የጣና በለስ ታሪካዊ የልማት ፕሮጀክት፤ ከመፈራረስና ውድመት እስከ መሸጥ

[ድርጊቱ ዘላቂ ግጭት እንጂ ዘላቂ ልማትን አያመጣም]
  • የጣና በለስ ፕሮጀክት አጭር ታሪክ
  • የጣና በለስ ፕሮጀክት ልማታዊ ግቦች/ህልሞች ምን ነበሩ?
  • የጣና በለስ ፕሮጀክት በአፄው ስርዓት ተጠንስሶ፥ በደርግ አብቦ፥ በህወሀት/ኢህአዴግ እንዴትና ለምን ፈራረሰ?
  • ዛሬ በጣና በለስ ላይ የተጋረጠው አዲስ እና አስደንጋጭ አደጋስ ምንድን ነው? መፍትሄውስ?

መግቢያ

የአባይ ተፋሰስ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ተፋሰሶች የላቀ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፋይዳ ያለው ልዩ ቦታ በመሆኑ በርካታ ጥናቶች ተደርገውበታል። የመጀመርያው የአባይና ጣና ዳሰሳ ጥናት የተካሄደው በእንግሊዞች ነበር። ቀጣዩ ዝርዝርና ጥልቅ ጥናት የተካሄደው በአጼ ኃይለሥላሴ ልዩ ጥያቄ ሲሆን ምክንያቱም አወዛጋቢው የእንግሊዝና ጣልያን በ1925 ዓ.ም የተፈራረሙት ውል ነበር። ይህ የወራሪ ሃይሎች ውል ጣልያን ኤርትራ የሚገኘውን ቅኝ ግዛቷንና ሶማሌ ያለውን ቅኝ ግዛቷን ለማገናኘት በኢትዮጵያ ላይ የባቡር ሀዲድ ግንባታ እንድትሰራ የሚፈቅድ ሲሆን እንግሊዝ ደግሞ በበኩሏ ጣና ኃይቅ ላይ ግድብ ገድባ ውሃውን በወቅቱ ቅኝ ግዛቷ ወደነበረችው ሱዳን እንድትልክ የሚያደርጋት ነበር i

ይሄው ውል የተንኮልና የኮሎኒያሊዝም ዳርዳርታ መሆኑ የገባቸው አጼ ኃይለሥላሴ፣ ለጣልያንና ለእንግሊዝ መንግስታት አለመስማማታቸውን አሳውቀው በልዩ ፍጥነት ከአሜሪካ ጋር መደራደር ጀመሩ። ድርድሩም አሜሪካውያኑ ወደሀገራችን መጥተው የጣና ኃይቅ ዳርቻ ላይ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመሆን ግድብ እንዲሰሩ፣ ከግድቡም ተለቆ ወደ ሱዳን የሚፈሰውን ውሃ የሱዳን ባለትልልቅ እርሻ ባለቤቶች ውሃውን በገንዘብ እንዲገዙ ስምምነት ተደርሶ አሜሪካ ውያኖቹ ስራ ጀመሩ። ከስራው በፊትም ተፋሰሱ እንዲጠና ኢትዮጵያ በመጠየቋ ኒውዮርክ የሚገኘው ጂፒ ኋይት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የተፋሰሱን ጥናት ማጥናት ጀመረ።

ከ1930 – 1934 እ.ኤ.ኣ ይሄው ኩባንያ የጣናና የዓባይ ተፋሰሶችን ሙሉ በሙሉ አጥንቶ፣ ለኢትዮጵያ መንግስት ያስረከበ ሲሆን፤ ጎን ለጎንም የአስር ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት በመቅረጽ በጣና ሓይቅ ዙርያ የታሰበውን የግድብና የውሃ ልማት ፕሮጀክት ለመተግበር እንቅስቃሴ ጀመረ። ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን እንግሊዝ ፕሮጀክቱን አስመልክቶ ክፉኛ ተቃውሞዋን አሰማች። ጥቂት ቆይቶም ጣልያን ኢትዮጵያን ወረረች። ሊሰራ የታሰበውም የጣና ተፋሰስ ልማታዊ እንቅስቃሴ ተቋረጠ። አሜሪካዊው ኩባንያም ኢትዮጵያን ለቆ ወጣii

