“የህዳሴ ግድብ ስምምነት ፊርማ እንዲዘገይ አመራር ሰጥቻለሁ” ጠ/ሚ/ር ዐቢይ

ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የተገዙ ሌት ከቀን እየደከሙ ነው

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን ጨምሮ ከአደራዳሪዎቹ ጋር በስልክ ከተነጋገሩ በኋላ የህዳሴ ግድብ ስምምነት ፊርማ እንዲዘገይ አመራር መስጠታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተናገሩ። ዐቢይ ከትራምፕ ጋር በስልክ መነጋገራቸው ይፋ ከሆነ በኋላ ራሳቸውን ተንታኝ ያደረጉ ወገኖች የስምምነት ፊርማው እንዲፈረም በተደራዳሪዎች ላይ ጫና እንደፈጠሩ በመግለጽ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሲያጠልሹዋቸው ከርመው ነበር።

ዶ/ር ዐቢይ ሰኞ በተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ባደረጉት ጥያቄና መልስ እንደገለጹት የህዳሴውን ግድብ አስመልክቶ የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎ መስጠትን በተመለከተ የሚደረግ አንድም ዓይነት ስምምነት እንደማይኖር አረጋግጠዋል።

ከፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ከአሜሪካው የገንዘብ ሚኒስትር ስቴፈን ሙኑሺን እና ከዓለም ባንኩ ፕሬዚዳንት ዴቪድ ማልፓስም ጋር በጋራ በስልክ መነጋገራቸውን ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ስለ ድርድሩ አካሄድ ከተገለጸላቸው በኋላ ፊርማው እንዲዘገይ አመራር መስጠታቸውን በይፋ አመልክተዋል። አደራዳሪዎቹ ኢትዮጵያ ላይ ጫና ያደርጋሉ በሚል ከየአቅጣጫው የሚሰነዘረውን ማጠልሸት ውሃ የደፉበት ዶ/ር ዐቢይ “ድርድሩ ሲጀመር ዋነኛው ጉዳይ የታችኛው ሀገራት ግድብ መሥራት አይችሉም የሚል ነበር፤ ነገር ግን መንግሥት በነበረው ቁርጠኛ አቋም ሥራውም ተጀምሯል፤ ድርድሩንም ጎን ለጎን እንዲካሄድ አድርጓል” ብለዋል።

“ዋናው ጉዳይ በእጃችን ነው” ያሉት ጠ/ሚ/ሩ ዋናው ቁም ነገር ሥራውን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ አመልክተዋል። ለስምንት ዓመታት ድርድር ሲካሄድ ቢቆይም መቋጫ አለመገኘቱን ያስታወሱት ዶ/ር ዐቢይ ከዓለም ባንክ እና ከአሜሪካ ጋር በተካሄደ ውይይት መግባባት ያልተፈጠረባቸው ጉዳዮች መልስ እያገኙ መምጣታቸውን፤ ነገር ግን አሁንም መታየት የሚገባቸው ጉዳዮች መኖራቸውን አስረድተዋል።

በድርድሩ በግብጽ በኩል ጉዳት ይቀነስልን የሚለው የስጋት ጥያቄ ቢኖርም ኢትዮጵያ የውሃ ሀብቷን እንዳትጠቀም በሚገድብ መልኩ እንደማይሆን እንቅጩን አስታውቀዋል። ግንባታው በፍጥነት ስህተቶቹን አርሞ እየተከናወነ መሆኑንንም አመልክተዋል። ግንባታው እየተፋጠነ ድርድሩ ባስቸኳይ መጠናቀቅ እንዳለበትም ጠቁመዋል።

“የምንገኘው ጊዜ 2012 ዓ.ም. ይባላል” ሲሉም ስለወቅቱ የፖለቲካ ግለትና ስጋት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። “አሁን 2012 ቢሆንም በ1960ዎቹ የፖለቲካ መስመር የሚጓዙ ፅንፈኞች የሚፈጥሩት የፓለቲካ ሤራ ሕዝብን እየጎዳ ነው። ዛሬ ትናንት አይደለምና ዋጋ እየተከፈለም ቢሆን ይህ ጊዜ ያልፋል” ሲሉ ውስብስቡ የፖለቲካ አየር እንደሚጠራ ገልጸዋል። ሲያብራሩም ታስሮ የተለቀቀ ጥጃ ሲፈታ እንደሚቦርቅና ሲደክመው እንደሚያርፍ ሁሉ በፖለቲካውም የሚጨፍሩት ወገኖች እንደ ጥጃው ጊዜያቸውን ጠብቀው ሲደክማቸው ያርፋሉ ብለዋል። 

