ኦፌኮ መጋጨት ጀመረ – ጃዋር በጸሃፊው በኩል የተሳሳተ መረጃ አሰራጨ

ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና እያወቁ ሕግን በመጣስ የወሰኑት ውሳኔ ወደ ሌላ ቀውስ ሊያመራ እንደሚችል ስጋት የገባቸው ወገኖች የተማጽንዖ ጥሪ አቀረቡ። ኦፌኮ ስህተቱን ከማረም ይልቅ እርስ በርስ የሚጣረስ መረጃ ማሰራጨቱ በፓርቲው ውስጥ መለያየት እየፈጠረ መሆኑና ጃዋር ደጋፊዎቹን በጅምላ ወደ አመጽ ለመምራት ዝግጅት እያደረገ መሆኑ ታወቀ። ጸሃፊው ያሰራጩት የተሳሳተ መረጃ በጃዋር መመሪያ ነው።

ስጋቱ የተነሳው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቀነ ገደብ አስቀምጦ ለኦፌኮ በድጋሚ የላከው የጃዋር ዜግነት ጉዳይን የሚመለከተውን ደብዳቤ ተከትሎ አዲስ “አስተምህሮት” መጀመሩ ነው። ለዚሁ የሕግ ይከበር ጥያቄ ቅድሚያ መልስ የሰጡት ሊቀመንበሩ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ነበሩ። በምላሻቸው “(ጃዋር) መልኩም ሲታይ ኢትዮጵያዊ ይመስላል” በማለት ስላቅ አዘል መላምት ካስቀመጡ በኋላ ጃዋር መልስ እንዲሰጥበት ደብዳቤው እንደተላከለት ጠቁመዋል። አያይዘውም እንደተባለው ጃዋር የአሜሪካ ዜግነቱን ጉዳይ ካልጨረሰ ፓርቲው እንደሚያሰናብተው ጠቁመው ነበር።

ለዚህ ዜና ቀዳሚ የነበረው ጎልጉል፤ የድረገጽ ጋዜጣ ባገኘው መረጃ ጃዋር ለቀረበለት ህጋዊ ጥያቄ የመረጠው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ በሆኑት ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻ ማሰራጨትና በቀጥታ ዛቻና ማስፈራሪያ መጻፍ ነበር።

ወ/ት ብርቱካን ዜግነታቸውን በስደት በቆዩበት አሜሪካ መቀየራቸውን ራሱ ጃዋር በሚደጉማቸውና በሚቀልባቸው የሚዲያ መስመሮች በስፋት ማሰራጨቱን የሚዲያዎቹን አፈጣጠር የሚያውቁ ይፋ ሲያደርጉ ሰንብተዋል። እነዚህ የመደበኛውና የማኅበራዊ ሚዲያ ተደጓሚዎች በጅምላ መረጃውን በመቀበል በእሳት ተፈትነው ያለፉትን ወ/ት ብርቱካንን ሲሰድቡና ሲረግሙ ሰንበተዋል።

ይህንን የስም ማጥፋት የቤት ሥራ ካሰራጨ በኋላ ጃዋር ለወ/ት ብርቱካን “አንቺ ሴት ከእኔ ምን ጉዳይ አለሽ? ብታርፊ ይሻላል” የሚል ማስፈራሪያና ዛቻ የታጨቀበት መልዕክት ኢሜል ማድረጉን ጎልጉል አረጋግጧል። ወ/ት ብርቱካን ምንም ምላሽ ሳይሰጡ የህግ ይከነበር ጥያቄያቸውን አጠንክረው፣ ቀነ ገደብ አስቀምጠው በድጋሚ ለኦፌኮ ደብዳቤ ልከዋል። ይህንኑ ዘገባ ጎልጉል አስቀድሞ ቢዘግብም እሳቸው በአሜሪካ ሬዲዮ በቃላቸው አረጋገጠዋል።

