

   የራስ እምሩ ባንዳ ሆኖ የኢጣሊያ ደመወዝ ተከፋይ መሆን የጠቀስነው ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም ካሳተሙት “አዳፍኔ” መጽሐፍ ገጽ 152 ላይ መሆኑን ጽሁፉ ላይ አስፍረናል፡፡ ፕ/ር መስፍንም ከራሳቸው ያመጡት ሳይሆን ያገኙበትን ምንጭ እዚያው ላይ ጠቅሰዋል፡፡

   ራስ እምሩ በእነ ዶ/ር ዓለምወርቅ በየነ የተመሰረተዉን “ጥቁር አንበሳ” የአርበኞች ህብረት ተቀላቅለዉ በምዕራብ ኢትዮጵያ አካባቢ ሲዋጉ ነበር፡፡ በኋላም ወለጋ ላይ በጠላት እጅ ወድቀዉ ወደ ጣሊያን በግዞት ተላኩ፡፡ ከሀዲስ ዓለማየሁና ከግርማቸዉ ተክለሃዋርያት ጋር ጣሊያን ዉስጥ በ“ሊፓሪ” ደሴት በክሩሴደሮች በተሰራ የመካከለኛዉ ዘመን ቤተመንግሥት ዉስጥ ታስረዉ ቆዩ፤ በኋላም “ካላብሪያ” ወደተባለች ትንሽዬ መንደር ሦስቱንም ግዞተኞች ወስደዋቸው እዚያ በእስር ቆዩ፤ ጣሊያን ከኢትዮጵያ ሊለቅ አንድ አመት ሲቀረዉ ራስ እምሩ ወደ አገርቤት ተመልሰዉ ነበር፡፡ ይህ መረጃ ካልታተመው የግርማቸው ተክለሃዋሪያት ግለታሪክ ላይ የሚገኝ ነው፡፡

   ለማንኛውም ስለ ራስ እምሩ የረፈደ ባንዳነት ፕ/ር መስፍን የተሳሳተ መረጃ (ትርጉምም ቢሆንም እንኳ) በመጽሃፋቸው “አዳፍኔ” ላይ የሚያወጡ ሰዉ ናቸው ብለን አናምንም፡፡ እርሳቸው ብዙ ወደረኞች እንዳሏቸውና ስህተታቸውን ጠብቀዉ ሊያላግጡባቸው የሚቋምጡ ሰዎች እንዳሉ ራሳቸው ጠንቅቀው ያዉቃሉ፡፡ እንኳንስ መጽሃፍ ላይ የሚታተም መረጃ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ የሚለጥፉትን ደራሽ ሃሳባቸውን እንኳን ፈትለው ፈታትለው ለሥርዓተ ነጥብ እንኳ ተጨንቀው ነዉ የሚለጥፉት – ይህ የእኛ ትዝብት ነው፡፡ እርስዎ የግድ መቀበል የለብዎትም፡፡ ሆኖም “አዳፍኔ” ላይ የሰፈረው “በሌለ ማስረጃ ነው” የሚሉ ከሆነ እኛም ሆነ ሌሎች በፕ/ር መስፍን መጽሐፍ “ተታልለን” እንዳንቀር በእርስዎ በኩል ያለውን ማስረጃ አጣቅሰው አንድ መጽሐፍ ለኅትመት ቢያቀርቡ ለትምህርት ይሆናል ብለን እናምናለን – ወይም እዚህ ላይ የክርክር ሃሳብዎን ቢያሰፍሩ መልካም ነው፡፡

   2. “የሚያዚያ 27 የድል ቀን ሰሞኑን ሲከበርና በናንተም ጽሑፍ የሚያንጸባርቀው ያልተሟላ ውጤት የሚያንጸባርቅ ነው። ኢትዮጵያ የተሟላ ድል አገኘች ሊባል የሚቻለው ለተፈጸመባት የጦር ወንጀል ሁሉ ተገቢውን ፍትሕ ስታገኝ ብቻ ነው…” እያለ ስለቫቲካን የሚያነሳ ጉዳይ በተመለከተ፤

