“ዲቃላ” የፍረጃ ፖለቲካ በኦሮሚያ የኃይል አሰላለፉን እየቀየረ ነው

በኦሮሚያ ክልል አዲስ የተነሳው የፍረጃ ፖለቲካ የኃይል አሰላለፉን እንደቀየረና በርካታ የክልሉን ተወላጆች እያሳሰበ መሆኑ ተገለጸ። አካሄዱ ወደ ዘር ማጽዳት ለሚደረገው ድብቅ ጉዞ አመላክች ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችል አስተያየት እየተሰጠ ነው።

ሲጀመር “ዲቃላ” የሚለው ፍረጃ በድንገት የተሰነዘረው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ስም በማንሳት ነው ቢባልም አቶ በቀለ ገርባ ቀደም ብለው ለዚህ አካሄድ ፍንጭ መስጠታቸውን ስጋት የገባቸው ለጎልጉል እንደመነሻ ያነሱታል።

“ከሌሎች ብሔረሰቦች ጋር አትጋቡ፣ አትነግዱ” ሲሉ ዲስኩር ያደረጉት አቶ በቀለ ገርባ ይህ ንግግራቸው በወቀቱ ከፍተኛ ተቃውሞ አስነስቶባቸው እንደነበር ያወሱት እነዚህ ክፍሎች፣ ይህንኑ መርዘኛ ቅስቀሳ ለማስተባበል ጃዋር መሐመድ የሚመራቸው ሚዲያዎች በዘመቻ መልክ መትጋታቸውን ያክላሉ።

በወቅቱ በፕሮፓጋንዳ ብዛት ነገሩ የተላዘበ ቢመስልም ሰሞኑንን ኦፌኮ ጃዋርን እየተከተለ ባካሄዳቸው ቅስቀሳዎች በርካታ ክፉ ነገሮች የቀረቡበት መድረክ መሆኑንን መርካቶ በንግድ ስራ የተሰማሩ የአዲስ ዓለም ነዋሪ “የጃዋርና የመረራ ቅስቀሳ ሌሎችን የሚገፋና ሰላምን የሚነሳ ነበር” ብለዋል።

በቅርቡ በሰላሌ አንድ ቄስ በማስከተል ዶ/ር መረራና ጃዋር እንዲተላለፍ ያደረጉት መልዕክት “የደብረ ሊባኖስን ገዳም ውረሱ” ከሚለው ጀምሮ በአገር ደረጃና በአካባቢው ተወላጆች ዘንድም ተቃውሞ የተነሳበት ቅስቀሳው ማብቃቱን ተከትሎ ነበር።

ሰላሌ

ከሁለት ቀን በፊት ጃዋር ከኢትዮ ቲዩብ ጋር ቃለ ምልልስ ሲያደርግ “የሰሜን ሸዋ አማሮች” ሲል የገለጻቸውን ኦሮሞዎች እሱ ከተወለደበት ጎሮጉቱ ወረዳ ደጋማ ክፍል መስፈራቸውን አትቷል። አያይዞም አካባቢው የኦነግ ትግል ያልተለየው ቢሆንም ደገኞቹ ያላቸው ሰላሌዎች ተሳትፎ እንዳልነበራቸው አመላክቷል።

ይህ ያበሳጫቸው የአካባቢው ተወላጆች ጃዋር ሰላሌ በመጣበት ወቅት የተቀበለው ስላልነበር ከብስጭት በመነሳት እንደተናገረው ያምናሉ። ይሁን እንጂ አካሄዱ አሁን አዲስ ጎልቶ የመጣው “የዲቃላ” ፖለቲካ መስመር መሆኑን ያሰምሩበታል።

በሰሜን ሸዋ ድምጽ የማግኘት ዕድላቸው እጅግ እንደመነመነ ስለሚያውቁ ሕዝቡን “በዲቃላነት” መፈረጃቸው ቁጣ በመፍጠሩ ካለፈው ጋር ተዳምሮ የጃዋር ፓርቲና የሰሜን ሸዋ ግንኙነት የተበጠሰ መሆኑንን ማሳየት አስፈላጊ ሆኖ ተግኝቷል ባይ ናቸው።

በጅማ የተደረገው የተቃውሞና የድጋፍ ሰልፍ በሰላሌ ሲባላላ ለቆየው ቅሬታ እንደ እርሾ ያገለገለ መሆኑንን ከሰልፉ አዘጋጆች መካከል አንዱ ነኝ ያለ ለጎልጉል የአዲስ አበባ ዘጋቢ አመልክቷል። ሰልፉን ስፖንሰር የሚያደርገው የብልጽግና ፓርቲ ነው ለሚለው “ቢሆን ችግር የለበትም። ግን ደጋፊዎች አቅም አለን። ከዚህም በላይ ማድረግ እንደምንችል ሊታወቅ ይገባል” የሚል ምላሽ ሰጥቷል።