የሚስተዋሉት የሠላም እና የደኅንነት ችግሮች ታስሮ የተፈታ ፖለቲካ የፈጠረው ያለመብሰል ችግር መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምክር ቤቱ አስረድተዋል። እየተለወጠች ባለች ሃገር ያልተለወጠ የፖለቲካ ሃሳብ ይዞ መጓዝ አሸናፊም ተሸናፊም እንደማይኖረውም አስምረውበታል።

ለማሸነፍ የሚፈልግ አካል ሁሉ ለምክክር፣ ለውይይት፣ ለሠላም እና አንዱ የሌላውን ክፍተት ለመሙላት መሥራት እንደሚጠበቅበትም አብራርተዋል። “የሕዝብ ግጭቶችን የፖለቲካ መንገድ አድርጎ መውሰድ ግን ለከፋ አደጋ ያጋልጣል” ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው።

የሕግ የበላይነትን ለማስከበር የሚከናወኑ ሥራዎችን ለምክር ቤት አባላቱ በዝርዝር ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሕግ ማስከበር ሥራው በተለይም በሁለት መንገዶች እንቅፋት እየገጠመው መሆኑን አንስተዋል። “ሕዝቡ በከፍተኛ ደረጃ መንግሥት ህግ እንዲያስከብር ይጠይቃል፤ ነገር ግን ህግ ለማስከበር እርምጃ መውሰድ ስንጀምር ደግሞ ቅሬታ ይነሳል” ብለዋል።

ሠላማዊ በሆነ መንገድ በማይንቀሳቀሱ እና ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት በሚሞክሩ አካላት ላይ በአንድ ሃገር ሁለት መንግሥት ስለማይኖር እርምጃ እንደሚወስዱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አልሸሸጉም።

ዶ/ር ዐቢይ ለግንዛቤ እንዲሆን በሚል ለውጡን አንቆ የያዘውን ጉዳይ “ጥልፍልፍ፣ የተወሳሰበ፣ በዘመድ፣ በቤተሰብ፣ በጓደኛነት፣ በክሊክ፣ በዘር፣ በጥቅም እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ የተተበተበ” በማለት ነው የገለጹት። ይህ ትብትብ ሲፈለግ የሚያስቆም፣ ሲፈለግ የሚዘጋ ሤራ አምራችና አከፋፋይ የሆነ እንቅስቃሴ ነው። አዲሱን ሃሳብ በአዲስ የሰው ኃይል ለመተግበር የተጀመረውን ሂደት ያጓተተውና ፈተና የሆነው ይህ ኃይል ነው ብለዋል።

በዚህ ጥልፍልፍ መረብ ሳቢያ አገረ መንግሥቱ ቅርጽ ኖሮት የማያውቅ፣ እንደ መሪ የተወሰኑ ሰዎች ፊት ለፊት ቢታዩም በአገሪቱ ውስጥ “ስቴት ካፕቸር” እንደነበር አስታወሰዋል (“ስቴት ካፕቸር” ማለት የግል ፍላጎት ስልታዊ በሆነ መንገድ ጠየፖለቲካ መበስበስን በማስከተል የመንግሥትን የውሳኔ አሰጣጥ ሒደትን ለራሱ ጥቅም መቆጣጠር ነው)። አያይዘውም ይህ ጥልፍልፍ እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ የዘለቀ በመሆኑ ለመበጣጠስ አስቸግሮ መቆየቱን አልሸሸጉም።

ህዝብ ጭብጡን እንዲይዝና የራሱን ፍርድ እንዲሰጥ ይህን አደገኛ ያሉትን የሤራ ድር ዕንቅፋት ለመሆን ቢያስብም በበርካታ ፈተና በርካታ በጎ ተግባሮች መፈጸማቸውን አውስተዋል።

