የኤርምያስ ለገሰ ቪዲዮዎች ፉከራ ሲጋለጥ

ኤርሚያስ ለገሠ … ዶ/ር ዐቢይ ላይ ድብቅ የ3 ሠዓት ቪዲዮ አለኝ ማለቱን ተከትሎ ብዙዎች ለዶ/ር ዐቢይ የወገብ ቅማል ሆነባቸው እያሉ ሲጠይቁ … ገሚሱ ሲያሞግሱ፣ ገሚሱ ሲወቅሱ አየሁና እኔም የማውቀውን እውነት ላካፍላችሁ ወደድሁ። በነገራችሁ ላይ ዶ/ር ዐቢይ በቪዲዮ ማስፈራሪያ ሲደርስባቸው (ብላክ ሜል) ሲደረጉ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ በመሆ ጉዳዩን በጥልቀት ለመርመሬ ምክንያት ሆኖኛል።

ከዛሬ ዓመት በፊት የኢሕአዴግ ሊቀመንበር ለመወዳደር ዶ/ር ዐቢይ በእጩነት በቀረቡ ጊዜ የቀድሞው የደህንነቱ ሹም ጌታቸው አሰፋም ዶ/ር ዐቢይ ላይ በድብቅ የተቀረጸ የድምጽና የምስል ማስረጃ አለኝ በማለት ዶክተሩን በማስፈራራት ቀዳሚው ሰው ሲሆን አሁን ደግሞ ዓመቱን ጠብቆ ኤርሚያስ ይሄን የቪዲዮ ጌም ይዞ ብቅ ብሏል። ሚስጥር በተወሰነ መልኩም ስለማውቅ እና የሀገሪቱን ፖለቲካ በንቃት ስለምከታተል የኤርምያስን ማስፈራሪያ እንደ ባዶ ጩኸት ቆጥሬ ባልሰማ ባላየ ማለፍ አልተቻለኝም። በተለይ ዐቢይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ተገፋሁ ብለው ያኮረፉት አቶ በረከት በተደጋጋሚ ወደ መቀሌ በመብረር ጌታቸው አሰፋ ጋር ጠንካራ ግንኙነት መስርተው እንደነበር እና ብዙ ውጥኖች ወጥነው እንደነበር ይነገራል። የበረከት ሳይጠበቅ መታሰር ጌታቸውን ለበቀል እንደሚያነሳሳው ሳይታለም የተፈታ ነው። ኤርሚያስ ከበረከት ስምዖን ጋር ያለውን ታማኝነት ዘመን የማይሽረው ወዳጅነት ከላይ ከጠቃቀስኳቸው ነግሮች ላይ በመደመር “የጌታቸው አሰፋ እና የኤርሚያስ ለገሠ ቪዲዮዎች የሚያገናኛቸው ቀጭን መንገድ ይኖር ይሆን” ብየ በመጠየቅ መረጃዎችን ማሰባሰብ ጀምርሁ።

