ፕ/ር ኃይሌ ላሬቦ እና “የቁቤው ትውልድ” ፖለቲካ

ለሰሞኑ ግርግር መንስኤ የሆኑት ፕ/ር ኃይሌ የተጠቀሟቸው ሁለት ቃላት ናቸው ተብሏል። “ጋላ” እና “እረኛ” የሚሉ ቃላት። በኢትዮጵያ የታሪክ መዛግብት ውስጥ እነዚህ ቃላት “ሰፍረዋል” ወይንስ “አልሰፈሩም” የሚለውን ጉዳይ ለግዜው እንተወው። ፕሮፌሰር ኃይሌ ላሬቦ በቃለ-መጠይቁ  እነዚህን ቃላት መጠቀማቸው “ስህተት ነው” ወይንም “ስህተት አይደለም” ወደሚለው ትንታኔም አልገባም። እነዚህን ጥያቄዎች ለታሪክ ለተመራማሪዎቹ  ልተውላቸው።

ፕሮፌሰሩ ከወንድማገኝ ጎሹ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ እነዚያን ቃላት ባይጠቀሙስ፣ ከስድብ እና ከአድማው ይድኑ ይሆን? የሚለው ጥያቄ ግን ትንሽ ወደ ኋላ እንድዞር አድርጎኛል።

“ዳግማዊ ምኒልክና ታሪካዊ ክንውኖቻቸው” በሚል ርዕስ አንጋፋው ጋዜጠኛ ተክሌ የኋላ ከሁለት አመት በፊት ሦስት እንግዶችን በጀርመን ድምጽ ሬዲዮ ጋብዞ አወያይቷቸው ነበር። እንግዶቹ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ፣ ዶ/ር ኃይሌ ላሬቦ፣ እና ዶ/ር ሹመት ሲሻኝ ነበሩ። በውይይቱ ሁለቱ የታሪክ ተመራማሪዎች የአቶ ቡልቻ ደመቅሳን በአፈ-ታሪክ የተቋጨ ሃሳብ በማስረጃ ውድቅ ስላደረጉት…፤ በጃዋር መሃመድ የሚመራው ቡድን ለጀርመን ድምጽ ራዲዮ የቦርድ ዳይሬክተር አቤቱታ (petition) አስገባ። አቤቱታው ቀጭን ተዕዛዝ ይዞ ነበር። “ተክሌ የኋላ ባስቸኳይ ከስራው ይባረር!” የሚል ትዕዛዝ። ግፊቱ በብዙ ተሞከረ። ግን አልተሳካም። ይልቁንም የጋዜጠኛ ተክሌ የኋላ ቃለ-መጠይቅ “መነጋገሪያ የሆነ ምርጥ ስራ” በሚል በቦርዱ ሙገሳን ነበር የተቸረው። በከሳሾቹ ግን እጅግ አዝኖ “እኛ አንስተነው እኛው ላይ ተነሳ” ብሎ የነገረኝ ትዝ ይለኛል።

በዚያው ሰሞን፣ ድምጻዊ ቴዲ አፍሮ “ጥቁር ሰው” የሚል አልበም ለቅቆ፤  የአጼ ምኒሊክን የጸረ-ቅኝ ግዛት ተጋድሎ አወድሶ ነበር። የ“ኦሮሞ ፈርስት አቀንቃኞች ያዙኝ-ልቀቁኝ ሲሉ አዋራ አስነሱ። የሄነከን (በደሌ) ቢራ ኮንሰርቱን ስፖንሰር እንዳያደርገው ይኸው ቡድን ዘመቻ ከፍቶ 18 ሺ ፊርማ አሰባስቧል። በወቅቱ እነ አባዱላ ገመዳ የሚመሩት- ኦሕዴድ ከ20ሺ በላይ የኦሮሞ ተወላጆች እስር ቤቱን አጨናንቀውት እንደነበር የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዘገባ ያሳያል። ይህ በደል ለ“ኦሮሞ ፈርስቶች” ከቶውንም የትኩረት አቅጣጫ አልነበረም።

ሦስት መቶ (300) የኦሮሞ ተወላጆች በኦሮሞነታቸው ብቻ ከዩኒቨርሲቲ ሲበረሩ የቁቤው ትውልድ አቀንቃኞች ምን እንዳደረጉም አይተናል። ጁነዲን ሳዶ የተማሪዎቹን መባረር የሚደግፍ መግለጫ ሰጠ። ይህ በደል ከሜንጫዎቹ ተቃውሞም ሆነ የፔትሽን ሃሳብ አልነበረውም። ይልቁንም እንደ አገዳ ተመጥጦ የተጣለው ጁነዲን ሳዶ ዛሬ ጀግና ሆኖ ታሪካችንን ሊነግረን የዲያስፖራ ብቅ ብሏል።

ፕ/ር ኃይሌ ባለሳምንት ናቸው። ነገ ሌላም ምሁር ይቀጥላል። የአጼ ምኒሊክን ስም የሚያነሳ ምሁር በሙሉ እንዲሸማቀቅ እና ዝም እንዲል የሚድረግ ሙከራ ነው። በመገናኛ ብዙሃን ቀርቦ የኢትዮጵያን ታሪክ የሚናገር ምሁር ወይንም፣ ታሪኩን እነሱ በሚፈልጉበት መንገድ ቀይሮ ካልተናገረ ላለመሰደቡ ዋስትና የለም። የፖለቲካውን ጡዘት የሚያወላግደው ከቶውንም እንደሰበዝ መዝዘው ባወጧቸው ቃላት አይደለም። ጸቡ ያለው ከዳግማዊ ሚኒሊክ እና እሳቸውን ከማወደስ ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ ከተመክሮዎቹ በግልጽ እናያለን።

