ሚዲያ አለኝ ተብሎ የሰው ስብዕና ላይ ክተት አይታወጅም

ሚዲያ እንደ ሰዎች አረዳድ የሚሰጠው ደረጃና አቅም የተለያየ ቢሆንም ያለ አንዳች ማመንታት “ኃይል” ወይም ኃይል ያላቸው መገልገያ መሆኑ ጥርጥር የለውም። ሁሉም ሚዲያ “የሕዝብ” መሆናቸውን ቢገልጹም ፍጹም ነጻና ገለልተኛ ሆነው አይታዩም። ወደ አገራችን ሚዲያ ስንመጣ በውጭ ያሉትም ሆኑ በአገር ቤት፣ የግል የሚባሉትም ሆነ የመንግሥት የራሳቸው ወገንተኛነትና መንሸዋረር ይታይባቸዋል። ይህ እውነት ባደጉት አገሮችም ቢሆን ረቀቅ ባለ መልኩ የሚዘወተር ነው። ከሁሉም የሚቀፈው ግን ፍጹም ጭፍንነት ነው። ምክንያቱም በጭፍንነት ውስጥ አንድ ሰው ከተነገረውና ከተሞላው በቀር አሻግሮ ማየት አይችልምና ነው።

“መቃብር ቆፋሪው እና የሬሳ ሳጥን ሻጩ የሚለው ተውኔት የተሰረቀ ነው” የማለት አዝማሚያ በሚስተዋልበት ስሜት የተጀመረ ቃለ ምልልስ። ሲጠናቀቅም የተለያዩ ጉዳዮች ውስጥ ትገባለህ “የባከንክ ነህ” በሚል “ስድብ” ነው። የግል ዝንባሌዎችን (ሆቢ) እንኳን ማከናወን የተነፈገ የመሰለበት ቃለ ምልልስ!

ጠያቂ ቴዎድሮስ ጸጋዬ፣ የ“ርዕዮት” አዘጋጅ ነው። ቃለ ምልልሱ የቀረበውም በebs ሲሆን በዩትዩብ ላይ የታተመው  26 ዲሰምበር 2016 ነው። ተጠያቂ ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ሲሆኑ መነሻ ጉዳዩም በቅርቡ ለንባብ ያበቁትና ሰፊ መነጋገሪያ የሆነው “የኦሮሞና አማራ እውነተኛ የዘር ምንጭ” የሚለው መጽሃፋቸው ነው።

ቃለመጠየቁ መከራከሪያ የሚሆኑ ሃሳቦችን የሚያነሳ ቢሆንም የተጠያቂውን የመናገር መብት፣ የመከራከር ስልጣን፣ የማስረዳት ጊዜ የነፈገ ነበር። ከሁሉም በላይ ዶ/ር ፍቅሬን ለማሳጣት፣ ለማንቋሸሽ፣ ስራዎቻቸው ላይ ጥያቄ ለማስነሳትና፣ እጀ ሰባራ አድርጎ ለማሳየት ሆን ተብሎ የታለመ ይመስላል። ጠያቂው ከሌሎች የሙያ ባለቤቶች ጋር ያደረገውን ዓይነት ቃለምልልስ ለፍቅሬ ቶሎሣ መንፈጉ ትልቅ ጥያቄ ውስጥ እንዲወድቅ ያደርገዋል። ማስረጃውን አንባቢ ተመልክቶ እንዲፈርድ እተወዋለሁ።

አንድን ሰው ሚዲያ ላይ አቅርቦ “አሁን ይህ ግጥም ነው፤ አሁን ይህ ሃሳብ ነው፣ አሁን እንደዚህ ለማለት መማር ያስፈልጋል፣ ብኩንነት…” እያለ መዛለፍ አግባብ መስሎ ስላልታየኝ አጭር አስተያየት ለማስፈር ወደድኩ።

በፌስቡክ በቀላሉ የሚጻፉ አነስተኛ ጉዳዮች ሳይቀሩ ተለቅመው ለስድብና ሰውን አሳንሶ ለማሳየት የቀረበበት ይህ ቃለ ምልልስ አማራና ኦሮሞን ለማባላት የፈሰሰውን “መዋዕለ ነዋይ” በሙሉ ገደል ውስጥ የሚከት ሆኖ መገኘቱ የፈጠረው ስሜት ይሆናል የሚል ግምት አለኝ። ለሁሉም ግን በአንድ ጉዳይ ጭፍን ሆኖ አንድን ሰው፣ ለአንድ ስውር ግን ግልጽ ለሆነ ዓላማ ዋጋ ቢስ አድርጎ ለማሳየት መሞከር “ጎዶሎ” አስተሳሰብ ከመሆን የዘለለ አይሆንም።