   በመሰረቱ ከሆነ ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ ይህንን ጽሁፍ ያወጣው እንደ አንድ የሚዲያ ውጤት የአርበኞችን ዉለታ አስቦ ለመዘከር ነው፡፡ ጎልጉል ከዚህ በላይ ማለትም ሕዝብን ከማሳወቅ በላይ ሊያደርግ የሚችለው ነገር የለም፡፡ በመሆኑም ዕለቱን ለመዘከር ያህል የአርበኞቹን ተጋድሎ በጨረፍታ ጠቃቀስን እንጂ ገድላቸው በድረገጽ ደረጃ በአንድ መጣጥፍ ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም፡፡ እርስዎም እንደሚያዉቁት የድረገጽ አንባቢ ገፋ ቦርቀቅ ያለ ጽሁፍ አይወድም፡፡ ፌስቡክ የሚባል መንደር የአንባቢዉን የንባብ ባህል ሰልቦታል፡፡ ጥቂት ልምዱ ያላቸዉ የድረገጽ አንባቢዎች ናቸዉ ታግሰዉ የሚያነቡት፡፡ ለዛ ነዉ በዝርዘር መግለጽ ያልተቻለዉ፡፡ ቢሆንም ግን አስተያየቱ ገንቢ በመሆኑ እንቀበላለን፡፡ በቀጣይም እናስተካክላለን፡፡

   ሌሎች የጠቀሷቸው ነጥቦች አስተያየቶች እኛም ሆንን ሌሎች አንባቢያን ዕውቀት እንዲኖረን ያሰፈሯቸው በመሆኑ እንዳሉ ትተናቸዋል፡፡

   በኢጣሊያ በወረራ ወቅት በኢትዮጵያ ላይ የደረሰውን መከራ፣ ሰቆቃ፣ ጉዳት እኛ የምንመለከተው በሌላ መነጽር ነው፡፡ እንዲያውም የማይጨው ወረራ በራሱ የአድዋ ሽንፈት የፈጠረው ብቻ አይደለም ብለን እናምናለን፡፡ ምክንያቱም አድዋንስ ምን ፈጠረው የሚለው ጥያቄ ምላሽ ያስፈልገዋልና፡፡ በመሆኑንም ጉዳዩ ወደ 16ኛው ክፍለዘመን ይወስደናል፡፡ ይህም በአውሮጳ የፕሮቴስታንት እምነት የመነሳት፣ የካቶሊክ እምነት የመዳከም፣ የፕሮቴስታንቱን ተሃድሶ ለመቃወም (Counter Reformation) በመሆንና የካቶሊክን እምነት እንዲያንሰራራ የተነሳው የኢየሱሳውያን (Jesuits) እንቅስቃሴ፤ በኢትዮጵያ ደግሞ በዚያው ዘመን አካባቢ የአህመድ ግራኝ ወረራ ወቅት የነበረውን ሁኔታ እንድናጠናና ለኢትዮጵያ ነገሥታት ከአውሮጳ የተሰጠውን ዕርዳታ እንድንመለከት ያስገድደናል፡፡ ከዚህ በኋላም ዓመታትን ቆጥሮ አጼ ሱስንዮስ የካቶሊክን ዕምነት መቀበላቸው፤ ሆኖም ዕምነቱ ከእርሳቸው በኋላ ይፋ የመንግሥት ወይም የኢትዮጵያ ሃይማኖት ሆኖ መቀጠል አለመቻሉ፤ ከዚህ ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ ኢየሱሳውያን (ጀዝዊትስ) ኢትዮጵያን ካቶሊካዊት አገር ለማድረግ የማሰባቸው ዕቅድ በተደጋጋሚ አለመሳካቱ፤ ለዚህም ታላቅ መስዋዕትነት መክፈላቸው፤ በ16ኛው ክፍለዘመን አጋማሽ ላይ የኢያሱሳውያን ጀማሪና መሪ (ጄኔራል) የነበረው ኢግናሺየስ ሎዮላ በወቅቱ ለነበሩት የኢትዮጵያ ንጉሥ ገላውዴዎስ “There is only one Catholic Church in the world and it can only be one under the Roman Pontiff and not under that of Alexandria” ብሎ ከጻፈው ደብዳቤ አንጻር ከአውሮጳ ይካሄድ የነበረው ግልጽ መንፈሣዊ ማባበያ፣ ጥቃትና ወረራ እና ከሌሎችም አንጻር መታየት ይገባዋል እንላለን፡፡ በተጨማሪም ከዚህ ሁሉ በፊት በ15ኛው ክፍለዘመን ውስጥ በቫቲካን አዝማችነት የተካሄደውና ለዓመታት የዘለቀው መንፈሣዊ “ወረራ” በኦርቶዶክስ ሃይማኖት ላይ ያስከተለው ከፍተኛ የእምነት ተጽዕኖ፤ በሃይማኖቱ ውስጥ የአስተምህሮ (ዶክትሪን) ለውጥ የመደረጉ ሁኔታ፣ የደቂቀ እስጢፋኖስና ሌሎች የእምነት አባቶች መስዋዕትነት፤ የአጼ ዘርዓ ያዕቆብ እንደ ንጉሥ በዚህ ውስጥ ያላቸው ተሳትፎና ተባባሪነት፣ … እጅግ በርካታ ጉዳዮች ከዚህ የቫቲካን ጥቃትና የኢጣሊያ ወረራ አንጻር መታየት ያለበት ይመስለናል፡፡ ምናልባትም ለዚህ ይሆናል የኢጣሊያ ወረራ በቫቲካን ቡራኬ የተፈጸመውና ኢትዮጵያ እስካሁን ለ“ይቅርታ”ና ካሣ ብቁ ያልሆነችው፡፡

