ሌላ አደገኛ የጦርነት አዋጅ በወገናችን ላይ ታወጀ!

በማህበረሰባችን መካከል ወልደህ ሳም የሚባል የተለመደ ምርቃን ነበር፤ ከአንደበት የሚወጣ ቃል ደግሞ በረከትን ወይም መርገምን ሊያስከትል እንደሚችል ይገመታል፤ በምድራችን ውስጥ ልጆች በጤና ተወልደው እንዲያድጉ ወላጆች የልጆቻቸውን የጤና ስጋት ለመቀነስ ሲሉ ገና ከእርግዝና በፊት ጀምሮ ገድል ከማሳዘልና እትፍ እትፍ ከሚሉ ሰዎች እስከ የቡና ስኒ ገልባጭ መናፍስት ጠሪዎች ድረስ በልጁ የማደግና የወደፊት የሕይወት እጣፋንታ ላይ ትንቢት መሰል ሟርት እያውጁበት እንዲያድግ ይደረጋል፤ በዚህ ሁሉ ግን ሁላችንም ምንም ዓይነት የጤና ድጋፍ በሌለበትና የመናፍስት ጠሪዎች ቁጥር በርካታ በሆነባት ምድር ውስጥ ተወልደን ማደጋችን ገብቶን በማወቅ ባናከብረውም የፈጣሪ ጥበቃና ምህረት እንደሆነ አምናለሁ።

ከዚህ ችግር ስፋትና ጥልቀት የተነሳ በርካታ ልጆች ተወልደው የማደግ እድል ሳያገኙ ከእናታቸው ጋር ሕይወታቸውን ያጡ ብዙ ናቸው፤ ሆኖም ግን ይህ ሁሉ ስጋት ታልፎ ተወልዶ፣ አድጎና ተምሮ ሃገር የሚረከብ ትውልድ በዘመናት ሁሉ ታጥቶ አለመታወቁ ምድርን ሙሏትና ግዟት የሚለው መለኮታዊ ትእዛዝ እስከ ፍጻሜው ድረስ የማያቋርጥ ለመሆኑ ምልክት ነው፤ ጥያቄ የሚሆነው ግን የዘመኑ ባላደራ ትውልድ ለተገኘበት ማህበረሰብ የሚበጅ ሥራ እያበረከተ ነውን? ወይስ ወላጆቹን በማስመረር ባልተወለድክ ወይም የወላድ መካን እያስባለ ነው? መልሱን ለአንባቢ ኀሊና ልተወው።

ይህ ጥያቄ ወደ እኔ አእምሮ የመጣው በድንገት አይደለም፤ ሁላችንም የተገኘንበት ማህበረሰብ በኑሮው እየደረሰበት ያለው መከራ ሳያንሰው ሰሞኑን መንፈሳዊ አስተማሪ የሆነው መምህር ምህረትአብ አሰፋ በፌስ ቡክና በዩቲዩብ የለቀቀው የጦርነት አዋጅ ነው፤ በመልካም አስተዳደር እጦት ለዘመናት እየተሰቃየ ባለ ሕዝብ ላይ ሌላ የሃይማኖት ጦርነት! ያውም ያገር እንደራሴ ሆና በቆየችው በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተወልደው ባደጉና ለሕዝቡ የፍቅር ምሳሌ ሊሆኑ በሚችሉ አገልጋዮች መካከል ሊፈጸም የታሰበ የወንድማማቾች የጦርነት አዋጅ! (እባክዎ የሚከተለውን ሊንክ በማስተዋል ይመልከቱና በመጽሐፍ ቅዱስ ይመዝኑት)

ለዚህ ነው በአንድ እጅ የፍቅር ምንጭ የሆነውን ወንጌለ ክርስቶስን፣ በሌላው እጅ ደግሞ ወንድምን ለመግደል የሚያስችል መሳሪያ አንግቦ በወገኖች መካከል የጦርነትን አዋጅ ለሚጎስሙ ለእነ ምህረተአብ አሰፋና መሰሎቹ በአውደ ምህረቱ ላይ እንደፈለጉ መፋነን የፈቀደች እናት ቤተ ክርስቲያናችንን እራሷን በእጇ ላይ ባለው መጽሐፍ ቅዱስ መዝና ወደ ቀደመ ማንነቷ ትመለስ/ትታደስ በማለት የምንጮኸው ይላሉ የዚችው ቤተ ክርስቲያን ካህናት፤ እዚህ ላይ እውነቱን ለይቶ የራስ ለማድረግ ግን የሁላችን ሃላፊነት መሆኑንና ሁሉንም ቆም ብለን በማስተዋል መዝነን የሚበጀንን መያዝ እንጂ በሃይማኖትና በባንዲራ ስም ለሚደረግ ጮኸት ሁሉ ሳይገባን ማጨብጨ የሌለብን።

እስቲ ተመልከቱ! ፍቅርና ጥል፣ ሐጢአትና ጽድቅ፣ ክርስቶስና ዲያብሎስ፣ ሞትና ሕይወት፣ ሥጋና መንፈስ፣ ጦርነትና የሰላም ወንጌል መቼ  ነው አብረው የሚሄዱት? ምናልባት ለምህረተአብ አዲስ ግኝት ወይም መገለጥ መስሎት ይሆን? ግን እኮ ሰይጣንም የብርሃን መልአክ መስሎ አይደል የሚመጣው? ስለዚህ ሁሉን መፈተን አምልጦ ማስመለጥ ስለሚሆን እናንተ ከእውነት የተወለዳችሁ ወገኖች በሙሉ እባካችሁ! ይህ የጠመጠመና መስቀል የጨበጠ ሁሉ እውነተኛ የመንፈስ አባት የሚመስለው የዋህ ወገናችን የጮሌዎች መጫዎቻ ሲሆን እያየን ዝም አንበል? የማህበረ ቅዱሳንና የተሐድሶ ጉዳይ ወደ አደባባይ ወጥቶና ሕዝብ በሙሉ አውቆት የራሱን ውሳኔ እንዲሰጥበት መድረኮች ይዘጋጁና ውይይት ይደረግበት፤ በውጭም በአገር ቤትም ያላችሁ የቤተ ክርስቲያኒቷ መሪ የሆናችሁ ጳጳሳትም ደግሞ እባካችሁ ዝምታውን ሰብራችሁ በመውጣት ይህ እግዚአብሔርን ፈልጎ ለማግኘ ከደብር ደብር በዚህ ጡንቸኛ ማህበር ስም የሚንከራተተው ምእመን እንዲያርፍና ከአሳራፊው ጋር እንዲገናኝ ሃላፊነታችሁን ተወጡ፤ እረፉ እኔም አምላክ እንደሆንኩ እወቁ ያለው ጌታ ቃሉን እንደ ሰው ለውጦ ከገዳም ገዳም ባዝኑ አላለምና።

በፖለቲካው መስክ የሚተራመሰው የህብረተሰብ ክፍል በዘር በሽታ ተልክፎ ለፖለቲካው ፍጆታ ሲል በዚህ አብሮ በኖረ ሕዝብ መካከል ይህን የዘር በሽታ መርዝ በማሰራጨቱ ምክንያት ወገናችን በሙሉ በማያባራ የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ገብቶ እየተሰቃየ ባለበት በዚህ ሁኔታ ላይ ይህን የመሰለ የሃይማኖት ጦርነት ማወጁ ለማን ጥቅም ነው? በእውነትስ የኦርቶዶክ ተዋህዶ ቤ/ክርስቲያን እውነተኛ ተቆርቋሪና ወዳጅ ማነው? ወዘተ ለመሳሰሉት ጥያቄዎች በመረጃ የተደገፈ መልስ ሁላችንም በመስጠትና ሚናችንን በመለየት ለሃገርና ለወገን ዘለቄታ ጥቅም በእውነት ለእውነት መነሳት አለብን እላለሁ፤ ሁላችንንም ሊበላ ያለ እሳት በዚህ መልኩ በየዋሁ ወገናችን መካከል ያውም በመንፈሳዊ አስተማሪዎች ነን ባዮች ሲጫር እያየን ቸል ልንለው አይገባምና በአለንበት አካባቢ ጉዳዩን አንስተን በመወያየት አቋም መውሰድ ይገባናል እላለሁ። እስቲ በዚህ ጉዳይ ላይ አቋም ከመውሰዳችን በፊት ማን? ማነው? ምንስ እየሠራ ነው? የሚሉትን ዋና ዋና ጥያቄዎች ለመመለስ የምህረትአብ አሰፋን ቡድን አስተምህሮና የተከሳሹን የተሃድሶን ወገን አስተምህሮ የሁለቱም መንፈሳዊ የክርስትና ትምህርት መሰረት ዋና መመሪያ በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ሚዛንነት አብረን እንየው፡

1/ ጦርነትን ያወጀው የምህረትአብና የመሰል ጓደኞቹ አስተምህሮ፡

 • እኛ ሃይማኖታችን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እንጂ ክርስቲያን አይደለንም፣ (ዩቲዩብ ላይ የምህረተአብ ትምህርትን ያዳምጡ)
 • የአዳም ሃይማኖት ኦርቶዶክስ ነበር ይላሉ፣
 • የአባታችን የአዳም አባት አፈር ስለሆነ አፈር አያታችን ነው፣
 • ስለዚህ ኦርቶዶክስ ቀጥተኛና እውነተኛ ሃይማኖት ስለሆነች ተሃድሶ ጨርሶ አያስፈልጋትም (ቃሉ ብቻ ይሰበክ=ተሃድሶ)
 • ልብሳችንን ለብሰው ተሃድሶ ብለው የተነሱት የአባቶቻችንን ሃይማኖት ለማጥፋት የተነሱ ናቸው ይላሉ (ቤተ ክርስቲያኒቱ ወልዳና አስተምራ ያሳደገችን ልጆቿ ስለሆን እንደ ፊተኛ ወገኖቻችን አኩርፈን ወይም እነ ምህረተአብ ባርከው ባልተረዳው ወገናችን እጅ የሚወርድብንን የድንጋይ በረዶ ፈርተን በመውጣት ወደ ሌላ ቤተ እምነት በመኮብለል እናት ቤተ ክርስቲያናችንን የወላድ መካን አናደርጋትምና የሚወጣው ይውጣ እንጂ እኛ አንወጣም፤ ልብሱና ቆቡም ቢሆን የምንወዳት እናታችን ያለበሰችን እንጂ እነምህረተአ ሲፈልጉ የሚቸሩን ካልፈለጉ ደግሞ የሚገፉን እርጥባን አይደለም ይላሉ ተሃድሶዎች) ወዘተ