እናቱ የጊምቢ ተወላጅ እንደሆኑ የሚናገረው ይኸው ወጣት እንዳለው “እነ ዶ/ር መረራና ጃዋር የጀመሩት የዲቃላ ፖለቲካ በርካታ ዘመዶቹን አሳዝኗቸዋል። ሰፊ የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆኗል” ብሏል። አያይዞም እንዲህ ያለው የዘቀጠ አመለካከት ኦሮሞን እንደማይመጥን ተናግሯል። እናቱም “ምን መጣብን ደግሞ?” ማለታቸውን አመልክቷል።

ጉዳዩ ከቤተሰብም በላይ የአገር በመሆኑ ልክ በጅማ እንደተደረገው የድጋፍ ሰልፍ ለማድረግ መወሰናቸውን በርካቶች እየገለጹ ነው። ጃዋር ክፉኛ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን የሚዘልፍበት አግባብና የ“ዲቃላነት” ጉዳይ በወጉ እንደሚወገዝም ለማወቅ ተችሏል።

የጅማው ሰልፍ አስተባባሪ ለቢቢሲ ሲናገር “ለውጡ መቀጠል አለበት፤ የኦሮሞ ሕዝብ መከፋፈል፤ መሰደብም የለበትም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ሌሎች የኦሮሞ ሕዝብም ሆነ እንደ አገር የተወከሉ መሪዎች መከበር አለባቸው በሚል ሃሳብ ሠልፉ ተዘጋጅቷል” ማለቱ ይታወሳል። የሠልፉ መነሻ ሃሳብ የኦፌኮ አባል የሆነው ጃዋር መሐመድ በተለያየ መድረኮች ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሲወረፉ መሰማታቸው ቅሬታ በመፍጠሩ እንደሆነም ነው አስተባባሪው የገለጸው።

የጎልጉል ዘጋቢ ያነጋገረው የቱሉቦሎ ነዋሪ “ኦሮሞ እኮ አብዛኛው በነሱ ቋንቋ የተዳቀለ ነው። ራሱ ጃዋር ምንድን ነው?” ሲል ይጠይቃል። አያይዞም “እንዲህ ያለ የፖለቲካ ቁማር ውስጥ መግባቱ በተለይም ለኦፌኮ ስጋት” መሆኑንን አመላክቷል።

የጅማ ኦፌኮ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ለቢቢሲ እንዳሉት “ጃዋር ወደ ኦፌኮ ከመጣ በኋላ ጥሩ ነገር የለም” ማለታቸውን ያስታወሰው የቱሉቦሎ ነዋሪ “እኔ ባለሁበት ወረዳዎችና እስከ ሰበታ ባሉት ከተሞች ሕዝቡን ብታየው ጠቅላላ የተዋለደና ደም የተጋራ ነው። ይህንን ህዝብ “ዲቃላ” ማለት በራስ ላይ ኪሳራ ማወጅ ነው” ብሏል።

የቡራዩ ነዋሪ የሆነው ታደለ (የአባቱን ስም መናገር አልፈለገም) በበኩሉ “አፍሬያለሁ። በመረራ አፈርኩ” ሲል ቅሬታውን ያስቀድማል። ኦሮሞ አቃፊ ህዝብ መሆኑንን በማሳየት አስተያየቱን ያከለው ታደለ “ይህን ሳይሰሙ የሞቱ አባቶቻችን ዕድለኞች ናቸው። የሚማልባቸው እነ ታደሰ ብሩ ለእንዲህ ያለ ዓላማ አልተነሱም። አሁን በአናቱ ገብተው ኦሮሞን የጠራና ዲቃላ እያሉ የሚከፍሉት ለምንና ምን ለማትረፍ ፈልገው እንደሆነ አይገባኝም” ብሏል። አክሎም “እንደ አንድ ኦሮሞ ቀና ብዬ ለመሄድ እንዳፍር አድርገውኛል። አፍሪካን እንመራለን ከሚለው ባህር ሃሳብ ወርደን የሒትለር የዘር ማጥራት ቅርጫት ውስጥ መቀርቀራችን የውድቀታችንን መፋጠን አመላካች ነው” በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል።

ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ የመድሃኒዓለም ትምህርት ቤት መምህር “በየትኛውም አገር የዘር ማጽዳት ዘመቻ ላይ ዋንኛ ተጠቂዎች ከሁለት የሚወለዱ ወይም በዘመኑ የነጃዋር ቋንቋ ዲቃላዎች ናቸው” ሲሉ ይገልጻሉ።