ጣና በለስ ፕሮጀክት፤ ከፅንሰት እስከ ውልደት

ከጣልያን ወ ረራ በኋላ የንጉሰ ነገስቱ መንግስት ዋና ተግባሩ በጣልያን የፈረሰውን ሀገር መገንባት፥    ሀገሪቱን ማረጋጋትና ድጋሚ ወረራ ቢቃጣ ለመመከት የሚቻልበትን የመከላከያ አቅም መገንባት ላይ ነበር። እንዚህ አንገብጋቢ እቅዶች መልስ ከተሰጠባቸው በሗላ በ1958 እ.ኤ.ኣ ታድያ ንጉሰ ነገስቱ ቀዳማዊ ሓይለ ስላሴ ኢትዮጵያ የአባይን ውሃ የመጠቀም ሙሉ መብት እንዳላት ለዓለም አሳውቀው የአባይ ልማት እንቅስቃሴ በድጋሚ ተጀመረ። ይህንንም ጥናት ለማስኬድ ይቻል ዘንድ ኢትዮጵያ 42 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ዶላር መድባ ጥናቱ ተጀመረ። ይህንን ጥናትና ልማትም የአሜሪካ መንግስት በብርቱ ድርድር በመቀበሉ ከአሜሪካ በኩል የThe Bureau of Reclamation of the US Department of Interior ሀላፊነት ተሰጥቶትና The USA-Ethiopia Cooperative Program for the Study of the [Blue Nile] Basin የሚባል መግባባት ተመስርቶ እጅግ ጥልቅ የአባይ ጥናት (Abay basin Master plan) ይካሄድ ጀመር። ከአምስት አመት ( 1958 -1964 እ.ኤ.ኣ) ጥናት በኋላም 17 ቅጽ ያለው እጅግ ዝርዝር የጥናት ሪፖርት አስረከበiii

ይሄውም የጥናት ሪፖርት አባይ ላይ ሊሰሩ የሚችሉ አምስት ግዙፍ ግድቦችን ከነሙሉ ቴክኒካዊ ሁኔታቸውና ዝርዝር ዲዛይ ናቸው ጋር አቀረበ። የጣናን ትርፍ ውሃም በትልልቅ ቱቦዎች ወደ ታች በመውሰድ ታላላቅ የልማት ፕሮጀክቶችን ማካሄድ እንደሚቻልና ለረጅም ግዜ በመታረሳቸው ከተጎዱ አካባቢዎች ዜጎችን በማስፈር አካባቢውን ምድራዊ ገነት ማድረግ የሚቻልበትን ዝርዝር ጥናት በማቅረቡ የጣና በለስ ልማት ሀሳብ ተወለደ። ይህን ሃሳብም ከታች የተፃፈውን በማንበብ ማመሳከር ይገባል።

“In the Abbay basin master plan study report (1958–64) it was suggested that Water be so transferred from Lake Tana to the Beles by a tunnel, then made available for large-scale irrigation in the valley downstream. Five hydroelectric power stations were envisaged in the upper stream, and the study indicated possibilities for irrigated agriculture and resettlement of farmers from the denuded and overcrowded highlands of northern Ethiopia. Settlers from the northern highlands of Wollo, Tigray, Gondar and Gojam would be the largest groups, comprising some 480,000 people”iv