ዶ/ር ፍቅሬ መናገር ተከልክለው፣ እየተሰደቡ ለአፍታ እንኳን ኃይለቃል ሳያሰሙ አመስግነው ቢሮውን ለቀው መውጣታቸው የሚያስመሰግናቸው ቢሆንም ለአድማጭ ይገባው ዘንድ መልዕክት ማስተላለፍ አለመቻላቸው አግባብ ሆኖ አላገኘሁትም። ይህንን ስል ግን ገና ለገና ተሰዱ ተብሎ እርሳቸውን በጭፍን መደገፍ ይገባል ማለቴ እንዳልሆነ ይታወቅልኝ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ መጽሃፋቸው ላይ የሚነሱትን የጭብጥ ወቀሳዎች አስመልክቶ በራሳቸው ፈቃደኛነት ማጠናከሪያ ቢያቀርቡ ደግ ነው እላለሁ። ሰውን መዝለፍ፣ ማሳጣትና ገና ለገና ሚዲያ አለኝ በሚል ስርዓት መልቀቅ ብዙ ውሎ አድሮ ከራስ ህሊና ጋር ያጋጫልና ሚዛን ቢጠበቅ መልካም ነው ለማለት እወዳለሁ።

ጠንካራ ዝግጅት ማቅረብ የሚቻለው ሰውን በመዛለፍ፣ በማቆሸሽ ሳይሆን በጨዋነት ሊሆን ግድ ነው!! ይህ ካልሆነ የህሊና መጨለምን ያመጣልና ከማይታየው የጽልመት በሽታ መውጣት አስፈላጊ ነው። ቃለ መጠይቁን በማዳመጥ አንባቢያን ለቡናዊ ምስክርነት እንድትሰጡ እማጸናለሁ።

