ጀንፎና ጅና!!

ዓመት ጠብቀው፤ ዐውደ ዓመትን ዙረው ከሚመጡት በዓላት አንዱ የገና (ልደት) በዓል ነው። ይህ በዓል በሀገራችን በያመቱ ታኅሣሥ 29 ቀን “ዮም ተወልደ ቤዛ ኵሉ ዓለም” (ዛሬ የዓለም ቤዛ ተወለደ) እያሉ የክርስትና እምነት ተከታይ ኢትዮጵያውያኖች በደማቅ ሥነ ሥርዓት በዓሉን ያከብራሉ። ለገና በዓል በቀረበ ግዜ በሀገራችን ከሚዘወተሩና ከሚወደዱ ክንዉኖች መካከል የገና ጨዋታ ዋናዉ ነዉ። የበአሉን መድረስ ተከትሎ ጎበዛዝት መጫወቻዋን ጥንግ የሚያሾሩበት የክትክታ ዱላ በመቁረጥ በደንብ እንዲጠነክር ቅቤ እያጠጡ ሲወለዉሉት ይከርሙና የገና በዓል ደረስኩ ደረስኩ ሲል ሰፈሩ ሲደምቅ ጨዋታዉ ሲደራ የክትክታዉ መታያ ቀን ይሆንና ለገና ጨዋታ የጎበዝ ጥሩር መለጊያ በትርነት ይዉላል።

ታድያ ይህ በትር እልህና ጉልበት በተቀላቀለበት ጎዝ እጅ የገባ ለት ጉልበቱ በደንብ ይታያል ሆኖም የምትለጋዋ ጥሩር ጥንካሬ በትሩን ከያዘዉ ጎበዝ ጋር በማበር አቅምና ጥንካሬዉን ይፈታተኑታል፤ መፈታተን ብቻም አይደል በትሩ የማታ ማታ መሰንጠቁ አይቀሬ ይሆናል። ታድያ በዚህ ግዜ ለአደጋ ግዜ ተብሎ የተዘጋጀ ከበሬ ጅራት ተቆርጦ የሚዘጋጅ  በተለምዶ አጠራር ጅና እንዲሁም ከብረት ጥቅል የተዘጋጀ ጀንፎ ተብለዉ በሚጠሩ  እቃዎች  በመታገዝ የመጀመሪያ እርዳታ ይደረግለታል። የበትሩ ስንጥቅ በደንብ እንዲያያዝና ክፍተት እንዳይኖረዉ በቁልቋል ደም እየተሞላ በጅና ይወጠራል ከዛም በደንብ እንዲጠነክር በጀንፎ ይታሰራል በዚህ ሁኔታ ጥገና ይደረግለትና እስከጨዋታዉ ማብቂያ ድረስ የጎበዝ አለቃ መተማመኛ በትር ይሆናል ጥንጓንም ያጎናታል።

መቸም ሰሞነ ገና ነዉና ከጅምሬ ስለምን መተየብ እንደፈለኩ ሳትገምቱ አልቀራችሁም። እርግጥ ነዉ ለመኖር ምክንያት የሆነን ለመዳናችን ዳግም የሰዉ ስጋን ለብሶ ወደ ምድር በበረት ተወልዷል ተብሎ በህዝበ ክርስትያን ዘንድ ይታመናልና ለመላዉ የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን አደረሳችሁ ለማለት እወዳለሁ። ከዚያም ሲያልፍ የጥምቀት መዳረሻ ነዉና ለጥምቀቱም ቀብድ ተደርጎ ይያዝልኝ።

ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ በሃገሬ ጉዳይ አንዳንድ እዉቀቶችና መረጃዎችን ለመቃረም በይነ መረብ ላይ ከወዲህ ወዲያ ስል ከረም ያለ በተንቀሳቃሽ ምስል የታጀበ በወርሃ ታህሳስ ግድም በደብረብርሃን ዩኒቨርስቲ የተካሄደ በሙሁራኞች የተሞላ የዉይይት መድረክ ሃሳቤን ገዛዉና እዛዉ መልህቄን ጣልኩ። የዚህ ዉይይት ጭብጥ የአማራና ኦሮሞ የህዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ቅኝት ማድረግ ሲሆን ከላይ እንደ መንደርደሪያ የሆነችዉን ሃሳብ ከዚሁ ውይይት ላይ በአንድ ሀገር ወዳድ ሙሁር ማጣቀሻ ምሳሌነት የቀረበች ነበረች ዉስጤ ቀርታለችና ላጋራችሁ ወደድኩ የፅሁፌ መነሻም መድረሻም ጭብጥ አደረኳት።

ነገሩ ወዲህ ነዉ ሀገሪቱን በማላብኝነት ለሃያ ሰባት ዓመት በበላይነት ሲዘዉራት የነበረዉ ሕዉሃት መራሹ የኢህአዴግ መንግስት የስልጣን እርካቡን ለማስፋት እንዲሁም መቀመጫዉን በተመች መሬት ላይ በማድረግ ጨለማ ሕልሙን ለማሳካት የመጀመሪያ እንቅፋት ነዉ ያለዉን በኢትዮጵያዉያን ደም ዉስጥ ያለዉን ሕብረ ብሔራዊ ስሜት፣ ፍፁም መከባበረና የመዋደድ ባህል በማጥፋት በዘርና በጎጥ በመከፋፈል ከሀገር ይልቅ ጎሳ ተኮር አስተሳሰብ በማህበረሰቡ ዉስጥ ማሳደግ ከዚያም ሲያልፍ የተመቻቸ አጋጣሚን በመፍጠር በተለያዩ ብሔረሰቦች መካከል ጥላቻን መሰረት ያደረጉ አስተምሮቶችን በማስፋት አንዱ ብሄር ስለሌላዉ ያለዉን መልካም አስተሳሰብ በማጥፋትና ታሪካዊ ትስስሩን ባልተገባ አስተምህሮት በመበረዝ ከዛም ሲያልፍ ለስልጣኔ ስጋት አይሆኑም ያላቸዉን ክልሎች መሳርያ በማስታጠቅ ጭምር ለእርድ ሲያደልብ መክረሙ ያደባባይ ሀቅ ነዉ።

ሕዉሃት ኢህአዴግ በተለይ በኦሮሞና በአማራ ብሔር ላይ መለያየትን በመፍጠር ሁለቱ ማህበረሰቦች እሳትና ጭድ እንዲሆኑ ስልጣን ከያዘበት ቀን አንስቶ ሲሰራበት ሲራቀቅበት ኖሯል እሰክ ቅርብ ግዜ ድረስም ሁለቱ ማህበረሰቦች በእቅዱ መሰረትም የሄዱ እስከሚመስል ድረስ ልዩነታቸዉ ሰፍቶና ጎልቶ ወጥቶ በአንድ መቆም እንዳይችሉ አድርጓቸዋል ለደከሙትም ማንቂያ ይሆን ዘንድ የአኖሌን ሃዉልት የመሳሰሉ ሳይቀር አቁሞላቸዋል።

ምሁሩ ንግግራቸዉን ሲቀጥሉ የአማራና ኦሮሞ ህዝቦች መሰረታቸዉ ጠንካራ በብዙ ታሪክ የታሰረና በአንድነት የብሔር ስሜት የታሸ አንድ ጠንካራ የጎበዝ ዱላ ናቸዉ የሚጫወትባቸዉ በዛና ተሰነጠቁ ይላሉ። ሕዉሃት ኢህአዴግ ለሃያ አምስት አመታት ይህንን ጠንካራ በትር ለመሰንጠቅ ብሄርተኝነት በሚል ጥሩር ሲለትማቸዉና አንዱን በዳይ አንዱን ተበዳይ በማድረግ ከሟለ ህፅናት እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ልዩ በጀት በመመደብ ያልተገባ ታሪካዊ አስተምህሮቶችን በመሰንቀር የጎበዝ አለቃ ጉልበት ሆኖ በመሃላቸዉ ያለዉን መተማመንና አንድነት ለሁለት በመሰንጠቅ ለመክፈል ከዛም የተከፈለዉን በትር መሰል ማህበረሰብ አርስ በርስ ለማጫረስ በሚጭረዉ እሳት ማገዶ በማድረግ ሀገራችንን ወደማትወጣዉ አዘቅት ለመጨመር ደክሟል ሰርቷል።

