“ሙዚቃ መምራትን ለዓለም ያስተዋወቀችው ኢትዮጵያ ናት”

የኢትዮ ጃዝ ፈጣሪ ሙላቱ አስታጥቄ

ሙዚቃን በተለየ መንገድ በማዋሐድ ሙላቱ አስታጥቄ የሙዚቃ ሳይንቲስት መሆኑን በአምስት አሠርታት የሙዚቃ ጉዞው ውስጥ አስመስክሯል፡፡ የተለያዩ ቅላፄዎችንና ምቶችን ከተለያዩ አፍሪካ አገሮች፣ አሜሪካና አውሮፓ ሙዚቃ በመውሰድና በማጣመር አዲስ የሆነ ሙዚቃንም ለዓለም አበርክቷል፡፡ የኢትዮ ጃዝ ፈጣሪው ሙላቱ አስታጥቄ የሙዚቃ ትምህርቱን ያጠናው በለንደን፣ ኒውዮርክና ቦስተን ከተሞች ሲሆን፣ የራሱን የሆነ የሙዚቃ ስልት ከኢትዮጵያ የሙዚቃ ቅኝቶች ጋር አጣምሮ ኢትዮ ጃዝን ፈጥሯል፡፡ በቀላሉ በዓለም አቀፍ ሙዚቃ አፍቃሪዎች ዘንድ ጆሮ ማግኘት የቻለው ሙላቱ ከመቶ ሺሕ በላይ የሚሆኑ ታዳሚዎችም ኮንሠርቱን ለማየት መሽቀዳደም የተለመደ ሆኗል፡፡ ከሙዚቃ ክህሎቱም በተጨማሪ በጥንታዊ ሙዚቃዎች ላይ ፈር ቀዳጅ የሆኑ ምርምሮችንም በማካሄድ ነው፡፡ የአምስት አሠርታት የሙዚቃ ጉዞውንም በተመለከተ ከሪፖርተሩ ጥበበሥላሴ ጥጋቡ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ ከነበረው የአውሮፓ የሙዚቃ ጉዞ እንጀምር እንዴት ነበር? ምን ያህል ኮንሠርቶችንስ አደረግክ?
አቶ ሙላቱ፡- ወደ ሃያ ያህል ኮንሠርቶችን አቅርቤያለሁ፤ የሚገርመው የእነዚህ ኮንሠርቶች የቲኬት ሽያጭ ቀድሞ ነው ያለቀው፡፡ በጣም አስገራሚ ነው፡፡ ከመቶ ሃያ ሺሕ ሕዝብ በላይ በተገኙባቸው ቦታዎች ላይ ዘፈኖቼን አቅርቤያለሁ፡፡ መድረክ ላይ ሆኜ አንዳንድ ጊዜ የሕዝቡን ብዛት በምመለከትበት ሰዓት ይኼ ሁሉ የእኔን ሙዚቃ ለመስማት ነው ብዬ ማመን ከብዶኝ ነበር፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ የማልጠብቃቸው ሰዎች ኢትዮ ጃዝን ለመስማት ሲመጡ ማየት ከአስገራሚም በላይ ነው፡፡ ለምሳሌ ብራዚል ኮንሠርት በነበረኝ ወቅት ፋቪላ ከሚባለው፣ በአደገኛነቱ ከሚጠራውና ከተጨናነቁ መንደሮች የመጡ ከሃያ ሺሕ በላይ ታዳሚዎች ተገኝተው ማየት አስደናቂ ነው፡፡ ከአደገኛ ዕፆች ጋር ተያይዞ ስማቸው ስለሚነሳ ከኮንሠርቱ በኋላ ሊያቅፉኝ ሲመጡ ትንሽ ተረብሻለሁ (ሳቅ)፡፡ ሰውነታቸው በንቅሳት የተሸፈኑና አስፈሪ የሚመስሉ ታዳሚዎች ሙዚቃዬን እየሰሙ ስሜን እየጠሩ ማየት የማይታመን ነበር፡፡ እነዚህ ሁሉ ኮንሠርቶች ለኔ ኃይል ይፈጥሩልኛል፣ ጠንክሬም እንድሠራ ያደርጉኛል፡፡ በዚህ ሁሉ መካከል ግን ምንጊዜም ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ባለውለታ የሆኑትን የኢትዮጵያ የሙዚቃ መሣሪያዎች ፈጣሪዎች፣ የቅኝቶቹን ጀማሪዎች ታላቅነታቸው ሳላስታውስና ሳላደንቅ አላልፍም፡፡Mulatu-Astatke

ሪፖርተር፡- ከኢትዮጵያ የባህል ሙዚቃ መሣሪያዎችና የኢትዮጵያን የሙዚቃ ቅኝቶች ጋር በተያያዘ የምርምር ሥራዎች እያካሄድክ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ስለሱ ጉዳይ በበለጠ ብትነግረን፣ ፍላጎቱስ የመነጨው ከምንድን ነው?