   በመጨረሻም Global Alliance for Justice – The Ethiopian Cause የሚያወጣቸውን መግለጫዎችና የሚያዘጋጃቸውን ፕሮግራሞች አንባቢ እንዲያውቅ በየጊዜው ስናትም ቆይተናል፡፡ ከዚህ በላይ እንደ ሚዲያ ማድረግ የምንችል አይመስለንም፡፡ እየቻልን ሳናደርግ የቀረነው ካለ ያሳስቡንና ለመፈጸም የሚቻለንን እንሞክራለን፡፡

   በድጋሚ ለሰጡት አስተያየት ከልብ እናመሰግናለን፡፡

   የጎልጉል አርታኢ

 2. ይቅርታ፤ ከላይ ባቀረብኩት ሐተታ፤ 2029 የተባለው 1929 መባል ነበረበት።

 3. በፈረንጆች አቆጣጠር በ May 5, 2017 ዓም፤ “የኢትዮጵያ አርበኞች ውለታና የባንዳዎች ዕዳ” በሚል አርዕስት ጎልጉል ድህረ ገጹ ላይ ልዑል ራስ እምሩ ባንዳ ነበሩ ብላችሁ ጽፋችኋል:: ለዚህም መረጃ የምትሉት “አዳፍኔ” በሚባለው መጽሃፋቸው ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም፤ ልዑል ራስ እምሩ ኋይለሥላሴ በጦርነቱ ጊዜ ከኢጣሊያን መንግሥት በወር 1 ሺህ ሊራ ደምወዝ ይቀበሉ ነበር ብለው በመጻፋቸው ነው። እርሳቸውም ለዚህ አባባላቸው የመረጃ ምንጫቸው ብለው የሚጠቅሱት ፕሮፌሰር አልቤርቶ ስባቺን ነው::
  ይሄ ፈጽሞ ከእውነት የራቀ እና ትንሽም ቢሆን ላሰበበት ሰው ሊሆን የማይችል ነገር መሆኑ ግልጽ ሊሆንለት ይገባው ነበር። ምክኒያቱም ልዑል ራስ እምሩ በታህሳስ ወር 1929 ዓም ከተማረኩበት ቀን ጀምሮ እጣሊያን እራሷ ተሸንፋ በመስከረም 1936 ዓም እስክትማረከችበት ቀን ድረስ ካለማቋረጥ በኢጣሊያን ሀገር ውስጥ እስረኛ ነበሩ:: በዚህም በእሥር ቆይታቸው ዘመን ኢጣሊያንን በመደገፍ የተናገሩትም ሆነ ያደረጉት አንድም ነገር የለም:: ጎልጉልም ሆነ፤ ፕሮፌሰር መስፍን፤ እንዲሁም ሌላ ማንም ሰው፤ ማስረጃ አል የሚል ከሆነ ያቅርብ:: ባለመኖሩም ምክንያት ልታቀርቡ እንደማትችሉ እናውቃለን::
  ልዑል ራስ እምሩ እንደተማረኩ ኢጣሊያኖች ከጦር ሜዳ ወደ አዲስ አበባ ካመጡአቸው በኋላ ወደ ኢጣሊያን ሀገር ተወሰዱ:: በመጀመሪያ አደገኛ እስረኛ ናቸው በመባል ከእነ አቶ ሃዲስ አለማየሁ ጋራ ፖንዛ የምትባል ደሴት ላይ ከታሰሩ በሁዋላ አሁንም አላርፍ ስላሉ ለብቻቸው ታሰሩ:: ይህንንም ፕሮፌሶር አልቤርቶ ስባቺ በሌላ ጥናታዊ ጽሁፍ አትሞ ጽፏል:: በዚህም ጽሁፉ ኢጣሊያን ሀገር ውስጥ የነበሩ ባንዳዎችን በግልጽ ሲዘረዝር: በዝርዝሩ ራስ እምሩ የሉበትም:: እንዲያውም ፕሮፌሶር ስባቺ ስለ ራስ እምሩ ሲጽፉ እስረኛ መሆናቸውንና አደገኛ ተብለው ወደ ፖንዛና ሌላ ደሴቶች መዛወራቸውን ነው የጻፉት። ህትመቱም የሚከተለው ነው:: The International Journal of African Historical Studies, volume 10, number two (1977) pages 209-241, published by the Boston University African Studies Center. በኋላም እንደገና በዚሁ አመጸኝነታቸው የተነሳ፤ ከሌሎች እሥረኞች ተነጥለው ብቻቸውን ታሠሩ።
  ግን እስቲ ደግሞ በቦታው ያልነበሩትን ፈረንጆች ትተን በቦታው የነበሩትን ሥመ ጥሩ ኢትዮጵያውያን የአይን ምሥክሮች ስለ ራስ እምሩ ጀግንነትና ኢትዮጵያዊነት የተናገሩትን እንመልከት።
  አቶ ሀዲስ ከራስ እምሩ ጋራ ስለ ፖንዛ እሥራቸው ሲአስታውሱ በዚሁ “ትዝታ” በተሰየመው መጸሀፋቸው በገጽ 217 እስከ 219 የሚከተለውን ያነሳሉ። ፖንዛ ደሴት ላይ ከራስ እምሩና ሌሎች ጥቂት እስረኞች ጋራ በታሰሩበት ወቅት ለራስ እምሩ ከሙሶሊኒ መልእክት ይዞ አንድ ከፍተኛ የኢጣሊያን ባለሥልጣን (የቅኝ ግዛት አስተዳደር ሚኒስቴሩ ይመስለኛል) ማሰሪያ ሥፍራ ድረስ መምጣቱን አቶ ሀዲስ ይናገራሉ። ልዑካኑ መልዕክቱን ለማድረስ ራስ እማሩ፤ አቶ ሀዲስና ሌሎች እሥረኞች የነበሩበት ከፍል ከኮሚሽ ነሩጋራ ሲገባ ራስ እምሩ ተቀምጠው ነበር። ለኢጣሊያኖቹ መቀመጫ ወንበር በቂ ስላልነበር አቶ ሀዲስ ወንበር ሊአመጡ ብድግ ሲሉ ራስ እምሩ ቀና ብለው “ሀዲስ ወንበር ለማምጣት እንደሆነ የምትሄደው አያስፈልግም ስላሉኝ መለስ አልኩ። ከዚያ እንዲያ ራስ ተቀምጠው ሁለቱ ሹማምንት [ኢጣሊያኖቹ] ቆመው በዝምታ ትንሽ ተፋጠው ከቆዩ በሁዋላ” ልኡካኑም እንደቆመ ራስ እምሩን ኢጣሊያንን ከተቀበሉ ምህረት ተደርጎላቸው ቤት ንብረታቸው ተመልሶላቸው ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመለሱ ከሙሶሊኒ የመጣ መልዓክት አስተላለፈ። ራስ እምሩም አልፈልግም ሀገሬ ነጻ ስትወጣ ሁሉም ይመለስልኛል ከእናንተ አልፈልግም ብለው መለሱለት።