2/ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ተሐድሶ ማህበር፡

 • ቤተ ክርስቲያናችን ከተመሰረተችበት የወንጌል ተልእኮ ወጥታለችና ወደ ቀደመ የወንጌል ቃል ትመለስ ይላሉ
 • የተሐድሶ ጥያቄ የቀደሙ የቤተ ክርስቲያኒቷ ሊቃውንትና መነኮሳት የጀመሩትና የሞቱለት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥያቄ እንጂ ዛሬ የተጀመረ ጉዳይ አለመሆኑን ይናገራሉ
 • ሕዝባችን ሊማርና ሊሰበከው የሚገባው ሕይወት፣ ፍቅርና ሰላም ሰጪ የሆነው የክርስቶስ ወንጌል ብቻ እንጂ መርገምን የሚያስከትል ልዩ ወንጌል መሆን የለበትም በማለት ይሟገታሉ፣
 • ቤተ ክስቲያኒቷ ከመናፍስት ጠሪዎችና ከልዩ ወንጌል ሰባኪዎች በቃሉ ብርሃን ትጽዳ፣
 • ቤተ ክርስቲያኒቷ ንጹህ ወንጌል ባለመስበኳ ምክንያት የቃሉ ራሃብተኛ የሆኑት በርካታ ልጆቿ ወደ ሌላ ቤተ እምነት በመኮብለል የወላድ መካን የሆነችበትን ችግር የተመለከተ አምላካችን በመንፈሱ ያመጣውንና በራሷ ልጆች ትከሻ ላይ የጣለውን ሰማያዊ አደራ እስከ ነፍስ ህቅታ ድረስ ዋጋ በመክፈል ቤ/ክርስቲያናችን የሚገሰጸውን እየገሰጸች የሚባረከውን ደግሞ እየባረከች በምድራችን ላይ የጽድቅ ተጽእኖ የምታመጣ ታማኝ የሰማይና ያገር እንደራሴ እንድትሆን ሳንታክት እንሠራለን ይላሉ፣
 • በምድሪቱ ውስጥ ያለው ሁለንተናዊ የሕይወት ችግራችን ምንጩ መንፈሳዊ ሕይወታችን ከእግዚአብሔር ህያው ቃል በመራቃችን ስለሆነ ክርስቲያናዊ ታሪካችን ከማንም ሃገርና ሕዝብ በፊት እጃችን በገባው መጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ይመዘን ይላሉ፣
 • የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እውነተኛ ወዳጅና ጠላት ማን እንደሆነ በሲኖዶሱ፣ በሊቃውንት ጉባኤውና በምእመኑ ፊት በግልጽነት ታውቆ ሁሉም አቋም እንዲኖረው ለማድረግ የሚያስችል መድረክ እንዲዘጋጅ ይፈልጋሉ፣
 • ባለው ሕግ መሰረት ፈቃድ አግኝተን ታሪክ የጣለብንን አደራ አሳድጎ ላስተማረን ወገናችን ለማበርከት በግልጽ በመንቀሳቀስ ላይ ሳለን የሥጋ ጉልበትና አቅም ያለው ሁሉ በተገኘው አጋጣሚ የበሬ ወለደ መርዝ በየዋህ ወገናችን መካከል በመርጨት ለጦርነት የማነሳሳቱን ኢሕጋዊ ሥራ መንግሥት ተከታትሎ ሕጋዊ እርምጃ ካልወሰደ አደጋው ለሁሉም ስለሚሆን የሰላም ሰዎች ሁሉ ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡት የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ በአጽንዖት ያሳስባል!!! (የሚከተለውን ሊንክ ለመረጃ ይመልከቱ፡)

ጥብቅ ማሳሰቢያ

ይህን ጽሑፍ የምታነቡ ወገኖች እባካችሁ ለዚህ እውነተኛ መነፈሳዊ መሪና አስተማሪ ለሌለውና በአስመሳዮች ትክሻው ለጎበጠው ሕዝባችን መትረፍና ማረፍ ለእውነት በእውነት በዚህ ጉዳይ ላይ ላልሰማ እያሰማን በጋራ እንነሳ???

የእውነት አምላክ የሆነው እግዚአብሔር ሃገራችንን/ሕዝባችንን ይጠብቅ

እውነቱ ይነገር:  eunethiwot@gmail.com

ከዝግጅት ክፍሉ፣ ይህ ጽሁፍ ሃይማኖታዊ ይዘት ያለውና የግለሰብን ስም የሚጠቅስ በመሆኑ ጎልጉል የየትኛውንም ወገን የሚደግፍ ወይም የሚቃወም አለመሆኑ እንዲታወቅ ይሁን። በጠየቅነው መሠረት የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ይህንን ጽሁፋቸውን ለመምህር ምህረተአብ በፌስቡክ ገጻቸው በኩል መላካቸውን ለጎልጉል አረጋግጠዋል። መምህር ምህረተአብ ለዚህ ጽሁፍ ምላሽ ካላቸው የምናስተናግድ መሆኑን እንገልጻለን።


“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡

Comments

 1. Tazabiw says:

  የአርዮስ ፍሬዎች
  መልስ
  “ለሌላ አደገኛ የጦርነት አዋጅ በወገናችን ላይ ታወጀ”

  ይህንን ጽሁፍ ለመጻፍ ያነሳሳኝ በጎልጉል ድረገጽ ላይ እራሳቸውን ተሃድሶ ብለው በሚጠሩ ነገር ግን እውነተኛ ማንነታቸው ለሰወሩት ወይንም በማንነታቸው ለሚያፍሩት ፣ የምንፍቅና አቀንቃኞች መልስ ይሆን ዘንድ ነው ። በመምህር ምህረተአብ ላይ ላቀረቡት ትችት ከሞላ ጎደል መልስ ይሆናቸዋል ብዬ አምናለሁ ።

  ጸሃፊው ፤ አቤቱታውን ሲያሰማ እንዲህ ይላል ፤ ተወልደን ባደግንበት ኦርቶዶክስ በቴ ክርስትያን “የፍቅር ምሳሌ ሊሆኑ በሚችሉ አገልጋዮች ላይ የጦርነት አዋጅ ታወጀብን” ተወልደን ያደግንበት ከማለት ፤ ተዘርተን የበቀልንበት ቢል ማንነቱን ይበልጥ ይገልጸዋል ብዬ አምናለሁ ። የመወለድና የመዘራት ትርጉሙ ካልገባቸው ለማለት ነው ። ሲጀመር ይህች ቤተ ክርስቲያን ባጎረሰች የተነከሰች ለመሆኗ ጸሃፊው እራሱ ይክደዋል ብዬ አላምንም ። የሉተር ፍልፍሎችና ቅፍቅፎች ፤ እንዲሁም የመለስ ዜናዊና ስብሃት ነጋ በመባል የሚታወቅ ዘላንና ሰካራም ወያኔ በለስ ቀንቶአቸው ኢትዮጵያን ከተቆጣተሩበት ጊዜ ጀምሮ አማራንና ኦርቶዶክስን አከርካሪውን ሰበርነው ፤ እያሉ ያወጁትንና የፎከሩበትን ተግባራዊ ለማድረግ ምኞታቸውን ከግብ ለማድረስ የሰሩት የስራ ውጤት ነው ። ምንም እንኳን ቢማርና ቢያውቅም ሆዱ ጭንቅላት የሆነበት አለማዊ ንዋይና ዝና ያሰከረውን ሟቹን አባ ዲያቢሎስን በቤተ ክህነት አናት ላይ አስቀምጠው አገር ማፍረስ ብቻ ሳይሆን አምነታችንንም ከስር መንግሎ ለመጣል እራሳቸውን ተሃድሶ ብለው በሚጠሩ አፍቅሮተ ንዋይ ያሸነፋቸውንና ሆድ አደር ወፍ ዘራሾችን በማሰባሰብና በማደራጀት ከምን ግዜውም በላይ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ላይ እንደተነሳሱ ይስተዋላል ።

  የምእራባውያን ንዋይ በገፍ በሚፈስላቸው ፤ የበግ ለምድ የለበሱ አሳዊ መሲሆች ፤ መጽሃፍ ቅዱስን በመሰረዝ ፤ በመደለዝ ፤ የሌለ በመጨመር ፤ ቀላል አማርኛ በሚል ቅጥ አንባሩ በጠፋ መጽሃፍ ቅዱስ ተብዬ በማወናበድ ፤ አዲሱን ትውልድ በየመድረኩ በሚወራጩ ፤ በሚደንሱ ፤ በሚንፈራገጡ ፤ ትያትረኞች ትርጉም የለሽ የአጋንንት ልሳን ትርኪ ምርኪ እየዘላበዱ ብዙዎችን ይዘው እንደጠፉ ቢታመንም ፤ “የፈሲታ ተቆጢታ” ሲሆኑ ግን ሊነገራቸው ይገባል ።

  ሲጀምር ቀና የሚያደርግ መንፈስ ቅዱስ እንጂ በየመድረኩ የሚዘርርና አረፋ የሚያስደፍቅ መንፈስ የጨለማው መንፈስ ካልሆነ ሌላ ሊሆን አይችልም ። ልሳኑም ቢሆን የሻምፓራራ ድግግሞሽ እራሱ ተናጋሪው የተናገረውን የማያውቀው ፤ የማይሰማ ፤ የማይተረጎም ፤ ቢተረጎመምም በየጊዜው አንድ የተለመደ ቃል እየቀባጠሩ ዛሬ የሚተረጉመው ሌላ ፤ ነገ የሚተረጉመው ሌላ ፤ ስለሆነ ምንጩ ማን እንደሆነ ሳይታለም የተፈታ የልጆች ጨዋታ ስለሆነ በግድ እኛን ካልመሰላችሁ ካልወረዳችሁ ብሎ ሙግት አብረን እንውደቅ ካልሆነ በቀር ሌላ ምንም ሊሆን ስለማይችል እዚያው በጸበላችሁ ።

  በመጨመር የኦርቶዶክስ ተዋህዶ አባቶች ባሉበት ለመከራከርም ጥያቄ ያነሳል ጸሃፊው ፣ በውነት እነዚህ አዋቂ ነን ባዮች የያዙትን ወንጌል በርግጥ አንብበውት ያውቃሉ? አይመስለኝም! ከሆነ ግን እምነት ለመከራከሪያ እንዳልሆነ ተጽፏል የተጻፈን እንኳን አንብቦ መረዳት የተሳናቸው ፤ የዞረባቸው እንደሆነ ከጽሁፉ በቀላሉ መረዳት ይቻላል ። ብታምን ታምናለህ ፣ ባታምን ወደመሰለህ ትሄዳለህ እንጂ ካንተ ጋር ተቀምጦ የሚከራከር የሚሟገት አይኖርም ። እምነት መከራከሪያ አለመሆኑን ስታውቁ ፤ ያኔ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ትክክለኛ እምነት እንደሆነች ትማራላችሁ ብዬ አምናለሁ ።

