ጃዋር ወደ መጨረሻው “የትግል” ስልቱ – አማራን ማበጣበጥ!

“ወንጀል የፈጸመም ያስፈጸመም ተይዞ ለህግ ይቀርባል” ታዬ

“ዲቃላ” በጃዋር ስሌት ዋስትና የሌላቸው ኦሮሞዎች

“በዐቢይ ላይ ቁርዓን ይዤ ጅማ እዘምታለሁ” ጃዋር

ጃዋር በሁለት ጠርዝ ወደ መጨረሻው ምዕራፍ እየበረረ መሆኑንን የሚያሳዩ ምልክቶች እየታዩ ናቸው። በገሃድ እንደታየው ቤተመንግሥት ለመግባት የተጫኑለትን ስሞች በሙሉ አራግፎ ፖለቲከኛ ሆኗል። ወደ ሥልጣን በሚያደርገው ጉዞ ዋንኛው ዓላማ የተደረገው አማራን ማበጣበጥ ነው። ለዚህም ምኞቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጅማና በመላው ኦሮሚያ እንዲጠሉ ቁርዓን ይዞ ዘመቻ እንደሚያደርግ ይፋ አድርጓል። በተመሳሳይ ደግሞ በጃዋር ጉዳይ መለሳለስ አሳይቷል እየተባለ የሚተቸው መንግሥት የተከማቸውን ፋይል ሊገልጥ ጫፍ መዳረሱን የሚያሳዩ ፍንጮችም ገሃድ እየወጡ ነው። በሌላ በኩል “ዲቃላ” በሚል ጃዋር የሚጠራቸው ኦሮሞዎች ዋስትናቸውን የማረጋገጥ ሥራ ላይ ናቸው።

የጎልጉል ታማኝ የመረጃ አቀባዮች በአዲስ ስታንዳርድና በቢቢሲ በኩል ጃዋር እንዳስነገረው ሳይሆን የዜግነት ጉዳይ ጣጣውን ገና ዳር አላደረሰም። ይሁን እንጂ አገሪቱን ለመምራት የምርጫ “ቅድመ ድል” ማወጁ ተሰምቷል። ይህንኑ በሄደበትና በረገጠው ሥፍራ ሁሉ እየሰበከ መጪው ምርጫ ላይ ያሰበው ባይሳካ አገሪቱን ወደ ሁከት ለመምራት የያዘውን ዕቅድ እያደላደለ ነው። ከዚህ በፊት “ለአገር ሰላምና ደኅንነት ብለን ነው እንጂ፤ ብንፈልግ በሁለት ቀን (በቄሮ ወይም በአንዳንዶች “መንጋ” በሚባለው በኩል) ልንጨርሰው እንችላለን” ብሎ መፎከሩን ልብ ይሏል።

ቀጣይ ዒላማ፤ ዶ/ር ዐቢይ፣ ምርጫ ቦርድና ወ/ሪት ብርቱካን  

ጃዋር ወደ መጨረሻው የትግል አማራጮቹ እየገሰገሰ መሆኑንን የሚጠቁሙት ክፍሎች ምርጫ ቦርድን፣ በተለይም ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን ማጠልሸትና ከወዲሁ ተዓማኒነት ማሳጣት በጃዋር በኩል እጅግ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ነው። ይህም የሚሆነው ጃዋር ሃሳቡን ካላሳካ፣ የምርጫ ውጤቱ መንግሥት የመሆን ህልሙን ካላቀዳጀው፣ ለማነሳሳት ላሰበው ነውጥ ምርጫ ቦርድ ታማኝነት እንዲያጣ ከወዲሁ የተዘየደ ስልት ነው። ለዚሁም ስኬት አሁን ከሚታወቁትና እሱ ከሚያስተዳድራቸው ሚዲያዎች በተጨማሪ ተቀማጭነታቸው በውጭ አገር የሆኑ ብሎገሮች/ጦማሪዎች እየተመለመሉ ነው።