ግርማ መርሃጽዮን ከስዊድን


“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡

Comments

 1. መሪራስ አማን በላይ፣
  ጸሀፌ-ታሪክ(ድንቄም)
  ሊ/ቀ ጠበብት ፍቅሬ ቶሎሳ ተላላኪ መሆናቸውን አልወደድኩትም!።ላኪው እንኳን የግዕዝ የአማርኛ ችሎታወም ያጠራጥራል፡ ” የተወለድኩት፣ የአደግኩትና የተማርኩት በዛው በጎንደርና በጎጃም ነው፡፡” ይህ አማራ ለመሆን አማርኛና ግዕዝ ቋንቋን በልዩ ችሎታ አውቆ ለመጎናጸፍ ምክንያትም ማስረጃና ማለፊያ አደለም።
  ** ከአማን በላይ የባሰ ደደብና መሃይም ታሪክ ቅበር የሚል መካሪ ሁለት ሌባ!
  “ዶክተር ኃይሉ ወልደአብ የሚባሉ ሀቀኛ ሙሁር ብራናዎቹን መርምረው፣ ይህ አንተ የጻፍከው መጽሃፍ እውነተኛው ታሪካችን በመሆኑ እሰከዛሬ የተጻፉትን ስለሚቃረን ችግር ይደርስብሃል፤ ስለዚህ አቆየው፣ ብለው መከሩኝ፡፡”
  ** “በመጨረሻ፥ ለመሪራስ አማን በላይ አንድ ጥያቄ ላቅርብ፤ አንዳንድ የታሪከ ነገሥት ቅጂዎች ተገኝተው ታትመዋል፤ የታተሙት ሁሉ የየራሳቸውን አዳዲስ ነገሮች አስተምረውናል። አንተም ያገኘኸው ታሪከ ነገሥት በአድያም ሰገድ ኢያሱ ዘመን የተቀዳ ስለሆነ፥ አንዳንድ ቅጅ ለአዲስ አበባ ወይም ለደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲ ልትሰጥ ትችላለህ። መሪራስ ሆይ፤ በጎውን ይምራህ።” ይህ ማለት አንተ ያልህ አዲስ አደለም አዲስ ከሆን ግን ሰው ይየው ማለት ለግሌ ስጠኝና ልሽጠው ማለት ነው። አልኩ ባይ ጨበርባሪ!
  **— ከኑብያ ካገኘሁአቸው መጻህፍት ውስጥ ታሪከ-ነገሥት ዘ ኢትዮጵያን ለ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኬኔዲ ቤተመጻህፍት እና የሱባንና የግዕዝ መዝገበቃላትን ለ ቤተመጻህፍት ወ መዘክር አንዳንድ ቅጂዎች አበርክቻለሁ፡፡ ዳሩ ግን ይህን ቁምነገር ብዬ በአዋጅ አላስነገርኩም፡፡ የብራናዎቹን ቅጂዎች በመስጠቴ ቤተመጻህፍት ወ መዘክር መቀበሉን የሚያንጸባርቅ የምስክር ወረቀት ሲሰጠኝ የኬነዲ ቤተመጻሀፍት ግን አመሰግናለሁ እንኩዋን አላለኝም፡፡(ምንም አዲስ ነገር ስላላገኙበት ነው።አራት ነጥብ።
  ***ይህ ከዚህ በታች ያለ ዓረፍተ ነገር መራሪስ አማን በላይን የቋንቋ እውቀት በብዙ ግድፈት ሰዋሰው ታስግምታልች!! የእኛ ኑቢያን
  “…ታሪከ-ነክ እና ባህረሃሳብን ጨምሮ ፕሮፌሰሩ የጻፉአቸውን መጻህፍት ሳነብ ምንም የታሪከ አውቅት የሌላቸውና የግእዝ ችሎታቸውም ደረጃ በጣም ዝቅ ያለ ሆኖ ስለአገኘሁት፣ በባህረሃሳባቸውም ውስጥ ከባድ ስህተት ፈጽመው ስለዐየሁአቸው የእኔን የግእዝ ብራናዎች፣ ያውም በጥንታዊ ግአዝ የተከተቡትን ተረድተው ለመፍረድ በጣም እንደሚያስቸግራቸው ተከሰተልኝ፡፡ ”
