ታሪክ የወረሰ ትውልድ፣ ያልተወለዱ ህልሞችና የማዋለጃው መንገድ

የዛሬ 150 ዓመት በሕይወት ብንኖር ኑሮ ብዙዎቻችን ምንአልባት ሁላችንም በዘመኑ ከኖሩት አባቶቻችን ጋር በአንድ የአስተሳሰብና የኑሮ ዘይቤ ምህዋር ላይ እንደምንተም እገምታለሁ። የነበረውን የህይወት ከባቢ እንደዘላለማዊና የማይቀየር እውነት በመቁጠር እንደምንመላለስ አስባለሁ። ፈጣሪ በማይቋረጠው የዘመናት ጐዳና ላይ በየዘመኑ የሚያስነሳቸው ታላላቆች ግን ጨለማ ባጠቆረው ሰማይ ላይ እንደሚበር አብሪ ኮከብ ለሁሉም እንዲታዩ ሆነው ይምዘገዘጋሉ። ኢትዮጵያ በታሪክ ደርሳናቷ ላይ የሚንቦገቦጉ፣ የዘመንን ጢሻ እየመነጠሩ ከትውልዶች ጋር የሚተሙ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ነበሯት። አሏት። ከእነርሱ መካከል ዛሬ ከምንዘክራቸው አፄ ቴዎድሮስ አስቀድመን የመጀመሪያው እረድፍ ላይ ማንን ልናቆም እንችላለን? እውቁ የዘመናዊ ታሪክ ፀሐፊው ሊቀ – ጠበብት ባህሩ ዘውዴ Society and State in Ethiopian History  በተሰኘው መፅሃፋቸው አፄ ቴዎድሮስ የመጀመሪያው ህልመኛ (Dreamer) እንደነበሩ፣ ዘውዱን በዘመነ መሣፍንት ከወደቀበት አዘቅት በማውጣት የኢትዮጵያን ንጉሣዊ አስተዳደር ወደቀደመ ከፍታው ለመመለስ ከፍ ያለ ሥራ እንደሰሩ ያስረዳሉ። አክለውም በሀገሪቷ ጥልቅ የኃላቀርነት ደረጃ ከፍተኛ ቁጭት ይበላቸው እንደ ነበር ይነግሩናል።ከቁጭታቸውም የተነሳ እራሳቸውን ጨምረው ሕዝቡን “የታወረ፣ የደነቆረና አህያ”  በማለት ጭምር ይገልፁ ነበር። በመጨረሻም ባህሩ እንደሚነግሩን በውስጣቸው ይነድ የነበረው የለውጥ እሳት እራሳቸውንም ሳያስቀር በላቸው።  ዛሬ የምንዘክራቸው ካልተማረና ደህ ህዝብ ጉያ፣ እጅግ ኃላቀርና በጐበዝ አለቆች ፍልሚያ ከተመናታለች ሀገር አብራክ ተፈጥረው ታላቅ የአንድነትና የዘመናዊነትን ሕልም አርግዘው ሳይገለገሉ የዛሬ 150 ዓመት የተሰውት የአፄ ቴዎድሮስ ዝክረ በአል ላይ በመገኘቴ የሚሰማኝ ክብር እጅግ ከፍ ያለ ነው።

መቼም እራሱን የቻለ  የዘመን አውድ ቢኖረውም አፄ ቴወድሮስ በዘመናቸው ብዙ የጭካኔ ተግባራት መፈፀማቸውን ግን አንክድም።  ነገር ግን አፄ ቴወድሮስን እንዳከብራቸው ከሚያደርጉኝ ነገሮች አንዱልጥቀስ። በመፅሃፍ ቅዱስ ውስጥሙሴ አንድ ለማመን የምቸገርበትን ነገር ተናግሮአል። “እነዚን በጐች ወይንም የዋህ እስራኤልአውያን ከምታጠፉ እኔን ከህይወት መፅሃፍ ደምስሰኝ” ብሎ ነበር። ለአንድ አማኝ ከፈጣሪ የሕይወት መዝገብ መደምሰስ የመጨረሻው የመስዋትነት ጥግ ነው። አፄ ቴወድሮስም አንዲት ወይዘሮ እንዳሉት ጥልቅ የሀይማኖት ትምህርት ዕውቀት የነበራቸው ነበሩ። እናም በመጨረሻዋ ሰዓት የገዛ ህይወታቸውን ሲያጠፉ በራሳቸው ላይ የምድርን ብቻ ሳይሆን የሰማይንም በሮችና መስኮቶች እየዘጉ እንደነበር ያውቁታል።  ስለዚህ የዜጐችን ሕይወት ሲያጠፉና ሲቀጥፉ ኑረው ሀገርን ጥለው አልኮበለሉም። እንደአንዳዶቹም ሞትን ለማምለጥ ሲሞክሩ ትቦ ውስጥ በሞት ሰይፍ አልተቀሉም። ይልቅስ ሀገርን ከሚያሳንስ፣ ሕዝብን ከሚያኮስስና ትውልድንም አንገት ከሚያስደፋ ታሪክ ለትውልድ ጥለው ከማለፍ ይልቅ በመለኮታዊ ችሎትምሳይቀር ተጠርቀው ወዳሲኦል ጥልቅ መወርወርን መርጠዋል። ይህ የሀገርንና የህዝብን ክብር ያስቀደመ  የመስዋዕትነት ጥግ ነው።  ዛሬ የዚህ ዘመን ትውልድ ከአፄ ቴወድሮስ የወረሰውም ይሄንን ከፍ ያለ የመሰዋትነት ታሪክ ነው።

ቴዎድሮስን ሳስብ የሚደንቀኝ አንድ ነገር አለ።በዚያን ዘመን ኢትዮጵያንየማዘመን ጥማቸውንና የታላቅነት ርሀባቸውንከየት ቀዱት? ምንስ እንደዚያ አንቦገቦገው? እያልኩ እየጠይቃለሁ።ባህሩ እንደሚነግሩን “ በዘመነ-መሳፍንት ተወልደውና በዘመነ መሣፍንት አድገው እንዴት የዘመነ መሣፍንት ማርከሻ ሆኑ? እላለሁ።የተሰጠኝ ዕርስ በወቅታዊ የኢትዮጵያ ሁኔታ ላይ ያመዝናልና ወደዚያው ላምራ። አንድ ፍሬ ሃሳብ ግን ላክል። የቴዎድሮስ ህልም ሙሉ በሙሉ ተወልዷል ብዬ ባለሰብም ከህልፈታቸው በኃላ ተወልዷል። ከእርሳቸው የመቅደላ ላይ ውድቀት በመማር ዮሃንስና ሚኒሊክ ታላላቅ ገድሎችን ፅፈዋል። አድዋን ሳልጠቅስ ማለፍ እንዴት ብዬ እችላለሁ? የኢትዮጵያውያን ሥነ-ልቦናም ከፍ ያለ ማማ ላይ ተሰቀሏል። ነገር ግን ሀገርን በማዘመን ፍቅር ቢጦፉም ይህ ህልማቸው መሬት የለቀቀ አይመስለኝም።ጠንካራና የተማከለ ሀገር የመገንባት ህልማቸው ግን በተወሰነ ደረጃ በአፄ ኃይለስላሴ ተወልዷል ለማለት ይቻላል።

ከ1935 ዓ.ም. በኋላበባላባታዊና ባህላዊ ባለስልጣኖች ባንድ ወገን የውጭ ሀገር ትምህርት የቀሰሙና በሀገራቸው ለከት ያጣ ድህነት ቁጭት የተቃጠሉ ወጣት ኢትዮጵያን ባለስልጣኖች በሌላ ወገን መካከል የነበረው ትንቅንቅ ከቴወድሮስ ሀገርን የማዘመን ህልም ጋር የተቆራኘ ነበር። ንጉሠ ነገስት ኃይለስላሴ ሚዛን ለመጠበቅ ሲሉ በሁለቱ ወገኖች መካከል የነበረው ፍትጊያ እንዲቀጥል ቢፈልጉም ውሎ አድሮ ግን ዳፋው ህልውናቸውን ጭምር የሚጠይቅ ሆኖዋል።