እንደተለመደው በሚመራቸው ሚዲያዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ለይቶ በማሳጣት ዓላማ ላይ ተተክሎ እየሠራ ቢሆንም፣ ልክ ህወሃት “እረኛውን ምታ በጎቹ ይበተናሉ” በሚል በዲጂታል ወያኔ ሚዲያዎች፣ በቅልብ አክቲቪስትና የአማራ ፖለቲከኞች እንደሚያደርገው በተመሳሳይ ጃዋርም የማጥላላት ዘመቻውን እያጠናከረ ነው።

ስልት፤ አማራን በማተራመስ የሥልጣን መንገዱን መጥረግ

ጃዋር የመጨረሻ ዕቅዱ የሚሳካውና በአመጽ ወደ ሥልጣን የሚመጣው የአማራ ክልል ሲተራመስና እርስ በርሱ ጎራ ለይቶ መባላት ሲጀመር እንደሆነ ታምኖበታል። እንደ ጎልጉል የመረጃ ሰዎች ጃዋር በምርጫ ሥልጣን ለመያዝ የአማራን ድጋፍ ይፈልጋል፤ ይህንን መተግበር ደግሞ አስቸጋሪ ሆኖበታል። ስለዚህ በማተራመስ ሥልጣን ለመያዝ አማራ ክልል በዋናነት መተራመስ አለበት በሚለው ድምዳሜ ላይ በመድረሱ ይህንኑ ተግባራዊ የሚያደርጉ አማሮችን ከቀድሞ በተጨማሪ እያዘጋጀ መሆኑ ተመልክቷል። በውጪ አገር ሆነው ይህንን ዘመቻ ለሚያካሂዱም በተዘዋዋሪ ድጎማ እንደሚሰጥ፣ ሆን ተብሎ የተሳሳተ መረጃ እንዲደርሳቸው እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

ከጅማ የተሰማው ጃዋርን የሚያስደነግጥ ዜና በኦሮሚያ እየሰፋ ከሄደ ጃዋር ሁለተኛው አማራጩን ለማስኬድ ቅድሚያ እንደሚሰጥ ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ይናገራሉ። “እኔ ከግራኝ መሐመድ በኋላ የተፈጠርኩ ተጽዕኖ ፈጣሪ ነኝ” ሲል አደባባይ የሚናገረው ጃዋር “ጅማ ቁርዓን ይዤ በመግባት እስልምናን በመጠቀም ዐቢይን ከምርጫ አስወጣዋለሁ” በሚል ሲዝት ነበር። ከጅማ የወጡ መረጃዎች እንደሚያረጋግጡት ከሆነ ጃዋር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቅ ታዟል።

የኦሮሞነት ዋስትና የሌላቸው “ዲቃላዎች”

ከተለያየ ቦታ እየመጣበት ያለው ተቃውሞ በመጨመሩ ጃዋር ኦሮሚያ ላይ ሙሉ በሙሉ ድምጽ አገኛለሁ የሚለው ሒሳቡ ጥያቄ ውስጥ ስለሚገባ፣ ብልጽግና ፓርቲ አስተማማኝ የሚደመሩ ድምጾች በእጁ ስላለው፣ ጃዋርን የሚቃወሙና በምርጫ የሚቀጡ “ዲቃላዎች” እየበረከቱ መሆናቸው የግድ ወደ ሁለተኛ አማራጩ እንዲያመራ ይገደዳል የሚለውን ጥቆማ ያጎላዋል።

ከኦሮሞና ከሌላ ብሔር የሚወለዱትን “ዲቃላ” በሚል የሚያገለውና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይንም በተመሳሳይ “ዲቃላ” ማለቱ ለጃዋር የፖለቲካ መዘዝ እየሆነበት ነው። ትራንስፖርት እየቀረበላቸው በተለያዩ ሥፍራዎች ነውጥ የሚቀሰቅሱት ካልሆኑ በስተቀር ሌሎች ወጣቶች ወደ ቀልባቸው እየተመለሱ ጃዋር ላይ ጥያቄ ማንሳት መጀመራቸው እየተሰማ ነው።

