የምሥራች ነፃነት ላጣው

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

«እስመ ናሁ እዜንወክሙ ዐቢየ ዜና ፍሥሓ…» « ትልቅ የምሥራች ዜናን እነግራችኋለሁ..»ሉቃ ፪፦፲-፲፬፤

ነገር ከሥሩ ውኃ ከጥሩ እንዲሉ የምሥራች ህገ ወንጌልን ለመታወጅ ያበቃውን ስንመረምር ፤ እግዚአብሔር አምላክ በጥንተ ፍጥረት የሰውን ልጅ ወደዚህ ምድር ፈጥሮ  እንዲያስተዳድረው ከማድርጉ  አስቀድሞ፤የሚተዳድርበትን የሥነ ፍጥረት ህግ አዘጋጀለት፤ ሥጋዊ አካሉ እንዳይዝል የሚያርፍበት ሌሊት ተሐድሶ የሚነሣበት መዓልትን ሰጠው፤ በጨረሯ ሙቀትን በነጸብራቋ ብርሃንን፤ በክበቧ ደስታን የምታጎናጽፈውን የሥሉስ ቅዱስ ተምሳሌት የሆነችውን ጨለማን የምታስወግደውን ፀሐይን አደለው። በልቶ የሚያረካውን ምግበ ሥጋን ሰጠው፤ በጥላው የሚጠለልብትን አበቦችን ዓይቶ በመንፈሱ የሚረካበትን ዕፀዋትን፤ አትክልትና አዝርዕትን የየብስ መደሰቻ መዝናኛውን አሳመረለት።በዝማርያቸው የሚያስደስቱት በአየር ላይ የሚበሩ በልዩ ልዩ ቀለማት የአሸበረቁ የተለያየ ጣዕመ ዜማ የአላቸውን በክንፍ የሚበሩ በእግር የሚሽከረከሩ የአእዋፍ ዝርያዎችን በሚያስደስት ሁኔታ እንዲቀበሉት በየብስ አሰለፋቸው።

የምድር ሁለት ሦስተኛው የሚበልጠው ክፍል ውኃ ነው፤ ውኃ ደግሞ በየብስም በባሕርም ሕያዋን ሆነው ለተፈጥሩ ሁሉ የሕይወት መሠረት ነው። በውኃው ጠጥቶ እንዲረካበት ታጥቦ እንዲነፃበት ዓይቶ እንዲደሰትበት የአዘጋጀለት ነው። በውስጡም በክንፍ የሚበሩ በእግር የሚሽከረከሩ በደም ነፍስ ሕያዋን ሆነው የሚኖሩ በየብስ ከሚኖሩት ፍጥረታት በአካሄዳቸው በግዙፍነታቸው በብዛታቸው በዓይነታቸውበውበታቸው በልጠውና ጎልተው እንደሚታዩ የተፈጥሮ ሳይንቲስቶች በየጊዜው በሚያወጡት መጽሔታቸው ያረጋግጣሉ። እነዚህንም ፍጥረታት እንደ የብሱ ለእሱ የሚያስደስቱ ለእሱ የሚታዘዙ፤ በእሱ እንዲተዳደሩ በአሉበት ጸንተው ቆመው የሰው ልጅ በእንግድነት ሲመጣ እንዲቀበሉት አዘጋጃቸው። የአቀባበሉን ዝግጅት ሁሉ በየረድፍ በየረድፉ በዚህ ዓይነት ለአምስት ቀናት ከአመቻቸ በኋላ በስድስተኛው ቀን በመላእክት በካልዕ ፍጥረት ታጅቦና አሳጅቦ የሰውን ልጅ እሱን መስሎ እንዲያሰተዳድር እንደራሴ አድርጎ አነገሠው(አምባሳደር አድርጎ) ሾመው።