አቶ ሙላቱ፡- በእውነቱ ከሆነ ፍላጎቱ የመጣው ለራሴ የቅኝቶቹን መነሻ ለማወቅ ከመፈለግ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ሙዚቃ መሠረት የሆኑትን አራቱን ቅኝቶች ማለትም አምባሰል፣ ባቲ፣ አንቺሆዬና ትዝታን ስለፈጠራቸው አካል የሚያትት ምንም ዓይነት የምርምር ጽሑፍ የለም፡፡ በጣም የሚያሳፍር ነው፡፡ ምንም እንኳን አብዛኛው ሕዝብ እነዚህን ቅኝቶች እያደመጠ፣ በእነዚህ ቅኝቶች እየተደሰተ ለዘመናት ቢቆይም ምንጫቸው የት እንደሆነ የሚያመላክት ሥራ የለም፡፡ አንዳንድ የሙዚቃ ባለሙያዎች ከቅዱስ ያሬድ የዜማ ስልቶች ማለትም ግዕዝ፣ ዕዝልና አራራይ ጋር ሊያገናኟቸው የሚሞክሩ አሉ፡፡ ለእኔ ግን የቤተ ክርስቲያን ዜማዎች ራሳቸውን ችለው የሚሄዱ ሲሆኑ እነዚህ ቅኝቶች ግን የተለዩ ናቸው፡፡ የምርምር ሥራዎች እጥረትና የዕውቀት ማነስ በቅኝቶች ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ የሙዚቃ ባህል መሣሪያዎች ላይም ይታያል፡፡ እንደነ ክራር፣ ማሲንቆ በገና ያሉትን የባህል የሙዚቃ መሣሪያዎች ማን እንደሠራቸው የሚጠቁም መረጃ የለም፡፡ በዓለም አቀፍ ዘንድ ታዋቂ ሙዚቀኛ የሆነችው ቢዮንሴ እስክስታን፣ እንዲሁም ከጉሙዝ ማኅበረሰብ አንዳንድ እንቅስቃሴዎችን ወስዳለች፡፡ ብዙዎች ራሷ ያመጣችው ይመስላቸዋል፡፡ ዕውነታው ግን ሌላ ነው፡፡ ሰፋ ባለ መልኩ ብንመለከተው ይኼ ሁኔታ የሚያሳየው ስለ ጥበብና ባህል ቦታ እንደማንሰጥ ነው፡፡ በአንዳንድ አጋጣሚዎች የተለያዩ የባህል ሙዚቃዎችን አዳዲስ ቀለም ሰጥተዋቸው ሲዘፍኑ እሰማለሁ፡፡ አርቲስቶቹ ማንኛውንም ሙዚቃ በፈለጉት መልኩ የመዝፈን ነፃነታቸው እንዳለ ሆኖ ቱባው የሙዚቃው መሠረት እንዳይበላሽ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አካሄድ የሚያሳየው የሙዚቃው ስረ መሠረቱ መዘንጋቱን ነው፡፡ በሚያሳዝን መልኩ እነዚህ ሙዚቃዎች ኋላቀር በመባልም ይጠራሉ፡፡ የኢትዮጵያ የሙዚቃ መሣሪያዎችን በምንመለከትበት ጊዜ ማሲንቆ የምዕራባውያኑን ቼሎ፤ በምዕራብ አካባቢ የሚጫወቱበት የሙዚቃ መሣሪያ ዙምባራ፣ ከትሮምቦን እንዲሁም ዋሽንት ከፍሉት ጋር ተመሳሳይነት አላቸው፡፡ እነዚህ የሙዚቃ መሣሪያዎች ጥንታዊና ከምዕራባውያኑም የሙዚቃ መሣሪያዎች ይቀድማሉ፡፡ ለዚህም ነው የኢትዮጵያ የባህል ሙዚቃ መሣሪያ ፈጣሪዎች ሳይንቲስቶች ናቸው የምለው፡፡

ሪፖርተር፡- በማሳቹስተስ ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ የምርምር ሥራህም ከኢትዮጵያ የባህል የሙዚቃ ሥራ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በምን ሁኔታ እየተካሄደ ነው?
