ሀዋሳ የጦርነት አውድማ አልሆነችም

በተነሳው ተቃውሞና ግጭት ጉዳት የደረሰባቸው አሉ

የሲዳማን የክልልነት ጥያቄ ለዛሬ ለማወጅ መቀጠሩን ተከትሎ በሐዋሳ እና አካባቢዋ ግጭት ተቃውሞ መከሰቱ ተገለፀ ። ከዚህ ጋር ተያይዞ ከተማዋ የጦርነት አውድማ እንደሆነች ተደርጎ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚወራው ሐሰት መሆኑ ተነገረ ።

የጥያቄ አራማጆች ለአዣንስ ፍራንስ ፕረስ እንደገለፁት የሲዳማ ሽማግሌዎች እና ወጣት የጉዳዩ አቀንቃኞች ዛሬ ጠዋት ሊያካሂዱት ያቀዱት ስብሰባ አካባቢውን በዘጉት በፀጥታ ኃይሎች ተደናቅፏል። ባለሥልጣናት ወደዚያ ባለመምጣታቸው፤ እና ወደ መሰብሰቢያው ስፍራም እንዳያልፉ ያገዷቸው የፀጥታ ኃይሎች ላይ ወጣቶቹ ድንጋይ መወርወራቸውንም ዘገባው አመልክቷል።

ሐዋሳ ከተማ ላይ በቁጣ ወደ ጎዳና የወጡት ዜጎች ጎማ በማቃጠል ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በተፈጠረው ግጭትም ቢያንስ የአንድ ሰው ሕይወት መጥፋቱን ሌሎች ደግሞ መጎዳታቸውን የሆስፒታል ምንጮች ለዶይቼ ቬለ «DW» ገልጸዋል።

የሐዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዝናው ሳርሚሶ ጭንቅላቱን በጥይት መመታቱ የተገለፀው ተጎጂ ወደ ሐኪም ቤት ከሄደ በኋላ ሕይወቱን ማጣቱን ለሐዋሳው ዘጋቢያችን ሸዋንግዛው ወጋየሁ ገልጸዋል።

«መጀመሪያ ላይ ትንሽ ጭንቅላቱ ላይ የቆሰለ ሰው ገብቷል። እሱ የመጀመሪያ ርዳታ ሰጥተን ወደ ቤቱ ሄዷል። ከዚያ ቀጥሎም ደግሞ አንድ ሴት ነበረች የመጣችው። ባጠቃላይ አራት ወንድ እና አንድ ሴት ነበር የመጡት። አንደኛው ከአዳሬ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የመጣ ከዚያ ሪፈር የተደረገ ሰው ነበረ ጭንቅላቱ ላይ ነበር ቆስሎ የነበረው፤ ቁስሉ አሁን ሀኪሞች እንዳረጋገጡት በጥይት የተመታ ይመስላል። ከፍተኛ የሆነ ቁስል ነው። እሱ አዳሬም ወደ እኛ እንደላከ እኛ ጋርም ብዙ ሳይቆይ ሊያርፍ ችሏል።»

ሌሎቹ ተጎጂዎችን በተመለከተ የሚታየው እስካሁን ለከፋ አደጋ የሚያደርስ እንዳልሆነም አክለው ገልጸዋል። ግጭት ተቃውሞው በሐዋሳ ከተማ የተወሰነ እንዳልሆነ ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ። ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ተገቢውን ምላሽ ካላገኙ ዛሬ ማለትም ሐምሌ 11 ቀን 2011ዓ,ም የሲዳማን ክልልነት ለማወጅ መዘጋጀታቸውን የጉዳዩ ጠያቂዎች ሲያሳስቡ መሰንበታቸው ይታወቃል።

ሐዋሳ ከተማ ሐሙስ ዕለት

ሐሙስ ከቀትር በፊት የሲዳማ አርነት ንቅናቄ ሲአን የሲዳማ ተወላጆች እንዲረጋጉ አሳስቦ ነበር። የሲአን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደስላኝ ሜሳ የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ጥያቄውን ተቀብሎ ሕዝበ ውሳኔ ለማድረግ እንዲቻል ቅድመ ዝግጅት በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ ለዶቼ ቨለ «DW» አረጋግጠዋል። እንዲያም ሆኖ እስካሁን አካባቢው ስለመረጋጋቱ የተሰማ ነገር የለም።

በሌላ በኩል ሀዋሳ ከተማ የጦርነት_አውድማ እንደሆነች ተደርጎ በማህበራዊ ሚዲያ የሚሠራጨው መረጃ ከእውነት የራቀ ነው። በዚህ ፈታኝ ወቅት ሀገሪቱን ወደማያባራ ግጭት ውስጥ እድትገባ ፅኑ ፍላጎት ያላቸው የፌስቡክ አርበኞች በመኖራቸው የምንሰማቸውን መረጃዎች በደንብ ልናጣራ እና ልንመረምራቸው ይገባል በማለት ነዋሪዎች ለቲክቫህ ኢትዮጵያና ተናግረዋል። ግጭቱ ከተነሳ ጀምሮ እስካሁን በሲዳማ ዞን እና ዙሪያው በሚገኙ ከተሞች የኢንተርኔት አገልግሎት እንደተቋረጠ ነው።

©DW

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ

Comments

  1. ህወሓት 24 ሰኣት በጀሌዎቹ አገር ውስጥና ከአገር ውጭ የጥፋት ወሬ እያሠራጨ ነው። እነርሱ በፈጸሙት ደባና ሌብነት ዶ/ር ዐቢይን እየወነጀሉት ነው። በአዋሳ፣ በአሦሳ፣ በአማራ በሚካሄደው ሁሉ እጃቸው አለበት፡፡ የሌባ ዐይነ ደረቅ መልሶ ልብ ያድርቅ ነው! በምን ተኣምር ነው ዶ/ር ዐቢይ በ1ኣመት ተኩል እነርሱ 27 ኣመት ሲመዘብሩ ዜጋ ላይ ግፍ ሲፈጽሙ የኖሩትን ማቃናት የሚችለው? ይገርማል እኮ! አገር ሁሉ ህወሓትን አይቀበልም አይፈልግም። የሚነዙትን ውሸት ማጋለጥ የያንዳንዳችን ሓላፊነት ነው። ለነገሩ ውዥንብር ይንዙ እንጂ አይሳካላቸውም!! ይህን እነርሱም አውቀውታል! ትልቁ የህወሓት ችግር የትግራይን ሕዝብ እንዴት አፍኖ እንደሚይዝ ነው። አንደኛው ብልሃት በዜና ማሠራጫቸው 24 ሰኣት ወሬ መንዛት ነው። ሌላኛው የጋራ ጠላት መጠፍጠፍ ነው። ሳያስቡ ያደረጉት አንድ መውደቂያቸው ጄኔራል ሰዐረን ትግራይ ወስዶ መቅበር ነው። የሰዐረ ቀብር ፈንጂ ሆኖ ይበትናቸዋል!

  2. ህወሃት ራሱ ገድሎ፡ «ገደሉት…» ብሎ አስወርቶ፡ አብሮህ ሃዘን የሚቀመጥ ቡድን ነው፡፡ እንዲያም ቢሂን ግን አብይም ቢሆን በርካታና አብዛኛውን ኢትዮጵያዊ ድጋፍ የሚያስገኝለትን እርምጃ መውሰድ አልቻለም፡፡ አንድ አመት ቀላል አይደለም፡፡

Speak Your Mind

*