በወታደራዊ መረጃ ምጡቅ እርምጃ

ዛሬ ታኅሣሥ 10፤2012ዓም ኢትዮጵያ በታሪኳ መጀመሪ የሆነውን ሳተላይት አምጥቃለች። ሳተላይቷ መረጃ አገልግሎት የምትሰጥ ነች የተባለ ሲሆን ይህም ባብዛኛው የመልከዓ ምድር ጥናትና የመሳሰሉትን ለማድግ የምትጠቅም መሆኗ ተነግሯል። ለወታደራዊ ግልጋሎት አትውልም የሚል ቢባም ሳተላቷ መረጃ ስትሰበስብ ይህ ቀረሽ እንደማትባል፤ “ከግዙፍ ክንውኖች እስከ ጥቃቅን እንቅስቃሴዎች” እንደምትመዘግብና እንደምታስተላልፍ ባለሙያዎቹ ይናገራሉ።

በዓለማችን ወታደራዊ የበላይነት የተጎናጸፉ አገራት በርካታ ሳተላይቶች በኅዋው ላይ አላቸው። ከምስራቅ አፍሪካ እንኳን በኬኒያና በሱዳን ተቀድመናል።

ከተለያየ አቅጣጫ የውጭ ጠላት ያላት አገራችን አንድ ብቻ አይደለም በርካታ ሳተላይቶች ያስፈልጓታል። በተለይ ደግሞ አገር ውስጥ ያሉ አፍራሾች የሚደርጉትን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር፣ ማባሪያ ያጣውን የወሰን እና የማንነት ችግሮችን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለመወሰን፤ መረን የለቀቀውን የጦር መሣሪያና የገንዘብ ዝውውር አደብ ለማስገዛት፣ የተስተጓጎለውን የሕዝብና ቤት ቆጠራ በትክክለኛ መንገድ ለመቁጠር፣ ወዘተ መረጃ በማቀበል ከፍተኛ አስተዋጽዖ ታደርጋለች። ይህ ኅዋ ለሰላማዊ እንቅስቃሴ ነው።

ኢትዮጵያ ሳተላይት ማምጠቋ ለምን ይጠቅማታል? በሚል ርዕስ ቢቢሲ አማርኛ ቀረበውን ዘገባ እንዲህ ይነበባል፤

ኢትዮጵያ በታሪኳ የመጀመሪያ የሆነችውን ሳተላይት ከቻይና የሳተላይት ማስወንጨፊያ ጣቢያ ወደ ህዋ ላከች። ሳተላይቷ ለግብርና፣ ለማዕድን፣ ለአካባቢ ጥበቃ፣ ለአየር ንብረት ጥበቃና ለመልከዓ ምድር ጥናት የመረጃ አገልግሎትን ትሰጣለች ተብሏል።

Ethiopian Remote Sensing Satellite – 01 (ETRSS – 01) የተሰኘችው ሳተላይት በቻይና መንግስት የተገነባች ሲሆን በግንባታው ሂደትም በርካታ ኢትዮጵያውያን ባለሞያዎች ከቻይና አጋሮቻቸው ጎን ተሰልፈው ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡

ከቻይና 6 ሚሊየን ዶላር ተለግሶ የተሠራችው ይህቺ ሳተላይት በአጠቃላይ 210 ሚሊየን እንደፈጀች ተነግሯል። የሳተላይቷ የመረጃ መቀበያ እንጦጦ ላይ የተሠራ ሲሆን ከማምጠቅ ሥራው ጀምሮ ቁጥጥሩ ሙሉ ለሙሉ እንጦጦ ላይ በኢትዮጵያውያን የህዋ ዘርፍ ባለሞያዎች ይከናወናል።

ይህ ሳተላየት የማምጠቅ ሥራ ከተለያዩ አካላት 10 ሚሊየን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ማግኘቱ የተነገረ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግሥትም ተጨማሪ በጀት መመደቡ ተገልጿል። ቻይናውያን ኢንጂነሮች ኢትጵያውያንን እያሰለጠኑ ሳተላይቱ ቻይና ውስጥ እንዲሁም በከፊል ኢትዮጵያ ውስጥ ተገነብቷል። 70 ኪሎ ግራም የሚመዝነው ሳተላይት ታኅሣሥ 10፣ 2012 ዓ. ም. ማለዳ ከቻይና መምጠቁ በቀጥታ በተላለፈ ፕሮግራም ታይቷል።

ሳተላይቱ በቻይና እገዛ ከምድረ ቻይና ይምጠቅ እንጂ፤ “ተቆጣጣሪዋም፣ አዛዧም ኢትዮጵያ ናት” ይላሉ የኢትዮጵያ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሰለሞን በላይ ለቢቢሲ።

ሳተላይት ማምጠቅ ለምን አስፈለገ?