ከጌታቸው አሰፋ ቪዲዮ በፊት… ኢፌዲሪ ጠ/ሚ እና የኢሕአዴግ ሊ/ር የነበሩት ኃ/ማሪያም ደሳለኝ በድንገት ከመንግሥትም ከፓርቲም ኃለፊነታቸውን በፈቃዳቸው መልቀቃቸውን ተከትሎ እሳቸውን የሚተካ ሊቀመንበር ለመምረጥ የግንባሩ አባል ድርጅቶች በዝግ ተሰብሰበዋል። እጩ የመጠቆም ስነ ስርዓቱ ተጀመረ እና ኦቦ ለማ ዶ/ር ዐቢይን በእጩነት አቀረቡ። በመቀጠልም በቀረቡት እጩ ላይ የድጋፍና የተቃውሞ ድምጾች መሰማት ጀመሩ። ከሌሎች እጩዎች በተለየ ሁኔታ የዶክተሩ በእጩነት መቅረብ የግንባሩን አባላት ለሁለት ከፍሎ አከራከረ። ረጅም ጊዜም ወሰደ። ሁሉም በደንብ ቅድመ ዝግጅት ባያደርግም ነገሮች በፍጥነት እየተጓዙ ነበር። በተለይ የለውጡ ኃይል ሚስጥራዊነቱም፣ ፍጥነቱም በመጨመሩ የማፊያው ቡድን ለክትትል እና ለማሰናከልም ሲቸገር ታየ።በተለይም ገድለን ቀብረናቸዋለን ያሏቸውን ጓድ ዐቢይን የኦህዴድ ሊቀመንበርነቱን ከኦቦ ለማ ተረክበው በድንገት ቤተመንግስቱ በራፍ ላይ ቆመው አገኟቸው፤ ደነገጡ። የጓድ ዐቢይን ከቤተመንግስቱ በፍጥነት የማራቅ ጉዳይም ጓድ ጌታቸው አሰፋ (የወቅቱ የደህንነት ሹም) የቤት ስራ ወሰዱ።

ከኤርሚያስ ለገሠ ቪዲዮ በፊት … የለውጡ ኃይል ስልጣን ጨበጠ። ኢትዮጵያዊያን ጮቤ ረገጡ። ኤርሚያስም ኢሳት ቴሌቪዥን በመጠቀም የለውጡን ችቦ አቀጣጠለው። ብዙ ትንታኔዎችን ሰጠ።

ኤርሚያስ ቀድሞ ኢህአዴግን በቃኝ ያለ ብቻ ሳይሆን መጽሐፍትን በመጻፍ ጭምር የድርጅቱን ድብቅ ሴራ ያጋለጠ ጀግና ሰው ነው። የውስጥ ሰው ስለነበር ጥሩ የመረጃ ምንጭ ሆኗል፤ በመጽሐፍቱ የብዙዎችን አይን ገልጧ። በአጭሩ ይህ ለውጥ እንዲመጣ የበኩሉን ሚና ተጫውቷል። ለውጡን ያመጡት ደግሞ የቀድሞ ጓዶቹ በመሆናቸው የኤርሚያስ ደስታ ተገቢ ነበር ማለት ተገቢ አስተያየት ነው።

በአቶ ገዱ አንዳርጋቸው የሚመራው የአዴፓ ልዑክ አሜሪካ በተገኘበት አንድ አዳራሽ ውስጥ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ክራቫቱን ግጥም አድርጎ ኤርሚያስ ለገሠ ከፊት ለፊት ተሰይሟል። ጥያቄ ለማቅረብ ዕድል ሲሰጠውም “አቶ ገዱ ምን እንድናግዛችሁ ትፈልጋላችሁ… አንድ ሁለት ሶስት ብላችሁ ቆጥራችሁ እንድትነግሩኝ እፈልጋለሁ አለ” አቶ ገዱ ሲመልሱም ከእናተ የምንፈልገው ሀገራችሁ ውደዱ፣ ኢንቨስት በማድረግ፣ ዶላር በመላክ ወዘተ ወዘተ አግዙን አሉ። አቶ ገዱ እንዲደረግላቸው ከሚፈልጉት እገዛ ዝርዝር ውስጥ ኤርሚያስ ለሀገሩ ሊያደርግ የሚፈልገውን “በተለይ ኤርሚያስ ወደ ፖለቲካው ተመልሰህ ከእኛ ጋር ሆነህ ሀገርህን በመምራት ሀገርህንም እኛንም አግዘን” የሚለውን አጣው። አቶ ገዱ ሳያውቁት ኤርሚያስን አስከፉት። ከአዳራሹ ውጭም ሌሎችን አማራጮችን ሞከረ ፊት የሚሰጠው አጣ። በተለይ ከበረከት ጋር ያለውን ቅርበት የሚያውቁት እነ ዶ/ር አምባቸው ፊት ነሱት። አዴፓ ላይ ጥርስ ነከሰ። በአዴፓ በኩል የቀድሞ ድርጅቱን ኦዲፒን ለመታረቅ የሞከረው ነገር ሲከሽፍ ዶ/ር ዐቢይን በሚቀርባቸው ሰው (ስማቸውን መጠቅስ አስፈላጊ ስለሆነ ነው) በኩል ማስታወሻ ላከ።

