የሰላማዊ ሰልፍ መንፈስ መመለስ

(ሳራ ግርማ ኖርዌይ ኦስሎ)

በበርካታ ኢትዮጲያዊያን ትውስታ ውስጥ ሰላማዊ ሰልፍ ሲባል ወደ አእምሮአቸው የሚመጣው በምርጫ 97 ሰሞን የነበሩት ህዝባዊ የመብት ጥያቄዎች ናቸው። በወቅቱም ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በቴሌቪዥን መስኮት ቀርበው ከአሁን በውሃላ ማንም ሰው አደለም ተሰልፎ ሰብሰብ ብሎም መቆም አይችልም ብለው ማስጠንቀቂያ በመስጠት ህዝቡን በየእስር ቤቶ ካጎሩት በውሃላ መብትን በሰልፍ የመጠየቅ ነገር በዛ በይስሙላ ህገ መንግስት ላይ ብቻ ተወስኖ በሰልፍ መብትን የማስከበር መንፈስም በእጅጉ ተቀዛቅዞ ነበር።

እንደውም በአንድ ወቅት ወ/ሪት ብርቱካን ሚዴቅሳን ከእስር መፈታት አስመልክቶ ለተጠራው ሰልፍ መንግስት ከሁለት መቶ ሃምሳ ሰው በላይ መሰለፍ አይፈቀድም የሚል ብዙዎችን በግርምት ያስደመመ ተሰምቶ የማያውቅ የሰላማዊ ሰልፍ ፍቃድ አሰጣጥ ሂደትንም አስተውለን ነበር።

ምንም እንኳን በራሱ በወያኔ ህገ መንግስት የዜጎች ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት ቢደነገግም ያው እንደሚታወቀው ህገ መንግስቱን እንዳሻው የሚቀያይረውም ሆነ የሚተረጉመው ራሱ ወያኔ ስለሆነ ለበርካታ አመታት የዜጎች መብትን በሰልፍ የመጠየቅ ነገር የሚያሰቅል ወንጀል ሆኖ ቆይቶ ነገር ግን ከጥቂት ግዜያት ወዲህ በመጠኑም ቢሆን የመመለስ መንፈስ እያሳየ ይገኛል። እሱም ቢሆን ኑሮው ስለከበደ፣ ግፉ ስለበዛ ፣ ህዝቡም አሁንስ የመጣው ይምጣ በማለቱ እንጂ የወያኔ መንግስት ተሻሽሎ ወይም ለውጥ አሳይቶ አይደለም።

ለዚህ የሰላማዊ ሰልፍ መንፈስ መመለስ የሰማያዊ ፓርቲና የአንድነት ፓርቲ አመራሮችና አባላት የሚያስመሰግን ስራን ሰርተዋል። የተቀዛቀዘውን የህዝቡን መብትን የመጠየቅና የማስከበር መንፈስ በማነሳሳትና መብትን የመጠየቅ እሳቤ ክህዝቡ አእምሮ ውስጥ ዳግም እንዲንሰራራ አድርገዋል። እኛም በርቱ በዚህ ቀጥሉ እንላለን። በቅርብ ቀንም ሴት እህቶቻችን “የጣይቱ ልጆች” በተዘጋጀው የሩጫ ውድድር ላይ ወያኔን ያስደነገጠ ፣ የመብት ረገጣን በፅኑ የሚቃወም ፣ የህዝቡንም በመንግስት ባዶ ፕሮፓጋንዳ መሰላቸት የሚያሳይ ፣ መጠኑ ለሰፋው የኑሮ ውድነት የመንግስት የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ ምላሽ እንዲሁም ሌሎች በርካታ ወያኔያዊ ግፎችን በከፍተኛ መልኩ ተቃውመው አስመስጋኝና አርአያ ሊሆን የሚችል ተግባር ፈፅመዋል። የወያኔ መንግስትም እንደተለመደው ሰብስቦ እስር ቤት አጉሯቸዋል።

ሳራ ግርማ

ሳራ ግርማ

እዚህጋ ሁላችንም በአግባቡ ማስተዋል ያለብን ህዝብ መብቱን በሰላማዊ ሰልፍ ለማስከበር ሲጀምር በርካታ ችግሮች ማለትም እስር፣ እንግልት እንዲሁም ከዛም የከፋ ችግር በወያኔ መንግስት አማካኝነት እንደሚፈጠር ነው። ነገር ግን የመብት ጥያቄ ተመልሶ የዜጎች መብት እስኪከበር እንዲሁም በህዝብ የተመረጠ የህዝብ አገልጋይ መንግስት እስኪፈጠር ድረስ የመብት ማስከበር ትግሉ መቀጠል አለበት።

የወቅቱም የሃገራችን በሰላማዊ ሰልፍ መብትን የማስከበር መንፈስ መመለስና መነቃቃት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የፖለቲካ ፓርቲዎችና የፖለቲካ ሰዎች እንዲሁም የዜጎች መብት መከበር ዙሪያ የሚሰሩ አካላት የተጠናከረ አስተዋፅዖ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

ኢትዮጲያ ለዘላለም ትኑር !!

Speak Your Mind

*