“ባድመ የኛ አይደለም!” በረከት ስምዖን

በባድመ ጉዳይ የሰሞኑ የህወሓትና የደጋፊዎቹ የማደናገሪያ ጉንጭ አልፋ ሙግት ብዙዎችን ያሰገረመ ከመሆኑ አልፎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድን በፓርላማ በሚያስጠይቅ መልኩ የቀረበ ትዕይንት ሆኖ አልፏል። ራሱ ህወሓት በቆሰቆሰው እሣት የኢትዮጵያን ሕዝብ በ“ድንበር ተደፈረ” ማጭበርበሪያ ካስማገደ እና የፈንጂ ማምከኛ ካደረገ በኋላ አልጀርስ ላይ የአሸባሪና ወንበዴው ህወሓት መሪ በነበረው መለስ ዜናዊ አማካኝነት ባድመን ለኤርትራ አስረክቧል። ከዚያም አልፎ በሌላው ወንበዴ ስዩም መስፍን የኢትዮጵያን ሕዝብ በመዋሸትና ባድመ የእኛ ሆነች ብሎ በይፋ በመናገር አገር የመክዳት ወንጀል ፈጽሟል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ያኔ መለስ እንደፈለገ ይነዳው በነበረው ፓርላማ አማካኝነት ህግ አርቅቆ በነጋሪት ጋዜጣ አስወጥቶ ባድመን ለኤርትራ አስረክቧል። ከዚህ ሁሉ በኋላ ባድመን አስረክቡ ሲባሉ የህወሓት አሸባሪ ቡድን ወንበዴዎች “የአልጀርሱን ውሳኔ በመርህ ደረጃ ተቀብለናል ግን ድንበር አከላለል ላይ የሚሠሩ ሥራዎች አሉ” በማለት ለዓመታት ሲያደነቁሩን ቆዩ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ህወሓት እንደፈለገ ሲያምታታበት የኖረውን ጉዳይ በፊት ለፊት አውጥተው ለኤርትራ ውሳኔው ይተግበር ሲሉ የህወሓት ወንበዴዎችና በተቃዋሚ ስም የተሰየሙትን ጨምሮ ከዳር እስከ ዳር ተንጫጩ፤ ሰላማዊ ሰልፍ ወጡ፤ ኦህዴድን ወነጀሉ፤ ዓቢይንና አመራሩን አንጓጠጡ። የዘነጉት ነገር ቢኖር የህወሓት አሸባሪዎች ከመለስ ጀምሮ እስከ ስዩም እስከ በረከት ስምዖን ድረስ ባድመ ለኤርትራ የተሰጠች መሆኗን መመስከራቸው ነው።

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ ኦክቶበር 23፤ 2012 (ጥቅምት 13፤2005 ዓም) በረከት ስምዖን “ባድመ የኛ አይደለም!” በማለት የ“Eritrean Oppositions Arabic Paltalk” ለሚባል የፓልቶክ መወያያ ክፍል የተናገረውን ጠቅሰን ዘግበን ነበር። ወንበዴና አሸባሪው በረከት ይህንን ሲናገር በወቅቱ ሰልፍ አልተወጣበትም፣ በፓርላማ አልተጠየቀም፣ አልተወገዘም፣ አልተኮነነም። ይህ ማስረጃ በአሁኑ ወቅት ለሚቀርበው የባድመ ከንቱ ክርክር አጋዥ ማስረጃ ስለሚሰጥ ከዚህ በታች ደግመን አትመነዋል።