የሰው ልጅ ግን ውለታውን ረስቶ የተሰጠውን ክብር ንቆና አዋርዶ በእንደራሴነት የተሰጠውን፤ የጠላት ድምፅ ሰምቶ እንደራሴነቱን ወደ ባለቤትነት ለወጠው። በዚህ ምክንያት ክብሩን አጣ፤ ከእንደራሴነቱ ተባረረ፤ ውብ ሆና የተፈጠረችለትን ምድር በአግባቡ ማስተዳደር ስለአልቻለ ምድርም በእሱ ምክንያት ተረገመች ፤ ተፈጥሮ የተፈጥሮ ህግ ተሻረ፤ አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ምድር በጠላት ግዛት ሥር ወደቀች። የሰው ልጅ(ዓለም) ለረዥም ዘመናት የተነጠቀውን ውቢቷን ምድር አንድ ብቻውን የጦር መሪ አዋጊ (ጄነራል) የጦር ሠራዊት ተዋጊ በመሆን ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍሶ እስከ መስቀል ደርሶ ከጠላት ነጥቆ ከአስረከበህ ሁለት ሺህ ዘመናትን አስቆጥረሕ ወደ ሦስተኛው ሺህ ከተሽጋገርክ ውለህ አድረኃል።

የነፃ አውጭህን የልደት ቀን በዚህ ሳምንት ለማክበር ደፋ ቀና እያልክ ትገኛለህ፤ የልደቱንም በዓል ወደ አንተ ክብር በመለወጥ የስጦታ መለዋወጫ አድርገኸዋል። በቤተልሔም “እስመ ናሁ እዜንወክሙ ዓቢየ ዜና ዘይከውን ለክሙ ፍሥሐ ለኩሉ ዓለም” ተብሎ የታወጀልህ የምሥራች ወንጌል  መሠረት ያደረገ በተለይም የተፈጥሮን ህግ ያገናዘበ በልበ ጽሌህ የተጻፈ ለመፈጸም ቀላል በፈቃድ ላይ የተመሠርተ ህገ ርትዕ (በህልውና ላይ የተመሠተ) ነበር።

ያ የዛሬ ሁለት ሺ ዓመታት በፊት በቤተልሔም ዋሻ የታወጀው የምሥራች የሰላም ህገ መንግሥት ወንጌል የታወጀው ለሕዝብ ለአሕዛብ ለወንድ ለሴት ለትልቅ ለትንሽ ለመሪ ለተመሪ ሰው ሆኖ ለተፈጥረ ሁሉ እንዲተገበረው በሕይወቱ ሁሉ ደስታን ሰላምን  አግኝቶ እንዲኖርበት የተሰጠ ነበር። ህገ መንግሥቱም የዲያብሎስን የባርነት ህገ መንግሥት የሚተካ፤ ለአምስት ሺ አምስት መቶ ዘመን በዲያብሎስ ግዞት የነበሩትንም ነፃ ያወጣ፤ የጠላት የዲያሎስንም ግዛት አንኮታኩቶ ጥሎ ሥልጣኑን የተቆጣጠረበት ነበር። የሰው ልጅ ግን የነበረ ክብሩንና መብቱን መልሶ  የአገኘውን ነፃነት በዚህ ዘመን አሽቀንጥሮ መጣሉን የሚያረጋግጡ ፤ በሦስት  ነጥቦች ላይ እንደሚከተለው አቀርበዋለሁ።

፩. ይህ የነፃነት ህገ መንግሥት ወንጌል የታወጀለት ዓለም ዛሬ የት ነው የአለው?

፪. ከሁሉ በፊት አዋጁ የደረሳት ኢትዮጵያ(ሕዝቧ) ዛሬ በምን ሁኔታ ላይ ትገኛለች?ይገኛል?

፫. በዲሲና በአካባቢው ለሚኖረው ኢትዮጵያዊ ተዋኅዶ እምነት ተከታይ፤ክርስትናውን የሚጠይቅ፤

፩.የሰው ልጅ(ዓለም)ዛሬ የት ነው ያለህው?