ከመቶ ዓመት በኋላ የሥጋና ደም ብቻ ሳይሆን የዕምነትም ወንድም አማቾቹ ገርማሜና መንግስቱ ንዋይም ቴወድሮስ ያማጡትን ሀገርን የማዘመን ምጥ ያምጡ ዘንድተገደው ነበር። ቴወድሮስ በመጨረሻዋ ሰዓት ለእንግሊዞች እንዳሉት “እናንተ ያሸነፋችሁኝ በስርዓት የሚመራ ህዝብ ስላላችሁ ነው” ብለው ነበር። ቀደም ብለው ይኸንን ቁጭታቸውን የሚያስታግስ የትምህርት ሥርዓትንም ሆነ የተግባቦት መስመር መዘርጋት አልቻሉም። ይልቅስ ህዝቡ ለምን ህልሜን አያልምም? ለምንስ ምጤን አያምጥም? ሲሉ ጨከኑበት። ጭካኔያቸውም ይገባቸው ነበርና መልሰው “ፈጣሪዬ ሆይ ምነው ወሰደኸኝ ህዝቡን ብታስርፈው” ይሉ ነበር።

እንደአፄ-ተዎድሮስ የከፋ ባይሆንም እነ-ጄኔራል መንግስቱም የገጠማቸው ተመሣሣይነት ነበረው። ሕዝቡ ብዙም ህልማቸው የገባው አልነበረም። ለዚህምነው ጄኔራል መንግስቱ ይግባኝ እንደማይጠቅ በፍርድ ቤት ባደረገው ንግግር የሚያስገርም ትንቢታዊ ንግግር የተናገረው።  “ወዮ ለእናንተ፣ ወዮ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሃሳቤ የገባው ቀን ወዩ ለእናንተ” ብሎ ነበር።  ጄኔራል መንግስቱ ወደ ንጉሠ ነገስቱ ይግባኝ እንደማይልና ይልቅስ እንደእርሱ ለዓላማ ሲሉ ወደተሰው ወንድሞቹ ለመሄድ  እንደናፈቀ ገልፆ ከሞት ከማፈግፈግ ይልቅ ወደመት ሲቸኩል ታይቷል።  ሰቅራጥስ ለእውነት ሲል ከሞት ጋር እንደተጠበቀ ጀኔራል መንግስቱም ወደ ሞት ናፈቀ።

ዛሬ ድረስ አያሌዎች የመደራጀትን አስፈላጊነት አበክረው ያሳስባሉ። ገርማሜ ንዋይ ምንአልባትም የመደራጀትን አስፈላጊነት ቀድሞ በመረዳት ማህበሮችን በመፍጠር የመደረጃት ሙከራ ቢያደርግም “አሁን ድረስ የዘለቀው የመሰነጣጠቅ አባዜ በጊዜው ችግር ሆኖበታል። ቴወድሮስ ህዝብ ህልማቸውን አልረዳ ሲል በብስጭት እርምጃ ይወስዱ እንደነበረው ሁሉ እነጀነራል መንግስቱም መፈንቅሉ መንግስቱ መክሸፉን ሲረዱ በብስጭት የሥርዓቱ ጐምቱ ባለስልጣናት ላይ እርምጃ ወስደዋል፤ ያልተገባ ቢሆንም።

ቴዎድሮስ በፀጋዬ ገብረ መድህን ተወኔት “እውነት ትውልድ ይፋረደኝ” እያለ እንደቃተተው ሁሉ እነጀኔራል መንግስቱም የተስፋአይኖቻቸውን በለጋ ተማሪዎች ላይ ያሳረፉ ይመስላሉ። ከመንፈቅለ መንግስቱ ሙከራ በፊት በ1951 ዓ.ም. የኮሌጅ ቀን ሲከበር የሕዝብን ብሶት ማንሳት የጀመሩት ተማሪዎች የእነርሱን ዓላማ አንግበው እንደሚንቀሳቀሱ በልባቸው የማይናወፅ እምነት ያሳደሩ ይመስላል። የመፈንቅለ መንግስቱ መሪዎች በኢትዮጵያ በሕግ የተገደበ (Constitutional Monarch) ለማቋሟም ብሎም ልማትን ለማፋጠን በይፋ ከመናገራቸውም በላይ ከተማሪዎች ጋር ትግላቸውን የማስተሳሰር ሙከራም አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ተማሪዎች ትግል ሲቀጣጠል ከእነጀነራል መንግስቱ መገደል በኋላ ብዙ ዓመታትን አልጠየቀም።የኮሌጅ ቀንን በማክበር የተጀመረው የተማሪዎች ተቃውሞ እየተቀጣጠለ መጣ። አፄ-ኃይለ ስላሴ በትምህርት  የለውጥ መሣሪያነት በማመን ከየአካባቢው ለጋ ኢትዮጵያውያንን ወደ ትምህርት ማዕድ ሲሰበስቡ አንዳንዶች” ይኸንን የደሃ ልጅ አስተምረህ አስተምረህ በራስህ ላይ መዘዝ እንዳታመጣ”  ብለዋቸው ነበር። ትንቢቱ ሰመረ። የተማሪዎቹ ትግል በንጉሡ ላይ አነጣጠረ።ለንጉሱ የኮሌጅ ቀን የውርደትና የዘለፉ ቀን ሆኖ ይታያቸው ገባ።

ይኸ ሁሉ ሲሆን ግን የተማሪወቹ ጥያቄ የዴሞክራሲ ጥያቄ የሚያሰኝ መልክ አልነበረውም። ምንአልባት የዴሞክራሲን ጉዳይ በሚመለከት ከሁለት ዓመት በኋላ አዲስ አለማየሁ ለንጉሠ ነገስቱ የፃፉት ደብዳቤ የመጀመሪያዋ የፖሊቲካና የዴሞክራሲ ሰነድ ተደርጋ ልትቆጠር ትችል ይሆናል። ይልቅስ በወቅቱ የዓለማችንን ሰማይ እያመሰቃቀለ የነበረው የሶሻሊዝም አውሎ ነፋስ በኢትዮጵያ ለዘመናት የተንሰራፋው የአገዛዝ ጥቅጥቅ ደመና ላይ ይነፍስበት ገባ። ተማሪዎቹ በሀገራቸው ሥር የሰደደ ድህነትና የአፈና ስርዓት በአንድ ወገን፣ ዓለምን እያካለለ ባለው የሶሻሊዝም ርዮተ ዓለም በሌላ ወገን መናጥ ጀመሩ። የተቃውሞ ጡጫቸው በንጉሡ ላይ ብቻ ሳየሆን በኢትዮጵያ ታሪክ ላይም አነጣጠረ።

አፄ ቴወድሮስም ሆኑ እነገርማሜ ያለውን ታሪክ አክብረው ሲነሱ ተማሪዎቹ ግን ለኢትዮጵያ ታሪክ ክብር አጡ። ቢያንስ ኦሮሞዎች፣ አጋዎችና፣ ትግሬዎች ያልተሣተፉበትን ታሪክ ለማስታወስ ያስቸግራል።ተማሪዎቹ ግን የኢትዮጵያ ታሪክ የፊውዳልና የአማራ ታሪክ ብቻ አድርገው ገነዙት። አሁን ድረስ የሀገራችንን መሠረት እያናጋ ያለው ዘረኝነት የትውልድ ክር የሚመዘዘውም ከተማሪዎች የተቃውሞ እንቅስቃሴ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን ምንም እንኳን የስልጣን ማማ ላፍ ለመውጣት ሲባል እና ልዩነትን ለመፍታት የሀይል ፍጥጫ ለዘመናት በኋላም የላንጋኖ እንደሁነኛ መሣሪያ ተቆጥሮ ጥቅም ላይ ቢውልም በሥነ-ፅሁፍ አማካኝነት መዘላለፍ ግን ምን አልባትም በተማሪዎች የተቃውሞ ትግል ውስጥ ሳይወለድ አልቀረም። በተለይም አንዳንዶች እንደሚሉት በብሔረሰቦች ጉዳይ ላይ የተፃፈው የጥላሁን ታከለ ፅሁፍ ተጠቃሽ ሆኖ እናገኘዋለን። በዚህ ረገድ በመዘላለፍ የተጀመረው የተማሪዎች ትግል በመገዳደል ተደመደመ።

“ከእኛ ጋር ካልሆንክ ከእነርሱ ጋር ነህ” ብሎ ሌላውን ማጥቃትና መዝለፍ፣ ተመሣሣይ ዓላማና ፕሮግራም ይዞም ለስልጣን ሲባል በውሃ ቀጠነ እርስ በእርሱ መባላት የተለመደ የፖለቲካችን አካል ሆኖዋል። የተማሪውን እንቅስቃሴ ስንቃኝ በጣም ብዙ ህፀፆችን በትችት ወረጦ መርጠን መልቀም ብንችልም ለዓመኑበት ነገር ሁለንተናን አሳልፎ የመስጠት ደረጃቸው ከድክመቶቻቸው በተጓዳኝ ጐልቶ የሚቆም ትልቅ የመስዋዕትነት ማማ ሆኖ ይታያል። በለጋ እድሜያቸው ለአመኑበትና እውነት ብለው ሞትን እስከመናቅ ያሳዩት ቁርጠኝነት በጣም ያስደምመኛል፡