የደርግ ወደ ስልጣን መምጣት እና የጣና በለስ ፕሮጀክት እጣ ፈንታ

አሳዛኙ ነገር ታድያ ከጢስ አባይና ፊንጫ ግድብ መገደብ ውጭ (ይህ የልማት ፕሮጀክት) እውን ሳይሆን ንጉሡ ከስልጣን ወረዱ። የሶማሌ መንግስትም ኢትዮጵያን በመውረሩ የሀገሪቱ ሙሉ ትኩረት እንደገና ድንበር ወደማስከበር ተመለሰ። የሶማሌ ወራሪ ጦር ተሸንፎ የተወሰነ መረጋጋት ሲገኝ ኮሎኔል መንግስቱ የሚመሩት የኢትዮጵያ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስት (ኢህድሪ) የጣና በለስ ፕሮጀክት ስራው እንዲጀመር እና በድርቅ የተጎዱ ወገኖችን ወደ ጣና በለስ እንዲሰፍሩ ተወስኖ ጣና በለስን የመገንባት እንቅስቃሴ ተጀመረ።

የጣና በለስ ፕሮጀክት የቀድሞ አርማ 1986-1991ዓ.-እ-ኤ-ኣ

የጣና በለስ ፕሮጀክት የቀድሞ አርማ 1986-1991ዓ.-እ-ኤ-ኣ

ለዚሁም ሥራ የጣልያን መንግስት ከ300 ሚሊዩን ሊሬ በላይ በእርዳታና በብድር በመስጠቱ የጣና በለስ ልዩ የልማት መንደር ግንባታ እንቅስቃሴ ተጀመረ። የጣና በለስ ገነት የሰፈራና የልማት ፕሮጀት እንዲካሄድ የተያዘለት አንድ ሚሊዮን ሄክታር ቢሆንም የተጀመረው ግን በ22 0,000 ሄክታር ላይ ነበር። ይሄው የሰፈራና የልማት ቦታም የተዋቀረውም በስድስት ወረዳዎችና በ42 ቀበሌዎች ነበር። ለታሰበው ልማት ይውሉ ዘንድ በመቶዎች የሚቆጠሩ ግሬደሮች፣ ትራክተ ሮች፣ ኮምባይነሮች፣ ኮምፓክተሮች እና ሌሎች ማሽኖች ተገዘተው ወደ ጣና በለስ ደረሱ። የመጀመርያው የስራ አካል የሆኑት ፓዌን መገንባትና ከዳንግላ ፓዌ ያለውን መንገድ መዘርጋት በሚገባ ተጠናቀቀ። የስራው ሌላ ምዕራፍ የሆኑትም የፓዌ አየር ማረፍያ ተገነባ። አንድ መቶ ሃያ ስድስት አልጋ የሚይዝ ልዩ ሆስፒታል ሥራ ቀጠለ። አካባቢው ላይ ሊመረት ለታቀደው ሩዝ መፈልፈያና ማብቀያ ማሽኖች ተተከሉ።

ለአርሷደሮችና ለባለሙያዎች የሚሆኑ በሺዎች የሚቆጠሩ የተለያዩ ቤቶች ተገነቡ። ልዩ ልዩ የጎጆ ፋብሪካዎች፣ የውሃ መስመሮች፣ እስከ አስር ሺህ ኩንታል መያዝ የሚችሉ መጋዘኖች፣ ወፍጮ ቤቶች፣ የውሃ ማጠጫ መስመሮች እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ተገነቡ። የእንሰሳት እርባታና የእርሻ ሰብል ማዕከላት ተገነቡ።

ፎቶ፡ የጣና በለስ መንደ

ፎቶ፡ የጣና በለስ መንደ

በመጨረሻም የጣና በለስን ግዙፍና ለም መሬትን በመስኖ ለማልማት የሚቻልበትን የመስኖ ካናሎች ዝርጋታ ተጀመረ። በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ በወሎ፣ ትግራይ፣ ከምባታ፣ ሀድያ፣ አላባ እና መሰል ቦታዎች ይኖሩ የነበሩ አርሶአደሮች በሰፈራ ፕሮግራም ወደዚህ ጣና በለስ እንዲሰፍሩ ተደረጉ። የሰፈራ ፕሮግራሙ ላይ የራሱ የሆኑ ችግሮች ቢኖሩም አርሷደሮቹ በጥቂት ግዜ ውስጥ በተለይ በሩዝና መሰል ተክሎች እጅግ የላቀ ምርትን ማስመዝገብ ጀመሩ። በአጭር ግዜ ውስጥም ጣና በለስ የምርት እምብርት ሆነች።

