የኦነግ ሁለት መልክና ሦስት ግብሮች – ቃርሚያው ኃይል ቅጥር ነፍሰገዳይ ሆኗል

ኦነግ አወዛጋቢ ማንነቱና ያልረጋ የፖለቲካ ሩጫው ዛሬም መነጋገሪያ ሆኗል። ቀደም ሲል ለኦሮሞ ትግል እንደ አንድ ብቸኛና ልዩ ምልክት ተደርጎ የተወሰደው ኦነግ በአራት ጎራ ተከፍሎ ቢቆይም አገር ቤት ከገባ በኋላ አንድ መሆን አልቻለም።

በኤርትራ በረሃ እያለ እርስበርስ ጎራ ለይቶ በጥይት የተጫረሰው ኦነግ፣ በአውሮፓና በአሜሪካ ባሉ የተለያዩ አመራሮቹ የስልጣን ሽኩቻ አንድ መሆን አቅቶት ሁለት ዐሥርተ ዓመታት አስቆጥሮ አሁን አገሪቱ ውስጥ በተፈጠረው የፖለቲካ ለውጥ ሁሉም አካላት ወደ አገር ቤት ቢገቡም ልዩነታቸውን ማስወገድ አልቻሉም።

ዳውድ ኢብሣ (ፍሬው ማሾ)፣ አባ ነጋ፣ ገላሳ ዲልቦና ጄኔራል ከማል ገልቹ የተቀራመቱት ኦነግ አራት መልክ ይዞ ወደ አገር ቤት ሲገባ ሕዝብ ጥያቄ ያነሳው “ለምን አንድ አትሆኑም? አንድ ሁኑና ኑ” የሚል ነበር። እነዚህ አራት ክንፎች እንኳን አንድ ሊሆኑ ይባስ ብሎ አቶ ዳውድ ኢብሣ የሚመሩት ኦነግ ሸኔ በሚል ሁለት መልክ ይዞ መጣ።

የፕሮፌሰር መረራ ፓርቲ ኦፌኮ ከአቶ ዳውዱ ኦነግ ሸኔና ከጄኔራል ከማል ገልቹ ሽራፊ ኦነግ ጋር ግንባር ለመፍጠር መስማማታቸው ይፋ ቢሆንም፣ አቶ ዳውድ መቀሌ የመሸገው ህወሓት ካደራጀው የፌደራሊስቶች ኃይል ጋር ፍቅር መጀመሩ በርካቶችን ጉድ ያሰኘና ህወሓት ክፉኛ በደል ሲፈጽምባቸው በነበሩ የኦሮሞ ልጆችና ቤተሰቦች እንዲሁም ባጠቃላይ የኦሮሞ ማኅበረሰብ ዘንድ “አይ ዳውድና ድርጅቱ!?” በሚል ሙሾና ሽሙጥ እየተሰነዘረበት ነው።

ኦነግ ሸኔ – መንታ ትግል

ዳውድ ኢብሣ የሚመሩት ኦነግ ሸኔ አንድም ቁራሽ መሬት በቁጥጥሩ ሳያውል ከኤርትራ የበረሃ ኑሮ ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ ወታደሮቹ ደግሞ በትግራይ በኩል ሲገቡ እነ ስብሃት ነጋ በቀይ ወጥ ግብዣ አድርገውላቸው ነበር። ኦነግ ሸኔ ወደ ትግራይ በረሃ ያሽቀነጠራቸውን ኃይል ለእንኳን ደህና መጣህና ለቀይ ወጥ ግብዣ ሲመርጡ ነበር ወዲያውኑ “የማይረጥቡ አሣዎች” የሚል ስያሜ የተሰጣቸው። “አይቼሽ ነው ባይኔ ወይስ በቴሌቪዥን” ሲሉ የዘፈኑላቸውም ጥቂት አልነበሩም።

ሥጋቱ ብዙም ሳይቆይ አቶ ዳውድ “ይቅርታ ሰጪም፣ ይቅርታ ተቀባይም የለም” ሲሉ የፍየል ከመድረሷ ቅጠል መቅንጠሷ ፖለቲካቸውን ጀመሩ። ቄሮ ትግሉን ባፋፋመበት ወቅት “የቄሮ አደረጃጀት ባለቤት ማንም ሳይሆን እኛ ነን” ሲሉ ከኤርትራ የጫጉላ ሰፈራቸው በወረዛ የቪዲዮ መልዕክት ያስተላለፉት አቶ ዳውድ በወቅቱ ጃዋርን “አትንተክተክ” ሲሉትም ተደምጠው ነበር።