የፖለቲካ ባህላችን የቀረጹ የተለያዩ ነገሮችን ማንሣት ቢቻልም ይኸንን በመሠለ አጭር ፅሑፍ ላይ መነካካት ግን አደጋው ከጥቅሙ ያመዝናል። ነገር ግን ጥቅል የሆነውን የፖለቲካችን ንጣፍ ላይ ጥቂት ነገር ማለት ተገቢ ይመስለኛል። በአጠቃላይ ዘመናችን ድረስ የዘለቀው የህዝብና የገዥወች ግብግብ መሠረት አንድ ጉዳይ ላይ ይመረኮዛል። ህዝብ ሊኖረው የሚሻው የአስተደደር አይነት ገዥዎች ሊጭኑበት ከሚፈልጉት የአገዛዝ ቀንበር ጋር መጣጣም አልቻለም።  ይህ በገዥዎችና በተገዥዎች መኮከል ያለውን ልዩነት ያሰመረና የተቀውምና የድጋፍ መሠረትም ሆኖ የቀጠለ ጉዳይ ነው። ገዥዎችም ህዝብም አንዱ በሌላው መገልገል ይፈልጋሉ። አንዱ በሌላው ላይ የሉዓላዊ ስልጠን ባለቤትነቱን፣ የሀገሩና የህልውና ባለቤት መሆኑን ማስረገጥ ይሻል። እስካሁን የዘለቀው የፖለቲካችን ችግር መሠረቱ በዋናነት ይኸው ነው። የህዝብ ሉዓላዊነት ሳይወለድ ዘመን ጠገቡ የአገዛዝ ልዕልና ቀንሷል።

ፖለቲካ የተለያዩ የሕዝብ ጥቅሞችና ፍላጐቶች ታርቀውና ተቻችለው እንዲሄዱ ሁነኛ መሣሪያ ቢሆንም ተግባር ላይ ማዋል አልተቻለም። ፖለቲካ የመወጋገዣና የተቀርኖ መፈልፈያና የጥላቻ ግንብ መሰረት ከመሆን እንዲዘል አልፈቅድንለትም።

ለዚህም ይመስላል በአገዛዞችና በህዝብ መካከል ፍርሃትና አለመተማመን የነገሠው።  ፖለቲካችን ህዝቡ መብቱን እንዲጠይቅ የሚያበረታታ ሳይሆን ወገቡን ሰብሮ ለገዥዎች ዙፋን ይሆን ዘንድ የሚገፋፋ ነው። ገዥዎች እንዲገዝፉ ህዝብ ለእነርሱ እንዲነጠፍና እንዲኮስስ የሚያደርግ ግንኙነት ነው፤ ከጥንት እስከ አሁን። ለዚህም ነው በአምናችን፣ በዘንድሮአችንና በከርሞአችን መካከል ብዙም ልዩነት የማናየው።

ምን አልባት የከፋ የከፋውን ብቻ እያየን ከበጐ ነገራችን  ጋር እንዳንተላለፍ መጠንቀቅ ተገቢ ነው። የእይታ መነፅራችንን የኢትዮጵያ አገዛዞች ከህዝብ ጋር የነበራቸውን የግንኙነት መስመር በህገ-መንግስት መሠረት ላይ ለመዘርጋት ተደጋጋሚ ሙከራዎች አድርገዋል። ወደዚያው እናዙር። ይህ ተግባር እንደበጐ ሙከራ ቢወሰድ ክፉት የለውም። በቀደመው የታሪካችን ክፍል ከ13ኛው እስከ 20ኛ ክፍለ ዘመን ክብረ-ነገስትና ፍትሀ-ነገስት በሚሉ ሁለት ድርሳናት ላይ ተመስርተው ህግና ሥርዓትን ለማስፈን ሙከራ ያደረጉ ነበር። በኋላ ላይ ግን በተለይም በአፄ ኃይለ ስላሴ ዘመን በዘመኑ ከነበረው የጃፖን ህገ-መንግስት እንደተቀዳ የሚነገርለት ህገ-መንግስት በ1923 ዓ.ም. መውጣቱን እናያለን። ይህ ህገ መንግስት ሀገሩንም ህዝቡንም ጠቅሎ ለንጉሡ የሚያስረክብ ሲሆን ለህዝብ ያጐናፀፈው መብት ዜግነትን ብቻ ይመስላል። በ1947 የወጣው ህገ-መንግስትም ቢሆንY የስልጣን ምንጩ ሕዝብ ሳይሆን መለኮት መሆኑን ያስቀጠለ ቢሆንም ተግባር ላይ በሚገባ አልዋለም እንጂ የተለያዩ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶችን የተካተቱበት ነበር።

ብዙዎች በቁጭት የሚያነሱት በአገዛዙ ላይ የተቃውሞው አንቅስቃሴ ተፋፍም በቀጠለበት ወቅት በሀምሌ 30/1966ዓ.ም ተረቆ የበረው ህገ-መንግስት ጥቅም ላይ ቢውል ኖሮ ምን አልባትም ከዚያ ዘመን እስከአሁን ከምንዳክርበት የፖለቲካ፤ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ችግር አረንቋ ሊያወጣን የሚችል ወይንም እንዳንዘፈቅ የሚያደርግ መሣሪያ ይሆን ነበር። ይሁን እንጁ ተፋፍሞ የነበረው የአቢዮት እሳት የረቂቅ ህገ-መንግስቱን ህልውና ብቻ ሳይሆን የገዥዎችንም ህልውና አከሰመው። የህልመኞቻችን የሊበራል ዲሞክራሲ ህልም በህልምነት ቀረ።

የደርግ ህገ-መንግስትም የስልጣን መሠረት እግዚዓብሔር ሳይሆን ሰፊው ህዝብ ነው አለ።  አክሎም በህገ-መንግስቱ አንቀጽ 3 ንዑስ አንቀስ 1 በኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ  ስልጣን ከህዝብም የሰርቶ አደሩ ነው ሲል ደነገገ።  በሰራተኛው ስም ደርግ የአፈ ሙዝን ልዕልና ከፍ አድርጐ አውለበለበ።  የአሁኑ የኢህአዴግ አገዛዝ ደግሞ የስልጣን ምንጭ እግዚአብሐር ወይንም ህዝብ ነው አላለም። ካስማውን ጐሣ ላይ ተከለ። የሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነት የተሰጠው ለህዝብ ሳይሆን ለየብሄሩ በየግል የሚታደል ሆነ።ኢህአዴግ ደጋግሞ ሊነግረን እንደሞከረው ህዝብ የመከረበትና ያፀደቀው ህገ-መንግስት አይደለም። የሕገ መንግስቱ አርቃቂ ኮሚሽን ሊቀመንበር የነበሩት ዶ/ር ነጋሦ እንደሚሉን ውይይቱ የተደረገው በኢህአዴግና በአንዳንድ ገለሠቦች መካከል ነበር። ያም ሆኖ እንኳን አጠቃላይ የህገ-መንግስቱ ረቂቅ ለህዝብ ቀርቦ ውሳኔ ህዝብ አልተሰጠበትም።የህዝብ የሉዓላዊነት የስልጣን ባለቤትነት ሳይሆን የገዥዎች ልዕልና ቀጠለ።

ቃልና ተግባሩ ተጣጥመው ባያውቁም በኢህአዴግ ሕገ መንግስት አያሌ የመብት ድንጋጌዎች ተቀምጠዋል። ይሁን እንጂ እንደሌሎቹ ህገ-መንግስቶች ሁሉ ዜጐችን ይቅርና ህገ-መንግስቱእራሱንም ከዘመኑ አንጋቾች መታደግ አልቻለም። አሁንም ዜጐች ከወረቀት በዘለለ የሉዋዓላዊ ሰልጣን ባለቤት መሆን አልቻሉም። አገዛዝም የአፈና እንጂ የነፃነት ምኩራብ ሊሆን አይችልም።  አልቻለም።

ከ13ኛው እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን ክብረ ነገስት፤ ፍትሀ ነገስት፤ ጉባኤ ሊቃውንት እና ህገ ስርዎ መንግስት (የመንግስት አስተዳድር መመሪያ) የሚባሉ ሰነዶች የሰላምም ሆነ የጦርነት መመሪያ ሆነው እንዳገለገሉ ሁሉ ህገመንግስቶችም በዋናነት የህዝብን መብት ለማክበር ሳይሆን የአገዛዞችን ህልውና ለማስቀጠል እና ለማጠናከር ጥቅም ላይ ውለዋል። የህዝብን ጥቅምና መብቶች የሚያስከብሩ ሁኔታዎች ባለመኖራቸው ብዙውን ጊዜ ውቅረ መንግስቱ የመርጋት ችግር ታይቶበታል-ይታይበታል። ቀደም ብለን እንዳየነው አጼ ቴድሮስ ትልቅ ትኩረት ከሰጧቸው ጉዳዮች አንዱ የአረጋውያንና በየጎጡ የመቧደን አዙሪት ውስጥ የወደቀውን ሀገር በማዋሃድ የተሻለ ውቅረ መንግስት ላይ ጠንካራ ሀገርን መገንባት ነበር።ይህ ህልምም ቢሆን በሙላት አልተወለደም።