ከጣና በለስ የሚመረተው የተትረፈረፈ የሩዝ፥ አኩሪ አተር ምክንያት የሀገሪቱ ሩዝና አኩሪ አተር ምርት እጅግ በከፍተኛ ቁጥር በመጨመሩ ከአካባቢው አልፎ ወደ መላው ኢትዮጵያ ይሰራጭ ጀመረ። ይህንን ልማት ለማፋጠንና የታቀደውን ሰፊ ቦታ ለማልማት ማስፋትና በወቅቱ የሀገሪቱን ኤሌክትሪክ መሸፈን የሚችል የኤሌክትሪክ ግድብ ስራ ተጀመረ። በጣም የሚገርም እክል ግን ከሌላ አቅጣጫ ተሰማ። ይህ አስደናቂ የሆነ ሥራ ሳይጠናቀቅ በህወሀት የሚመራው አማጺ ጦር አዲስ አበባን ተቆጣጠረ።

ውድቀተ ደርግ፥ የህወሀት/ኢሕአዴግ ወደ ስልጣን መምጣትና የጣና በለስ ፕሮጀክት የገጠመው አዲስ
ፈተና፤ ህልም ሲጨናገፍ!!!

ይህ ወቅት ግን ለጣና በለስ ፕሮጀከት አስከፊ ምዕራፍ ነበር። በህወሀት የሚመራው አዲሱ መንግስት አዲስ አበባን በተቆጣጠረ በጥቂት ግዜያት ውስጥ የጣና በለስ ፕሮከጀትን በሚያስገርም፣ እንግዳ በሆነ ሁኔታ ማፈራረስ ጀመረ። ለማመን በሚገርም ሁኔታም ፕሮጀክቱ ላይ የነበሩ ዶዘሮች፣ ኤክስካቬተሮች፣ ትራከተሮችና ሌሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ልዩ ልዩ ማሽነሪዎችንና መኪናዎችን እየጫነ ወደ ትግራይ ማጓጓዝ ጀመረ። በቦታው የነበሩትን የልማትና የአነስተኛ አግሮ ኢንደስትሪ ተቋማትም በሙሉ

ፎቶ፡ የጣና በለስ የሩዝ ምርት

ፎቶ፡ የጣና በለስ የሩዝ ምርት

በማፈራረስ መጫን ጀመረ። የተጀመረውን የግድብ ስራ እንቅስቃሴ ንብረቶችንም ሙሉ በሙሉ በመዝረፍ ስራውን አቋረጠ። በልማት እንቅስቃሴዋ ከፍተኛ እመርታ ያሳየችው ጣና በለስን አወደማት። በቢሊዩን በሚቆጠር ብር የተገዙ የተለያዩ የፕሮጀክቱ ንብረቶች በሙሉ በህወሀት ተዘረፉ። ብሩህ ተስፋ አይተው የነበሩት አርሷደሮችም ተስፋቸው ጨለመ።

የኢህድሪ (ኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ) ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ፍቅረሥላሴ ወግደረስ ፕሮጀክቱን በመጽሃፋቸው እንዲህ ሲሉ ያብራሩታል፡