  ጸሃፊውም ሆነ መሰሎቹ አንድ ሊያውቁት የሚገባ ነገር ቢኖር ኢትዮጵያ መላው ዓለም በተለይም የመናፍቃኑ መሪዎችና አቀንቃኝ የሆኑት ምዕራባውያኑ ድንጋይ እየቀረጹና እንጨት እየፈለጡ በሺ የሚቆጠሩ ጣኦታትን በሚያመልኩበት ዘመን ኢትዮጵያ አንድ አምላክ ብላ በስነ ልቦና ፈጣሪን የተቀበለች ፤ ከዚያም በኦሪት ዘመን ብሉይ ኪዳንን የተቀበለች ፤ ከጌታችን ከመድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ በኋላም አዲስ ኪዳንን በመቀበል በትክክለኛው እምነትና መንገድ ጸንታ የኖረች ወደፊትም እስከ ምፅዓት በዚሁ በጸናው እምነቷ ጸንታ እንደምትኖር እነ ፍራሽ አዳሽ ሳይሆኑ ዓለም የሚመሰክርላት እና ሊያውቀው የሚገባ የማይታበል ሃቅ ነው ። የመናፍቁ አባትና መሪ እንኳን ከክህደቱ በፊት ለ 1,500 ዓመታት ኦርቶዶክስ ስታስተምረው እንደቆየችና በማናቸውም ነገር እንደምትቀድመው ፤ እንደምትበልጠው እንዴት ሊሰወርባቸው እንደቻለ ግልጽ አይደለም ። ዛሬ ዛሬ “ከኋላ የመጣ አይን አወጣ” ወይንም “ምጥ ለናቷ አስተማረች” ሆነና ውሃው ሽቅብ ካልፈሰስኩ ብሎ ይሞግታል ።

  ሌላው የቤት ክህንትን ልብሰ ተክህኖን መዝረፍን በተመለከተ ይሆናል ። ይህም ምንም ከእውነት የራቀ አይደለም ፤ እርግጥ የቤተ ክህነትን ልብሰ ተክህኖና የቀሳውስቱን አለባበስ ይሄው አራሱን ተሃድሶ ብሎ የሚጠራው የጴንጤው አቀንቃኝ አለአግባብ ሲጠቀሙበት ይስተዋላል ። ከመደበኛው ጴንጤ ምንም የሚለያቸው ነገር ሳይኖር ለምን እራሳቸውንም ኦርቶዶክስ ብለው እንደሚጠሩ ከማንም የተሰወረ ባይሆንም ዋና አላማው ምዕመኑን ለማሳሳትና ለማወናበድ ቀላል ዘዴ ሆኖ ስለተገኘ ነው ። ስብከታቸውም ሆነ እምነታቸው እንዳለ የጴንጤው እንደሆነና ውሎና አዳራቸውም ከነሱ ፓስተሮችና ተከታዮቻቸው ጋር እንደሆነ ያደባባይ ሚስጥር ነው ። አለባበሳቸውንም እንደ መሰል ፓስተር ጓዶቻቸው ሱፍና ከረባት እንዳይለብሱ የኦርቶዶክን ቆብና ቀሚስ ያስፈለገበት አብዩ ምክንያት አሳቹ ተኩላ በግ መስሎ መምጣቱ የግድ ስለሆነ ነው ። አላማውን ለመገንዘብ እምብዛም ምርምር አያሻም ። በማናቸውም መንገድ ኦርቶዶክስ ተዋህዶን አስመስሎ መቅረቡ ተቀባይነትን ሊያስገኝላቸው ስለሚችል የተኩላው መመሳሰል ግድ ይላል ። እሱ ብቻም ሳይሆን ተኩላው አስመስሎ ሊመጣና ብዙዎችን እንደሚያስት የተነገረውም ትንቢት ይፈጸው ዘንድ የግድ ነውና ።

  ተኩላው በሚገርም ሁኔታ የጌታችን የመድሃኒታችን እናት የሆነችውን የድንግል ማርያምን ምስል ከሚሰበሰቡበት መጋዘን ከሰባኪያቸው ጀርባ ለምዕመናን በግላጭ እንዲታይ አድርጎ ማስቀመጥ አንዱ የማሳቻ ዘዴያቸው ሲሆን ፤ እዚህ ላይ ማስተዋል ያለብን ነገር ቢኖር ግን ስዕሏን ያስቀምጡ እንጂ ስለእመቤታችን ድንግል ማርያም በድንግልና መውለድና ፤ በድንግልና ለዘለዓለም የጸናች መሆኗን ፤ አማላጃችን መሆኗን ፤ የማይተነፍሱ ነገር ግን ስዕሏን አላግባብ በማስቀመጥ ፤ የዋሃንን ለማሳት ፤ አይነተኛ ዘዴ አድርገው ሲጠቀሙበት ይታያል ። ከዚህ ቀደም እንደምናውቃቸው መናፍቃን በግላጭ ድንግልን ፤ መላይክትንና ጻድቃንን ከመስደብ ተቆጥበው ዋና ጨዋታ አድርገው የያዙት ፤ ጭራሽ ስማቸውን ባለማንሳት ምስላቸውን ብቻ እያሳዩ ኦርቶዶክሳዊ መስሎ በመቅረብ ፤ ገድላቸውን በማዳፈን ፤ አማላጅነታቸውን ባለመመስከር ፤ የማስረሳትና የማዘናጋት ጨዋታ እየተጫወቱ እንደሆነ ለብዙሃኑ አስተዋይ እና ብሩህ አይምሮ ላለው ኢትዮጵያዊ የማይሰራ ተራ የመንደር ትያትር እየተገበሩ እንደሆነ ነጋሪ ቢያገኙና ቢነገራቸው አካሄዳቸውን ለማስተካከል ይረዳቸው ይሆናል ።

  በጣም አሳዛኙ ተግባራቸው ግን እየገረፉ ለምን እንደሚያለቃቅሱ ሊገባኝ አልቻለም ። እንደሚታወቀው ተሃድሶ ተባለ ጴንጤ ያንድ ሳንቲም ሁለት ገጾች እንደሆኑ ጸሃፊው እራሱ እንደማይክደው አምናለሁ ። ታዲያ ለምን ኦርቶዶክስ ተዋህዶን መስሎ መቅረብ አስፈለገ? ሁለተኛ መቼም አንድ ሰው ወይንም ቡድን በማይመስለው እምነት አዳራሽ ገብቶ የራሱን የእምነት አመለካከት እንዲሰብክ በማናቸውም የእምነት ተቋም እንደማይፈቀድ የማያውቅ ይኖራል ብዬ አልገምትም ። ታዲያ የኛ ፍራሽ አዳሾች ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤት ምን ይሰራሉ? ድርሽ እንዳይሉ ተከልክለውም ከሆነ አግባብ ነው እላለሁ ። በሶስተኛ ደረጃ ይሄው የበግ ለምድ ለባሽ ለምን በየጴንጤው መጋዘን ይሰብካል? ተጋባዥ እንግዳ ሆኖ ይቀርባል? ለምንስ መደበኛው ጴንጤ ተሃድሶ ተብዬውን ሊያጠናክረው የገንዘንና የቁሳቁስ እርዳታ ያደርግለታል? ይሄንን እውነታ ፈጥሬ ሳይሆን በትንሹ አኔ በማውቀው ቅዳሜ ቅዳሜ (8:00AM to 11AM eastern US standard time) በምስራቃዊ አሜሪካ ሰዓት አቆጣጠር ጠኋት ስምንት ሰዓት ላይ የጀመረ አስከረፋዱ አስራ አንድ ስዓት ድረስ (Ethiopian christian plus all) በሚባል የጴንጤዎች የፓል ቶክ ክፍል ውስጥ ፕሮግራም ተይዞላቸው ኦርቶዶክስን ሲሰድቡና ሲያሰድቡ ፤ ድንግልንም ሆነ መላይክትን እንዲሁም ጻድቃንን ሲያንጓጥጡ እንደሚውሉ ማንም ኢትዮጵያዊ የሆነ እዚህ የመናፍቃን የፓል ቶክ ክፍል በመምጣት የፍራሽ አዳሹን እውነተኛ ማንንነት ማወቅ ይችላል ።

  ታዲያ ይህ ሁሉ እውነታ ስለናንተ እየታወቀና እያለ ሁለት ቦታ መረጋገጡ ምን ለማምጣት ነው እነ ተሃድሶ? እስቲ ጥያቄያችሁን በጥያቄ ልቅረበው ። ለምን ሁሉ አማረሽ ሆናችሁ? ስለምንስ አንድ ቦታ መርጋት አቃታችሁ? ስለምንስ የኦርቶዶክስን ስም መዋስ አስፈለጋችሁ? እውነተኛ ማንነታችሁን የማያውቅ ያለ ይመስላችሁ ይሆን? ከሆነ በርግጥ በጣም የዋሆች ናችሁ ።

  አምነት የመዳን ጉዳይ እንጂ ፣ የቲፎዞ ወይንም የደጋፊ መብዛት ጉዳይ ከመሰላችሁ እጅግ በጣም ተሳስታችኋል ። መንግስተ ሰማይ በቲፎዞ ብዛት ሳይሆን የምትወረሰው በእምነትና በተግባር አንደሆነ የያዛችሁትን ወንጌል መመርመር ያሻል ። ስለሆነ በየጴንጤው መጋዘን ደጋፊ ፍለጋ መንጦዝጦዝና ደጅ መጥናት የመንግስተ ሰማይን ደጃፍ አያስከፍትም ምድራዊ አንቱታን ከሆነ ይቻል ይሆናል ያውም የከንቱ አንቱታ ።

  ታዛቢው

  መቼም ይህ ድረገጽ በዚህ አቋሙ በመጽናት የኔንም አስተያየት ለንባብ ያበቃልኝል ብዬ አምናለሁ ።

  ከዝግጅት ክፍሉ፣ ይህ ጽሁፍ ሃይማኖታዊ ይዘት ያለውና የግለሰብን ስም የሚጠቅስ በመሆኑ ጎልጉል የየትኛውንም ወገን የሚደግፍ ወይም የሚቃወም አለመሆኑ እንዲታወቅ ይሁን። በጠየቅነው መሠረት የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ይህንን ጽሁፋቸውን ለመምህር ምህረተአብ በፌስቡክ ገጻቸው በኩል መላካቸውን ለጎልጉል አረጋግጠዋል። መምህር ምህረተአብ ለዚህ ጽሁፍ ምላሽ ካላቸው የምናስተናግድ መሆኑን እንገልጻለን ።

 2. በለው! says:

  »> አርዕስቱና ትንታኔው የነገሩ ጭብጥ ተበታተነ!
  “በመልካም አስተዳደር እጦት ለዘመናት እየተሰቃየ ባለ ሕዝብ ላይ ሌላ የሃይማኖት ጦርነት! ያ አዳሜ በሰይጣን ኮከብ በሃይማኖት ነጻነት እንዲህ እየተቆላህ!?
  https://youtu.be/tJc80tgJnBg
  “እስቲ ተመልከቱ! ፍቅርና ጥል፣ ሐጢአትና ጽድቅ፣ ክርስቶስና ዲያብሎስ፣ ሞትና ሕይወት፣ ሥጋና መንፈስ፣ ጦርነትና የሰላም ወንጌል መቼ ነው አብረው የሚሄዱት? ምናልባት ለምህረተአብ አዲስ ግኝት ወይም መገለጥ መስሎት ይሆን? ግን እኮ ሰይጣንም የብርሃን መልአክ መስሎ አይደል የሚመጣው?
  ‘ጥብቅ ማሳሰቢያ
  “ይህን ጽሑፍ የምታነቡ ወገኖች እባካችሁ ለዚህ እውነተኛ መነፈሳዊ መሪና አስተማሪ ለሌለውና በአስመሳዮች ትክሻው ለጎበጠው ሕዝባችን መትረፍና ማረፍ ለእውነት በእውነት በዚህ ጉዳይ ላይ ላልሰማ እያሰማን በጋራ እንነሳ???
  የእውነት አምላክ የሆነው እግዚአብሔር ሃገራችንን/ሕዝባችንን ይጠብቅ። አሜን!