አንድ ነገር ግልጽ ይሁን። በኦሮሞ ሕዝብ መሃል ኖረናል። ባህሉን፣ ስነ-ልቦናውን እና ቋንቋውንም ጭምር እናውቃለን። የምናውቀው ኦሮሞ ፍጹም ጨዋ እና ትእግስተኛ ሕዝብ መሆኑን ነው። የኦሮሞ አባቶች ለትውልድ አውርሰው ያለፏቸው እሴቶች ብዙ ናቸው። እነዚያ እሴቶች፣ በባህላዊ የጋዳ ስርዓት፤ ችግርን በንግግር መፍታት፣ ፍትሃዊ አስተዳደርን፣ ጨዋነትን እና አርቆ አሳቢነትን እንጂ ነውርን፣ ስድብን እና ዋልጌነትን አልነበረም።

የፕሮፌሰር ኃይሌ ላሬቦ ቃለ-ምልልስ በኢሳት እንደተለቀቀ የፓንዶራው ሳጥን የተከፈተ ያህል በርካታ ስድቦችን በማህበራዊ ድረ-ገጾች ተመልክተናል። ጉዳዩ በስድብ እና በተቃውሞ ብቻ አላበቃም። ከኢሳት ቦርድ በጉዳዩ መግለጫ እንዲያወጣም ተደርጓል። መግለጫውም ነገሩን አላስቆመውም። የይቅርታ ነገርም ተነስቷል።

ኃይሌ ላሬቦ ከሚያስተምሩበት ቦታ እንዲባረሩ በኢንተርኔት አቤቱታ እየተሰባሰበ ነው። ርምጃው ሁሉ ብዙ የሚያስኬድ ባይሆንም ነገሩ እንዲሁ እየተንከባለለ መቀጠሉ ግን አይቀርም። ምክንያቱም ለተነሳው ጉዳይ ምላሽ መፍትሄው መጮህ፣ መሳደብ እና አድማ መጥራት አይደለም። መፍትሄው መጋፈጥ እና ማስረዳት፣ ጉዳዩን ጠረጴዛ ላይ አፍረጥርጦ መበታተን።

የፕሮፌሰሩን የታሪክ ትንታኔ ቃል በቃል የመሞገት ጉልበት ያላቸው የኦሮሞ ተወላጅ ምሁራን ጠፍተው ነው ለማለት ይከብዳል። ከአክቲቪስቶቹ  መካከል ፕሮፌሰር ሕዝቅዔል ገቢሣም አሉ። የታሪክ ምሁር ናቸው። ይህንን ጉዳይ ከሳቸው እይታ ይተነትኑታል ብሎ ያልገመተ አልነበረም። ቃለ-ምልልሱ ውስጥ ይቀርቡ የነበሩት መረጃዎችም ሆኑ ማስረጃዎች ውስጥ ስህተት አለ ብለው ካመኑ፣ በዚሁ መገናኛ ብዙሃን ቀርቦ መሞገት ምሁራዊ ተግባር ነው። ጉዳዩን በማስረጃ የማፍረስ ክህሎት ካላቸው፣ አደባባይ ወጣ ብለው ችግሩን ይፈቱት ነበር። እሳቸው ግን ከምሁራዊ ማዕዘን ጉዳዩን ከማስረዳት ይልቅ ጥላቻ መስበክን መምረጣቸው ያሳዝናል። እርግጥ ነው።  በታሪክ ተመራማሪነታቸው ከሰሩት ስራዎች ውስጥ ሲፈለግ የሚገኘው ስለ ሃረር ጫት እድገት የጻፉት ብቻ ነው። (Leaf Of Allah: Khat & Agricultural Transformation In Harerge Ethiopia 1875-1991) ሌላ ነገር የለም።  ከእኝህ ምሁር ብዙ ጠብቀን ያገኘነው ግን ምሁራዊ ትንታኔ ሳይሆን ጥላቻ ነው። በኦሮሚያ ሚዲያ  ኔትወርክ ቀርበው እንዲህ ይላሉ።

ከቤተሰቤ መካከል አማርኛ የምችለው እኔ ብቻ ነኝ። ሌሎች አስራ ሶስት ወንድምና እህቶቼ አማርኛን እንዳይሰሙም እንዳይናገሩም አድርገን በጥሩ ሁኔታ አሳድገናቸዋል። አሁን ያለዉ የቁቤ ትዉልድም ከሞላ ጎደል አማርኛን የማይናገር የማይሰማ ጀግና ትዉልድ ሆኗል!”