እግዚአብሔር ሕያው ዘለዓለማዊ እንደመሆኑ መጠን የፈጠረው ፍጥረት ሁሉ ከእሱ በነሳው ሕያው ሆኖ በአለማቋረጥ  በመንቀሳቀስ ላይ የተመሠረተ ነው። ትናንትና የተፀንሰው ዛሬ ይወለዳል፣  ዛሬ የተወለደው ነገ ያድጋል፤ ትናንት የተዘራው የተተከለው ዛሬ ይበቅላል፣ዛሬ የበቀለው ነገ ያፈራል፤የትናንትናውን ለዛሬ የዛሬውን ለነገ ማድረግ አትችልም። ሁሉንም በጊዜውና በወቅቱ ማከናወን ካልቻልክ ህያውነት ወደ በድንነት ይለወጣል።የአንድ ሀገር ሕዝብ ከተፈጥሮ ጋር እኩል መንቀሳቀስ ሲችል፣  ምድራዊ ሕይወቱ በእንቅስቃሴው መጠን ያድጋል ማኅበራዊው ሕይወቱ ይለወጣል፤ ምጣኔ ሀብቱ ይዳብራል፣  በመንፈሳዊው ሕይወቱም ከእንቅስቃሴ ጋር እኩል እንዲጓዝ ያበቃውን አምላኩን ያመሰግናል።genna

ሰው(ዓለም) ሆይ ይህ ነበር የተፈጠርክበት ዓላማ፤ ያከበርህን፤ ነጻነት የአጎናጸፈህን፤ የዳንክበት፤ በደም ማኅተም ታትሞ የተሰጠህን ከሕይወትሕ ጋር የሚጓዝ ህገ መንግሥት ወንጌልን አሽቀንጥርህ ጥለህ በምን ህገ መንግሥት እየተመራሕ ነው? ፈጥሮ የሚገዛህን ትተህ በምን በማን እየተገዛህ እያመለክህ ነው? አምስት ሺ አምስት መቶ ዘመናት በባርነት ይገዛህ ለነበረው የጥንት ጠላትህ ለነበረው ሰይጣን (ዲያብሎስ) የሚመለክበት  የአምልኮት ቦታ (ሥፍራ) አዘጋጅተህ እያመለከውና እያስመለከው አይደለምን? ለተረካቢው ትውልድ የሰይጣን ትምህርት ቤት አቋቁምህ ህፃናቱን እየበክልክ ለአራዊትነት ግብር እያዘጋጀኃቸው አይደለምን ?

ውብ ሆኖ የተሰጠህን በፍቅር የምትመሰጥበትን ለክብር የምትበቃበትን አንተነትህንና ዘለዓለማዊነትህን አጥተህ ሰብአዊ ባሕርይህን ለውጠሕ እንስሳዊ ባሕርይህን በአዋጅ ያጸድቅህ አንተ ሰው የት ነው የአለህው? የሚጠብቅህ ምን እንደሆነ ዘንግተኸዋል፣  ላስታውስህ። ሮሜ ፩፦፳፮-፳፯፤፪ ጴጥ ፪፦፮-፲፤  የአራዊት ግብር(ባሕርይ) ጭካኔን አንግበህ በሄሮድስ ግብር ጸንተህ ጉዞ ከጀመርክ ውለህ አድርኃል። በግፍና በከንቱ የፈሰሰው የአንድ ዘካርያስ ደም ጩኸት ከአሰማና መልስ ከአገኘ፤ በየቀኑ በሚልዮን የሚቆጠሩ ህፃናት ደም ጩኸት ምንስ ያመጣብህ ይሆን? ኤር ፮፤-፫፤፲፫-፳፤ ፴፩፦፲፭፤ይሁ ፩፤-፲፩፤ራእ ፲፮፦፲፱–፳፩፤ አንተ ሰው (ዓለም) ከአራተኛው የዕውቀት ደረጃ አልፈህ ወደ አሥረኛው ደረጃ ለመድረስ እየተፍጨረጨክ ነው። በአንተ ክሂሎት አለመሆኑን ተረዳ። ተቆንጥሮ የተሰጠህ ከመቶ አሥር ብቻ ነው።