  • አንተነህ ጌትነት ሙላቱ says:

   ጎልጉሎች በተደጋጋሜ የኦርቶዶክስ ተዋህዶን የሚያረክስ ጽሁፍ ለምን እንደምታወጡ አይገባኝም?ይህ የሚያሳየው ሙሉ ለሙሉ ፀረ-ኦርቶዶክስ መሆናችሁን ነው።ለምን?ከዚህ በፊት በመረጃ ስለ ግንቦት7 እና ኢሳት ሰዎች በስም በመጥቀስ ስልክላችሁ የግለሰቦችን ስም ማውጣ ትክክል እንዳልሆነ በመግለፅ የላኩላችሁን ጽሁፎች ውድቅ ማድረጋችሁ የማትክዱት ነው።ዛሬ ግን በዲያቆን ምርእተአብ ላይ ፀያፍ አባባሎች እንደወረደ ስታቀርቡ በውጭ የምትኖሮ ጋዜጠኛ ተብየዎች ህሊና የሚባል ነገር እንዳልፈጠረባችሁ ይህ ተጨባጭ መረጃ ነው።እንዲህ ያለ ነግር ተልኮ ያለው “ከእናት ጡት ነካሾች” የሚጠበቅ በመሆኑ የሚገርመን አይደለም።

   • Editor says:

    አንተነህ ጌትነት ሙላቱ

    “አትንኩኝ ባይነት” ካልሆነ በስተቀር ስለ ጎልጉል የጻፉት የተሳሳተ ሃሳብ ነው። “ጸረ-ኦርቶዶክስ” የሚለው አባባልዎ ቢያንስ በየጊዜው እየተላከልን የምናትመውን የቀሲስ አስተርአየን እና የወንድሙ መኰንን ጽሁፍ ያላነበቡ መሆንዎን ነው።

    በጽህፉ ላይ ስለ መምህር ምህረተአብ የሠፈረ ምንም “ጸያፍ” ቃል አላገኘንም። ሌላው ጸሃፊው ይህንን ጽሁፋቸውን ለመምህር ምህረተአብ ልከውላቸው እንዲደርሳቸው ተደርጓል። ከዚህ በተጨማሪ ይህንን ብለናል:

    ከዝግጅት ክፍሉ፣ ይህ ጽሁፍ ሃይማኖታዊ ይዘት ያለውና የግለሰብን ስም የሚጠቅስ በመሆኑ ጎልጉል የየትኛውንም ወገን የሚደግፍ ወይም የሚቃወም አለመሆኑ እንዲታወቅ ይሁን። በጠየቅነው መሠረት የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ይህንን ጽሁፋቸውን ለመምህር ምህረተአብ በፌስቡክ ገጻቸው በኩል መላካቸውን ለጎልጉል አረጋግጠዋል። መምህር ምህረተአብ ለዚህ ጽሁፍ ምላሽ ካላቸው የምናስተናግድ መሆኑን እንገልጻለን።

    ከዚህ ሌላ እርስዎ ስለጠቀሱት ጽሁፍ አሁን የምናስታውሰው ባይኖርም የግለሰቦች ስም እየተዘለፈ ወይም እየተከሰሰ የሚጻፍ ጽሁፍን አናትምም። ነገር ግን የሰዎችን ርዕዮት (አስተሳሰብ) ትክክል አይደለም በማለት ሃሳባቸውን በጨዋነት የሚገልጹ ጽሁፎችን እንደ አጻጻፋቸውና ሃሳብ አገላለጻቸው እየገመገምን እናትማለን። የተጻፈባቸው ሰዎች ፅሁፉን የሚያነቡበትንና ከቻሉም ምላሽ የሚሰጡበትን መንገድ እናመቻቻለን። ለዚህ ደግሞ ሥራችን ምሥክር ነውና ሌላ ምስክር ወይም ዋስትና አንፈልግም።

    መርሳት የሌለብዎ ይህ በነጻ ለሕዝባችን የምንሠጠው አገልግሎት ነው እንጂ ተቀጥረን በትዕዛዝ የምንሠራው አይደለም።

    አሁንም ጽሁፍ ካለዎት ያቅርቡ – ሃሳብን በሃሳብ ይሞግቱ። የሰውን ስብዕና ሳይነካ ሃሳብን አብጠጥሮ መቃወምን በጣም እንደግፋለን።

    ከሰላምታ ጋር

    የጎልጉል አርታኢ

 3. እውነት says:

  አጨር ቃል ተሐድሶ የሚባል ነገር የለም መናፍቃን ናቸው። ሰርገው የገቡ የተደበቁ መናፍቃን። ይህንንም ወያኔ ውስጥ ያሉ መናፍቃን ጠቅላይ ሚኒስትር ተብዬ እና ሌሎቹም መናፍቃን የሚደግፉት በጎጥ ምክንያትም በቤተክህንት ያሉ ጳጳሳት የሆኑና ለዚሁ ስራ ሰርገው የገቡ የቤተክህንት ሰራተኞች የሚደግፉት ኢትዮጵያን እና የ ኦርቶዶክስ እምነትን ለማዳከም የታቀና እየተሰራ ያለ የመናፍቃን እንቅስቃሴ ነው። መ. ምህረተ አብያወጀው ቤተክርስቲያን ማወጅ የነበረባትን ነው። የፈለጋችሁተን እዛው ውጡና አምልኩ። እኛ የምናመልከውን እናውቀዋለን። ድንግል ማርያም ቅዱሳን መላእክት አማላጆች ናቸው። ስለ እነርሱም ይሰበካል። እኛ በተሰቀለው አምላክ በሆነው በሚፈርደው አማላጅ ባልሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን። እናንተ በሃሳዊ መሲህ እመኑ።

 4. የሥጋ ወንድሞቼ፡

  1) ታዛቢው፣
  2) በለው፣
  3) አንተነህና
  4) እውነት

  ምነው ”የምጣዱ ቀርቶ የእንቅቡ ተንጣጣ” እንደሚባለው የጦርነቱን አዋጅ በየዋሁ ወገናችን መካከል በይፋ ያወጀው መምህር ምህረታብ ደብዳቤው በፌስቡክ ደርሶት አንዳች ነገር ትንፍሽ ሳይል እናንተ ያልተወከላችሁ ጠበቆች ብቻ መድረኩን የቅቤ ገበያ አስመሰላችሁት?

  እስቲ ለራሳችሁ ላልተበከለ ህሊና የሚከተሉትን ጥያቄዎች በፍቅር ላቅርብላችሁ፡

  1) ይህን በወገናችን ላይ በመረጃ የተደገፈ የጦርነት አዋጅ ስትደግፉ በኦሮሞና በአማራ ላይ የተደረገውንና እየተደረገ ያለውን ጦርነት መቃዎም የምትችሉበት ሌላ ተለዋጭ ህሊና አላችሁ ማለት ነው? ወይስ የጠመጠመና መስቀል የያዘ ሰው ካወጀው ዓይናችሁን ጨፍናችሁ ቢሆን አሜን በሉ ነው የምትሉን? ይህን ደግሞ እግዜር እራሱ ቃሉን ባስተላለፈልን በመጽሐፍ ቅዱስ ዮሐ 13፡17 በማወቅና በማድረግ እንድንከተለው በመንፈሱ ስላስተማረን ለእኛ ጨርሶ አይመቸንም፤

  2) ወንጌለ ክርስቶስ፡
  ”በመንፈሴ እንጂ በኃይልና በብርታት አይደለም”/ዘካ 4:6/፣ ”ሰይፍ የሚያነሱ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉና ሰይፍህን ወደ ስፍራው መልስ” /ማቴ 26፡52/ እና ”ሰላምን እተውላችኋለሁ፣ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም”/የሐ 14፡27/ የሜል የፍቅርና የሰላም ወንጌል ሆኖ ሳለ ሰውንና ቅርስን የሚበላ ጦርነትን ማወጅና መደገፍ ከየት ተማራችሁት? ምናልባት ታዛቢው በስም አባ ዲያብሎስ ብለው በጽሁፋቸው እንደጠቀሱት በዮሐ 10፡10 ላይ ”ሌባው ሊሰርቅና ሊያርድ፣ ሊያጠፋም እንጂ ስለ ሌላ አይመጣም” የተባለለትን የሰውና የክርስቶስ ተቃዋሚ መንፈስ ምናልባት እየደገፋችሁ እንዳይሆን እሰጋለሁ??? እግዜር ነጻ ፈቃድ በመስጠት ውብ አድርጎ ቢፈጥረንም የመሰላችሁን መደገፍና መቃወም ግን መብታችሁ ነው!!! /ሞት ወይም ሕይወት?/

  3) እራሳችሁን የኦርቶዶክስ ዋና ወዳጅና ተቆርቋሪ! ሌላውን ኦርቶዶክስ ሃይማኖትንና ቅርስን አውዳሚ አድርጋችሁ የፈረጃችሁበትን ስልጣን ማን ሰጥቷችሁ ነው? በቤተ ክርስቲያኒቷ ውስጥ ተወለደው ያደጉትን ሊቃውንት ውጡና ግቡ የምትሉት? እንደ እነ አለቃ ታየ ያሉ አባቶቻችን የወንጌል ቃል ብቻ ይብቃ! ካስፈለገም በበሬ ወለደ ወሬ ሕዝቡን የእንጀራ መበያና ከብር ማስጠበቂያ ከማድረግ የራሷ የቤተ ክርስቲያኒቷ መጽሐፍት በአትሮንሱ ላይ ተዘርግተው ዓይናማ በሆኑ የድጓ፣ የቅኔ፣ የዜማ፣ የመጻሕፍት፣ የአቋቋም ወዘተ መምህራን ፊት በሰከነ መንፋስ ነገሩን እንወያይበት ማለታችንን ታዛቢው ክርክር ሃጤአት ነውና አይቻልም የሚል መሸፈኛ አቅርበዋል! ማን ምን እንደሆነ ሕዝቡ ይወቅና የራሱን ምርጫ እንዲወስን እድል ይሰጠው የሚለውን ጥያቄ ለምን ፈራችሁት???

