ውሉ ፈርሷል

ባልተረጋገጠ የዶክትሬት ማዕረግ ራሱን የፒ.ኤች.ዲ. ዲግሪ ሸልሞ የሚጠራው ጸጋዬ አራርሣና ጓደኞቹ በቀጣሪያቸው ጃዋር መሃመድ መካከል የነበረው ውል መፍረሱን ራሱ ጸጋዬ ይፋ አደረገ። ጃዋር ያልተለመደ ተግባር እንዳላደረገ በቅርብ የሚከታተሉት ይመሰክራሉ።

በተለምዶ በእንግሊዝኛው “down under” ወይም “እንጦሮጦስ” ተብሎ ሊጠራ ከሚችለው አውስትራሊያ ያለማቋረጥ በጥላቻ የተሞላውን መርዝ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚያስተላልፍ ነው። ያለመታከት በአማርኛ፣ በእንግሊዝኛና በኦሮሚኛ ይጽፋል፤ በማንኛውም ሚዲያ ከተጠራ እምቢ ማለትን አያውቅም፤ በተለይ ጸረ-ኢትዮጵያ አቋም ባለው ሚዲያ ላይ ደጋግሞ ቢቀርብ አይጠግብም፤ ከጃዋር መሃመድ ጋር የገጠመው አገርንና ሕዝብን ሊያድን ለሚችል ትልቅ ዓላማ ሳይሆን በጥላቻ ሰላምና ዕረፍት ያጣችውን ነፍሱን በበቀል ለማርካት ነበር። ጸጋዬ ረጋሣ አራርሣ ይባላል፤ የጃዋር ሎሌ ሆኖ በታማኝነት አገልግሏል፤ ከእርሱም ጋር አብሮ ሕዝቅኤል ገቢሣ ሌላው ተጠቃሽ ነው።

ወደ አውስትራሊያ ለትምህርት ሄዶ በዘመናዊው የሃሜታ ሰፈር (ፌስቡክ) በወሬ ተጥዶ በመዋል ጥላቻን ሲሰብክና ሲያሰራጭ በመዋሉ ትምህርቱን መከታተል አቅቶት የተሰናበተው ጸጋዬ፤ ከሕዝቅኤልና መሰሎቹ ጋር በመሆን የጥላቻና የግጭት መልዕክቶችን ሲያሰራጭ ቆይቷል። ጃዋር ባቋቋመው ኦኤምኤን ላይ ያለመታከት በመቅረብ እንዴት አንዱ ማኅበረሰብ በሌላው ላይ መነሳት እንዳለበት በዝርዝር ሲያስረዳና ሲተነትን ሰንብቷ።

ጸጋዬ ከ“እንጦሮጦስ” ሆኖ በየዕለቱ በተደጋጋሚ ወደ አገር ውስጥ እሣት ይለኩሳል፣ ግልጽ ጦርነት ያውጃል፤ ጃዋር ደግሞ ከአገር ውስጥ ሆኖ በፖለቲካና በሰላማዊ መንገድ ትግል መካሄድ አለበት እያለ በስልት ግን እንደ ትህነግ/ህወሓት ካሉ የጥፋት ኃይሎች ጋር በመወገን ሕዝብ ያስጨርሳል፣ እሣቱን ያቀጣጥላል።

በተሃድሶ የተጀመረውን የዶ/ር ዐቢይን አስተዳደር ያለመታከት በመክሰስ ሥልጣን እንዲለቅ፣ ሕጋዊነት እንደሌለው፣ አዲስ አበባ የኢትዮጵያ መዲና መሆን እንደሌለባት፣ ሁላችንንም የሚያስማማ አዲስ ዋና ከተማ መመሥረት እንዳለበት፣ የምኒልክ ቤተመንግሥትም መፍረስ እንዳለበት፣ ሌላ አዲስ ቤተመንግሥት መሠራት እንዳለበት፣ በደቡብና በአማራ ክልል የሚገኙ ማኅበረሰቦች “በክልልነት” ሽፋን አንዱ በሌላው ላይ መነሳት እንዳለበት፤ ወዘተ ማባሪያ የሌለው የጥፋት መልዕክቶችን ሲቀምም የሚውለው ጸጋዬ አራርሣ በጃዋር መሃመድ ላይ የሰላ ሒስ ሰንዝሯል።

ጃዋር መሃመድ በባህርዩ ሆነ በተግባሩ ወዳጅ የለውም። የ“ድምጻችን ይሰማ” ትግልን ለመቀልበስና በሥሩ ለማድረግ ሙከራ በማድረግ በጥሩ መስመር ላይ የነበረውን አካሄድ ለራሱ ጥቅም ለመዘወር በወሰደው አቋም ትግሉ ወደ ሜንጫ ትግል በመቀልበስ ካከሸፈው በኋላ ቀጣይ ፊቱን ያዞረው የኦሮሞ ሚዲያ ለመመሥረት ካሰቡ ጋር በመወዳጀት ነበር።