  በዚህም ዓመጸኝነታቸውና የአመጽ አመራራቸው ነው ከሌሎች እሥረኞች ተለይተው የታሠሩትና ከዚያም ወደ ሊፓሪና ሎንጎቡኮ ወደ ሚባሉ ደሴቶች ለብቻቸው የተዛወሩት።

  ስለ ደምወዝ ጉዳይ እናውራ ከተባለ፤ ልዑል ራስ እምሩ እስረኛ እንደመሆናቸው መጠን ደምወዝ ሊኖራቸው አይችልም:: በየት ሀገር ነው እሥረኛ ደመወዝ የሚከፈለው? ነገር ግን ለቀለባቸው፤ እንዳያመልጡ ለሚጠብቋቸው ወታደሮችና ዘበኞች ለመሳሰሉ ወጪዎች በእርግጥ የኢጣልያን መንግስት በጀት አውጥቶ እንደ ወቺ መመዝገቡ አያስገርምም:: ራስ እምሩ ገሚሱን ግዜ የታሰሩት ብቻቸውን ስለነበር ወጭው ሲመዘገብ በእርሳቸው ሥም መመዝገቡ አይገርምም:: እንዲያውም አቶ ሀዲስ በዚሁ “ትዝታ በተሰየመው መጸሀፋቸው ስለ ቀለብ ጉዳይ ሲጽፉ የሚከተለውን ብለዋል፤

  “ክቡር ራስ እምሩ ሀይለስላሴና ክቡር ደጃዝማች ታዬ ጉልላቴ መጀመሪያ እጣሊያን ሀገር እንደሄዱ ያረፉት ፎርና [ፖንዛ ያለች መንደር] ነበረ…እዚያ ፖንዛ የመንግሥቱ ተቃዋሚዎች የሆኑ ብዙ ግዞተኞች (ኮንፊናቲ) ይኖሩ ነበር።…ሥመ ጥሩ የሆኑ ፈላስፋዎች፤ ፕሮፌሰሮች፤ ጋዜጠኞችና ባለልዩ ልዩ ሙያ የፖለቲካ ሰዎች ነበሩባቸው።
  ፎርና ራስ እምሩና ደጃዝማች ታዬ የነበሩበት እኛም ከደረስን የገባንበት ያንድ ሴት ቤት ነበር። ሴትየዋ ባለቤታቸው ሞተው ከሽማግሌ አባታቸውና ከሁለት ወጣት ወንዶች ልጆቻቸው ጋር ይኖሩ ነበር። ታዲያ እርሳቸውም ከነቤተሰቦቻቸው ከሚኖሩበት ሌላ ሁለት ትርፍ ቤቶች ስለነበራቸው፤ እኒያን ትርፍ ቤቶች ለኛ መኖሪያ ለመንግሥት አከራይተው በዚያ ላይ ምግባችንንምና የጽዳትም ሌላም የሚአስፈልገንን አገልግሎት እሳቸው ችለው፤ በየወሩ ሂሳባቸውን ከመንግሥት ይቀበላሉ። ስለዚህ ፎርና አምስት ወር፤ ወይም ከዚያ ትንሽ በለጠ ግዜ ስንቆይ፤…ምንም የምናገኘው [ገንዘብ] አልነበረም።”
  ትዝታ፤ሀዲስ አለማየሁ፤ ገጽ 215