  4) እስከ መቼ ነው ጮሌዎች አንድ እውነትን ፈላጊና በራሱ የሚተማመን ኢትዮጵያዊ ለሃገሩና ለወገኑ ባለው ፍቅር ተቃዋሚዎች በሚደረጉት ስብሰባ ተሳትፎ ሲወጣ የተመለከተው የመንግስት ካድሬ በሚያቀርበው መረጃ ተመስርቶ መንግሥት ተቃዋሚ ነው ብሎ በመፈረጅ በወጣበት በገባበት እየተከታተለ መከራውን ሲያሳየው ተቃዋሚዎችም መንግሥት በሚያደርገው ስብሰባ የተካፈለን ሰው በዚያው መልኩ ጠልተው ሲያስጠሉና ስም ሲያጎድፉ ማየት የተለመደ ቆሻሻ የፖለቲካ ሥራ ሆኗል!!! ታዲያ እናንተ ወገኖቼ የኦንሊ ጅሰስ ተከታይ ከሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር እኛን በስላሴ የምናምንን የኦርቶዶክስ ተሃድሶን አማኞች አንድ አድርጋችሁ በመፈረጅ ለጥላቻችሁ መጠቀሚያ ስታደርጉት: ሀ/ የእምነት ልዩነቱን ጭራሺ የማታውቁ ”ጨዋ” ናችሁ ማለት ነው ? ለ/ ነው ወይስ ይህን ጉሉህ የእምነት ልዩነት ሕዝቡ ፈጽሞ አያውቅም በማለት ንቃችሁት? ሐ/ ወይስ ”ሊበሏት የፈለጓትን አሞራ ይሏታል ጅግራ” ከሆነ ነገራችሁ፡ ለመንስቱ ሥራ በመንፈሱ በእውነት ለእውነት የጠራንና የሚጠብቀን የአባቶቻችን አምላክ አይተኛም አያንቀላፋምና እስከ ነፍሳችን ህቅታ በዚህ ጉዳይ ላይ ፍቅር ብቻ ሳይሆን የሚባላ እሳት ጭምር የሆነው ጨካኙ ያስጨከነን መሆኑን ዛሬ ላይ ሆነን በሰማይ ፍቅር ስም እናረጋግጥላችኋለን!!!

  5) በመጨረሻም በጎልጉሎች አሠራር ላይ ትችት ላቀረበከው አቶ ጌትነት ጎልጉሎች ከሰጡህ መረጃ በተጨማሪ የጋዜጣው ኤዲተር ስህተት ላለመሥራት ያደረገውን ሙያዊ ጥረትና ብቃት /professional ethics/ በማስረጃ ለማወቅ ከፈለጉ ከእኔ ጋር ያደረግናቸውን የኢሜል ሙግቶች ልልክልዎ እችላለሁና ኢሜልዎን ቢልኩልኝ ደስ ይለኛል!

  ከዚህ በተረፈ ለሁለንተናዊ ችግሮቻችን በስነ ሥርዓትና በሰከነ መንፈስ ተወያይተን መፍታት የምንችልበትን ጊዜ እናፍቃለሁ!
  አባቶቻችን አደዋ ላይ እየፎከሩ ቆመው ይተኩሱ የነበረው የወቅቱ የወንድነት መለኪያ ንቃተ ህሊና ስለነበረ ነውና፣
  ወገኖቼ እባካችሁ እባካችሁ ዛሬ ላይ ቆመን ትናንትን ሚዛን አድርገን በመጠቀም:
  ወደቀ ሲባል ተሰበረ!በማለት አትንኩኝ ወይም አትድፈሩኝ! ካልሆነ ያዙኝ ልቀቁኝ!በለው!አሳደው!ውገረው!
  ለሚል የጦርነት አዋጅ በባለጉዳዩ ሳንጠየቅ ጥብቅና መቆም ሰውየው ንስሃ ገብቶ ከተመለሰ መቼ ጠየኳችሁ ሊል ይችላልና
  ማስተዋሉና የራስ ህሊና ባለቤት መሆኑ ብልህነት ነው እላለሁ!!!!
  ሊላው አፍ የሚጎርሰውን እጅ ይመጥነዋል እንዲሉ
  አንደበታችሁን ስድብ ሳይሆን መልካም የሆነ ቃል!
  የሚያስተምርና የሚያንጽ ቃል ተናገሩበት!
  የሳተ ካለ መልሱበት !!!

  ***የጠ/ሚ/ሩንና የእኛን እምነት አንድ አድርጎ ያቀረበውን ሰው አስተያየት ጎልጉሎች መረጃ ቢጠይቁ ኖሮ አያወጡትም ነበር፤
  እኔ ግን ባለማወቅ ከተነገረ መማማር ስለምንችል ማውጣችሁን ደግፊዋለሁ።

  በተረፈ ወደዳችሁም ጠላችሁም እኛ ተሃድሶዎች እንደ እናንተው በኢትዮጵያ ምድር ያውም በኦርቶዶክስ ቤ/ክ ቅኔውን ከነሰሙና ወርቁ ጋር ቆጥረን የምናስቆጥር ተቀኝተን የምናስቀኝ ያገር ተወላጆች እንጂ ከሰማይ የመጣን ዩፎ በራሪዎች /ልዩ ፍጥረቶች/ አለመሆናችንና እንደ እናንተው ለሃገርና ለወገን የምናስብና የምንጨነቅ መሆናችንን ማሳወቅ እንሻለን!!! ካልተዋጠላችሁ ከእናንተ በተሻለ መለኩ ሰው ሁሉ በልቶት በሚረካበት ፍሬ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለምድራችን ቃል በገባልን ጌታ ስም በጸጋው በሆነ እምነት ስንገለጥ ታዩናላችሁ!!!! ለሁላችንም እድሜ ይስጠን???አሜን።

  ዛሬም :

  የእናንተው ወገን!

  እውነቱ ይነገር ነኝ
  ካለሁበት

  • zibrikrik says:

   አቶ ውነቱ ይነገር ባለፈው ትችቴ ተወልደን ባደግንበት ባልከው ጽሁፍህ ላይ ተዘርተን በበቀልንበት ብለህ ጽሁፍህን እንድታስተካክል ማሳሰቢያ አቅርቤ ነበር ነገር ግን አልሆነም ፣ አሁንም ስምህን እውነቱ ይነገር የሚለውን ቀይረህ ሃሰቱ ይለፈፍ ብትለው የተሻለ ማንነትህን ይገልጸዋል ብዬ አምናለኡና እባክህ ተመከር ። ነገር በጭራሽ የማይገባህ ግለሰብ እንደሆንክ በደንብ ተረድቻለሁ ፣ እራስን መቆለልና አንቱ በሉኝ የመናፍቅ ዋና መለያ ታፔላ እንደሆነ ይገባኛል ፣ አንተ መምህር ምህረተአብንም ሆነ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖትን ተንጠራርተህ ስትዘረጥጥ አንተን ማን ባለ መብትና ባለስልጣን እንዳረገህ የታወቀህ አትመስልም ሲጀመር ነገር የሚገባህ እንዳልሆንክ ነግሬሃለሁ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ለመምህር ምህረተ አብ ብቻ የተሰጠች ሌላውን የማያገባው አድርገህ ለመግለጽ መሞከርህ በራሱ ትንሽ አይምሮ እንዳለህ ፍንትው አድርጎ ያሳብቅብሃል ። ሲጀመር አሁንም እንደማይገባህ ባውቅም በድጋሚ እነግርሃለሁ ሃይማኖት መከራከሪያ ሳይሆን ግለሰብ በፈቀደበት የሚሄድበት ጉዳይ ነው እሳትና ውሃ ቀርቦልሃል እጅህን ወደፈቀድከው መስደድ መብትህ ነው ። መምህር ምህረተ አብም መልስ ያልሰጠህ ወይንም የማይሰጥህ ከዚህ በመነጨ አስተሳሰብ ሊሆን ይችላል ካልሆነም የምትናቅ ስለሆንክ ንቆል ሊሆን ይችላል ብዬ እገምታለሁ ።

