ኢትዮጵያ ውስጥ የመገንጠል ጥያቄ ማንሳት ይቻላልን?

(ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)

ይህንን ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት በቅድሚያ ሀገር ማለት ራሱ ምን ማለት ነው? እንዴትስ ትፈጠራለች? የሚሉትን ጥያቄዎች መመለስ ይኖርብናል፡፡ ሀገር ማለት በአንድ ጥላ ስር የሚኖርባት ትልቅ ቤት ማለት ናት፣ ሀገር ማለት ጋርዮሽ ማለት ናት፣ ሀገር ማለት ከመንደር ከቀየ የገዘፈች የጋራ ጥቅም የፈጠሩ ሕዝቦች የራሳችን የግላችን የሚሉት የተከለለ ምድርና በውስጡ ያሉ ሁሉ ነገሮች ማለት ናት፡፡

ሀገር እንዴት ትፈጠራለች?

ሀገር በሦስት መንገድ ትፈጠራለች

 1. የተለያየ ቋንቋ ባሕል ሃይማኖት ወዘተ ያላቸው ሕዝቦች በመልክአ ምድር አቀማመጥ በአየር ንብረት መመሳሰልና ተጽዕኖ ሊጋሩት በሚፈልጉት ወይም በሚገደዱት የተፈጥሮ ሀብት አጣማሪነት በስምምነት ትፈጠራለች፡፡
 2. የጋራ ጥቅም ባላቸው ወይም በፈጠሩ አንድ ዓይነት ቋንቋ ባሕል ሃይማኖት ወዘተ ባለው ሕዝብ ያንን የጋራ ጥቅም ለራሳቸው ብቻ ለመጠቀምና ከሌሎች ለመከላከል ባላቸው ጽኑ ፍላጐት ትፈጠራለች፡፡
 3. በኃያላን ገዥዎች ወይም ብሔረሰቦች ፍላጎት አቅማቸው በፈቀደላቸው መጠን ጥቅማቸውን ለማስከበር ለራሳቸው ለማድረግ በጣሩት መጠን ልክ ትፈጠራለች፡፡

እንግዲህ በዓለማችን ያሉ ሀገራት በዚህ መልኩ ሲፈጠሩ በተፈጠሩበት መልክም እንደገና ከውስጣቸውም ሌላ ሀገር ሲፈጠር ማለት እየፈረሱ ሲሠሩ አሁን ካሉበት ደረጃ ደርሰዋል፡፡ ከሀገራት መፈጠር የሚቀድመው ግን የጎጥ መፈጠር ነው፡፡ ፍላጎትና አቅም ከጎጥ ሲያልፍና አስተሳሰብ እየሰፋ እየጎለመሰ ሲሄድ ጎጥ ትጠበዋለች በሂደቱም ሀገር ትወለዳለች፡፡ በመሆኑም ሀገር የሥልጣኔ ፍሬ ናት ማለት ነው፡፡ የሆነ ሆኖ እንደ ዓለማዊ ተረክ ከሰው ልጅ ታሪክ አንፃር ካየነው ሀሳቡ ከ 10ሽዎች ዓታት በፊት የነበረ ሆኖም (አንድ ዓይነት ዝርያ ያላቸው ኅብረተሰቦች ሥፍራቸውን ከሌሎቹ የመጠበቅ የመከላከል ድርጊቶች ነበሩና) መልክና ቅርጽ እያየዘ የመጣው በዚሀ ዘመን ነው ለማለት እጅግ የሚያስቸግርና ምድር በአራቱም ማዕዘናት በሰው ልጆች ከመሞላቷ በኋላም የቀጠለ አሁንም ድረስ ያልተጠናቀቀ ሁልጊዜም አዲስ የቤት ሥራ እየሆነ አንድ ዓይነት መግባባት ላይ ለመድረስ ያልተቻለበት ጉዳይ ነው፡፡ ይሄም ሆኖ ከጥንት ከመሠረት ጀምሮ የሚታወቁ ሀገራት አሉ እንደ ዓለም ታሪክና መንፈሳዊው ተረክ ስናይ ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ከተመሠረቱ ህልው ከሆኑ ሦስት ሀገራት አንዷ ናት፡፡ በዚህ ዙሪያ የተለያዩ ተረኮች አሉ፡፡

አንደኛው ኢትዮጵያን የመሠረታት የአዳም ልጅ አሪ ወይም አራም ዓለም በተፈጠረ በ 970ዓመት ነው፡፡ የመጀመሪያ ንጉሷም እሱ ነው እስከ የጥፋት ወኃ ድረስ 21ነገሥታት ነግሠው ለ 1286ዓመታት ኢትዮጵያን ገዝተዋል የሚል ተረክ ለብቻው አለ፡፡ ከጥፋት ውኃ በኋላም ኖኅ ዓለምን ለሦስቱ ልጆቹ ሲያከፋፍል አፍሪካ ለካም ደርሳው ነበርና ኢትዮጵያ ውስጥ ከነገሡት የነገደ ካም ነገሥታት የመጀመሪያው ካም ነው ብለው ከካም የሚጀምሩ አሉ፡፡ አይ አይደለም ከካም ሦስተኛ ትውልድ 2545 ዓመት ቅ.ል.ክ ከሰብታህ ነው የሚጀምረው ብለው ከሰብታህ የሚጀምሩም አሉ፡፡ በዚያም ሆነ በዚህ ሀገሪቱ ጥንታዊትና በሀገር ደረጃ በቀዳሚነት ከተጠሩ ሀገራት አንዷ ናት፡፡ በጥንት የዓለም ታሪክ መጻሕፍትም ሆነ በመንፈሳዊ መጻሕፍት ዛሬ አፍሪካ ብለን የምንጠራውን እንዳለ ኢትዮጵያ ነበር የሚሉት፡፡ በጥንቱ የአውሮፓዊያን የዓለም ካርታ ላይ አትላንቲክ ውቅያኖስን “የኢትዮጵያ ውቅያኖስ” ሲል ይጠራዋል፡፡ በሌላ በኩል ማሊ፣ ቻድ፣ ኒጀር ወደታችም ታንዛኒያ በሌሎች በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራትም ምንጫቸው ኢትዮጵያ እንደሆነ የሚናገሩ በርካታ ማኅበረሰቦች አሉ፡፡ ባሕር ተሻግረን እስክ ቻይና የባሕር ጠረፍ ድረስ እንደገዛንም የዓለም ታሪክ ይናገራል፡፡

