የሰባት አመቷ ህፃን በፀሎት ብርሃኑ – ተሰርቃ፣ ተደፍራ በግፍ የተገደለች‼ ገዳዩ የማያዳግምና ሌላውን ሊያስተምር የሚችል እርምጃ እንዲወሰድበትም ነዋሪዎች ጠይቀዋል

ከጥቂት ቀናት በፊት በደሴ ከተማ አንድ የሰባት አመት ታዳጊ ለቀናት ከጠፋች በኋላ፤ ተገድላ መገኘቷን ተከትሎ የተቆጡ ነዋሪዎች የተቃውሞ ሰልፍ አድርገው ነበር። በወቅቱ ታዳጊዋ ከመገደሏ በፊት መደፈሯን ነዋሪዎች ተናግረዋል። በተያያዘ ታዳጊዋን አስገድዶ በመድፈር የተጠረጠረ ግለሰብ በቁጥጥር ስር መዋሉን የአማራ ቴሌቪዥን መዘገቡ ይታወቃል።

አሰቃቂ ወንጀል በሚፈጽሙ ግለሰቦች ላይ ቀደም ሲል የሚሰጠው የፍርድ ውሳኔ ተመጣጣኝ ባለመሆኑ በርካቶች ሌላ የወንጀል ድርጊት እንዲፈጽሙ እያደረገ ነው  ሲሉ የደሴ ከተማ ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ገለጹ።

በርካታ ቁጥር ያላቸው የደሴ ከተማዋ ነዋሪዎች የሰባት ዓመት ህጻን በአሰቃቂ ሁኔታ የገደለው ግለሰብ የማያዳግምና ሌላውን ሊያስተምር የሚችል እርምጃ እንዲወሰድበትም ትላንት በአደባባይ ጠይቀዋል።

የሟች ህጻን በጸሎት ብርሃኑ እናት ወይዘሮ አበባ ሙህዬ ልጃቸው ባለፈው ጥቅምት 24 ቀን 2011 ዓ.ም ለጨዋታ እንደወጣች ሳትመለስ መቅረቷን ይናገራሉ።

በልጃቸው ያልተለመደ መዘግየትና ወጥቶ መቀረት የተደናገጡት እናት ከአካባቢው ሰዎች ጋር በመሆን ፍለጋ ቢያካሂዱም ህጻኗ ሳትገኝ ቀርታለች።

ጥቅምት 27 ቀን 2011 ዓ.ም ህጻኗ በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድላ አስክሬኗ መገኘቱን የገለጹት ወይዘሮ አበባ በጥርጣሬ ከተያዙት ግለሰቦች ከአንዱ ጋር በትዳር አብረው የቆዩ መሆናቸውንና አንድ ልጅ ከወለዱለት በኋላ መፋታታቸውን ተናግረዋል።

ፍቺውን ተከትሎ ግለሰቡ ለመግደል በተደጋጋሚ ሲዝትባቸው መቆየቱን ነው የጠቆሙት።

ህጻኗ በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድላ አስክሬኗ መገኘቱ እንደተሰማ ትላንት በደሴ ከተማ አለመረጋጋት ተፈጥሮ የነበረ ሲሆን በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎችም ወንጀሉን በፈጸመው ሰው ላይ የማያዳግምና ሌላውን ሊያስተምር የሚችል ርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀዋል።

የደሴ ከተማ አስተዳደርና ጸጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ወንደሰን ጸጋዬ በበኩላቸው ድርጊቱ አሳዛኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የህጻኗ አስከሬን ከትናንት በስቲያ በምትኖርበት አካባቢ ከሚገኝ ጫካ በጆንያ ውስጥ ተጠቅልሎ መገኘቱን ተከትሎ ፖሊስ ባደረገው ክትትል ከጉዳዩ ጋር ግንኙት ይኖራቸዋል የተባሉ ሦስት ሰዎችን ፖሊስ በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገልጸዋል።

ዛሬ በደሴ ከተማ ተፈጥሮ የነበረው ውጥረት መረጋጋቱን ለመስማት ተችሏል።

ጎልጉል ከኢዜአ እና ከሌሎች የሚዲያ ውጤቶች ያቀናበረው።

Speak Your Mind

*