ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ለሹመት ወደ ኢትዮጵያ ይመለሳሉ የምርጫ ቦርድን ወይም የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንን ይመራሉ ተብሎ ይጠበቃል

ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ መንግሥት ባደረገላቸው ጥሪ መሠረት ነገ ጠዋት 1:30 አዲስ አበባ ~ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ይደርሳሉ። ተወልደው ባደጉበት አዲስ አበባ ፈረንሳይ ሌጋሲዮን ሠፈር ለብርቱካን ደማቅ አቀባበል ለማድረግ ዝግጅቶች ተጠናቀዋል።

ሪፖርተር በዘገበው መሠረት ብርቱካን “በመንግሥት ጥሪ ወደ አገር ቤት ጠቅልለው ከተመለሱ ምናልባትም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር፣ ወይም የፌዴራል የመጀመርያ ወይም የከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ተደርገው ሊሾሙ እንደሚችሉ ከወዲሁ ትንበያዎች እየተሰሙ ነው” ብሏል።

ወ/ሪት ብርቱካን ወደ አዲስ አበባ ከመብረራቸው በፊት ለአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ በሰጡት አስተያየት “አገሪቱ ባለችበት ሁኔታ ለመርዳት ማንም ሰው የሚችለውን ነገር ለማድረግ ወደ ኋላ የሚልበት ጊዜ አለመሆኑን በመረዳት እኔም በበኩሌ ባለኝ አቅም፣ በሞያዬ፣ በልምድና በዕውቀቴ የምችለውን ለማዋጣት እና ያም ምን እንደሚሆን ለመወያየት ነው የምሄደው። በጣም ጥሩ ቀን ነው ለእኔ” ብለዋል።

ቪኦኤ ያነጋገራቸው የፌዴራሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ብርሃኑ ፀጋዬ “ወደ አገራቸው ተመልሰው በሕግም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ለአገሪቱም ለሕዝቡም ባላቸው ዕውቀትና ልምድ አስተዋጾ ማበርከት ፈልገው መምጣታቸው የሚያስመሰግናቸው ነው። … በአገሪቱ በሚካሄደው እንቅስቃሴ እንዲያግዙ እንፈልጋለን። አብረናቸው ለመስራትም ዝግጁ ነን” ብለዋል። እኛም አብረናቸው ለመስራት ዝግጁ ነን።”

ጎልጉል ያነጋገራቸው የዐቃቤ ሕግ መ/ቤት ባለሙያ ደግሞ ብርቱካን ለቪኦኤ ከሰጡት መግለጫ እና ከሌሎች ባለን መረጃ መሠረት የምርጫ ቦርድን ወይም የሰብዓዊ መብቶችን ኮሚሽንን ይመሩ ይሆናል የሚል ከፍተኛ ግምት አለ። የጠቅላይ ፍርቤት ፕሬዚዳንቷ ሴት በመሆናቸው በከፍተኛው ፍርድ ቤትም በከፍተኛ ኃላፊነት ሌላ ሴት ለመሾም የሚያስችል ክፍተት ቢኖርም ወ/ሪት ብርቱካን ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በሕግ ካለመሥራታቸው ጋር ተያይዞ ከሕግ ሥራ ለ13 ዓመታት ተለይተው በመቆየታቸው በፍርድ ቤት አካባቢ የመሾማቸውን ዕድል ያጠበዋል ይላሉ።

ሪፖርተር እንደ ዘገበው፤ “ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ1988 ዓ.ም. በሕግ ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያገኙት ወ/ሪት ብርቱካን፣ በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኛ በመሆንም ከ1989 ዓ.ም. እስከ 1990ዎቹ አጋማሽ ድረስ ከመሥራታቸውም በተጨማሪ፣ ለእስር እስከተዳረጉበት ጥቅምት ወር 1998 ዓ.ም. ድረስ ጠበቃና የሕግ አማካሪ ሆነው ሠርተዋል። … ወ/ሪት ብርቱካን ከእስር እንደተፈቱ ወደ አሜሪካ ሄደው ላለፉት ሰባት ዓመታት ቆይተዋል። በቆይታቸውም በታዋቂው ሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ በሕዝብ አስተዳደር ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ማግኘታቸው ታውቋል”።

(ፎቶዎቹ ከማኅበራዊ ሚዲያ የተገኙ ናቸው)

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ

Comments

  1. መልካም ዜና ለወ/ሮ ብርቱካን እንኳንም ደስ ኣሎት። አገራችን ጠንካራ መሪዎች የምትፈልግበት ጊዜ ነው። በጠማማ ትውልድ ውስጥ መልካም ሥነምግባርና መልካም መሪዎች አስተማሪዎች የሚያስፈልጉበት ጊዜ ነው። የዘረፋና በለቤት ኣልባ የነበረችውን ኢትዮጵያ በንፁህ ታታሪና ታማኝ ልጆችዋ ተመልሳ በመልካም መሠረት ላይ ትታነፃለች። ሌቦችና ወንበዴዎች የአገራችን ጣላት ሆነው ሲዘርፉና ሲያዘርፉ ቆይተው ተመልሰው ወደ ጫካ ተመልሰዋል ። ዛሬ የአገር አድን ጥሪ መመለስ የሚችሉት የመከራውን ገፈት የቀመሱት ለፍትህ ሲሉ ዋጋ የከፈሉት ዛሬ ሊካሱና የተገደሉለት ፍትህ በእግሩ እንዲሄድና ለምድራችን ተሰፋ እነዲሆን ታላቅ ምኞታችን ነው። የሰላም ፣ የፍትህ፣ የዲሞክራሲና የእኩልነት ድምፅ አሁንም ፍትህ ሙሉ በሙሉ እስኪሰፍን ድረስ ትግሉን በአገርና በውጭ ይቀጥላል ። ፍትህ ለመላው የኢትዮጵያና ለሰው ልጆች በሙሉ።

Speak Your Mind

*