የጌታቸው አሰፋ ሌጋሲ እና ቀጣይ አቅጣጫዎች!

የህወሓት ነባር ታጋይ የሆነው ጌታቸው አሰፋ የመረጃና ደህንነት ዳይሬክተር ሆኖ የተሾመው 1993 ዓ.ም ላይ ነበር። ክንፈ ገ/መድህንን የተካው ጌታቸው አሰፋ ከቀደመው የመረጃና የደኅንነት ሰው ፍጹም የተለየ ባህሪ እንዳለው የመረጃ ምንጮቻችን ይጠቁማሉ። ከሸራተን ሆቴል ውጭ እምብዛም የማይዝናናው ጥንቁቁ የመረጃ ሰው ሲበዛ ተጠራጣሪና ደመቀዝቃዛ እንደሆነ ይነገርለታል። በኤምባሲዎች ራት ግብዣ ላይ እንኳን ለመገኘት ከኤምባሲ ኤምባሲ፣ ከአምባሳደርም አምባሳደር የሚያማርጠው የደህንነቱ ቁንጮ፣ በህይወት እያለ ምሽት ላይ ከቦሌ ወሎ ሰፈር ግሮሰሪዎች በአንዱ ከማይታጣው ክንፈ ገ/መድህን አኳያ የተለየ ባህርይ ብቻ ሳይሆን የረቀቀ የአፈና መዋቅር በአገር ውስጥም ሆነ በቀጠናው ላይ መዘርጋት የሚችል ሰው መሆኑ ከቀደመው የመረጃ ሰው እንደሚለየው ይነገርለታል።

በማህበራዊ ድረገጽ የተለቀቀው የጌታቸው አሰፋ ፎቶ

ሰውየው ራሱን እንደመንፈስ ጋርዶ ከህዝባዊ ዕይታ ተከልሎ ላለፉት አስራ ስምንት ዓመታት የመረጃና ደህንነት መስሪያ ቤቱን ሲመራ ቆይቷል። በቅርቡ በማህበራዊ ድረገጽ የተለቀቀውን ፎቶግራፉን ያነሱት የኦህዴድ የደህንነት ሰዎች ሲሆኑ፤ ፎቶግራፉ በድብቅ የተነሳ በመሆኑ የሰውየው ሙሉ ቁመናና ገጽታ ሊታይ ባይችልም፤ ለዓመታት እንደመንፈስ ራሱን ጋርዶ የኖረው የመረጃና የደኅንነቱ ቁንጮ ራሱ ባልፈቀደበትና ይሁንታውን ባልሰጠበት ሁኔታ ፎቶግራፉ ለአደባባይ መዋሉ ቁጣ ጭሮበታል።

በህወሓት ውስጥ የጌታቸው አሰፋ ሚና በሁለት ምዕራፍ ይከፈላል የሚሉት የጎልጉል የመረጃ ምንጮች፤ ሰውየውን ቅድመ-መለስ እና ድህረ-መለስ በሚል በሁለት መልክ ይገልጹታል። እንደመረጃ ምንጮቻቸን ዘገባ ጌታቸው አሰፋ፣ መለስ ዜናዊ በህይወት በነበረበት ወቅት ሥርዓቱን ለማስቀጠል በሚረዱ የአገር ውስጥና የጎረቤት አገራት የአፈና ተግባራት ላይ ብቻ ያተኩር ነበር። በሟቹ መለስ ተጽዕኖ ፈጣሪነት ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ እንዲሳተፍ የማይፈቀድለት ጌታቸው አሰፋ፣ የፖለቲካውን መበላሸት ለማስተካከል በሚካሄዱ የእመቃ ተግባራት ግንባር ቀደም ተሳታፊ ሰው ነበር። ከ1993 ዓ.ም ጀምሮ እስከ መለስ ህልፈት ድረስ ከተካሄዱ መንግሥታዊ ፍጅቶች ጀርባ ሰውየው በዕቅድ አውጭነትና አስፈጻሚነት የጎላ ሚና ነበረው። ለአብነት፡-

