በመቶዎች የሚቆጠሩ ጋዜጣዊ መግለጫዎች

ገዢው አምባገነን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት በየዕለቱ በሚያደርገው ፀረ-ኢትዮጵያዊ ተግባር፤ የተለያዩ የፖለቲካ ሕዝባዊ ስብስቦች መግለጫ ያወጣሉ። አዳዲስና ነባር የፖለቲካ ድርጅቶች፤ አለን በማለት ስማቸውን በአንባቢዎች ያስመዘግባሉ። ለመሆኑ ጋዜጣዊ መገለጫዎች ለምንድን ጉዳይ ነው የሚወጡት? ማነው የሚያወጣቸው? መግለጫዎችን ተከትሎ የሚተገበሩት ምንድን ናቸው? አሉስ ወይ? መግለጫ አውጪዎቹና መግለጫ ያላወጡ የፖለቲካ ሕዝባዊ አካሎች መለያቸው ምንድን ነው? መግለጫዎችና አውጪዎቻቸው፤ ሕዝባዊ ናቸው ወይንስ ጠባብ ወገንተኛ? መልዕክት አላቸው ወይንስ አደረግሁ ለማለት የተወረወሩ? አስፈላጊነታቸውስ ምን ያህል ነው? በተደጋጋሚ ጋዜጣዊ መግለጫ በተንጎደጎዱ ወቅት የደረሱኝ እጦማሮች ነበሩ። ሁሉም ወቀሳዎች ናቸው። “ለምን መግለጫ አታወጣም?” “ካሁን በፊትም ዝም ብለሃል!” የሚሉና ሌሎችም ከጠላት ጋር ወግነሃል ያሉኝም ነበሩባቸው። ለምንድን ነው መግለጫ ማውጣት ያለብኝ? መግለጫ አላወጣም። ይሄን ግልጽ በሆነ መንገድ ማስቀመጥ አለብኝ።

መንግሥታትና ድርጅቶች መግለጫ ሲያወጡ፤ መሠረታዊ ዓላማው፤ ጉዳዩ ካተኮረባቸው አካላት ጋር ተባባሪ መሆናቸውን አንባቢ ወይንም አዳማጭ እንዲያውቅላቸው አይደለም። መግለጫውን የሚያወጡት፤ ነግ ለኔ ብለው፤ ካሁኑ ቀድሜ እርምጃ እወስዳለሁ ማለታቸው ነው። ከማንኛውም መግለጫ ጋር፤ አብሮ የሚሄድ መልዕክት አለ። “የሚያስፈልገውን ለማድረግ እንጥራለን!” “ከዛሬ ጀምሮ ይሄን ወይንም ያኛውን እናደርጋለን!” “በሚያስፈልገው ነገር ሁሉ ልንረዳችሁ ዝግጁ ነን!” “ሊረዷችሁ የሚችሉ ሰዎችን ልከንላችኋል!” “ለመቋቋሚያ እንዲያግዛችሁ ገንዘብ ልከንላችኋል!” እና የመሳሰሉት ናቸው። እንግዲህ ልብ ብለን ብናጤነው፤ ዋናው የመግለጫው ማሠሪያ፣ ይሄ ከወደኋላ የተከተለው ተግባር ነው። እስኪ ወደኛ፤ በተለይም የገዢውን ቡድን ተግባር የሚያወግዙትን ጋዜጣዊ መግለጫዎችና አውጪዎቻቸውን እንመለስ።

በጠላትን ፈርጀው የሚታጋሉትን ገዢ ቡድን፤ “ይሄን በማድረጉ አውግዘናል!” ማለት ምንድን ነው ትርጉሙ? ካወገዙስ በኋላ ምንድን አንው የተከተለው? “ድርጅታችን የበለጠ ትግሉን ይቀጥላል!” ማለትስ ምንድን ነው ትርጉሙ? “ያንን እስኪያደርግ ድረስ የበለጠ አልተጋልንም!” የሚል ኑዛዜ ነው? “የታሰሩትን እንዲፈታ እንጠይቃለን!” ማለት ለፌዝ ነው? “ከሌሎች ጋር እንተባበራለን!” የሚል ማስፈራሪያ አስቀምጦ ድምፅን ማጥፋትስ ለምን አስፈለገ? በተለይ የመተባበርን ጉዳይ አስመልክቶ፤ “እተባበራለሁ!” ያላለ ድርጅት የለም። ትግሉ “ያለአንድነት የትም አይደርስም!” ያላለ ድርጅት የለም። አስፈላጊነቱን ያላሰመረ፣ የሕዝቡ ጥያቄ መሆኑን ያላስገነዘበና ጥሪውን በተደጋጋሚ ያላወጀ ድርጅት የለም። ታዲያ አሁን የት ላይ ቆመናል? መግለጫዎቹ አደረግሁ ለማለት ነበር የወጡት? ለመተባበር ጥሪ ያደረገ ድርጅት፤ ከወዲሁ አብሮ የመሥራትን አስፈላጊነት ማመን ብቻ ሳይሆን፤ ለማስተባበርም ኃላፊነቱን መውሰዱ ነው። ታዲያ ያንን ኃላፊነት ለመውሰድ የወሰነ ድርጅት፤ ሌሎች ለሚጠሩት ትብብር ለምን መልስ መሥጠት ገደደው? ምን መልስ ሠጠ? እኔ ለጠራሁት ሌሎች መልስ ይሥጡ እንጂ፤ ሌሎች ለጠሩት እኔ መልስ አልሠጥም ማለት ይሆን? አስመሳይነት ማለት ምን ማለት ነው? ዋሾነት በምን ይከሰታል? በዚህ ጉንጉን የተተበተበ ሂደት ምን ያህል ካለበት ፎቀቅ ማለ ይቻላል?

እዚህ ላይ ነው የኔ መግለጫ አለማውጣት ትርጉም የሚሠጠው። የምደግፈው ተግባራዊ ጉልበት በማልሠጥበት ሂደት፤ መግለጫ አላወጣም። በርግጥ አንዳንድ ያደረግኋቸውን ለማመላከት፤ የእስላሞችን እንቅስቃሴ አስመልክቶ በግፍ መሪዎቻቸው ሲታሰሩ እኛም ሰለምን፤ በማለት ከትቤያለሁ። አብረሃ ደስታ ሲታሰር አሻንጉሊቶች ናችሁ በማለት ከትቤያለሁ። ሌሎችንም በዚሁ ማስታወሻ መድረኬ ጠቃቅሻለሁ። ዋናው ቁም ነገር ግን፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላት ብዬ ያሰቀመጥኩትን ቡድን፤ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ይሄን! ወይንም ያንን! ሠራ ብዬ መግለጫ በማውጣት ውግዘት አላሽጎደጉድም። ጠላት ከዚያ የተለዬ ምን ሊያደርግ ኖሯልና! ጠላቴ ብዬ ፈርጀዋለሁ እኮ! ይልቅስ ይሄንን ጠላት ብለን የፈረጅነውን አካል፤ በተግባር በመተባበር ለመጣል በአንድነት እንሰለፍ።

አንዱዓለም ተፈራ – የእስከመቼ አዘጋጅ

ማክሰኞ መጋቢት ፲፫ ቀን፣ ፳፻፰ ዓመተ ምህረት

eske.meche@yahoo.com


“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡

Speak Your Mind

*