ናዚ በዘር ማጽዳት ሂሳብ አይሁዶችን፣ ጂፕሲዎችን፣ አካለ ስንኩሎችን፣ ግብረሰዶማውያን ሲጨፈጭፍ ትኩረት ሰጥቶ ያጠፋቸው “ዲቃላ” ያላቸውን ከሁለት ዘር የሚወለዱትን ነው። በዚያን ዘመን በመቶዎች የሚቆጠሩ ከሁለት ዘር የሚወለዱ “ዲቃላ” ልጆች ዘራቸው እንዲመክን ተደርጓል።

በጭፍጨፋው መጀመሪያ ሥር የሰደደው “ንጹህ ጀርመኖች (የአሪያን ዘር የበላይ ማድረግ)” የሚለው አጉል ትምክህት መሆኑን ያስረዳሉ። አያይዘውም “የነጃዋር ሒሳብና እነ መረራ ሳያውቁ የተነከሩበት ሩጫ ንጹህ ኦሮሞና ዲቃላ ፖለቲካ እንደ አቅሚቲ የናዚ ሃሳብ መሆኗ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ግን አይሰራም” ብለዋል።

ኦፌኮ ውስጥ የተሰባሰቡ ሰዎች ለኦሮሞ ሕዝብ መብትና ፌዴራላዊ አስተዳደር እታገላሁ እያሉ በሌላ ወገን ግን “የዲቃላ” ፖለቲካ ማራመዳቸው ደጋፊዎቻቸውን ጨምሮ ሌሎች ኦሮሞዎችን ከማስከፋት አልፎ በጃዋር ዜግነት ጉዳይ ሰሞኑን ሲናጥ ለቆየው ኦፌኮ አደጋ ላይ የጣለ፤ በርካታ ኦሮሞዎችን ቅስም የሰበረ መሆኑ በስፋት እየተነገረ ነው።


ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ንብረት ናቸው። ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን።

Comments

  1. እኛ ውህድ የኦሮሞ ህዝብ አቃፊነትን ማሳያ የሆንን ተወላጆች በዘረኝነት አረቄ በሰከሩት ዲቃላ ተብለን የተደገሰልንን የዘር ማጥራት የጭፍጨፋ ድግስ ከወዲሁ የተገነዘቡ የጅማ ወገኖቻችን ይህንንም ለመቀልበስ በማውገዝ የጀመሩትን ቅዱስ ዐላማ ያለውን ትግል በመከተል የአጥንትና ደም ፍላጫችን የሆነው በሁሉም የአገሪቱ ክፍል የሚገኝ ኦሮሞ ከጎናችን በመቆም እነዚህን የኦሮሞ ኢንተር አሞይ ለመሆ በመንደርደር ላይ ያሉትን በፖለቲካ ድርጅት ጭምብል የተሸፈኑ ቅጥረኛ ነብሰ ገዳይ የሆኑ ቡድኖችና ግለሰቦችን አላማቸውን ከግብ ከማድረሳቸው በፊት ከጎናችን በመቆም ትውልድ የጣለባችሁን አደራ በመገንዘብ እነዚህን የታሪክ አተላ የሆኑ የኦሮሞ ህዝብ አንድነት ጠላቶችን እኩይ ተግባር ከመንገድ ማስቀሪያው ጊዜው አሁን ነውና ከጎናችን በመቆም የተደገሰልንን የእርስ በርስ ጪፍጨፋ ማስቆምና በኛ መነገድ ይብቃችሁ ስትሉ ነገ ዛሬ ሳትሉ ሙት ሃሳባቸውን በአደባይ በህያው ሃሳብ ትመቱት ዘንድ እየጠየቅን ዛሬ እነሱ እያቀነቀኑ ያሉት ውህድ የሆኑ ዜጎችን የማጥፋት አባዜ ታሪክ እንደሚያሳየን በነ ሂትለሯ ጀርመን ከመፈፀሙ በፊት አነሳሱ እንደዛሬዎቹ የኛ የናዚ ፖርቲ አምሳያ የሆኑ ቡድኖች በውህድ ዜጎች ላይ እንደሚያደርጉት በማድረግ ነውና::
    ዛሬ በእኛ ኦሮሞ የዘር ሃረግ ባለብን ልጆች ዙርያ ጫፍ በረገጡ ዘረኞች እየተቀነቀነ ያለው እንዲፈፀምብን የተሻተው የዘር ማጥራት እንቅስቃሴ በሌላውም ብሄር ዉስጥ ባሉ ዘረኞች የማይከሰትበት ምክንያት የለምና በኢትዮጵያችን ዉስጥ የምንገኝ ውህድ ማንነት ያለን ውህዳን ከወዲሁ ከማንም በፊት ቀድመን ዘረኝነትን አምርረን ልንታግል ይገባል::
    (ከወዲያ ማዶ ሆኖ ክፉ ሰው ተጣራው
    ከወዲህ ማዶ ሆኖ ክፉ ስው ወይ እለው
    ጎበዝ ተጠራጠር ይህ ነገር ለኛ ነው :: )

Speak Your Mind

*