መንግሥትና ኦዲፒ የጃዋርን የድጎማ በጀት ጥያቄ ውድቅ አደረጉ

የኦሮሞ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ሥራ አስኪያጅና ባለቤት ጃዋር መሃመድ ለድርጅቱ በጀት እንዲመደብና በቋሚነት እንዲረዳ ለመንግሥት ያቀረበው ጥያቄ ውድቅ መደረጉ ታወቀ። የጎልጉል የኦዲፒ የመረጃ ምንጮች እንዳሉት የድጎማ ጥያቄው ውድቅ መደረጉ ጃዋር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይና በኦዲፒ ላይ የጥላቻ ሪፖርት ተጠናክሮ እንደሚሠራ መናገራቸውን አመልክተዋል። በተያያዘ ጃዋር የሚመራው ኦ.ኤም.ኤን. ለሸዋ ተወላጅ ኦሮሞዎች መድረክ እንደማይሰጥና ኦነግ በንጹሃን ላይ እየፈጸመ ያለውን ግድያም ሽፋን እንዲሰጥ እንደማይፈቅድ ተገልጿል።

እንደ መረጃ አቀባዮቹ ከሆነ ጃዋር ለሚመራው “የትግል ሚዲያ” ከፍተኛ በጀት የጠየቀው ሚዲያው ለተገኘው ለውጥ ትልቁን ሚና ተጫውቷል በሚል ነው። ኦ.ኤም.ኤን. በትግሉ ወቅት የአንበሳውን ድርሻ በመጫወቱ የኦሮሚያ ክልልም ሆነ መንግሥት ሊደጉመው እንደሚገባ በተደጋጋሚ ያቀረበው ጥያቄ ውድቅ የተደረገው በሥራ አስፈጻሚ ውሳኔ ነው።

ጃዋር ድጎማው እንደማይሰጠው ከተገለጸለት በኋላ በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ላይ ያነጣጠረ ዘመቻ በስፋት የአየር ሰዓት እንዲያገኝ ትዕዛዝ መስጠቱን ኦ.ኤም.ኤን. የሚሠሩ እንደነገሯቸው የመረጃው ክፍሎች ለጎልጉል የአዲስ አበባ ዘጋቢ አስታውቀዋል።

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዓለም ሰላም የኖቤል ተሸላሚ መሆናቸው ይፋ መሆኑንን ተከትሎ የዓለም ሚዲያ ሰፊ ሽፋን ቢሰጡትም ኦ.ኤም.ኤን. ግን ቀዳሚ ዜና እንኳን ያላደረገው በዚሁ ምክንያት እንደሆነ ታውቋል። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ታላቅ ሽልማት አስመልክቶ በተለያዩ የኦሮሚያና የክልል ከተሞች የተደረገውን የድጋፍና የደስታ መግለጫ ሰልፍ ኦ.ኤም.ኤን. በተመሳሳይ የሚገባውን ሽፋን እንዳልሰጠው መረጃ የሰጡት ክፍሎች ገልጸዋል። በዚህ ጉዳይ ላይ በማኅበራዊ ሚዲያም ጃዋር መሃመድ በስፋት ሲወገዝ ተሰምቷል።

ጃዋር በፌስቡክ ገጹ የእንኳን ደስ አለህ አጭር መልዕክት ከመለጠፉ በዘለለ የተገኘውን ዜና ሁሉ “ሰበር” ለማለት የማያቅማማው ኦ.ኤም.ኤን. ለዜናው ጆሮ ዳባ ማለቱ በተለያዩ የኦሮሞ ተወላጆች ዘንድ ጉምጉምታ እንደፈጠረ ጎልጉል ያናገራቸው አስረድተዋል።

ኦ.ኤም.ኤን. አገር ውስጥ በአንድ ጎረምሣ ስም ተመዝግቦ የሚሠራ ተቋም ሲሆን የድርጅቱ ገንዘብም በዚሁ ወጣት ስም በተከፈተ አካውንት እንደሚንቀሳቀስ የሚዲያው ምንጮች ይናገራሉ። ጃዋር በዜግነት ኢትዮጵያዊ ባለመሆኑ አንድ በገንዘቡ ላይ እንደፈለገ እንዲናኝ የተፈቀደለት ወጣት መሰየሙን የገለጹት ምንጮች ኦ.ኤም.ኤን. ነጻነት የሌለበት፣ ገቢና ውጪው የፋይናንስ ደንብን በአግባቡ የማይከተል ድርጅት እንደሆነ ጠቁመዋል።

ከወራት በፊት ራሳቸውን በዩቲዩብ ይፋ ያደረጉ ይህንኑ የተዝረከረከና አንድ ሰው እንዳሻው ለፈለገው ተግባር የሚጠቀምበት ሚዲያ ወደ ህግ ለማቅረብ እንደሚሠሩ መናገራቸው የሚታወስ ነው።