   አባ ዲያቢሎስ እንኳን ማንን እንደሚያመለክት ያልገባህ ሌላ ጠለቅ ያለ ሚስጥር ይገባሃል ብዬ ባልገምትም ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ኢትዮጵያዊ ወገኔ ነህና ላቀናህና ልደግፍህ እሞክራለሁ የለም አሻፈረኝ እንደ ርያ ከጭቃዬ ላይ ልንከባለል ተወኝ ካልክ ምርጫው አሁንም ያንተው ነው ። ነገር አይገባህም የምልህ እንዲያው ከመሬት ተነስቼ ሳይሆን እውነታው እሱና እሱ ብቻ ስለሆነ ነው ። ወንድሜ ሃሰቱ ይለፈፍ የዞረብህ እንደሆንክ ሃይማኖትንና ፖለቲካን ባንድ ላይ እየገመድክ ማቅረብህ ምን ያክል አርቆ የማያይ አይምሮ እንዳለህ አሁንም በድጋሚ ያሳብቅብሃል “ይህን በወገናችን ላይ በመረጃ የተደገፈ የጦርነት አዋጅ ስትደግፉ በኦሮሞና በአማራ ላይ የተደረገውንና እየተደረገ ያለውን ጦርነት መቃዎም የምትችሉበት ሌላ ተለዋጭ ህሊና አላችሁ ማለት ነው።” ስትል ትችትህን አቅርበሃል ፣ አየህ ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ ማለት ይሄ ነው ። እየተነጋገርን ያለነው ስለሰማያዊ እምነት እንጂ ስለ ምድራዊ ፖለቲካ እንኳን እንዳልሆነ አልገባህም በጣም ዞሮብሃል ፣ አማራ ኦሮሞ እያልክ በቅሎን ይመስል “አባትሽ ማነው ስትባል ፈረስ አጎቴ ነው” ያለችው አይነት አቀራረብ መቅረብህ የምታሳዝን ሳትሆን ሊታዘንልህ የሚገባ እንደሆንክ ምስክር ነው ። ይሄንን ላንተ ለማብራራት አልደክምም ነገር ግን የዘባረቅከውን መዘባረቅ ዝም ብዬ ባልፍም ባለማወቅህ ላይ ጭል ጭል የምትለውን የብርሃን ሻማ ከናካቴው ማጥፋት ስለሚሆንብኝ ለዘባረቅከው መዘባረቅ ባጭሩ አንድ ጥያቄ ብጠይቅህ ጥያቄው በራሱ መልስ ሊሆንህ ይችላል ብዬ አምናለሁ ጥያቄው ካልገባህ ያውቃሉ ያልካቸው አለቃ ማንትስ ያልካቸው ያንተ ሊቅ ዘንድ ሄደህ ይሄ ምን ማለት ነው ያብራሩልኝ በላቸው እሺ? ሲጀመር የአማራም ሆነ የኦሮሞ እንዲሁም የሌላው ብሄር የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታይ እንዳለ ታምናለህ? በተመሳሳይ ሁኔታ አንዲሁ ከነዚህ ብሄር ብሄረሰቦች መካከል እንዳንተው መናፍቅ እንዳለ ታምናለህ? እኔስ አማራ ልሁን ኦሮሞ የምታውቀው ነገር አለህ? አየህ ለዚህ ነው አባትህን ስትጠየቅ ፈረስ አጎቴ ነው አትበል ያልኩህ ፣ የዚህን ጥያቄ መልስ ካገኘህ ነገሮች ገብተውሃል ማለት ነው ለጥያቀዬ መልስ ከሌለህ ግን ውሃ አልወቅጥም እያዘንኩ አሰናብትሃለሁ ። ውሃና ዘይትን ለመቀላቀል አትሞክር ሚስጥሩ ከረቀቀብህ አሁንም አለቃ ማንትስዬን ጠይቀህ ሚስጥሩን ለመረዳት ሞክር ።

   አሁንም በድጋሚ አንተም በመጋዘንህ እኛም በቤተ መቅደሳችን ቃለ እግዚአብሄርን ሰምተን በልቦናችን ጽላት እንዲጽፍልን እንጸልይ እንጂ ክርክር የተፈቀደ አይደለም የያዝከውን ወንጌል (ወንጀል)አንብብ ፣ ሁሉም በያለበት የገባውን ያስተምራል ምዕመኑ የመሰለውን ይከተላል ። አንተ በያዝከው ወንጌል(ወንጀል)ላይ ባይኖርም እኛ በምንቀበለውና በምናምነው ወንጌል ላይ በይሁዳ መልዕክት ምዕራፍ ፩ ቁጥር ፫ ላይ እንዲህ ይላል፣ “ወዳጆች ሆይ ስለምከፍለው ስለመዳናችን ልጽፍላችሁ እጅግ ተግቼ ሳለሁ ለቅዱሳን አንድ ግዜ ፈጽሞ ስለተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኳችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ” ይላል አየህ ለእምነት ተጋደል ሲል አማኙን ሁሉ እንጂ ያልጠመጠመ ወይንም መምህር ምህረተአብ ካልሆነ ሌሎቻችሁ አያገባችሁም አላለም ለነገሩ የይሁዳ መልክት አንተ ላይ ስለሌለ ከየት አምጥተህ ታውቀዋለህ? ድከም ብሎኝ እንጂ ።

   አንተ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሰበከችው ፣ አስተማረችው ፣ ወየው ብለህ ጭርጭር ያረገህ ከብዙ በጥቂቱ ከዚህ በታች ያለው እንደሆነ ይገባኛል ። አዎ በቀላል አማርኛ ተብሎ አረም ብቻ በሆነው ወንጀል ውስጥ የለም አታገኘውም ግን እውነታውና ሃቁ ያሳበደህ ይሄ እንደሆነ ሳይታለም የተፈታ ነው ። ባለፈውም ጴንጤዎች ናችሁ እራሳችሁን አትደብቁ በራሳችሁ ተማመኑ የኦርቶዶክስን ልብሰ ተክህኖም ሆነ ስሟን አትጠቀሙ እዚያው ፓስተሮቻችሁን ስም አውጡልን በሏቸው ዳቦው ባይቆረስም ስም ይውጣላችሁ መናፍቃን የስም ችግር የለባቸው ይሄው ዛሬ በዓለማችን ላይ ከ33,000 በላይ ደርሰዋል ስለሆነም እናንተን 33,001 ያርጓችሁ ከሰው ትከሻ ውረዱ ።

   በል እውነተኛውን ወንጌል ፈልገህ እነዚህን ጥቅሶች ተመልከት ቢያምህም ቢመርህም ቻለው መድሃኒት ጣፍጦም አያውቅ መረር ማለቱ አይቀርምና ተዳፍረህ ተቀበለው ።

   ኦሪት ዘጽአት ፳፫፣ ፳ , ኦሪት ዘጽአት ፳፩ ፣ ፳፫ , ኦሪት ዘጽአት ፲፱፣ ፲፬ , ትንቢተ ዳንኤል ፲፪ ፣፲፮ , ትንቢተ ዘካርያስ ፩፣፲፪ , መዝሙር ፴፫ ፣ ፮ , መዝሙር ፴፫ ፣ ፳፩ መዝሙር ፴፫፣ ፲፭-፲፮ , መዝሙር ፻፩፩ ፣ ፮ , መጽሃፈ ምሳሌ ፲፣ ፮ , ማቲዮስ ፲፣ ፵-፵፪ , ወደ እብራውያን ፩፣ ፲፫-፲፬

   ወንድሜ ብዙ ብዙ ማለት ይቻላል ፣ ሆኖም ግን አውቆ የተኛ ቢቀሰቅሱት አይሰማም ነውና በዚሁ ላይ አበቃለሁ ፣ እወቅ ያለው ባርባ ቀኑ ያውቃል አትወቅ ያለው ደግሞ ባርባ ዘመኑን ደንቁሮ ያደናቁራልና ድጋሚ አንተንና መሰሎችህን በተመለከተ አልመለስም ።

   ታዛቢው

  • በለው! says:

   እውነቱ ይነገር ካልከንማ! ተመልከት ስማ ላልሰማም አሰማ!
   https://youtu.be/xd3eZ2VtWR0
   “የሌባ ዓይነ ደረቅ መልሶ ልብ ያደርቅ!”
   ፩) በኦሮሞና በአማራ ላይ የተደረገውንና እየተደረገ ያለውን ጦርነት መቃዎም የምትችሉበት ሌላ ተለዋጭ ህሊና አላችሁ ማለት ነው?
   __ የፖለቲካ ሽቀላ ይቁም!ይህ በድሃ እሬሳና እንባ መሞላፈጥ ጀግና አያደርግም! “እኛ በምንኖርበት አካባቢ ፺፰ ከመቶ ሙስሊም ስለሆነ ቀና ብሎ የተናገረውን አንገቱን በሜንጫ(በቡጢ) ነው የምንለው ሲሉ የጀዋሪያን አብዮተኞች አብራችሁ በእየአዳራሹ ታሽቋልጣላችሁ እንጂ አርባ ጉጉ፡ በደኖን የታረደ ክእነነፍሱ ታስሮ ገደል የተወረወረውን ኦርቶዶክስ..ቤተክርስቲያን በላያቸው ላይ የተቃጠለባቸውንም ክርስቲያን ኦሮሞዎች አላዳናችሁም!?።
   ፪) የፍቅርና የሰላም ወንጌል ሆኖ ሳለ ሰውንና ቅርስን የሚበላ ጦርነትን ማወጅና መደገፍ ከየት ተማራችሁት?
   ___ ተነስ! ንቃ! እራስህን ከሰው በላ ጠብቅ ማለት..ከላይ በቪዲዎቹ ማስረጃ እንዳስቀመጠኩልህ.. በርህን አፍክን ከፍተህ ሀገርና ሕዝብህን አስበላ የሚል ትምህርትና ቡራኬ አንተ ከየት ተማረክ? የፖለቲካና ሃይማኖት ወቀጣውን እንዴት እውነት ብለህ ትቅጥፋክለህ!?
   ፫) እራሳችሁን የኦርቶዶክስ ዋና ወዳጅና ተቆርቋሪ! ሌላውን ኦርቶዶክስ ሃይማኖትንና ቅርስን አውዳሚ አድርጋችሁ የፈረጃችሁበትን ስልጣን ማን ሰጥቷችሁ ነው?
   ___ ከጥንትም ሃይማኖት የግል ሀገር የጋራ ነው።አሁንም ምንም የሃይማኖት ነጻነት ቢባዛ ሃይማኖተኛ አንሷል..አስመሳይ ሸቃይ በዝቷል እያልን ነው ይሰማል? የሌላውን ሥርዓት ከመጋፋት ትውልዱን ከማወናበድ ወደሥራ እንዲሰማራ ጭንቀላቱን ባታናውጡት አወርቶ በል ጀዝባ እንዳይሆን ባትጠልፉትስ?
   ፬) “የኦንሊ ጅሰስ ተከታይ ከሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር እኛን በስላሴ የምናምንን የኦርቶዶክስ ተሃድሶን አማኞች አንድ አድርጋችሁ በመፈረጅ ለጥላቻችሁ መጠቀሚያ ስታደርጉት: ሀ/ የእምነት ልዩነቱን ጭራሺ የማታውቁ ”ጨዋ” ናችሁ ማለት ነው ?
   __ ይህ እራሱን የቻለ ዝባዝንኬ ነው…ማንነትና ምንነት እነሱው የሰጡህ መብት ነው(ጥልቅ (ተሃደሶ/ታድሶ)…አይመሳሰልም!? አዳሜ እርስ በእርስ እየተላፋሽ እንታገላለን ትያለሽ አደለም አደል?ዋሸሁ እንዴ? ”ሊበሏት የፈለጓትን አሞራ ይሏታል ጅግራ” ሰውን ጨርሳችኋል ጅግራስ ቢተርፋችሁ አደለም?
   ፭) “አባቶቻችን አደዋ ላይ እየፎከሩ ቆመው ይተኩሱ የነበረው የወቅቱ የወንድነት መለኪያ ንቃተ ህሊና ስለነበረ ነውና፣
   ወገኖቼ እባካችሁ እባካችሁ ዛሬ ላይ ቆመን ትናንትን ሚዛን አድርገን በመጠቀም:
   ___ በአድዋ ድል ሰሞን ነጋሪት ይጎሰም የሚመስላቸው ፈሪዎች እንጂ ‘ፈርሃ እግዝሕብሔር’ ያላቸው አያሰኝም። ለግልሰቡ የተጻፈን ደብዳቤ እንደ ዓለም መጨረሻ አድርጎ ጉልጉል ጋዜጣ ላይ መለጠፍ ትክክለኛነትን አያጎናጽፍም፡ ጭራሽም ጭር ሲል አልወድም የሚል አርዕስት ፈጠራ፡ የተጯጯሁና የጉልጎል ባለቤቶች ሰዓትና መልካም ሥራቸውን ለመበከል ሆን ተብሎ የተጣደ ነገር መሰለኝ!? የራሳችሁ ድረ ገፅና ጋዜጣ የላችሁም!?እዚህ ላይ የረጅም ግዜ ተጠቃሚ ነኝ እንዲህ ያለ የጸብ አጫሪ ጽሁፍ አላየሁም።ለማንኛውም ግን ይህን የጅምላ ቱማታ አልቀበልም በግሌ ህሳብ ላይ ግን ሐሳብ መስጠት ችግር የለብኝም ።
   እየተከባበርን…