በኦነግ ምስኪን ወታደሮች ላይ የተፈጸመው የእርስ በእርስ መገዳደልና በአመራር ውሳኔ ህይወታቸውን ያጡ፣ የተሰቃዩ፣ በእስር ማቅቀው ያለፉት ጉዳይ ራሱን የቻለ አጣሪ እንደሚያስፈልገው የዳውድ ኢብሣ ኮቴ አዲስ አበባ ሲረግጥ መወትወት የጀመሩ ቢኖሩም አዋራው የፈጠረው ጩኸት ሰሚ እንዲያገኙ አላስቻላቸውም። በተመረዘ ምግብ በአንድ አዳር ዳውድ ሲተርፉ የተቀሩት እምሽክ ያሉበት ግፍና የኦነግ ሠራዊት ኤርትራ በረሃ የደረሰበት አስነዋሪ ግፍ ፋይል ግን አልተዘጋም። ቀኑን ጠብቆ ይከፈታል የሚል እምነት በበርካቶች ዘንድ አለ።

ሁሉም ቀርቶ ኦነግ ሸኔ ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ ቅድሚያ ሥራው የነበረው በወለጋ የተለያዩ ዞኖችና በቤኒሻንጉል ጫካዎችና ትምህርት ቤቶች ውስጥ ህጻናትን ለውትድርና መልምሎ በማሰልጠንና በማስታጠቅ ነበር የጀመረው። የጎልጉል የአዲስ አበባ ዘጋቢ የቤኒሻንጉል አንድ ከፍተኛ አመራርን አነጋግሮ እንደተረዳው ኦነግ ሸኔ በርካታ ቁጥር ያላቸውን ህጻናት ሲያሰለጥንና ሲመለምል ያልታደሰው የኦዲፒ ኃይል፣ መከላከያውና ደኅንነት/ጸጥታ ውስጥ ያለው መዋቅር ያውቅ ነበር። ከማወቅም በላይ ተባባሪ የነበሩ፣ መሣሪያ በማጓጓዝና በማስዘረፍ የሚተባበሩ ነበሩ።

በዚህ መልክ አጋጣሚን ተገን አድርጎ በአኩራፊ ጡንቸኛ ኃይላት ድጋፍ የደረጀው ኦነግ ሸኔ የሰላማዊ ትግል እያጣቀሰ ራሱን ለትጥቅ ትግል ሲያዘጋጅ ዋና መሪው መቀመጫውን ኡጋንዳ ያደረገው ዱጋሣ ባካኮ የሚባለው የቀድሞ ኦነግ የሠራዊት መሪ ነው። ዱጋሣ ኦነግ ሸኔ ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ አብሮ የመጣ ሲሆን ይህንኑ ሚሽን ተቀብሎ ወዲያው አገር ጥሎ እንደወጣ ይታወቃል።

እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ጃል መሮ የሚመራው ሽፍታ የሚባለው ድራማ የሸኔዎች ማምታቻና የተገዙ ሚዲያዎች ስብከት ነው። በአባ ነጋ የሚመራው ኦነግ አባል እንደሚለው ዳውድ ኢብሣና ዱጋሣ ባካኮ አንድና ሊለያዩ የማይችሉ ናቸው። ይህ ታማኝ የሠራዊት መሪ ይህ ኃላፊነት እንዲሰጠው የተደረገውም በዚሁ ትሥሥር እንጂ በሌላ አይደለም። ሰኞ በተላለፈው ዘገባ ለቪኦኤ መግለጫ የሰጡት የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽነር አራርሣ መርዳሣም ያረጋገጡት ይህንኑ ነው።

ዱጋሣ ባካኮ

እሳቸው እንዳሉት ኦነግ ሸኔ በሁለት እግሩ እየተጫወተ ነው። አዲስ አበባ ያለውና ጫካ የከተመው ኦነግ ሸኔ በሚገባ አንድ ናቸው። የኮሚሽነሩን መግለጫ “የት ከርመሽ” ሲሉ የተቹት የአባ ነጋ ኦነግ አባል “ይህ ጉዳይ በግልጽ ከድሮ ጀምሮ የሚታወቅ፣ የአደባባይ ሚስጢር ነው። ዛሬም አልረፈደም። ሕዝብ መርሮታል። ለሁለት መንግሥት መገበር ሰልቸኝ እያለ እያለቀሰ ነው። ሰላማዊ ሰልፍ አድርጎ አረጋግጧል” ይላሉ።

ኦነግ ሸኔ – ቃርሚያ ሲጀመር ለምን ይጮሃል?

