በአሜሪካ የንቦች ሞት ቁጥር ጨመረ

“ከፍተኛ ሃሳብና ጭንቀት” ምክንያት ነው ተብሏል

በአሜሪካ በብሔራዊ ደረጃ በተደረገ ምርምር የንቦች ቁጥር 40 በመቶ እንደሚቀንስ ተነገረ፡፡ ለንቦቹ መሞት ዋንኛ ምክንያት ንቦቹ በከፍተኛ ሃሳብና ጭንቀት ውስጥ መግባታቸው እንደሆነ ተመልክቷል፡፡

ሰኞ (ግንቦት 10/ሜይ 18) ዕለት የሜነሶታ የሕዝብ ሬዲዮ (Minnesota Public Radio News) እንደዘገበው በአሜሪካ ውስጥ በአጠቃላይ በተደረገው አዲስ ጥናት 6ሺህ ንብ አርቢዎች መጠይቅ የተደረገላቸው ሲሆን በዚህም መሠረት የሟች ንቦች ቁጥር በተለይ በበጋ ወራት እንደሚጨምር ተገልጾዋል፡፡ በተቃራኒው በክረምት ወራት ቁጥሩ በመጠነኛ ደረጃ እንደሚቀንስ ጥናቱ አመልክቷል፡፡ በአሜሪካ ከሚገኙት ጠቅላይ ግዛቶች በሰሜን በምትገኘው የሜነሶታ ግዛት የሟቾቹ ንቦች ቁጥር ከፍ እንደሚል ዘገባው ጨምሮ አስታውቋል፡፡

በሜሪላንድ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ የሆኑትና ጥናቱን የመሩት ዴኒስ ቫንኢንግልስድሮፕ እንደሚሉት ከሆነ ለንቦቹ መሞት አዲስ ምክንያት ከጥናቱ ለመመልከት መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡ እንደምክንያት የጠቀሱትም “ንቦቹ እጅግ ከፍተኛ በሆነ ሃሳብና ጭንቀት ውስጥ መግባታቸው” መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሆኖም የጭንቀቱ ምክንያት ምን እንደሆነ ለእርሳቸውም ግልጽ እንዳልሆነ እና ይልቁንም ጉዳዩ ተጨማሪ ጥናት የሚጠይቅ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በጥናቱ የተሳተፉት ንብ አርቢዎችም ለንቦቻቸው መሞት ምክንያት ይህ ነው የሚሉት ምክንያት እንደሌላቸው የገለጹ ሲሆን በበጋ ወራት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ንብ የሚሞትባቸው መሆኑን ለእነርሱም እንቆቅልሽ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የበጋው አኻዝ ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መምጣቱንና የዚህ ዓመቱም ከፍ እንዳለ በጥናቱ ተመልክቷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ለንቦቹ መሞት የተሰጠው መላምት የምግብ እጥረትና የተባይ መከላከያ ሊሆን ይችላል የሚል ነው፡፡ ሆኖም ግን የምግብ ዕጥረቱም ሆነ የተባይ መከላከያው በተለይ በበጋ ወራት ከሚጨምረው የንቦቹ መሞት ጋር እንዴት እንደሚዛመድ ተመራማሪዎቹ ሊረዱ አለመቻላቸውን የጥናቱ መሪ ዴኒስ መናገራቸውን ዜናው ዘግቧል፡፡

ይህ በአሜሪካ አገር የታየው የንቦች ሞት ጉዳይ በሌሎች የአውሮጳ፣ እስያና አፍሪካ አገራት የመኖሩ ጉዳይ በዘገባው ላይ ያልተመለከተ ሲሆን በተመራማሪዎቹ ዘንድ ጉዳዩ በዓለምአቀፍ ደረጃ መጠናት ያለበት ስለመሆኑም የተነገረ ነገር የለም፡፡


ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡

Speak Your Mind

*