የጎልጉል የአዲስ አበባ ዘጋቢ ከጅማ ያነጋገራቸው እንዳሉት ጃዋር ፈተና ይጠብቀዋል። “እሱ ማን ሆኖ ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ዲቃላ የሚለው” የሚሉት የጅማ ነዋሪዎች “በኦሮሚያ አብዛኞች ከተለያዩ ብሔረሰቦች የተዋለዱ ናቸው። ከእነዚህ አብዛኛውን ቁጥር ያያዙትን የኦሮሞ ልጆች ዲቃላ ማለት አይቻልም። የሚፈቅድለት የለም። በዚህ ስብከት ማታለል አይቻልም። ይቅርታ እንኳን ቢጠይቅ ትልቅ ጠባሳ ነው። ዋጋም ያስከፍለዋል” ብለዋል።

ሸምቀቆው እየጠበቀ ነው – “ወንጀል የፈጸመም ያስፈጸመም ተይዞ ለህግ ይቀርባል”

የጃዋር ትግል አቀንቃኝ ከሆኑት መካከል ከአንዱ ጋር ኢመደበኛ ውይይት ያደረገው የጎልጉል ዘጋቢ እንዳለው አሁን ጃዋር ላቀደው ዕቅድ በአማራ ክልል ያለው የእርስ በእርስ መባላት አመቺ ሁኔታን ፈጥሮለታል። ይሁን እንጂ መንግሥትም ከወትሮው በተለየ ሸምቀቆውን እያጠበበ መሆኑንን አይክድም። ምልክቶች እንዳሉም ያምናል። በተለይ በምርጫ ቦርድ በኩል የተያዘው የህግ ጉዳይ ጃዋርን ከምርጫው ጣጣ ሊያስወጣው እንደሚችል ይገምታል። ይህ ጉዳይ ለጃዋር ፖለቲካዊ ሞት ይሆናል።

አቶ ታዬ ደንደአ ይህንኑ የሚያጠናክር ሃሳብ ሰኞ ሰንዝረዋል። እሳቸው እንደሚሉት ጃዋር አገሪቱን ለማተራመስ በያዘው ዕቅድ መሠረት እስካሁን ከሞከራቸው በባሰ መልኩ ሰኞ ሆን ብሎ ለብጥብጥ የሚጋብዝ ምስል ይፋ አድርጓል።

በስዕሉ እንደሚታየው ህገ ወጥ ተግባር የሚፈጽሙት አካላት እነማን እንደሆኑ ተደብቋል። ቦታው ድሬዳዋ እንደሆነ ተደርጎ የተሰራጨው ምስል አማራ ኦሮሞን እንደሚያሰቃይ ተደርጎ የቀረበ መሆኑን በማተት አቶ ታዬ ጃዋርን አጋልጠዋል። ራሱ ምስሉን በሚፈልገው መልኩ ማዘጋጀቱንና ከዚህ ቀደም ዘጠና የሚሆኑ ንጹሃን ዜጎች የተገደሉበትን ሪኮርድ አስታወሰው “ይመጣል። እንደ ትናንቱ በንጹሃን ደም እና ስቃይ በመጫወት GoFundMe መክፈት የለም። ወንጀል የፈጸመም ያስፈጸመም ተይዞ ለህግ ይቀርባል። ምርመራም ተጀምሯል” ብለዋል።