ምክትል ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ አዲስ አበባ ያለው ኦነግ ሸኔና በረሃ ያለው ሽፍታው ኦነግ ሸኔ አንድ መሆናቸውን ለቢቢሲ በቅርቡ በይፋ ተናግረዋል። ይህንኑ ኃይል ለመደምሰስ መንግሥት በይፋ ዘመቻ መክፈቱንም አረጋግጠዋል። የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽንም ይህ ኦነግ ሸኔ በወጉ መመታቱን አስታውቀዋል። እንደ መንግሥት ገለጻ ከሆነ አሁን ተበትኖ ወደ ትውልድ ቀዬው መሸሽ የቻለውን ኃይል እየቃረሙ ነው።

ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ

እንግዲህ ሰሞኑን “አባላቶቼ ታሰሩብኝ፣ አባላቶቼ ተገረፉ፣ ተሳደዱ…” በሚል የአዲስ አበባው ኦነግ ሸኔ በአቶ ዳውድ ፊርማ ሰሞኑንን ተከታታይ መግለጫ እያወጣ ነው። የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽነር አራርሣ መርዳሣ የጸጥታ አስከባሪዎቻችን፣ የሲቪል መሥሪያ ቤት ሠራተኞች፣ ሰላማዊ ነዋሪዎች፣ ሚሊሻዎች በኦነግ ሸኔ ታታቂ ሽፍቶች ሲገደሉ አዲስ አበባ ያለው ቢሮ ያለው ነገር ያለም። ለምን? በማለት ይጠይቃሉ።  

እርሳቸውን እንዲያስተባበሉ የቪኦኤው ሙክታር ጀማል ያናገራቸው የአዲስ አበባው ኦነግ ሸኔ ሥራ አሥፈጻሚ ሚካኤል በረን “አንድ አይደለንም” ሲሉ ጫካ ሆኖ ንጹሃንን ስለሚገድለው ኦነግ ሸኔ ይናገራሉ። አያይዘውም መንግሥትን ጨምሮ ሁሉም ኃይሎች የሚሳተፉበት መፍትሔ ካልተፈለገ አንድን ኃይል ወይም ቡድን በማጠልሸት ወደሚፈለገው ሰላም አያመጣም” ሲሉ ሁሉ አቀፍ የመፍትሔ እርምጃ እንዲወሰድ ይወተውታሉ።

ዛሬ መንግሥት ቃርሚያ ላይ መሆኑንን፣ በተለያዩ የኦሮሚያ ክልሎች መንግሥትን የሚደግፉ ሰላማዊ ሰልፎች ወለጋን ጨምሮ መደረጉ በኦሮሚያ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን አስደንግጧል። ይህ ሽፍታ ቡድን በርካታ ለጋ ምልምሎቹ የተማረኩና የተደመሰሱ መሆናቸው፣ ሕዝቡም ለእነሱ ቀለብ መስፈር መሰላቸቱ፣ ሥራውን መሥራትና ምርቱን ወደ ገበያ ማውጣት አለመቻሉ ስላስመረረው የሸኔ ጉዞ የጨለመ መስሏል። እናም ጩኸቱ “ጩኸቴን ቀሙኝ” ከመሆን አያልፍም።

የዘወትር የጎልጉል መረጃ አቀባይ የኦፌኮ የመካከለኛ ደረጃ አመራር እንደሚለው ኦፌኮም የሸኔ ሰለባ እንዳይሆን ሥጋት አለ። አቶ በቀለ ገርባ ፕሮፌሰር መረራን ቆርጠው ኦፌኮን ከኦነግ ሸኔ ጋር አብረው ሊገምዱት ጫፍ ደርሰው እንደነበር ያስታወቀው ይኸው መረጃ አቀባይ የተጀመረው አብሮ የመሥራት ስምምነት ወደ ውኅደት ያላደገው ከውስጥ ባለ ጫና ነው ” ይላል።