ከዚህ ከዚህ የምንረዳው ኢትዮጵያ ምን ያህል ረጅም ታሪክና ሰፊ ግዛት ዕውቅና የነበራት መሆኗን ነው፡፡ ባጠቃላይ ሀገራችን ኢትዮጵያ መጀመሪያ ኩሽ (በካም ልጅ ስም) ዓረቦች ወደ አፍሪካ ከመግቦታቸው በፊት ግብጽ ይኖሩ በነበሩት ጥቁር ሕዝቦች ዘንድ ደግሞ ቶ ኔቶር(ሀገረ እግዝአብሔር) ከዚያ አቢሲኒያ (በንጉሥ አቢስ ስም) ከዚያ ኢትዮጵያ (በንጉሥ ኢትዮጵ ስም) በእነዚህ ስሞች እይተጠራች ኖራለች፡፡ በዚህ እረጂም ጊዜ የቆዳ ስፋቷ ይስፋም ይጥበብ ያልተለወጠ ነገር ቢኖር ማዕከሉ ነው፡፡ የዚህ እጅግ የረጅም ዘመን አገዛዝ ወይም አስተዳደር ዓባይንና ምንጩን ጣናን እንብርት ማዕከል ያረገ ነበርና፡፡ አፍሪካ ኢትዮጵያ ከሚለው የተለየ ስም ለመያዟና አሁን በምናያቸው ሀገራት ብዛት ለመከፋፈሏ አስቀድሞ የዓረቦች ወደ አፍሪካ መግባት ወደ ኋላ ደግሞ የአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች ቅርምት ድርሻ ከፍተኛ ነው፡፡

እንግዲህ ኢትዮጵያ እንዲህ እንዲህ እያለች እየጠበበች እየጠበበች መጥታ በከፍተኛ መሥዋዕትነት አሁን ያላትን ገጽታ ብቻ ይዛ ልትገኝ ችላለች፡፡ እንደሚታወቀው ይሄንንም ቢሆን ለማፈራረስና የሀገሪቱን ህልውና ፍጻሜ ላይ ለማድረስ ከውጭና ከውስጥ ምን ያህል እያሰፈሰፉ እያቆበቆቡ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

ኢትዮጵያን ለመገንጠል የሚፈልጉ አካላት የፍላጎታቸው መንስኤ ምንድን ነው?

በእኔ እምነት ለዚህ ጥያቄ መንስኤ ሊሆኑ የሚችሉት ጉዳዮች ሦስት ናቸው

 1. ጭቆናና በደል ይደርስብናል ከሚል ቅሬታ
 2. ከራሳችን አልፎ ለተቀረው የሚተርፍ ሀብት አለን ይሄንን ሀብት ለብቻችን ማድረግ ብንችል የበለጠ ተጠቃሚ እንሆናለን ከሚል የተሳሳተ እምነት
 3. ቅጥረኝነት(ባንዳነት) ሀገርንና ወገንን ከድቶ ለጠላት ጥቅምና ዓላማ ማደር ናቸው፡፡

የእነዚህ መንስኤዎች ተጨባጭነት ምን ያህል ነው?

የመጀመሪያውን መንስኤ ስናይ በእርግጥ በሀገራትን ጭቆናና በደል አልነበረም ማለት ፈጽሞ አይቻልም፡፡ ተጨባጩና የሚያሳዝነው ነገር ቢኖር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ በሕዝብ በብሔረሰብ ደረጃ ተጨቆነ ተበደለ ተረገጠ ተበዘበዘ የሚባል ሕዝብ ካለ የአማራን ሕዝብ ያህል ኢትየጵያ ውስጥ እንዳልነበር ታሪካችንን ስንፈትሽ የአማራ ገበሬ በነገሥታቱ ዘመን ያሳለፈውን ሕይዎት ስናይ የምንረዳው ሀቅ ነው፡፡ የዚህ ምክንያቱ እንደ አለመታደል ሆኖ ሀገሪቱ ከጥንት ጀምሮ ለጦርነት የታደለች ሀገር ከመሆኗ ጋር ተያይዞ የአማራ ሕዝብ ለነገሥታቱ በቅርብ ርቀት ከመገኘቱና ይሄንን የመንግሥት ሥርዓት ከማስቀጠል ኃላፊነትና ግዴታ አንፃር ለሚያጋጥሙ ጦርነቶች ልጆቹን ከመገበር አልፎ ሠራዊቱ ደሞዝ አልባ ነበርና ይህ ሕዝብ ለመንግሥት ከሚሰጠው ግብር በላይ በየመንግሥት ታጣቂው በዘፈቀደ እንደተፈለገ እየተዘረፈ የመመገብ ግዴታን ሲያስተናገድ የነበረ ስለሆነ ነው፡፡