ፕሮፌሰር ሕዝቅዔል ገቢሣ የነበረውን ታሪክ ማምከን እንኳ ባይደፍሩ፣  ቢያንስ ዶናልድ ትራምፕ እንደሚለው አማራጭ እውነታዎችን (alternative facts) ያሳዩናል ስንል፣ ጭራሹን ሌላ ቋንቋን መናገር እንደ ድንቁርና የሚወስደው ሃሳባቸውን ነገሩን። እንዲህ እያሉ በአመክንዮ ሳይሆን በስሜት ብቻ የሚመራውን ቡድን፣ ፍሬን በሌለው መሽከርክሪት ቁልቁል ይነዱታል። ይህ ደግሞ ማንን እየተቀመ፣ ማንን እየጎዳ እንደሆነ ከወዲሁ እያየነው ነው።

ከምሁራን አክቲቪስቶቹ ይልቅ ያልጠበቅነው በውቀቱ ስዩም ፕሮፈሰር ኃይሌን በመሞገት ማብራርያ ይሰጣል፣

“ኦሮሞ የሚለው ቃል ፕሮፌሰር ላሬቦ እንደሚለው አሁን የመጣ ሳይሆን፣ከጥንት ጀምሮ የህዝቡ ስም ነው። ስያሜው በብዙ ቀደምት ያውሮፓ መንገደኞች  መፃህፍት ውስጥ ተመዝግቦ መገኘቱ ለዚህ ማስረጃ ይሆናል።  ለምሳሌ እንጦኒዮስ ዳባዲ የተባለ መንገደኛ በ1888 ላሳተመው ጥናት የሰጠው ርእስ ‘ጋላ በሚል ስም ለስለሚጠሩት ኦሮሞች – ያፍሪካ ታላቅ ህዝብ’ የሚል ነበር። ወንድሙ ሚካኤልም፤ ደጃዝማች ጎሹ ስላደረጉት ዘመቻ ሲፅፍ፣ ‘ጋላ በሚባሉት ኦሮሞዎች ላይ የተካሄደ ዘመቻ፤ (campagne contre les ilmormas dits gallas’ ይላል”

“ቱቸር የተባለ የጀርመን ሊቅ ሁለት የኦሮሞ ተወላጆችን በ1844 ሙኒክ ላይ አግኝቶ ከነሱ እያጠያየቀ መዝገበቃላት አሰናዳ።  በመዝገበ ቃላቱ Oromo የሚለውን ቃል ሲፈታ ‘The name by which the Gallas call themselves in comparison with other nations’ ይላል።

“ጣልያናዊው ፕሮፌሰር ቪትርቦ በ1887፣ ያሳተሙት የሰዋስው መፅሀፍ ርእስ ‘Grammmatica Della lingua Oromonica’ የሚል ነው።”

ሲል በውቀቱ ስዩም ታሪክ እየጠቀሰ ለማብራራት ሞክሯል። ወንድም በውቀቱ ስዩም ጥሩ አብረርቶታል። ጉዳዩን ግን ጠለቅ ብለን በመስመሮች መካከል የምናነበው ነገር አይደለም። በውቀቱ ስዩም ያልገባው፣ ወይንም ገብቶት ያላስገባው አንድ ነገር እንዳለ አንዘንጋ።

አንድ ህዝብ “በዚህ ስም መጠራት አልፈልግም!” ካለ ይህ መብቱ መከበር አለበት። በዚህ የሚደራደር አይኖርም። ሕወሃት ስልጣን ከያዘ በኋላም በርካታ የጎሳ ስሞች ተቀይረዋል። ሲዳሞ ወደ ሲዳማ፣ ጃንጀሮ ይባል የነበረ አሁን የም እንዲባል፣ አዋሳ የነበረው ሃዋሳ እንዲባል… ወዘተ። አፍሪካ-ሜሪካኖች ኔግሮ በሚለው ስም መጠራት አንፈልግም በማለታቸው ይህንን መብታቸውን አስከብረዋል። በጥቁሮች ላይ መጥፎ ስሜት (bad connotation) የሚያሳድረው “ኔግሮ” የሚለው ስም በግልጽ ይቁም እንጂ ከታሪክ መዛግብት ግን አልጠፋም። ሞኝና ወረቀት የያዘውን አይለቅም እንዲሉ ታሪክ ነውና ሊጠፋ አይችልም። በድጋሚ ነገሩ ያለው የቃለ-ምልልሱ ይዘት ላይ አይደለም። አንድን ምሁር ነጻ ሆኖ የምርምሩን ውጤት በመናገሩ ብቻ  በማይገባው ክብር የሚነካ አጸያፊ ስድብ ማውረድ፣ ማዋረድ መሞከር፣ ከስራው እንዲሰናበት አቤቱታ ማሰባሰብ ላይ ነው ጉዳዩ።

ፕ/ር ኃይሌ ላሬቦ የታሪክ ምሁር ናቸው። እድሚያቸውን በሙሉ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ሲመራመሩ ቆይተዋል። በቃለ-ምልልሳቸው የፖለቲካ ትንታኔ አልነበረም ይሰጡ የነበረው። በኢትዮጵያ ታሪክ ሲመራመሩ ያገኙትን እንደወረደ አስቀመጡ። የታሪክ ሰዎች የፖለቲካ ትክክለኝነት (political correctness) አይገዳቸም።