ወዘተ የመሳሰሉ በዓለምአቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በሚያስጠይቁ መንግሥታዊ ፍጅቶች ላይ ተሳታፊ ነበር። ከዚህ ጎን ለጎን በመሀል አገር ጋዜጠኞችን፣ የተቃውሞ ፖለቲካ አመራሮችንና የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎችን በማሰር፣ ስቅየት በመፈጸም እና ከአገር በማሳደድ በአኩይ ድርጊት የተጠመደ ሰው መሆኑ የሚዘነጋ አይደለም።

የአገር ውስጥና ዓለምአቀፍ መረጃዎችን በጣምራ የሚከታተለው የደኅንነቱ ሰው ጌታቸው ከአሜሪካው ሲ.አይ.ኤ.፣ ከእስራኤሉ ሞሳድ፣ ከራሺው ኬ.ጂ.ቢ.፣ ከእንግሊዙ ኤም.አይ ሲክስ፣ ወዘተ ታላላቅ የደኅንነት ተቋማት ሰዎች ጋር አጋርነት አለው። ምስራቅ አፍሪቃ ላይ ነግሶ የነበረውን አልሸባብንና  የመረጃ መረቡን ለመበጣጠስ በነበረው የስለላና የመረጃ ልውውጥ ተግባራት የሰውየው ሚና የሚናቅ አልነበረም። በቀጠናው ላይ “ሽብርተኝነትን ለመዋጋት” በሚሉ ዘመቻዎች ላይ ሰውየው የቀጠናው ተጽዕኖ ፈጣሪ ሊሆን ችሏል። እ.ኤ.አ 2012 ሱዳን ውስጥ የነበረውን “ያርሙክ” የተባለ ንብረትነቱ የኢራን የሆነ የጦር መሣሪያ ማምረቻ ድርጅት ሞሳድ ሲያወድመው ጌታቸው አሰፋ ቀጠናዊ መረጃዎችን በመሰብሰብ የሞሳድ ቁልፍ የመረጃ አጋር ነበር። ከዚህ ጋር በተያያዘ ይህ በሚሳኤል የወደመው የጦር መሣሪያ ፋብሪካ ያመርት የነበረው የጦር መሳሪያ መዳረሻውን ሊባኖስ ያደረገ እና ለሂዝቦላ ማጠናከሪያ ይውል እንደነበር እስራኤል ከጥቃቱ በኋላ መግለጫ መስጠቷ ይታወሳል። በዚህ መሰል ዘመቻዎች ሰውየው በኢራኑ IRGC (Islamic Revolutionary Guard Corps) እና በሊባኖሱ ሂዝቦላ ጥርስ ውስጥ ቢገባም በሲ.አይ.ኤ. እና በሞሳድ በኩል ተወዳጅነት ሊያገኝ ችሏል።

የደቡብ ሱዳንን ነጻነትን ከሲ.አይ.ኤ. ሰዎች ጋር በመሆን ያዋለደው የመረጃና ደኅንነቱ ሰው፣ በጊዜ ሂደት ራሱን ያበቃ እንደሆነ ይነገርለታል። የምስራቅ አፍሪቃ መረጃዎችን በመሸጥ ተሰሚነቱን ያጎላው ሰው፤ መለስ ዜናዊ ከመሞቱ በፊት በወልደሥላሴ ሊተካው እንደነበር የጎልጉል የመረጃ ምንጮቻችን ያስታውሳሉ። መረጃ በማገት እና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በመሸጥ ተፈላጊነቱን እያጎላ የመጣው የደኅንነቱ ሞተር ለመለስ ዜናዊ እንኳ ቀጠናዊ መረጃዎችን የሸሸገባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ። መለስ ሞት ባይቀድመው ሰውየውን ሊያሰናብተው ይፈልግ እንደነበር የመረጃ ምንጮቻችን ያስታውሳሉ።