ይህ ድርጊት በሀገራችን ብቻ የነበረ ሳይሆን ተመሳሳይ የመንግሥት ሥርዓት በነበረባቸው ሀገራትም የነበረ ድርጊት ነው፡፡ የአማራው ሕዝብ በዚህ ዓይነት ግዴታ የማለፉ ውጤት አሁን ላይ የኢትዮጵያን ገበሬዎች ሕይወት ተዘዋውረን ስናይ ከሌሎቹ ብሔረሰቦቻችን ይልቅ የአማራ ገበሬዎች ሕይወት እጅግ በሚያሳዝንና ልብን በሚነካ የድህነት ዓይነት የሚኖሩ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ የአማራ ገበሬ በፍጹም ጥሪት መቋጠር የሚችልበትን ዕዳል አግኝቶ አያውቅም ሁለ ነገሩን ለሀገሪቱ ህልውና ለነጻነቱ ከፍሎታል፡፡ ከመኖሪያ ቤቱ አቅም እንኳን ብታዩ የአማራ ገቤሬዎች ቤቶች ከሌሎቹ ብሔረሰቦች ገበሬዎች ቤቶች የደከመና ደሳሳ ነው፡፡ በአንጻሩ የሌሎቹ የደረጀና ጥብቅ አቋም ያለው ሆኗል፡፡ ልብ በሉ እያወራሁ ያለሁት ስለ አማራው ሕዝብ እንጂ ስለ አማራ ነገሥታት አይደለም፡፡ ምንም እንኳን ጥቂቶች የሳቱ የብሔረሰቡ አባላት ብለዋልና ብየ ይህ የመገንጠል ጥያቄ የኦሮሞን ሕዝብ የወክላል ባልልም ለምሳሌ የኦሮሞን ሕዝብ ወይም ገበሬዎች ሕይዎት ብንመለከት ከአማራ በእጅጉ የተሸለ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በቅርቡ በደናቁርት ተሳዳቢ የወያኔ ባለ ሥልጣናት እንደተገለጸው የአማራ ገበሬዎች ሕይዎት እኮ በ 21ኛው መቶ ክፍለ ዘመንም እንኳን ቢሆን ጫማ ለማድረግ ያልታደለ ኅብረተሰብ ነው፡፡ የልብሱም ነገር እንደዚያው ነው፡፡ ምን አለፋቹህ ባጠቃላይ ለዚህች ሀገር እራሱን የሰዋ ሕዝብ ነው፡፡

ታዲያ ለሀገር ሲል በከፈለው ዋጋ ለችጋር መዳረጉ ሊያስመሰግነው እንጂ ሊያስነቅፈው ሊያዘልፈው ይገባ ነበር እንዴ? ለችግር ቢዳረግም ነጻነትን ያህል በምንም ሊገዛ ሊለወጥ የማይችልን ሀብት አትርፏልና፡፡ ይሄ አኩሪ እሴት የአውሮፓ ሀገራት እንኳን የላቸውም አንዱ በሌላው የተገዛ ነውና፡፡ ይህ ሕዝብ በዚህ ትምክህት ያልተሰማው በሌላ በምን ሊመካ ይችላል? ትምክህተኛ ተብሎ መኮነኑ በምን ሒሳብ ነው አግባብነት ሊኖረው የሚችለው? ለነገሩ ያላቸውን ነው ሊሰጡን የሚችሉት የሌላቸውን ከየት ያመጡታል? ሕዝብን በፍቅር ገዝቶና አሳምኖ እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ እንድ ቃል ተናጋሪ በአንድ ሐሳብ አስማምቶ ለልማት እንዲነሣ ማድረጉንማ ከየት አምጥተውት? ችሎታና ሰብእናቸው አይፈቅድላቸውማ? ፍቅርና ክብር አያውቁማ? እንደ እንስሳ ቆጥረው በግዳጅ እያሰለፉ የግብር ውጣ ሥራ ያሠሩ እንጂ፡፡

 ከዚህ ባሻገር ስላሉ ነገሮች ስናወራ በሀገራችን በርካታ ብሔረሰቦች የሚያቀርቡት ቅሬታ አለ፡፡ በማንነታችን እንድናፍር እንድንሸማቀቅ እንደረግ ነበር፣ እንደ ዜጋ አንታይም ነበር የሚለው ቅሬታ ወይም በደል አልነበረም አልተፈጸመም ማለት አይቻልም ነገር ግን ምክንያታዊ እንደነበር ልንገነዘብ ይገባል፡፡ በአርግጥ ዛሬ ላይ ሆነን ስናየው ፍጹም አግባብነት የሌለው ሆኖ አናገኘዋልን፡፡ ነገር ግን ይህ ከጥንት ጀምሮ የነበረ ጥቃት እንዴት ሊፈጠር ቻለ? የሚለው ጉዳይ መጤን መመርመር ያለበት ጉዳይ ይመስለኛል፡፡ ያለ ምክንያት የሚፈጸም ምንም ነገር የለምና አንዴትና ለምን የመገለል እንደ ዜጋ ያለመቆጠር ጥቃት ሊደርስባቸው ቻለ ለሚለው ቅሬታ የኦሮሞን ብሔረሰብ በተመለከተ ወደ 16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ወደ ኋላ፤ የትግሬን ብሔረሰብ በተመለከተ ወደ አምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመንና አምስት መቶ ዓመታት ከዚያ ወደኋላ በመመለስ በዚያ ወቅት የነበረውን ሁኔታ ብናየው የዚህ በደል መንስኤ ምን እንደሆነ እንረዳለን፡፡