አልቃይዳና አልሸባብ ብቻ ሳይሆኑ ከአገር ውስጥ ሁኔታዎችን የሚያመቻቹ መኖራቸውን ያልሸሸጉት ዶ/ር ዐቢይ የመከላከያና የደኅነት ኃይሉ ስላከሸፈው ከፍተኛ የሽብር መረብ በቅርቡ ሰፊ ማብራሪያ እንደሚቀርብ አመልክተዋል። በዚሁ ጥቆማቸው በአማራና ኦሮሚያ ክልል በርካታ ሰዎች በገንዘብ ኃይል በተላላኪዎች መመልመላቸውን በጨረፍታ ጠቁመዋል።

የትግራይ ህዝብ ወኪሎችን ታባርራላችሁ ለተባለው “በሚኒስትርነት ቦታ ከአስር በላይ አሉ” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ በፌደራል መንግሥቱ የትግራይ ሕዝብ ውክልና ወደፊትም ቢሆን እንደሚቀጥል አስረድተዋል። ጠያቂዋን የምክር ቤት አባል በጅምላ ያለ ሙሉ መረጃ ሃሳብ ማቅረብ አግባብ እንዳልሆነ ገስጸው “አሁን አገር እየመራ ያለው የብልጽግና ፓርቲ ነው። በምርጫ ቦርድ ሕግ መሠረት ሕጋዊ ወራሽ ነው። በዚህ ጉዳይ መምታታት የለም። እኔም ካቢኔዬን በፈለኩት መንገድ የማዋቀር ሕገመንግስታዊ ሥልጣንም እንዳለኝ መታወቅ አለበት” ሲሉ የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ትህነግ/ህወሓትንና የትግራይ ህዝብን ለይቶ ማየት እንደሚያስፈልግም አስረድተዋል።

ከምርጫ ጋር ተያይዞ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምርጫ ቦርድ ተጠሪነቱ ለጠ/ሚ/ሩ ሳይሆን ለሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት በመሆኑ ምክርቤቱ የምርጫ ቦርድ ኃላፊዎችን እንዲጠይቅ የምክርቤቱን የሥራ ኃላፊነት አስታውሰዋል። ምርጫን በተመለከተ አሥፈጻሚው አካል የሎጂስቲክና የመሳሰለው ሥራዎችን ከመሥራት በስተቀር ምርጫ መቼ መካሄድ እንዳለበት የመሳሰለውን የሚወስን ባለመሆኑ የተከበረው ም/ቤትና ጠያቂ ጥያቄውን ወደሚመለከተው እንዲወስድ አሳስበዋል።

“ለገጽ ግንባታ ነው የሚሠራው” በሚል ለቀረበላቸው ዘለግ መልስ የሰጡት ዶ/ር ዐቢይ የተሃድሶ ኃይሉ ወደ ሥልጣን ሲመጣ መጀመሪያ ያፈረሰው እንዲያውም የገጽ ግንባታ ሚ/ርን እንደሆነ አስታውሰዋል። በኢንዱስትሪ ፓርክ፣ በስኳር ፕሮጀክት፣ በኃይል (ኤሌክትሪክ) አቅርቦት፣ በቴሌኮም፣ በገቢ አሰባሰብ፣ በሕዳሴ ግድብ፣ ወዘተ የተሠሩ የልማት ዝርዝሮችን ከተናገሩ በኋላ ይህ እንደ ፕሮፓጋንዳ መነገር ሲገባው እንዲያውም የመንግሥት ችግር የተሠራውን እንደሚገባው ለሕዝቡ አለመናገር መሆኑን አስታውቀዋል። ይህ ሁሉ ሥራ ግን የገጽ ግንባታ ሳይሆን የልማት ሥራ መሆኑን አስታውሰዋል።

ከዚህ ውጪ ግን ምክርቤቱ ባጸደቀው በጀት ውስጥ አንድም ብር ለገጽ ግንባታ የሚል እንዳልነበረ ያወሱት ጠ/ሚ/ር ዐቢይ በአዲስ አበባ የሚሠሩትን በተመለከተ ከሆነ ለፕሮጀክቶቹ የሚወጣው ወጪ ከኢትዮፕያውያን ባለሃብቶችና ከውጪ ለጋሶች የተገኘ መሆኑን አስታውሰዋል።

“የብዙ ችግሮች ምንጭ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ለነበሩ ችግሮች ዋንኛ ምንጭ የነበረው ራሱ ገዢው ፓርቲ ነው” ያሉት ዶ/ር ዐቢይ “ነገርግን ለዚህ ምክርቤት ማረጋገጥ የምፈልገው በአጭር ጊዜ፣ በመካከለኛ ጊዜ፣ በብቃት ለእንደከወንነው ሁሉ የሤራ፣ የተንኮል፣ የደባ፣ የሽብር ፖለቲካውንም አሸንፈን ኢትዮጵያን የምናስቀጥል መሆኑን ግን በልበሙሉነት ልገልጽላችሁ እችላለሁ” ብለዋል።


ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ንብረት ናቸው። ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን።

Comments

  1. ፓለቲከኞች በሰው ህይወት ላይ ጥባጥቤ የሚጫወቱ የቀልደኞች ጥርቅም ናቸው። አንድ በብሄር ነጻነት ስም ሲነግድ፤ ሌላው በቋንቋውና በሃይማኖቱ ይሰለፋል። በሃበሻው ምድር ደግሞ መናቆርና ከእጣት እጣት ይበልጣል ብሎ መፋለም ወግና ባህል ሆኖ ህዝባችን ለመከራ እየዳረገ ይገኛል። ያለፈው ከአሁኑ የሚለይበት በክልሉ የሚተነፍስ መሆኑ ነው። ለአመታት እይታቸው ሁለገብ ነው የተባለላቸው እንደ መራራ ያሉት ፓለቲከኞች በዘራቸው ተሰልፈው አላማቸው የሚኒሊክን ቤተመንግሥስት በማፍረስ የኦሮሞን መገባት ነው እያሉ ሲለፉ መስማት የቱን ያህል የሃገራችን ፓለቲካ እንደተሳከረ ያሳያል። ሌላው የኦሮሞ የውስልትና ፓለቲካ በዶ/ር አብይ ላይ የተከፈተው ዘመቻ ነው። እንደ ጃዋር ያሉት የሙታን ስብስቦች የሚያሰራጩት የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ እንኳን ተምሬአለሁ እያለ ጉራ ከሚነዛ ፓለቲከኛ ቀርቶ ፊደልን ካልቆጠረ የሚመነጭ ሃሳብ አይሆንም። አማራ አቅፎ እያደረ ኦሮሞ ነኝ ይላል ይሉናል እብዶቹ የኦሮሞ ፓለቲከኞች። ሌላው ከወያኔ ጋር ቂጡን ገጥሞ “ከእኔ እቃ መግዛት ከፈለክ ኦሮምኛ መናገር አለብህ” ብሎ ያላዝናል። የሚያሳዝነው ይህ ሰው የቋንቋ መምህር መሆኑ ነው። የሙታን ፓለቲካ ይሉሃል ይህ ነው። ይህ ቀባጣሪና ዘረኛ ፓለቲከኛ “እኔ የምታገለው ለኦሮሞ ህዝብ ነው። በኦሮሞ ክልል ውስጥ ለሚኖሩ ሌሎች ህዝቦች አልታገልም” ድሮስ ጠባብ ብሄርተኞችን እናውቃቸው የለ። ሰውነታዊና አለም አቀፋዊ እይታ መች ኑሮአቸው ያውቃል። የሚያስቡበትና የሚተነፍሱበት ጭንቅላትና ሳንባ የተገጠመላቸው እዛው ዘራቸው ጉያ ሥር ነው። ጠባራ ፓለቲከኞች!
    አሁን ጠ/ሚሩ ፓርላማ ቀርበው ያሉት ሁሉ ግማሽ እውነት ሌላው ደግሞ በባዶ ሥፍራ የተሞላ እህል የማያበቅል አፈር ነው። የታገቱት ተማሪዎች ሁሉም ተማሪዎች አይደሉም ሲባል ስሰማ ባይማር ሰው መታገት አለበት እንዴ? ሌላው የወያኔ ባለስልጣኖች በዘራቸው የተነሳ ተባረሩ ይሉናል። አይ ጊዜ በእውነት አሁን ሰው በዘሩ መባረር የጀመረው አሁን ነው? 27 ዓመት ሲገድሉ፤ በቆመ ሰው ላይ መኪና ሲነድ መርዝ ሲያበሉ ሲያስሩ የኖሩት እነርሱ አይደሉምን? ጥያቄው ከትግራይ ተወላጅ መምጣቱ ምን ያህል የዘረኝነት ፓለቲካ ሥር እንደ ሰደደ ያሳያል። የዶ/ር አብይ ውጊያ ከወያኔ፤ ከኦሮሞ አክራሪ ሃይሎች፤ በዚሁ ዙሪያ ከሚደርሰው ደባ ጋር ተያይዞ መንግስታቸው አፋጣኝ ምላሽ ለነገሮች አለመስጠቱን