አቶ ሙላቱ፡- ከኢትዮ ጃዝ በዓለም አቀፍ ዘንድ ታዋቂነቱ ከመጨመር ጋር ተያይዞ ብዙ የሙዚቃ ጉዞዎችን እያደረግኩ ስለሆነ ትንሽ የምርምር ሥራውን ለጊዜው ወደጎን ትቸዋለሁ፡፡ በቅርብ ግን እመለስበታለሁ፡፡ እስካሁን በነበረው ቆይታዬ የባህል የሙዚቃ መሣሪያዎችን ከማሻሻልና ከማሳደግ ጋር የተያያዙ ሥራዎችን ሠርቼያለሁ፡፡ የመጀመሪያ ሥራዬ የነበረው ክራር ላይ ሲሆን፣ የጃዝ ስታንዳርድ ቅላፄዎችን ክራር እንዲጫወት አስችያለሁ፡፡ እነዚህ ቅላፄዎች ከአራቱ የኢትዮጵያ ቅኝቶች ውጭ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ የሙዚቃ መሣሪያዎች ሲሻሻሉ ወይም ሲያድጉ የሙዚቃችን ሳይንቲስቶች የሆኑት አዝማሪዎችም የዕድገቱ አካል ይሆናሉ፡፡ ከክራር መሻሻልም ጋር ተያይዞ አዝማሪዎች ከለመዱት የሙዚቃ ቅላፄዎች (ኖትስ) ወጥተው በአሥራ ሁለት ቅላፄዎች (ኖትስ) MulatuAstatkeandThe-Heliocentricsእንዲሞክሩ በር ከፋች ነው፡፡ “ብሪንጊንግ አዝማሪስ ቱ ቲዌንቲ ፈርስት ሴንቸሪ” (አዝማሪዎችን ወደ ሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ማምጣት) የሚለውም ፕሮጀክቴ ከዚህ ዓላማ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ እኔ እንደማምነው ክራር ጊታር ሊሠራው የሚችለውን ሁሉ መሥራት ይችላል፡፡ ይኼ የሚሆነው ግን ጊዜ ተወስዶበት ዕድገቱ ላይ ሲሠራ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ጠለቅ ያሉና ጠንካራ ሐሳቦችን ስለሰበሰብኩ ወደ ምርምሩ በምመለስበት ጊዜ የበለጠ ጥሩ ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- እነዚህ የሙዚቃ መሣሪያዎች እስካሁን ያልተሻሻሉበት ምክንያት ምንድነው?
አቶ ሙላቱ፡- ይኼንን መመለስ ይከብዳል፡፡ እንደማየው ግን ከሙዚቀኞቹ ወይም ከሙዚቃ ባለሙያተኞች ፍላጎት ጋር ተያይዞ ይመስለኛል፡፡ የሙዚቃ ባለሙያተኞቹ ምርምራቸውን አጠናክረው መሥራትና ሙዚቃውን ወደ ቀጣዩ ደረጃ ለማሳደግ ፍላጎት ስለሌለ ይመስለኛል፡፡ ይኼ ለኔ ህልሜ ነው፣ ለማሻሻልም ሞክሬም ተሳክቶልኛል፡፡ ወደ ኤምአይቲም (ማሳቹሴትስ ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ) ተመልሼ እቀጥልበታለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮ ጃዝ የሙዚቃ ስልት ዝና በዓለም ደረጃ እየናኘ ያለበት ወቅት ነው፡፡ በዓለም ላይ ስመ ጥር የሆኑት ዘፋኞች እንደነ ካንዬ ዌስት፣ ናስና ዴሚየን ማርሌይ ሥራዎችህን ቀንጭበው ተጠቅመውበታል፡፡ ኢትዮ ጃዝ እዚህ ደረጃ ላይ ይደርሳል ብለህ አስበህ ታውቃለህ?
አቶ ሙላቱ፡- ኢትዮ ጃዝን ስፈጥር ዋናው ዓላማዬ የነበረው የኢትዮጵያ የሙዚቃ አስተዋጽኦን በዓለም ዘንድ ለማሳየት ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢትዮ ጃዝ የተፈጠረበትን ሃምሳ ሁለተኛ ዓመት ክብረ በዓል ለማክበር በዝግጅት ላይ ነን፡፡ በአምስት አሠርታት ውስጥ ኢትዮ ጃዝ እንደ ሬጌ፣ ብሉዝ፣ የመሳሰሉት የሙዚቃ ስልቶች የደረሱበት ደረጃ መድረስ ችሏል፡፡ ብዙ ከፍተኛ የሆኑ ሽልማቶችን አግኝቼበታለሁ፡፡ በመላው ዓለም ኢትዮ ጃዝን እንደ ሙዚቃ ስልት አድርገው የሚዘፍኑ ባንዶችን በኒውዮርክ፣ በእንግሊዝ፣ በጀርመን፣ በእንግሊዝ አግኝቻለሁ፡፡ ኢትዮጵያም ውስጥ የኢትዮ ጃዝ ሙዚቀኞች ቁጥር እየተበራከተ ነው፡፡ በበርክሌይ Mulatu_Astatkeየክብር ዶክትሬት ያገኘሁት “ዩር ኮንትሪብሽን ቱ ዘ ወርልድ ሚዩዚክ ኢንደስትሪ” (ለዓለም አቀፉ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ላደረግከው አስተዋጽኦ በሚል ነው፡፡ እዚህ ደረጃ በመድረሱም ደስታዬ ከፍ ያለ ነው፡፡ ይኼን ሁሉ ስመለከት ኢትዮ ጃዝ የተጠነሰሰበትን ኒውዮርክን ያስታውሰኛል፡፡ ለዛም ነው ክብረ በዓሉን ኒውዮርክ ለማድረግ ያሰብነው፡፡ በዚህ ዓመት በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች የሙዚቃ ዝግጅቶች አለኝ፤ እንግዲህ ካሰብነው ጊዜ ጋር ከተገጣጠመ ክብረ በዓሉንም በአጋጣሚው እናደርገዋለን፡፡ ምንም እንኳን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ቢያገኝም በመጀመሪያው ወቅት አስቸጋሪ ጉዳዮች ኢትዮጵያ ውስጥ አጋጥመውኛል፡፡ በአምባሳደር ቴአትር በገናን፣ ፒያኖና እንዲሁም በሌሎች የሙዚቃ መሣሪያዎች የታጀበ “ዴይስ ኦፍ ሜሎዲስ” በሚል ሥራዬን አቀረብኩ፡፡ ብዙዎች ተቃውሟቸውን በጩኸት የገለጹበትና ከመድረኩ ውረድም ተብያለሁ፡፡ ተቃውሟቸው ብዙ ጊዜ ከመንፈሳዊ ዝማሬ ጋር ተያይዞ የሚጠቀሙበትን በገናን ከሌሎች የሙዚቃ መሣሪያዎች ጋር አጣምሬ በመጫወቴ ወይም ሙዚቃዬ ስላልገባቸው ይሆናል፡፡ ሆነም ቀረም ብዙዎች አልተቀበሉትም ነበር፡፡ ከነበረው ተቃውሞ አንጻር ሕዝቡ ሙዚቃዬን አልወደደውም ብሎ ማቆም ይቻል ነበር፡፡ እኔ ግን ይኼ አጋጣሚ የተለየ ኃይል ሰጠኝ፤ የበለጠም ጠንክሬ እንድሠራና ገፍቼ እንድሄድ አደረገኝ፡፡ በተቃራኒው ደግሞ አሜሪካውያንና አውሮፓውያን እንዲሁም በዓለም ላይ የሙዚቃ አፍቃሪዎች አዕምሮዎቻቸውን ክፍት አድርገው መቀበላቸው አበረታች ነበር፡፡ በመላው ዓለም አድናቂዎችን አፍርቼያለሁ፡፡ በቅርቡም የሙዚቃ ሥራዬን እንዳቀርብ ኢራን ተጋብዤያለሁ፡፡ እስቲ አስቡት ኢራን የሙዚቃ ኮንሠርት ማቅረብን፣ ሙዚቃዬንም እንደሚወዱ ሰምቼያለሁ፡፡ በቅርቡ በነበረኝ የሞስኮ ኮንሠርትም ብዙዎች በደስታ ሲዘሉ አይቻለሁ፡፡ ይኼ ኮንሠርት ከታዋቂው የአሜሪካ ሂፕ ሆፕ አርቲስት ታሊብ ክዌሊ ጋር ተጣምሬ የሠራሁበት ነው፡፡ አጠቃላይ ሁኔታው ከመጠን በላይ አስደሳች ነው፤ በዓለም አቀፍ ዘንድ ኢትዮ ጃዝ ውበት በተሞላበት መልኩ ተሠራጭቷል፡፡

ሪፖርተር፡- “የገሌ ትዝታ”፣ “የከርሞ ሰው” እና “ጉብልዬ” የተባሉት ሥራዎችህ በኦስካር ዕጩ ለነበረው “ብሮክን ፍላወርስ” ለሚለው ፊልም ማጀቢያ መሆናቸው ታዋቂነትህን ጨምሮታል ትላለህ?
አቶ ሙላቱ፡- ኢትዮ ጃዝ በኒውዮርክ ከመጀመርያው ጀምሮ ተቀባይነትን እንዲሁም ታዋቂነትን mulatu brokenአግኝቷል፡፡ በሌላው ዓለም ዘንድ “ብሮክን ፍላወርስ” ሰፋ ያለ አድማጭ እንዳገኝ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ በአሁኑ ወቅት አስደሳችና አስገራሚ ነገሮች እየተፈጠሩ ነው፡፡ ከተለያዩ ሙዚቀኞች ጋር ተጣምሬ የምሠራበትም ብዙ አጋጣሚ አለ፡፡ በቅርቡ ለንደን ውስጥ ብራዚል ውስጥ ታዋቂ ከሆነ ራፕ አርቲስት ክሪዮሎ ጋር የሠራነው ዝግጅት አስደማሚ ነበር፡፡ በየትኛውም ቦታዎች የታዳሚው ቁጥር እየጨመረ እስከ መቶ አርባ ሺሕ በላይ ታዳሚዎች የሚገኙበት አጋጣሚም አለ፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህ ደረጃ ታዋቂ መሆን ምን ዓይነት ስሜት አለው?
