የአጋንንት ፖለቲካ – ውጣ!!

(ርዕሰ አንቀጽ)

ልብ ማለት ያቃተን ለምን ይሆን? የማንሰለጥነውስ ለምንድን ነው? በፖለቲካ ትግል ውስጥ ዕድሜ ገፍተን የማንበስለው እስከመቼ ነው? አድሮ ቃሪያ፣ አድሮ ጥሬ … እንዲሉ በጫጫታ ትውልድን የምናሰቃየው ስለ ምንድን ነው? ብዙ ጥያቄዎችን ማንሳት ይቻላል። ይህ በድህነትና በችጋር የሚቃጠለው ህዝብስ ማን ያስብለት? ማን ይድረስለት? በእነማን ብርሃን ይመልከት? ማን ከጨለማ እንዲወጣ ይምራው? ሩብ ምዕተ ዓመት እንደተባላን እንቀጥል? ያሳዝናል? ያስለቅሳል፣ እጅግ ያንገበግባል … ንስሃ የማያውቅ የአጋንንት ፖለቲካ ይሏል እኛ ነን!!

ችግሩ አንድ ወገን ዘንድ ብቻ አይደለም። ችግሩ ሁሉም ዘንድ በውጭም በውስጥም ነው። በውስጥ የተመቸ የመፎካከሪያ ሜዳ የለም። እያደር ይሻላል ሲባል ጭራሹኑ ህወሃት/ኢህአዴግ ሌሎችን “አያገባችሁም” አለና አረፈው። ይህ አልበቃ ብሎ ምክንያት እየተፈለገ ማሳደድና በበትር መግዛትን መረጠ። እያከረረ ሲሄድ ከረረበትና “በጥልቁ ልታደስ፣ ታድሼ መልስ እሰጣለሁ፣ ስልጣን ህዝብን ማገልገያ እንጂ …” እስከማለት፣ ከዚያም አልፎ አስቸኳይ አዋጅ እስከማውጣት ደረሰ። የሆነውንና የሚሆነውን እያየነው ነው!!

በውስጥ ተቀናቃኝ ፖለቲከኞች አንድ ርምጃ ወደፊት ተራምደው ብዙ ርምጃ ወደኋላ መመለስ ባህላቸው ሆኖ የደጋፊዎቻቸው ማፈሪያ፣ ለሚጠሏቸው መሳለቂያ ሲሆኑ ማየት የተለመደ ነው። እርስ በእርስ ሙግት እየገጠሙ የሚታገሉትን ኢህአዴግን ገላጋይ አድርገው አውጫጪኝ መቀመጥን መሰረታዊ መርሃቸው ይመስላል። ስም አንዘረዝርም። “ወጣ ወጣና” የተባለው ሰማያዊ ፓርቲ የቅርብ ማሳያ ነው (ግፍ እየተጋቱ ያሉትን ወገኖች ሳይሆን የፓርቲውን አመራር)። ነገም ሌላ ይሰማል። እዚህ ላይ ኢህአዴግ “ሰርጎ እየገባ ነው” የሚል ምክንያት ሲሰጥ ይሰማል። በራቸውን ከፍተውለት አይደለም ሳይከፍቱለት በርግዶ ለሚገባው ኢህአዴግ ለምን ክፍት ይሆናሉ? ከተደለሉ ይደልላል። ከተሸጡ ይገዛቸዋል። ከረከሱ የበለጠ ያረክሳቸዋል። እየተከታተለ ተቃዋሚዎቹን ማስለሉ ራሱን ዞሮ የሚጎዳውና አገሪቱንም ወደማይጠቅም ችግር መጎተቱ የማይቀር ቢሆንም፣ ለምን “እምቢ” የሚሉ ቆፍጣና ታጋዮች አይፈጠሩም? ይህንን ስንል በአገር ውስጥ እስከ አሁኑ ደቂቃ ድረስ የህይወት መስዋዕትነት የሚከፍሉትን ዘንግተን እንዳልሆነ ስተዋልልን። እያልን ያለው እንደ ተቀናቃኝ የፖለቲካ ድርጅት ነው!

በውጭ አገር የሚሆነውን ላስተዋለ የሚገርም፣ የሚደንቅ፣ የሚዘገንን፣ የሚሰለች፣ ምን እየሆን እንደሆነ እስከማይገባ ድረስ አንጎል የሚያዞር ትዕይንት ነው የሚታየው። መነጋገር የሚባል ነገር በአዋጅ የተከለከለ ይመስላል። “አማራ ይደራጅ” የሚሉ ይደመጣሉ። እነሱን የሚቃወሙ ይደመጣሉ፤ “ሁሉም በአንድ ማዕቀፍ ሥር ይሁኑና ትግሉን ወጥ ያድርጉት” የሚሉ አሉ። ጽንፈኝነት አፍንጫቸው ደርሶ ሜንጫና ቢላ የሚሉ ደግሞ “ለአማራ ብሄርተኛነት ወደፊት” በማለት እውቅና ሲሰጡ … ጉዱ ብዙ ነው። በፌስቡክ የሚወርደው ስድብና የእርስ በርስ አተካሮ እንደ እሳተ ጎመራ የሚንተከተክ ነው። ይህ ሁሉ የሚያርፈው ኢትዮጵያችን ላይ ነው!! ያሳዝናል።

ነጻ አመለካከት ያላቸው ሲተነፍሱ ይፈረጃሉ። ወያኔ ወይም ግንቦት 7 ይባላሉ። በሁሉም አቅጣጫ ነጻ ሚዲያ እንዳያብብ ከውስጥ ህወሃት/ኢህአዴግ፤ ከውጭ የዳያስጶራው ኃይል የመጀመሪያ ተከፊ ይሆናሉ። በዚህ መልኩ እንዴት ይቀጥላል? መሻሻልስ እንዴት ይመጣል?