አገዛዞቹ የቅርጽ እንጂ የይዞት ልዩነት አልነበራቸውም። ህዝብ ሁልጊዜም ለአገልጋይነት እንጂ ለተገልጋይነት አይታጭም። በዜጎች እና በአገዛዞች መካከል የግንኙነት መስመሩን ለመዘርጋት የሚዘጋጁ ሰነዶች ህዝብ ያመነባቸው የቃል ኪዳን ሰነዶች ሳይሆኑ ህዝብ እንዴት መገዛት እንዳለበት አበክረው የሚያሳዩ ናቸው። ያ ማለት በሀገራችን ውስጥ ምንም አይነት የዲሞክራሲ ተሞክሮ ፈጽሞ የለም ማለት አይደለም። የሚገባውን ያህል ያልዘመርንለትና ለዓለም ያላስተዋወቅነው የገዳ ዲሞክራሲ እና በደቡብ በሀገራችን ክፍሎች አንዳንድ አካባቢዎች የነበሩ የህዝብ ተሳትፎ ላይ የተመሰረቱ አስተዳድራዊ መስተጋብሮች ነበሩን። የህዝብ ፈቃድ መኖር እና አለመኖር አገዛዞች የሚያወርዱት አስተዳድራዊና ፖለቲካዊ መመሪያዎች እንዲሳኩ ወይንም እንዳይሳኩ የማድረግ አቅም አለው። ለዚህም ነው ሀገራችን ለዘመናት ባለችበት የምትረግጠው። ህዝብ ስለችግር፣ ጥቅሞቹ፣ መብቶቹና ተስፋዎቹ መምከር በእነርሱም ላይ መወሰን ባልቻለባት ኢትዮጵያ ነገራችን ሁሉ የእንቧይ ከባብ ሆኖ ቀጥሏል። የዛሬ 60 እና 70 አመት ከዚያም በቀደሙ አመታት ያነሳናቸው አጀንዳዎች ዛሬም አጀንዳዎቻችን ናቸው፤ የትላንቱን ከዛሬ የዛሬውን ከነገ የምናስተሳስርበት  የርዮት ድር የለንም። አምናችንን እና ዛሬያችንን ተደባልቀዋል። ነገአችንስ እንዴት ይሆን? ካለፈው እና ከዛሬው ባልተማርን መጠን ነጋችንን ከትናትና ከዛሪያችን ጋር መመሳሰሉ አይቀርም ።

ከአላሚዎቻችን በመማር ነገአችንን የተሻለ ማድረግ ይገባል። ቀደም ብለን እንዳየነው የቴድሮስ ሀገሩን ከዘመነ መሳፍንት አዙሪት በማውጣት ጠንካራ፣ የረጋ እና የዘመነ ሀገርን የመፍጠር ህልም ነገን የተሻለ ማድረግ ላይ ያተኮረ ነበር። የ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ከዚያም በኋላ ከአድማሳቸው ባሻገር  ያለውን አለም ስልጣኔ ምን ላይ እንደደረሰ በአካል በመገኘት ያረጋገጡ ኢትዮጲያውያን ህልምም ኢትዮጵያን የማዘመን ህልም ነበር። እነጀነራል መንግስቱ ንዋይ አያሌ ዘመናትን ካስቆጠረው ዘውዳዊ አገዛዝ ጋር ግብግብ የገጠሙት ነገን የተሻለ ለማድረግ ከሰነቁት ህልም ጋር የተቆራኘ ነው። የኢትዮጲያ ተማሪዎች መሬት ላራሹ፣ የብሄር ብሄረሰቦች እኩልነት ይከበርና ህዝባዊ መንግስት ይቋቋም የሚሉ መፈክሮችን አንግበው የወጡት በራሳቸው አውድ መሰረት ነገን ለህዝባቸው የተሻለ ለማድረግ ነው።

በእርግጥ ጊዜና ሁኔታ ተመቻችተውላቸው ያሰቡትን እርምጃ በዘመናቸው መራመድ ቢችሉ ምን ይፈጠር ነበር? የሚለውን መመለስ እንዳንችል ሁኔታዎች አይፈቅዱም ባልተፈጸመ ነገር ላይ ፍርድ መስጠት ተገቢ አይሆንም።

በኢትዮጵያ ዲሞክራሲን የማስፈን ህልም ካልተወለዱ ህልሞቻችን አንዱ ነው። እነጀነራል መንግስቱ የንጉሳዊ ስርአቱን ስልጣን በመገደብ የተሻለ መንግስት ለመመስረት ቢያልሙ ቢሳካላቸው ኢትዮጵያን ዲሞክራሲያዊት ያደርጓት ነበር ወይ ? የሚለውን ጥያቄ በአውንታ ለመመለስ የሚያበቃ ማስረጃ የለንም። የሀምሌ 30/1966ቱ ሊብራል ህገ መንግስት ቢታወጅ ኢትዮጲያን የዲሞክራሲ ምድር ያደርጋት ነበር ወይ? ከግምት ያለፈ መናገር አንችልም። ህዝባዊ መንግስት ይቋቋም የሚለው መፈክር ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጲያን እንመስርት ማለት ነበር? ነው ብዬ ለመቀበል እቸገራለሁ። በሶሻሊዝም እርእዮት አለም ፍቅር የተነደፉ ወጣቶች የህዝብን ሉአላዊነት የሚያረጋግጥ ዲሞክራሲያዊ መንግስት ይፈጥር ነበር ብዬ መቀበል ከፍ ያለ የዋህነት ይመስላል። ምክንያቱም ማርክሊዝም ህዝብን በሀይል ለአንድ ዓላማ ማስገዛት እንጂ የህዝብን ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት ማድረግ አይደለም።

የተማሪዎች ትግል ካፈራቸው የፖለቲካ ቡድኖች አንዱ የሆነው ህዝባዊ ሃርነት ትግራይ (ህውሀት) ስለዲሞክራሲ ሲባል አያሌዎች ዋጋ ከፍለዋል ቢልም በተግባር የምናስተውለው የቀድሞው የአገዛዝ ስርአት በአዲስ ትረካ  (narration) ሲቀጥል ነው። በትግሉ ወቅት ህይወታቸውን የከፈሉ የህውሀት ታጋዮች ዛሬ ጓደኞቻቸው በኢትዮጲያ ህዝብ ጫንቃ ላይ የጫኑትን የአገዛዝ ቀንበር ቢያዩ ምን ይሉ ነበር? ምን አልባት የተማሪዎች ትግል በጥቂት የደርግ ወታደሮች እንደተነጠቀ ሁሉ የህውሀት ትግልም የጥቂት አጤዎች መጠቀሚያ ከመሆን አልዘለለም።

በ1983 ዓ.ም በአብዮት የመጣው አገዛዝ ሌላ አብዮት ባፈረጠመው አገዛዝ ሲተካ በእርስ በእርስ ጦርነት የተዳከመችው ኢትዮጵያ እና ህዝቧ ወዴት ያመራሉ? የሚለውን ጥያቄ ቁርጥ መልስ አልነበረውም። ብዙዎች የኢትዮጵያን እጣ በአውንታዊ ይወስናል የተባለው የሽግግር መንግስት ሁሉንም የኢትዮጵያ ጉዳይ የሚያገባቸው ወገኖች ያላካተተ ከመሆኑም በላይ የየብሄሩ ተወካዮችን በመደርደር በዲሞክራሲ ላይ የሚሰራ የአገዛዞች የሸፍጥ ጉዞ ተጀመረ። የሽግግር መንግስቱ ሁነኛ አካል ኦነግ ከሽግግር መንግስቱ ወጣ ። በመጣንበት መንገድ መርገጣችንቀጠለ ።