በዚሁ ተቆንጥራ በተሰጥችህ ብልጭታ ምህዋረ ከዋክብትን ፈለከ ፈለካትን አየረ አየራትን በመቆጣጥርህ እኔ አደረኩት እኔ ሠራሁት እኔ እኔ በማለት አትመካ።እኔ በማለት ነው ሳጥናኤል የተዋረደው፤ ወደ ኋላ ተመልስህ ሃያ ሠላሳ ዓመታት ትጠቀምበት የነበረውን ብዙውን ዛሬ አትጠቅምበትም፣  ዛሬ የምትጥቀምበት ደግሞ በነገ ይለወጣል፣ ቋሚ ነው የእኔ ነው የምትለው ምንም የለህም። በዚህ ትምክህትህ እንደ አንተው ተፈጥሮ መሰልህ አይሲስ ብለህ ስም የሰጠህው የገነባህውን ሲያፈራርስብህ የአለማህውን ሲያወድምብህ ልጆችህን ሲያርድብህ ሲረሽንብህ ዓለም በሥጋትና በፍርሐት ተወጥራ በውጥረት ላይ መሆኗ፤አንተም አጻፋውን በመስጠት የምታደርሰው ጥፋትና ውድመት ከዚያ ቢብስ እንጂ የሚተናነስ ሆኖ አይታይም።

ይህም የአጻፋ የብቀላ ምት መፍትሔ የሚሰጥ አይደለም። መፍትሔ የሚሰጥ ቢሆን ኖሮ ለአለፉት ዘመናት በዓለም ዙርያ የተካሄዱ በርካታ ጦርነቶች መፍትሔ በሰጡ ነበር። ይልቅስ የዛሬ ሁለት ሺህ ዓመታት የታወጀው «ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን እናንተም አድርጉላቸው» የምትለውን ህገ ርትዕ ወንጌልን በመመርያነት መቀበል፤ በዚህ ወር ልደቱን የምታከብረው ፣የሰላም አለቃ የዘለዓለም አባት› ለመሪዎች ሰላምን የሚሰጥ ለሰላሙም ፍጻሜ የለውም ተብሎ የተነገረለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በግልም በማኅበርም በሀገር በዓለም አቀፍ በመምራትና በመመራት የአለህ ሁሉ እሱን አምነህ መመርያውን ተቀብለህ ተግባራዊ ከማድረግ በቀር አሁን በመቃተት ላይ ለአለቸው ዓለማችን ሌላ አማራጭ እንደሌላት በዚህ አጋጣሚ ላስገነዝብ እወዳለሁ።

ይህንን ባታደርግ ግን የባሰ በግልህ በቀይህ ሞት፤ በቤትህና በመሥርያ ቤትህ ሞት፤ በመስጊድህና በቤተ ክርስቲያንህ ሞት፤ በማኅበር ሞት፤ በሀገር ሞት ፤በንብረትሕ ውድመትና ጥፋት የሚጠብቅህ መሆኑን አስታውስኃለሁ፤(አስጠነቅቅሃለሁ)። በትዕቢት ተወጥሮ «ሕዝቤንም አለቅም እግዚአብሔርን አላውቅም» በማለት በማን አለብኝ እስራኤላውያንን ያሰቃይ የነበረ የግብጹ መሪ የጥንቱ ፈርዖን ሞት ሲታዘዝበት ነው ሕዝቡን የለቀቀው፤ በዓለም ዙርያ የአለህ የዚህ ዘመን ፈርዖን ሆይ ሞት ታዞብኃል ቶሎ ብለህ ዘጠኙኝ ፈቃዳተ ነፍስ ከታሠሩበት ልቀቅ ።

. ከሁሉ በፊት የምሥራቹ የወንጌል አዋጅ የደረስት ኢትዮጵያ ዛሬ የት ነው የአለችው?

እንደ አለመታደል ሆነና «የፊተኞች ኋለኞች» እንዲሉ እንደ ግመል ሽንት የኋሊት ፤የኢትዮጵያ ሕዝብ የነበረበትን በታሪክ መነጽር ሲመለከትና አሁን የአለበትን ሲያነጻጽር መልሱ የትዬለሌ ነው። የምሥራች ሕገ ርትዕ ወንጌልን ከመቀበሏ በፊት ባልተጻፈ ህገ  ልቡና በተጻፈ ህገ በቀል ኦሪት የሚመራ በመሆኑ «ዛሬ ያዘዝኩህን የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ሰምተህ ብትጠብቃት ብታድርጋትም እግዚአብሔር እራስ ያደርገሃል እንጂ ጅራት አያደርግህም፤ሁል ጊዜ በላይ እንጂ በታች አትሆንም።»የአለውን መመርያ ተግባራዊ በማድረግህ አገርህን አስፍተህ እስከ ማዳጋሥካር እስከ የመን፤ መከር ሠምሮልህ የዳቦ ቅርጫት፤ የማንነትህ መታወቂያ በመጀመርያው በአፍሪካ ፊደል ቀርጸሕ ማሳወቅህ፤ የመሳሰለው ባለቤት ነበርክ።