   • Editor says:

    የዘወትር የጎልጉል ወዳጅ በለው፥

    በዚህ ጽሁፍ ምክንያት ብዙ ተብለናል። ነገር ግን እንደ እርስዎ ያለ ስለ እኛ አቋም ምስክርነት መስጠት የሚችል ሰው በመኖሩና ይህንንም በገሃድ በመናገሩ ለሌሎች ትምህርት የሚሰጥ ይመስለናልና ምስጋናችን ይድረስዎ።

    የማሰብ፥ የመናገር፥ የመጻፍ ወዘተ መብቶችን በማክበር ነበር ይህንን ጽሁፍ ፈቃድ ሰጥተን የለጠፍነው። ሆኖም በርካታው ምላሽ ሰጪ ሃሳብን በሃሳብ ከመሞገት ይልቅ ወደ ዘለፋ መሄዱም አማራጭ አድርጎ ስናይ ገና ብዙ ይቀረናል እንድንል ያደርገናል። ከዚህ ሌላ የሃይማኖት ጽንፈኝነት በርካታዎችን “አትንኩኝ ባይ” እንዳደረገው ምስክር ሆኗል ለማለት አስደፍሮናል።

    ኢትዮጵያውያን ከጥንት ጀምረን እጅግ ሥልጡን ሕዝብ ነን። ንግግራችንም ሆነ ሙግታችን ጨዋና ሃሳብን የሚሞግት እንደነበር የእሠጥ አገባ እና ሌሎች ተሞክሮአችን ምስክር ናቸው። ከዚያ ወርደን ዘለፋና ስድብ ውስጥ መግባታችን ያሳዝናል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ሃይማኖተኛ ነን የሚሉ ሰዎች በዚህ ረድፍ ተሰልፈው ማየት እጅግ ያሳፍራል።

    በቅኔ፥ በዘዬ፥ በሰምና ወርቅ፥ ወዘተ የከረረ ሙግት መግጠም የሚችሉት አባቶቻችን የኛን እዚህ ደረጃ መዝቀጥ ሳያዩ ማለፋቸው ዕድለኛ የሚያደርጋቸው ይመስለናል።

    የጎልጉል አርታኢ

    • በለው! says:

     “ኢትዮጵያውያን ከጥንት ጀምረን እጅግ ሥልጡን ሕዝብ ነን። ንግግራችንም ሆነ ሙግታችን ጨዋና ሃሳብን የሚሞግት እንደነበር የእሠጥ አገባ እና ሌሎች ተሞክሮአችን ምስክር ናቸው። ከዚያ ወርደን ዘለፋና ስድብ ውስጥ መግባታችን ያሳዝናል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ሃይማኖተኛ ነን የሚሉ ሰዎች በዚህ ረድፍ ተሰልፈው ማየት እጅግ ያሳፍራል።”…. “ዋናው የውድቀታችን ምንጭ ተማሪና አስተማሪው እኩል ማወራታቸው ነው።”
     __ይህ መንግስት ያወረሰን ራዕይ..’ትውልድ ማምከንና ማባከን’ ሥርዓቱን ብንቀይር እንኳ ያጠፉትን ሀገርና ትውልድ ደግሞ ለመገንባት ቢያንስ አንድ ዓርባ ይፈጅብናል።…ተፈወስ ያላለው ሕዝብ ዓርባ ዓመት ይባላል….(ቅድስት ሀገረ ኢትዮጵያ ብዙም ጫጫታ አትወድም ታስለቅሰናለች!)
     __ አዎን! “በቅኔ፥ በዘዬ፥ በሰምና ወርቅ፥ ወዘተ የከረረ ሙግት መግጠም የሚችሉት አባቶቻችን የኛን እዚህ ደረጃ መዝቀጥ ሳያዩ ማለፋቸው ዕድለኛ የሚያደርጋቸው ይመስለናል።” ፈላስፋ በዛ ልበል? አዋቂ በዛ ልበል? አውቆ አበድ ጨመረ ይሆን? ጥፋታዊ አውርቶ አደር በረከተ?
     ‘ይብላኝ ለቋሚው የሞተ ዓረፈ በለው!’ በመፈቃቀደና በመፈቃቀር ሀገሩን በክልል ለውጦ ማንነቱ የጣላ ጠፋብኝ ብሎ ይጮሃል!? ምግብ፡ውሃ፡ ጤና፡ ትምህርት ለተቸገረ የዋህ ቅን ሕዝብ ‘ፖለቲካና ሃይማኖት አብኩተው ጋግረው” ጥጋብኛ ይሉታል። ዘይገርምዩ !ሠላም ለለሁሉም ይሁን።
     ከምሥጋና ጋር!
     https://youtu.be/n90ThLH1w3M
     https://youtu.be/U8tiLCN1BNI

 5. The Angry Ethiopian/ቆሽቱ የበገነው says:

  ጉግሎች – የድህረ-ገፅ ጋዜጣ ከመክፈታችሁ በፊት፣ ጉግል ተብሎ የሚታተም ጋዜጣ ነበራችሁ እንዴ ?

 6. ጥበቡ ሞላልኝ says:

  ለታዛቢው

  በመጀመሪያ ጤና ይስጥልኝ! የእግዚአብሔር ቸርነትና ምህረት ይብዛልዎ እያልኩ ከዚህ በመቀጠል እኔም እንደ እርስዎ የኦርቶዶክስ ቤተ እምነት ተከታይ ወይም ምእመን በመሆኔ የኦርቶዶክስ ትርጉም ቀጥተኛና እውነተኛ ማለት ስለሆነ እንደ ስማችን ሆነን መገኘት አለብን ብዬ አምናለሁ።

  በመጀመሪያ ሲጀምሩ “ማንነታቸውን ለሰወሩት ወይም በማንነታቸው ለሚያፍሩት” ብለው ጀመሩ፤ ጸሐፊው እውነቱ ይነገር ብለው ስማቸውን አስቀምጠዋል፤ ነገር ግን እርስዎ እራስዎ ታዛቢው ብለው ነው ስምዎትን ያስቀመጡት፤ ታዲያ የራስዎን ስም ደብቀው የሰውን ማንነት መጠየቅዎ እርስዎ ያልሆኑትን ሌላው እንዲሆን መፈለግዎ ትንሽ ግራ የሚያጋባ አይመስልዎትም? እንደ እኔ መረዳት ቁምነገሩ ያለው ስማቸው ወይም ማንነታቸዉ ላይ ሳይሆን የጻፉት ጽሑፍ ይዘት ላይ ሊሆን ይገባ ነበር። በዚህ መሰረት ጸሐፊው ባስቀመጡዋቸው ነጥቦች ላይ አስተያየትዎን ይሰጣሉ ብዬ ስጠብቅ ምንም ተጨባጭነት የሌላቸው ሃሳቦች (Unsubstantiated argument)፣ የራስዎን ግምት ወይም ውስን እውቀት ነው ሊያሳዩን የሞከሩት። እኔ በጣም የሚገርመኝ እኛ ኦርቶዶክሳዊያን ለምን መጸሐፍ ቅዱስን ገልጠን መነጋገር እንደማንችል ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስን ጠቅሰን በተነሱት ነጥቦች ላይ ከመነጋገር ይልቅ ስድብና ምንም ፋይዳ በማይሰጥ እሰጥ አገባ ውድ የሆነውን ጊዜአችንን ማቃጠላችን ያሳዝነኛል። ኢትዮጵያዊ ነን እንላለን ግን ኢትዮጵያዊ ስነ ምግባር አይታይብንም፤ ክርስትያን ነን እንላለን ክርስቲያናዊ ስነምግባር እርሱም ወንድምህን እንደ ራስህ ውደድ የሚለውን ቃል ከነጭራሹ የምናውቀው አይመስለኝም፤ ለነገሩ የክርስትና መነሻና ዋና ማእከል የሆነውን ክርስቶስን ትተን በብዙ አማልክትና ከእውነት በራቁ ትምህርቶች ተጠምቀን እንዴት ክርስቲያን ተብለን ልንጠራ እንችላለን??? ራሳችንን በቃሉ መስተዋት ብናይ ጥሩ ነበር ብዬ አምናለሁ፤ መጽሐፍ “የጠቢብ አይን ወደ ራሱ ነው” እንደሚል ራሳችንን ብንፈትሽ ባልተፈረደብን ነበር። ሰለዚህ አቶ ታዛቢው የሌላውን እምነት ከመንቀፍዎ በፊት የራስዎን እምነት ጠንቅቀው ይወቁ እላለሁ፤ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያናችን ስድብንና ወንድምን መጥላትን አላስተማረችንም፤ ስለዚህ እርስዎም ሆኑ ሌሎች የሚሳደቡ ሁሉ እኛን ኦርቶዶክሳዊያንን አትወክሉንምና ቤተ ክርስቲያኒቱ በስርዓቷ መሰረት መድባ ሳትልካችሁ በስሟ ባትናገሩና ባታስንቋት መልካም ነው እላለሁ።