እንግዳ እቤታችሁ እንዳረፈ አስቡና በእንግደነቱ ሰሞን የሚኖረውን የምትሰጡትን መብት አጢኑት ይህ እንግዳ እቤታችሁ ለዘለቄታው የመቆየት የመኖር ዕድል ቢኖረው ደግሞ ከቤተሰብ አባላት እንደ አንዱ የመቆጠር ዕድል ቢያገኝም ቅሉ በሁሉም ጉዳይ ላይ ግን ልክ ከቤተሰብ አባል አንዱ ሆኖ እንደማይቆጠር እሙን ነው፡፡ ከዚህ አንጻር መሠረታዊ ጉዳዮች በተነሡ ቁጥር የቤቱ ባለቤት “ስንት ለፍቸ ስንት መሥዋዕትነት ከፍዬ ባቀናሁት ቤቴ እኩል ሊገዳደረኝ፣ የባለቤትነት መብቴን ሊጋፋኝ አይገባም” ከሚል አስተሳሰብ የተነሣ እንግደነቱን እንዳይረሳ ለማድረግ፣ እኩል ደራ ደራ ማለቱን ለማቀብ በእንግድነቱ ሊያገኘው ከሚገባው ጥቅም በላይ በቸርነት የተሰጠውን ቤቱን የመጠቀም እንደቤተሰብ የመቆጠር ዕድልን በቂ አድርጎ እንዲያስብ ለማድረግ የተለያዩ ሸንቆጣ ባለቤቱ በእንግዳው ላይ ማድረሱ የማይቀር ይሆናል፡፡ ይህ ሽንቆጣ እንግዳው በእንግድነቱ ዘናትን ባስቆጠረ ቁጥር እንግደነቱ ተረስቶ የቤተሰብ አንዱ አባል እንደሆነ በተቆጠረ ጊዜ ሽንቆጣው ከባድ በደል እንደሆነ ደርጎ የመቆጠር አጋጣሚ ይፈጠራል፡፡ ዛሬ ላይ ተናቅን እንደ ዜጋ አንቆጠርም በማንነታችን እንድናፍር እንድንሸማቀቅ እንደረጋን የሚሉ ወገኖቻችን ይህንን ሁሉ ቅሬታቸውን ዛሬ ላይ አግባብ ሆኖ ብናገኘውም ትላንትና ላይ ግን በፍጹም ሊነሣ አይደለም ሊታሰብ የማይችል ቅሬታ ነበር የእንግድነትን መብት ጠንቅቆ ከመረዳት አንጻር ማለቴ ነው፡፡ እንግዲህ ይህ ሥነ ልቡና ነው እንዲህ ዓይነቱን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት የፈጠረው፡፡ ታሪካዊ ዳራ ምክንያት ሰበብ አለው እንዲሁ ከየትም የመጣ አይደለም ለማለት ነው፡፡ የሆኖ ሆኖ አሁን ላይ በመዋለድም በምንም ባለ መብት ያልሆነ የለምና በደም ተሳስሯልና ቅሬታው አግባብነት ያለውና መቀረፍም ያለበት ነው፡፡

article 39ወደ ሁለተኛው መንስኤ ስንሄድ ላይ ላዩን ስናየውን እንገንጠል ለሚሉት ወገኖች እውነት ሊመስል ይችላል፡፡ ጠለቅ ብለን ስናየው ግን ሀብቱ መኖሩ ስስ እውነት ቢሆንም በተለያዩ የተሳሰሩ ምክንያቶች እንገነጠላለን ባዮችን እንደ ሀገር ህልውና አዝይዞ ለመቀጠል ፍጹም የማያስችል ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ አሁን በምናውቃት ኢትዮጵያ የችኛውም ክልል ተገንጥሎ እንደ ሀገር ህልውና አግኝቶ ለመኖር የሚያስችል አቅም ዕድል ያለው ክልል የለም፡፡ የኢትዮ ኤርትራን ግጭትና ጦርነት የፈጠረውም ጉዳይ ሌላ ምንም ሳይሆን ይሄው ነው፡፡ ከዚህ አንጻር እኔ በግሌ በተለይ ምሁራን መገንጠልን መፍትሔ አድርገው ያምናሉ ብየ አላስብም፡፡ መገንጠልን መፍትሔ አድርገው የሚያምኑ ምሁራን ካሉ ግን ምሁርነታቸው በጣሙን አጠያያቂ ይሆናል፡፡ እኔ የሚመስለኝ የተማረው ክፍል የመገንጠልን ጥያቄ የሚያንጸባርቀው በመፍትሔነቱ አምኖበት ሳይሆን ለማስፈራራትና በምላሹ መብትን ለማስከበር የመደራደራያ አቅም ለማግኘት፣ ጫና ለመፍጠር ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ዓላማው ለዚህ ቢሆንም እንኳ እልህ ነገሩን ወዳልታሰበ አቅጣጫ ሊወስደው ከመቻሉና ያልተማረውንም ኅብረተሰብ ስለሚያሳስት በማስፈራሪያነትም እንኳን ቢሆን ማንሣቱ ፍጹም ተገቢ ያልሆነና ኃላፊነትም የጎደለው ነው፡፡