“የግብፆችን ጠላትነትና ተቃውሞ በማጤን የጣና በለስ ስራ በጣና ኃይቅ ዙሪያ (ከፍተኛው የዓባይ ወንዝ መነሻ) የዓባይን ወንዝ ገድቦ የኃይቁን ውሃ ከፍ በማድረግና ውሃውን በቦይ እንዲያልፍና ተሽከርካሪዎች ተጠቅሞ የሚወርደውን ውሃ ለመስኖ እርሻ መጠቀም ነበር። እቅዱ ሙሉ ስራ ላይ ሲውል በዚህ አካባቢ ብቻ አንድ ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለመስኖ እርሻ ለማዋል ነበር። የጣና በለስ “በአስደሳች ሁኔታ ተጀመረ። ከጣልያን አገር አግሮኖሚስቶች (የእርሻ ባለሞያዎች)፤ የተለያዩ የቴክኒክ እውቀት ያላቸው ባለሞያዎች መጡ። ኢትዮጵያውያን የእርሻ ባለሞያዎችና በሺህ የሚቆጠሩ ሠራተኞች ከጣልያኖች ጋር ተቀናጅተው እንዲሰሩ ተደረገ። የአፈር ምርመራ፤ የመስኖ መሥመር ዝርጋታ፤ የሙከራ ጣቢያዎች ግንባታ፤ የውሃ፤ የኤሌክትሪክና የቴሌፎን ዝርጋታ ስራ ተጀመረ። የእርሻው አካባቢ ተቀየሰ። ወደፊት ከተማ ሊሆኑ የሚችሉ ጣቢያዎች ተቆረቆሩ። የመንገድ ግንባታ በየአቅጣጫው ተጀመረ። ከድህነትና ከረሃብ የመገላገል ተስፋችን ለመለመ። ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ የውሃ ምንጭ እየተባለች በመስኖ መጠቀም ተስኗት ለዘመናት በረሃብ መጠበሷ ያከትማል የሚል ተስፋ አደረብን።” አስደናቂ ዘመናዊና የተያያዘ የልማት ስራ መካሄድ ጀመረ ማለት ነው። በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ይኼን የሚመስሉ እቅዶችና ጅምሮች ነበሩ። የጣናን ኃይቅና የዓባይን ወንዝ በጥናትና አግባብ ባለው እቅድ በስፋት ሲሰራ የመጀመሪያው መሆኑ ነው። ከዚያስ ምን ተከተለ? እኛ እንደሰት እንጅ ጠላቶቻችን (ግብፆች፤ ሻቢያ፤ ህወሓት) በጣና በለስ ፕሮጀክት ቅሬታ ተሰምቷቸዋል። በዚህም የተነሳ ህወሓት አካባቢውን በያዘበት ጊዜ እንዳልሆነ አድርጎ ፕሮጀክቱን አፈራረሰ። ለፕሮጀክቱ ስራ ይጠቅማሉ ተብለው የመጡትን የግንባታና የእርሻ መሣሪያዎች በሙሉ እየጫኑ ወደሚፈልጉበት አካባቢ አጓጓዙ። ጠቃሚ መስሎ የታየውን ማንኛውንም እቃ እየነቀለ ወሰደ። በዘመናዊ የሕክምና መሣሪያዎች ተደራጅቶ የተቋቋመውን ሆስፒታል አፈራረሰ። የኤክስሬይና ዘመናዊ የምርመራ መሠራሪያዎችን ነቃቅሎ አጓጓዘ። የተዘረጉ ቧንቧዎች ሳይቀሩ ተነቃቅለው ተወሰዱ።v

ፎቶ፡ በህወሀት ተዘርፈው ወደ ዳንሻና መሰል እርሻ ልማቶች የተወሰዱ የጣና በለስ ትራክተሮች

ፎቶ፡ በህወሀት ተዘርፈው ወደ ዳንሻና መሰል እርሻ ልማቶች የተወሰዱ የጣና በለስ ትራክተሮች

በህወሀት የሚመራው ኢህአዴግ መንግስት ጣና በለስን ካፈራረሰና ከ15 ዓመት በኋላ ግን “የጣና በለስ ኤሌክትሪክ ኃይል ግድብን” ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታወቀ። ይሄው ግድብ የቀድሞው የጣና በለስ የተቀናጀ ፕሮጀክት አንድ አካል ነበር።

የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ መሰራቱ ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም ከግድቡ የሚወጣውን ውሃ ማልማት በሚል ምክንያት ጣና በለስ ሸለቆ አርሷአደር ላይ ሌላ መከራ አመጣ። ይሄውም ይህ የ ጣናበለስ እቅድ እንደቀድሞው አርሷደሩን ተጠቃሚ መሰረትና ማዕከል ባደረገ ሁኔታ ሳይሆን አርሷደሩን አንስቶ በ75 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ መንግስት የስኳር እርሻና ፋብሪካ በመትከል አካባቢውን ለስኳር እንደሚፈልገው በማሳወቅ በሺዎች የሚቆጠሩ አርሷደሮችን ለዘመናት ከኖሩበት ቦታ ማፈናቀሉን ቀጠለ። በተለይም እንደፈንድቃ ከተማ ያሉ አርሷደሮች ሙሉ ለሙሉ በሚባል ሁኔታ ለዘ መናት ከኖሩበት የአያት ቅድመአያቶቻቸው ርስት ተነቅለው፣ ትርፍ አምራች የነበሩት አርሶአደሮች አገዳ ቆራጭ እንዲሆኑ ተደርገዋል። ይሄው ፕሮጀክትም ወደ አለፋና መተማ አድማሱን በማስፋት ከአለፋ በርካታ ቀበሌዎች ውስጥ ያሉ አርሷደሮች እየተነሱ ነው።

ይበልጥ የሚያስዝነው ግን አንዱን አንስቶ ሌላውን ለመትከል የሚደረገው ሩጫ ነው። እንደ ፈንድቃ ከተማ ላይ ይኖሩ የነበሩ አርሷደሮች ከተነሱ በኋላ የስኳር ፕሮጀቱን ሊሰራ ነው የተባለው ሜቴክ እጅግ በሚገርም ሁኔታ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከትግራይ አምጥቶ ማፍሰሱ ነው። በመሰረቱ ኢትዮጵያ የኢትዮጵያውያን ናት። ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የትም ሄዶ ሰርቶ መኖር አለበት። ነገር ግን ለዘመናት የኖረውን አርሷደር በልማት ተነሺ ስም አፈናቅሎ ከሌላ ቦታ ሌሎች አርሷደሮችን አምጥቶ ማስፈር ግን ምን ማለት ነው? ማንም ሄዶ ማረጋገጥ በሚችለው መልኩ አሁን ጣና በለስ ላይ ያለው ሁኔታ ነባሩን አርሷደር በልማት ስም አንስቶ በሌላ የመተካትና የአካባቢውን ማህበረሰባዊ ገፅታ (demography) የመቀየር ከፍተኛ ስራ እየተካሄደ ነው።

የጣና በለስ የአኩሪ አተር ምርት

የጣና በለስ የአኩሪ አተር ምርት

እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ውስጥ አስራ ሁለት ተፋሰሶች አሉ። ከነዚህ ውስጥ በኤኮኖሚ፣ በፖለቲካዊና ማህበራዊ ፋይዳው ትልቁ የሚባለው የአባይ ተፋሰስ ነው። የዚህ ተፋሰሰ ዋና ንኡስ ተፋሰስ አንዱ ደግሞ የጣናና የበለስ ንኡስ ተፋሰሶች ናቸው። ከጣና እስከ በለስ ያለው ቦታ ከውሃ አቅሙና ድንግልና በተመቸ መሬቱ የተነሳ ከፍተኛ የልማት አቅም ያለው የምርት እምብርት በመባል የሚታወቅ ቦታ ነው። የተለያዩ ጥናቶች እንዳረጋገጡት ያንን ቦታ በማልማት ብቻ የሀገሪቱን የምርት መጠን በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር ና የምግብ እህልን ማትረፍረፍ ይቻላል vi