ኤርትራዊ ሆነው በኢትዮጵያ ከፍተኛ የስልጣን ሃላፊነት የተሸከሙት አቶ በረከት ስምዖን በኢትዮጵያ ላይ የሚፈርድ፣ ዜጎችን የሚያሸማቅቅ፣ ለአገራቸው የተሰውትን የሚያናንቅና በተለይም በውድ አገራቸው የሚመኩ ወገኖችን የሚያኮስስ ንግግር ማድረጋቸው በህወሃት ነባር ታጋዮች ዘንድ ቅሬታ ማስነሳቱ ታወቀ። አቶ ስዬ አብርሃ፣ አቶ ገብሩ አስራት፣ እነ አቶ ተወልደን በስም በመጥራት በኤርትራ ጉዳይ ላይ ጥፋተኛ ያደረጉት አቶ በረከት “አንድነትና አንድ አገር” የሻዕቢያ መዝሙር መሆኑን በመናገር ኢትዮጵያ ውስጥ መገንጠል ለሚፈልጉ ጊዜው ሲደርስ እንደ ኤርትራ መገንጠል መብታቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በሚኒስትር ማዕረግ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ በረከት ይህንን የተናገሩት Eritrean Oppositions Arabic Paltalk በሚሰኝ የኤርትራ ተቃዋሚዎች የፓልቶክ መወያያ ክፍል እንግዳ ሆነው ባካሄዱት የጥያቄና መልስ ነው።

ከአጀማመሩ የሻዕቢያ ውልድ እንደሆነ የተነገረለት ሕወሓት ሲመሠረት ምልመላውንም ሆነ አመራሩን የሻዕቢያ ሰዎች እንደተቆጣጠሩት ሲነገር የኖረ ነው፡፡ በተለይም “የሻዕቢያ ከፍተኛ አመራሮች ሙሴ ባራኪና የማነ ኪዳኔ (ጃማይካ) ሃላፊና መሪ ሆነው ወደ ትግራይ” እንደገቡና የሕወሓት ፕሮግራም “ኤርትራ የኢትዮጵያ አይደለችም፤ የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ናት፤ … ለኤርትራ መገንጠል ሙሉ ኃይላችንን እናውላለን፤ እስከመጨረሻውም ደማችንን እናፈሳለን…” በሚል አቋም ላይ እንዲሆን ማድረጋቸውን የወያኔ ታላቅ ሤራ ገጽ 49 ላይ ተገልጾዋል። ለዚህም ፕሮግራም አስፈጻሚነት ኤርትራውያኑ መለስ (ለገሠ) ዜናዊ፣ ዓባይ (አትክልት) ጸሐዬ፣ ሥዩም በርሄ … ተመልምለው የሻዕቢያን ፕሮፓጋንዳ በሚያስፋፉበት ወቅት አካሄዱ ትክክል አለመሆኑን በመቃወም አሠራሩ “በጠባብ ብሔረተኝነት ያስወቅሰናል … በኢትዮጵያ ሕዝብም ያስመታናል” በሚል ተቃውሞ በማስነሳት “ዓባይ ጸሐዬና መለስ ዜናዊ የሚሠሩት ትክክል አይደለም … በቶሎ በቁጥጥር ሥር ማዋል አለብን” በማለት የተንቀሳቀሱትን መምህር ዳዊት፣ አጽብሃ ዳኘው፣ ዕቁባግዚ በየነ፣ ሕንጻ ሽፈራው፣ ወርቅነህ ሐጎስ፣ በርሄ ጥማሎ፣ መንገሻ በላይ፣ ዓባይ ደግፈኒ፣ ሙሉጌታ አብርሃም፣ አልማዝ አስፋው፣ ኪዳኔ ግርማ፣ ሃዲሽ ዮሐንስ … (ሁሉም የትግራይ ተወላጆች) ባለራዕዩና ታላቁ መሪ መለስ ከዓባይ ጸሐዬና ስብሃት ነጋ ጋር በመሆን በሌሊት አሳፍነው በማስወሰድ ካስገደሉ በኋላ በቀጣይ ከሻዕቢያ ቀንደኛ አመራሮች ከነመሐመድ ረመዳንና ስብሐት ኤፍሬም ጋር በመሆን የሻዕቢያን ዓላማ እስከመጨረሻው ለማስፈጸም እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ትንቢታዊ በሆነ መልኩ በዚሁ ጽሑፍ ላይ ተገልጾ ነበር፡፡