የመለስን ሞት ተከትሎ ወትሮውንም ቢሆን በመረጃ እገታው ፈርጥሞ የነበረው ጌታቸው አሰፋ በመረጃና ደህንነት መስሪያ ቤቱ ውስጥ የእርሱ ትከሻ ተጋፊ የነበረውን የአገር ውስጥ የመረጃና ደህንነት መምሪያ ኃላፊውን ወልደሥላሴን በሙስና ወንጀል ወደቃሊቲ በመወርወር ያለተጋፊ ራሱን ማደላደል ቻለ። በመለስ ጊዜ “አትድረስበት” የተባለውን የፖለቲካውን ማዕከል በድህረ-መለስ ለመጨበጥ አልተቸገረም ነበር። ለኢትዮጵያ ፖለቲካ አንግዳ ክስተት ቢሆንም የአገሪቱ የመረጃና የደህንነት ኃላፊ ሰው ከ2005ዓ.ም ጀምሮ የህወሓት የፖሊት ቢሮ አባል በመሆን  የህወሓትን ሁለንተናዊ የበላይነት በግልጽ ማጠናከር ችሏል። የግሉን ፕሬስ መዝጋት፣ ጋዜጠኞችን ማዋከብ፣ ማሰር፣ እንዲሰደዱ ማድረግ፤ ጠንካራ የተቃውሞ መሰረት ባላቸው የተቃውሞ ፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ አባላትን በስውር ማስረግ፣ ፓርቲዎችን መከፋፈልና እርስ በርስ ማባላት፣ ማሰርና ማንገላታት፣ቤተሰቦቻቸውን እንደማገቻ መጠቀም፣ በኃይማኖት ተቋማትና በሲቪክ ማህበራት ውስጥ የስለላና የመረጃ መረብ መዘርጋት ወዘተ የመሳሰሉ የአገር ውስጥ የአፈና ተግባራት የአገዛዙ መገለጫዎችና በመለስ ዜናዊ ጊዜም የሚታወቁ እኩይ ድርጊቶች ቢሆኑም በድህረ-መለስ ጊዜያት በመረጃና ደኅንነቱ ሰው በረቀቀ መንገድ ተጠናክረዉ እንዲቀጥሉ ተደርገዋል።

ለኃይለማርያም ደሳለኝ ከሁለት ገጽ ተኩል በላይ ሪፖርት የማያቀርበው የመረጃና የደኅንነቱ ቁንጮ ሰው ከኃይል አልባው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀርባ ስውሩ ጠ/ሚ ሆኖ አገሪቱን በትውልድ ደም አጥቧታል። የትውልዱን ደም ጎዳና ላይ ከማፍሰሱ ጎን ለጎን የአገሪቱን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ ሊጎዳ በሚችል መልኩ በኢትዮጵያ ሶማሌ በኩል ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር (money laundering) በመፈጸም አገሪቱን ሲያደማ የኖረው ጌታቸው አሰፋ፤ ለዚህ ዘረፋው ቀዳሚ ተባባሪው ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት የሆነው አብዲ ኢሌ ነው። ይህን ውለታውን እያሰበ ይመስላል በቁጥር ከሰባት መቶ ሺህ በላይ የሆኑ የኦሮሞ ተወላጆችን ከሶማሌ ክልል በግፍ እንዲፈናቀሉ ሲያደርግ ከጌታቸው አሰፋና ከሌሎች የህወሓት አመራሮች “ግፋ በለው” ዓይነት የዝምታ ምላሽ የተሰጠው። አብዲ ኢሌን ከሥልጣኑ የሚነቀንቅ ባይኖርም ጌታቸው አሰፋን ከመረጃ ቁንጮ ኃላፊነቱ የሚያነሳ የፖለቲካ ለውጥ ግን ተካሂዷል።