አዎ እንደወረደ። በቃለ ምልልሳቸው “አማራ የሚባል ጎሳ ወይንም ብሔር የለም” ብለዋል። ጎጃሜ፣ ጎንደሬ፣ ይፋቴ፣ መንዜ፣ ወሎዬ፣… ወዘተ እንጂ አማራ ነኝ የሚል ጎሳ ወይንም የሸዋ፣ የጎጃም፣ የአገው፣ የወሎ እንጂ የአማራ መንግስት የሚል ነገር፤ በታሪክ መዝገብ ላይ የሌለ መሆኑን ለማስረዳት ሞክረዋል። ይህ ገለጻቸው ስለ ኦሮሞ ከተናገሯቸው ቃላቶች እጅግ የከፋ ነው። ግና የአማራው ሕዝብም ሆነ በአማራ የተደራጁ ወገኖች ሲሳደቡ፣  ሲያወግዙ ወይንም አቤቱታ ሲያሰባስቡባቸው አላየንም። በአንጻሩ “ኦሮሞ የሚባል ብሔር ወይንም ጎሳ የለም። ጉጂ፣ ሰላሌ፣ ወለጋ፣ … እንጂ” ቢሉ ኖሮ እንደ ሳልማን ሩሽዲ በተገኙበት ይገደሉ የሚል ፍርድ እንደሚጠብቃቸው መገመት አያዳግትም።

ድርጊቱ በራስ መተማመንን፣ና ታሪክን እና ማንነትን ጠንቅቆ ማወቅን ይጠይቃል። ኢትዮጵያ የሁሉም ሃገር ናት። ማንም ሰው የበላይ ሊሆን አይችልም። ያለራሱ ሙሉ ፈቃድ ድርግሞ ማንም ሰው ከሌላው የበታች አይሆንም። ፍጹም ጥላቻ እየነዳቸው ሌላውን ወገን “ውጡልን፣ እንገንጠል…” እያሉ ራስን ማሳነስ ከበታችነት ስሜት የሚመነጭ ህመም ነው። ለሕዝቡ አዝነው ሳይሆን ለራሳቸው የስልጣን ጥማት መወጫ ሲሉ ብቻ፣ ትላቁን ሕዝብ ትንሽ በሚያደርጉ ተግባራት ላይ ተወጥረዋል።

የኦሮምያ ፈርስት ሌላው አቀንቃኝ  ዶ/ር ጸጋዬ አራርሳ ናቸው። የግርግሩን ነፋስ ለማጽዳት እሳቸውም አንድ ነገር ያደርጋሉ ብለን ነበር። ግን ከምሁራዊ ትንታኔ ከመስጠት ይልቅ፣ በኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ OMN የቀረቡትን የአቶ አዴኦ ቦሩ ንግግር በፌስ ቡክ ገጻቸው ላይ ለጥፈውታል።  ጽሁፉ እንደሚከተለው ይነበባል።

“ወያኔን በቀኝ እጅ እየተዋጋን በግራ እጅ ያለፈው የፋሺስት የነፍጠኛ ስርዓት እንያዳንሰራራ መዋጋት ያስፈልጋል። ከነፍጠኛ ጋር ያልተገባ ጋብቻ መፍጠር አስፈላጊ አይደለም። ሊገሉ፣ ሊወሩ፣ ሊዘርፉ የተዘጋጁትን የአበሻ የቀድሞ የፋሺስት ድርጅቶች ጋር ፈፅሞ፣ ከነሱ ጋር ህብረት መፍጠር ፈፅሞ አያስፈልግም። ፈፅሞ!  በኦሮሞ ሕዝብ ከነዚህ ጋር እየሰራ ያለ ድርጅት በኦሮሞ ሕዝብ የፖለቲካ ሽርሙጥና እየሰራ ነው። ከነዚህ ጋር ምንም ህብረት የለንም። የኦሮሞ ሕዝብ ትግል ድል እንደሚያመጣ ባለ ሙሉ ተስፋ ነኝ። ኦሮሞ ነፃ ከወጣ በላ፣ መሬቱን ካስመለሰ በላ፣ ባህሉን ካስጠበቀ በ ከፈለገ አብሮ ይኖራል፣ ካልፈለገ ለብቻው ይኖራል፣ ከፈለገ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች ጋር ሌላ ሀገር ፈጥሮ ይኖራል።

ዶ/ር ጸጋዬ አራርሳም ሆኑ የአቶ አዴኦ ቦሩ የፖለቲካ ስትራቴጂ ድንቅ ነው። ሁለት እግር ስላለን ሁለት ዛፍ በአንዴ እንወጣለን ነው የሚሉት። ሁለት እጅ ስላለን ሁለት ጠላት በአንዴ እንመታለን ነው የሚሉት። ግና ጣታቸውን የቀሰሩበት ሁለተኛው ጠላታቸውን ነፍጠኛው ከማለት ውጭ  በግልጽ አላስቀመጡትም። አማራውን ማለታቸው ይሆን ወይንስ ፕ/ር ኃይሌ ላሬቦን፣ ራስ ጎበናን ማለታቸው ነው ወይንስ ፊታውራሪ ሃብተጊዮርጊስ ዲነግዴን፣ ራስ ጢኖን ማለታቸው ይሆን ወይንስ ባልቻ አባ ነብሶን….?

