“ሥር ነቀል ለውጦች ብዙ ዋጋ አስከፍለውናል … ሀገር በድርድር ነው የሚገነባው”

ከውይይቱ ምን ይጠበቃል?

በሀገሪቱ የተፈጠሩ ተቃውሞና ግጭቶችን ተከትሎ አንጋፋዎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከገዥው ፓርቲ ጋር የድርድርና ውይይት መድረክ እንዲዘጋጅላቸው በተደጋጋሚ መወትወታቸው አይዘነጋም፡፡

የመጀመሪያው የድርድርና የውይይት መድረክም ባለፈው ሳምንት በፓርላማ ተካሂዷል። አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ውይይቶቹና ድርድሮቹ ለመገናኛ ብዙኃን ፍጆታ የሚውሉና የይስሙላ እንዳይሆኑ ስጋት ቢኖራቸውም አብዛኞቹ በመድረኩ መዘጋጀት ደስተኞች ናቸው። ውይይቱ በታቀደው መሰረት በተከታታይ የሚቀጥል ከሆነ፣ እያንዳንዱ ፓርቲ የውይይት አጀንዳዎቹን ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡

ለመሆኑ ተቃዋሚዎች ከኢህአዴግ/መንግስት ጋር መወያየት ያለባቸው በምን ጉዳዮች ላይ ነው? ሂደቱስ? ከውይይቱ ምን ይጠበቃል? ከተወያዮቹስ?

የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ በዚህ ዙሪያ የጦማሪያንን ሃሳብና አስተያየት እንደሚከተለው አጠናቅሯል፡፡

“የተቃዋሚዎችን የመደራደር አቅም እጠራጠራለሁ” አጥናፈ ብርሃኔ (ጦማሪ)

የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋትና ትንሽ መላወሻ ቦታ የሚያመጣ ከሆነ፣ ድርድሩን እንደ መልካም ውጤት አድርጌ ነው የምወስደው፡፡ አሁን የሚደራደሩት ፓርቲዎች ይሄን ለማድረግ ከቻሉ ትልቅ ነገር ነው፡፡

ኢህአዴግስ እውነት የሚያምንበትን ነው እያደረገ ያለው? በሚለው ላይ ጥርጣሬ አለኝ፡፡ ከዚህ ቀደም የተደረጉ ድርድሮች አሉ፡፡ የምርጫ ስነ ምግባርን በተመለከተ ድርድር ተደርጓል፡፡ ግን ምን ውጤት አመጣ? ያ ድርድር ለማን ነው የጠቀመው? ከዚያ ድርድር በኋላ በምርጫ ምን ውጤት መጣ? ይሄ መመርመር አለበት፡፡ ይህ የምርጫ ስነ ምግባር ድርድር ላልተደራደሩ ፓርቲዎች ማነቆ ሆኖ ነበር። ብዙ ተጎድተውበታል። ችግሮችን ሲፈጥርባቸው ነበር፡፡ አሁን ላይም ተቃዋሚዎቹ የመደራደር አቅማቸውን እጠራጠራለሁ፡፡ ከዚያ ውጪ ገዥው ፓርቲ እስካሁን ምንም አይነት መለሳለስ እያሳየ አለመሆኑ ሌላው ተግዳሮት ነው።

የአድርባይነት ስሜት የህዝብን አመኔታ የሸረሸረ በመሆኑ የገዥው ፓርቲ መጠቀሚያ እንዳይሆኑ ነው የምሰጋው፡፡ አቅም ኖሯቸው መደራደር ቢችሉ እንዲደራደሩባቸው ከሚያስፈልጉ ጉዳዮች ዋናው፡- ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ ጉዳይ፣ የፖለቲካ መጫወቻ ሜዳው መጥበብ፣ የፖለቲካ እስረኞች ጉዳይ ዋናዎቹ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ዶ/ር መረራን ጨምሮ በእስር ላይ የሚገኙ የመድረክ አመራሮች ካሉ፣ እነሱ መፈታት በሚችሉበት ጉዳይ ላይ መደራደር አለባቸው፡፡ በግሌ ውጤት ያመጣል ብዬ ባልጠብቅም ውጤቱን ከሂደቱ መጠበቅ አለብን፡፡

