ደጋፊ ያጣው ጎልማሳ ለአረብ ሀገር ስደተኛ

“ስደት ይብቃ!”

የስደትን አስከፊነትና በወገኖቻችን እየደረሰ ያለቀውን ሰቆቃ እንደ አዲስ እናየው ዘንድ በአረባዊቷ አፍሪካ ሀገረ በሊቢያ የሚፈጸመውን ግፍ እያየን ነው በታላቅ ክብርና ሞገስ የሚታወቀው ወገኔ ዛሬ ክብሩ ቀርቶ ለሽያጭ በደረሰ የግፍ ቀንበር ተጭኖበታል … ውርደት አንገታችን አስደፍቶናል፣ ከሰው ተራ አውጥቶናል! በቀረው የባህረ ሰላጤ ሀገራት ስደት በአረብ ሀገሩ ስደት በሚሊዮን የምንቆጠር የአብዛኞቻችን ኑሮ እየከፋ ለመምጣቱ የተሻለ የሚባለውን የሳውዲ ስደት እየኖርኩበት ነውና ዛሬም እውነቱን እነግራችኋለሁ!

ሳውዲዎች “ህገ ወጦች ከሀገሬ ይውጡ” ብለው በጀመሩት የምህረት አዋጅ የማስወጣት ዘመቻ 228 ሽህ የሚጠጉ ዜጎችን ማስወጣታቸውን በቅርቡ ነግረውናል። በሳውዲ ቅጣቱን የፈራው ሩብ ሚሊዮን ኢትዮጵያዊ በወጣ ማግስት በውጡው ዘመቻ የወጡት ተመልሰው ስለመ ምጣታቸው ጭብጥ መረጃ ከወደ የመን እየሰማን ነው። ትናንት የሳውዲ መንግስት ባወጣው አዲስ መረጃ በቅርብ ጊዜያት ድንበር አቋርጠው ሲገቡ ከተያዙት መካከል ከ 1300 ዜጎች ባላይ ኢትዮጵያውን መሆናቸውን ወንጀል ጨምሮ አርድቶናል።

ይህ ከፍቶ የቀጠለውን ስደት ካሳያችሁ በሚል ያቀረብኩት “ስደት ይብቃ” ብለን ሰቆቃውን ስናይ ብቻ የምናለቅሰውም ለቅሶ እንድንመረምረው ለማሳሰብ ወድጄ ነው። “ስደት ይብቃ” ስንል ስለ ስደት ብዙ መሰራት ያለባቸውን ስራዎች ተቀናጅተን ስለማንሰራ ጎድቶል። ተቀናጅተን ላለመስራታችን “ስደት ያብቃ” ብሎ ስለ አረብ ሀገር ስደተኛ የሚለፋ የሚደክመውን ደጋፊ ያጣው ጎልማሳ ወዳጄን አዘክረው ዘንድ ግድ ብሎኛል። የወዳጄን ህልም አዘክሬ ስለሚያገባን የወገን መከራ መወገድ ለድጋፍ እንድንተጋ ለማሳሰብና ለጉምቱው ወዳጄ ክብርና ምስጋና ለማቅረብ ብዕር አንስቻለሁ…

ደጋፊ ያጣው ጎልማሳ …

ብርቱ ወዳጄን መሳይ አክሊሉን Nubiya Kush Kedamawi ይባላል። መሳይን የማውቀው መሸታ ቤት መለኪያ ስናጋጭ አለያም ባንድ ማዕድ ተቀምጠን ጮማና ቁርጥ እየቆረጥን አይደለም። መሳይ ወገኖቻችን በአረብ ሀገር እንግልት ሲያጋጥማቸው እሱም የስደተኛ እህቶቹ የመከራና ሰቆቃ እንባ ጠርቶት ስለ በደላቸው ሲመሰክር ብቻ ሳይሆን መላ ሲፈልግ ተገናኘን። አንድ ወዳጄ መሳይን ሲገልጽ እንዳለው “የእኛው ሰው፣ የእኛው ስደተኛ አንባሳደር በተባበሩት ኢምሬት” ይለው ነበር። እውነት ነው!

ወዳጄ መሳይ የአረብ ሀገር ስደተኞች ካሳለፍነው 6 ዓመት ወዲህ ሲነሳ ስሙ አብሮ ይነሳል። በዱባይ የስደት ቆይታው እራሱን ከሚያስተዳድርበት የኩባንያ ስራ ጎን ለጎን በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ስለ ስደቱ መከራ መረጃ በማቀበል፣ ተስፋ አቢሲኒያ ራዲዮን አምጦ ወልዶ የወገኖችን ሮሮ በማሰማት፣ ለተጎዱት የስነ ጽሁፍ ምሽት በማዘጋጀት ድጋፍ በማድረግ ባደረገው ትጋት መሳይን አከብረዋለሁ፣ ብዙዎች እናከብረዋለን።

ዛሬ መሳይ ወደ ሀገር ቤት ተመልሷል! መሳይ ከኢምሬት ለእኔ የቀረበ ሰው ሆኖ በሚያገናኘን የወገን ስቃይ ስንመካከር ባጅተናል። እኔም እንደ አቅሜ ሳውዲ ስላለው መረጃ “አታስብ ” እያልኩት በክፉ ደጉ በወገን መከራ ተገናኝተን በመረጃው መረብ ተጎዳኝተን ብዙ ሆነን ብዙ ሰርተናል። ዛሬ ወዳጄ ኢምሬት በአካል ባይኖርም … ኢምሬት ላይ ወገን ሲቸገር ቀድሞ ይደርሳልና የለም አልልም፣ አለ!