  *** “ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳም ልብወለድ ወይም (ሚት) አልጻፈም;; ከኔ መጻህፍት በተጨማሪ በ 42 በተለያዩ የታሪክ ዋቢ መጻሃፍት ላይ ተንተርሶ ነው፡፡ ከዚህ በፊት አኔም ሆንኩ ሌሎች ባለታሪኮች ያልደረሱትንና ያልደረሱበትን የሀገራችንን አደገኛ ውጥረት የሚያረግብ መጽሀፍ የጻፈው፡፡ ”
  __የሊቀጠበብት ፍቅሬ ቶሎሳን ጥረት ሊ/ጠበብት ጌታቸው ኅይሌ አድንቀዋል እኔም እንደዜጋ አከብራቸዋለሁ ግን ለመሪራስ አማን በላይ የኑቢያ መጽሐፍ ግኝት ሲባል ምሁራን ጠበብት መምከርና መከራከር አያስፈልግም ከተባለ ታሪክ ሳይሆን የመሪራስ ‘ራዕይ’ ሳያዩ የሚያምኑ ብጹአን ናቸው መሆኑ ነው? የመለስ የከፋፍለህ ብላው ራዕይ የ፵፫ ዓመቱ ልቃቂት አይበቃም!?
  ___በመጨረሻም፣ መሪራሰ አማን በላይን እኔ ወደ እኔ ና ብዬው ሳይመጣ ቀረ ስለ አልከኝ ከኔ አንድ ነገር ለማግኘት የፈለግከው አንተ ስለሆንክ ወደ እኔ መምጣት የነበረብህ አንተ ነህ፡፡ አንተ ትፈልገኛለህ እንጂ ለእኔ አታስፈልገኝምና;;
  አዎን! በእጅ አዙር ይህን መልካም ሰው ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳን ሀገርና ሕዝብ ወዳድነቱን ተጠቅመህ በሁለት ነገድ መሐል ሽቀላ ለማጧጧፍ ካልሆን እውነቱ ለትላልቅ የትምህርት ተቋማት ቢሰጥ ችግር አልነበረበትም። ሌሎች ከጀርመን ካቶሊክ ቄስ(ሚሽነሪስት) የኮረጁትን የገለበጡትን ልብወለድ(ሚት) ለድሃ ኦሮሞ ልጅ ፵፫ ዓመት በግድ ሲግቱት ኖረው ኢትዮጵያዊነቱን እንዲክድ የኢትዮጵያ ባሪያ ነህ ሲሉ ሲያዋርዱትና አያት ቅድመ አያቱን ሲያስረግሙት ይታያሉ በሀገሩ እንደከብት ‘ከልለውና ከልክለው’ ብቋንቋው ጠርንፈው አላላውስ ብለውታል አሁንም የመጽሐፍ ንግዳቸው የፖለቲካ ቁማራቸውን ተቧድነው በድሃ ልጅ እሬሳ ልመናና ሽቀላቸውን ተያይዘውታል። ይህም አይደገፍም። የጎንደርና ጎጃም መወለድ (ጎጎ) ማኅበር ማቋቋም ወይንም የብአዴን የፓርቲ አባል ለመሆን ያበቃ እንደሆን እንጂ የእውነተኛ (ኦሪጂናል) ታሪክ ከሳጥን ቆፍሮ ማግኘት በቋንቋ ምጥቅ ሳይሆን ዝቅጥ ያደርጋል በለው!!
  (ወዳጄ ክቡር ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳም ዙሪያውን ማር እሰጥ አገባን አቁመው ሌላ ሥራቸውን ቢቀጥሉ ይሻላል ከምሥጋና ጋር !)