አቶ ሙላቱ፡- ኢትዮጵያ የት እንደምትገኝ የማያውቁ፣ ነገር ግን ኢትዮ ጃዝ ሙዚቃን የሚያደንቁ ሰዎች በሙዚቃዬ አገሪቷን ሲያውቁ በጣም ኩራት ይሰማኛል፡፡ ኢትዮ ጃዝ እዚህ ደረጃ ይደርሳል ብዬ አላሰብኩም፡፡ ነገር ግን በዓለም አቀፍ ያሉ ሙዚቃዬ የገባቸው አድማጮች ድጋፍና ፍቅር እዚህ አድርሶኛል፡፡ ድጋፋቸውን ይቀጥላሉ የሚልም ተስፋ አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ከዓመታት በኋላ በደራሼ ማኅበረሰብ ሙዚቃ እንዲሁም የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ዜማዎች ላይ ተመሥርተህ ሙዚቃዎችን ሠርተሃል፡፡ ኢትዮ ጃዝን ስትፈጥር መነሻ ያደረግከው ምን ነበር?
አቶ ሙላቱ፡- ከአምስት አሠርታት በፊት ብዙ ሙከራዎች ያደረግኩት በአራቱ ቅኝቶች ላይ ነው፡፡ የሙዚቃ ትምህርቴን በርክሌይ ዩኒቨርሲቲ በምከታተልበት ወቅት “ራሳችሁን ሁኑ” እያለ የሚመክረን አንድ ፕሮፌሰር ነበር፡፡ በዚያን ወቅት ታላላቅ የሚባሉ ሙዚቀኞችን እንደነ ኮልትሬን፣ ማይልስ ዴቪስና ኩዩንሲ ጆንስ ሥራዎችን በጥልቀት የምንመረምርበት ወቅት ነበር፡፡ የፕሮፌሰሩም አባባል ጥያቄ ይፈጥርብኝ ጀመር፡፡ እነዚህ ታላላቅ ሙዚቀኞች ራሳቸውን እንዴት ሆኑ? አፍሪካ አሜሪካዊው ሙዚቀኛ ኮልትሬን እንዴት ታላቅ ሆነ? እኔም እንደሱ አዕምሮ አለኝ፡፡ ታላቅ የማልሆንበት ምክንያት ምንድነው? በማለት ራሴን በመጠየቅ የፕሮፌሰሩን ምክር ተግባራዊ አደረግኩ፡፡ ኢትዮ ጃዝንም ስፈጥር የራሴን የሆነ የተለየ የሙዚቃ አካሄድ ተከተልኩ፡፡ የሙዚቃ ጉዞዬም አምስት የሙዚቃ ቅላፄዎችን ከአሥራ ሁለት የሙዚቃ ቅላፄዎች ጋር ማጣመር ነበር፡፡ በእውነቱ ከሆነ ሁለቱ ሳይቃረኑ ተዋሕደው እንዲሄዱ ማድረግ ከባድ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ነው ረዥም ጊዜ የወሰደብኝ፡፡ ምንም እንኳን አስቸጋሪ ቢሆንም የሁለቱን ድብልቅ ጥሩ ዉሕደት መፍጠር ችያለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ሁለቱን የሙዚቃ ቅላፄዎች (ኖትስ) ለማዋሐድ ከባዱ ፈተና ምንድን ነው?