ይህንን ሁሉ ያነሳነው አዲስ ጉዳይ ሆኖ ሳይሆን እንደዜጋ ግራ መጋባታችንን ለመግለጽና የመፈትሄው አካል ለመሆን በማሰብ ነው። ሁሉም በፈለገው መንገድ ይደራጅ፣ ይታገል፣ ህዝብ ፈራጅ ነውና!! አማራ ሲፈለግ በነጻ አውጪ፣ ሲፈልግ ራስን በመከላከል፣ ሲያሻው በብሄራዊ ደረጃ፣ አለያም በከፋኝ ስም ይዋቀር … አስር ድርጅቶች ይሁኑ፣ መቶም ይሙሉ ሌላው ለምን የራሱን ስራ አይሰራም? የራስን ሥራ በመሥራት የሕዝብን አእምሮና ልብ የራስ ማድረግ ይቻላል። ወቀሳና ውርጅብን ላይ ከማተኮር ሥራን መሥራት በሕዝብ ዘንድ ተዓማኒ ደርጋል። ሕዝብ ይሰማል፣ የሚሸጥለትን ሐሳብ ይመረምራል፣ የሚያሳምነው ሲሆን ይገዛል። ሐሳባቸው ያልተገዛላቸው ይከስራሉ፤ ከጨዋታው ውጭ ይሆናሉ። ነገርግን “ለፍቼ ያከማቸሁት በግ እንዳይሰረቅብኝ” በሚል አስተሳሰብ ሳይተኮስበት ዘራፍ ማለት፤ የሌሎችን አሠራርና አደረጃጀት መቃወም፣ ማብጠልጠል፣ ማዋረድ፣ … “በጠላቶቻችን መቃብር ላይ አቢዮታችንን እንገነባለን” የሚለው የደርግ መፈክር ብቻ ሳይሆን የግራው ልክፍት መሆኑን ማረጋገጫ ነው፡፡ ልክፍቱ ደግሞ አሁን ድረስ በውርስ እንደተላለፈብን የሚያሳይ ንሰሃ የማያውቅ የአጋንንት ፖለቲካ ለመሆኑ ማሳያ ነው፡፡

ኢትዮጵያን ብለው የሚታገሉ ስራቸውን ይስሩ፣ ከተራ ጉንጭ አልፋ ንትርክ ይልቅ ሰርተው ያሳዩ፤ በውጤት አፍ ማስያዝ ስለሚቻል ተግባር ላይ ይትጉ። ሁሉም ወገኖች በህዝብ እይታ የራሳቸው ደረጃና ዋጋ ስላላቸው፣ ዞሮ ዞሮ ይሁንታ የሚሰጣቸው ህዝብ ስላለ አስቀድሞ የሚደረገው ውዝግብ ማንንም አያራምድምና ይቁም። ሁሉም እምነቱን ይዞ ጠረጴዛ ዘንድ ይቀመጥ፤ መገንጠል የሸዋው፣ የሃረሩ፣ የወለጋው፣ የአርሲው፣ የጅማው፣ የባሌው፣ የቦረናው …. ኦሮሞ ልባዊ እምነት ከሆነ ወደፊት የሚታይ ነውና በጽንፈኛነት እንቀጥል የሚሉትም ይቅናቸው። ስድብ፣ ማግለል፣ ጥላቻ፣ ለኔ መኖር የሌላው መጥፋት ወሳኝ ነው በማለት መትጋት፣ ሃሳብን ሸጦ ሕዝብን ከማሳመን ይልቅ በግለሰብም ሆነ በድርጅት ላይ ማኅበራዊ ድቅር በመፍጠር አድልዖና መድልዖ ማድረስ፣ ከሃሳብን ከመሞገት ይልቅ ዘር፣ ማንነት፣ የፖለቲካ አመለካከት፣ እና ሌሎችም ላይ በማተኮር በተቀናቃኝ ስም የሚደረጉ የማያባሩ ጥቃቶች በሙሉ የአጋንንት ፖለቲካ ውጤት ነው፡፡ ከዚህ መውጣት የማይፈልጉ መኖራቸው የማይካድ ቢሆንም መውጣት ግን የግድ ነው፡፡ ሐሳብን ሸጦ፣ ዓላማን በተግባር አሳይቶ የህዝብን ቀልብ መሳብና ልቡን ማሸነፍ ንሰሐው ነው፡፡


ይህ ርዕሰ አንቀጽ የ“ጎልጉል: የድረገጽ ጋዜጣ®” አቋም ነው፡፡

Speak Your Mind

*