“ሀገር በድርድር ነው የሚገነባው” አቤል ዋበላ (ጦማሪ)

እንደ ሀገር ባለፉት ሁለት ስርአቶች የተፈፀሙ ስር ነቀል ለውጦች ብዙ ዋጋ አስከፍለውናል፡፡ ስር ነቀል ሲሆን ብዙ ነገር ወደ ኋላ ይመለሳል፡፡ አሁንም ቢሆን ስር ነቀል ለውጥ የሚታለም ከሆነ፣ ለህዝቡ የተሻለ ለውጥ ያመጣል ብዬ አላስብም፡፡ ያለውን ስርአት ለማስተካከል ንግግሩ መጀመሩ በራሱ ጥሩ ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡

ድርድር ሲባል የሚታወቀው በተመጣጣኝ ኃይሎች መካከል የሚደረግ ነገር ነው፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ እውነታ፣ ተቃዋሚው በመንግስት በደረሰበት ተደጋጋሚ ጫና በጣም ተዳክሞ ነው የሚገኘው፡፡ ድርድሩ የምር ችግር ፈቺ እንዲሆን ከተፈለገ፣ በተቃዋሚው ወገን ያለውን የኃይል መሳሳት የሚቀንስ መሆን አለበት፡፡ ተቃዋሚው እንደፈለገ ህዝቡን በዙሪያው እንዲያሰባስብ ክፍት መሆን አለበት፡፡ መሪዎቻቸው የታሰሩባቸው ፓርቲዎች አሉ፡፡ እነዚህ መሪዎቻቸው እንዲለቀቁላቸው ያስፈልጋል፡፡ ይህ ከሆነ ተቃዋሚዎችም በህዝብ ዘንድ ያላቸው አመኔታ ስለሚጨምር ድርድሩ አቅምና ውጤት እንዲሁም ተአማኒነት ይኖረዋል፡፡ ድርድራቸውን በሚዲያዎች አጠቃቀም፣ በፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ላይ ቢያደርጉ የበለጠ ውጤት ማምጣት ይቻላል፡፡

ኢህአዴግ ለፖለቲካ ትርፍ ሲል ብዙ ጥፋቶች ሰርቷል፡፡ አሁን ግን ስልጣንን የማዳን ሳይሆን ሀገርን የማዳን ስራ ነው መስራት ያለበት፡፡ ይህ ድርድር የዚህ አይነት ውጤት ይዞ መምጣት አለበት፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም እንደ ፊጋ በሬ ኢህአዴግን ሳያስደነግጡት፣ በአግባቡ በኃላፊነት ስሜት ሊደራደሩ ይገባል ብዬ አምናለሁ፡፡ ኢህአዴግም ይሄን እድል ማባከን የለበትም፡፡ ሀገር በድርድር ነው የሚገነባው፡፡

“ድርድሩ በቅንነትና በቁርጠኝነት መካሄድ አለበት” በላይ ማናዬ (ጦማሪና ጋዜጠኛ)

ድርድሩ ከልብ የሚካሄድ ከሆነ መልካም ነው። በተለያየ አጋጣሚ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችም ሆኑ ሌሎች በሃገራቸው ጉዳይ ይመለከተናል የሚሉ ሰዎች ሲጠይቁት የነበረው የነበረው ይሄንኑ የድርድና የውይይት መንገድ ነው፡፡ የጋራ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ከልብ መነጋገር፣ መደራደር በየትኛውም ሁኔታ የሚደገፍ ነው፡፡ እኔ በግልም በተደጋጋሚ በፅሁፎቼ ስጠይቅ የነበረው መነጋገር ወሳኝ እንደሆነ ነበር። ይሄ ድርድርና ውይይት ግን ቅንነት በተሞላበት መንገድ፣ በደንብ ችግሮችን እያነሱ በጥንቃቄ መካሄድ አለበት። እንዲሁ ለይስሙላ የአንድ ሰሞን ጫጫታ ብቻ ሆኖ እንዳያልፍ በአንክሮ መከታተል ያስፈልጋል፡፡