የጌታቸው አሰፋ የ ቪዲዮ ጌም

ጌቾ ጉባዔው ውስጥ መግባት ባይፈቀድለትም ወደ ጉባኤው ለመግባት ግን የ እሱ መልካም ፈቃድ በቂ ስለነበር ይጠበቅ ከጉባኤው አዳራሽ ውስጥ በመገኘት የመጣበትን ጉዳይ አብራራ “ጓድ ዶ/ር ዐቢይ ሊቀመንበራችን አይሁን … ይሁን እያላችሁ ረጅም ጊዜ በክርክር መወሰዳችሁን ሰማሁና ነው መምጣቴ። መረጃውን ቀድሜ ባለማደረሴ ዶክተሩ ላይ ጊዜ እንድታጠፉ በማድረጌ ይቅርታ ልጠይቃችሁ አፈልጋለሁ። የጓድ ዐቢይን ስም ከእጩነትም ከጭንቅላታችሁ አውጡት። ዶክተሩ ላይ ለሀገራችንም ለድርጅታንም ህለውና እጅግ አደገኛ የሆነ አስደንጋጭ ሚስጥራዊ የቪዲዮ፣ የድምጽና የፎቶግራፍ መረጃዎች የደህንነት መስሪያ ቤቱ ውስጥ ይገኛል ስለዚህ በሰውየው ላይ ጊዜ አታጥፉ አትልፉ አይሆንም” አለ።

የጌታቸው ንግግር ለደጋፊዎቻቸው መርዶ፣ ለተቃዋሚዎቻቸው ደግሞ የምስራች ሆነ። ይህም ለሌላ ክርክር በር ከፈተ። ኦቦ ለማ ቪዲዮውን እዚሁ መጥቶ ካላየነው በአንገቴ ቢላ ይግባ ሲሉ። አቶ ኃ/ማሪያም ደሳለኝ የሰው ሚስጥር አደባባይ ላይ ማውጣት ተገቢ ስላልሆነ ባይታይ ምርጫቸው እንደሆነ ተናገሩ። አቶ ደመቀ መኮንን የሚደበቅ ነገር የለም … ያለህን አምጣውና እዚሁ እንየው አሉ። ጌታቸው “ለሀገራችን፣ ለፓርቲያችን በተለይ ለኦህዴድ ክብር ሲባል በእኔ ይሁንባችሁ ቪዲዮ ማየቱ ይቅርባችሁ” ብሎ ጉባዔውን በተደጋጋሚ ተማጸነ። በተለይ ኦቦ ለማ “ጓድ ዐቢይ ጥፋት ካለባቸው፣ እንደተባለው የሀገር ክህደት ከፈጸሙ እኔም ሆነ ደርጅቴ ኦህዴድ በጽኑ ልንታገላቸውና ልናወግዛቸው ስለሚገባን ቪዲዮውን ማየት እንፈልጋለን” በማለት የጌታቸውን ተማጽኖ አምረረው ኮነኑት። ብዙዎችም ደገፏቸው ስለ ጓድ ዐቢይ ደህንነቱ አለኝ የሚለውን መረጃ ሁሉ ከሰዓት በኋላ አምጥቶ ለጉባኤው እንዲያሳይ በአብልጫ ድምጽ ተወሰነ። ጌታቸውም በዚህ ጉዳይ ተስማማ። ዶ/ር ዐቢይ ትንፍሽ ሳይሉ የምሳ ሰዓት ደረሰና ለምሳ ተበተኑ።