አቶ በረከት ይህንን ታሪካዊ የወያኔና የሻዕቢያ ትስስር ባልካደ መልኩ ነበር ቃለምልልሱ ያደረጉት፡፡ “በኢትዮጵያ ቅኝ ግዢ ተይዘናል” በሚል “ነጻነት” እንደሚፈልጉ ወስነው በነበሩ የኤርትራ ተወላጆች ላይ የተወሰደው ወደ አገራቸው የመመለስ ሂደት ፍጹም ስህተት እንደሆነ የተናገሩት አቶ በረከት፣ በወቅቱ ለተወሰደው እርምጃ አቶ ስዬ አብርሃ፣ አቶ ገብሩ አስራትና እነ አቶ ተወልደን ተጠያቂ አድርገዋል። ስህተቱንም አንድ ወቅት የተደረገ፣ ካሁን በኋላ የማይደገም እንደሆነ ዋስትና ሰጥተዋል። አቶ በረከት የከሰሷቸው የተጠቀሱት የቀድሞ የሕወሓት ባለስልጣናት ሟቹን አቶ መለስን በአገር ክህደት የወነጀሉና ሻዕቢያ መደምሰስ አለበት በማለት ቁርጠኛ አቋም በመያዝ በድርጅታቸው የታገሉ እንደነበሩ በብዙዎች ዘንድ አይዘነጋም።

ኤርትራ “ቅኝ ግዢ በቃኝ” ካለች በኋላ አመራሮቿ በኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች የንግድ ዝርፊያ ሲያካሂዱ እንደ ነበር በስፋት የተወሳ ቢሆንም አቶ በረከት የሃሰት (ፎርጂድ) ዶላር በማተም፣ ቡናና ሰሊጥ “በኮንትሮባንድ” በማጋዝ ሲሰራ የነበረውን ሸፍጥ ጠቁመዋል። ኢትዮጵያ ላይ እንዲህ አይነቱ ሸፍጥ መሰራቱን ሲናገሩ ለምን የሻዕቢያ አመራሮችና ወኪሎቻቸው እንዳልተከለከሉ አላብራሩም። ይህ ህገወጥ ንግድ ለባድመ ወረራ ምክንያት መሆኑን ግን ጠቁመዋል። ከባድመ ወረራ ጀርባ የተለያዩ ችግሮች አንዳሉም አመላክተዋል።

“ባድመ መሬቱ የኢትዮጵያ እንዳልሆነ ይታወቃል” በማለት የሚያስተዳድሯትን አገር በክህደት ጅራፍ እየገረፉ መናገራቸውን በቁጭት የገለጹ አስተያየት ሰጪ “ልቤን ያደማኝ” በማለት የተናገሩት አቶ በረከት “በባድመ ጉዳይ ፍርድ ቤት እንሂድ ያልነው እኛ ነን” በማለት እንደ ትልቅ ጀብዱ መናገራቸውን ነው ይላሉ።

በወረራ ወቅት በተለይም በትምህርት ገበታቸው ላይ በነበሩት በአይደር ትምህርት ቤት ተማሪዎች ላይ በጠራራ ጸሃይ ቦንብ ላወረደባቸው ሻዕቢያ ተመጣጣኝ ምላሽ በመስጠት ጦርነቱ ተጠናቀቀ ሲባል፣ ወደ ፍርድ ቤት ለመሄድ የተስማሙትና መላው የትግራይ ሕዝብ “ተጎዲእና” ብሎ መሪር ሐዘኑ የገለጸላቸው ባለራዕዩ መሪ የፈጸሙት ክህደት ለሚያንገበግባቸው ክፍሎች አቶ በረከት ባድመን አስመልክቶ የሰጡት ምላሽ አንድ አገር ወክሎ ከሚናገር ሰው የሚጠበቅ አለመሆኑን ከአስተያየት ሰጪው ገለጻ ለመረዳት ተችሏል።