  አንድን ተመራማሪ ወይም ሪሰርቸር ተመራማሪ የሚአደርገው ሌላው የጻፈውን ገልብጦ በማስቀመጡ ብቻ አይደለም:: ይሄማ ገልባጭ ወይ ወሬኛ ነው የሚአሰኘው:: ተመራማሪ የሚአሰኘው ተመራምሮ: የማሰብ ችሎታውን ተጠቅሞ: የሚአውቀውንም ሆነ አዲስ የሚአገኘውን ማስረጃ አመዛዝኖና ትክክለኛነቱን ከሌላ ከሚታወቁ ነገሮች ጋራ አመሳክሮ አንድ አይነት ግምጋሜ ላይ ሲደርስ ነው:: በእጣሊያን ቆይታቸው በሙሉ ራስ እምሩ እስረኛ እንደነበሩ እያወቁና: ራስ እምሩ አንዴም እንኳን እጣሊያንን በመደገፍም ሆነ: የኢትዮጵያ ህዝብ የኢጣሊያንን አገዛዝ እንዲቀበል የገፋፉበት አንድ እንኳን ሳይኖር “ስባቺ ደምወዝ ተቀብለዋል ብሏል እውነት መሆን አለበት: ባንዳ ነበሩ” ማለታችሁ ሊአሳፍራችሁ የሚገባችሁና የሚአስገምታችሁ ነው።
  ልዑል ራስ እምሩ ለኢጣሊያኖች በጣም ከፍ ያለ ዋጋ የነበራቸው እሥረኛ ነበሩ። ምንም ቢሆን የጦር ጀግና ከመሆናቸውም በላይ ጃንሆይ ሲወጡ የሀገሪቱ አስተዳዳሪ ልዑል ነበሩ (Prince Regent)። እውነት ደሞዝ እየተቀበሉ ባንዳ ሆነው ከነበረ ኢጣሊያን ለምን ለፕሮፓጋንዳና ሕዝቡን ለማሳረፍ አልተጠቀመባቸውም? ኢጣሊያን ባንዳ መግዛቱ ዋናው አላማው ይሄ ነበረና። ባንዳ የመግዛቱም ምክንያት ይሄ መሆኑም ግልጽ ያልሆነለት ሰው ካል: ስለባንዳዎች ሲጽፍ ስባቺ በግልጽ ጽፎታል። ከላይ የጠቀስኩትን የስባቺን ህትመት ይመልከቱ። በነገራችን ላይ በ 1000 ሊራ ራስ እምሩን ገመታችኋቸው? ሌሎቹ የታወቁት ባንዳዎች የተከፈላቸው በወር ከ7000 ሊራ እስከ 40000 ሊራ ድረስ ሲሆን ራስ እምሩ ባንዳ ቢሆኑ ኑሮ 1000 ሊራ ብቻ የሚከፈሏቸው ይመስላችኋል? እረ ሥም ከማጥፋታችሁ በፊት ማሰብን ተጠቀሙ።

  የልዑል ራስ እምሩን ግምት ማወቅ ከፈለጋችሁ፤ ከላይ የጠቀስኩትን የአቶ ሀዲስን መጽሀፍ ብቻ ሳይሆን ስለ አመራረካቸው አንቶኒ ሞክለር የኃይለሥላሴ ጦርነት በሚለው መጽሀፉ የጻፈውን አንብቡ። ከብዙ ምሣሌዎች አንዱ ነው። የተጻፈው በእንግሊዝኛ ሲሆን ከታች ያለው ትርጉሙ የቤተሰቡ ነው። ትርጉሙ ካልተመቻችሁ በእራሳችሁ ማስተርጎም ትችላላችሁ።
  “በጅማው ጦርና በሸዋዎቹ ማህል ሙሉ ቀን የዋለ የሞቀ ውጊያ ነበር:: ሲመሽ የራስ እምሩጦር ሰብሮ ወጣ።
  ነገር ግን ጥይታቸው ስላለቀባቸው መጨረሻ ላይ ራስ እምሩና ወታደሮቻቸው በጩቤና በጎራዴ ነበር የሚዋጉት::
  በዚህም ማህል በቴሲቶሪ የሚመራው ሶስተኛው ረድፍ በስተሰሚኤን መንገድ ሊዘጋባቸው መሻገርን ተረዱ::
  ከ 5 ቀን በኋላ ቴሲቶሪ እያሳደዳቸው ወደ ማጂ ሲአመሩና ጎጀብን ለመሻገር ሲሞክሩ መንገዳቸው በኢጣሊያኖች ተዘግቶና ተከበው አገኙት::
  እምሩ እጅ ለመስጠት ለመደራደር 3 መኮንኖቻቸውን ሲልኩ የኢጣሊያኑ መኮንን ሚናቲ ካለ ምንም ድርድር እጅ እንዲሰጡ አዘዛቸው:: ራስ እምሩም አብረውኝ ያሉት ሰዎች ከውጊያው አካባቢ በሠላም መውጣት ካልቻሉ እጄን አልሰጥም ብለው መለሱለት:: በመጨረሻም እጣሊያኑ ተስማምቶ ከራስ እምሩ ጦር ጋራ የነበሩት ሴቶች: ልጆችና አዛውንቶች በሰላም እንዲሄዱ ተደረገ::
  አሁንም ግን ራስ እምሩ እያቅማሙና እየዘገዩ ስላስቸገሩና ቀኑ እየመሸ ስለመጣ እጣሊያኖቹ በጥቂት ሰአቶች ውስጥ እጃቸውን ካልሰጡ በ ቦምብና በጋዝ እንደሚአጠፏቸው ላኩባቸው:: ራስ እምሩም “የሄማ ሠርጋችን (ወይም ሠርጋችሁ) ነው ብለው መለሱለት::
  ይሄንን ሁሉ መዘግየት ያደረጉት ራስ እምሩ አላማቸው ቢያዙ ሞት የሚጠብቃቸውን አበረዋቸው የነበሩትን 50 ኤርትራውያን ወታደሮችን ሲመሽ ለማስመለጥ ነበር:: ሌሊቱን አስመልጠዋቸው ወደ ኬንያ ጠረፈ ከላኩአቸው በኋላ ሲነጋ የነበራቸውን መሳሪያ በሙሉ ሰብረው ከጥቅም ውጪ ካደረጉበኋላ ንጉሲ የሰጡአቸውን ሽጉጥ ወንዝ ውስጥ ከወረወሩ በኋላ: ፈረሳቸው ላይ ወጥተው እጣሊያኖች ጦር ሠፈር ሂደው እጃቸውን ሰጡ::”
  Haile Selassie’s War, Anthony Mockler, Pg. 168