በዚሁ የአሜሪካ ሬዲዮ ወ/ት ብርቱካን ስለ ዜግነታቸው ማብራሪያቸው ተጠይቀው ደጋግመው “ያሳዝናል” ሲሉ ነበር ምላሽ የሰጡት። በዘመነ ህወሓት ተገድደው በስደት አሜሪካ ከመቀመጣቸው በቀር ዜግነት ስለመቀየር አስበው እንደማያውቁ የቀድሞዋ ዳኛ ብርቱካን “ያሳዝናል፣ ያውም እኔ” በማለት ሲያስረዱ፣ የሰው ድምጽ ቀርቶ ኮቴ እንኳን በማይሰማበት የህወሓት ማሰቃያ ጨለማ እስር ቤት ውስጥ ሆነው ለዴሞክራሲ ማበብ የከፈሉትን ዋጋና ያለፉበትን መንገድ ለማይረሱ ሁሉ ንግግራቸው ዕረፈት የሚነሳ እንደነበር አስተያየት የሰጡ ተናግረዋል።

የጃዋርን ዜና የማስቀየር ሃሜታ በተመለከተ “ያቀረብነው የህግ ጥያቄ ነው። ቀጣዩም እርምጃ በህጉ መሰረት የሚታይ ነው” ያሉት ወ/ት ብርቱካን፣ በለሰለሰ አንደበት ኦፌኮ የተጠየቀውን እንዲፈጽም መክረዋል። ጃዋር ላቀረበው ዛቻ ግን ያሉት አንዳችም ነገር የለም።

ይህንኑ ተከትሎ የኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ፤ ጃዋር የተጠየቀውን ካላሟላ ለፓርቲው ህልውና ሲባል እንዲሰናበት እንደሚደረግ ምላሽ ሰጥተዋል። ይህ የምክትል ሊቀመንበሩ ምላሽ ያላስደሰተው ጃዋር መቆጣቱን የዘወትር የጎልጉል የኦፌኮ መረጃ አቀባዮች ጠቁመዋል።

ጃዋርን የሚያመልኩትና እየተሽቆተቆጡ የሚያወያዩት የራሱ ተቀጣሪዎችም ሆኑ “ጋዜጠኞች” እና “ጠንከር ያለ ቃለ ምልልስ የማቀርብላችሁ” የምትለዋ ሌላዋ የጭውውት ክፍለ ጊዜ አዘጋጅ፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ጃዋር “ምጡቅ ትንተናውን” ከህግ አንጻር እንዲያስረዳ እንደወትሮ አለመፍጠናቸው በአብዛኞች ዘንድ መነጋገሪያ ሆኗል።

ጃዋርን አበሳጨ የተባለው የምክትል ሊቀመንበሩ አቶ ሙላቱ የቪኦኤ መግለጫ አንድ ቀን ሳይሞው ቢቢሲ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ፓርቲ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና የፓርቲው ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጥሩነህ ገምታን ይዞ ብቅ ብሏል። “ጃዋር መሐመድ ኢትዮጵያዊ እንዳይሆን ገደብ የሚጥልበት ሕግ የለም፤ ኢትዮጵያዊ ነው” ሲሉ በቢቢሲ በኩል አቶ ጥሩነህ አስታውቀዋል።

ስጋታቸውን የሚገልጹት ወገኖች የስጋታቸው መጠን እየጨመረ የመጣውም ከዚህ መግለጫ በኋላ ነው። ለጃዋር እንቅስቃሴ ቅርብ የሆኑ የጎልጉል የመረጃ ሰዎች እንደሚሉት ጃዋር ወደ ፖለቲካ እንቅስቃሴ ሳይገባ አስቀድሞ የሚታወቀው ዜግነትን መልሶ የማግኛው መንገድ ለኦፌኮ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ጥሩነህ ተራ ጉዳይ እንደሆነ ተደርጎ የተገለጸው ሆን ተብሎ ነው።