በነገራችን ላይ ዶ/ር ጸጋዬ አራርሳ የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት – ኦሕዴድ አባል ሆነው በሲቪል ሰርቪስ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አንጋፋ ምሁራን ሲያፈሩ የነበሩ የህወሃትን አገልጋይ ነበሩ። በምናባቸው የተፈጠረ ታሪክ እና በዘር ጥላቻ ተለክፈው እድሜያቸውን እኩሌታ ከሚሰቃዩ ምሁራን አንዱ ናቸው። ከሺዎች ማይል ርቀት ላይ ሆነው ኢትዮጵያ የምትባለውን አብስትራክት ነገር የማፍረስ ህልም ያልማሉ። መቼም ሕልም አይከለከልም። አወዛጋቢዎቹ የአትላንታና የለንደን ኮንፈረንሶች፣ የ”ኦሮሚያ የነጻነት ቻርተር” ወዘተ ሁሉ ይኸው ጥላቻ አርግዞ የወለዳቸው የቂም ልጆች ናቸው።

የህሊና አይናቸው ካልታወረ በስተቀር፤ ከፕ/ር ኃይሌ ላሬቦ ንግግር ይልቅ የአዲሱ የማስታወቂያ ሚኒስትር የዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ንግግር ነበር የኦሮሞን ሕዝብ የሚያደማው። ነገሪ ሌንጮ ሰሞኑን ከፋይናንሻል ታይምስ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ የኦሮሞን አመጽ በማፈን እና በመስበር ድል እንደተቀዳጁ ነግረውናል። ሺዎች የተገደሉበት፣ በመቶ ሺዎች የታሰሩበት፣ የሰው ልጅ መብቶች በሙሉ የተገፈፈበትን እርምጃ ዶ/ር ነገሪ “ስኬታማ ድርጊት” ብለውታል። የ”ቁቤ ትውልድ” ነኝ ለሚለው ቡድን ግን ከዚህ በአፍንጫው ስር እንደቅጠል ከሚረግፈው ወገኑ በበለጠ የሚያሳምመው፣  የማያውቀው የምኒሊክ የጀግንነት ታሪክ ነው። የቁቤ ፖለቲካ፤ ከቁቤው ላቲን ፊደል ትምህርት በተጓዳኝ ከህወሃት የትምህርት ቢሮ እንደ ክትባት የሚሰጥ መርዝ ነው። መርዙ አንድ ትውልድ ላይ የከፋ ጥላቻ እና ያለመትማመንን ፈጥሯል። ትውልዱ ዛሬን ሳይሆን ትላንትን ብቻ እያመነዠከ እንዲቆይ፤ ለገዥው ፓርቲ እና ለተቀጽላው ኦህዴድ መሰንበቻ የታሰበ የፖለቲካ ንድፍ … ከሳጥን ውስጥ ያልወጣ አስተሳሰብ (out of the box thinking) ይዘው እንዲያድጉ የተደረገ ጥናት።

የትናንት ቁስል የሌለው ሕዝብ የለም። አሜሪካም፣ ጣልያንም፣ ጀርመንም ሁሉም የቆየ ህመም አላቸው። ልዩነቱ ቁስሉ በእነሱ ላይ ጋንግሪን ሆኖ ያለመቆየቱ ነው። የትላንት ችግር ሊከተላቸው ቢሞክርም እንኳን፣ አትኩረው የሚመለከቱት ዛሬን እና ነገን ነው። ዶ/ር መረራ ጉዲና ከመታሰራቸው ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ አምስተርዳም ላይ ባደረጉት ምክር አዘል ንግግር፣ “የታሪክ ሂሳብ አታወራርዱ።” ብለዋቸው ነበር። ዶ/ር መረራ ይህንን ያለምክንያት አልተናገሩም። በታሪክ ከሚወራረደው ሂሳብ እዳ በአብላጫው ማን ዘንድ እንዳለ ያውቁታል። የጥንት ታሪካችንን እያነሳን ወደ 16ኛው ክፍለዘመን ከተጓዝን ብዙ የሚጎረብጡ ነገሮችን ልናነሳ ነው።

ያም ሆኖ አሁን “የቁቤ ትውልድ ነኝ” በሚል በተነሳው በኦሮሞ “አክቲቪስት” ስም የሚደረገው ነገር የኦሮሞ መልካም ሕዝብን ስም ያጎድፋል። የታሪክ ተመራማሪው ከተናገሩት ውስጥ አንዲት ቃል መዝዞ በማውጣት በአጸያፊ ቃላት መሳደብና ጨዋነትን አያመለክትም። የፕ/ር ኃይሌን ዘር እየጠቀሱ ማንቋሸሽ  የኦሮሞ ህዝብ ባሕል አይደለም።

ጃዋር መሃመድ በአንድ ወቅት ሲፎክር በአካባቢው ቀና የሚል ክርስትያን ካለ አንገቱን በሜንጫ እንደሚቆርጥ ነግሮናል። ይህንን ወንጀል በአንደበቱ የተናገረበት ማስረጃ አሁንም በግልጽ ተቀምጧል። እስካሁን አላስተባበለም። ይቅርታም አልጠየቀም። ይህንን የወንጀል ሸክም ከራሱ ላይ ሳያወርድ ዛሬ እሱ የሚመራው የኦሮሞ አክቲቪስት “ኢሳት ይቅርታ ይጠይቅ” “ፕ/ር ኃይሌ ላሬቦ ለተናገሩት ይቅርታ ይጠይቁ!” ሲለን መብቃቱ እንዴት አድርጎ ቢንቀን ይሆን? በእርግጥ ይቅርታ መጠየቅ ትልቅነት ነው። እያወራን ያለነው ግን ሰለ ባልና ሚስት ጸብ አይደለም። ጉዳዩ የፖለቲካ ነው። የፖለቲካ ይቅርታ ደግሞ ከኋላው እየተጎተቱ የሚመጡ በርካታ ነገሮች አሉበት። ይህ ባይሆን የአውስትራሊያ መንግስት አቦርጅኖችን ይቅርታ ጠይቆ በተገላገለ ነበር።