 ወደ ሦስተኛው መንስኤ ሔድን፡- እንደሚታወቀው ሀገራችን ከጥንት ጀምሮ ዛሬም ድረስ ብዙ ጠላት የሆኑባት ሀገራት ነበሩ አሉም፡፡ ከእነኝህ ሀገራት ጥንተ ጠላት የሆኑቱ ሀገራችን ያለችበት ስልታዊ ቦታና የተፈጥሮ ሀብቷ ህልውናችን ለህልውናቸው አደጋ እንደሆነ በማሰብ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ጠላት ሲሆኑን፡፡ አዳዲሶቹ ጠላት ሀገራት ደግሞ ከጥቅማቸው ጋራ የዘረኝነት በሽታቸው ተጽእኖ ፈጥሮባቸዋል፡፡ እነዚህኞቹ እንደሰው የማያስቡና ጨካኞችም ናቸው ልክ እነሱ እራሳቸውን ፈለጉት ዘርና የቆዳ ቀለም እንደፈጠሩ ሁሉ ለዚያ የከፋ ጥላቻና ጥቃት ምክንያት ሊሆን የማይችል የማይገባን የቆዳ ቀለምና የዘር ልዩነትን መንስኤ ያደርጋሉና፡፡ የጥቁርን ዘር እንደመገልገያ ዕቃ ቆጥረው ዝንተ ዓለም በቅኝ ግዛት ሲገጥቡት ለመኖር ይፈልጉ የነበሩ ሲሆኑ፤ ሀገራችን ይሄንን ግፈኛ አገዛዝና ኢሰብአዊ ኢፍትሐዊ አስተሳሰብ ከአቅንኦተ ግንኙነት (ዲፕሎማሲ) እስከ ወታደሮቿን በቀጥታ አሰልፋ ቅኝ ግዛትን እንዲያከትምለት ስላደረገች፣ ጥቁር ከነጭ የማያንስ በአንዳንድ ጉዳዮች እንዲያውም የተሻለ የበለጠ መሆኑን በሥልጣኔዋ ማስመስከሯ በጉሮሯቸው ላይ እንደቆመች በመቁጠር ከእርኩሳዊ ቅናትም ጭምር ጥርሳቸውን ነክሰውብን ባጋጠማቸው ዕድል ሁሉ ሲበቀሉን ቆይተዋል ወደፊትም ቢብስባቸው እንጂ ይተውናል ብየ አላስብም፡፡ እንግዲህ እነኝህ ጠላቶቻችን ሁሉም ከድሮ ጀምረው በየራሳቸው ምክንያትና ዓላማ ተሰልፈውብን በየዘመኑ በቀጥታና በተዘዋዋሪ ሲያጠቁን ኖረዋል፡፡ ለእኛ የከፋብን ግን በተዘዋዋሪ ያደረሱብን ጥቃት ነው፡፡ ምክንያቱም በተዘዋዋሪ የሚደርስብን ጥቃት ዜጎቻችንን በክህደት በማጥመቅ ወደ ባንዳነት ቅጥረኛነት በመለወጥ በመሆኑ ከሚደርሰው ጉዳት በላይ በእነዚህ ዜጎች እንደዚያ መሆን በሀገር ላይ በተለያዩ ምክንያቶች ለዘለቄታው ጥሎት የሚያልፈው የችግርና የጦስ መዘዝ የማይነቀል እሾህ የማይድን ነቀርሳ ይተክላልና ነው፡፡

እዚህ ላይ ወያኔን በምሳሌነት ማንሣት እንችላለን፡፡ ወያኔን ማን አሳድጎ ማን ደግፎ ምን ዓላማ አስይዘው ከቆዳ ቀለማቸውና ከስማቸው በስተቀር ኢትዮጵያዊ ቃና ለዛ ማንነት አልባ አድርገው ቀርጸው ጸረ ኢትዮጵያ አቋም አስታጥቀው ማን ለዚህ እንዳበቃቸው መለስ ብሎ ማጤኑ ለዚህ በቂ ምስክር ነው፡፡ ብዙ ሰው የኪነብጀታ (ቴክኖሎጂ) ውጤት እጅግ ያስደንቀዋል፡፡ እኔን እጅግ የሚገርመኝ የሚደንቀኝ ነገር ግን ጠላቶቻችን ወያኔዎችን እንዴት አድርገው ለምንስ ጥቅም አታለው በገዛ ሀገራቸውና ሕዝባቸው ላይ እንደዚህ ዓይነት ጠላት እንዲሆኑ ማድረግ መቻላቸው ነው፡፡ መታየት ያለበት ከገዥ መደብ አለመሆናቸው አይደለም ይሄ ፈጽሞ እንደምክንያት መወሰድ የለበትም ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ብሔረሰቦች ሁሉ ከ4500 ዓመታት በላይ ለሆነው ታሪኳ፣ ነጻነቷ፣ ሥልጣኔዋ፣ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እስተዋጽኦ ያላደረገ አንድም ብሔረሰብ የለም፡፡ እንዴትስ ሊኖርስ ይችላል? በመሆኑም የሐገሪቱን ታሪክና ሥልጣኔ የአንድ ብሔረሰብ ብቻ አድርጎ ማሰብ ከቶውንም አይቻልም፡፡ እንዲህ አድርጎ ማሰብ ካልተቻለ በዓለማችን በየትኛውም ሀገር ያሉ ሁሉ ሀገራቸውን ሀገራችን ማለት ባልቻሉ ነበር፡፡

በየትኛውም ሀገር ብንሔድ ለየሀገሩ ሥልጣኔና ህልውና የአንዱ ብሔረሰብ አስተዋጽኦ ጎልቶ መታየቱ አይቀርም እንዲህ በመሆኑ ግን ሌሎቹ ሀገሪቱንና አጠቃላይ እሴቷን የኛ አይደለም እንዲሉ አላደረገም፡፡ በአንዱም ባይሆን በሌላው በቀጥታም ባይሆን በተዘዋዋሪ ለዚያች ሀገር አስተዋጽኦ ማድረጋቸው አይቀርምና፡፡ በመሆኑም ሀገሪቱ ሀገራቸው ናት ታሪኳም ታሪካቸው ነው፡፡ እውነታው እንዲህ በሆነበት ሁኔታ ሰው እንዴት በገዛ ሀገሩ ታሪክ፣ ሥልጣኔ፣ ሉዓላዊነት፣ መለያ፣ ማንነት፣ ክብር፣ እሴት፣ ሀብት ላይ የጥፋት ሰይፍ ታጥቆ ይዘምታል? ጥቅማቸውና ትርፋቸውስ ምንድን ነው? ለዜጎች ከሀገራቸው የበለጠ ጥቅም ዋጋ ክብር ትርፍ ምን ነገር ኖሮ ለዚያ ሊጓጉ ሊቋምጡ ሊታለሉ ቻሉ? ለማንኛውም ጠላቶቻችን ይሄንን ያህል ተሳክቶላቸዋል፡፡ እጣ ፋንታችንም በመዳፋቸው ውስጥ እንደሆነ ያስባሉ ልክ ገመዱን በአንገታችን ላይ እንዳጠለቁና ገመዱን ሸምቅቀው ለህልፈት የማብቃትና ያለማብቃት ጉዳይ በእነሱ ፍላጎት እንደሚወሰንም፡፡ እውን ግን እንደዚያ ይሆን ይሆን?

የመገንጠልን ጥያቄ አግባብነት የሚያሳጡ አመክንዮዎች?