አቶ በረከት “ፍርድ ቤት ሄደን ተሸንፈናል። ውሳኔውን መቀበል ግዳጅ ነው። የኛ ያልሆነ መሬት ወደኛ እንዲመጣ አንፈልግም። መሬቱንም የመስጠት ችግር የለብንም…” ማለታቸውን ኢትዮጵያን የማኮሰስ፣ ህዝብን የመናቅ፣ ወረራውን ለመመከት የተሰውትን የኢትዮጵያ ልጆች ደም የሚረግጥ፣ በአንድነቱ የማይደራደረውን የትግራይን ህዝብ “ምን ታመጣለህ” በሚል አኮስሶ የመመልከት ያህል ተደርጎ መወሰዱን አኚሁ አስተያየት ሰጪ ተናግረዋል። አክለውም ወዳጆቻቸው የቀድሞ ታጋዮች በጉዳዩ ዙሪያ እየመከሩበት እንደሆነ አመልክተዋል። ከባድመ በፊት ሻዕቢያ ሊወገድ እንደሚችል አስታውቀዋል።

በስደት እንግሊዝ አገር የሚኖሩ አቶ ሰለሞን የተባሉ ኢትዮጵያዊ አቶ በረከት በህወሃት ሰዎች ዘንድ ቀድሞውንም ተቀባይነት እንደሌላቸው አስታውቀዋል። ንግግራቸው በቀድሞ ታጋዮች ዘንድ እሳት መጫሩንም አመልክተዋል። ሻዕቢያ የምንጊዜም የኢትዮጵያ፣ በተለይም የትግራይ ህዝብ ጠላት መሆኑን አምነው ከበረሃ ጀምሮ በዚሁ አቋማቸው የጸኑ ነባር ታጋዮች አቶ በረከት ላይ ዘመቻ መጀመራቸውን ጠቁመዋል፡፡ አቶ በረከት “የኤርትራን ተወላጆች ማባረር አግባብ አልነበረም” ሲሉ ጥርሳቸው ሳይቀር እየተነቀለ በረሃ የተወረወሩና በአሰብ ወደብ በኩል ያስገቡት ንብረት ተዘርፎባቸው በዜሮ ስለወጡ ወገኖች የተሰማቸውን ሃዘን አልገለጹም። አስተያየት ሰጪው አክለውም አንዳንድ ሚዲያዎች ከራሳቸው ድብቅ ፍላጎት አንጻር የአቶ በረከትን ቃለ ምልልስ በመቆንጠር በአማርኛ በመተርጎም ቅድሚያ መውሰዳቸውን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያዊያንን ከኤርትራ ማባረር የጀመረው ሻዕቢያ መሆኑን፣ ኢትዮጵያም በንዴት የኤርትራ ተወላጆችን ማባረሯን ያመለከቱት አቶ በረከት ሻዕቢያ ተው ሲባል አልሰማ ብሎ ወረራ ማካሄዱን አትተዋል። ከውጊያው በኋላ በፍርድ ቤት ውሳኔ መሰረት ድንበር ለማካለል ይቻል ዘንድ ለመነጋገር የቀረበለትን ጥያቄ ሻዕቢያ አልቀበልም ማለቱን፣ ድንበሩን ለማካለል ግን የግድ መነጋገር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የኢሳያስ መንግስት ተቃዋሚዎች ነው በተባለው የፓልቶክ ክፍል ቃለ ምልልስ ያደረጉት አቶ በረከት በኤርትራ የነጻነት ጥያቄው ምላሽ ቢያገኝም ያልተመለሱ፣ የታፈኑ፣ የጎሳና የቋንቋ ጥያቄዎች መኖራቸውን አመላክተዋል። በኤርትራ የመብት ጥያቄ ያነሱትን ክፍሎችንም እንደሚረዱ አስታውቀዋል። ይህ ማለት ግን “መገንጠልን በማበረታት” አይደለም ብለዋል።