ይህንን ለማሳካት ብዙ ሺህ ንፁኋን ዜጎች ደማቸዉ ያለምክንያት ፈሷል  በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር የህዝብ ገንዘብ በከንቱ ፈሷል። ታድያ ይህ ሁሉ ነብስ ያለአግባብ የሚጠፋዉ ይህ ሁሉ ገንዘብ የሚባክነዉ የሚላስ የሚቀመስ አተዉ በየቀኑ እንደቅጠል በሚረግፉባትና የአስከፊ ድህነት ተምሳሌት በሆነችዉ ሀገራችን መሆኑን ልብ ይሏል። ደግሞም ይህ መንገድ ላለፉት ሃያ አምስት አመታት በስኬት ጎዳና በማንፈላለስ በትረ ስልጣኑን ያለተቀናቃኝ የሀገሪቱን አንጡረ ሀብት ያለጠያቂ ሲሰፍር፣ ሲዘርፍ ይበጀኛል ያለዉን ሲጠቅም የጠላዉን ከማዕከላዊ እስከ ሸዋሮቢት ከዝዋይ እሰክ ደዴሳ እንዲሁም ስም ያልወጣላቸዉና በፊንፊኔ አዲሳባችን መሃል በድብቅ በመገንባት ንፁኋን ዜጎች ላይ አሰቃቂ ተግባር ሲፈፅምና ሲገድል ቆይቷል ይህ ግፍ ደግሞ በዋናነት በሁለቱ ማህበረሰቦች ላይ ያነጣጠረ ሆኖ ከርሟል።

እርግጥ ነዉ ከነዚህ ማህበረሰቦች ጋር በማበር በሕብረብሄራዊ ፅኑ ስሜት የታገሉትን በሙሉ ፍሬን እንደበጠሰ ከባድ መኪና ያለርህራሄ ሲጨፈልቅ ኖሯል አሁንም ቀጥሎበታል።  ግና ይህ ሕዝብ እየተገፋም አይተበደለም እየተገደለም በየማሰቃያዉ የዘር ፍሬዉ እየተኮላሸም ጥፍሮቹ በጉጠት እየተነቀሉም በሀገሪቱ ፍትህ ይመጣ ዘንድ በቡድንም በተናጥልም ሲመክር እድሉን ሲያገኝ ሲታገል ኖሯል። ሆኖም የህዉሃት ኢህአዴግ ግፍና ኢ-ፍትሃዊነትነቱን ለማስቆምም ሆነ ለማስታገስ በምክር አልሆነምና በዝክር ሊሉት የአህያ ምንትስ በሆዱ ነዉ እንዲሉ አበው ሕዝብ አላዋቂ ሳይሆን ታጋሽ መሆኑን በተግባር ሊያሳይ በጎንደር ከተማ በሕዉሃት ኢህአዴግ የተሰነጠቀዉን የአንድነት በትር መልሶ ሊገጥም ልክ እንደቁልቋል ደም በጎዳና የፈሰሰዉን የኦሮሞ ወገኖቹን ደም ደሜ ብሎ አጋንንት፣ ጠባብተኛ  የተባለዉን ወንድሙን አለሁልህ ብሎ የጠራ የተከበረ ዜጋ መሆኑን ሊመሰክር  ስንጥቃቱን ሊገጥም አደባባይ ወጣ በዛም አጋጣሚ ብዙኋን በአደባባይ የሞትን መራር ፅዋ እንደ ኦሮሞ ወንድሞቻቸዉ ተጎነጩ።