በሀገራችን ችግሮች አሉ ተብሎ መገንጠልን በመፍትሔነት መውሰድና ለመውሰድ መሞከሩ ፍጹም አግባብነት አይኖረውም፡፡ መገንጠል በምንም ተአምር መፍትሔ ሊሆን አይችልም አግተልትሎ የሚያስከትላቸው በርካታ ጥያቄዎች አሉና፡፡ ብቸኛው መፍትሔ በደሉ ቅሬታው ችግሩ እንዲቀር እንዲወገድ ለማድረግ ፍትሕ እኩልነት እንዲሰፍን መታገል ብቻና ብቻ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ያለ የኢትዮጵያ ሕዝብ አካል የሆነ ሕዝብ የመገንጠል መብት ሊኖረው የማይችልበት አምስት ዐበይት ምክንያቶች አሉ፡፡

 1. መግቢያችን ላይ ስለ ሀገር ትርጉም ባብራራንበት ወቅት ሀገር በጋራ የሚኖርባት ትልቅ ቤት ነች ማለታችን ይታሳል፡፡ በመሆኑም የዚያ ቤት መፍረስ በየትኛውም ጫፍ ላለ የዚያ ቤት ነዋሪ በቀጥታ ይመለከታዋል ይገደዋል ማለት ነው እንጂ ገንጣዩ ያለበትን አንድ ጫፍ አፍርሼ እወስዳለሁ ስለለ ጉዳዩ የሱ ብቻ ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም፡፡ ቤቱ የፈረሰው በአንድ ጫፍ በኩል ይሁን እንጂ የቤቱ መፍረስ በሌላኛው ጫፍ ላለው የቤቱ ነዋሪ ጉዳትና አደጋ ማድረሱ አይቀርምና፣ ሀገሬ ብሎ እዚያ ድረስ እየዘመተ በትውልድ ሁሉ ዋጋ ሲከፍል ኖሯልና፣ መሥዋዕት ሆኗልና፣ ከእነሱ አንዱ የዚያች ሀገር (የጋራ ቤት) ሕዝብ አካል የነበረ ብሔረሰብ መገንጠል ቢፈልግ ሌሎቹ ወይም ከፊሎቹ የማይፈልጉ ይሆናሉና፣ በዚህ ሰዓት በአንድም ወይም በሌላ አጋጣሚ የመገንጠሉ ዓላማ ቢሳካም እንኳ ግጭቱን ወይም ችግሩን ወደ ሌላ ዓይነት የቀውስ ዙር መለወጥ እንጅ የሰላም መፍትሔ ሆኖ አናገኝውምና፣ መገንጠሉን የማይፈልገው ቡድን የተገነጠለውን የሀገሩን ክፍል ለመመለስ መዋጋቱ አይቀርምና፣ የአንድ ጫፍ መፍረስ ከነአካቴውም ለአጠቃላዩ የቤት መፍረስ መንስኤ ይሆናልና በእነዚህ ምክንያቶች አንዱ ሌሎቹን አያገባችሁም ውሳኔው የግሌ ነው ሊል አይችልም ማለት ነው፡፡ በዚያ ቤት ጉዳይ ላይ ሁሉም ነዋሪዎች ይመለከታቸዋል ማለት ነው፡፡ ያ ቤት ለመገንባቱ የሁሉም አስተዋጽኦ ሊኖርበት ግድ እንዳለ ሁሉ በሌላው ጉዳይም እንዲሁ እኩል ይመለከታቸዋል፡፡
 2. በየትኛውም መመዘኛ ቢሆን እራስን ማጥፋት መፍትሔ አይደለም፡፡ ሀገር መገነጣጠል እራስን እንደማጥፋት ይቆጠራል፡፡ ሰው መቸም ካልታመመ የአእምሮ ጤናውን ካላጣ በስተቀር እራሱን አያጠፋም ካልታመመ የአእምሮ ጤናውን ካላጣ በስተቀር እራሱን አያጠፋም፡፡ በመሆኑም ሀገርን እንገነጣጥል የሚሉ አካላት ጤናም እንዲሁ ነውና መብት ሊሆን አይችልም፡፡ ራስን ማጥፋት ወንጀል ነው ወንጀልነቱ እራሱን ለሚያጠፋው ብቻ ሳይሆን እራሱን ሲያጠፋ በዝምታ ለሚመለከተውም ጭምር ነው፡፡ ስለሆነም የአእምሮ ጤና የተጓደለባቸውን ወገኖች ይሁንላችሁ እንዳሻችሁ ልንል አይቻለንም፡፡
 3. በአንድ ወቅት ያለ ሕዝብ በሌላ ወቅት የሚመጣን ሕዝብ መወከል ስለማይችል በእጣ ፋንታውም ላይ መደራደር አይችልም ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም የውክልናውን የአግባብነት ጉዳይ ጥያቄ ስለሚያስነሣ፡፡ በአካል የሌለ ግን የሚመጣ ሕዝብ አሁን ያለን ሕዝብ መወከልም ስለማይችል፡፡ አሁን ያለውም አሁን በሌለው ግን በሚመጣው ሕዝብ መወከል ስለማይችል፡፡ ይሄ በሆነበት ሁኔታ ሁለቱም አካላት እኩል መብት አላቸውና አንደኛው በሌላኛው እጣ ፋንታ ላይ እውቅናና ውክልና ባልተሰጣጣበት ሁኔታ ሊወስንበት አይችልም መብት የለውም፡፡ ይህንና መሰል ጉዳዮችን በተመለከተ የየትኛውም ትውልድ መብቱ የሚሆነው የነበረውን ጠብቆ ተንከባክቦ የተቀበለውን እሱም የማስተላለፍ ብቻ ነው፡፡ እሴት መቀነስ አይችልም መጨመር እንጂ፡፡
 4. የመገንጠል ጥያቄ መልስ መገንጠል በፈለገው አካባቢ በሚኖረው ሕዝብ ፍላጎት ከተወሰነና መብት እንደሆነ ከታመነ “ከዚህ በፊት ማንዴላ በሚለው ግጥሜ ላይ እንደገለጽኩት” ለኔ ለብቻዬ የሚለው ጥያቄ የመጨረሻ ማቆሚያ ግለሰብ ላይ ይሆናል እንጅ ብሔረሰብ ላይ ብቻ የሚቆም አይሆንም፡፡ ሀገሪቱ ከ 80 በላይ ብሔረሰብ አላትና ከሰማኒያ ብቻ ተቆራርጣ የምትቀር አይሆንም፡፡ በአሁኑ ወቅት በሀገራችን የተለያዩ ስፍራዎች በጎሳዎች መካከል በግጦሽ መሬትና በውኃ ሳቢያ የኔ ነው የኔ በመባባል እየተጋጨ አየተጫረሰ እንደምናየው የኔ የብቻዬ የሚለው ጥያቄ ወደ ጎሳም ይወርዳል ከጎሳም ወደ ንኡስ ጎሳ ከንዑስ ወደ ንዑስ እያለ ወደ አባወራ ይወርዳል፡፡ በመሆኑም አስተሳሰቡ ከቀላል ችግር ወደ ካባድና ወደ ሰፊ ችግር የሚከት እንጂ መፍትሔና ሰላምን የሚሰጥ አይደለም፡፡ እናም አስተሳሰቡ የተሳሳተ ብስለት የጎደለው የሰው ልጅን የሠለጠነ አስተሳሰብ ወደ ኋላ የሚመልስ ኋላ ቀር አስተሳሰብ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ መግቢያዬ ላይ እንዳልኩት ሀገርን የፈጠራት ሰፊ ፍላጎትና የአቅም ማደግ ነው ብለናልና፡፡
 5. ነባራዊ ሁኔታ ነው፡፡ ምን ማለቴ ነው እገነጣላለሁ የሚለው አካል ማንነት ጉዳይ ነው፡፡ እገነጠላለሁ የሚለው አካል ማንም ቢሆን የመገንጠል ዕድሉ ይሰፋል ማለቴ ሳይሆን በተለይም ደግሞ እገነጠላለሁ የሚለው ብሔረሰብ የኋላ ታሪክ ሲታይ ለዚያች ሀገር እንግዳ ወይም ባዕድ ከሆነ ሁኔታው አስገራሚ ገጽታ ይኖረዋል፡፡ ለምሳሌ ይህንን ጉዳይ በሀገራችን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ብናይ ኢትዮጵያ ውስጥ የመገንጠል ጥያቄ ያነሡትን እራሳቸውን የኦሮሞ ብሔረሰብ ተወካይ አድርገው የሚጠሩትን ኦነግን ብናይ የራስን ታሪክ ጠንቅቆ ካለማወቅ ካልሆነ በስተቀር የኦሮሞ ሕዝብ ለኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ እንግዳ ሕዝብ እንደሆኑ እያወቁ ይኘየንን ጥያቄ ማንሣት እጅግ የዋህነት ነው ልክ ሊሆኑና ጤነኞችም ሊያሰኛቸው የሚችለው ባለቤት አልባ መሬት ቢሆን ነበር፡፡ በመሆኑም ይሀንን ጥያቄ ማንሣቱ አግባብነት አይኖረውም ማለት ነው፡፡

