ዋናዎቹ “መዥገሮች” ትንንሾቹን ነቀሉ!

ህወሓት/ኢህአዴግ በራሱ ጉባዔ (ፓርላማ)፣ በራሱ ባለሥልጣናት፣ በራሱ ፈቃድ፣ በራሱ በሚተዳደረው ሚዲያ፣ ፈቅዶም ሆነ ሳይፈቅድ በሚገዛለት ሕዝብ ፊት ይፋ ያደረገው የስኳር ፕሮጀክት ዝርፊያ በራሱ አስፈላጊ ርምጃ ለመውሰድ በቂ ሆኖ ሳለ ሙስናን በመታገል ስም እስካሁን መቆየቱ በራሱ አነጋጋሪ ነው፡፡ ምክንቱም አፈቀላጤ ነገሪ ሌንጮ እንዳለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ እንደመዥገር ተጣብቀው ደሙን የሚጠጡት የበላይ ኃላፊዎች እነማን እንደሆኑ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነውና፡፡ ችግሩ ያለው ዋናዎቹን መዥገሮች ማን ይንቀላቸው የሚለው ላይ ነው፡፡

በኢህአዴግ ውስጥ የሚፈጠሩ አደገኛ የፖለቲካ ልዩነቶች ለማስተንፈስና የአመራሩንና አባላቱን አፍ ለማስዘጋት መለስ ዜናዊ ያደርገው እንደነበረው “የሙስና ዘመቻ” ሲጀመር ይህ ያሁኑ የመጀመሪያው አይደለም፡፡ በቅርቡ “ጥልቅ ተሃድሶ” በሚል “ዘመቻ” ሲጀመር “ማበስበስ” በሚባለው የህወሓት ስልት መሠረት ፋይሎች ተከፍተው የቀረበው የስኳር ፕሮጀክት የኦዲት ሪፖርት ሰሚውን ግራ ያጋባ፣ ዲዳውን “ፓርላማ” ያስደነገጠ፣ የኢህአዴግን ጭፍሮች “ኢህአዴግ አለ ወይ” ያስባለ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ሪፖርቱን ያራገቡት የነበረከት ስምዖን ጋዜጦች ይህንኑ የውስጥ የፖለቲካ ትኩሳት ለማስተንፈስ ወደ እነ አባይ ጸሃዬ እና ስብሃት ነጋ ያመራሉ ተብሎ ሲጠበቅ የሙስናው “ዘመቻ” ድንኳኑን የበታች ኃላፊዎች ላይ ተከለ፡፡

ቀደም ሲል በዚሁ “ዘመቻ” በቁጥጥር ሥር የዋሉት ከመቶ በላይ ሰዎች ጉዳይ ግማሹ ከእስር ወዲያው በመለቀቅ፣ ግማሹ ከአገር በመውጣት፣ ግማሹ እንዳሻው በየሥርቻው ተደብቆ ብይኑ ያልተሰማ “ክስ” ሆኖ ቀርቷል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ አፈቀላጤ ነገሪ ሌንጮ በመዥገር እየመሰለ ጥርሱን ነክሶ፣ ቦክስ ጨብጦ “ገና ይቀጥላል፤ አሁን እየነገርኳችሁ ያለው ቁጥር ገና ይጨምራል፤ ይህ የቁርጠኝነታችንና የጥልቅ ተሃድሷችን ውጤት ነው፤ በቁጥጥር ሥር የዋሉትን ደም መጣጮች በቅርቡ ይፋ እናደርጋለን” በማለት በቀጠሮ ቢያቆየውም ዛሬ ይፋ የሆነው የተጠርጣሪዎች ዝርዝር ነገሩን ሁሉ ዕርቃኑን አውጥቶ “የቁርጠኝነታቸውን” ክሽፈት አሳብቋል፡፡