የህዋ ጥናት በዓለም ላይ በፍጥነት እየዘመኑ ካሉ ዘርፎች መካከል ይጠቀሳል። የሰው ልጅ ምድር ጠባው አልያም ከምንኖርበት ዓለም ውጪ ያለውን ለማወቅ ጓጉቶ ዘወትር እየቆፈረ ነው። ከህዋ ፍተሻ በተጨማሪ ህዋን ተጠቅሞ መሬትን ማሰስ የመሬት ምልከታ ሳተላይት ተግባር ነው። ሳተላይቱ መረጃ ሲሰበስብ ይህ ቀረህ አይባለውም። ከግዙፍ ክንውኖች እስከ ጥቃቅን እንቅስቃሴዎች ይመዘግባል።

እንደ ባለሙያዎች አባባል ሳተላይቱ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው። የአየር ንብረት ለውጥን ለመቆጣጠር፣ የተፈጥሮ አደጋዎች ከመድረሳቸው አስቀድሞ ለመተንበይ፣ ደህንነትን ለመጠበቅ ወዘተርፈ ይውላል።

በእርግጥ ብዙዎች በታዳጊ ሀገር የህዋ ጥናት አስፈላጊነቱ ላይ ጥያቄ ቢያነሱም፤ ዶ/ር ሰለሞን “ህዋ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገሮች የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ ነው፤ ቅንጦት አይደለም” ይላሉ። የአየር ንብረት ለውጥ የመላው ዓለም ስጋት በሆነበት ዘመን፤ አንዳች ተፈጥሯዊ አደጋ ከመድረሱ በፊት አስቀድሞ መረጃ ማግኘት ብልህነት ነው።

የዛፍ ቁጥር፣ የአየር ንብረት ለውጥና ሌሎችም መረጃዎች ከተሰበቡ በኋላ እንደ ጎርፍ ያሉ አደጋዎች ከመከሰታቸው በፊት መተንበይ ይቻላል። ግብርና ቀዳሚ መተዳደሪያ በሆነባት ሀገር የቱ አካባቢ ምርታማ ነው? የአየር ንብረት ለውጥ ይኖር ይሆን? የሚሉ ጥያቄዎች በቀላሉ እንዲመለሱ የሳተላይቱ መረጃ አስፈላጊ ይሆናል።

ዶ/ር ሰለሞን እንደሚሉት፤ አንድ የግብርና አካባቢን የሚያሳይ ፎቶግራፍ ስለ እርሻ መሬቱ፣ ስለ ውሀው፣ ስለ አፈሩ ዝርዘር መረጃ ይሰጣል። መረጃዎቹን በመጠቀም ምርታማ የሆኑ አካባቢዎችን መለየት፣ የምርት መጠንን በትክክል ማወቅም ይቻላል። ኢንዱስትሪዎች እየተስፋፉ በመጡባት ኢትዮጵያ፤ ፋብሪካዎች የት መገንባት አለባቸው? ለሚለው ጥያቄ የሳተላይቱ መረጃ መልስ ሊሰጥ ይችላል።

ሕዝብ መቁጠር ሲያስፈልግ ከዘልማዳዊው መንገድ ሳተላይቱን መጠቀም ይመረጣል። ትክክለኛ መረጃ ከማግኘት፣ ገንዘብና የሰው ሀይል ከማዳን አንጻርም የተሻለው አማራጭ ነው። ሳተላይቱን ደህንነትን ከመጠበቅ ጋር የሚያስተሳስሩት ባለሙያዎች አሉ።

ዶ/ር ሰለሞን በበኩላቸው “በመርህ ደረጃ ህዋ የሚውለው ለሰላማዊ እንቅስቃሴ ነው” ብለው፤ ለጦርነት፣ ለጦር መሳሪያ ማሳለጫነት እንደማይውል ያስረዳሉ። የ’ኢንተርናሽናል የአውተር ስፔስ’ ተቋም አባል መሆን፤ ኢትዮጵያን ከመሰል ድርጊቶች እንደሚያግዳትም አክለዋል።

ኢትዮጵያ እስካሁን መረጃውን እንዴት ታገኝ ነበር?