አቶ ሙላቱ፡- ዋናው ሥራ አምስቱን ቅላፄዎች ከአሥራ ሁለቱ ቅላፄዎች ጋር ማጣመር ብቻ አይደለም፤ አብረው ሊሄዱ የሚችሉበትን ዉሕደት መፍጠር ነው፡፡ ይኼንንም ማድረግ ችያለሁ፡፡ በመጀመሪያዎቹ አካባቢዎች ሙዚቃዬን የሰሙ ሰዎች የላቲን ሙዚቃ ነው ወይ በማለት አስተያየት ይሰጡ ነበር፡፡ ለኔ የላቲን ሙዚቃ መነሻው አፍሪካ ነው፡፡ በላቲን ማኅበረሰብ ዘንድ ታዋቂ የሆኑት ቻቻና ሩምባ የተባሉት የሙዚቃ ስልቶች በደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢ ይገኛሉ፡፡ ብዙ የሙዚቃ ስልቶች ከአፍሪካ ተወስደው የተለያዩ ቅላፄዎች ተጨምረውባቸዋል፡፡ የላቲን ጃዝም አመጣጡ ከዚሁ መሠረት ጋር በተያያዘ ነው፡፡ በኪዩባና በሜክሲኮ በተጫወትኩበትም ጊዜ እነዚህ ምቶች ከአፍሪካ እንደተወሰዱ ተናግሬያለሁ፡፡ የእነሱ ብቻ ሙዚቃ ሳይሆን ኢትዮ ጃዝም የዓለም ሙዚቃዎች ጥምረት ነው፡፡ ምንም እንኳን ይኼ ቢሆንም ግልፅ መሆን ያለበት የኢትዮጵያ ቅኝቶች ምንጊዜም ከላይ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት የዓለም ሙዚቃ (ወርልድ ሚዩዚክ) የሚል ዘርፍ ፈጥረዋል፡፡ ወደ እኔም መጥተውም በጠየቁኝ ጊዜ የገለጽኩላቸው የዓለም ሙዚቃን ከሃምሳ ሁለት ዓመት በፊት መጀመሬን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮ ጃዝ የሚለው ስም በቅፅበት ነው የመጣልህ?
አቶ ሙላቱ፡- በመጀመርያ አፍሮ ላቲን ሶውል የሚል ስያሜ ነበር የሰጠሁት፡፡ ያለውን የሙዚቃ ይዘት ካየሁ በኋላ ነው “ኢትዮ ጃዝ” የሚል መጠሪያ የሰጠሁት፡፡

ሪፖርተር፡- የደራሼ ማኅበረሰብ ሙዚቃና የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ዜማዎችን እንድትመራመር ያነሳሳህ ምንድነው? የጀመርክበት ወቅትስ መቼ ነው?
አቶ ሙላቱ፡- ወደ ደቡብ ሙዚቃ መሳብ የጀመርኩት ከረዥም ጊዜ በፊት ሲሆን ከአሜሪካ Mulatu-Celo-and-Masinkoበተመለስኩበት ወቅት ነው፡፡ የደቡብ ሙዚቃዎችን ማድመጥና ምርምሮችን ማድረግም ጀመርኩኝ፡፡ በአፄ ኃይለ ሥላሴ አገዛዝ ወቅትም ከጋምቤላ ሙዚቀኞች አምጥቼ በመጣመርም ሠርቼያለሁ፡፡ በጥልቀት መመራመሬንም ቀጠልኩበት፡፡ ክራር፣ በገናና ዋሽንት ላይ የተለያዩ ሙከራዎችን ማድረግ ጀመርኩ፡፡ የሕዝብ ለሕዝብም የሙዚቃ ጉዞም እነዚህን የተለያዩ ሥራዎችን ለማቅረብ ጥሩ መድረክ ነበር፡፡ በዚህ ወቅትም ነበር አስገራሚውን የደራሼን ማኅበረሰብ ሙዚቃ የሰማሁት፡፡ የደራሼ ሙዚቃ ከኢትዮጵያ አራቱ ቅኝቶች አምባሰል፣ አንቺሆዬ፣ ትዝታና ባቲ ውጭ ናቸው፡፡ ይኼ ማኅበረሰብ ለዘመናት የ12 ሙዚቃ ቅላፄ (ኖት) ሲጫወት ነበር በአምስት ቅላፄ በሚጫወትበት አገር መካከል ተከበው 12 ቅላፄዎች የመጫወታቸው ምስጢር አስደናቂ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ “ዲሚኒሽድ ስኬል” የሚባል የተወሳሰበና ነፃነት ያለው የሙዚቃ አሠራርን ከጥንት ጀምሮ በመጫወት የሚታወቁ ናቸው፡፡ የእነሱን ሙዚቃ ከሌላ የሙዚቃ ዓይነት ጋር አጣምሬ በመሥራት በሀርቫርድና በበርክሌ ዩኒቨርሲቲ አቅርቤያለሁ፡፡ ስለማኅበረሰቡም የሙዚቃ ክህሎት ጥናት አቅርቤያለሁ፡፡ ለኔ እንደ ጥያቄ ያነሳሁትም የዘመናዊ ጃዝ ሙዚቃ ፈጣሪ የሚባለው ቻርሊ ፓርከር “ዲሚኒሽድ ስኬልን” ፈጣሪ ይባላል፡፡ ነገር ግን የደራሼ ማኅበረሰብ ከጥንት ጀምሮ ቻርሊ ፓርከር ፈጠረው ከመባሉ በፊት ሲጫወቱት ነበር፡፡ ጥያቄዬም ዲሚኒሽድ ስኬልን የፈጠሩት የደራሼ ማኅበረሰብ ወይስ ቻርሊ ፓርከር? በበርክሌ ዩኒቨርሲቲ የሙዚቃ ፕሮፌሰርን በጠየቅኩበት ወቅትም ፕሮፌሰሩ ማለት የቻለውም “ሙላቱ አገኘኸኝ” ብቻ ነበር፡፡ ይኼ ሁኔታም “በዲሚኒሽድ ስኬል” ላይ የተለየ ምርምር እንዲሠራ በር የከፈተ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- “በዲሚኒሽድ ስኬል” ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ሙዚቃ የመምራትን ፅንሰ ሐሳብን መቋሚያን በመጠቀም ቀዳሚ እንደሆነች ትናገራለህ፡፡ ስለዚህ ጉዳይ እስቲ የበለጠ ንገረን፡፡
አቶ ሙላቱ፡- መቋሚያ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከስድስተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የቤተ ክርስቲያን ዜማን ለመምራት ተጠቅመውበታል፡፡ ምንም እንኳን መቋሚያን ብዙዎች ከድጋፍ ጋር ቢያያይዙትም የመቋሚያ ዋና ዓላማ ዜማን መምራት ነው፡፡ የሙዚቃ መምራት (ኮንደክቲንግ) ፅንሰ ሐሳብ በተለያዩ ኦርኬስትራዎች ላይ ሲጠና እንቅስቃሴው የሚወሰነው መሪው በሚይዘው ዘንግ (ስቲክ) ነው፡፡ መቋሚያንም በተመለከተ አንድ ጥናት ሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ አቀረብኩ፡፡ ጥናቴም የሚያተኩረው ሙዚቃ መምራት በኢትዮጵያ እንደተጀመረና ለዓለምም ክላሲካል ሙዚቃ ዘርፍም ኢትዮጵያ አስተዋጽኦ እንዳደረገች የሚጠቁም ነው፡፡ በየትኛውም የሙዚቃ ምርምርም ሆነ ኢንሳይክሎፒዲያ በስድስተኛው ክፍለ ዘመን ውስጥ የሲምፎኒ ኦርኬስትራ፣ እንዲሁም ሙዚቃ መምራት እንደነበር የሚያሳይ ምንም መረጃ የለም፡፡ ይኼ ዕውቅናም ለቅዱስ ያሬድ መሰጠት እንዳለበት በማጠቃለልም አፅንኦት ሰጥቼ ጥናቴን አቀረብኩ፡፡ በዚህም መሪ ሐሳብም አንድ መርጌታና አንድ አውሮፓዊ የሙዚቃ መሪ (ኮንዳክተር) እኔ የጻፍኩትን ኦፔራ እንዲመሩ አደረግኩኝ፡፡ ይኼ ሁኔታ ለዓለም ሙዚቃ አዲስ ግኝት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እነዚህን የመሳሰሉ አዳዲስ ሐሳቦች በምታቀርብበት ወቅት ተቀባይነት ታገኛለህ ወይስ ተቃውሞ አለው?mulatu -
አቶ ሙላቱ፡- ምንም እንኳን የአውሮፓውያን (የምዕራባውያኑን) የሙዚቃ ታሪክ እየተፈታተንኩ ቢሆንም አውሮፓውያን አዕምሮአቸው ክፍት ነው፡፡ ይኼንን ሐሳቤን ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱ የመዚቃ ተመራማሪዎች በተገኙበት በሀርቫርድ ባቀረብኩበት ጊዜ ምንም ለማለት አልተቻላቸውም፡፡ ከተሳሳትኩ ለመታረምና በሐሳብ ለመፋጨት ዝግጁ ነበርኩ፡፡ ነገር ግን መልስ አልነበራቸውም፡፡ ይኼው ማለት ኢትዮጵያ አሸነፈች ማለት ነው፡፡ አውሮፓውያን አዳዲስ ሐሳቦችን መስማት ይወዳሉ፤ ስለዚህ ተቀባይነቱ መቶ በመቶ ነው ማለት ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- ብዙዎቹ የቤተ ክርስቲያን ዜማዎች ከቤተ ክርስቲያኗ ብቻ ተወስነው ከመቅረታቸው አንፃር የምርምር ሥራህ እንዴት ነበር?