በሚሊዮን ብሮች የሚገመቱ እጅግ ዘመናዊ ተሽከርካሪዎችን የሚሸምተውና “ቱጃር” የሚባለው ጃዋር መሃመድ አቋሙን ግልጽ አድርጎ ወደ ፖለቲካ የማይገባው በዚሁ የሚዲያ ነጋዴነት ለመቀጠል ሲል የቀድሞ የቦርድ አባላትን ማሰናበቱን የሚገልጸው የኦ.ኤም.ኤን. ባልደረባ “ጃዋር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ላይ አነጣጥረው ዘመቻ ለሚያካሂዱ የሚዲያ አውታሮችና የፌስቡክ አርበኞች ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ድጋፍ የማድረግ ዕቅድ መንደፉን አስቀድሜ አውቃለሁ” ሲል ተናግሯል። ይሁን እንጂ እነማን እንደሆኑ የሚዲያ አውታሮቹን በስም አልጠራም። ከዕቅዱ ሌላ አንዳንዶቹን በድብቅ ቀጥተኛ ድጋፍ እያደረገላቸው እንዳለ ይነገራል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ኦነግ-ሸኔ ባለፈው ቅዳሜ በምስራቅ ጉጂ ዞን ስለገደላቸው ስድስት ንጹሃን ዜጎች ኦ.ኤም.ኤን. ዘገባ አላቀረበም። አባቱ የተገደሉበት ሀጻን “አባቴ ገጠር ካለው ቤቱ ለሥራ ሄዶ ቁርስ እየበላ ሳለ የኦነግ ታጣቂዎች ገብተው ገድለውት ሄዱ” ሲል ለአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ (ቪ.ኦ.ኤ.) ቢናገርም ለኦ.ኤም.ኤን. የዜና ፍጆታ ብቁ አለመሆኑ በኦሮሞዎችም ሆኑ በሰላም ወዳድ ዜጎች መነጋገሪያ መሆኑ ታውቋል።

የኦ.ኤም.ኤን. ባለቤት ጃዋር መሃመድ የቅማንት ዜና ላይ ሙጥኝ በማለት የህወሓት አጀንዳ አስፈጻሚ መሆኑና ዘንድ “እረኛውን ግደል፣ መንጋው ይበተናል” የሚለውን የዲጂታል ወያኔ ዓላማ መደገፉ፣ ዝምታን በመረጡት አብዛኛው የኦሮሞ ተወላጆና ነዋሪዎች ዘንድ እየተብሰለሰለ ያለ ጉዳይ እንደሆነ በርካቶች እየተናገሩ ነው።

ጃዋር የአሜሪካ ዜግነቱን እንደሚመልስ (ቀድጄ እጥለዋለሁ እስከማለት) በተደጋጋሚ ቢናገርም እስካሁን እርሱም ሆነ ቤተሰቡ የሚታወቁት በአሜሪካ ዜግነት ነው። በአሜሪካ አገር የተከፈተው ኦ.ኤም.ኤን. በሕግ የተመዘገበው በትርፍ አልባ ድርጅት ስም ሲሆን እኤአ ከ2014 እስከ 2017 አምኖ ለአሜሪካ መንግሥት ሪፖርት ያደረገው የድርጅቱ አጠቃላይ ገቢ ከ2.8 ሚሊየን ዶላር በላይ (በብር እስከ 100 ሚሊየን) ነው። ይህ የ2018 ዓም የድርጅቱን ገቢውን ሳይጨምር ነው።

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ የኦ.ኤም.ኤን. የቀድሞ የቦርድ አባልትም ሆኑ መረጃ ያላቸው ወገኖች አስተያየት መስጠት ከፈለጉ ለማስተናገድ ዝግጁ ነው። ጃዋርን በስልክ ለማግኘት የአዲስ አበባ ዘጋቢያችን ሙከራ ቢያደርግም ሊሳካለት አልቻለም።

በተያያዘ ዜና በምን ምክንያት እንደሆነ በውል ባይታወቅም ቀደም ሲል የኦነግ-ሸኔ ወታደሮችን ጫካ ድረስ እየሄዱ ሲያደራድሩና ሲያስማሙ የነበሩት እንዲሁም ወደ ካምፕ እንዲገቡ በማድረጉ ውስጥ ቀዳሚ የነበሩት በቀለ ገርባ በቅርቡ ኢትዮ ፎረም ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ “ሸኔ የሚባል ቡድን የለም” ሲሉ ተደምጠዋል።


ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ንብረት ናቸው። ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን።

Speak Your Mind

*