አገዛዙ ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ ተነስቶ ወደ ሊብራል ዲሞክራሲ አመራለሁ ሲለን ለመሞኘት ተዘጋጅተን ጠብቀነው። ጋዜጠኞች ጋዜጣዎችን ማተም ጀመሩ። እንዲያውም አገዛዙ አውቆ በነፃነት እንዲጽፉ እያደረገ ነው እስኪባል ድረስ በጎ ጅማሪዎች ታዩ። ፓለቲከኞች የፓለቲካ ማህበሮችን ፈጠሩ። አለም አቀፍ ማህበረሰቡም በተግባራዊ ሂደት አገዛዙን ለመቀየር (Constructive engagement) በሚል ወዳጅነት ሽር ጉድ ማለቱን ተያያዘው። የአገዛዝ ወፍጮ ድምፅ ከሩቅ ድረስ ቢሰማም ቋቱ ላይ ግን ጠብ የሚል ጠፋ። አብዮታዊ ዲሞክራሲ ሊቢራል ዲሞክራሲን ይወልድ ዘንድ ማርያም ማርያም ብንልም የተፈጥሮ ህገ አሸናፈ። አብዮታዊ ዲሞክራሲ እየደጋገመ እራሱን ወለደ።

በሁሉም ዘንድ መነቃቃትን የፈጠረውን አብዮታዊ ዲሞክራሲ ሊብራል ዲሞክራሲን ይወልዳል በሚል ተስፋ ብዙዎች በአዋላጅነት የተሰበሰቡበትን ታሪካዊ ወቅት 1997ን ዛሬ እንደታሪክ ልነግራችሁ አልችልም። በቦታው ባትኖሩም እንኳን በያላችሁበት ማሪያም ማርያም ስትሉ ነበርና። የዴሞክራሲ የመወለድ ጭንቅ አገራችን ሰቅዞ ቢያሰቃያትም ሕይወቷን አልጠየቀም። የዲሞክራሲ ሺል ግን በትክክለኛ መንገድ ከእውነተኛ እና ትክክለኛ ዘር አልተገኘምና ብርሀን ሳያይ ተጨናገፈ። ሳይወለድ ቀረ።

ዲሞክራሲን የተራቡ ኢትዮጵያውያን ከገጠር እስከ ከተማ፣ ከከተማ እስከ ውጪ ሀገር ልደቱን ሊያከብሩና ሊዘክሩት የነበረው የዲሞክራሲ ንጋት ለዘመናት  በዘለቀው የአገዛዝ ባሩድ ጽልመት ለብሶ ዜጎችየነበራቸው የተስፋ ሙላት ወደ ጥልቅ ብሶትና የተስፋ እጦት ተቀየረ። አያሌ ኢትዮጵያውያን ወደ ማጎሪያ ካንፖች ተጓዙ፤ የህይወትን እሸት ለመቃም የተዘጋጁ ወጣቶች በአገዛዙ አፈር በሉ። የህዝብ የሉአላዊ ስልጣን ባለቤት የመሆን ትግል በአገዛዙ ፈርጣማ ጡጫ ድባቅ ተመታ። ህዝብ አምጦ የወለደው ቅንጅት ለአንድነት እና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ዋነኛ የአገዛዙ ሰለባ ሆነ።

የአገዛዙ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ባቡር የማስመሰያ ጭንብሉን አውልቆ በአፈና ሀዲዱ ላይ መትመም ቀጠለ። የኋልዮሽ ተምዘገዘገ። በዚህ የኋልዮሽ ጉዛ ፍርኃትን ሰብረው እና ሞትን ንቀው የሚውተረተሩ ኢትዮጲያውያንን ማደን፣ ታፔላ እየለጠፉ መቀመቅ ማውረድ የሚመጻደቅበት የጀግና ውሎ አደረገው። በጨለመበት ሰአት ከአለም እንደሚሰወር መናኝ ለአመታት ከህዝብ፣ ከወገን እና ከሚያባቡ ልጆቻችን ተለይተን አመታትን ተጋፈጥን ። እድሜ ይፍታህ ተባልን። እድሜን የሚሰጥ ፈጣሪ እንጂ ሰው አይደለም። ውሳኔው አልሰመረም። የትግሉ መርዘም እና ማጠር በህዝብ የትግል ጽናት እንጂ በገዥዎች እብሪት አይወሰንም በመጨረሻም ለዛሬ ቀን በቃን።

ዛሬ ጭላጭል ይታያል። አገዛዙ የመጣበት መንገድ የትም እንደማያደርሰው የተረዳ ይመስለኛል። ለጋ ወጣቶችን ለህዝባዊ ልእልና ሲሉ ያላቸውን የመጨረሻ መስዋእትነት ህይወታቸውን በክብር ገብረዋል። ችግሩ አገዛዙ ትግሉ ጋብ ሲል ወደ ጥንካሬው የተመለሰ ህዝቡም ያከበረውና የደገፈው ይመስለዋል፡ ይህን አይነት ግንዛቤ አሁንም ይዘው የሚቀጥሉ ከሆነ የክፍለ ዘመኑን ታላቅ ስህተት ይሰራሉ። አሁን አገዛዙ ለህዝብ ሉአላዊ የስልጣን ባለቤትነት ሊገዛ ግድ ይለዋል ።

መፍትሄዎችን ሁሉ ከአገዛዙ እንስራ እንዲንቆረቆሩልን መጠበቅ ስህተት ነው። ኢትዮጵያን የምታክል ሀገር መፍትሄን ከአንድ ሰው መጠበቅም አይገባም። ሁሉም የራሱን ጽዋ ሊያነሳ ይገባዋል። ተቀዋሚዎች እያለፈ ያለውን ዘመን ሳያልፍብን ልንሰራ ይገባል። ከዘመነ-መሳፍንትም ሆነ ከተማሪዎች እንቅስቃሴ የሚጨለፈውን ያለመቻቻልና የመለያየት ፖለቲካ ልንቀብረው ይኸው ዘመን ግድ ይለናል ። እልህ መጋባት ያለብን ዲሞክራሲን እውን ለማድረግ እንጂ ለመጠፋፋት መሆን አይገባውም።

በሀገራችን ተጀምሮ የሚቋጭ ለውጥ ማምጣት አልቻልንም። ነገራችን ሁሉ ድንገቴ ታስቦ፣ ታልሞ የማይሰራና የማይዘልቅ ሆኗል። ዋነኛ ምክንያቱ ህዝብ የሀገሩ ባለቤት ባለመሆኑ፣ ህዝብ ያላመነበት እንቅስቃሴ ደግሞ ለውጤት አይበቃም። ከአጼ ቴዎድሮስ ጀምሮ የኢትዮጵያ ገዢዎች ጠንካራ መንግስት ሊፈጥሩ ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም። የህዝብ መንግስታት ስላልሆኑ። ጠንካራ መንግስት የሚባለው በመሳሪያ ክምችት፣ በሰራዊት ብዛትና በታንክ ጋጋታ አይደለም። የህዝብን ይሁንታ ያገኘና ስር በሰደደ ፍትሀዊ ተቋማት መሰረት ላይ የተገነባ መሆን አለበት። የአፄ ኃይለስላሴ ዘውዳዊ ስርዓት በ6 ወራት ትቢያ ሲሆን ታይቷል። በአፍሪካ እንኳን ገዝፎ ይታይ የነበረው የደርግ ሰራዊት በአይናችን ስር የዶግ አመድ ሲሆን አይተናል ። ጥንካሬውን በተተበተበ የጎሳ መረብ ላይ የመሰረተው የዚህ ዘመን አገዛዝም ቢሆን በህዝብ ሰላማዊ የአመጽ ትግል አጽሙ ሲቀር ሁሉም ታዝቧል።  ይኸኛውን ልዩ የሚያደርገው የሀገራችን መሰረትም ማናጋቱ ነው። በመሆኑም በኢትዮጵያ የተረጋጋና የሰመረ ዘመን ይነጋ ዘንድ ህዝብ የሉአላዊ ስልጣን ባለቤት ሊሆን ይገባዋል።

የአገዛዞች የአፈና ናዳ ቢበዛም በባህላችን እና ታሪካችን ያሉን የውል ተዘክሮዎቻችንና መስተጋብሮቻችን ስር የሰደዱ በመሆናቸው የናዳውን ውርጅብኝ ተቋቁመን ለማለፍ ትልቅ ሀይል ሆነውናል። እስከ አሁን ያለው አንዱ የሌላውን ሀሳብ ትርጉም ያለመስጠት ወይንም የማበሻቀጥ ሂደት የትም አያደርስም። ተግዳሮቶቻችንን ተቋቁመን ተስፋዎቻችንን ለመጨበጥ በጋራ ታሪኮቻችን ላይ መሰማማት ይገባናል። በታሪካችን ሳንግባባ ሁላችን የምንወዳት ሀገር መገንባት አንችልም። አንዳችን የምንሰራውን ሌሎቻችን እያፈረስን እንቀጥላለን። ምክንያቱም የታሪክ ትንታኔዎቻችን ይለያያሉና። የታሪክ ህፀፅ የሌለበት ሀገርም ሆነ ሕዝብ የለም ልዩነቱ ከታሪክ ተምሮ መጭውን ዘመን በአስተማማኝ መሰረት ላይ መገንባቱ ነው።

ዛሬ የሀገር አንድነትን ውቅረ መንግስት ለመፍጠር ትልቅ ተጋድሎ ያደረጉትን የአፄ ቴዎድሮስ 150 የሕልፈተ-ዓመት ስንዘክር ኢትዮጵያውን ጎሳቸውን እንደዮኒቨርስ ማየት በጀመሩበት ወቅት ነው።

ዛሬ ጎሳን መሰረት ባደረገው የአገዛዙ ስሌት ሀገር ምድሩ ተናግቷል። ስነ ልቦናችን ተዛብቷል። አንዱ የእኔ ብሔር ሰው የሚለው ስልጣን ሲይዝ ሲደሰት ሌላው ስለነገው እርግጠኛ መሆን ይሳነዋል። የሰውን ልጆች ሁሉ ክብር የሚቀበል ዴሞክራሲያዊ መንግስት ይገባናል። ሁሉም የሚደመጥበትና ሀገሬ ብሎ የሚኮራበትን ማዕቀፍ መዘርጋት ለነገ የሚያድር ስራ አይደለም። በጋራ ርዕዮት ላይ የጋራ ሀገር ለመገንባት መቀራረብ መወያየትና መግባባት ተቀዳሚው አጀንዳችን ሊሆን ይገባል። የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች ሁሉ የሚመክሩበት ጉባኤ መጠራት ይገባዋል። ለውጥ በተለይም መልካም ለውጥ በኢትዮጵያ ከኤሊም በላይ ያዘግማል። አሁን እንደቀድሞው እንቀጥል ዘንድ ዘመኑ አይደለም። የአጣዳፊ ለውጥ ዘመን ነው። አገዛዙ ሳይውል ሳያድር መድረኩን ሊያዘጋጅ ከሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ የፖለቲካ ሃይሎች ደግሞ ዘመኑን ለሚመጥን የፖለቲካ ለውጥ ሊዘጋጁ ይገባል።

ሂሳብ የማወራረድ ባህልና ፍላጎት ዝቅ ብሎ ሊቀበር ይገባዋል። አብዛኛዎቹ የፓለቲካ ችግሮቻችን የሚፈቱት በፓለቲካ እንጂ በህግ አይደለም። በእርግጥ ዴሞክራሲን ለመገንባት የሕግ የበላይነት እንደንጣፍ ሆኖ ያገለግላል። ነገር ግን ሁሉን ነገር በህግ ቋጥረን ልናልፍ አንችልም። በይቅርባይነት አንዳችን ለሌለው የእዳ ስረዛ ልናደርግ ይገባል። “እርቅ ደም ያድርቅ” እንደሚባለው ለብሄራዊ እርቅ እና ወንድማማችነት ልባችንን አጥበንና ታጥለን መገኘት አለብን።

ይህ የእርቅ መንገድ ህዝባዊ ልዕልና የሰፈነባት ጠንካራ ሀገር ትኖረን ዘንድ እጅግ አስፈላጊ ነው። ይህን የእርቅና የወንድማማችነት መንገድ በከፋ ችግሮች ውስጥ ተዘፍቀው የነበሩ ሀገሮች ሲጠቀሙበት አይተናል። ጊዜው አንዳችን በሌለው ውስጥ ያለውን በጎ አስተዋፅዖ ለማስተዋል ለራሳችን እድል የምንሰጥበት ነው። ጊዜው የዴሞክራሲ ለውጥ ያመጡ ዘንድ ጥቂት ግለሰቦችን የምንጠብቅበት ሳይሆን ሁላችንም ሌላውን ሳንጠብቅ ሃላፊነታችንን የምንወጣበት ነው። ጊዜው በቲኒኒሽ ድሎች የምንኮፈስበት ሳይሆን የሁላችንም የዘመናት ናፍቆት የሆነውን የዴሞክራሲ ንጋት እውን ለማድረግ ያለንን ሁሉ የምንሰጥበት ነው። ቀይ ባህር አጠገብ ቆመናል። የአገዛዝን ባህር ከፍለን ወደ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ መገስገስ ወይንም በቀጫጭን የልዩነት ድሮች ተተብትበን ባህሩ ውስጥ መስመጥ። እኔ የአገዛዝን ባህር በእርቅ፣ በፍቅርና በወንድማማችነት በትር ከፍዬ ሊሻገር ቆርጫለሁ። ነገር ግን ብቻዬን መሻገር አልችልም። ብቻዬንም መሻገር አልፈልግም። ወደ ተስፋችን ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ለመሻገር የፀና የሰላማዊ ትግል መስመር ላይ አብረን ተስፋችን ሳንጨብጥ ወደኋላ ሳናይ ለመጓዝ አሁን እንቀሳቀስ። ዴሞክራሲን የማዋለጃው መንገድም ይኸው ነው።

ፍትህ እንደ ቀትር ፀሐይ ፍቅር እንደ ሃይለኛ ጅረት ወንድማማችነትም እንደጉንጉን አበባ በኢትዮጵያ ላይ ይንገስ!

(ፍራንክፈርት፤ ግንቦት 2010 ዓ.ም)

Delivering an unborn dream left to us by history

Andualem Aragie*

If we go back in time to 150 years ago, we would not be living and thinking any different from our ancestors of the time. I would even think that we would consider the environment and context of the time as an immutable absolute. In this infinite thread of time,only the greats graced to each era by the Creator navigate across times like shooting stars on a dark sky, for all to see.Ethiopia always had Ethiopian greats that sparkle its accounts, cut across the maze of time to move at pace with living generations. It still does. Yet, from their midst, whom else can we place ahead of the figure we commemorate today, Atse Tewodros II? The famous historian Bahru Zewde in his Society and State in Ethiopian History (2012) calls Atse Tewodros II the “first dreamer” and explains the Emperor’s grand work of lifting the crown out of the catacombs of Zemene Mesafint and restoring the monarchy to its former heights. Bahru also holds that Atse Tewodros II felt great grief at the deep backwardness of the country. His sorrow was such that he lamentedthe people, himself included, were “blind, ignorant donkeys”. In the end and as Bahru also states, this desire for change that blazed inside Atse Tewodros II spared no one, not even himself. I feel great honour to be here today, at this event, to commemorate Atse Tewodros II martyred 150 years ago without engendering the dream of unity and modernity he conceived despite being himself the child of this deeply backward country, tired by squirmy chieftains and of uneducated, impoverished people.

Although retrospect makes for an unjust judge, we cannot deny that Atse Tewodros committed many acts of cruelty. Allow me nonetheless to state one of the reasons that inspire in me only great respect for Atse Tewodros. In the Bible, we read Moses proclaiming something that I personally find hard to believe. He intercedes for Israelites and says “But now, please forgive their sin–but if not, then blot me out of the book you have written.” (Exodus 32:32, New International Version) For a believer, to be “blotted out” of the book of life is the ultimate sacrifice. Atse Tewodros, as accounts have it, was one with in-depth religious schooling. Hence, when, at the last hour, he took the decision to take his own life, he was acutely aware that he would be closing not just the earthly doors on himself but also the heavenly ones. After rampantly slaughtering people, he was not among those who then decide to flee into exile. Nor, like others, was he caught in a ditch attempting to escape death. Instead, perhaps also aided by spiritual guidance, rather than leaving a legacy that would disparage his country, demean his people and shame generations to come, he chose to be thrown into the abyss of hell. It is a sacrifice that put a country and a people’s honour above all else. It is this legacy of sacrifice that Atse Tewodros has bequeathed our generation.

Something baffles me when I think of Atse Tewodros. I wonder where he drew this thirst for modernising Ethiopia and this hunger for greatness. What fuelled its fire? As Bahru puts it, “how did a man who grew up under Zemene Mesafint then become the latter’s downfall?” However, since the topic I was asked to speak on concerns current Ethiopia let me get on with the subject. First, one last point. Although I do not believe that Tewodros’s dream was fully delivered, the dream was conceived again after his death. From Tewodros’s fall at Maqdala, Yonannes IV and Menelik II have both achieved great feats. How can I go without mentioning Adwa? A victory that firmly positioned the consciousness of Ethiopians on a high ground. Still, although burning with a passion for modernizing his country, Atse Tewodros’s dream never took off ground. Similarly, his dream to build a strong and unified nation was realised much later and only to an extent with Atse Haile Sellassie.