በዚህ ድርድር ላይ በተቃዋሚዎች ቢነሳ ብዬ የማስበው፣ በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት ለእስር ተዳርገውብናል ያሏቸው ሰዎች እንዲለቀቁ፣ የፓርቲ አመራሮች፣ ጋዜጠኞች፣ ብሎገሮች ታስረዋል፤ እነዚህ ተፈተው የድርድሩ አካል መሆን አለባቸው። በትክክል የድርድሩ አካል መሆን ያለባቸው የታሠሩ የፖለቲካ አመራሮች አሉ፤ እነሱ እንዲሳተፉ መጠየቅ አለባቸው፡፡

ሌላው ከህገ መንግስቱ ተፃራሪ ናቸው እየተባሉ በህግ ባለሙያዎች አስተያየት ይሰጥባቸው የነበሩ ህጎች ላይ ጠለቅ ያለ ድርድር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ አንዳንዶቹ በህግ ባለሙያዎች ተጠንተው ቢሰረዙ ምኞቴ ነው፡፡ ከኢህአዴግ ጋር በሚደረገው ድርድር ተቃዋሚዎች የህዝቡን ሃሳብና ስሜት በማንፀባረቅ ከልባቸው ሊሰሩ ይገባል ብዬ አምናለሁ፡፡ መንግስት ቁርጠኝነቱን እስከ መጨረሻው የሚቀጥል ከሆነ ጥሩ ነው፡፡ ግን በተደጋጋሚ ካየነው ልምድ ስንነሳ፣ ቁርጠኝነቱ እስከ ምን ድረስ ነው በሚለው ላይ ጥርጣሬ ያድርብኛል። ግን ካለመነጋገር መነጋገሩ የተሻለ በመሆኑ ጠንክሮ መደራደሩ የተቃዋሚዎች ሚና ነው ብዬ አምናለሁ። በሌላ በኩል በድርድሩ የተገለሉ የፖለቲካ ሃይሎች እንዳይኖሩ ቢደረግና ሁሉንም አካታች ቢሆን መልካም ውጤት ያመጣል፡፡

የህዝቡ ድምፅ በሙሉ እንዲሠማ ከተፈለገ፣ አሁን ካሉት ፓርቲዎች በተጨማሪ ሌሎች ያገባናል የሚሉም መካተት አለባቸው፡፡ በዚህ መንገድ የሚካሄድ ከሆነ፣ ድርድሩና ውይይቱ ውጤት ሊያመጣ ይችላል የሚል ተስፋ አለኝ፡፡

“በድርድሩ ሁሉም እኩል መሆን አለባቸው” ናትናኤል ፈለቀ (ጦማሪ)

በአንድ አካል መልካም ፍቃደኝነት ላይ የተመሰረተ፣ ሌሎች ደግሞ ተለማማጭ ሆነው የሚካሄድ ድርድር ትክክለኛ ውጤት አያስገኝም። ድርድር ከተባለ ሁሉም በእኩልነት መጥተው፣ ለሁሉም ምቹ የሆነ ውጤት እንዲኖረው ነው የሚፈለገው፡፡ ነገር ግን አንዱ የፈለገውን ማድረግ የሚችል፤ ሌሎቹ ደግሞ አሉ ለመባል ያህል የሚገቡበት ድርድር የአንደኛውን ወገን ብቻ ፍላጎት ይዞ እንደሚጠናቀቅ መተንበይ ቀላል ነው። እኔ ለምሳሌ “ከዚህ ድርድር መልካም ውጤት ትጠብቃለህ ወይ?” ብባል፣ እንድጠብቅ የሚያደርገኝ ነገር ስላላየሁ አልጠብቅም፡፡ ከዚህ በፊትም እንዲህ ያለው ነገር በተለያዩ ስሞችና ቅርፆች ተሞክሯል፤ ግን ምንም የተለየ ነገር አላመጣም፡፡ ይሄም ያመጣል ብዬ አልጠብቅም፡፡