ይህ መራር እዉነታ አፍንጫ ሲመታ እንደሚባለዉ ነዉና የኦሮሞ ሕዝብ አጋርነቱን ዳግም ለማሳየት የተሰነተቀዉን የአንድነት በትር ለማከም ያለዉን ቁርጠኝነት በአዳማ ላይ በነቂስ በመዉጣት ሕዉሃት ኢህአዴግ አብሮት ተወልዶ አብሮት የሚኖረዉን የክፋት ጋኔል በአንድነትና በሕብረብሄራዊ ስሜት አጠመቀዉ ይህምም ሕዉሃትን እንደ ክፉ በሽታ ሲንጠዉና ሲያንዘፈዝፈው እረፍትም ሲያሳጣዉ በማናለብኝነት የሚገዛቸዉ የመረጃ ማሰራጫ አዉታሮች ለዘመናት የሰራበት የመከፋፈል፣ እሳትና ጭድ የማድረግ ሴራና ስሌት እንዴት ሲደፈር አለ።

ሆኖም ይህ የዘረኝነት ገመድ ዳግም ላይገመድ አንዴ በኦሮማራ ጉብሎችና ቄሮዎች ተጎምዷል!! የሁለቱ ማህበረሰብ አንድነት ዳግም ላይገረሰስ ስንጥቃቱን ለማሻር በደማቸዉ የታሪክ አሻራዎቻቸዉን አኖሩ ይህም  ባሳለፍነዉ የሁለት አመታት በላይ ያለማቋረጥ የተካሄደዉ ሕዝባዊ እንቢተኝነት ፍም እሳት ዋናዉ ማገዶ አቀባይ ሆኖት ዘልቋል። ይህ የአንድነትና የአብሮነት የመቻቻልና የህብረብሄራዊነት ስሜት ከሕዝቡም አልፎ በሕዉሃት የበኩር ልጆች ኦህዴድና ብአዴን ቤቶችም በደማቁ ያለማቋረጥ ያንኳኳ ጉዳይ ከመሆንም አልፎ ዘልቆ በመግባት ይህ የህዝብ ትግልና ቁርጠኝነት ከስልጣን ይልቅ የሀገርን ጥቅም የማስቀደም ጥያቄ በአመራሮቹ የደም ዝዉዉር ዉስጥ በመግባት በጥልቅ ከተኙበት እንቅልፍ ያነቃቸዉ ጉዳይ ከመሆነም አልፎ እስትንፋሳቸዉና የፖለቲካ ቅኝታቸዉ ሁሉ አንድነትን መሰረት ያደረገ ፣ ፍትህን ያስቀደመ የአንድ ብሔር ሳይሆን የሕግ የበላይነት የሰፈነባት ሀገር ትመሰረት ዘንድ እራሳቸዉን እንደ አብረሃም ልጅ ያቆብ ለመስዋእትነት በማቅረብ ሕዉሃት ለዘመናት የገነባዉን የጎሳና የብሔር  ድልድይ ለመሻገር ያላቸዉን ቁርጠኝነት በተግባር ማሳየት ጀምረዋል።

ለዚህም መሳካት የተጠናና የጋራ መተሳሰብን በሁለቱ ብሔሮች ለማጠንከርም ከሕዝቡ ጋር በመሆን ተግባርን መሰረት ያደረጉ ስራዎችን መስራት ከጀመሩ ከራርመዋል በተለይም፤