ኦነግ ሸኔና – ዕድገት ወደ ቅጥር ነፍሰ ገዳይነት

በወለጋ የቴሌኮሙኒኬሽን ኃላፊን ከቤቱ አስጠርቶ ቤተሰቡ ፊት የገደለው የኦነግ ሸኔ ክንፍ በርካታ ንጹሃንን ገሏል። በቤኒሻንጉል መንገድ ላይ እየጠበቀ ባለሥልጣንን ገድሏል። በአምቦና በኢጀሬ መካከል ሚሊሻዎችን ገሏል። የመንግሥት ተቋማትን ዘርፏል። የኦሮሚያ ፖሊስ ይፋ እንዳደረገው በቡራዩ ኮማንደር ሰለሞን ታደሰን ገሏል፣ አንድ አርቲስትና ሁለት ተጨማሪ ዜጎችን አቁስሏል። ኮማንደር ሰለሞንና ሁለቱ የቆሰሉት ወገኖች የሰላሌ ተወላጆች መሆናቸው ጉዳዩን “እየመረጡና እየለዩ መግደል” የሚል ስም እንዲሰጠው አድርጎታል።

ይህ ሳያንስ በአምቦ ለብልጽግና ፓርቲ ድጋፍ ለመስጠት አደባባይ በወጡ ሰልፈኞች ላይ ቦምብ ተወርውሮ ሃያ ዘጠኝ ሰዎች ላይ የመቁሰል አደጋ ደርሷል። ይህም አደጋ በቀጥታ የኦነግ ሸኔ ኃይሎች የፈጸሙት መሆኑ ተገልጿል።

ኮማንደር ሰለሞን ከመገደላቸው በፊት በቡራዩ የሆቴል ምረቃ ላይ ጃል መሮ የሚባለውን የዚህ ክፋት አቀናባሪ ምስል ጨረታ ለማቅረብ ሲሞከር ጸብ መነሳቱ ይታወሳል። በጸቡ “ይህን ከሃዲ የወያኔ ተላላኪ ፎቶ ለጨረታ ማቅረብ አይቻልም። የት እናውቀዋለን” ባሉ የቡራዩ አካባቢ ነዋሪዎች ላይ ጥቃት ለማድረስ ተሞክሮ በተነሳ ጸብ ከኖርዌይ የሄደችው የጨረታ አስተባባሪ ጨምሮ ጉዳት ደርሷል። ፖሊስ ይህንን ጉዳይ በቁጥጥር ሥር ባዋለ በቀናት ውስጥ የኮማንደሩ መገደል ጉዳዩን ከኦነግ ሸኔ ሽፍታ ጋር በቀጥታ እንደሚያገናኘው የበርካቶች እምነት ነው።

ከሽፍታነት ወደ ቅጥር ነፍሰ ገዳይነት ዕድገት ያሳየው የኦነግ ሸኔ የትግል ያሳሰባቸው፤ በፊት ሲጠየፉት ወደ ነበረው የሽግግር መንግሥት ጥያቄ፣ የብሔራዊ መግባባት ጥሪ፣ የመተባበር አዋጅ ተዛውረዋል። መንግሥት ደግሞ በር ዘግቶና ዙሪያውን ከቦ የደቆሰውን ኃይል እስከ መጨረሻ የማጥፋት ሥራ ላይ ተጠምዷል። ቃርሚያውንም ቢሆን በአካባቢ ሚሊሻና የሸኔ ተግባር ባማረራቸው ዜጎች ድጋፍ ሊቋጨው፣ እንዲሁም የህዝብ የሰላም ይከበር ጥያቄ የተበራከተ በመሆኑ በሁለት እግር የሚጫወቱትን እግራቸውን ለማሳጠር እርምጃ መውሰድ የመረጠ መሆኑንን የፖሊስ ኮሚሽነሩ ቃል ያረጋግጣል። ከወንጀሎቹ ጋር በተያያዘ የተያዙት ላይ ምርመራው ሲጠናቀቅ ይኸው ተግባር እንደሚፈጸም ይጠበቃል።

የኦነግ ሸኔ – ሦስተኛው እግር

የኦነግ ሸነኔ ሦስተኛው እግር ለውጡን ተከትሎ አቶ ዳውድን አጅቦ አዲስ አበባ ገብቶ ተመልሶ ከአገር የወጣው ኃይል ነው። ይህ ኃይል በውጪ አገር ሆኖ ገንዘብ እያሰባሰበ ጫካ ያለውን ኦነግ ሸኔ የሚቀልብ፣ ትጥቅ የሚገዛ፣ አዲስ አበባ ላለው “የሰላማዊ ትግል ቡድን” ሽፋን የሚሰጥ እንደሆነ እንቅስቃሴውን በቅርብ የሚያውቁ ይናገራሉ።

