እንዴት ከዘቀጥንበት ወጥተን ወደ ፊት እንራመድ?

ባለፉት ወራት ባገራችን የተከሰተውን አሳዝኝና ትርጉም የለሽ ግድያን በተመለከተ የተለያዩ የመንግሥትና የግል ሚዲያ ተቋማት በየፊናቸው ያስተላልፉ የነበረውን ዜና ከያለንበት ሆነን ስንሰማውና በቴሌቪዥን መስኮቶቻችን ስንመለከተው እንደነበር ይታወሳል። አዎ! ሰዎች በግልጽ በአደባባይ እየተቀጠቀጡ ሲገደሉ አይተን በእጅጉ አዘንን።

እጅግ በጣም አሳዛኝና ምነው ኢትዮጵያ ውስጥ ባልተፈጠርኩ የሚያሰኝ የጭካኔ ጣራ የታየበት ዓመት! በወጣትነት ዘመናችን ሲነገረን የነበረውና እኛም እንደወረደ ስንጋተው የነበረው ኢትዮጵያዊ ጨዋነት፣ ባህሉን አክባሪና ከሁሉም ጋር ተስማምቶ በፍቅር ኗሪ፣ የደከመውን የሚያበረታታና ያዘነውን የሚያጽናና፣ ፈሪሃ እግዚአብሄርን በመላበሱ በአምላክ ፍጡር ላይ ጉዳትን የማያደርስ ቅዱስ ሕዝብ ወዘተ የሚባለው ባሕላዊ እሴቶቻችን ወዴት እንደተነኑ በበኩሌ አልገባ ካለኝ ውሎ ሰንብቷል።

የዚያኑ ያህል የሚዘገንነው ደግሞ የሕዝባችን ከሚያየው ይልቅ ከሚሰማው ብቻ ተነስቶ እርምጃ ለመውሰድ ያለውን ችሎታ ነው። ብዙውን ጊዜ እንዳስተዋልኩት ከሆነ ሕዝቦቻችን የሚሰሙትን ወሬ እውነተኝነት ለማረጋገጥ ሴኮንድ እንኳ ሳያጠፉ፣ የሰሙትን ወሬ እንዳለ፣ ከተቻለም ጆሮያቸው ሊሰማ በሚፈልገው ልክ አመቻችተው ተመሳሳይ አስተሳሰብን ለሚያስተናግዱ ጓደኞቻቸው ያቀብላሉ።

በዚሁ ሂደት ውስጥ ውጭ አገር የከተሙ የግል ሚዲያዎችና አፍቃረ – ፌስቡኮች ደግሞ ወሬው እንደደረሳቸው ለአርዕስታቸውም እንደሚመች አሳምረውት፣ አገሪቷ ከሰሜን እስከ ደቡብ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ታምሳና ሕዝቦች ተገዳድለው ሕልውናዋ በቀጭን ገመድ ላይ ተንጠንጥሎ ይገኛል ብለው ማስተጋባት ይጀምራሉ። የወሬዎቹ ይዘትም ወገንተኛና አንዱ ቡድን በሌላው ላይ ስላደረሰው ወይም ሊያደርስ ስለተዘጋጀው ጥቃትና እንዴት ለመከላከል ብሎም ለመልሶ ማጥቃት መዘጋጀት እንዳለባቸው ነው። በአጭሩ፣ በአገሪቷ ሰፍኖ ያለው ድባብ “እኛና” “እነሱ” በሚል ሁለት ጎራ የተከፈለ ይመስለኛል። የዚህ ሁሉ ፊታውራሪ ደግሞ ከሁሉም ብሄር የተውጣጡ፣ ሳይወከሉ ተወክለናል ወይም የሕዝባችን አደራ አለብን የሚሉ ጽንፈኛ ኤሊቶች ናቸው።


“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ። ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣአቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው።

Comments

  1. Thanks

Speak Your Mind

*