የምሥራች ህገ ርትዕ ወንጌልን ከሁሉ በፊት ተቀብለህ ሀገሪቷን የክርስቲያን ደሴት ሕዝቡ ሕዝበ እግዚአብሔር እየተባለ ከመታወቁም በላይ የታፈረች የበለፀግች ሀገር ነበርችህ። አንተም ጨብጦ የሚያደቅ ሮጠህ የሚቀድም አነጣጥሮ የሚተኩስ ተኩሶ የማይስት አንድነቱ እንደ ብረት የጠነከረ ፍቅረ እግዚአብሔርና ፍቅረ ቢጽ የተፈጸመለት ሕዝብ ነበርክ፤የአንተ ባልነበረው በአለፈው ትናንትና ነበር እያልክ የምታቅራራ ወገኔ ዛሬ የት ነው የአለኸው? አንድነትህ የሚያስፈራው ጠላት (ወያኔ) ተበታተን ሲልህ አሜን፤ ወደብ አያስፈልግህም ሲል አሜን፣ ልጅህ ከጉያህ እየተነጠቀ ሲገደል፤ ሲታሠር ዝም፤ መሬትህ እየተሸንሸነ ለባዕዳን ሲቸር ዝም፤ለአፍሪካ ሕዝብ መኩሪያ የአፍሪካ ጥንታዊ ፊደልህ ትናንት በተገኘ በጠላት በላቲን ፊደል ሲተካ ዝም፤ የበርሐ ወንበዴ ተሰባስቦ ልግዛህ ሲል አሜን፤ ካድሬውን የቤተ ክርስቲያንና የመስጊድ አለቃ አድርጎ ሲሰይምልህ አሜን፤ ኦርቶዶክሱንና አማራውን አከርካሪውን መታንልህ ሲባል አሜን፤ የተከፋፈለችውን ቤተ ክርስቲያን አንድ ለማድረግ የሰላም ጉባኤው ሲኮነን አባላቱ ሲባረሩ የሞት ፍርድ ሲበየንበት ዝም ፤ “እስከ ማዕዜኑ”  እስከመቼ ወገኔ ዝምታው በዛ ማስተዋሉ ጠፋ፤ «ዝምታ አይነቅዝም»የሚባለው ለመልካም ሲሆን አሜን ደግሞ እውነትን ማረጋገጫ ነበር፤ ዛሬ ያለ ቦታው ሆነና ጣዕሙ ወደ ምሬትነት ተለውጦ ምሬቱ ይሰማኛል (እየተሰማኝም) ነው።

ወገኔ አንተስ አይሰማህም (አልተሰማህም) ምሬቱ? የዘንድሮን የልደትን በዓል ስታከብር ይህንን ምሬት በምን ልታጣፍጠው ተዘጋጅተኃል? «ዶሮ ማታ ዶሮ ማታ»በማለት በማስምሰልና በውሸት? መልሱን ላንተው፣ በዓለም ዙርያና በሀገር ቤት ለአለኸው ወገኔ ትቸዋለሁ።

፫. በዲሲና በአካባቢ ለምትኖረው እትዮጵያዊ ወገኔ፤

የምሥራች የሰላም ወንጌል የታወጀበት መላእክት ከኖሎት ኖሎት ከመላእክት ጋር  የአምስት ሺህ አምስት መቶ የረዥም ዘመን የጸብ ግርግዳ ፈርሶ እርቅ ወርዶ «ሰላም በምድር”የሚለው የውል ሰነድ የተረጋገጠበትና በሰማይ በማኅበረ መላእክት በምድር በደቂቀ አዳም ዘንድ የተሰበከበትና የታወጀበትን ይህንን ብሔራዊ የነጻነት በዓል ስናከብር በንጽጽሩ ደግሞ «የአንተ ደም የእኔ ደም ነው የእኔ ደም የአንተ ደም ነው»፤(«የአማራው ደም የኦሮሞው ደም ነው፣ የኦሮሞው ደምም የአማራው ደም ነው”) በማለት የነበረውን የደም የውል ሰነድ ያስታውሰናል። ዛሬ እዚሁ በመካከላችሁ በመሆን የዘንድሮውን የልደት በዓል እንኳን አደረሳችሁ ስል የአለፈው ዓመት እንዴት በየት በምን ዓይነት ሁኔታ እንዳሳለፍኩ እንዳስታውስ ህሊናዬ ያስገድደኛል።

ወገኖቼ ሁላችሁም እንደምታውቁት በቅን ህሊና በመንፈሳዊ ልቡና በተሰጠኝ ፀጋ ሁሉ  እውነቱን እውነት ሀሰቱን ሀሰት በማለት ማገልግሌ «ወርቅ ላበደረ ጠጠር» እንዲሉ ወንድሞቼ ካህናት እንዲሁም በዕድሜ ፀጋቸው በአገልግሎት ዘመናቸው ሊቀ ካህናቱ ኤሊን የሚስተካከሉ የእኔታ ህሊናቸው መንፈሳቸው እያወቀና እየተረዳ በአልዋልኩበት በሌለሁበት በአድማ ዘመቱብኝ፤ በውሸት ጦር ወጉኝ፤ በቅናት ጅራፍ ገረፉኝ፤ በምቀኝነት ሠይፍ አርደው አውጥተው ጣሉኝ። የመንፈስ ልጆቼ ከውድቅሁበት አንስተው የዛለው ሰውነቴ እንዲረታ የቆሰለው መንፈሴ እንዲፈወስ (እንዲሽር) ወደ ኢየሩሳሌም ላኩኝ።

እኔ የአለፈውን ዓመት በቤተ ልሔም የልደትን በዓል አከበርኩ። ወገኔ በዚያ እንዴት እንዳሳለፍኩ ምን እንደአጋጠመኝ ምን እንደሠራሁ፤ የጎበኘኋቸውን ቅዱሳት መካናትንና ከማን ጋር የሚለውን በዚህ በአጭር እንኳን አደርሳችህ የልደት መልእክት ማጣበብ ስለሚሆን “አታሎ ማስገደድ አስገድዶ መድፈር” በሚለው ጦማር ተመዝግቧል።ወደ እዚያ እንድታቀኑ ግብዣዬ ነው።በተረፈ በዲሲና በአካባቢው ለምትኖረው ወገኔ እንኳን ለበዓለ ልደቱ በሰላም ሳይሆን በደኅና አድረስህ። በተለይ የዲሲ ግብረ ኃይልና ነፃነት ለኢትዮጵያ የሬድዮ አገልግሎት እውነቱን ፈልፍሎ ለማውጣት የከፈልከውን መስዋዕትነት አደንቃለሁ፣ ታሪክም ሲያስታወሰው ይኖራል።

እንዲሁም ካህናተ አይሁድ ጌታችንን ከምኩራባቸው አስወጥተው ሕዝቡን በአድማ አሳምጸው በደል ሳይኖርበት ኮንነው፤በጲላጦስ አደባባይ አቁመው ከሰው አእምሮ ግምት በላይ ገርፈው  ከአቅሙ በላይ መስቀል አሸክመው  የተራራማውን ጉዞ ሲወድቅ ሲንሳ ላቡ እንደ ክረምት ዝናም ሲወርድ ደሙ ምድሩን ሲያርሰው፤ የሾክ አክሊል ደፍተው ሲያሾፉበት የተደረገውን ግፍ ሁሉ የተመለከቱ አዋልደ ኢየሩሳሌምን በግብር የመስላችሁ«እውነት ነፃ ታወጣችኋለች» ያለውን መለኮታው ኃይለ ቃል አንግባችሁ፤ እውነትን አውቃችሁ እውነት ተከትላችሁ በዝርወት ከእውነት ጋር የቆማችሁ አባቶቼ እናቶች እንዲሁምልጆቼ ህጻናት ሁላችሁ፤ በዝርወት ያለምንም አገልግሎት ለአንድ ዓመት ቆይታችሁ ዛሬ ግን እንደ አንድ ልብ መካሪ አንድ ቃል ተናጋሪ በመሆን የዘንድሮውን በዓለ ልደት ለማክበር ስለ በቃችሁ እንኳን ደስ ያላችሁ፤እንኳን ለዚህ ነፃነት በዓል አደረሳችሁ።