  • ከሁለት መቶ በላይ የሚሆኑ ቄሮዎች “ጣና ኬኛ” ብለዉ ከኦሮሚያ ወደ ባህርዳር በመዉረድ በአንባገነኑ ድብቅ ሴራ እንዲሁም በእንቦጭ ላይ ዘምተዋል፤ ይህ የተሳካ ይሆን ዘንድ የሁለቱ ማህበረሰብ ርዕሰ መስተዳድሮች ያደረጉት የተቀናጀ ስራም ዉጤቱ ያማረ እንዲሆን ቁልፍ ሚናን መጫወቱ፤
  • ከዛም ስናልፍ በኦህዴዱ መሪ አቶ ለማ መገርሳ የሚመራዉ የኦሮሚያ ሉዑካን ቡድን ከብአዴን አቻዉ ከአቶ ገዱ አንዳርጋቸዉ ጋር በጋራ መስራት ስለሚቻልበት ጉዳይ ለመምከር ባህርዳር ድረስ መዝለቃቸዉ፤
  • ከዚያም ስንሻገር በተለያዩ ሕዝባዊና የድርጅት መድረኮች ያለምንም ማወላወል የጎሳ ሳይሆን የህዝብ የበላይነት መከበር እንዳለበት “በጎድ ፋዘር” የመራት ዘመን እንዳከተመ ከንግዲህ በግልባጭ ደብዳቤ ትእዛዝ ክልሎች መተዳደሪያ ደንባቸዉን እንደማይቀይሩ፤ በአንፃሩ ከህዝብ ጋር አብሮ በመቆም የህዝብን ፍላጎት በማስቀደም ለስልጣን ሳይሆን ለሀገር ደህንነት ቅድሚያ ለመስጠት ያላቸዉን ቁርጠኝነት የገለፁባቸዉ አጋጣሚዎችን መመልከቱ ….

በነዚህ ሁለት መስተዳድሮች ዉስጥ የተፈጠረዉን የለዉጥ መነሳሳት ስሜትና ቁርጠኘንት የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ በሕዉሃት ኢህአዴግ ጡጫ የተሰነተቀውን የአንድነት በትር ለማሻር ጀንፎና ጅና በመሆን ህመሙን ለመፈወስ ቁስሉን እንዲጠግ ለማድረግ እስካሁን ለአንድነትና ለሕዝቦች ነፃነት ለፍትህና ለኩልነት ሲባል በፈሰሱ የንፁሃን ደም ጋር አንድ ላይ በማበር አስከፊዉን ስርዓት መገዳደርም ብቻ ሳይሆን አንገዳግደዉ ደደቢት ገደል ለመክተት መሰረቱን መናድ ከጀመሩ ሰነባበተዋል። እኛም ገልቱዎቹን እነ ወርቅነህ ገበየሁና ካሳ ተክለ ብርሃንን ካረጀ የዘረኝነት አስተሳሰብ አላቆ ልቦና ይስጣችሁ ስንል ለአቶ ለማ መገርሳና ለአቶ ገዱ አንዳርጋቸዉ እንዲሁም አብረዋቸዉ በዚህ ትግል መድረክ ባልተንሸዋረረ አቋም ለቆሙት ሁሉ ገለቶማ ማለት ወደናል።