የኤርሚያስ ለገሠ የቪዲዮ ጌም

ኤርሚያስ ለጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ የላከው ማስታወሻ ከሶስት ወር በኋላ ጠ/ሚ/ሩ ጋር ደረሰ። የማስታወሻዋ ይዘትም በአጭሩ “ኤርሚያስ ጠ/ሚ/ሩን በግል ማገዝ እንደሚሻ እና ሀገሩን ማገልግል እንደሚፈልግ በግልጽ አስቀምጧል። ለጠ/ሚው ሊያድርግ ስለሚችለው ድጋፎች ውስጥም” ከህወኃት ባልተናነሰ የድሮው ብአዴን የአሁኑ አዴፓ ሚስጥራዊ ዶክመንቶች፣ ቪዲዮዎች ወዘተ በእጁ እንደሚገኙና እነዚህን ለጠ/ሚው አሳልፎ መስጠት አንዱ ነው። ታዲያ ግን ይህንን የሚያደርገው ጥሩ ሹመት፣ ቤት እና መኪና እና ሌሎች ጥቅማጥቅሞች ሲሟሉለት እንደሆነ ይገልጻል። ኤርሚሻ በዚህ አላበቃም ቢሾሙ ጥሩ ነው ያላቸውን የአራት ሰዎችን ስም ዝርዝርም አስፍሯል።

ምሳ ሰዓቱ በዝምታ እና በጭንቀት አሳልፈው ጓድ ጌታቸው አሰፋ ጓድ ዶ/ር ዐቢይ ላይ አለኝ ያለውን ቪዲዮ ለማየት በጉባዔው አዳራሽ ጉባዔተኛው በጊዜ ታድሟል። ሰዓት መቁጠሩን ቀጥሏል። ጌታቸው አሰፋም ሆነ ሌላ የደህንነት መስሪያ ቤቱ ሰው ወደ አዳራሹ ዝር አላሉም። ጥበቃው ቀጥሏል። ኦቦ ለማና አቶ ደመቀ መቁነጥነጥ ጀምረዋል። ጌታቸው አሰፋ አመጣዋለሁ ያለውን ቪዲዮ ይዞ ሊመጣ ይቅርና ደብዛው ጠፋ። በዶ/ር ደብረጺዮን
በኩል ሲደወልለትም ስልኩን አጠፋ። ጉባዔው ወደ ሌላ አጀንዳ ተሻገረ።

“መብላቷን ሳታውቅ እጇን ታጠበች” እንደሚባለው ኤርሚያስ ለገሠ ወደ ሀገር ውስጥ በሹመት፣ ቤትና መኪና ተሰጥቶት ወደ አዲስ አበባ ሊሄድ እንደሆነ እንደሆነ ለኢሳት ባልደረቦቹ ማስወራት ጀመረ። የጠ/ሚውን ምላሽ ሳይጠብቅም ሀገር ውስጥ ጃክሮስ አካባቢ በሚኖሩ የቅርብ ሰዎቹ አማካኝነት የቤቱን ጉዳይ በቶሎ እንዲጨርሱለት ወደ ክፍለ ከተማው መልዕክት ላከ። ያገኘው መልስ ግን የሚፈልገው አይደለም። ሁሉም ሰው ወደ ሀገሩ የገባው ወዶና ፈቅዶ እንጂ በመደለያ አይደለም … ኤርሚያስም ከፈለገ እንደሌሎቹ መምጣት ይችላል የሚል ነበር።

ኤርሚሻ ተበሳጨ። የክፍለ ከተማ ሰዎችን ልክ ለማስገባትም የጃክሮሶቹን ጉዳይ አስፈጻሚ ወደ አዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ላከ። ታከለም የመጡት ሁሉ ያረፉት ሆቴል ወይም በየዘመዶቻቸው ቤት ነው። ፓትሪያሪኩ እንኳ ማረፊያ ቤት የተዘጋጀላቸው ከመጡ በኋላ እንጂ ገና ሳይመጡ አልነበረም። ስለዚህም ለኤርሚያስ ከሁሉም በተለየ ሁኔታ ቤት እና መኪና አዘጋጅተን የምንጠብቅበት ምንም ምክንያት የለም እርማችሁን አውጡ አላቸው።