በእነዚህ አምስት ነጥቦች ምክንያት ኢትዮጵያ ውስጥ የመገንጠል ጥያቄን ማስተናገድ ከቶውንም አይቻልም ድርጊቱም መፍትሔ ሳይሆን ጥፋት ነው፡፡

የወያኔ ሕገ መንግሥትና የመገንጠል ጥያቄ

ያደጉ ሀገራት ሕገ መንግሥታት ለምሳሌ የዩ.ኤስ. አሜሪካን ሕገ መንግሥት ያየን እንደሆነ እነኝህን ከላይ የጠቅስናቸውን አምስት ነጥቦች በቅጡ የተረዳ ይመስላል፡፡ ምክንያቱም ስለ ሉዓላዊ ሥልጣን ሲናገር ያውም በሀገሪቱ ላይ ሳይሆን በሕገ መንግሥቱ ላይ ነው “ሕገ መንግሥቱ የተመሠረተው በሕዝቡ በመሆኑ ሉዓላዊነቱም የሕዝቡ እንጂ የነገድ፣ የጎሳ ወይም የሃይማኖት ቡድኖች አይደለም” ይላል ፡፡ ልብ በሉ ሉዓላዊ ሥልጣን አንድ ሕጋዊ ሰውነት ያለው የአጠቃላይ የአሜሪካ ሕዝብ ነው አለ እንጂ በነገድ በጎሳ ስም የተለያየ ህልውና ላላቸው አካላት አላደረገም፡፡ ያውም በሕገ መንግሥቱ ላይ እንጅ በሀገሪቱ ላይ በእጣ ፈንታዋ ላይ ለመወሰን ዕድልና ክፍተት አልሰጠም ምን ያህል ጥንያቄ እንዳደረገ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ወደ ወያኔ ሕገ መንግሥት ስንመጣ ግን እጅግ በሚገርምና በሚያሳዝን መልኩ ነገሮችን ጠልቆና ረቆ ያለመረዳት ችግር ያለበት ግልብነትና እንጭጭነት ጎልቶ የሚታይበት ነው፡፡