እውነታው ይህ ቢሆ ንም አሁን የተያዘው አካሄድ ብዙ የሚያጠያይቅ ነው። የጣና በለስ ተፋሰስ ም ዕራብ ጎጃም፣ ሰሜን ጎንደር፣ ቤኒሻንጉል እና የመተማ አካባቢዎችን የያዘ ሰፊና ብዙ አትክልቶችንና ሰብሎችን ማብቀል የሚችል ቦታ ነው። በመጀመርያ ያንን ቦታ ለሸንኮራ አገዳ ብቻ ማዋሉ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዘነ ነው። ሁለተኛ ለዘመናት የኖረውን ነዋሪ በልማት ስም እያፈናቀሉና “የኔ” የሚሉትን ሌላ ሰው ከሌሎች ቦታዎች በአልሚ ስም በማምጣት የአካባቢውን ዴሞግራፊ የመቀየር ሙከራ የሚያመጣው ዘላቂ ግጭት እንጂ ዘላቂ ልማት አይደለም።

የጣና በለስ ማሽላ

የጣና በለስ ማሽላ

ይበልጥ ግራ የሚያጋባው ደግሞ ይሄን እምብርት የልማት ቦታ 75% ለውጭ ባለሃብት የመሰጠቱ ዜና ከራሳችው የዜና ምንጭ መሰማቱ  ነው። በመሰረቱ ኢንቨስትመንትን የሚጠላ የለም። ነገር ግን በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ አለ የሚባለውን ዋና የልማት ቦታ  75 ፐርሰንቱን ለውጭ ባለሀብት መስጠት ሀገር ከመሸጥ እኩል ነው። በክልልም ደረጃ ስናየው ይሄ ቦታ የሚያጠቃልለው ምዕራብ ጎጃምን፣ አለፋን፣    መተማንና የቤኒሻንጉል አካባቢዎችን ነው። በዚህ ስሌት ም መሰረት የምዕራብ አማራ ሰፊና ለም ቦታ ለቱርክ መስጠቱ አጠያያቂ ብቻም ሳይሆን አስደንጋጭም ነው።