ወደ ሀገር ቤት ሲመለስ ተስፋ አቢሲኒያ ራዲዮን ይዞ ነው ወደ ሀገር የገባው ብርቱው መሳይ በብስራት ኤፍ ኤም 101.1  ሬዲዮና በአማራ ራዲዮ ስደት ይበቃ ዘንድ መረጃ ይሰጣል፣ ይቀበላል፣ ስለ መፍትሔው ውይይት ያቀርባል። ስለስደት ክፉነት ሰምቶ ሳይሆን ኑሮበት ሳይታክት የስደቱን አስከፊነት ይሰብካል። “ጎልማሳው አይታክቴ ነው” ማለቱ ብቻ ማንነቱን ይገልጸው ይሆን? አይገልጸውም እሱ እንዲህ ነው መሳይ አክሊሉ!

ታታሪው መሳይ ዛሬም ሀገር ቤት ሆኖ ይለፋል ይደክማል፣ ሀገር ቤት ሆኖ የወገኖቹን እንባ ሊጠርግ ፍግም ፍግም ይላል ። ሀገር ቤት ሆኖ ወገኖቹ ስደትን አማራጭ እንዳያደርጉ በመገናኛ ብዙሃን ይመሰክራል፣ በተስፋ አቢሲኒያ ራዲዮ ወድቆ እየተነሳ ያለመታከት አድካሚ ስራን ይሰራል። ሲሆንለት ይሰማል፣ ደስ ይለዋል፣ ደስ ይለናል። ድካሙ ሲሰናከል ሳይሆንለት ዝም ይላል፣  እኛም ከጎኑ ሁነን ባንደግፈው ቅኑ ሰው ስላልሆነለት እናዝናለን። ተስፋ አይቆርጤው ግን “አንድ ቀን ይሳካልኛል” በሚል ተስፋ ከስደትና ከስደት መልስ ለአረብ ሀገር ስደተኞች የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም!

ወንድም መሳይ የኢምሬት ዱባይ ስደት ኑሮውን በቃኝ ብሎ ከተመለሰ  አንድ አመት ከ8 ወር ሆኖታል። አንድ አመት ከ8 ወር ደግሞ ብዙ ቀናቶች ፣ በብዙ አሳዛኝ ውጣ ውረዶች ታጭቋል። ይህን ሁሉ ጊዜ፣ የማይነገረውን ፈታኝ ውጣ ውረድ ለድካሙ 5 ሳንቲም ሳያገኝ “ለስደተኛው የተሻለ ብሩህ ቀን ይመጣል!” በሚል እየገፋው ዛሬ ላይ ደርሷል። በአይበገሬ መንፈስ ሲጓዝ ለዛሬው በተሻለ ማማ መረጃውን የማቀበል ስኬት በቀዳሚነት የሙያ አጋሩ ከጋዜጠኛ ትንሳኤ ታደለን ያመሰግናል። መሳይ ከጋዜጠኛ ትንሳኤ  ጋር በራዲዮ ዝግጅቱ የወጣ የወረደበትን መሰናክል ብዙ ቢሆንም አይሻገረው የለ በድል ተሻግሮታል። ይህ ሲሆን የተከፈለው መስዋዕትነት ቀላል እንዳልሆነ አውቃለሁና እመሰክራለሁ! ስለብርታቱም አድናቆቴን እገልጻለሁ!

ትንታጉ ጋዜጠኛ መሳይ አክሊሉ የስደተኛውን ድምጽ ለማሰማት የመረጠው የአባቱ መንገድ መረጃ ቅበላ ነበር። መረጃ ቅበላው ደግሞ አድካሚና አሰልች እየሆነ መምጣቱ ሌላው ፈተና ነበር። ያም ሆኖ “የአረብ ሀገር ስደት መከራና ሰቆቃ እውነቱን ሀገሬው አንድ ቀን ይረዳና የኛ ቀን ይመጣል” በሎ በማለም የጀመረው ጉዞ በግል የረባ ድጋፍ አደረግኩ ባልልም ነገር ግን እኔን ጨምሮ የጋዜጠኛ ግሩም ተክለሐይማኖት፣ የእህት ሰላም ተስፋዬ፣ የወንድም ኒዛር ዳጊ፣ የጋዜጠኛ ናቲ ቪሎፒያና በመላው አለም ያሉ አድናቂ ወዳጆቹ “አይዞህ ” የሚል እገዛና መረጃ ቅበላቸው ባይታከልበት ኖሮ ህልሙ እንደ ጉም ይበን እንደነበር አጫውቶኛል። የአማራ ሬዲዮ ያለማቋረጥ የሚያቀርበውን የቅዳሜ ምሽት የራዲዮ ዝግጅት  ወደ እሁድ ቀን አመቺ ሰዓት እንዲሸጋገር በማድረግ ትብብር አድርገውለታል። ምንም እንኳ በኳስ ምክንያት ስርጭቱ በቅርቡ እየተስተጓጎለ ቢሄድም  ብስራት ኤፍ ኤም የአየር ሰዓቱን በመስጠት ወገናዊ ትብብር በማድረጋቸውን መሳይ ምስጋና ያቀርባል። ስለ እውነት ወገናዊ ትብብር ላደረጉት ለሁሉም ምስጋና ይገባቸዋል!