በድርድሩ ለምሳሌ “ህገ መንግስቱ ይከበር” የሚባል ከሆነ ምንም አዲስ ነገር የለውም፡፡ ዋናው ተግባር ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ተደራድረው ቢለያዩ፣ አንደኛው ወገን ስልጣን ሁሉ በእጁ ያለ በመሆኑ ስምምነቱን እንደፈለገ ሊጠቀምበት ይችላል፡፡ ግን ድርድሩ የታሠሩ ፖለቲከኞች ይፈቱ፣ ሚዲያው ነፃ ይሁን፣ የፖለቲካ ስልጣን እንጋራ . . . ከሆነ ጥሩ ሊሆን ይችላል፡፡ ፓርቲዎቹ የምርጫ ስርአቱ ላይ ብቻ ተደራድረው ሊወጡም ይችላሉ፡፡ ይሄ ደግሞ ያን ያህል ውጤት የለውም፡፡ በየትኛውም ሥርዓት ውስጥ በሃቀኝነትና በቁርጠኝነት ከተሰራ ለውጥ ይመጣል፡፡ ስለዚህ መንግስት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ሊያደርግባቸው በሚገቡ ጉዳዮች ላይ አጠንክረው ቢደራደሩ ነው መልካም የሚሆነው፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ በፖለቲካ መሳተፍ አስፈሪ በሆነበት ሰዓት የተፈጠሩ ፓርቲዎች በመሆናቸው፣ይብዛም ይነስም በዚህ ድፍረት ውስጥ ያሉ ፓርቲዎችን ልናበረታታ ይገባል፡፡ ሌላ ወካይ እስከሌለ ድረስ ህዝቡን ወክለው መደራደር ይችላሉ የሚል እምነትም አለኝ፡፡

Comments

 1. Lusif says:

  First thing first. The ruling party has to honestly honor and respect human and political rights. It must be willing to abrogate all laws, rules and regulations that curtail free exercise of those rights. By doing that, all political prisoners will be set free.
  The ruling party needs to believe in a lawful democratic competitions, having in mind that there is another chance, a second chance.
  Currently, the trust between the government and the citizens is badly damaged. It is probable that peace can be maintained in the existing relationships and practices.
  Obviously, the oppositions have nothing to offer or to challenge or to force the ruling party to come to there terms. Since the relationship b/n the government and the citizens is in the worst shape, the oppositions may serve the ruling party as a safe haven to moderate/ smooth out the anger of the people.
  I do not blame those bloggers are ambivalent to trust the government. Time and time again, the ruling party breached its own promises and failed to deliver what it was supposed to deliver.
  I strongly believe, it is up to the ruling party to exonerate and prove itself that in this point in time, it is serious and it means honest business. The power, the choose and the ball is in the hands of the ruling party. If it plays by the rule and well there is always a chance for all of us to win some, to loss some. That way everybody would be comfortable with that he wins.
  The Ethiopian citizens have been with win – loss relationship with the ruling party thus far. That kind relationships have brought a lot of suffering to the greater majority of citizens. Winner take all relationship and practice need to ended. We all need a fair share, a fair shot. I guise, that is not much to ask, rather it is fair.

 2. Berhan Tamiru says:

  The whole idea that TPLF will negotiate in good faith is nothing but a mirage. There will never be a peaceful change in Ethiopia until TPLF accepts that the majority of the Ethiopian people had enough of their ethno-racist policy. Unless the fascist junta accepts the fact that most of the political parties which have been invited to this worthless meeting are nothing but puppets are not worthy of spending time with them. However, TPLF perfectly knows this, the whole strategy of this useless meeting is to buy time for TPLF nothing else. Genuine discussion can only be done with detained political activists, exiled political leaders and respected individuals in the auspicious of well respected organisations like the EEU. Unfortunately the AU has no any credibility to be invited at all. All political prisoners have to be released without any precondition, the state of emergency has to be lifted, freed media outlets should be allowed to operate without fear. That has to happen to build any confidence. Anything less than that is just nothing but a complete waste of time & we will continue fighting this regime until the end.

Speak Your Mind

*