ኢሳትም ሆነ ፕ/ር ኃይሌ ላሬቦ በዚህ ጉዳይ ይቅርታ ማድረግ ካለባቸው በቅድሚያ ዘመናዊው የኢትዮጵያን ታሪክ ለመሻር መወሰናቸውን ሲያሳውቁ ብቻ መሆን አለበት። መገናኛ ብዙሃንም ተጨባጭ ነገር ማቅረብ እንጂ ሁሉንም ወገን ለማስደሰት ብሎ መስራት የለበትም።

ፕሮፌሰር ኃይሌ ላሬቦን ለመደገፍ የተዘጋጅው አቤቱታ ድረ-ገጽ ላይ በመፈረም፣ የኚህን ምሁር ሞራል እንጠብቅ። ይህንን ለማድረግ የሚከተለውን ሊንክ እዚህ ላይ ይጫኑ

ፕሮፌሰር ኃይሌ ላሬቦ ከወንድማገኝ ጎሹ ጋር ያደረጓቸውን ቃለ-ምልልሶች ለመመልከት የሚከተሉትን ሊንኮች እዚህ እና እዚህ ላይ በመጫን ይመልከቱ።

(ክንፉአሰፋ)


“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡

Comments

 1. I took my precious time to conduct further research and learn the History of Oromos from “Professor’ Haile Larebo from his recent interview as well as previous writings. I finished reading his article ምኒልክን ብትወቅሱ ማንነታችሁን ትረሱ – ከዶ/ር ኃይሌ ላሬቦ (ባለ 51 ገጽ ሰፊ ትንታኔ)with agony. Bellow are my overall review of his historical claims on Oromos:

  1. He maintains that history should not be told or written based on oral folktales. But then, he goes on to cite folktales to back up his favorite claims. His claims about Menelik’s name etc are all folktales. He believes that only the ones that he cherry-picks are credible. He has no any reference to cite for most of the statements.

  2. It is incredulous to see that he conducts himself on the same level of tekle yeshaw. He, like Tekle Yeshaw, claims that the anole history is a fabrication of tesfaye gebreab. Wow! the funny part is that he cites several account of atrocities similar to the one arsi oromo claims to had been subjected to. His own parent’s account is very powerful testimony of the atrocities that was taking place. He believed what his parents told him. But, he is disparaging arsi oromo for believing what their parents told them? He did not deny that Meneliks chopped off legs and arms from POWs at the adwa battle. Then, the logical truth is that Menelik did not invent this method just there; it is the method he used in all the previous battles. He most likely learned from from Tewodros when he was taken to Gondor at early age.

  3. He admits that there were so many wrongs that were committed but he just believes that oromos were never at the receiving end, they were instead the perpetrators.

  4. He seems to be driven by his hate for the oromo people. His hate seems to have emanated from that he believes oromo people had evicted his ancestors, kembata, from arsi area. Again, this is based on folktales. I won’t disparage him for that since he most likely heard this from kembata peoples’ oral tradition. The trouble is that he does not respect other peoples’ right to believe their oral history.

  5. Finally, yes Menelik established a country that looks like a true federation. But then, did that continue the same way before the system was dismantled by the 1974 revolution? I will leave this question for the good professor.

  In short, this article does not help us to move beyond our past and focus on our current issues. I am sorry, you are trying to settle your own scores against some Oromo elites under the guise of writing a history. The people and the country are bigger than your egocentric and unethical use of your profession.