ኤርሚያስ ታከለ ላይ ቂም ቋጠረ። ታከለን ልክ አስገባዋለሁ በማለትም ዶ/ር ዐቢይ ጋር ማስታወሻ የወሰደለትን ሰው ፈልጎ አገኘው እና የደረሰበትን ጉዳይ ዘርዝሮ ለዶ/ር ዐቢይ እንዲያደርስለት ጠየቀው ሰውየው ግን ለኤርሚያስ ባለፈው ለዶክተሩ የላከውን ማስታወሻ ጠ/ሚው ካነበቡ በኋላ “ይቺ ትሪክ አሁንም አለች ” በማለት ቦጫጭቀው ቅርጫት ውስጥ እንዳጣሉት መርዶ አረዳው። ኤርሚሻ ዶ/ር ዐቢይ ላይ ጥርስ ነከሰ። ተበሳጨ።

ለጠ/ሚው የሹመት እጅ መንሻ “የህወሓትና የአዴፓ ሚስጥራዊ ቪዲዮ” አለኝ ብሎ ማስታዋሻ መላኩን ረሳውና “ጠ/ሚው ላይ ሚስጥራዊ ቪዲዮ” አለኝ ወደ ማለት ተሻገረ። በቪዲዮ ከማማለል በቪዲዮ ወደ ማስፈራራት ተሸጋገረ። ኤርሚያስ አስቂኙ ነገር አለኝ ያለው ቪዲዮ አለ ያለው አበበ ገላው ጋር መሆኑ ነው። ቀደም ሲል ኤርሚያስ እነ አበበ ገላው ላይ “ሀገሬ ስሄድ እኔ እንደ እናንተ ፔኒሲዮን አላርፍም ” እያለ በጉራው መቀመጫ መቆሚያ አሳጥቷቸው ስለነበር … አቤ በተራው ኤርሚያስ ላይ ሙድ በመያዝ ሲዝናና የሚውል ሰው ነው።

ኤርሚያስ አሁን ዙሪያውን ሲቃኝ እጁ ላይ ያለው ያላልጨረሰው (ፕሮሰስ ላይ ያለው) የመኖሪያ ፈቃዱ (ግሪን ካርዱ) ነው። የእሷን ፕሮሰስ ለመጨረስ ደግሞ ጠ/ሚውን መጥመድ ይጠቅመኛል ብሎ ድማዳሜ ላይ ደርሷል። ኤርሚያስ ለገሠ ከሀገር ከመውጣቱ በፊት አለቃየ ስለነበረ በመጠኑ አውቃዋለሁ (አንተ ማለቴ የዕድሜ አቻዬ በመሆኑ ነው)። ኤርሚሻ ከፓርቲው በላይ ለአንድ ግለሰብ ያላቸውን ታማኝነት የምናውቅ ካድሬዎች “የሁለት እናቶች ልጅ” የሚል ተቀጥላ ስም አውጥተንለት ነበር። ኤርሚያስ ሁለት እናቶች አምጠው የወለዱት ሰው ነው። አንዴ ወላጅ እናቱ ሁለተኛ ደግሞ የስምዖን ልጅ በረከት። አሁን በኢሳት ቴሌቪዥን (ጽሁፉ የወጣው ኤርሚያስ ከኢሣት ሳይለቅ ነበር) የምናየውን ኤርሚያስ አምጦ የወለደው ስምዖን ልጅ በረከት ነው። አምጦ መውለድ ብቻ ሳይሆን የኤርሚያስ ለገሠ … የፖለቲካ ሰብዕና የተገነባው በስምዖን ልጅ በረከት ነው። የኤርሚያስ ስሚንቶውም፣ ብሎኬቱም፣ ማገሩም፣ ምሰሶውም፣ ጣራውም፣ መንገዱም፣ ሰማዩም፣ ምድሩም፣ ዜማውም፣ ቅኝቱም በረከት ነው። በረከት አቡክቶ የሰራት ሰብዕና ደግሞ ሴራ ከኦክስጅን በላይ ትሻለች። ሴራ ስራዋ ነው።