From 1935 E.C. onwards, the clash between young Ethiopian public officials educated abroad and angry at the extreme poverty of their country on the one hand and noblemen and traditional leaders on the other was only a continuation of Atse Tewodros’s dream for modernity. Although Atse HaileSellassie thrived in this tension that allowed him to maintain balance, in the final analysis, its splinters threatened his very own existence.

A hundred years after Maqdala, the brothers in blood and belief that were Mengistu and Girmame Neway conceived this same dream of propelling their country into modernity. Atse Tewodros had told the British in his final days “you gained the upper hand because your people abide by direction”. Yet he set up neither an education system nor a “social contract” that would mitigate this lament of his. Rather, fuming at the inability of his people to dream his vision and to labour his passion, he punished them. However, appalled at his own cruelty, he often prayed for death so “his people would find respite”.

Although not as forbidding as what Tewodros faced, General Mengistu and co faced similar popular resistance. The people did not quite understand the general’s dream. This explains why, at his trial, the general elaborating on his refusal to appeal for pardon from the Emperor famously said “I pity you, I lament for you when the day comes and Ethiopians finally understand my intention.”General Mengistu expressed, in his refusal to appeal the sentence, his hurry to join in death the comrades who sacrificed themselves for his dream. The general longed for death much as Socrates accepted to die for truth.

Today as well, several stress the importance of organising. Girmame Neway as perhaps the pioneer in understanding the importance of organising attempted to set up associations but was discouraged by the curse of fragmentation that is still alive today.Just as a frustrated Tewodros raged against his people, General Mengistu, upon realising that the coup d’état was aborted, took irreversible and unnecessary measures on the revered high officials of the regime.

In a scene that recalls Tewodros’s plea to future generations “to be his judge” in Tsegaye Gebre Medhin’s play, General Mengistu’s own hope hinged on budding students. Indeed the general seemed to be convinced that the yet nascent student protests began just ahead of the attempted coup d’état, in 1951 E.C. was an expression of his own dream. The leaders of the attempted coup d’état announced freely that their goal was to establish a Constitutional Monarchy bound by law and to accelerate development and tried to link their struggle to that of the students.

It was not many years after the general and his crew died that the student protests spread like wildfire. The protests that began with the celebration of College Day took larger proportions. Convinced of its power as an instrument of change, Atse Haile Sellassie introduced young Ethiopians from all over the country to education against the advice of some who foresaw that these students will turn on the Emperor himself. The prophecy happened. The student struggle directly targeted the Emperor. For the Emperor, College Day became a day of humiliation and insults.

Nevertheless, the students’ demand is a far cry from a call for democracy. Perhaps, in terms of calling for democracy, Haddis Alemayehu’s letter to the Emperor two years after College Day, can be considered the very first political and democratic document. Instead, the storm of socialism wreaking havoc on the world’s horizons started blowing on the thick clouds of the system that ruled our country for millenniums. The students vacillated between the age-old poverty and stifling governance in their country on the one hand and a socialist ideology gaining traction across the globe. Now their fists were not just directed at the Emperor but at the very history of Ethiopia.

While Atse Tewodros and the Girmame crew respected the existing history and went with it, the students had no esteem for the history of Ethiopia. It is impossible to find a historical event in which at the very least Oromos, Agas and Tigres did not take part. However, the students embalmed the entire history of Ethiopia as feudal and Amhara. The thread of racism/xenophobia that is still shaking the foundation of our country can be traced back to this student movement. In addition, even though a show of force has for years been used to climb to the top of power and to resolve differences, the student movement also introduced the culture of using writing to disparage one another. In particular, as some maintain, the paper by Tilahun Takele on the issue of ethnic groups can be cited as an example. A student protest that began with vilifying one another ended with killing one another.

Calling out the other for “siding against us if not with us”’, destroying one another over trifles even when one has convergent goals and programmes is now part and parcel of our political culture. While we can go on nit-picking several problems from the student movements, their willingness to give themselves wholly for what they believed in should equally stand out as the height of sacrifice. I am awed by the contempt for death they displayed at such a young age for what they believed to be true.

We can cite many other examples that shaped our political culture but this short paper will not do them justice. Perhaps, it is appropriate to mention a few points on the overall picture. In general, this ongoing battle between the people and its rulers is rooted in one thing. The governance desired by the people and the governance that its rulers want to impose is a complete mismatch. This incongruity continues to heighten the dissonance between the governors and the governed and remains the basis for gaining or losing support. Both the governed and the governors want the other’s subservience. Both want to force themselves as sole owner of sovereign power, of the country and of the country’s very own existence. The problems in our politics that remain to this day are all fundamentally down to this. While the people’s sovereignty is not realised the age-old absolute power of the governors has somewhat minimised.

Even though politics is an instrument of compromise of various interests and desires, we could not apply it in practice. Instead, we did not allow politics to be used other than to breed differences and build walls of hatred. It is perhaps why fear and mistrust prevail between the people and the governors. Our politics is not one that encourages the people to demand their rights but one that forcefully bends the people’s back to serve as a stepping-stone for the rulers. From past to present, it remains a relationship where people are subjugated to aggrandize the rulers. This continues to be the reason why we do not see much difference between our yesteryears, our present and our future.

Perhaps it is erroneous to miss the good while focusing on the worst. Hence, our overview now takes us to the repeated attempts by our country’s rulers to bind their relationship with the people on a constitution. It would not hurt to consider this attempt as one positive effort. In the early years of our history, between the 13th and 20th century, the Kibra Negest and the Fitha Negest were the main documents attempting to introduce law and order. Much later, during Atse Haile Sellassie’s reign, we see the first constitution purported to have been inspired from the Japanese experience, see the day in 1923 E.C[1]. This constitution made the Emperor sole proprietor of both country and the people and the only right it accorded the people seems to be their nationality. The 1947 E.C constitution on its part proclaimed the source of power to be divine and not popular but, although never applied, provided some civil and political rights to the people.

Many regret the constitution drafted in Hamle 30, 1966E.C. at the height of the anger and protests against the government, which they think, if adopted, would have perhaps saved us or at least prevented us from the political, economic and social crisis that we find ourselves still mired in. However, the flames of revolution already raging consumed along with the draft constitution the entire existence of the rulers. The dream for liberal democracy of our dreamers stayed just a dream.

The Derg regime’s constitution recognized that the source of power lies with the people and not with God. It went even further and stated, in its article 3 (1) that the Ethiopian People’s Democratic Republic lies not just with any people but its workers. In the name of the workers though, Derg only waved high the sovereignty of the barrel of the gun. The current EPRDF regime on its part recognized neither God nor the people as the source of power. It rather dug its claws in ethnicity/tribalism. Sovereign power is not given to the people but is rather handed out to each ethnic group separately. As EPRDF itself repeatedly tried to tell us, the constitution was not adopted by popular consent. Dr Negasso [Gidada] who was chairperson of the constitution drafting commission also said that the consultation took place only between EPRDF and a few individuals. Even if that were the case, the draft was never put to popular consultation and referendum. The sovereignty of the government continued to trump the sovereignty of the people.

Even if its word and its action always diverged, EPRDF’s constitution contains a number of rights provisions. However, just like the preceding constitutions, it could not even protect itself from the power mongers of our time much less protect the people. Sovereignty of the people is still not achieved. The rulers have still not, indeed cannot, become harbingers of freedom but of oppression.

While the 13th and 20th century, the Kibre Negest, the Fitha Negest, Book of the Synods (?),HigeSerweMengist (directives on government administration) served as directives in times of war and of peace, the constitutions’ main purpose was not to uphold the people’s rights but to entrench and prolong the lifespan of the rulers. Since the people’s interests and rights were never protected,the governments were never safe from shaking to their core. As we saw earlier, Atse Tewodros’s main goal was to build a strong and unified nation around a better government wrenched away from warring old men.He could not even fully deliver this dream.

The various rulers came in different shapes but in similar content. The people were subservient but never served. The documents that governed the relationship between the rulers and the people were never instruments of mutual commitment consented by the people but tools of subservience of the people. It does not mean that experiences of democracy do not exist in our country. The Gada system that we have not popularised sufficiently and other community participation based governance systems in the southern parts of our country were all democratic practices. Popular consent or lack thereof has the power to determine the success or failure of administrative and political directives from the rulers. It is the reason why our country has been standing still for so many years. It will be futile to expect results if the people are not allowed to consult on their problems, their interests and their hopes. The issues we raised 60 and 70 years ago are still our issues. We do not have an ideological thread that ties our yesteryears to the present. Our past and present are all jumbled up together. How will our tomorrow be then? Well,if we do not learn from the past and from the present it will be inevitable that our tomorrow will stay the same.