 2. *** ” ….አንድ ነገር ግልጽ ይሁን። በኦሮሞ ሕዝብ መሃል ኖረናል። ባህሉን፣ ስነ-ልቦናውን እና ቋንቋውንም ጭምር እናውቃለን። የምናውቀው ኦሮሞ ፍጹም ጨዋ እና ትእግስተኛ ሕዝብ መሆኑን ነው። የኦሮሞ አባቶች ለትውልድ አውርሰው ያለፏቸው እሴቶች ብዙ ናቸው። እነዚያ እሴቶች፣ በባህላዊ የጋዳ ስርዓት፤ ችግርን በንግግር መፍታት፣ ፍትሃዊ አስተዳደርን፣ ጨዋነትን እና አርቆ አሳቢነትን እንጂ ነውርን፣ ስድብን እና ዋልጌነትን አልነበረም።”
  ***” ፕሮፌሰር ሕዝቅዔል ገቢሣ በታሪክ ተመራማሪነታቸው ከሰሩት ስራዎች ውስጥ ሲፈለግ የሚገኘው ስለ ሃረር ጫት እድገት የጻፉት ብቻ ነው። (Khat & Agricultural Transformation in Harerge, Ethiopia, 1875–1991) ሌላ ነገር የለም። ከእኝህ ምሁር ብዙ ጠብቀን ያገኘነው ግን ምሁራዊ ትንታኔ ሳይሆን ጥላቻ ነው። በኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ቀርበው እንዲህ ይላሉ።
  “ከቤተሰቤ መካከል አማርኛ የምችለው እኔ ብቻ ነኝ። ሌሎች አስራ ሶስት ወንድምና እህቶቼ አማርኛን እንዳይሰሙም እንዳይናገሩም አድርገን በጥሩ ሁኔታ አሳድገናቸዋል። አሁን ያለዉ የቁቤ ትዉልድም ከሞላ ጎደል አማርኛን የማይናገር የማይሰማ ጀግና ትዉልድ ሆኗል!” (ታዲያ ከህወአት ለምን ይጣላሉ!?) የውጭው ተቃዋሚ ሳይሆን ፎጋሪና ተለጣፊ ባንዳ ነው!?
  _____ **የኢትዮጵያ ሕዝብ ፮ ሚሊየን በነበረበት ግዜ ፲ሚሊየን ኦሮሞ ተጨፍጭፎ እናቶች ጡታቸው ተቆርጦ የእስቅዔል ጋቢሳ እናት ብቻ ተርፋ የኦሮሞን ቁጥር ከኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር አንደኛ ለማድረግ ተቻለ። አሁን የኦሮሞ ሕዝብ ቁጥር የሞጋሳውም የጉዲፈቻውም ተቆጥሮ ከሌላ ዘር የተወለደውም ተቆጥሮ ስንት ነው? ንጹሕ ኦሮሞ ፮ ወይስ ፯ ወይስ ፴፬ሚሊየን ያለው ማን ነበር?
  በዕውቀቱ ሥዩም እንደሚገጥመው ሲሰብርም ያው ነው። (አባቴ አያቱን አጣ በኋላም እራሱን አጣ ከባሕር እንደወጣ አለ)
  ++ “ኦሮሞ የሚለው ቃል ፕሮፌሰር ላሬቦ እንደሚለው አሁን የመጣ ሳይሆን፣ከጥንት ጀምሮ የህዝቡ ስም ነው። ስያሜው በብዙ ቀደምት ያውሮፓ መንገደኞች መፃህፍት ውስጥ ተመዝግቦ መገኘቱ ለዚህ ማስረጃ ይሆናል። ለምሳሌ እንጦኒዮስ ዳባዲ የተባለ መንገደኛ በ1888 ላሳተመው ጥናት የሰጠው ርእስ ‘ጋላ በሚል ስም ለስለሚጠሩት ኦሮሞች -ያፍሪካ ታላቅ ህዝብ ‘ የሚል ነበር። ወንድሙ ሚካኤልም ፤ ደጃዝማች ጎሹ ስላደረጉት ዘመቻ ሲፅፍ፣ ‘ጋላ በሚባሉት ኦሮሞዎች ላይ የተካሄደ ዘመቻ፤ (campagne contre les ilmormas dits gallas ‘ ይላል”
  ___”ያውሮፓ መንገደኞች” እንኝህ ከደቡብ አፍሪካ ትነስተው ወደ ግብጽ ባቡር እንዘረጋለን ያሉት እንግሊዞች ይሆኑ? ወይንስ ከጅቡቲ ወደ ጊኒ ቢሳው እና ኮንክሬ የባቡር ሐዲድ እንዘርጋለን ያሉት ፈረንሳዮች ይሆኑ? መንገደኛ ማለት ታሪክ ጣፊ ነውን? ጎብኝ ነው? አልፎ ሀጅ? ሰፋሪም ነዋሪም አጥኒም አይሆንም አደል? ዋሸን እንዴ ?
  ++ “ቱቸር የተባለ የጀርመን ሊቅ ሁለት የኦሮሞ ተወላጆችን በ1844 ሙኒክ ላይ አግኝቶ ከነሱ እያጠያየቀ መዝገበቃላት አሰናዳ። በመዝገበ ቃላቱ Oromo የሚለውን ቃል ሲፈታ ‘The name by which the Gallas call themselves in comparison with other nations’ ይላል።
  ___ ፲፰፵፬ ሁለት ኦሮሞዎች ጀርመን ላይ መንገደኞች ነበሩ? ሁለት ሰዎች የኦሮምኛን ቃል በአምሮአቸ ይዘው ክጎጃም ተነስተው ሲጓዙ አልጠፋባቸውም? እራሳቸው ለራሳቸው ያወጡት ቃልና መዝገበ ቃል በለው! መራራስ አማን በላይ የብራና መጽሐፍ ከእነ መዝገበቃሉ ኑቢያ እሳጥን ውስጥ እንደተገለጠላቸው ማለት ነው።
  ++ “ጣልያናዊው ፕሮፌሰር ቪትርቦ በ1887፣ ያሳተሙት የሰዋስው መፅሀፍ ርእስ ‘Grammmatica Della lingua Oromonica’ የሚል ነው።”