ገና ከጅምሩ ነገሩን በጥርጣሬ ሲመለከቱ የነበሩ እንደሚሉት ኢህአዴግ የቢሊዮን ስም ጠርቶ፣ ኃላፊነታቸውን አልተወጡም፣ መዥገር ናቸው፣ ወዘተ በማለት በቁጥጥር ሥር ዋላቸው ሰዎች ይፋ ሲሆኑ አንድም ከፍተኛ የህወሃት ባለሥልጣን አልታየበትም፡፡ ቀደም ሲል ጀምሮ ከሙስና ጋር በተያያዘ የሃብት ባህር ውስጥ የሚዋኙት ቱጃሮችናና የሙስናው ሻርኮች የሆኑት የህወሓት ሰዎች ዛሬም አሳሪዎች፣ ዛሬም የተሃድሶ አራማጆች፣ ዛሬም አብዮታዊ ዴሞክራት መሪዎች፣ ዛሬም የመለስ ሌጋሲ አስፈጻሚዎች ብቻ ሳይሆኑ ዛሬም “የመንግሥት ሌቦች”፣ ዛሬም ደም መጣጭ (በነገሪ ሌንጮ አነጋገር) “መዥገሮች” ሆነው መቀጠላቸውን ያረጋገጠ መሆኑን ጉዳዩን የሚከታተሉ ወገኖች ይናገራሉ፡፡

ለጎልጉል በውስጥ መስመር አስተያየታቸውን የላኩ እንዳሉት ነገሪ ሌንጮ የማይችልበትን ፉከራ ወደኋላ ትቶ በወጉ አብዮታዊና ልማታዊ ጋዜጠኞችን ወደ ማሰልጠኑ ሙያ ቢመለስ ይሻላል፤ ከዚያ ያለፈ ወኔ ካለው ግን በትክክል መዥገሮቹ ደማቸውን መጥጠው በቁም እየገደሏቸው ያሉትን ወገኖች ቢታደግ የተሻለ ነው፡፡ ምክንያቱም የተቀመጠው ባረረ ምጣድ ላይ ነውና፤ ይህ ካልሆነ ግን ራሱ በተናገረው ንግግር ወደ ህወሓት ማበስበሻ እየገባ መሆኑን ሊያውቀው ይገባል ብለዋል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ዛሬ ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ በሰበር ዜና መልክ የወጣውን የተጠርጣሪ ሞሳኞች ዝርዝር የተመለከቱ ሌላ አስተያየት ሰጪ ኢህአዴግን በበላይነት የሚገዛው የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግምባር (ህወሓት) አገሪቱን በብሔር ብሔረሰብ ሸንሽኖ እየገዛ ያለበት የፌዴራል አወቃቀር በሙስና ላይ ሲሆን ተመሳሳይ የብሔር ብሔረሰብ ተዋጽዖ ስብጥር አለማሳየቱ የፌዴራል ሥርዓቱን የሚቃወም ሆኖ እንዳገኙት በመግለጽ ተሳልቀዋል፡፡

ነገሪ ሌንጮም ሆነ ማንም ሊመልስ የማይችለው ጥያቄ “የመሬት ባላባቱን”፤ የሙስናውን “ሻርኮች” ማን ይድፈራቸው? “መዥገሮቹን” ማን ይንቀላቸው? የሚለው ነው፡፡ ይህ ተግባራዊ መሆን በማይችልባት አገር የሚደረገው “የሙስና ዘመቻ” ትርጉሙ ምንም ሳይሆን “ሙስናን በስንጥር” ከማለት የሚያልፍ አይሆንም፡፡

ሪፖርተር “ከ1.1 ቢሊዮን ብር በላይ ጉዳት በማድረስ የተጠረጠሩ ባለሥልጣናትና ነጋዴዎች ስም ዝርዝር” በማለት ያወጣው መረጃ እንዲህ ይነበባል፤

ማክሰኞ ሐምሌ 18 ቀን 2009 ዓ.ም. መንግሥት እምነት በማጉደልና ሥልጣንን ያላግባብ በመገልገል በአገር ላይ ከ1.15 ቢሊዮን ብር በላይ ጉዳት አድርሰዋል ያላቸው ተጠርጣሪዎች ስም ዝርዝር ከዚህ እንደሚከተለው ነው፡፡

የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን

    ኢንጂነር ፍቃዱ ኃይሌ

    ኢንጂነር ዋሲሁን

    ኢንጂነር አህመዲን

    ሚስተር ሚናሽ ሌቪ (ትህዳር ኮንስትራክሽን ኩባንያ)

(ከ198 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት በማድረስ)

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን

    አቶ አብዶ መሐመድ

    አቶ በቀለ ንጉሤ

    አቶ ገላና ቦሪ

    አቶ የኔነህ አሰፋ

    አቶ በቀለ ባልቻ

    አቶ ገብረ አናንያ ፃዲቅ

(ከ646 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት በማድረስ)

መተሐራ ስኳር ፋብሪካ

    አቶ እንዳልካቸው ግርማ

    ወ/ሮ ሰናይት ወርቁ

    አቶ አየነው አሰፋ

    አቶ በለጠ ዘለለው

(ከ13 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት በማድረስ)

ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር

    አቶ ሙሳ መሐመድ

    አቶ መስፍን ወርቅነህ

    አቶ ዋሲሁን አባተ

    አቶ ሥዩም ጎበና

    አቶ ታምራት አማረ

    አቶ አክሎግ ደምሴ

    አቶ ጌታቸው ነገራ

    ዶ/ር ወርቁ አብነት (የሚኒስቴሩ ባልደረባ ያልሆኑ)

    አቶ ታመነ ደባልቄ (የሚኒስቴሩ ባልደረባ ያልሆኑ)

    አቶ ዮናስ መርአዊ (የሚኒስቴሩ ባልደረባ ያልሆኑ)

(2.2 ሚሊዮን ዶላር ወይም 51.2 ሚሊዮን ብር ጉዳት በማድረስ)

ተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ

    አቶ አበበ ተስፋዬ

    አቶ ቢልልኝ ጣሰው

(ከ31 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት በማድረስ)

    አቶ አበበ ተስፋዬ

    አቶ የማነ ግርማይ (ጂዋይቢ ኮንስትራክሽን ኩባንያ)

    አቶ ዳንኤል አበበ

(ከ20 ሚሊዮን በላይ ጉዳት በማድረስ)

    አቶ ፈለቀ ታደሰ

    አቶ ኤፍሬም ታደሰ

(ከ10 ሚሊዮን በላይ ጉዳት በማድረስ)

ኦሞ ኩራዝ ስኳር ቁጥር 5 ፋብሪካ

    አቶ መስፍን መልካሙ

    አቶ ሰለሞን ከበደ

    ሚስተር ሊዮ (የቻይና ጁጂአይሺኢ ኩባንያ ሥራ አስኪያጅ)

    አቶ ፀጋዬ ገብረ እግዚአብሔር ብርሃነ

    ወ/ሮ ሳሌም ከበደ

(ከ184 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት በማድረስ) (በታምሩ ጽጌ)


ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡

Comments

  1. ውድ ጎልጉል፣ ብዙ ሰው ያልተገነዘበው ጉዳይ አለ፦ ህወሓት በሙስና የራሱን ሰዎች ጨምሮ አሠረ፤ አማራና ኦሮሞውን ብቻ መርጦ አሠረ ለውጥ አያመጣም። ሁለቱም ውሳኔዎች ለህወሓት መፈናቀል የሚያደርጉት አስተዋጽዖ ተቀራራቢ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ጅል አይደለም። ህወሓት “ሽምግልና” ብሎ ከአማራና ከትግራይ እራሱ የመረጣቸውን ሰዎች ሰባስቦ አወያየሁ አለ። ስልቱ አንድ ነው። ፓርቲ ብሎ ለደቡብ ሰዎች፣ ለአማራና ለኦሮሞ የራሱን ሰዎች መደበ። ቀጥሎ ሆድ አደር ሰዎችን ከየብሄሩ ሾመ፤ ቀጥሎ እንደ ወርቅነህ ገበየሁ ያሉትን በደም ትግራይ ስማቸውን ወደ ኦሮሞ ቀይረው ሾመ። በሃያ አምስት አመት ውስጥ ስልቱ አልተለወጠም። የሚያሳዝነው “ተቃዋሚ” የተባለው መጃጃሉ ነው። ሌላኛው ጉዳይ፣ የድረገጾች ሚና ነው። ኢትዮሚድያን እንዴት እሳካሁን ማንም እንዳልታዘበ ገርሞኛል። ኢትዮሚድያ በቅድሚያ መልስ ሊሰጥባቸው የሚገቡ ጉዳዮች አሉ። 1/ ድረገጹን በአዲስ መልክ ለማደራጀት መዋጮ ሲጠይቅ ነበር፤ የማሰባሰቡን ውጤት ለሕዝብ አላስታወቀም፤ ማስታወቅ ግዴታ አለበት። ምንም መዋጮ ካላሰባሰበ የሚነግረን ነገር አለና ነው። 2/ የቦርድ አባላቱን ስም ይፋ ማድረግ አለበት፤ 3/ ከአይጋ ፎረም ጋር ያለውን ግንኙነት ከመቸ ጀምሮና ምን እንደሆነ ይፋ ማድረግ አለበት 4/ ከተቋቋመበት ከ2002 እንደ አውሮጳ ጀምሮ ያከማቸውን ሰነድ በ10 ቀን ጊዜ ውስጥ “ዳውንሎድ አድርጉ” ሲለን ቆየ፤ ለተማራማሪዎች መረጃዎቹ በሥርዓት መጠበቃቸው አስፈላጊ ሆኖ ሳለ፣ እንዲህ ችላ ማለቱ ሳያስበው የኢትዮሚድያን አዘጋጅ ዓላማ ፍንትው አድርጎታል [ገንዘብና ፖለቲካ]። ሰሞኑን ሰነዶቹን አቅርቤአለሁ እያለ ነው። እያላገጠ መሆኑን አንባቢ ገጹን ገልጦ ይመልከት። ኢትዮሚድያ በቻይና እና በኢትዮጵያ ተከልክሏል ብሎ ሲያታልለን ከረመ። ለመሆኑ ኢትዮሚድያ ለቻይና ምኑ ነው? ኢትዮጵያስ የህወሓቱ ሪፖርተር ከሚዘግበው ምን የባሰ ለመንግሥት አስጊ የሆነ ሪፖርት በኢትዮሚድያ ላይ ተነበበ? በነገራችን ላይ፣ ከተከማቹት ሰነዶች ውስጥ ስንቱ ተወግዷል? 5/ የኢትዮሚድያ አዘጋጅ ህወሓትን የሚነኩ ዋነኛ ጽሑፎችን ለምን አይለጥፋቸውም? ከለጠፈስ በኋላ ለምን በብዕር ስም አንባቢውን ያወናብዳል? እዚህ ላይ ለጊዜው ላብቃ። ጊዜው ሲደርስ መረጃ እናቀርባለን።