አቶ ሙላቱ፡- በጠዋት ማልጄ እንጦጦ ማርያም ቤተ ክርስቲያን በመሄድ የመቋሚያ እንቅስቃሴን እንዲሁም የተለያዩ ዜማዎችን አጥንቼያለሁ፡፡ ከዚህም በተጨማሪም በቤተ ክርስቲያኗ ካሉ መርጌታና ሊቀ ሊቃውንቶችም ጋር በመቅረብ ስለ ቅዱስ ያሬድ ዜማዎች ተምሬያለሁ፡፡ ይኼንንም ተከትሎ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የተላለፈ “ንዋየ ማህሌት” የሚል ሥራም ሠርቻለሁ፡፡ ይኼ ሁሉ ግን ኢትዮጵያ እንዲሁም አፍሪካ ለዓለም ሙዚቃ ያደረጉትን አስተዋጽኦ የሚያሳይ ነው፡፡ በአፍሪካም ሆነ በኤዥያ ያሉ ነባር ሕዝቦች ያደረጉት አስተዋጽኦ ምንጊዜም መታወስ እንዳለበት የሚያሳይ ጥናት ነው፡፡ የሚያሳዝነው ግን ይኼ ዕውቀትም ሆነ እነዚህ ማኅበረሰቦች ዕውቅናና ክብር አለማግኘታቸው ነው፡፡ ምዕራባውያን ፒያኖ፣ ሣክስፎን የመሳሰሉትን ሙዚቃ የሠሩ ሰዎች ያከብራሉ፡፡ ለምሳሌ የፒያኖን ድምፅ የሚመስል ኢምቢራ የሚባል የሙዚቃ መሣሪያ አፍሪካ ውስጥ አለ፡፡ እምቢራ ከፒያኖ በፊት ነበር፣ አሁንም አለ፡፡ ከዚምባቡዌ እምቢራ ተጫዋቾችም ጋር የሙዚቃ ኮንሠርት በኦስትሪያ አድርጌ ነበር፡፡ ብዙዎቹንም አስደምሟል፡፡ በሙዚቃ ብቻ ሳይሆን በፀጉር ስታይልም ሆነ በዳንስ ብዙ አስተዋጽኦ አፍሪካ አድርጋለች፡፡ ይኼ ዕውቅና ሊሰጠው ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- በአምስት አሠርታት ውስጥ ብዙ ምርምሮች ማድረግህ ምን ያህል ሙዚቃህ ላይ ተፅዕኖ ፈጥሯል?
አቶ ሙላቱ፡- ኢትዮ ጃዝ ብዙ ተሻሽሏል፣ አድጓል፡፡ ከሃምሳ ዓመት በፊት የነበረውን የኢትዮ ጃዝ ሙዚቃ በመስማት ለውጡን መስማት ይቻላል፡፡ የሙዚቃው ዉሕደት፣ ስሜቱና ምቱም ተቀይሯል፡፡ ለወደፊቱም የኢትዮጵያ የሙዚቃ ሥራዎችን የማሻሻል ምርምሬን ስጨርስ ኢትዮ ጃዝን በባህላዊ ሙዚቃ መሣሪያ ብቻ እጫወተዋለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ወደኋላ እየሄድክ እንደአዲስ እንደድጓ፣ ጾመ ድጓ የመሳሰሉትንና የቤተ ክርስቲያን ዜማዎች እያጠናህ ነው፡፡ በቀላሉ እንዲገኝ ምን መደረግ ነበረበት?
አቶ ሙላቱ፡- የጥንት የቤተ ክርስቲያን ዕውቀቶች በሥርዓተ ትምህርቱ ውስጥ ቢካተቱ በብዙ ዕውቀት የተሟላ ኢትዮጵያዊ መፍጠር እንችል ነበር፡፡ ምዕራባውያኑ ሙዚቃንና ሥነ ጥበብን የትምህርታቸው አንድ አካል አድርገውታል፡፡ እኛም ከእነሱ ትምህርት በመውሰድ የጥንቱን ከአዲሱ ጋር በማጣመር ማስተማር መቻል አለብን፡፡ እንግሊዝ ውስጥ የሁለተኛ ደረጃ በምማርበት ወቅት መምህራኑ የዕለት ተዕለት አትኩሮታችንና ዝንባሌያችን በመከታተል ወደየት ማዘንበል እንዳለብን አስተያየት ይሰጡን ነበር፡፡ የዚህ አትኩሮት ውጤትም አስደናቂ ችሎታ ያላቸውን የሒሳብ ምሁራንና የፊዚክስ ሊቅ ማፍራት አስችሏል፡፡ የኢትዮጵያ ዋናው ችግር በትምህርት አትኩሮት ላይ ኃላፊዎቹ ባህልና ጥበቡን ችላ በማለታቸው ምክንያት፣ በሙያቸው ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱ ሰዎችን ማፍራት አልቻልንም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ዶክተሮችም ሆኑ ኢንጂነሮች መካከለኛ ደረጃ ላይ ያሉ ናቸው፡፡ ይኼንን ክፍተትም በማየት የትምህርት ሚኒስቴርም ሆነ የተለያዩ የባለድርሻ አካላት የትምህርት ካሪኩለሙን (ሥርዓተ ትምህርቱን) ሊያጤኑትና ሊያስቡበት ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- መጨረሻ የምትለው ነገር ካለ?
አቶ ሙላቱ፡- ሙዚቃ፣ ፍቅርና ሰላም!!!

(ምንጭ: ሪፖርተር )

Speak Your Mind

*