“ኤርሚያስ ለገሠ ሆይ ለምትወዳት ሀገርህ ስትል እባክህን ቪዲዮውን ልቀቀው! ልቀቀው!” ሲሉት አበበ ገላውን መጠበቅ ግድ ሆነ።

በ20/07/2011 በኢሳት ቲቪ ኤርምያስና አበበ ጎን ለጎን ተቀመጡ፣ ማብራሪያው ሲጀመር ኤርምያስ ቪዲዮ የተባለው በፅሑፍ ነው ብሎ ማንበብ ጀመረ ምንም የለም፣ የአበበ ተራ ደረሰና ንግግር ተጀመረ አበበ ገላው የሚለቀቅ ቪድዮ የለም ሲለው ክው ብሎ ቀረ። በአፉ አረፋውን መቆጣጠር ተሳነው፤ አፈረ። አበበ እንዲዋሽለት ተማፀነ፤ ግን አልሆነም፤ አሁንም ለአቤ እድል ተሰጠው፤ ኧ አረ ስለ ዶ/ር አቢይ መጥፎነት የሚያወራ ምንም ነገር የለም አለ። ይልቁንስ ሀገር ቤት ሰዎች እንደልባቸው ያለ ፍርሃቻ የፈለጉት መናገር ጀምረዋል፤ ወያኔ ብን ብላ ጠፍታለች፤ ብሎ ሁለተኛ ኤርምያስን አመድ አለበሰው።

ኤርሚያስ መጀመሪያ ደኢህዲንም ነበር እዚያ በነበረበት ጊዜ ስልጣን ፈልጎ አጣና አኩርፎ ኦህዴድን ተቀላቀላ በስመ አያት ስም “ዋቅጅራ” አንደምንም የበረከት ምክትል ሆኖ ስራ ሲጀምር መስሪያቤቱ አዲስ ሆኖበት አይታወቅም የኮሙኒኬሽን ስራ ከበደው። እዚያ ላይ የኢህአዴግ ግምገማ መቋቋም ተሳነው፤ ችሎታው ወረደ፣የጋዜጠኞች መሳለቂያ ሆነ ከዚያ በስራ አጋጣሚ አሜሪካ ሄዶ በዚያው ፈረጠጠ።

ኤርምያስ ዶ/ር አቢይን አጀንዳው የሚያደረገው

1) ስልጣን ፈልጎ ስላላገኘ
2) በአሜሪካን ሀገር እንደ ታማኝ በየነ ክብር ተሰጥቶት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ስላልተጠራ
3) ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደ እነ ጃዋርን፣ ዶ/ር ብርሃኑ፣ አንዳርጋቸው እና ሌሎችም ፖለቲከኞች ሲያናግሩ ኤርምያስ ተናቅሁኝ የሚል አስተሳሰብ በአእምሮው ውስጥ በመቀረፁ
4) ኤርምያስ ሀገር ቤት ግባ የሚለው ሰው ማጣቱ
5) ኤርምያስ ቅናተኛ ነው፤ እውቅና ባገኙ ሌሎች ፖለቲከኞች ይቀናል
6) ኤርምያስ የሰውን መተቸት እንጂ ስለ ሚዲያ በቂ እውቀት የለውም

እውነታው ይህ ነው

በአንዳርጌ ፍጡሩ (ዶ/ር)


“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ። ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣአቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው።

Comments

 1. ዐብይ አሕመድ ኦሕአዴግ፣ አብይ አሕመድ ኦሕዴድ ነበረ………… ኢሕአዴግ ኦሕዴድ ደግሞ የወያ ሎሌወችና ጭፍራወች ስብስብ ነው….. ሲደገድል የነበረ ጌታቸው አሰፋ ብቻ ሲሰርቅ የነበረ በረከት ስምዖን ብቻ ነው የሚል ካለ ጅላጅል ነው…… የሕወሐት ኢሕአዴግ ዘመን ግፍና ዝርፊ ቪዲዮ አለ የለም በሚል የሚድበሰበስ አይደለም…!

