“ዕድሜ ለግንቦት ሃያ…”

በግንቦት 20 ዋዜማ ዋልታ ቴሌቪዥንን እያየሁ ነው።

ጋዜጠኛው ዝግጅቱን ከአመት አመት በማይቀየሩት መፈክሮች (ለምሳሌ “ግንቦት 20 የህዝቦች ሁሉ የዘመናት ጥያቄ ምላሽ ያገኘበት ቀን ነው) ጀመረና፣ ዛሬም በጭንቅላቴ ውስጥ የሚፈነጩትን ጥያቄዎች ዘርዝሬ ለማሰብ እንኳን እድል ሳይሰጠኝ፣ “ከግንቦት 20 ወዲህ የተወለዱ ልጆች ስለዚህ ቀን ምን ያውቃሉ?” ብሎ ለመጠየቅ በየትምህርት ቤቱ መዞር ጀመረ።

የ17 አመቷ ቆንጅዬ ልጅ በፍፁም የራስ መተማመን፣ ” እኛ ባንደርስበትም በአባቶቻችንና በእናቶቻችን ላይ ላይ የነበረው ጭቆና የቀረበት ቀን ነው” አለች።

ከልጅቱ በኋላ አንድም ሳያነቅፋቸው ቀኑን በኢቲቪኛ፣ በፋናኛ እና በዋልታኛ የሚተነትኑ ወጣቶችን ሳይ ቆይቼ፤

ሌላ የ18 አመት ልጅ ብቅ ብሎ ” ግንቦት ሃያ ባይኖር እኔም እዚህ አልገኝም ነበር” ሲል ውሃዬን ተጎንጭቼ ዋልታን ደረገምኩት።

ኢትዮጵያ ፈጣሪ በቸራት ሀብት እና ውበት አሸብርቃ፣ ስንቶች ለዘመናት በከፈሉላት መስዋዕትነት ፀንታ የቆየች፣ ፀንታ የቆመች ሀገር ናት።

ሆኖም በየአመቱ ከጅማሬዋ ጀምሮ ከሰማይዋ ስር የተፈጠረ ደግ ደጉ ሁሉ፣ በምድሯ የበቀለ ድንቅ ነገር ሁሉ ከግንቦት ሃያ ጋር ሲያያዝ፣
በ”እድሜ ለግንቦት ሃያ” ሲታጀብ ፣

የጆርጅ ኦርዌል “የእንስሳት ዕድር” መፅሃፍ ውስጥ ያሉት ዶሮ እና ላም ትዝ ይሉኛል።

ዶሮዋ “ዕድሜ ለታላቁ መሪያችን ናፖሊዮን አመራር፣ በስድስት ቀናት ውስጥ አምስት እንቁላሎች ጣልኩ!” ስትል፣ ላሟ ደግሞ “ዕድሜ ለታላቁ መሪያችን በእሳቸው አመራር ስር ሆነን የምንጎነጨው የወንዝ ውሃ ጣዕሙ ልዩ ነው!” ያሉት ትዝ ይለኛል።

ለሺህ አመታት ከሃገሬ ሰማይ ስር የተከሰተ በጎ ነገር ሁሉ፣ በምድሯ የበቀለ ውብ ነገር ሁሉ ከግንቦት ሃያ ጋር ሲያያዝ ይህች ዶሮ እና ላም ትዝ ይሉኛል።

(ምንጭ: ነቆራ እና ሌሎችም ወጎች ከሕይወት እምሻው ጋር – Hiwot Emishaw)

Speak Your Mind

*