ፕሮፌሰር መረራና ምክትላቸው አቶ ሙላቱ “ካልሆነና ጃዋር የተጠየቀውን የማያሟላ ከሆነ እንዲሰናበት ይደረጋል” ሲሉ፣ አቶ ጥሩነህ በአናቱ መጥተው “ጃዋር ኢትዮጵያዊ ነው። ኢትዮጵያዊ እንዳይሆን ገደብ የሚጥልበት ሕግ የለም” ማለታቸው “ጃዋር ደጋፊው ብዙ ስለሆነና ስለሚያሸንፍ ሆን ተብሎ ኢትዮጵያዊ ዜግነቱን” ተነጠቀ በሚል ጉዳዩን ወደ ነውጥና አመጽ ለመምራት የሚደረግ ቅድመ ዝግጅት መሆኑንን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ የዜግነት አዋጅ ቁጥር 378/1996 አንቀጽ 22 የኢትዮጵያዊ ዜግነት እንዴት መልሶ ማግኘት እንደሚቻል በግልጽ በነጋሪት ጋዜጣ በ1996 አሳትሞ አስቀምጧል።

አስቀድሞ ኢትዮጵያዊ የነበረና በሕግ የሌላ አገር ዜግነት ያገኘ ሰው፤

ሀ/ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ በመምጣት መደበኛ መኖሪያው በኢትዮጵያ ከመሠረተ

ለ/ ይዞት የነበረው የሌላ አገር ዜግነት ከተወ እና

ሐ/ ዜግነቱ እንዲመለስለት ለባለስልጣኑ ካመለከት የኢትዮጰያ ዜግነቱን መልሶ ያገኛል ይላል። 

እንደ አቶ ጥሩነህ ማብራሪያና ትንታኔ ጃዋር “አንደኛ ወደ አገር ተመልሶ እየኖረ ነው። ሁለተኛ ዜግነቱን ለአሜሪካ መልሷል። ሦስተኛ ደግሞ ለሚመለከተው አካል ዜግነቱን እንዲመለስለት አመልክቷል። ከዚህ ውጪ ሕግ የሚጠይቀው ነገር የለም። ስለዚህ ጃዋር መሐመድ የኢትዮጵያ ዜጋ ነው” ሲሉ መናገራቸውን ቢቢሲ አስነብቧል። ይሁን እንጂ ቢቢሲን የወከለውን ሪፖርት ጋዜጠኛው ሲሰራ አዋጁ በፊደል (ለ) ላይ የሚገኘውን “ይዞት የነበረውን የሌላ አገር ዜግነት ከተወ”  የምትለዋን ቁልፍ ጥያቄ ለአቶ ጥሩነት አላነሳም። ይህንን ወሳኝ ጥያቄ ለምን እንዳለፈው ግልጽ አይደለም።

ለሙያው ቅርብ የሆኑ አስተያየት ሰጪ ሲናገሩ “ጋዜጠኛ የሚለው ላይ አስምሩልኝ፤ አንድ ጋዜጠኛ የሆነ ሰው ለዜናውና ለሃተታው ቁልፍ የሆነውን አጀንዳ የሸፈነውን ጉዳይ ቆዳውን ገፎ ዋናዋ ብልት ላይ አተኩሮ ሪፖርቱን ያጠናክራል እንጂ ኮቴና ሸኾና ሲለቅም አይውልም” ብለዋል። ቀጥለውም “የሰውየው (የጥሩነህ) መልስ ግን በጃዋር ደጋፊዎች ዘንድ ጃዋር ሕጋዊ፣ ምርጫ ቦርድ ከልካይና ሕገወጥ ሆኖ እንዲሳል ለማድረግ ያሰበ የሞብ (የመንጋ) ጥሪ ይመስላል። ጋዜጠኛው ይህንን ጉዳይ ለሕዝብ የጠራ መግለጫ ለመስጠት ሲል ግልጥ አድርጎ ሊያብራራው በተገባ ነበር” ሲሉ አድርባይነት የታየበትን አዘጋገብ አጣጥለዋል።