በዚህ አጋጣሚ በዲሲና በአካባቢው ለምትኖረው ክርስቲያን ወገኔ የማዳኝብህ ነገር አለኝ።ክርስትና ምንድነው? ክርስትና እውነት ነው፤ ክርስትና ክርስቶስ ነው፤ክርስትና ቅድስተ ቅዱሳን ንጽሕተ ንጹሐን ወላዲተ አምላክ ናት፤ ክርስትና ጻድቃን ሰማዕታት ናቸው፤ክርስትና አርበኞች ናቸው፤ክርስትና ከውሸት ከፍርሐት ከማስምሰል ከእኔነት ተላቀው በእውነት የቆሙ ናቸው።

ከእነዚህ ከተዘረዘሩ ውስጥ በየትኛው ነህ? ወንጌላዊው ዮሐንስ በራእዩ የአስቀመጠውን ብናነብ በየትኛው ጎራ እንዳለን(ህ) ያረጋግጥልናል(ኃል)።«አንተን የምነቅፍሕ ነገር አለኝ ፤ሳትሆን እራሷን ነቢዪት ብላ የሰየመችውን ያችን ሴት ኤልዛቤልን ዝም ብልኃታልና» የሚል ነው፤ ወገኔ ኤልዛቤል ማናት? በመጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ በምዕራፍ ፳ እንደምናነበው ይህች ሴት በትዕቢት የአበጠች በተንኮል የረቀቀች ውሸት ጭካኔን ገንዘቧ ያደረገች፤ የደኃውን የናቡቴን እርስት የቀማች ያስቀማች፤ናቡቴን የገደለች ያስገደለች፤ዛሬ ወያኔ በኢትዮጵያና በሕዝቧ ላይ የሚያደርገውን ግፍና በደል የምታስታውሰን ናት።ወገኔ የምነቅፍህ የማዳኝብህ ነገር ምንድነው?

በዚህ በአሳለፍከው አንድ ዓመት የፈጸምከውን ላስታውስህ፤ «እውነቱን እውነት ሐሰቱን ሐሰት በሉ» ቢል ወንጌሉ አንተ ግን የውሸት ሻሽ በጠመጠሙ የቅናት ካባ ባጠለቁ በነአዲሱ አድማ መሪነት ቤተ ክርስቲያንህ ሲበጠበጥ ማጨብጨብ፤ መርጠሕ ያስቀመጥከው ቦርድ ሲባረርና ሲሰደብ ማጨብጨብ፤ እመቤታችንን የአድመኞች፤ የአመጸኞችና የሠባሪዎች ተባባሪ በማድርግ ሲነገር እልልታ፤ የረዥም ዘመን ካህንህ ሲባረር ዝም፤  አንተን ከአገልግሎት ጨዋታ አውጥቶ ንብረትህን ለመንጠቅ ሲደራጅ ዝም፤ ኢሀደግ በውጪ የአሉትን አብያተ ክርስቲያናት ለመቆጣጠር አምስት ለአንድ፣ አንድ ለአምስት በአቀደው መሠረት ይህችን ቤተ ክርስቲያን ሲቆጣጠራት ዝም፤ በዝምታህ በአድር ባይነትህ በፍርሐትህ ሀገርህን አጣህ፤ ንብረትህን  ተነጥቀህ።ሕይወትህን ለማትረፍ አቀበቱን ወጣህ፣ ቁልቁለቱን ወረድክ፣  ወንዙን ተሻገርክ ውቅያኖስን አቋርጥክ፤ ከአንተ ጋር አብሮ የወጣ ወንድምህ በድንበር ጠባቂ ተገደለ፤ በአውሬ ተበላ፤በውቅያኖስ ውስጥ ሰጥሞ ቀር፤አንተ ግን በጥረትህ ብቻ ሳይሆን በእግዚአብሔር ቸርነት በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ሠርተህ የምታገኝበት ተምረህ የምታውቅበት በነፃነት የምትኖርበት ዓለም (ሀገር) ደርስክ።