Dereje Begi የሚባሉት የጃዋር ደጋፊ ጃዋር ያስተላለፈው ምስል ድሬዳዋ ሳይሆን “አሁን በማኅበራዊ ሚዲያ በተለይም በፊስቡክ በመዘዋወር ላይ የሚገኘው እና ድሬዳዋ ፖሊስ ፈጽሞታል ተብሎ በመዘዋወር ላይ የሚገኘው ቪዲዮ ድሬዳዋ አካባቢ ያለተፈመጸ ድርጊት ሲሆን ድርጊቱ የተፈጸመው በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዋና ከተማ በአሶሳ ልዩ ስሙ ጎንድል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሁለት ጨቅላ ሕፃናትን ጨምሮ በአራት ሰዎች ላይ የግድያ እንዲሁም በአምስት ግለሰቦች ላይ ጉዳት ያደረሰ ወጣትን በወረዳው ፖሊስ ጣቢያ ቅጥር ጊቢ ውስጥ የተፈጸመ ነው” የአቶ ታዬ ደንደአ ሙሉ ሃሳብ እዚህ ላይ ይገኛል።

የዜግነቱ ጉዳይ ትልቅ ቅርቃር ውስጥ የከተተው ጃዋር በምርጫ ለመሹለክ ያቀደው ሁሉ ውሃ ተደፍቶበታል። ይህም ትልቅ ኪሣራ ወደ አራት ኪሎ የሚወስደውን መንገድ አርቆበታል። ስድስት ወር አካባቢ የቀረውን ምርጫ የምረጡኝ ዘመቻ አድርጎም ይሁን ኮሮጆ ገልብጦ የማሳካት ዕድሉም እየጠበበ መጥቷል። ይህ የተስፋ ጭላንጭል ያልጠፋው ለፓርቲው ህልውና ሲል ኦፌኮ ስላላባረረው ነው። እንዲህ አስተማማኝ የሆነ ነገር በሌለበት ሁኔታ በምርጫ መታመን ትልቅ ኪሣራ ስለሚያመጣ በመንጋ የሚነዳ ነውጥ አማራጭ ይሆናል። ይህ ደግሞ ተግባራዊ የሚሆነው አማራ ሲበጣበጥ፣ እርስበርሱ ሲናከስ፣ በማያስፈልግና በማያንጽ አጀንዳ ጊዜ ሲባክን መሆኑን በደንብ ያጠናው ጃዋር የመጨረሻ ካርዱን በመምዘዝ ላይ ነው፤ ተከታዮቹም “ንገረን፤ እየጠበቅን ነው” እያሉ ነው። በአማራ ጉዳይ ላይ በንቃት የሚሳተፉ ሁሉ ይህንን ሰከን ብለው ቢያስቡበት መልካም ነው። ለጃዋር ግን ይህ የተውኔቱ የመጨረሻ ክፍል ሊሆን ይችላል።     


ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ንብረት ናቸው። ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን።

Comments

  1. እኛ ውህድ ማንነት ያለን ከማንኛውም ኦሮሞ በላይ ኦሮሞ ነን ብለን ለመመፃደቅ ባይዳዳንም ኦሮሞ መሆናችን ዲቃላ ብለው ከጠሩን የኦሮሞ ደም ሳይኖራቸዉ ለፖለቲካ ትርፋቸው ሲሉ ያልሆኑትን ምንም የዘር ሃረጋቸው ያልተመዘዘበትን የእነሱን ወፍ ዘራሽነት ለመሸፈን የኦሮሞን ስም እየጠሩ ከሚያላዝኑ አሳይ መሲዊችን ሴራ እየመከትን የኦሮሞን ኢትዮጵያውነት በደማችንና አጥንታችን እያረጋገጥን የመጣንና ሲልም እየቀጠልን ያለን አንቱ የተባልን የኦሮሞ ልጆች እንጂ ጭንጋፎች እንደጠሩን ዲ.. አይደለንም እኛም እንላለን ዲቃላ ካለበት አለ::