ለጎልጉል አስተያየታቸውን የሰጡ እንደሚሉት፤ የደኅንነቱ ቁንጮ ጌታቸው አሰፋ፣ ጋምቤላ ውስጥ ለሚስቱ ቤተሰቦች ሰፊ የእርሻ መሬት በኢንቨስትመንት ስም በወረራ ማሰጠቱ፣ ከቀድሞው የልማት ባንክ ዋና ዳይሬክተር ኢሳያስ ባህረ ጋር በመሻረክ ለዘመዶቹ በአነስተኛ ወለድ በአስር ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እንዲበደሩ ማድረጉ ቆይቶ ደግሞ “የተበላሸ ብድር” በሚል ዕዳቸው እንዲሰረዝ ማድረጉ፣ የእርሱንና የሚስቱን ዘመዶች ቻይናና ዱባይ ተመላላሽ ነጋዴ እንዲሆኑ ማድረጉ፣ ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ማካሄዱ፣ በይፋ ኦዲት ከማይደረገው የመረጃና ደኅንነት መስሪያ ቤቱ ዓመታዊ በጀት ውስጥ እንዳሻው ስለዘረፈ፣ … ወዘተ አይደለም የምንጠላውና የምናወግዘው፤ ደረጃው ቢለያይም ይህን መሰል ድርጊቶች በርካታ ባለሥልጣናት አድርገውታል፤ አዲስ ነገር የለውም። ይልቁንስ የአገሪቱን ብሔራዊ ቅራኔ በሚያከሩና አገሪቱን ወደመበተን ጠርዝ በሚገፏት አደገኛ የፖለቲካ ሓጢአቶች ተሳታፊና መሪ በመሆኑ፤ በትልልቅ መንግሥታዊ ፍጅቶች ላይ እጁ ረዥም በመሆኑ፣ የአገሪቱን ፖለቲካ ባህል ጭራሹኑ በማቆሸሽ ከመለስ ዜናዊ ቀጥሎ ግንባር ቀደሙ ተጠያቂ በመሆኑና በሌሎች ወንጀሎቹ ነው የምንኮንነናውና የምናወግዘው ብለዋል።

ሌላው ሁሉ ቀርቶ በአገሪቱ ሰሜን ምዕራብ አካባቢ በህገወጥ የሰው አካል ሕገወጥ ዝውውር (organ trafficking) ተሳታፊ የሆኑ የደኅንቱ ሰራተኞችን እንኳ እያየ በቸልታ የሚያልፍ፣ ወንድ እስረኞችን በተመሳሳይ ፆታ የሚያስደፍር አረመኔ ሰው መሆኑን ዓለም ባይረዳልን እንኳ ኢትዮጵያዊያን ሊያውቁት ይገባል በማት በምሬት ይናገራሉ። ሌሎች ደግሞ “በርግጥ የጌታቸው አሰፋን ማንነትና ሌጋሲውን በቀላሉ ዘርዝሮ መጨረስ የሚቻል አይደለም፤ ታሪኩ ደርዘን ጥራዝ የሚወጣው ቢሆንም ሰውየው በኢትዮጵያ ዘመናዊ ፖለቲካ ውስጥ ያልተነገረለት የጥፋት ፊትአውራሪ መሆኑ በየጊዜው ሊነገር ይገባል” ይላሉ።

