በአማራና ትግራይ ህዝብ መካካል አብሮነቱ እንዲጠናከር የሁለቱ ክልሎች ፖለቲከኞች ተቀራርበው ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለጸ

በአማራና በትግራይ ክልል ህዝቦች መካካል ለዘመናት የዘለቀው የአብሮነት እሴት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሁለቱ ክልሎች መንግሥታትና ፖለቲከኞች ልብ ለልብ ተቀራርበው ሊሰሩ ይገባል ሲሉ በጎንደር ከተማ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ተናገሩ።

የጎንደር ከተማ አስተዳደር በከተማው ከሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ጋር በወቅታዊ፣ ክልላዊና ሀገራዊ ሁኔታ ላይ ያዘጋጀው የምክክር መድረክ ዛሬ ተካሂዷል።

በምክክር መድረኩ ላይ ተሳታፊ የሆኑ የትግራይ ተወላጆች እንደተናገሩት መንግስትና የፖለቲካ ስርአት አላፊ ሲሆኑ፤ ህዝብና አገር ግን የሚቀጥሉና የታሪክ ባለቤት ናቸው።

“ጎንደር ያደኩባት፣ የሸመገልኩባት፣ ልጅ ወልጄና አሳድጌ ለወግ ማዕረግ የበቃሁባት ህዝቡም በፍቅር ያኖረኝ ከተማ ነች” ያሉት አቶ ወልደገብርኤል ተክኤ የተባሉ ነዋሪ ናቸው።

“በኖርኩባቸው 40 ዓመታት በከተማው አማራ እና ትግሬ ተባብለን አናውቅም፤ የብሔርም ጠብና ግጭትም አልነበረም” ያሉት አቶ ወልደገብርኤል አሁን በታሪካቸው የማያውቁት ነገር እየተከሰተ በመሆኑ ማዘናቸውን ተናግረዋል።

መንግስት ቢያልፍም ህዝብና ሀገር ቀጣይ መሆናቸውን ገልጸው የሁለቱ ክልሎች መንግስታትና ፖለቲከኞች ተቀራርበው በመስራት ከግጭት ይልቅ የሁለቱን ህዝቦች አንድነትና አብሮነት በሚያስቀጥሉ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩሩ ጠይቀዋል።

ላለፉት 44 ዓመታት በጎንደር ከተማ ከህዝቡ ጋር በፍቅር መኖራቸውንና ጎንደር ከተማንም በምክትል ከንቲባነት ጭምር ማስተዳደራቸውን የተናገሩት ደግሞ አቶ አያሌው ተስፋይ ናቸው።

የብሔር ፖለቲካ ሁለቱን ህዝቦች ለመከፋፋልና ለማጋጨት በር መክፈቱን የተናገሩት አቶ አያሌው፥ አሁን ሁለቱን ህዝቦች ለማቀራረብ የተዘጋጀው መድረክ ቢዘገይም ጅምሩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አስገንዝበዋል።

በሁለቱ ክልል ህዝቦች መካከል ለዘመናት የቆየው አብሮነት እንዲጠናከር የክልሎቹ አመራሮችም ሆነ ፖለቲከኞች እርስ በርስ ከመገፋፋት ይልቅ ከልብ ተቀራርበው ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በህዝባዊ የምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት የትግራይ ዴሞክራሲ ትብብር ፓርቲ ምክትል ሊቀ-መንበር ኢንጂነር ግደይ ዘርአጽዮን በበኩላቸው የአማራና የትግራ ህዝብ ዘመናት የዘለቀ አብሮነት ያለው ኩሩና አቃፊ ህዝብ መሆኑን ተናግረዋል።

አጼ ዮሐንስ መተማ ላይ መስዋዕት የሆኑት ለትግራይ ሳይሆን ለአንዲት ኢትዮጵያና ህዝቧ መሆኑን ገልጸዋል።

“የዛሬ ፖለቲከኞችና ስልጣን ፈላጊዎች ህዝብን ከህዝብ በማጋጨት የራሳቸውን ህልውና ለማስቀጠል የሚያደርጉትን የፖለቲካ ሴራ ሁለቱ ህዝቦች በጋራ ቆመው መታገል አላባቸው ብለዋል።

ኢንጂነር ግደይ እንዳሉት ፓርቲው በግጭት ምክንያት ከአማራ ክልል የተፈናቀሉ የትግራይ ተወላጆች ዳግም ወደአካባቢው እንደሚመለሱና እንዲቋቋሙ ለማድረግ ከአማራ ክልል መንግስት ጋር ጥረት እያደረገ ነው።

የአማራ ክልል መንግስት ይህን መሰል የህዝብ ለህዝብ የምክክር መድረክ እንዲዘጋጅ በመፍቀዱ አመስግነው በሌሎች መድረኮችም ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡
የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሙሉብርሃን ኃይሌ በበኩላቸው “የፖለቲካ ስርአቱ እንጂ የአማራ ህዝብ የትግራይን ህዝብ አላፈናቀለም” ብለዋል።

“የአማራ ህዝብ ሦስት ዓመት ሙሉ ተፈናቅለው የሄዱ የትግራይ ተወላጆችን ቤትና ንብረት ሳያስነካ እየጠበቀ ስለመሆኑ በቂ ማስረጃ አለኝ” ሲሉም ተናግረዋል።

“የምክክር መድረኩ የሁለቱን ህዝቦች ዘመናት የዘለቀውን አብሮነት በማስቀጠል የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ዳግም ለማጠናከር ያለመ ነው” ያሉት ደግሞ የጎንደር ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ተሸመ አግማስ ናቸው።

የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥ በማስቀጠል ረገድ ሁለቱ ህዝቦች የጎላ ሚና እንዳላቸው ተናግረው በአገሪቱ የገጠመውን የአንድነት ፈተና በጽናት በመቆም በጋራ መሻገር እንደሚገባ አመልክተዋል።

በምክክር መድረኩ ከከተማው የተለያዩ ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ የትግራይ ተወላጆችን ጨምሮ ከፍተኛ አመራሮችና የከተማው የሰላምና የልማት ሸንጎ አባላት እንዲሁም የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አመራሮች ተሳታፊ ሆነዋል።

ምንጭ ፦ኢዜአ

Speak Your Mind

*