  2. ሃገሩ ላይ ቆሞ ሃገሬ እሄዳለሁ የሚሉ ትውልዶች ባፈራች ሃገር ተምሬአለሁ የሚለው የኦሮሞ ጽንፈኛ ጃዋር ከጀርባው አይዞህ የሚለውና ትጥቅና ስንቅ የሚያቀብለው የሃገርና የውጭ ሃይሎች እንዳሉ መገንዘብ ያስፈልጋል። በውጭ ያሉ የኦሮሞ ተወላጆች በእርግጥም ለኦሮሞ ህዝብ ይታገላል በማለት ያው ለፍተው ከሚያገኙትና በየቤ/ክርስቲያኑ ተጨቁነን እያሉ በማላዝን ከሚያሰባስቡት ለጃዋርና ለመሰል ፓለቲከኞች ማቀበላቸው እንደ ቀጠለ ነው። በሌላው መልኩ የኢትዮጵያን አንድነት የሚጠሉ ታሪካዊ ጠላቱቿ ይህ ነጩንና በአመዛኙ የአረቡን አለም ይጨምራል በእጅ አዙር የሚያደርጉት ድጋፍ እንዳለ መረጃዎች ይጠቁማሉ። አሁን ቁራን ይዤ ጂማ እገባለሁ የሚለው ጃዋር የያዘውን ቁራን እንኳን የማያውቅ በጥላቻ ፓለቲካ የተቃመሰ ዘረኛና ጠባብ ብሄርተኛ ነው። መስሎት ነው እንጂ ፓለቲካ ሶሞናዊ ነው። አሁን የሚያጨበጭቡለትና መዋጮ የሚከፍሉት ተመልሰው ጠላቱ ይሆናሉ። በመሰረቱ የሃበሻው ፓለቲካ የሚጠቅመውንም የሚጎዳውንም ለይቶ አያውቅም። በዚህም የተነሳ ሁሉም በየጊዜው አፈር እየተመለሰባቸውና ከሃገር እየተባረሩ ዘንተ ዓለም ፓለቲካን ሲያላዝኑ ወደ እማይመለሱበት ዓለም ያሸልባሉ። የደላቸው አስከሬናቸው ባልኖሩበት መንደራቸው ይቀበራል። ያልደላቸውም በአረፉበት ሃገር ግባተ መሬታቸው ይፈጸማል። በእኔ እይታ በአሁና ኢትዮጵያ 3 ዓይነት ፓለቲከኞች አሉ። ይህን በመረጃ ላስቀምጥ።
    የመጀመሪያው ዶ/ር ደብረጽዪንን የሚመስሉ ናቸው። በረድ ሲሉት የሚሞቅ፤ መጣ ሲሉት የሚሄድ ሁሌ አምታች ሃሳብን ብቻ እያስተጋባ በማደናገር አለም ውስጥ ብቻ መኖር የሚሻ። ሌላው እንደ በቀለ ገርባ ያለ እውነትን አክ እንትፍ ብሎ በጨለማ የፓለቲካ እይታ ውስጥ የገባ ኦሮሞ ነኝ ከሚለውና ቋንቋውን ከሚናገረው ሌላ ሰው ሰው የማይመስለው በየጊዜው የሚናገራቸው ነገሮች ሁሉ ከሶስት ዓመት ህጻን አፍ የወጣ የሚመስል የሙት ፓለቲካ አራማጅ። ከዚሁ ዘረኛ ብሄርተኛ ጋር ብዙዎች አማራዎች፤ ኦሮሞች፤ ትግራይ ተወላጆች፤ የክልል ፓለቲካ ያሰከራቸው የደቡብና የምስራቅ፤ ምዕራብ ሰዎች ይመደባሉ። ሶስተኛዎቹ ፓለቲከኞች ሃገራችን ያልተጠቀመችባቸው ጥሩ እይታ ለሁሉም ህዝብ ያላቸው፡ በጥላቻ ፓለቲካ መንገዳቸው ጥላቻ የተቀባ እንደ አቶ ልደቱ አያሌው ያሉ አሉ። ስለሆነም ሃገር በጩኽት እንደ ኢያሪኮ ግንብ ይደረመሳል በማለት ጃዋርና ደጋፊዎቹ ጅማ ላይ ሊያደርጉ ያሰቡት የፓለቲካ እብደት ደም የሚያቃባ እንደሚሆን ከአሁኑ መተንበይ ይሻላል። ይህ ሃሳብ ጨለምተኝነት ሳይሆን ካለው ከባቢ የሃይል አስተላለፍ አንጻር ነብይ ነይ ሳይሉ መተንበይ ይቻላል። የኦሮሞ ትርኪ ምርኪ ፓለቲካ ኢትዮጵያዊነትን ተላብሶ ሁሉን ህዝብ በእኩልነት እስካላሳተፈ ድረስ ንፋስ የነካው የአሽዋ ክምር እንደሚሆን ጠንቋይ አያሻውም። ጠ/ሚ ያለ እኛ ፈቃድ እንዳይመለሱ አድርገን ከአዲስ አበባ አባረርናቸው፤ የብልጽግና ፓርቲ የኦሮሞ ፓርቲ ነው፤ ጨቋኞቻችን አከርካሪያቸውን ሰብረናል እያሉ የሚወናጨፉትም እኩይ ፓለቲካ ነው። ከሚነድ እሳት ላይ ነዳጅ እንደማርከፍከፍ። በመሰረቱ የዘር ፓለቲካ የእንስሳ አሰላለፍ ነው። አብሮ ለመኖር አይበጅም። የወያኔም የብሄር ብሄሮች የፓለቲካ አደረጃጀት ለምዝበራና ለቁጥጥር እንዲያመች ተብሎ የተሰመረ የክልል ፓለቲካ ነው። አንድ ነገር ጨምሬ ይብቃኝ።
    የጋሞ ህዝቦች የፓለቲካ መከራ የመነጨው ከሁለት ነገሮች ነው። ለምን ጋሞን አነሳሁ ስለምወዳቸው። አንደኛው ኢትዮጵያዊነትንና፤ አቃፊነትን ስለሚወዱ ነው። ሌላው ደግሞ በሃገራቸው ያለው ለም መሬትና መልካም ነገሮች እነርሱን አግልሎ የዘመኑን ሃብታሞችና ዘራፊዎች ብቻ በስፍራው ስላስቀመጠ ነው። የሉሲ እርሻ ልማት ለዚህ አንድ ማስረጃ ነው። የከባቢን ህዝብ እያስራቡ ሃብታምን የበለጠ ሃብታም ማረግ። አምራቹ ተቆጣጣሪው ሽያጩ የዚያው ሃገር ተወላጅና ሰራተኛ መሆን ነበረበት። ይህ ግን አልሆነም። ግን የወያኔና የኦሮሞ ፓለቲካ ሁልጊዜም ለእኛ ብቻ የሚል ነው። ፓለቲካቸውም ይህን ሁሉ ገመና ያደረሰባችሁ አማራ ነው በማለት ህዝብን ከህዝብ አላታሚ የጥላቻ ፓለቲካ ነው። ዛሬ ሥራ አጥ የሆኑት የጋሞ ተማሪዎች ተምረው እንዳልተማሩ የበይ ተመልካች በመሆን በምድራቸው ላይ ተጥለዋል። መቼ ይሆን ፍትህ በምድሪቱ የሚሰፍነው። ወይም ሁላችንም ነደን አመድ በመሆን እኛም ባንኖርበት በእኛ ምክንያት ፍዳቸውን የሚያዪት የቀንድ፤ የጋማና የድር አራዊቶች እፎይ የሚሉት? ያ ቀን አይታየኝም። ሲገድሉና ሲገዳደሉ መኖር አይሰለችም?

Speak Your Mind

*