ስለዚህ፥ ከዚህ በመቀጠል የሰፈሩ ሃሳቦችን አውዳሚነትና መፍትሄ በሚገባ ልናጤን ያስፈልጋል፥

  1. የጣና በለስ ሃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ውሃውን የሚያገኘው ከጣና ሃይቅ መሆኑ ይታወቃል። ወደ ጣና የሚገባውና የሚወጣው የውሃ ሚዛን ጉድለት እያሳየ በመሆኑ በግዜ ሂደት የጣና ሃይቅ አደጋ ውስጥ ገብቷል። ይህንንም ችግር ለማስወገድና የጣና አካባቢን ለመንከባከብ በብዙ ሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ብድር ቢወስድም፥ ጣና ላይ እዚህ ግባ የሚባል የውሃ እንክብካቤ ስራ እየተሰራ አይደለም። በዚህም ምክንያት የጣና ሃይቅ በደለል፣ በጎርፍ፣ ባልተቀናጀ የመስኖ ልማት፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ፍሰት እና በመሳሰሉት ጉዳዮች አደጋ ውስጥ ገብቷልvii። ይህ ችግር ጣናን እንደ ዓለማያ ሃይቅ ሳያደርቀው በፊት አስፈላጊው እንክብካቤ ይደረግ እና ልዩ ትኩረት ይሰጠው ዘንድ እንጠይቃለን።
  2. ማንኛውም ልማት የሚካሄደው በአካባቢው የሚገኙ ማህበረሰቦችን ለመጥቀምና አልፎ ተርፎም በሀገር ደረጃ ምጣኔ ሃብታዊ እገዛ ለማድረግ ነው። ጣና በለስ ተፋሰስ ላይ ግን የሚደረገው አካሄድ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው። ከምዕራብ ጎጃም እስከ አለፋ ድረስ አርሷደሮች በልማት ስምና በህገ ወጥ ሰፋሪ ሽፋን  ስም እየተነሱ ነው። በሚያሳዝን ሁኔታ ደግሞ በአልሚ ስም ከሌሎች ቦታዎች ሰዎች እየመጡ እንዲሰፍሩ እየተደረጉ ነው። ይሄ በሌሎች ቦታዎች እንደሚታየው ዘላቂ ግጭት እንጂ ዘላቂ ልማትን አያመጣም። ስለዚህ የኢትዮጵያ “መንግስት” በልማት ስም ኗሪውን እያነሳ የዴሞግራፊ ለውጥ ለማድረግ የሚያካሂደውን ስውር ደባ አጥብቀን እንቃወማለን። ለተነሺዎችም ሙሉ ካሳ፣ ምትክ መሬትና ማህበራዊ ግልጋሎቶች እንዲሟሉላቸው እና ወደ አያት ቅድመ አያቶቻቸው ቀዬም ይመለሱ ዘንድ እንጠይቃለን።
  3. የጣና በለስ ስኳር ልማት 75 ፐርሰንቱ ለቱርኩ በዴሳ ግሩፕ መሰጠትን አጥብቀን እንቃመዋለን። እስካሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ግልፅ ያልሆነ የኢንቨስትመንት ሂደት የገቡ ትልልቅ ኩባንያዎች የአካባቢውን ተፈጥሮ አውድመው ከመሄድ እና የመጡበትን ሀገር የምግብ እህል ዓላማ ከማሳካት በስተቀር ይህ ነው የሚባል ልማት አላከናወኑም፤ ያከናውናሉ ብለንም መጠበቅ ፍፁም የዋህነት ነው። ለምሳሌ በብዙ ሺህ ሄክታር መሬት ተሰጥ ቶት የነበረውን የህንዱን ካራቱሪን መጥቀስ ይቻላል። ሌሎች በኢንቨስትመንት ስም የገቡና በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር እንደሚያፈሱ የተነገረላቸው የቱርክ ኩባንያዎችም ሀገር ውስጥ ከገቡ በኋላ የመብራት ሂሳብ መክፈል አቅቷቸው ከመንግስት ጋር እሰጥ እገባ ውስጥ እንደገቡ በተለያዩ የሀገሪቱ ሚድያዎች ም ጭምር ተገልጻል። አሁንም ለበዴሳ ይህን ያህል መሬት የተሰጠበት ግልጽ የጨረታ ሂደት የለም። ቱርክ ለኢትዮጵያ ካላት ታሪካዊና አንጻራዊ ስፍራ አኳያም ይህን ያህል ለምና ስትራቴጂክ መሬት ለቱርክ ኩባንያ መስጠቱ በምንም መስፈርት አይደገፍም።

ለአማራው ህዝብም ሆነ ለመላ ኢትዮጵያውያን ንብረታቸው፥ ተስፋ ቸው፥ እና መመኪያ ቸው የሆነውን ይህን ፕሮጀክት ለመሸጥ ወይም ለብዙ አስርት ዓመታት በሊዝ ለማከራየት የሚደረግ ማናቸውንም እንቅስቃሴ በአስቸኳይ እንዲቆም አበክረን እንጠይቃለን። ለዚሁም ዘመቻ የበኩላችንን በማድረግ እንቀሳቀስ ዘንድ የአማራ ባለሙያዎች ህብረት (አምባ – Amhara Professionals Union) አደራ ይላል።

ህዳር 29፥2009 ዓ.ም

ዋሽንግተን ዲሲ
አምባ – የአማራ ባለሙያዎች ህብረት (Amba – Amhara professionals Union)
Empowering our People for a Brighter Future!

(ምንጭ: አምባ – የአማራ ባለሙያዎች ህብረት፥ ጽሁፉን በPDF ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ)


ኢህአዴግ ጣና በለስን ለምን አፈራረሰው?  በሚል ርዕስ (June 8, 2013) ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ ያተመውን ጽሁፍ ለማን እዚህ ላይ ይጫኑ። (የመግቢያ ፎቶ BELES inlet)

Comments

  1. Truth is two sided,yes,I don’t support the TPLF because they were just like derg,they had no real plan for ethiopia but I stopped reading this article when you tried to justify derg.

  2. Tadesse, you can compare TPLF and Derg. TPLF is not Ethiopian: it planned to destroy Ethiopia in disguise. It is an agent of colonizers. Derg was really Ethiopian though it was killer and arrogant.

Speak Your Mind

*