ኢትዮጵያ እነዚህን መረጃዎች ሳተላይት አምጥቀው ፎቶ ከሚያስነሱ ሀገሮች ትሸምት ነበር። ዶ/ር ሰለሞን የሚያጣቅሱት ከአራት ዓመት በፊት በተሰራ ጥናት መሰረት ኢትዮጵያ የሳተላይት መረጃን ለመግዛት በዓመት 250 ሚሊየን ብር ታወጣለች።

ጥናቱ ለደህንነት የሚወጣውንና ዩኒቨርስቲዎች የሚከፍሉትን አያካትትም። ወጪው ከዓመት ወደ ዓመት እንደሚጨምርም ያስረዳሉ። የከተሞች መስፋፋት፣ ኢንቨስትመንቶች እየጨመሩ ሲሄዱም በዛው መጠን የመረጃው አስፈላጊነት ይንራል። የሚወጣው ገንዘብም እንዲሁ። ሳተላይት ማምጠቅ እነዚህን ወጪዎች እንደሚቀንስ ይጠበቃል።

አፍሪካ ውስጥ መሰል ሳተላይት ለሌላቸው ሀገሮች መረጃ መሸጥም ይቻላል። የኢትዮጵያ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተሩ “ትልቅ ቢዝነስ ነው” የሚሉትም ለዚሁ ነው። “ሲያስፈልግ መረጃ እንሸጣለን። ከኛ የላቀ ቴክኖሎጂ ካላቸው ሀገሮች ጋር መረጃ መለዋወጥም ይቻላል፤”

ኢትዮጵያ በህዋ ጥናት የት ደረሰች?

ዓለም በህዋ ጥናት ቴክኖሎጂ እየመጠቀ ሄዷል። ኢትዮጵያ ከተቀረው ዓለም አንጻር ጀማሪ ናት። አፍሪካ ውስጥ ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ አልጄሪያና ግብጽ ጥሩ ስም አላቸው።

ኢትዮጵያ “ህዋ ለልማት” የሚል የምሥራቅ አፍሪካ ሀገሮች ትብብር ቢሮ አቋቁማ አበረታች እንቅስቃሴ ማድረጓ ተጠቃሽ ስኬት ነው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በ2030 ይደረስባቸዋል ብሎ ካስቀመጣው ግቦች አብዛኞቹ የህዋ ቴክኖሎጂን ያማከሉ መሆናቸው፤ ዘርፉን ችላ ማለት እንደማያዋጣ ያመላክታል።

ዶ/ር ሰለሞን የመሬት ምልከታ ሳተላይት ማምጠቅ ኢትዮጵያ በህዋ ሳይንስ ዘርፍ እንቅስቃሴ እያደረገች ስለመሆኑ ለዓለም መልእክት ማስተላለፊያ መንገድ እንደሚሆን ያምናሉ።

“ቴክኖሎጂው እጅግ አስፈላጊ ነው፤ ሳተላይቱን ማምጠቅ ኢትዮጵያን በህዋ ዘርፍ ጠንካራ ተወዳዳሪና እኩል ተጽእኖ ፈጣሪ ማድረግ የሚያስችል ነው”። ሳተላይቱ አንዴ ከመጠቀ በኋላ ከሶስት እስከ አራት ዓመት ያገለግላል። ከዛ በላይ ሊቆይም ይችላል። በዓለም አቀፍ ሕግ መሰረት፤ የመሬት ምልከታ ሳተላይቶች ህዋ ላይ እንዲቆዩ የሚፈቀደው ለስምንት ዓመት ነው።

ኢትዮጵያ ከምታመጥቀው ሳተላይት፤ በየአራት ቀኑ የመላው ኢትዮጵያ መረጃ የዓለም ደግሞ በ55 ቀን ይገኛል።

በህዋ ምርምር ዘርፍ ቅርብ ጊዜ እውን ይሆናሉ ተብለው ከሚጠበቁ ፕሮጀክቶች ውስጥ ላሊበላ ላይ ይገነባል የተባለው ዓለም አቀፍ ኦፕቲክ ቴሌስኮፕ አንዱ ነው።

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ

Speak Your Mind

*