አንተም አምላክህ ለአደረገልህ ምሥጋን የምታቀርብበት ቦታ ገዝተህ አገልግሎት መስጫውን አመቻችተህ ካህናት አስመጥተህ  አገልግሎት እንዲሰጥ ከማድረግህም በላይ ራእይ (ዓላማ) ቀርጸህ የአጭርና የረዥም ጊዜ እቅድ አውጥትህ ህንፃ ቤተ ክርስቲያን ለመግንባት ገንዘብ አሰባስበህ በእቅድህ መሠረት የመጀመርያውን ህንፃ አስጀምረህ በመሠራት ላይ እያለ ተነጥቀኃል ሥራውም ቆሟል።«በሬ ከአራጁ አብሮ ይውላል? እንደሚባል ሆነና አውቅኸውም ሆን ሳታውቀው እውነትን አውቆ የወያኔን ተኮል ተረድቶ የካህናቱን ውሸታምነት አጋልጦ በዝርወት ከአለው ወንድምህ (ወገንህ)ተለይተህ ቀርተህ እንደ ጥገት ገንዘብህን ትታለባለህ።  የውሸታሞችን ውሸት በጭብጨባ ታጸድቃለህ፤ በእልልታ ታዳምቃለህ፤ እውነት በሚነገርበት ነፃነት በስፈነበት ሀገር ይህን ሁሉ ሠርክስ የምትፈጽመው ምን ለማግኝት ነው? ለመጽደቅ? መንግሥተ ሰማያት ለመግባትእንዳትለኝ፤ ወገኔ እንኳን ጽድቅ ማግኘት መንግሥተ ሰማያት መግባት ቀርቶ ሀገርህ አትገባም፤ ንብረትህንም አታገኝም።

ይልቅስ ወገኔ ወደ «ኅሊናህ ተመልስህ ንስሐ ግባ፤ ቅዱሳት መጻሕፍትን መርምራቸው መመርያህ አድርጋቸው፤ልብንና ኩላሊትን የምመረምር እኔ እንደሆንኩ፤ከእናንተ ለየአንዳንዳችሁም እንደ ሥራችሁ እከፍላችኋለሁ።»ራእ ፪፦፳–፳፫፤ ..«እንዴት እንደተቀበልክ እንዴት እንደተማርክ አስብ እንግዲህ ተመለስ፤ባትመለስ ግን እንደሌባ ድንገት እደርስብሀለሁ፤ በማናቸው ሰዓት እንደምመጣብህ አታውቅምና» ።…«እኔ የምወዳቸውን እመክራቸዋለሁ፤አስተምራቸዋለሁ እንግዲህ ለንስሐ ቅና። እነሆ ከበር ቆሜ አንኳኳለሁ፤ድምፄን ሰምቶ የሚከፍትልኝ ቢኖር ያን ጊዜ እገባለሁ ከእርሱ ጋርም እቀመጣለሁ፤እርሱም ከእኔ ጋር።»ራእ ፫፦፲፱–፳። ወገኔ እነዚህን ጥቅሶች አስላስላቸው ከራስህ ሕይወት ጋር አገናዝባቸው። ይቆየን፤ አሜን።

እንኳን ለብርሃነ ልደቱ ወጥምቀቱ  እንዲሁም ለዚህ ሀገር አዲስ ዓመት በጤና አደረሰን።

ሊቀ ማእመራን ቀሲስ ዶክተር አማረ ካሣዬ (amare.kassaye@gmail.com)፤ በዝርወት ላይ ያለችው የርእሰ አድባራት ደብረ ሰላም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ፤ (ዋሽንግተን፣ ዲሲ ጽሁፉ የተላከው  በዮሐንስ ገ/ኢየሱስ (lijyohannes@gmail.com)

ታህሣሥ ፲፫ ፳፻፱-December 22, 2016


“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡

Speak Your Mind

*