“ፓስፖርቴን መልሻለሁ። በእኔ በኩል የሚጠበቀውን ጨርሻያለሁ። ምንም የሚያግደን ነገር የለም” ሲል ጃዋር በዚሁ በቢቢሲ አስተያየት መስጠቱ በራሱ በሪፖርቱ ላይ ጥያቄ የሚያስነሳ መሆኑንን ባለሙያው ጠቁመዋል። አስተያየታቸውን ሲያጠናክሩ “ጃዋር ቀደም ሲል የተዘለለችውን የማስረጃ ጉዳይ እንዲያጠራና እንዲመልስ በደንብ ቢጠይቅ፣ ማስረጃም ካለው እንዲያቀርብ ቢወተወት፣ ካላቀረበም ተጥይቆ በቃሉ ከመናገሩ ውጪ ማስረጃውን ለማሳየት ፈቃደኛ አለመሆኑ ተጠቅሶ ቢጻፍ፣ ዛሬ ጉዳዩ አጀንዳ ባልሆነ ነበር” ባይ ናቸው።

ለቪኦኤ ጥያቄ ምላሽ የሰጠው የአሜሪካ ኤምባሲ “የዜጎቻችን ጉዳይ ምሥጢር ነው። ይህንን መናገር የሚችለው ራሱ ግለሰቡ ብቻ ነው” ሲል ምላሽ መስጠቱ ጃዋር አሁንም የአሜሪካ ዜጋ መሆኑን ኤምባሲው በቀጥታ ሳይናገር አረጋግጧል። ሆኖም ግን የጃዋር ዜግነትን መመለስ ሂደት ተጀምሮም ከሆነ የት ደረጃ ላይ እንዳለ እንዲሁም ዜግነቱን ሲመልስ ከአሜሪካ የሚሰጠውን “Certificate of Loss of Nationality” (ዜግነትን የማጣት ሰርቲፊኬት) ስለመቀበል አለመቀበሉ የቢቢሲ ሪፖርት አቅራቢ ግንዛቤ ውስጥ ሳያስገባ መጠየቁ የብቃት ማነስ ብቻ ሳይሆን የጤና እንዳልሆነባቸው ባለሙያው አክለው ገልጸዋል። “ፓስፖርቴን መልሻለሁ” ማለቱ ብቻ ተቀባይነት እንዳለው መረጃ ሪፖርተሩ መቀበሉ የሚያጠያይቅ ብቻ ሳይሆን በሚዲያዎች የተንሸዋረረ አካሄድ ወደ ብሔር የመሳብ ጣጣ አደገኛነት ትልልቅ ሚዲያ በሚባሉትም ውስጥ ሰርጎ መግባቱ ለጊዜው ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉት ባለሙያ ተናግረዋል። በደፈና በተለያዩ ሚዲያዎች የሚተላለፉ ሪፖርቶች አሳፋሪ መሆናቸውንም አልሸሸጉም። በወገናዊነትና በግዴለሽነት የሚሠሩ ዘገባዎች ዞሮ ዞሮ አገሪቱን እንደሚጎዳት አለመረዳታቸውም ሌላው አሳፋሪና አሳዛኝ መሆኑን ጠቅሰዋል። 

በኦፌኮ ባልተለመደ ሁኔታ እርስ በርሱ የሚጣረስ መረጃ መውጣቱ ያሳሰባቸው ጃዋር ፓርቲውን እንዳይንጠው፣ ደጋፊዎቹን ሃይ ብሎ ፓርቲውን ለአደጋ እንዳይጥለው ፍርሃቻ አላቸው። የኦፌኮ ደጋፊዎች ዘንድ ይህ ስጋት መኖሩን የሚገልጸው የድርጅቱ መካከለኛ አመራር “እነ መረራ ከማይወጡት ቅርቃር ውስጥ ገብተዋል” ይላል።