መንግስት የሚረዳቸው በብሄርና በብሄራዊ ፓርቲ ደረጃ የተደራጁ የኤርትራ ተቃዋሚ ድርጅቶች ሻዕቢያን የሃይማኖት፣ የብሄር፣ የጎሳ፣ የቋንቋና የተለያዩ የዲሞክራሲ ጥያቄዎች በማንሳት በተለያየ መልኩ እየታገሉ መሆኑ ይታወቃል። አዲስ አበባ ላይ ተሰብስበው የስደት መንግስትም ማቋቋማቸው አይዘነጋም። በተለይም በርካታ ቁጥር ያላቸው ቆለኞችና “አሰብን ተነጥቄያለሁ” የሚለው የአፋር ንቅናቄ አቅሙ ከጎለበተ ለኤርትራ የወደፊቱ ፈተና ሊሆን እንደሚችል በተደጋጋሚ የሚገለጽ ጉዳይ ነው። አቶ መለስ በሻዕቢያና በኤርትራ ላይ ባላቸው ተለሳላሽነት እንጂ የኢትዮጵያ አፋሮች ትግል ሙሉ ድጋፍ ቢደረግለት ኤርትራ ለኢትዮጵያ ስጋት መሆኗ ተረት ሊሆን እንደሚችል ባለሙያዎች በተለያዩ ወቅቶች አስተያየት የሰጡበት ጉዳይ እንደነበር አይዘነጋም።

“የኤርትራ የውስጥ ችግሯ ይበታትናታል ወይም አንድ ያደርጋታል” ሲሉ ወደ ተቃዋሚዎች አጋድለው የደሰኮሩት አቶ በረከት፣ የኤርትራ የውስጥ ችግር አለመፈታቱን በማስረዳት ወደ ኦጋዴን ችግር ተዛውረዋል። የመገንጠል በሽታንና የብሄር ፖለቲካን ወደ ኤርትራ ስለመግፋታቸው ሲጠየቁ፣ የኦጋዴን ጉዳይም የተነሳባቸው አቶ በረከት “የኦጋዴን ህዝብ የመገንጠል ጥያቄ አላነሳም” ካሉ በኋላ እንደ ኤርትራ አብሮ መኖር የማይቻልበት ደረጃ ሲደረስ ሌሎችም ሊገነጠሉ ይችላሉ” የሚል መልስ ሰንዝረዋል። “የኤርትራ ተወላጆች አንድ ነን። ልዩነት የለንም፣ ‘አንድ አገር – አንድ ልብ’ የሚለው ዘፈን ግን የሻዕቢያ መንገድ ነው” ሲሉ መበታተንን ለኢትዮጵያ በሚመኝ መልኩ መልዕክታቸውን አስታላልፈዋል።

አቶ በረከት በተጠየቁበት ወቅት ከጥያቄ አቅራቢዎቹ መካከል የትግራይ ትግርኛ ተናጋሪዎች ይገኙበታል። አቶ በረከት በአረብኛ የቀረበላቸውን ጥያቄ በአስተርጓሚ የተቀበሉ ሲሆን በክፍሉ ውስጥ የረጅም ጊዜ ቆይታ አላደረጉም። በዩቲዩብ በተሰራጨው በዚሁ ቃለ ምልልስ ቅጂ አቶ በረከት መጀመሪያ ሰፊ ማብራሪያ አቅርበዋል። አቶ በረከት የወነጀሏቸው ሶስቱ የቀድሞ ባለስልጣናት ዜናውን አስመልክቶ መልስ ለመስጠት ከፈቀዱ ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ ለማስተናገድ ፈቃደኛ መሆኑን ይገልጻል።

የበረከትን ቃለምልልስ ለማዳመጥ እዚህ ላይ ይጫኑ።


ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ንብረት ናቸው። ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን።

Speak Your Mind

*