  2. >» የህወአት/ኢህአዴግ ሙስና መር ኢኮኖሚ…ማኒፌስቶአዊ የልዩ ጥቅማጥቅም(እከክልኝ ልከክልህ…ብላና አባላ…ለአንተ ልጆች እስታዲየም ለነጻ አውጭህ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ…በመፈቃቀድና በመፈቃቀር መድፈር…ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት… አብዮታዊ ዲሞክራሲ…ብሶት የወለደው ስኳር ሲቅም ሌላው በምሬት ይሰደዳል፡ የባህር ገብቶ አዞ ይበላዋል፡ ከፎቅ ተፈጥፍጦ ይሞታል።…እንዲያው በዚህ የሙስና ድሪያ ላይ እንደ ደህንነቱና መከላከያው እንደኢኮኖሚው ዕድገት የብሔር ተዋፅዎው እንዴት ነው!?የስኳሩ አባት አባይ ጸሐዬ ሚስት ወ/ሮ ሳሌም ከበደ… እንደጂነዲን ሳዶ ሚስት ይሆንና ባለቤቷን ለህወአት ኢኮኖሚና ሥልጣን ግንባታ፡ ለአማራ ልጆች ውድቀት፡ ለሠራውና ለሠረሰረው ውለታ ሲባል በክብር ለትምህርት ውጭ ሀገር ልኮ እንዲከዳ መረዳት፡ ኢሳት ላይ እሳት እንዲጭር ማድረግ የተለመደ አሠራር ነው።
    __ ሲበሉና ሲያባሉ የነበሩ ባለውለታዎች የእንባ አሳዳሪነት ማዕረግ ተሰጥቶ እራቅ ብለው እንዲቆሙ ሲደረግ፡ ለህወአት ኢኮኖሚ ሞኖፖል ሲዋደቁ የነበሩ፡ ጥቁር ልብስና መነጽር ተከራይተው/ተውሰው ለታላቁ መሪ አልቃሽ የመለመሉ፡ ካኒቲራና ፎቶ ያባዙ ዛሬ አገልግሎታቸውን ጨርሰው ዶ/ር የለም፡ መሐንዲስ፡ አገልግል አስቋጥሮ አቧራ ላይ አንደባለለው!…እነኝህ ምልምል ተሞሳሟሾች ከባለቤቶቹ በፊት ወድቀው “ኢኮኖሚው፡ ዕድገቱ፡ ትምህርቱ፡ጤናው፡ ግድቡ፡ ሀዲዱ፡መብራቱ፡ ፈጠራው ህወሓት/ኢሃዴግ ከአፍሪካ አንደኛ፡ ከዓለም ሁለተኛ፡ እያሉ ትምህርታዊ ትንታኔና ቱልቱላ/ጥሩ’ንባ ሲነፉ/ሲረጩ አልነበረም!? __ ለመሆኑ ይቺ ገንዘብ ለዚህ ሁሉ አድርባይ ሲካፈል ምን አላት? ይህ ገንዘብ በሶስት ጡረተኛ ጄነራሎች ሥም ብቻ ያለ የገንዘብ መጠን አደለምን!? በአንድ ክልል ፵፭ ትላልቅ ነጋዴዎች ግብር ካልከፈሉ ፳ ተጠርናፊ ቢኖራቸው ፱፲፻ ተሞሳሟሽ ጠርንፈው ታላቁ መሪ ላይ ንፍጥና ልሃጫቸውን በማዝረከረክ የተካኑ በክልል የተፈለፈሉ ጥቅማጥቅመኞች ሕዝቤ የሚሉትን አጅዝበው/የበይ ተመለካች ሆኖ እነሱም ባንዳ(ሹምባሽ) በመሆናቸው ሥርዓት እንዳይለወጥ፡ ሀገር እንዲናወጥ፡ ወገናቸውን ያስበሉ ስንቶች ቃሚና ተጠቃሚ ናቸው?። ይህ በብድርና በልመና የቆመ አብዮታዊ ገዢ/አውራ ፓርቲና መንግስት(!?)
    ” የሕንጻውን መሠረት ሳያወቁ ቅርንጫፍ ባንክ የሚከፍቱ” አለ ከያኒው.. አብዮት ልጇን ትበላለች ካላችሁ ግቡ እንያችሁ።

  3. የተፈጠረውን አለመረጋጋት ለማስቆምና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ሥራዎችን በተመለከተም በሁከትና ብጥብጡ ተሳትፈዋል የተባሉ ከኦሮሚያ ክልል 4136፣ ከአማራ ክልል 1888፣ ከደቡብ ክልል 1166፣ ከአዲስ አበባ 547 በድምሩ 7737 ተጠርጣሪዎች በተለያየ ደረጃ ባሉ ፍርድ ቤቶች ክሳቸውን እየተከታተሉ መሆኑ ተጠቁሟል፡

    ከትግራይ አንድም ታሳሪ አለመኖሩን ልብ ብላችኋል?

Speak Your Mind

*