ሁሉም ሉዓላዊ ሥልጣን በኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ውስጥ ይሆናል በማለት የብሐረብሔረሰቦችን መብት እስከ መገንጠል ድረስ ነው በማለት የሀገሪቱን ህልውና አደጋ ላይ በመጣልና ለማፍረስ በማሴር ተጀምሮ እስኪጨርስ የሚያወራው ብሐር ብሔረሰቦች እያለ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ አንድ ሀገር ሕዝብ ሕዝብ ተብሎ በወል የሚያስጠራውን ለሀገሩ ያለውን የጋራ የሀሳብ አንድነት አፈራርሶ ሕዝቦች በማለት አንድ ሀሳብና ፍላጎት ለአንድ ሀገር እንደሌላቸው ወይም እንዳይኖራቸው አድርጓል፡፡ ከዚህም በላይ ሀገርን በርእሰ ጉዳይ አንሥቶ ዕውቅና እንኳን ለመስጠት ሀገራችን ብሎ ስለሀገር ለማውራት የተሳነው የሞራል (የቅስም) ብቃትና ድፍረት የጎደለው ቁንጽል ደካማና ባዕድ ሕገ መንግሥት ነው፡፡

በአንድ በኩል የዚህ አስተሳሰብ መሠረት የወያኔ ባልሥልጣናት በተለያዬ ጊዜ ሲገልጹ እንደተደመጡት “የብሔር ብሔረሰቦች መብት እስከመገንጠል የሚለው መብት የተቀመጠው የብሔር ብሔረሰቦች መብት የት ድረስ እንደሆነ ለማሳየት እንጂ እንዲገነጣጠሉ ለማድረግ አይደለም፡፡ መብታቸው እስከተከበረላቸው ጊዜ ድረስ ይሄንን የመገንጠል ጥያቄ የሚያነሣ አይኖርምና መብታቸውን የሚነፍግ ሁኔታ ካጋጠመ ግን ዋስትናቸው ሕገ መንግሥቱ ነው በዚያ መሠረት የመሰላቸውን የመወሰን መብት አላቸው” ይላሉ እነ አቶ መለስ ያልተረዱት ያልገባቸው ነገር ቢኖር አንድ ብሔረሰብ የመገንጠል ጥያቄ ሊያነሣ የሚችለው መብቱና እኩልነቱ ካልተረጋገጠለት ብቻ አለመሆኑን ነው፡፡ መብታቸው ያለ እንከን ቢጠበቅላቸውም እንኳን ይህ የመገንጠል ጥያቄ ሊነሣ መቻሉን ነው፡፡ ለምሳሌ በአንዳንድ ሀገራት ላይ እንደተስተዋለው ሀብት ያለው የተወሰነው የሀገሪቱ ክፍል በመሳሳትና የተሻለ የሕዝባዊ ኑሮ እድገት ላሉበት ለሚኖሩበት የራሳችን ለሚሉት በዚያ አካባቢ ላለ ሕዝብ በመመኘት ከተቀረው የሀገሪቱ ከፍል መገንጠልን የሚፈልጉበት አጋጣሚ በተደጋጋሚ ነዳጅና የከበሩ መአድናት በተገኙባቸው የሌሎች ሀገራት የተለያዩ ቦታዎች የተከሰቱ ጉዳዮች አሉ፡፡ ልዩነትን ካላቻቻሉት በስተቀር መፈጠሩን ማቆም አይቻልም ይህ ገሀዳዊ እውነታ ነው፡፡ እንኳን በሀገር ማለት በጋርዮሽ ውስጥ ይቅርና በአንድ ሰው ውስጥ እንኳን ይፈጠራል ሰው ከራሱ ጋር መግባባት የሚሳነው ጊዜ በርካታ ነውና፡፡ ልዩነት ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ይሄንን መግታት ከቶውንም አይቻልም፡፡ ማድረግ የሚቻለው ማቻቻል ነው፡፡

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

የወያኔ ሕገመንግሥት ይሄንን ሀቅ መገንዘብ አልቻለም፡፡ ያውም እኮ ላያደርጉት ነው፡፡ እንግዲህ ለዚህ ነው ልዩነት በተፈጠረ ቁጥር ውሳኔው ያንተ ነው መባል አለበት የሚለው አስተሳሰብ ያልበሰለ ነው ይምለው፡፡ እናም የወያኔ ሕገ መንግሥት የአመለካከት አድማሱ በጣም የጠበበ ግራ ቀኝ የማያማትር ከአድማስ ትዕይንት(scenery) ጀርባ ስለሚኖረውና ስላለው ነገር ሁሉ ምንም የሚያውቀው ነገር የሌለው እንዳለም የማይረዳ ደካማ ሕገ መንግሥት ነው፡፡ እንዲያው ነገሩን አልኩ እንጂ ሕገ መንግሥታቸው የብሔር ብሔረሰቦች መብት እያለ ይደስኩር እንጂ የተባሉት መብቶቻቸው ለአንድም ቀን ቢሆን ተከብሮ አያውቅም፡፡ ወያኔ ህልውናውን የመሠረተውና ያረጋገጠው የእነሱን መብት በመንፈግና እነርሱን ጠርፎ በማሰር ላይ ነውና፡፡ ስለ እውነት ለመናገር ሳንወድ በግድ ቢሆንም ሀገሬ እንዲህ ዓይነት ሕገ መንግሥት እንዲኖራት ስለተደረገች እንዴት ሀፍረትና ውርደት ይሰማኛል መሰላችሁ፡፡

ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

amsalugkidan@gmail.com

ዕንቁ ቅጽ 6 ቁጥር 114 መጋቢት 2006 ዓ.ም.

Comments

 1. Why you lie?? It is surprising and sad that Amhara elites still don’t want to talk and write the truth. This elites were backwards in their thinking. They undermine the beuties of other non Amhara Ethiopians but they praise for unity. Oromo and other nations had been paying more lives in ethiopia wars. Because war is their main aim of Amharas to kill other non Amhara people by being in power and to reduce the non amhara population. During the feudal regimes, Non Amhara nations of Ethiopia had been paying more than 50% of their income to the government where as the northern Amhara and Tigre don’t pay any tax to the government. Still these stupid elites want and praise those regime system to come back.What can I tell you is that it is already died forever, design how to live in equality with other nations!!

 2. Thank you for the great article and God bless you Artist Amsalu.

Speak Your Mind

*