ከሦስት ዓመት ወዲህ በአገሪቱ ላይ በታየው ህዝባዊ አመጽ የተነሳ ህወሓት የነበረውን የበላይነት ለማስቀጠል መጠነ ሰፊ መንግሥታዊ ፍጅትና እመቃ ቢያካሂድም አመጹ ቀድሞውን የተቦረቦረውን የግንባሩን አባል ድርጅቶች ልዩነት አስፍቶት ተቃርኖው ጎልቶ እንዲወጣ አድርጓል። ተቃርኖው ባይሰክን እንኳ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር አዋልዷል። አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስተር በኢትዮጵያ ዘመናዊ ፖለቲካ ውስጥ እና ከአገዛዙ ተፈጥሯዊ ባህሪ አኳያ አይነኬ ይመስሉ የነበሩ ሁነቶችን በመገለባበጥ ላይ መሆናቸው የብዙዎች ኢትዮጵያዊያን ተስፋና ስጋት ሆኖ በመታየት ላይ ነው። የፖለቲካ መገለባበጡ ዕጣ ጌታቸው አሰፋ ላይ ደርሶ ከመረጃና ደህንነት ኃላፊነቱ በይፋ ተነስቷል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ሁለት ሀሳቦች ይንጸባረቃሉ። አንደኛው ጌታቸው አሰፋ በመስሪያ ቤቱ ካሳለፈው ረዥም ጊዜ፣ ከዘረጋው የመረጃ መረብ ውስብስብነትና በመስሪያ ቤቱ ውስጥ የትግራይ ተወላጆች ቁልፍ ቁልፍ ቦታዎችን በመያዛቸው ከሰውየው ተጽዕኖ ፈጣሪነት አኳያ ከደኅንነት ሥራው እንዲሁ ተቆራርጦ ይቀራል ማለት ዘበት ነው የሚል ሲሆን፤ ሁለተኛው አስተያየት ደግሞ ሰውየውን የዶ/ር አብይ አህመድ የሪፎርም ጎርፍ ጠርጎ ወስዶታል የሚል ነው። እንደ ጎልጉል የመረጃ ምንጮች ጩኸት የበዛበት ወንበር ላይ ረዘም ላሉ ዓመታት የተቀመጠው ጌታቸው አሰፋ ጩኸቱን ለመቀነስ ከወንበሩ መነሳቱ  ምርጫው ሆኗል። የመለስን ሞት ተከትሎ የጌታቸው አሰፋን በግላጭ የህወሓት ፖሊት ቢሮ አባል መሆን እና በኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ውስጥ ገብቶ ፖለቲካውን መፈትፈቱን የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚ/ር (ስቴት ዲፓርትመንትም) ሆነ ሲ.አይ.ኤ. እንዳልወደዱለት የሚያስታውሱት የመረጃ ምንጮቻችን፤ የቅርቡ ህዝባዊ አመጽና የመንግሥታዊ ፍጅቱ ማየል ያሳሰባቸው ምዕራባዊያን ጫና ሲያሳድሩ መቆየታቸው ይታወቃል። በአዲሱ ጠ/ሚ በኩል የተጀመረው ሪፎርም የደህንነት መስሪያ ቤቱንም ሊጎበኘው ይገባል የሚል አቋም በመንጸባረቁ፣ ሰውየው ከአሜሪካኖቹ ጋር መቃቃሩ ከራሱ አልፎ አንገቱን ሊሰጥለት ለተዘጋጀለት ድርጅቱ ህወሓት ሥልጣንም የሚያሰጋ በመሆኑ ከመረጃና ደኅንነት ዳይሬክተርነቱ መነሳትን መርጧል። ይህ ጉዳይ ሰውየው ከፊት ገለል ብሎ ከኋላ ለመዘወር እንዳለመ አድርገው የሚወስዱት አስተያየት ሰጪዎችን ግምት የሚያጠናክር ሆኖ ተገኝቷል።

ህወሓት እንደ ኃይል ማዕከሉ አድርጎ ይጠቀምበት የነበረውን መስሪያ ቤት እንዲህ በዋዛ ሙሉ በሙሉ  ያስረክባል ተብሎ ባይጠበቅም በምዕራባዊያን ግፊት ሪፎርሙን ሳይወድ በግዱ እንዲቀበል ተገዷል። በርግጥም ጌታቸው አሰፋ ከመረጃና ደኅንነት ኃላፊነቱ ቢነሳም በአገሪቱና በቀጠናው ላይ ባሉ ጉዳዮች ላይ ካለው የካበተ ልምድ አኳያ ይፋዊ ባልሆነ መልኩ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደኅንነት አማካሪ ሆኖ የመቀጠል ዕድል አለው የሚሉት የጎልጉል ምንጮች፣ ለዚህ መከራሪያቸው የኢህአዴግ የፖለቲካ አመራሮች ቢቀያየሩም ህወሓት ሥልጣን ሲይዝ የደርጉን ደኅንነት ኃላፊ ተስፋዬ ወ/ሥላሴን ይጠቀምበት እንደነበር አዲሱ ጠ/ሚ/ር ጌታቸውንም በደህንነት ጉዳዮች ዙሪያ ከማማከር ወደኋላ የሚሉ አይመሰልም። በተለይም በአሁኑ ሰዓት ከኤርትራ ጋር ያለው ግንኙነት ከ“አልጀርሱ ስምምነት” አፈፃፀም ጋር ተያይዞ የትግራይ ጩኸትንና ከኤርትራ ጋር ስለሚኖሩ የደኅንነት ጉዳዮች እንዴት ይያዛሉ የሚለው ጉዳይ ጥንቃቄ የሚያሻቸው ጉዳዮች በመሆናቸው አገዛዙ እንደ ሥርዓት እስከቀጠለ ድረስ ጌታቸው አሰፋ እንዲህ በዋዛ የሚሸኝ ሰው አይደለም።