 2. »> ክቡር ግርማ ሌላ ቪዲዮ አይተው ካልተገረሙ ቃለመጠይቁ ምንም እንከን አይወጣለትም። ችግሩ አሁን ኑሮአችን ሁሉ በደቦ ስለሆነ የእኛ ያልነው ሰው በተነካ ቁጥር በባዶ ሜዳ ቡራ ከረዮ እጅግ ያሳፍራል።ለዚህም ነው የመንጋ አስተሳሰብ ቀርቶ የሰው ልጅ ተጠየቅ አስረዳ የሚባልበት ነጻነት ያስፈልገዋል የሚባለው እንጂ አዋቂ ነን ያሉ ሁሉ ጥያቄ እንዳይጠየቁ በክብር ይልፉ ማለት እንኳንም ብዙ ሚዲያ የለን ሊኖረንም አይገባም። ከለጠፉት የቪዲዮ ሊንክ ሥር ግን ብዙ ታዘብኩ የትውልዱን ጋጠ ወጥነትና መጋዣነት ” ዓይነ ሥውር ማለት..ሥውረ ብርሃን የሳሎኑን አጥፍቶ የጓዳውን ያበራ ማለት ልበ ብርሃን ነው።”
  በጋዜጠኛው ስብዕና ላይ የተጣለው አስተያየት በዚህም ጽሑፍ ላይ ተተፍቷል ጥንቃቄ ቢደረግ መጻፍ የቻለ ደርሲ ቃላት የደረደረ ሁሉ ገጣሚ ባዶ ቦታ አግኝቶ ፅሑፍ የለጠፈ ሁሉ አዋቂና ተቆርቋሪ ፡ቅንፍ ያስቀመጠ ሁሉ በማስረጃ ይተቻል፡ ማለት አደለም በጥያቄ እንዲህ ጉድ ይፍረጠረጣልና!
  ** በእውነቱ ጋዜጠኛው መራሪስ አማን በላይን አቅርቦ ቢያንቀረቅበው እጅግ ደስ ባለኝ…ያላሳየውን ማስረጃና መረጃ በወሬ እኔ ጋ የለም እሩቅ ነው እያለ ሊትዮጵያ የትምህርት ተቋማት ሳይሰጥ የደበቀ ጩልሌ “ተወልጄ ያደኩት ጎጃምና ጎንደር(ጎጎ) ሲል ይሞላፈጣል ለመሆኑ እዚህ አካባቢ መወለድና ማደግ የግዕዝ ቋንቋ ለዩ ችሎታና የኑቢያ ድንቅ ባለችሎታ መቃብር ቆፋሪ ያደርጋል!?( ኅይለማረያም ላሬቦን ይላክበት)ሌላ ምን ይባላል።
  *********!
  ሀ) ጋዜጠኛው ለጠየቀው ቀጥተኛ መልስ ካላገኘ የአየር ሰዓቱን ከማስታወቂያ ሰከንዱ ጋር ለማጣጣም ማቋረጥ፥እንዲያሳጥር ማድረግ ወይም ጭራሽ ጥያቄውን ማቆም ይችላል። ስለብራና ስትጠየቅ ስለ አማን በላይ መጽሐፍ… ስለተዓማኒነት የታተመበት ቦታ፡ዓመተ ምህረት፤ማተሚያ ቤት ስትጠየቅ በእምነት ላይ የተመሠረተ እውነታ ካልክ አራንባና ቆቦ ሆኖ ጨዋታው ፈረሰ ይሆናል።፩)“መቃብር ቆፋሪው እና የሬሳ ሳጥን ሻጩ የሚለው ተውኔት የተሰረቀ ነው” አደለም የራሴ ፈጠራ ነው…ይባላል ስላላ ነው ማለት አደለም።
  ፪) የተለያዩ ጉዳዮች ውስጥ ትገባለህ “የባከንክ ነህ” .. ሙዚቃ ..ድርሰት..ወደፊትም ቲቪ ለመክፈት አቅደሃል..(ባተሌ)ሆንክ ?ተጨነክ? በሀሳብ ተውጠርክ? ለምን አንዱን መርጠህ ከግብ አታደርስም ማለት ነውሩ ምንድነው?
  ፫)አንድን ሰው ሚዲያ ላይ አቅርቦ “አሁን ይህ ግጥም ነው፤” ማለት!? ጠያቂ ቴዎደሮስ ፀጋዬ እጅግ በጣም ተዘጋጅቶ ጠብቆታል ማስረጃም መረጃም አለው። ተጠያቂው ከራሱ አዲስ መጽሀፍ እንኳ ገልጦ ማስተባበያ አላቀረበም ግጥሞቹም “የግዜ ማሳለፊያ መተከዣ እንጉንጉሮ የሚሆኑ እንጂ በከፍተኛ ትምሀረት ደረጃ ላይ ያለ የሚገጥመው አደሉም ከፍታ ደረጃ ላይ ሆኖ ማንቃረር ይቻል ይሆናል!?እረኛውና የጠጅ ቤት አዝማሪ እንኳ ዛሬ መጥቋል።
  ፬)”ጠንካራ ዝግጅት ማቅረብ የሚቻለው ሰውን በመዛለፍ፣ በማቆሸሽ ሳይሆን በጨዋነት ሊሆን ግድ ነው!! ይህ ካልሆነ የህሊና መጨለምን ያመጣልና ከማይታየው የጽልመት በሽታ መውጣት አስፈላጊ ነው። ጥያቄውና ትችቱ ጩኸቱ ሁሉ የጠያቂውን ስብዕና ለመንካት ልቡም ታውሯል ለማለት ነው!? የሚገርመው ጠያቂው የሀገሩን ታሪክና መጽሐፎችን በደንብ ማንበብና ከሌሎችም ጋር የተሟገተበት ስለሆነ የሚያውቀውን መዛለል ስላልፈለገ ቀጨው።
  ***በዚህ አጋጣሚ የክቡር ፍቅሬ ቶሎሳ ስለሕዝብ አንድነት፡ ሰላምና ፍቅር ስለሀገራቸው ፍቅርና የሚያደርጉት የበላይነት ተጋድሎ አድናቂ ነኝ…በዚህ ሥራቸው ግን ችግሩን ያበረታው ባታይም እመን ያላቸው በመጽሐፍ እንዲሞሉ እንጂ በአፍ ሙሉ እንዲናገሩ አልረዳቸውም ጥያቄው ሃያል ነው ይሆናል።
  ግርማ መርሃጽዮን ከሀገረ ስዊዲን ሆይ፡
  xxx ከሁሉም በላይ ዶ/ር ፍቅሬን ለማሳጣት፣ ለማንቋሸሽ፣ ስራዎቻቸው ላይ ጥያቄ ለማስነሳትና፣ እጀ ሰባራ አድርጎ ለማሳየት ሆን ተብሎ የታለመ ይመስላል።++ይህንን ስል ግን ገና ለገና ተሰዱ ተብሎ እርሳቸውን በጭፍን መደገፍ ይገባል ማለቴ እንዳልሆነ ይታወቅልኝ፡፡==ከዚህም በተጨማሪ መጽሃፋቸው ላይ የሚነሱትን የጭብጥ ወቀሳዎች አስመልክቶ በራሳቸው ፈቃደኛነት ማጠናከሪያ ቢያቀርቡ ደግ ነው እላለሁ።” እኛም እንላለን በቸር ይግጠመን

Speak Your Mind

*