ይህ ሦስተኛው የኦነግ ሸኔ እግር መንግሥት የጣምራ ዜግነትን እንዲፈቅድ የሚወተውትና በዚሁ ጣምራ ዜግነት በመውሰድ አገር ቤት የፖለቲካ ስልጣን ማግኘት የሚሻ ቡድን ነው። ይህ ቡድን ጫካ ያለውን ኃይል የማገዝ አጀንዳ ተረክቦ ኡጋንዳ ከሚገኘው ዱጋሣ ባካኮ ጋር በመሆን የሚሠራ ነው። የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽንም ሆነ መከላከያ ሚኒስቴር ይህንኑ በወጉ ስለሚያውቁት አስፈላጊውን ስራ እየሰሩ መሆኑ ተሰምቷል።

አሁን ከዚሁ የኦነግ ሸኔ ሦስተኛው እግር የሚሰማው አዲስ ጉዳይ ቢኖር ዘመቻውን በውጪ አገር ማጠናከር ነው። ዜጎች ታፈኑ፣ ታሰሩ፣ ተገረፉ፣ ተሳደዱ በሚል መንግሥት የወሰደውን እርምጃና ወደፊትም የሚወስደውን እርምጃ እንዲያቆም ማሳጣት ላይ እንዲጠመዱ ነው አቅጣጫ የተቀመጠለት። የጎልጉል የአሜሪካ ሪፖርተር እንዳጣራው በውጪ ያለው የኦነግ ሸኔ በዚህ ተግባር ሲሰማራ፣ የአዲስ አበባው ኦነግ ሸኔ ደግሞ ስለ ብሔራዊ መግባባትና የአገራዊ እርቅ ጥሪ ላይ አብዝቶ ይጮሃል።

እንደ ቀድሞ መንገድ ዝጉ፣ አገልግሎት አቋርጡ የሚለው የክተት ጥሪ ስለማይሠራ ዘመቻው “ብሔራዊ እርቅ” ወደሚለው አዋጅ መዘዋወሩን የሰሞኑን መግለጫዎች የሚከታተሉ የሚሰጡት አስተያየት ነው። ፕሮፌሰር መረራ “አሁን ባለው ሁኔታ በገዢው ፓርቲ ውስጥም ሆነ በተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል የሚታየው ፍጥጫና መጠላለፉ አገሪቱን ወደማትወጣው የፖለቲካ ቅርቃር ውስጥ እየከተታት ይገኛል” ብለዋል፤ አክለውም “ይህም ዳግም በ1960ዎቹ ወደነበረው የመጠፋፋት ፖለቲካ አንዳይመልስን ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል” ሲሉ ለጀርመን ድምጽ ተናግረዋል።

በአሁኑ ውቅት በአገሪቱ በሚገኙ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል እየሰፋ የመጣውን የፖለቲካ ፈጥጫ ወይም በእሳቸው አባባል political polarization ለማለዘብ የጋራ ብሔራዊ መግባባትን መፍጠር እንደሚገባ የተናገሩት በሃዋሳ በተደረገ የምክክር መድረክ ላይ ነው። “ሰጋሁ” ያሉት መረራ በዚሁ መድረክ የኢጄቶ ነፍሰገዳዮችና ደም አፍሳሾች ከእሥር እንዲፈቱ ግፊት እንደሚደረግ ሲጠየቅ ሲያጨበጭቡ ነበር።

የጃዋርን ድጋፍ እቀራመታለሁ በሚል ራሱን ኦነግ ሸኔ ውስጥ የቀረቀረው ኦፌኮ የቆመበት መንገድ የትኛው እንደሆነ አስረግጦ መናገር ባይቻልም፣ አሁን እየሆነ ባለው የኦነግ ሸኔ አካሄድ ግን አደጋ ውስጥ መግባቱን አባላቱ በቅሬታ እየገለጹ ነው። በተለይም በጃዋር የፖለቲካ መተጣጠፍ የተሰላቹ “ጃዋርን የሚጠሉ ኦፌኮንም ሳይፈልጉ ይለዩታል። በተለይም የዲቃላ ፖለቲካ ሰለባ እንዲሆኑ የተፈረደባቸው ኦሮሞዎች ጃዋር ካለበት ፖለቲካ እየሸሹ ነው” የሚል አስተያየት እየሰጡ ነው።


ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ንብረት ናቸው። ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን።

Speak Your Mind

*