 2. ስለ እውነታው ባላውቅም አቀራረቡ ሳቢ ነው ።

 3. ሠላም ጤና ይስጥልኝ ውድ “ዶ/ር” ድሮ የዶክትሬት ማዕረግ እጅግ ውድና ብርቅየ ከመሆኑም በላይ ለዚህ ትልቅ የእውቀት ጥግ ለመድረስም ከፍተኛ ልፋትና ጥረት ብሎም በርካታ ምርምሮችንና ሥራዎችን መሥራት ያስፈልግ ነበር, የዛሬን አያድርገውና (በኢትዮጵያ ማለቴ ነው) አንዳርጌ ፍጡሩ (ዶ/ር) የተባልከው ግን ለምን ይህንን ያህል መውረድ እንደፈለግህ ባይገባኝም ከአንድ ፊደል ከቆጠረ ሰው እንደዚህ ዓይነት የአሉባልታ ጽሁፍ ማቅረብ አልነበረብህም ፥ ከዚህ በፊትም እንደዚሁ የፃፍከውን ተመልክቼዋለሁ ፥ ውሃ የማይቋጥርና እራስህንም ከትዝብት ላይ የሚጥል እንጂ የኤርሚያስ ለገሰን አንዳች ማንነት ወይም ክብር የሚቀንስ ወይም ዝቅ የሚያደርግ አይደለም ፥ አንድ ሰው እንደዚህ ነበር ብሎ ወይም እንደዚህ ካልተደረገልኝ ብሎ ስለአለ ነው እንደዚህ የሚሆነው ብሎ በሰው ላይ መበየን አግባብ አይደለም ፥ በነገራችን ላይ አንተም ሆንክ ኤርምያስ ለገሰ ለእኔ አንድ ናችሁ ፥ ምክንያት ከሁለታችሁም ጋር ምንም ዓይነት ትውውቅም ሆነ ንግግር የለኝም ፥ ነገር ግን ኤርምያስን በተለያዩ ስብሰባዎችና በቲቪ መስኮት በሚያስተላልፋቸው ድንቅ መልእክቶች አውቀዋለሁ ፥ ኤርምያስ ለእኔ ምርጥ ኢትዮጵያዊ ነው ፥ ለአንተ ደግሞ ሴረኛውና ዘረኛው ብሎም ጸረ – ኢትዮጵያዊው አብይ(ግራኝ)አህመድ አሊ ምርጥ ዘረኛህ እንደሆነ ከምትሞነጫጭረው ድኩማን ሃሳብህ መረዳት ይቻላል ፥ ለማንኛውም ለአንተ ልቦና ይስጥህ ፥ እንደተማሩት እንጂ እንደ መንጋው አታስብ !!!

 4. ጽሁፋ ተራ የመንደር ወሬ ይመስላል ምክንያታዊ ሰውን አያሳምንም

 5. Isn’t this issue too late? Why didn’t you post it by then instead of now? And why don’t you be decent to express your feelings? Please use modest language.

  • Girma Belay – thaks for your comment.

   This is not the writing of Golgul. It is an “opinion” by the person mentioned.

   We posted it now because we received it now. It is just that simple.

   Editor

 6. Wow 👏👏👏👏👏

 7. በጣም ትክክል ያው ድሮም እኮ ወያኔ የወጋው ምኑ ይታመናል…ይሄ ፔንዱለም… ትላንት ያወራውን ነገ አይኑን አፍጥጦ ይክዳል!!! የሚገርም አቀራረብ! እናመሰግናለን!

Speak Your Mind

*