We have to learn from our dreamers and make our tomorrow a better one. As we saw earlier Tewodros’s dream to lift his country out of ZemeneMesafint and build a stable and modern country came out of his yearning for a better tomorrow. Those Ethiopians who have had the exposure to the level of development the world had reached in the early 20th century also dreamed of a modern Ethiopia. General Mengistu and his crew’s confrontation with the age-old monarchy is also related to the same dream of modernising Ethiopia. The students who protested with slogans of land to the tiller, equality to the ethnic groups, also dreamed, within their own ideological framework, for a better tomorrow for their people.

What would have happened if the circumstances and the times allowed them to succeed? It is a question we cannot answer because it is impossible to judge what did not happen.

A democratic Ethiopia is one of our unborn dreams. If General Mengistu and co had succeeded to bring about a constitutional monarchy, would it have led Ethiopia to democracy? We have no evidence to answer this question affirmatively. If the Hamle 30, 1966 E.C. constitution was adopted would it have made Ethiopia a land of democracy? We can only speculate. Was the call for a “people’s government” a call for a democratic Ethiopia? I find it hard to say. I for one think it is naïve to expect a democratic government and people’s sovereignty from youngsters crazed by a socialist ideology. After all, Marxism is about subjugating people by force for a common goal and not about giving power to the people.

Even though Tigray People’s Liberation Front (TPLF), itself a product of the student movement, claims that several were martyred for democracy, what we observe is a continuation of the old governance system with a new narration. What would their comrades in struggle feel if they came today to see what kind of governance their friends have set up? Perhaps we can speculate a few strongmen, like the student movement by a few Derg soldiers, hijacked their cause.

When in 1983 E.C one revolutionary government was replaced by another, also fattened by revolution, it was not clear where, Ethiopia, by then worn out by civil war, was headed. The transitional government, which many hoped would decide the country’s fate in a positive manner, not only was not inclusive of the many first hand stakeholders but having lined up a series of ethnic groups went about setting up a plot of strongmen on democracy itself. The transitional government’s key component the Oromo Liberation Front (OLF) walked out. Thus began our flight back to where we started.

When the ensuing government still professed to lead us to a liberal democracy we believed, we waited. Journalists published newspapers. Several hopeful beginnings flourished to the point of suspicions about the intentions of the government. Politicians formed political associations. The international community cosied up to ostensibly positively influence the government with “constructive engagement”. The mills of the governance were heard far and wide but its pipes remained empty and nothing substantive came of it. We hailed Mary for revolutionary democracy to engender liberal democracy but we could not change the law of nature. Revolutionary democracy only multiplied itself.

You do not need me to remind you of the historic 1997 E.C when several midwives hoped to deliver liberal democracy from revolutionary democracy since, even those of you who were away from home still hailed Mary for the country. Democracy has always been a painful pregnancy for Ethiopia but has so far not cost the motherland’s life. Yet, the foetus of democracy, not sown from the right seed, was aborted without seeing light. It remains unborn.

The dawn of democracy, awaited by Ethiopians hungry for it from rural towns to the cities, from the cities to foreign countries, was shot to darkness by the governance that has gone on for years and muted the overflowing feelings of hope into deep frustration and helplessness. Countless Ethiopians were dragged to concentration camps; the lives of budding youths taken by the government. The people’s struggle to become sovereign squashed by the government’s heavy fist. The people’s own child, the Coalition for Unity and Democracy (CUD), became one of the government’s principal victims.

The government’s train of revolutionary democracy now shed all pretense and continue driding its rail of oppression. The train flew backwards. In its journey backwards, it took cowardly pride in hunting, labeling and throwing away in jail the Ethiopians who broke the spell of fear and shunned death.Like hermits who recluse themselves in dark times, we faced isolation from our people, our loved ones and our beloved children. They called it a life sentence. But life is a gift from the Creator and not men. Their judgement did not hold. People’s will and determination decides the length of the struggle, not the arrogance of rulers. It is the reason you find us, here, today.

Today, we see some glimmer of light. I think the rulers have understood that the path it has taken will lead it nowhere. Youngsters and youths have paid the ultimate sacrifice of life for the sovereignty of the people. The trouble is that when the struggle slows pace, the government believes it is strong and respected by the people. If it continues with this belief, it would be making the century’s biggest mistake. It is imperative that the government now submits itself to the sovereignty of the people.

It is a mistake to expect all the solutions to pour down on us from the government. It is wrong to expect one person to be the solution for a country as big as Ethiopia. Everyone should do his or her part. Us the opposition should get acting now. We should bury for the last time the culture of intolerance and divergence that has plagued us since Zemene Mesafint or the student movement. We should be enraged for democracy not raging to destroy each other.

We have not succeeded in bringing about a lasting change for our country. Everything we have done so far was impulsive, unreasoned and unsustainable. The main reason was that the people,without whose participation nothing can be achieved, were not owners of their country’s affairs. The rulers of Ethiopia since Atse Tewodros have not succeeded in establishing a strong government because they were not governments of the people. No amount of weapons, nor gold reserves can make a government strong. Governments should obtain the blessing of the people and be founded on deeply rooted and just institutions. We have witnessed the Atse Haile Sellassie regime come to dust within 6 months. The mighty Derg army feared across Africa went to ashes before our eyes. We have seen the current regime’s labyrinthine weaves of tribalism that form its foundation stripped down to skeleton by the peaceful struggle of the people. Perhaps what differs this last situation is that it quivered with it the very foundation of our country. Thus, for stable and prosperous times to come to Ethiopia the people must become the sovereign source of power.

Even though the hands of the oppressive rulers were heavy, the deep roots of our cultural and historical social contracts and social practices have been our strength to withstand all. It will lead us nowhere to denigrate or malign one another’s ideas. To overcome our defects and to take back our hopes we need to find a common ground on our shared history. If we do not come to terms with our history, we cannot build a country we love. We will continue to cancel out each other’s achievements if our interpretations of the past is conflicting. No country, no people exists that is without faults in its history. The difference is in how they have learnt from their past and built a reliable foundation for their future.

We mark today the 150th commemoration of the passing of Atse Tewodros II who fell in the battle to build a unifying government at a time when Ethiopians are revolving their universe around their tribe.

Today the entire country is trembling from the tribe based zero sum game the government has played. Our consciousness has tipped sideways. As one side celebrates the ascending to power of their ethnic group another wakes with uncertainty about their tomorrow. We deserve a democratic government that believes in the dignity of all human beings. We cannot sleep on the duty to set up the framework for a country about which everyone is proud and where everyone is heard. To build a shared country with a shared vision we need to make it our agenda to come closer to each other and foster understanding. A congress bringing together all those who feel concerned about Ethiopia’s affairs should be called. Change and in particular positive change advances at a tortoise pace in Ethiopia. But this is not the time for business as usual. We are in fast moving times. The government should rush to facilitate such a forum,while the political forces inside and outside the country should fast adapt to the current political needs.

The culture of and desire for reciprocal retribution should be buried deep. Politics and not law can solve our political problems. It is true that rule of law is the basis for democracy. However, we cannot rely on the law alone to bring about all the solutions. We should cancel each other’s debt with forgiveness. Just as we say “forgiveness dries blood” we need to open our hearts to national reconciliation and brotherhood.

Forgiveness is indispensable for us to build a strong country where the people are sovereign. We have seen countries in worse situations than ours apply reconciliation and forgiveness. This is the time for allowing ourselves to see the contribution of the other. This is not the time for expecting democracy to come from a few individuals but for all of us to do our part without waiting for others. This is not the time for heroism over small victories but the time to give everything to birth the democracy we have been longing for years. We are at the edge of the Red Sea: to part the sea of oppressive governance and head towards a democratic Ethiopia or to get entangled on thin threads of differences and drown. I, myself, have resolved to cross the sea of oppression with forgiveness, love and brotherhood. But I cannot cross it alone. Indeed, I do not want to cross it alone.

Let us now stride, together, without losing hope and without dwelling on the past, the path of unwavering peaceful struggle and cross to our hoped democratic Ethiopia. This is the only way to deliver democracy.

May justice like midday sun, love like a strong current and brotherhood like a wreath of flowers triumph in Ethiopia!

  • AndualemAragie, Speech at the 150th Commemoration of the Victory of Maqdala and the passing of Emperor Atse Tewodros II of Ethiopia in Frankfurt, Germany- May 12, 2018
  • [1]All dates follow the Ethiopian Calendar unless otherwise indicated (EC).

[1]All dates follow the Ethiopian Calendar unless otherwise indicated (EC).


Notice: Reports, rebuttals, analyses, press releases and/or recommendations offered by the author/s or organization/s do not necessarily reflect that of Goolgule: Amharic Internet Newspaper’s stand.

Speak Your Mind

*