  ___ አሁን ኦሮሞዎቹ ለጀርመናዊ በቃላቸው ከነገሩት በኋላ ጀርመናዊው ለጣሊያኖቹ ተሰጥቶ ቪትርቦ ፲፰፰፯ አሳተመው? ወይንስ መጀመሪያም ሁለቱ ኦሮሞዎች ጀርምኖች ነበሩ!? እንጦኖጦኒዎስ ዳባዲ (አብዲ)(ዲባባ)(ዳዲ) (ዳባ) የተባለ መንገደኛ በ1888 ላሳተመው ጥናት የሰጠው ርእስ ‘ጋላ በሚል ስም ለስለሚጠሩት ኦሮሞች -ያፍሪካ ታላቅ ህዝብ ‘ የሚል ነበር። (ይህንን ቃል የተረጎመው ከሁለቱ ኦሮሞዎች ነው ካጣሊያኑ ነው!? ኦርሞ ነበሩ በኋላ ጋላ ሆኑ? ይህ በኢትዮጵያ የሰሜን ተራሮች ላይ የነበረ ኦሮሞ ከኬንያ፡ ታንዛኒያ፡ ሩዋንዳ፡ ካሉት ጋሎች ጋር ምንም ዝምድና ከሌለው የምሥራቅ አፍሪካ ኅያል(ብዙ) ሕዝብ ሊያሰኘው እንዴት ቻለ? ለምንስ የጽሑፍ ፊደላቸው አንድ አልሆነም!?…. ሌሎች ሀገራት ጉዲፍቻ..ገዳ..እሬቻ..ዋቃ! አከባበርና ሥርዓቱ ሁሉ አንድ ነው? አለ!?
  *** የኦሮምያ ፈርስት ሌላው አቀንቃኝ ዶ/ር ጸጋዬ አራርሳ ናቸው።
  “አባቴ እጄን ይዞ እያንዳንዱን የአዲስ አበባ ጉራንጉር አሳይቶኛል…. የደም ሀገር በደም የተጨማለቀች ከተማ እንደሆነች አስተምሮኛል …. ይህ የሚታየው ህዝብ ሁሉ በግድ በግፍ የሰፈረ መጤ ነው ለኦሮሞ ማንነት ዕውቀና ካልሰጠ ወየውለት!።” ሲል ኢህአዴግ ተጠቅሞበት የጣለው ከጁነዲን ሳዶ ጋር ሀገር ሲሰረስር ዩኒቨርሲቲ ወጣት ሲመለምል የተቋሙን መረጃና ማስረጃ ከህወአት ቡደን ተሻርኮ ሲያመክን የነበረ በጥቅማጥቅም እጦት የሚሰቃይ የሁለት ዘር ማንነት እንደ ጃዋር መሐመድ የሚያንከራትተው ሰው አልባ ሰው ነው።(ፎረም ፷፭ ላይ ቀርቦ የተፋውን ማድመጡ የበታችነት ሥቃዩን መጋራት ነው።)
  *** ““ወያኔን በቀኝ እጅ እየተዋጋን በግራ እጅ ያለፈው የፋሺስት የነፍጠኛ ስርዓት እንያዳንሰራራ መዋጋት ያስፈልጋል። ከነፍጠኛጋር ያልተገባ ጋብቻ መፍጠር አስፈላጊ አይደለም። ሊገሉ ፣ ሊወሩ ፣ ሊዘርፉ የተዘጋጁትን የአበሻ የቀድሞ የፋሺስትድርጅቶች ጋር ፈፅሞ፣ ከነሱ ጋር ህብረት መፍጠር ፈፅሞ አያስፈልግም…።”
  ___ ይህ የኦፌኮ መድረክ ቃል ነው።መኢአድ፡ አንድነትና ሰማያዊ ፓርቲ ምን እንደተደረጉ ማየት ነው። በየነ ጴጥሮስም ይህንኑ ሲል ዲሲ ስብሰባ ላይ ሲያስጨበጭብ ነበር። እነኝህ ፺፱ ከመቶ የቋንቋና ዘር ተኮር ፌደራሊዝም አራማጆች…የጥቅማጥቀመኛው ህገመንግስት አፍቃሪ፡ ገንጣዮች ክልላዊ የሙስና ኢምፓየር የገነቡ፡የውጭ ፎጋሪ ተቃዋሚዎች በውስጥ በኦፒዲዮ ቅርብ ውክልናና ድጋፍ ያላቸው ሞላጫ አስመሳይ ናቸው። እያንዳንዱን ኅብረት፤አንደነት፤ትብብር፤ጥምረት፤ የሚበትኑ አደገኛ መርዞች ናቸው።
  ” በኦሮሞ ሕዝብ ከነዚህ ጋር እየሰራ ያለድርጅት በኦሮሞ ሕዝብ የፖለቲካ ሽርሙጥና እየሰራ ነው።” ከለንደን ስበሰባ ኢትዮጵያን ማፈራረስና ኦሮሚያን መገንባት…ከአትላንታው የኦሮሞ ቻረተር ምሥረታና ኦሮሚያን በጦር ቀጠና ለመምራት ሻለቃና ኮሎኔል ምደባ…. (ኦሮሞ ነፃ ከወጣ በህዋላ ፣ መሬቱን ካስመለሰ በህዋላ ፣ ባህሉን ካስጠበቀ በህዋላ ከፈለገ አብሮ ይኖራል ፣ ካልፈለገ ለብቻው ይኖራል ፣ ከፈለገ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች ጋር ሌላ ሀገር ፈጥሮ ይኖራል።”** ይህንን አብሮ የሚያንቆለጳጵስ አማራ ይሁን ሌላ ጎሳና ነገድ (ሚዲያ) ጋዜጠኛም ይሁን ጋዜጣ በል የፓለቲካ ሸርሙጣ መሆኑንም ነግረዋቸዋል። አዳሜ አሁንስ ገባችሁ ይሰማል! አደለም እንዴ?
  *** ያም ሆኖ አሁን “የቁቤ ትውልድ ነኝ” በሚል በተነሳው በኦሮሞ “አክቲቪስት” ስም የሚደረገው ነገር የኦሮሞ መልካም ሕዝብን ስም ያጎድፋል። የታሪክ ተመራማሪው ከተናገሩት ውስጥ አንዲት ቃል መዝዞ በማውጣት በአጸያፊ ቃላት መሳደብና ጨዋነትን አያመለክትም። የፕ/ር ኃይሌን ዘር እየጠቀሱ ማንቋሸሽ የኦሮሞ ህዝብ ባሕል አይደለም። ነጻነት! ነጻነቱ ምኑ ላይ ነው?

Speak Your Mind

*