“ገና ለገና ከፍተኛ ብር እንሰበስባለን፣ ድጋፍ እናገኛለን በሚል ስሌት ሕግ መጣስ ዋጋ እንደሚያስከፍል ገብቶኛል” የሚለው የኦፌኮ አባል “ጃዋር ማስረጃ ማቅረብ ሳይችል ቀርቶ ከድርጅቱ ከተሰናበተ፣ ዜግነት አልሰጥም ብለው ከምርጫ አገዱኝ በማለት ብጥብጥ ለማነሳት ከወዲሁ ፍንጭ አለ። ይህ አስጊ ነው። የደሃ ልጆችን ይቀጥፋል” ብሏል። አክሎም “እነ መረራ በዚህ በኩል ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል። በስማቸውም ሆነ በኦፌኮ ታሪክ ተሰምቶ የማያውቅ ደም እንዳይፈስ እጃቸውን እንዲሰበስቡ” መክሯል። “ጉዳዩ በፓርቲው የተለያዩ ቻፕተሮች መወያያ እንደሆነና ይህ ጉምጉምታ አድጎ ፓርቲውንም ለሁለት ሊሰነጥቀው ይችላል” ሲል ተናግሯል።

ባለፉት በርካታ ዓመታት እንደታየው ፓርቲዎች ባንድ ጉዳይ ላይ የተለያየና እርስበርሱ የሚጣረስ መግለጫ ማውጣት ሲጀምሩ የፍጻሜያቸው መጀመሪያ ከመሆን አልፎ ሲሰነጣጥቃቸው ቆይቷል። በአንድ ግለሰብ ጉዳይ ላይ በግልጽና በማያሻማ ሁኔታ ማንም ሊያስተውለው የሚችል የሕግ አሠራር ተቀምጦ እያለ ኦፌኮ በአራት ምላስ መናገር መጀመሩ ፍጻሜውን እያፋጠነ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት ተሰጥቶታል።

ጃዋር አሁን ያለ አንዳች ማስረጃ “ኢትዮጵያዊ ሆኛለሁ” ቢልም ከዚህ በፊት ግን በአሜሪካ በነበረበት ጊዜ በተጠራ ሰልፍ ላይ “ኢትዮጵያ ከኦሮሚያ ትውጣ” (Ethiopia out of Oromia) በማለት ባደባባይ ሲለፍፍ እንደነበር ይታወቃል።

ማምሻው (አርብ) የተላለፈው የአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ ዘገባ ላይ የኦፌኮው መሪ መረራ ጉዲና የጃዋርን ዜግነት አስመልክቶ ምርጫ ቦርድ ስለላከው ደብዳቤ ሲጠየቁ የመለሱት በተሰጠው ቀነገደብ ምላሽ እንደሚሰጡ ተናግረዋል። “አቶ ጃዋር ለምርጫ ቦርድ (የሚሰጠውን) መልስ እንዲያቀርብ ጠይቀነዋል፤ ሲያቀርብ ለምርጫ ቦርድ እናቀርባለን” ብለዋል። ጃዋር የሚያቀርበው ሕጋዊ ምላሽ አለመኖሩና የአሜሪካ ኤምባሲም በተዘዋዋሪ ዜጋችን ብሎ መጥቀሱ ኦፌኮ የጃዋር መልስ ምን ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ ያወቀውና በቀጣይ መወሰድ የሚገባው እርምጃ ምን እንደሆነ ግልጽ አድርጎታል። የፕሮፌሰር መረራ ምላሽም ፓርቲያቸው የሚሄድበትን አቅጣጫ የሚጠቁም ሲሆን አስቀድሞ ይህ ሊወሰንበት እንደሚችል የገመተው ጃዋር “የዜግነት መብቴን ተነፈግሁኝ” በሚል ሌላ ደም መፋሰስ በኦፌኮ ስም ይጭራል የሚለው ትኩረት የሳበ ጉዳይ ሆኗል።


ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ንብረት ናቸው። ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን።

   

Comments

  1. Shame on you!, Mr.Tourney Gemta.

Speak Your Mind

*