  አንድ ሰው ካለው ሀብት ሁሉ የሚበልጠው ሥሙ ነው:: ታዲያ የሚአሳዝነው ነገር አንድ ሰው እድሜ ልኩን ሳያቋርጥ ሀገሩንና ሕዝቡን በማገልገልና እራሱን በመሰዋት የገነባውን ሥም፡ አንድ የኪቦርድ አርበኛ (keyboard guerrilla)፤ ከሞቀ ቤቱ ሶፋ ላይ ተንፈላሶና የኮምፕዩተር keyboard በመቀጥቀጥ ብቻ ባንድ ደቂቃ ለማፍረስ መቻሉ ነው:: በሌላ ሰው ላይ ሊሠራ ይችል ይሆናል። በእኝህ ሰው ላይ ግን ሊሠራ አይችልም። የአይን ምሥክሩና የታሪክ ማስረጃው ብዙ ነውና።
  የልዑል ራስ እምሩ ኃይለሥላሴ ቤተሰቦችና ወዳጆች

  • Dear Shalu Mikael,

   Many thanks for your emails, comments (both on our webpage and fb), etc.

   Regarding Ras Imru and what was stated in the published article, we have already commented and explained the matter in detail to what a certain person by the name “Wogene” said. Please click here to read our reply.

   We didn’t have any ill motive to anyone when we published the article – nor we had any pretext to do any harm to anyone. Besides we are not some “የኪቦርድ አርበኛ (keyboard guerrilla)፤ ከሞቀ ቤቱ ሶፋ ላይ ተንፈላሶና የኮምፕዩተር keyboard በመቀጥቀጥ ብቻ ባንድ ደቂቃ ለማፍረስ መቻሉ ነው”. We are not in the business of tarnishing anyone’s name either – but you are entitled to your comments.

   All we stated was evidenced by a written document – not some sort of Wiki… stuff or bogus website were our sources.

   Prof. Mesfin is the one who wrote about Ras Imru and all others in his book “አዳፍኔ”. We also stated the page with the source. This is not unfamiliar to a wise noble man as you are. But we are stating all these just to set the record straight.

   If the info is wrong, as you are attesting in your write-ups, then the mistake is not ours.

   We have published your rejoinder styled comment under the article. We will also publish if you have more to say in this regard. Feel free to come up with a rebuttal to what we wrote – we will entertain that as well.

   Hope this settles the matter.

   Kindest regards,

   አርታኢ/Editor
   ጎልጉል: የድረገጽ ጋዜጣ
   editor@goolgule.com

   PS: the same message is emailed to:
   sahlumikael@gmail.com
   sahlu@smikalaw.com

Speak Your Mind

*