ለጀግናው አትሌት ስንብት!

(ትዝታ ዘ ምሩፅ)

. . . በዚያ ቀውጢ ጊዜ – በዚያ ቀውጢ ዘመን፣

ከአገር በራቀበት – የደስታ ሰመመን፤

ያገር ፍቅር ስሜት –  መገለጫ ፈርጦች፣

ብቸኛው አማራጭ – የደስታችን ምንጮች፣

ነበሩን! ነበሩ! “አረንጓዴ ጎርፎች”. . .፤

እንዲህ እንደዛሬው – ሳይዘምን ዘመኑ፣

ያለም መገናኛ – ሳይራቀቅ ኪኑ፣

ዩ ቲዩብ፣ ኢንተርኔት፣ ስማርት ፎን..ሳይኖር፣

ዜና መቀበያው – ራድዮናችን ነበር፤

179-ቶሎሣ ቆቱ 178 - መሐመድ ከድር

179-ቶሎሣ ቆቱ 178 – መሐመድ ከድር

“. . . ክቡራትና ክቡራን ውድ አድማጮቻችን..”፣

የኦሎምፒክ ውጤት፣ ልክ እንደደረሰን፣ እናስደምጣለን…”፤

በለሆሳስ ሙዚቃ መሳሪያ ቅንብር መሻገሪያ ዜማ፣

ከተራራ ጫፍ ላይ፣ ወይ ከሰማየ-ሰማያት ከሩቅ እሚሰማ፣

“የኛ ነው ድሉ-ድሉ፣ የኛ ነው ድሉ-ድሉ፣

በርቱና ታገሉ..”፤

አገር ትንፋሽ አጥሮት – ጸጥ-ረጭ ብሎ፣

ዐይኖቹን ጎልጉሎ –  ራድዮን ላይ ተክሎ፣

የውጥረት ደቂቆች፣ የጭንቀት ሴኮንዶች፣ እንደ ሰዓት ረዝመው፣

የማታ –  የማታ ድሉ የኛ ሲሆን፣ ደስታው ወሰን የለው፤

“የኛ ነው ድሉ -ድሉ፣ የኛ ነው ድሉ -ድሉ

በርቱና ታገሉ…”

ከድሎቹ ሁሉ – ባለም ላይ የላቀው፣

በታሪክ ተከትቦ – ለትውልድ እሚያልፈው፣

ትዝታ ወ ሞስኮ – በኦሎምፒክ ሜዳ፣

ምሩጽና ዮሐንስ

ምሩጽና ዮሐንስ

ባምስት ሺ፣ ባስር ሺ – ዓለም ያስከነዳ፣

በዮሐንስ መሐመድ፣ በቶሎሳ ቆቱ፣…

በመሐመድ ከድር ታጅቦ የተሸኘው፣

በድል አሸብርቆ – ማማው ላይ ከፍ ያለው፣

ጀግናው አትሌታችን  – ተርቡ ምሩፅ ይፍጠር፣

እማይበገረው  – የኢትዮጵያ ልጅ ነበር!

(እሱ በአበበ ውስጥ..፣ በርሱ ውስጥ ኃይሌ..፣

የድል ቅብብሎሽ የታሪክ “ርሌ”…።)

የኦሎምፒክ ዜና

የድል ብስራት ፋና!

ምስጋና ለስሙ፣ ለውለታው ክብር!

ሰላማዊ ዕረፍት! ጀግናው ምሩፅ ይፍጠር!

ጌታቸው አበራ
ታኅሣሥ 2009 ዓ/ም
(ጃንዋሪ 2017 – ፎቶዎቹ የተወሰዱት ከዚህ ነው)

Comments

  1. It is nice to hear a positive comment of a tigrian,thank you.

Speak Your Mind

*