የነገሩ ክፋት ደግሞ ጌታቸው አሰፋን እንዲተካ የተደረገው “ጄኔራል” አደም መሐመድ የተሰናባቹን ሰውዬ ያህል ስለአገር ውስጥም ሆነ ስለቀጠናው የመረጃና ደህንነት ጉዳዮች የቀደመ እውቀት የሌለው አቅመ ቢስ ሰው መሆኑ ነው የሚሉት የጎልጉል የመረጃ ምንጮች፣ ቦታው ለብአዴን ቃል የተገባለት በመሆኑ ለቦታው የሚመጥነው የሞሳድ ሰልጣኝ የሆነው በአሁኑ ሰዓት የኢሳያስ ወ/ጊዮርጊስን ቦታ ተክቶ የአገር ውስጥ ደህንነት መምሪያ ኃላፊ ሆኖ እየሰራ ያለው አቶ ባዘዘው ደርሶ ወይም አዲሱ ተሿሚ የኢንሳው ተመስገን ጥሩነህ ነበር ሲሉ አስተያየታቸውን ይሰጣሉ። ዞረም ቀረም፣ ጌታቸው አሰፋ ከወንበሩ ተነሳ ተባለ እንጂ ከፖለቲካው ውስብስብነትና ከቀጠናው አይረጌነት አኳያ ለቦታው የሚመጥን ሰው እስካልተቀመጠ ድረስ ሰውየው እጁ ረዥም ነውና በፖለቲካውም ሆነ በደኅንነቱ ዙሪያ መፈትፈቱን የሚያቆም አይመሰልም። ቀጣዩን የኢትዮጵያን የታሪክ አቅጣጫ የሚቀይስ የፖለቲካ ምዕራፍ ላይ ያለችው አገራችን እንደ ጌታቸው አሰፋ ያሉ ነፍሰበላ ሰዎች ለፍርድ ሳይቀርቡ አገዛዙ የዴሞክራሲ ሽግግር ያደርጋል ተብሎ አይጠበቅም።

ሆኖም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ የያዙት ግልጽና ደፋር አካሄድ የአገሪቱን ፖለቲካዊ መልከዓምድር ባልተጠበቀ ሁኔታ ይቀይረዋል ተብሎ በሕዝብ ዘንድ በሰፊው ይታመናል።

(የጌታቸው ፎቶ ይህ ነው ብሎ ማረጋገጥ አይቻልም፤ ሆኖም እዚህ ላይ ያተምው የእርሱ ፎቶዎች ናቸው ተብለው ኢንተርኔት ላይ የተለቀቁትን ነው)


ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ንብረት ናቸው። ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን።

Comments

  1. ጎልጉሎች!! ለሃገሩ ምንም ይደረጋል!! እንኮራበታለን እንጂ፤ ኣናፍርበትም!

  2. ጎልግሎች!! እንዴት ናችሁ?? በጣም ነው የጠላኋችሁ!

  3. I can’t found any thing new you bring some speculation just as a hypothetical case. Nothing new and true.

  4. Million Assefa says:

    If what you say is true, this guy has two strong enemies from which he would have to hide – Iran Republican Guards, and Hezbollah. His local enemies may as well seek the support of this guys in their agenda against him. Really, the politics of Ethiopia is getting very complex.

Speak Your Mind

*