ተከትሎ ከአጥፊ ሃይሎች ጋር አብረው የሚነጉዱ ተላላዎች ከሚያናፍሱት የፈጠራ ከሚያመነጨው መርዝ ጋር ነው። የወያኔም ሆነ የኦሮሞ ሃይሎች ዋና አላማ ጠ/ሚሩ ከሥልጣን አውርዶ ራሳቸውን መንበሩ ላይ ለማስቀመጥ ነው። የኦሮሞ ፓለቲከኞች ሁለት ነገርን ይጠጠላሉ። ኢትዮጵያዊነትንና የኢትዮጵያ ተዋህዶ ኦርቶዶክስ ቤ/ክ። መጤዎች እየተባሉ ከቀያቸው ተፈናቅለው መከራ ላይ ያሉት ወገኖቻችን ምስክር ናቸው። ሴትን የሚደፍር፤ አንገት የሚቆርጥ፤ የሰውን የመኖሪያ ቤትና የንግድ ተቋማት በእሳት የሚያጋይ የኦሮሞ መንጋ እየተንጋጋ አንድም ቀን ይህ ነገር ልክ አይደለም አቁሙ የሚል አንድም የኦሮሞ ፓለቲከኛ የለም። አላማቸው በምንም ይሁን በማንም ስልጣን ላይ መውጣት ስለሆነ ያው መንገዛገዛቸው እየታየ ነው። ትላንት ወያኔ እልፎችን ሲጨርስ ምንም ድምጽ ያላሰሙት አሁን የዶ/ር አብይ መንግሥት ይህን ሰርቶ ያን ሰርቶ የሚሉት በማጥላላት እርሱን ከስልጣን አውርደው ሌላ መዝባሪ በቦታው ለመተካት እንጂ የተሻለ መንግሥት ይመጣል ብሎ ማሰብ ቂልነት ነው።
    የአባይ ግድብን በተመለከተ የፊርማው ጉዳይ መዘግየቱ መልካም ነው። የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ድንፋታም ሆነ ማስፈራሪያም መወሰድ ያለበት “አንፈራም” በሚልና የራስን ጥቅም በማስከበር ላይ መሆን አለበት። በመሰረቱ የአለም ባንክ አስታራቂ መሆኑ ቀበሮን በግ ጠብቂልኝ እንደማለት ነው። የዓለም ባንክ የ3ኛ አለም ሃገሮችን እድል ፈንታ ያጨለመ፤ ለምዝበራና ለመዝባሪ አሳልፎ የሰጠ የሃያላን በተለይም የአሜሪካ የመመዝበሪያ ሃይል ነው። ስለሆነም ጠ/ሚሩ የሚደረገውን ሁሉ ሁሉ በሃገር ውስጥ ካሉ የተፋሳሽ ወንዞች ባለሙያዎች ጋር፤ ቢቻል በአለም ላይ ካሉ ምርጥ ምሁሮች ጋር ከተመከረበት በህዋላ ቢፈረም ይመረጣል። የውጫሌው ውሉ ለኢትዮጵያዊያን ትምህርት ሊሆን ይገባል። የግብጽ የሃበሻውን ምድር በአባይ የተነሳ እወራለሁ ማለት ተንጋሎ መትፋት ነው። አይሆንም፤ አይሳካም። የአባይን ወንዝ አቅጣጫ በማዞር ግብጽን ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማስጎብደድ ይቻላልና!
    በመጨረሻም የዶ/ር አብይ መንግሥት ብዙ ችግሮች ውስጥ የገባና ገና የበፊቱን የወያኔ የአሰራር ስልት ያልበጠሰ በብዙ ገፊ ሃይሎች ውስጥ ሆኖ ለመራመድ የሚሞክር መንግሥት ነው። የዶ/ር አብይ መንግስት ከፈራረሰ የቀን ጅቦችን የሚያስንቅ ሌላ ባለ ቀንድ ጅብ እንደሚመጣ መጠራጠር የለባችሁም። የዶ/ር አብይ መንግስት ሊደገፍ ይገባል ባይ ነኝ። ከዚህ ውጭ ያለው አተካራ ሁሉ የሃገሪቱን መከራ ያራዝማል እንጂ ፋይዳ አያመጣም።

Speak Your Mind

*