ኦኤምኤን ሲመሠረት ሃሳቡ የራሱ አልነበረም፤ እሱ ቢቀበለውና ቢያራግበውም ሃሳቡን በፋና ወጊነት የጀመሩት ሌሎች ናቸው፤ ሚዲያውን ሲጀምሩ ተባብረው “ኦሮሞ ፈርስት” በማለት ገንዘብ ለመሰብሰብ እንዲያመቻቸው ጃዋር የቀዳሚነቱን ሥፍራ በመውሰድ ሰሜን አሜሪካንና አውሮጳን ዞሩ። ዙረቱ ሲያልቅና ሚዲያው ሲመሠረት ጃዋር እያንዳንዱን አብረውት የነበሩትን ጓዶች ቀስ በቀስ ቀነጠሳቸው። ተቀንጣሾቹም በኦሮሞ መካከል ልዩነት ላለመፍጠር በሚል አፋቸውን ዘግተው እስካሁን አሉ፤ እነዚህ የቅርብ የትግል አጋሮቹና የዕድሜ እኩዮቹ ናቸው። ጊዜው ሲደርስ ይፋ የሚያወጡት ቢኖርም ጃዋር ግን ወዳጅ አልባ እንደሆነ አንድ ምስክር ሆነዋል።

ጸጋዬ፣ ሕዝቅኤልና መሰሎቻቸው በኦኤምኤን ላይ “ጃዋር እንዳለው” እያሉ የጃዋርን አቋም ሲያስተጋቡ ለዓመታት ቆይተዋል። አስፈላጊ ሲሆንም ጃዋር፤ ሕዝቅኤል ገቢሣን፣ በቀለ ገርባን ወደ ትግራይ እንዲዘምቱ በማድረግ ከህወሓት ጋር “የፍቅር ፎቶ በማስነሳት” አስጠቁሯቸዋል፤ ወይም በትህነግ/ህወሓት አነጋገር “አበስብሷቸዋል”። ጸጋዬም ወደ አገር ለመመለስ በሚከብደው መልኩ ከውጪ ሆኖ በየቀኑ መርዙን እንዲረጭ ጃዋር እስኪበቃው ተጠቅሞበታል። ጃዋር በፌስቡኩና በሚዲያው የማይናገረውን ጥላቻ በድፍረትና በወኔ የሰበከለት ጸጋዬ አራርሣ ነው። 

በፌዴራሊስት ስም ከህወሓት ጋር ሊፈጸም የነበረው “ጋብቻ” ገና ጥሎሽ ሳይጣል መፈረካከስ ሲጀምር በጃዋርና በሎሌዎቹ መካከልም ልዩነቶች እየሰፉ መጡ። በፊት እንደፈለጉ በጃዋር ሚዲያ ላይ ያለገደብ ይቀርቡ የነበሩት ሕዝቅኤልና ጸጋዬ ህወሓት ባዲስ መልክ በፈጠረችው “ኩሽ ሚዲያ” ላይ ዕለታዊ ደምበኞች መሆን ጀመሩ። ይባሱንም ብሎ ጃዋር የፖለቲካ ማርሹን ያልታሰበ መንገድ ላይ ቀየረ።

“ተከብቤአለሁ” በሚል የፌስቡክ ወሬ ለ86 ሰዎች በግፍ መሞት ተጠያቂ መሆን የሚገባው ጃዋር መሃመድ፤ በተለይ አሜሪካና አውሮጳ ደርሶ ከመጣ በኋላ “አገር አዳኝ” በመሆን በየሚዲያው ላይ መቅረብ ጀመረ። በኦነግ ሸኔ ላይ መንግሥት ተገቢውን እርምጃ እንዲወስድ ሁሉም የኦሮሞ ድርጅቶች ተሰባስበው ሲወስኑ እርሱም አብሮ “ይውደም” አለ። ይህ የአቋም ለውጥ በተለይም ከዐቢይ መንግሥት ጋር ሆኖ መሥራት ከጥንስሱ ጀምሮ ለጸጋዬና ለሕዝቅኤል አልተዋጠላቸውም ነበር። ጃዋር ባለፈው ከአሜሪካ ዙረት በኋላ አውሮጳ ሲሄድ በቅርብ መረጃ ያገኝ ነበረው የጎልጉል ሰው በእነ ጸጋዬና ሕዝቅኤል የአቋም ግትረኝነት ባለመደሰት “ጽንፈኛ፣ አክራሪ” እያለ በመጥራት ጃዋር ሲያናንቃቸው እንደነበር ይጠቅሳል።