የመሳይ ህልም የእኛ ህልም …

የጋዜጠኛ መሳይ ህልም “ስደት ይብቃ” ብሎ ስለ ስደቱ ህይዎት መረጃ መስጠት ነው። የአክቲቪስቱ መሳይ ህልም በስደት ህይዎት የተጎሳቆሉት ይደገፉ ዘንድ “የድረሱልኝ” ጥሪቸውን ለሚሰማ መፍትሔ ፈላጊ አካል ማቅረብ ነው። የሩቅ አሳቢው መሳይ ህልምና ፍላጎት ወገናችን ወደ ስደት የሚገፉትን ደላሎች መምከር ነው። የመሳይ ህልሙ በደላሎች የሚሰናከሉትን ታሪክ ነግሮ ማስተማር፣  መንግስትና የሚመለከታቸው የችግሩን ጥልቀት የረድተው ለመፍትሔ እንዲተጉ ማድረግ ነው። የመሳይ ህልሙ ቅጥ ያጣው ዘመናዊ ባርነትን የረቀቀ ግንኙነት መስርተው በወገናቸው ደም የሚበለጽጉትን ክፉዎች ድለላ ግፉን እንዲያቆሙ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ድምጹን ከፍ አድርጎ ማሰማት ነው!

የመሳይ ህልም በአደባባይ “ስደት ይብቃ” ብለው የሚምሉ የሚገዘቱት ባለድርሻዎች አካላት ቅን የትብብር እጅ አላረፈበትም። እውነቱ ይህ በመሆኑ የመሳይ ጉዞው የከበደ ቢሆንም እሱ ታከተኝ ሳይል እየተጓዘ ነው። መሳይን ደጋግሜ ሳስበው በአካል የማላውቀው የወዳጄ የሀገር ፍቅር የታከለበት ወኔ ያኮራኛል! ግንሳ … የጎልማሳ ድካም ጥረቱን ፣ ቅንነቱና  የማይሞት ተስፋውን ያልተሳካበት ምክንያት በአደባባይ “ስደት በቃ!” እያሉ እያነቡ በተግባር የሌሉበት ባለድርሻ አካላትና ታዋቂ ግለሰቦች ትብብር ስለማይደረግለት መሆኑ በድፍረት መናገር እችላለሁ!

ግንሳ …የጎልማሳውን ህልምና ቅንነቱን አይቶ የሁላችን የሆነውን ህልም ይዞ ሲጓዝ የሚረዳው የሚደግፈው ያስፈልገዋል።  ዛሬም የስደቱ መከራና ሰቆቃ ከፍቷል ፣ ዛሬም ደላሎች የከፋውን የሰው ንግድ አላቆመም። ዛሬም የተጎጅ ወገኖች የምንሰማው የመከራ ሰቆቃ ድምጽ ያስተጋባልና ስደቱን በተወሰነ ደረጃ ለማስቆም ማድረግ የሚቻለውን ለማድረግ አልመሸም። ፈተናውን አውጥቸ አውርጀ አንድ ብቻውን እንዴት ይንደድ? እልና እጠይቅና መልሱ ራሴው እመልሰዋለሁ! “ስደት ይብቃ!” የሚል መንግስታዊ፣ ሀገር በቀል የእርዳታ ድርጅት እና ታዋቂ ሰዎች ድጋፍ የሀገር ህልም የሆነውን የመሳይን ህልም ለማሳካት ያስፈልገዋል እላለሁ! ዛሬ የምላችሁ ስለ ወገኑ ህልመኛ ሆኖ ደጋፊ ያጣውን ጎልማሳ ለአረብ ሀገር ስደተኛ እንደግፈው ነው!

ዛሬን የምለው ከመረጃ መስጠት ድጋፍ ባለፈ የወዳጃችን “ስደት ይብቃ” ህልምን በበቂ ሁኔታ መደገፍ ያልቻልን እኛ አቅመ ቢሶች ለወዳጃችን ጋዜጠኛ መሳይ አክሊሉ ክብር በመስጠት ምስጋናችን እናቀርባለን!

ወዳጄ መሳይ Nubiya Kush Kedamawi – መሳይ አክሊሉ እናመሰግንሃለን

ክብር ለሚገባ ክብር እሰጣለሁ!
ቸር ያሰማን

ነቢዩ ሲራክ

ህዳር 22 ቀን 2010 ዓም


“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ። ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣአቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው።

Speak Your Mind

*