ከዚህ ስናልፍ በተለይም የሰሞኑን የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ስብሰባ የብአዴንና የኦህዴድ ቁልፍ አመራሮች በአንድነት በፅናት መዝለቃቸዉ እሱን ተከትሎም ከመንግስት ነኝ ባዩ ህዉሃት ኢህአዴግ መንደር የተሰማዉ የህሊና እስረኞችን የመፍታት ጭምጭምታ የመነሻዉ ሃሳብ ፍንትዉ አድርጎ የሚያሳይ ይሆናል ብዬ እገምታለሁ። ሆኖም ይህ የህዝብ ትግል በተለይም የኋላ ኋላ እነ ለማን እነ ገዱን እነ አብይን እንዲሁም ስማቸዉን ለመዘርዘር የሚችግረኝ እልፍ የሁዋላ ደጀኖችን ያሳተፈዉ ትግል መነሻና መዳረሻ ጭብጡ የሕግ ታራሚዎችን ማስፈታት ሳይሆን ሕዉሃት ኢህአዴግ በህሊና እስረኛነት ግዞት ስር ያስቀመጣቸዉ እነ አንዱዓለም አራጌ፣ እነ አንዳርጋቸዉ ፅጌ፣ እነ እስክንድር ነጋ፣ እነ በቀለ ገርባ፣ እነ መረራ ጉዲና የታሰሩለት እነ አበበ ካሴ፣ እነ መቶ አለቃ ጌታቸዉ በግፍ ተደብድበዉ የተኮላሹበት እነ ሃሊማ፣ እነ ንግስት እምነትና ሴትነታቸው የተዋረደበት  እንዲሁም እልፍ ህልቆ መሳፍርት የነብስ ዋጋ የከፈሉት ለመሞታቸዉ፣ ለመታሰራቸዉ፣ በግፍ ለመደፈራቸዉና ለመኮላሸታቸዉ ምክንያት የሆነዉ የዜጎች በእኩል የመተዳደርና የሕግ የበላይነት እንዲሁም በምንም መንገድ የማይደራደሩበት የአንድነት መሰርታችን የሆነችዉን ኢትዮጵያን ከጥፋት አዉሎንፋስ በማትረፍ ለሁላችንም የሁላችንም እኩል የሆነች ከልዩነታችን አንድነታችን የበለጠባት ሀገር እንድትኖረን የሚለዉ ፅኑ አላማ ነዉና ይህንን ከግብ ለማድረስ ህዝብም በሕዉሃት ኢህአዴግ የተለመደ የሞኝ ዘፈን ሁል ግዜ አበባዬ አይነት ማደናገሪያና ማዘናጊያ ዜና ነችና መዘናጋት እንደሌለብንና ከትግል ሜዳ እንዳንርቅ ማሳሰብ እወዳለሁ።

በተለይም የስርዓቱን የፈረጠመ ጡንቻ ሳይፈሩ ፊት ለፊት የተጋፈጡትን የዘመናችን ዳዊቶች በማጎበዝ ማገዝ በስነልቦናም በሃሳብም ማጠንከር ከዛም ሲያልፍ የህዉሃት መራር የበቀል እርምጃ ሰለባ እንዳይሆኑ ነቅቶ በመጠበቅ ትግላችን ግቡን መቶ በአንባገነኖች መቃብር ላይ ለመቆም እስከምንበቃ ትግላችንን አጠናክረን መቀጠል በተገኙት ድሎች መርካት ሳይሆን እንደ አቀጣጣይ ቤንዚን በመጠቀም በታደሰ ሞራል የስኬታችን መሰረት የሆነዉን ሕብረ ብሄራዊነትን በማንገብ ወደፊት መጓዝ ይኖርብናል።

በዚህ አጋጣሚ የፅሁፌ ጭብጥ በዋናነት ያጠነጠነዉ በኦሮሚያና በአማራ (ኦሮማራ)ስለሆነ ትኩረቴን በዛዉ አደረኩ እንጂ በዚህ የሞት ሽረት ትግል ዉስጥ በአራቱም ማዕዘን ያሉ እልፍ አእላፍ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዉያኖች በሀገራችን እኩልነት፣ አንድነት፣ ፍትህና ዴሞክራሲ እንዲሰፍን ከፊታችን በልበሙሉነት የሕይወት ዋጋ መክፈላቸዉንና እየከፈሉ መሆኑን ይህም ከምንም በላይ የሚያኮራና የአንድ ኩሩ ዜጋ ተቀዳሚ ተግባር መሆኑን ሳልጠቅስ ማለፍ አልወደድኩም። በመጨረሻም  ታጥቦ ለማይጠራዉ  ለሕዉሃት ኢህአዴግ መንግስት እንዲህ እላለሁ የህሊና እስረኞችን ሳይሆን ፍትህን ፍቱልን!! ማዕከላዊን ዝጉልን!! በማዕከላዊ ግፍ የፈፀሙትን ለፍርድ አቅርቡልን!! ፍርድ አልባ ፍርድ ቤቶችንም ዝጉልን!!

ኢትዮጵያዊነት በሀገር ወዳድ ዜጋ ደም ዉስጥ የሚኖር ሱስ ነዉ!!

መብራቱ ከስቶክሆልም (soranet2011@gmail.com)


“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ። ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣአቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው።

Speak Your Mind

*