በኦነግ ሸኔ ላይ መንግሥት እርምጃ እንዲወስድ የኦሮሞ ድርጅቶች ከተስማሙ በኋላ ህወሓት የጠራው የፌዴራሊስቶች ግምባርም እነ ሕዝቅኤል ገቢሣና አስፋው ወዳጆ ያለ ልክ ጮኸውበት መሰነጣጠቅ የጀመረው ገና ስብሰባው ሳያልቅ ነበር። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ጃዋር “አንዱ የመጫወቻ ካርዴ” ያለው በፌዴራሊስት ግምባር ስም ለማ መገርሣን መሪ በማድረግ መቀሌ ላይ ሊቆረስ የታሰበው “ኬክ” በአቶ ለማ ከብልጽግና ጋር አብሮ ለመሥራት ሲከሽፍ ጃዋር አሰላለፉን ማስተካከል ገፋበት። በኦፌኮ አምኜ “ተጠምቄአለሁ” በማለት የመረራን ፓርቲ ተቀላቀለ። ህወሓትም ከብልጽግና ጋር አብሬ አልሠራም ብላ ስትወስን “መቃብርሽ መቃብራችን” ያሏት እነ ትዕግስቱ አወልና ዘርዓይ ወልደሰንበት “ደህና ሁኚ ፍቕሬ” አሏት።

በዚህ ሁሉ የፖለቲካ ውጣ ውረድ ውስጥ የመጫወቻ ካርዱ እያለቀበት የመጣው ጃዋር ከኦፌኮ ጋር በመሆን የፖለቲካና የምርጫ ተግባር ማካሄዱን በይፋ ጀመረው። ይህም ለእነ ጸጋዬ ሊቀበሉት የማይችሉት ዱብዕዳ ሆነባቸው። “የውሉ መፍረስ” በግልጽ የታየው ጸጋዬ በፌስቡክ ገጹ ላይ ሰሞኑን “ምንደኛ አክቲቪስት”፣ የተሸጡ አክቲቪስቶች፣ ወዘተ እያለ በአሽሙር ሲጎነትለው የቆየውን ጃዋር በግልጽ ስሙን በመጥራት “የኦሮሞ ሕዝብ መሥዋዕትነት የከፈለው የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች (እና የቀድሞ አክቲቪስቶች የነበሩትን እነ ጃዋር መሃመድ) በምሥጢር ከዐቢይ አሕመድ ጋር እንዲደራደሩ ለመፍቀድ ብቻ አይደለም” ብሏል። እንዲያውም ጃዋር የተቀላቀለው ኦፌኮ በቅርቡ ሐረርጌ ያደረገውን ፎቶ በመለጠፍ “ኦፌኮ ይህንን የሚያደርገው ለዐቢይ ጭምብል ለማድረግና ሕጋዊነት ለመሥጠት እንዳልሆነ ተስፋ አደርጋለሁ” በማለት በቀለ ገርባን ከመረራ ጉዲናን ጋር አብሮ ወርፏቸዋል።

ጃዋር መሃመድ ከዚህ በፊት ሲናገር መለስ ዜናዊን እንደሚያደንቀው ገልጾ ነበር። በግልጽ በቃላት ባያስቀምጠውም የመለስን ማኪያቬላዊ አሠራርና በተፈለገው ጊዜ ፍሬቻ ሳያበሩ የመታጠፍ ባህርዩን እንደሚያደንቅ ንግግሩ ያሳብቅ ነበር። የመለስ ተማሪ የሆነው ጃዋር እንደ መምህሩ ምንም ወዳጅ የለውም፤ የእርሱን ጥቅም የሚያሳካ ከሆነ አምጣ የወለደችውንም እናቱን ሳይቀር አሳልፎ እንደሚሰጥ በቅርብ የሚያውቁት ይናገራሉ።

አሁንም እነ ጸጋዬ አራርሣንና ሕዝቅኤል ገቢሣን የበላቸው ይመስላል። “ፍቅራቸው” ያለቀ፤ ውላቸው የፈረሰ፣ ጋብቻቸው ያከተመ ይመስላል። በቀጣይ ደግሞ “ጤና ይስጥልኝ” ብሎ የተቀላቀለውን የኦፌኮ ፓርቲ መሪን ፕሮፌሰር መረራ ጉዲናን፤ “አልታዘዝም” ካለ ደግሞ በቀለ ገርባን ከመለስ በለመደው ስልት እንደሚቀነጥሳቸው የበፊት “አፈጻጸሙ” ሕያው ምስክር ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ “የመረራን ፓርቲ የተቀላቀልኩት የሸዋን ድምጽ ለመሰብሰብ ነው” በማለት ጃዋር የተናገረውን ተመርኮዙ ያወጣውን ሪፖርት ማንበብ ይቻላል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ፤ ባለፈው ሳምንት ጃዋር መሃመድ ኤል ቲቪ ላይ ከቤተልሔም ታፈሰ ጋር ባደረገው ጭውውት “አምባገነን ነህ ወይ?” በማለት ቤተልሔም ላቀረበችለት ጥያቄ “ማንም ሰው አምባገነን ነው” በማለት መመለሱ ይታወሳል።


ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ንብረት ናቸው። ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን።

Speak Your Mind

*