  ከዚህ በተጨማሪ ጸሐፊው ቁጭ ብሎ በጠረጴዛ ዙሪያ ስለመነጋገር ያቀረቡትን ሃሳብ እርስዎ ሲመልሱ፡ “እምነት ለመከራከሪያ አይደለም፣ ካንተ ጋር ቁጭ ብሎ የሚነጋገር የለም” ብለው ሲኖዶሱን ወክለው መልስ የሰጡ ነው ያስመሰለብዎት! ለምንድነው ተሃድሶ የሚባሉት ከኦርቶዶክስ አባቶች (ከሲኖዶሱ) ጋርቁጭ ብለው መነጋገር መፈለጋቸውን የሚቃወሙት??? ምክንያቱም በመነጋገር ወደ አንድ ከፍ ያለ ደረጃ ይደረሳል ብዬ ስለማምን ነው። እርስዎ ራስዎ በርዕስዎ ላይ ያስቀመጡት (የአርዮስ ፍሬዎች) የሚለው ታሪካዊ አመጣጡና አስተምህሮቱ እንዴት እንደ ተወገዘ አላነበቡምን??? ታሪኩን ካላወቁ ባጭሩ፦ ወደ 350 የሚሆኑ አባቶች ተቀምጠው አሪዮስ በሚያስተምረው ትምህርት ላይ ለ3 አመት ያህል ከተነጋገሩና ከተከራከሩ በኋላ ነበር 350 ከሚደርሱ አባቶች መካከል 318ቱ በአንድ ሃሳብ በመስማማታቸው ምክንያት አሪዮስንና ትምህርቱን ሊያወግዙ የቻሉት፤ መጸሃፍ ቅዱስ (በሐዋርያት ሥራ 17:10-11) ላይ ስለ ቤሪያ ሰዎች አስተዋይነት ዛሬ ላይ ያለን ሰዎች ከነሱ እንድንማር የሚከተለውን ይለናል፡ “ወዲያውም ወንድሞች ጳውሎስንና ሲላስን በሌሊት ወደ ቤርያ ሰደዱአቸው፥ በደረሱም ጊዜ ወደ አይሁድ ምኵራብ ገቡ፤ እነዚህም በተሰሎንቄ ከሚኖሩት ይልቅ ልበ ሰፊዎች ነበሩና። ነገሩ እንደዚሁ ይሆንን? ብለው ዕለት ዕለት መጻሕፍትን እየመረመሩ ቃሉን በሙሉ ፈቃድ ተቀበሉ።”
  ከዚህ የምንማረው ምንድነው? እነዚህ የቤርያ ሰዎች በጣም አስተዋዮችና ልበ ሰፊዎች እንደነበሩ ነው፤ ሐዋሪያ የሆነው ቅዱስ ጳውሎስ ወንጌልን ስለሰበከላቸው ብቻ ሳይሆን የተቀበሉት (ያመኑት)፥ ነገሩ እንደዚሁ ይሆንን??? ብለው ዕለት ዕለት መጻሕፍትን ይመረምሩ ስለነበረ ነው። ስለዚህ ኦርቶዶክሳዊያን አባቶቼ፣ እናቶቼ፣ ወንድሞቼና እህቶቼ አንድን ነገር ከመቀበላችንም ሆነ ከማውገዛችን በፊት የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸውንና የእምነት አባቶች ተስማምተው ያጸደቋቸውን ቅዱሳት መጽሐፍቶችን በደንብ በመመርመርና በማጥናት ተርፈን ቤተ ክርስቲያናችንን ማስጠበቅ ይኖርብናል፤ ለዚህም የእግዚአብሔር መንፈስ እንዲገልጥልን በጾም በጸሎት እየተጋን እውነትን ማወቅና ማደግ እንችላለን እንጂ መንፈሳዊ ነገር እንዲሁ ባካኪ ዘራፍ ፉከራ ጭራሺ የሚሆን አይመስለኝም፤ በስጋ ጉልበት የሚከናወን ሥራ ስላልሆነ!!! ዛሬም ቢሆን በኦርቶዶክስ ስርአትና ደንብ መሠረት ሊቃውንት አባቶች (ሲኖዶሱ) አንድን ሰው ወይም ማህበር ስለሚያስተምረው ትምህርት ጠርተው ከማነጋገራቸው በፊት ግለሰቡንም ሆነ አስተምህሮቱን ወይንም የዛን ትምህርት ተከታይ የሆኑትን ምዕመናኑን የማውገዝም ሆነ የመገዘት ስልጣን የላቸውም ስለሚል፤ አቶ ታዛቢው ከማን ሰምተው ወይም ተምረው ነው መናፍቅ፣ የሉተር ፍልፍሎች፣ ፍራሽ አዳሾች ወዘተ. እያሉ ሲኖዶሱ ያላወገዛቸውን እንደውም ገና ያላነጋገራቸውን ሰዎች እርስዎና መሰሎችዎ እንዴት ባለ ድፍረት ነው የምታወግዙት???? “አወቅሽ አወቅሽ ቢሉዋት የባልዋን መጽሐፍ አጠበችው” እንዲሉ፤ ይልቁንስ ይሄን አዲሱን ትውልድ ከሌሎች ቤተ እምነቶች ማትረፍ የምንችለው የቀደመችውን የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እውነተኛ የወንጌል አስተምህሮና ክርስቲያን የተሰኘንበትን መሠረት (1ኛ ቆሮ 3:10-11) ጠንቅቆ እንዲያውቅና እንዲመረምር ስንፈቅድለት ብቻ ነው። በተጨማሪም እርስዎ መጋዘን ብለው የጠሩትም ስፍራ ሆነ እኛ ቤተክርስቲያን ብለን ስለምናስቀድስበት ስፍራ መጽሐፍ ቅዱስን ካነበቡ ሲናገር፦ በአዲስ ኪዳን ቤተመቅደስ የሚለው በጌታችን በመድሃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ያመኑትን ሰዎች እንጂ ህንጻውን አይደለም። (1ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 3:16)ን ይመልከቱ።

  በመጨረሻም በጣም ልቤን ያሳዘነኝ ነገር ቢኖር ስለ አለቃ ታዬ በንቀት የተናገሩት ነገር ነው፤ ይኼውም “ሂድና ለዛ ለአለቃህ ንገረው፣ ጠይቀው፣ወዘተ.” ያሉትን ቃላቶች ሳነባቸው በጣም ደንግጪ ተገርሜያለሁ፤ ምክንያቱም እኚህ በዘመናቸው ታዋቂ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሊቅ የነበሩ፣ በቤተክህነት ዋና አገልጋይ የነበሩ፣ ኢትዮጵያን ወክለው በጀርመን ሀገር የግዕዝን ቋንቋ በ (University Level) እንዲሰጥና እስከዛሬ ድረስ ስማችንን እያስጠሩ ያሉ የቤተክርስቲያናችንን አይናማ ሊቅ ከመሬት አንስተው ሲያፈርጧቸው ሳይ ኢትዮጵያዊ ስነምግባር ይጎድልዎታል እንድል አስገድዶኛል። በባህላችን እንኳ ሙታንን መውቀስ እንደ ነውር ይቆጠራል (ሙት ወቃሽ አያርገኝ ይባላል)፤ እንኳን ጥሩ ቅርስ ጥለውልን ያለፉትን አባቶች ይቅርና ክፉዎችንም እንኳ ቢሆን በክፉ አናነሳም፤ ስለዚህ አለቃ ታዬን ፈጽመው የሚያውቋቸው አልመሰለኝምና ስለእሳቸው ማወቅ ከፈለጉ የኢትዮጵያን ክርስትናና የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን ታሪክ ጠንቅቀው እንዲያጠኑ በትህትና እጋብዝዎታለሁ።

  ብዙ የምለው ነገር ነበረኝ፤ ነገር ግን የልቤን ሁሉ አውጥቼ በአንዴ መዘርገፍ ስለማልችል ለዛሬ ይብቃኝ! በማስተዋል ሰምቶ ለሚጠቀምበት ይህ በቂ ከበቂም በላይ ነው እላለሁ።
  ቸር ያቆየን!!!

  እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!
  ጥበቡ ሞላልኝ

 7. Zibrikrik says:

  ጥበቡ ሞላልኝ ፣ በቅድሚያ ምንም የሞላልህ ጥበብ እንደለሌ ልነግርህ እወዳለሁ ፣ አንተም ሆንክ እውነቱ ይነገር ነኝ ባዩ ሁለታችሁም ስማችሁ እንዳልሆነ አንተም ታውቃለህ እኔም አበጥሬ አውቃለሁ ። ነገር አይገባችሁም የምለው ከመሬት ተነስቼ አይደለም ። አንተም ስታነብ ነገሩ በደንብ እንዲገባህ አድርገህ አንብብ ተነካሁ በሚል በግንፍለኝነት አትናገር ፣ ማንነታችሁን አትደብቁ ነው ያልኩት ጮኬ መጻፍ አልችል ጮኬ መናገር እንጂ ። ጥበቡ ተባለ እውነቱ ከናንተ የብዕር ስም አይደለም ጉዳዬ ጴንጤ ስትሆኑ አንዴ ተሃድሶ አንዴ ኦርቶዶክስ አትበሉሉሉሉሉ……….. አማርኛ ይገባችኋል? ወይንስ የማደናቆር ጨዋታ ነው የያዛች ሁት? ማስረጃ አንዲሆን https://www.youtube.com/watch?v=Hd78BCB37t0 ይሄንን ማስፈንጠሪያ ተመልከትና እራስህንና ጓደኛህን እዚያ በተንቀሳቃሽ ቪዲዮ ስለምታይ ያኔ የምናገረው ይገባህ ይሆናል ። እዚህም ናቸው እዚያም ናቸው ይላል ፓስተራችሁ ፣ አየህ ለዚህ ነው አንዴ ተሃድሶ ፣ አንዴ ኦርቶዶክስ ገለመሌ ብላችሁ እራሳችሁን እየደበቃችሁ አትምጡ የምለው ። ሁለትና ሶስት ቦታ አትረጋግጡ አንድ ቦታ እረግታችሁ ጽኑ አታታክተኝ ። እኛ የቀድሞ ኦርቶዶክሶች ዛሬ ግን ተገንጥለን ጴንጤ የሆነው ካላችሁ ያኔ በቁም ነገር ልናወራ እንችል ይሆናል ። እንዲያው ጻድቅና የተባረከ ለመምስለል እየተለሳለሳችሁ ሌላውን ምግባረ ብልሹ ለማስመሰል እራሳችሁን አጽድቃችሁ የምትለሳለሱበትን ሊቀበልህ ወደሚችለው ውሰደው እንጂ እኔጋ አይሰራም ። አሁንም በድጋሚ እንደማይገባችሁ እያወቅኩ ግን እደግመዋለሁ “ሃይማኖት መከራከሪያ አይደለም” አትከራከሩ ይላል የያዝከውን ወንጌል ተብዬ ተመልከተው ። ያንን ማለቴ ሲኖዶስን ወክለህ ተናገርክ አልክ ሲኖዶስ ነው እንዴ ወንጌልን የጻፈው? እንደናንተ ወንጌል ተብዬ ማንም ያሻውን የሚጨምርበትና ያሻውን የሚያስወጣበት መስሎህ ይሆን ወንጌሉ? መልስ ከመስጠትህ በፊት ይሄ ሰው ስለምንድነው የሚያወራው ብለህ ነገሩን ለመረዳት ሞክር ። አንተን ያስደነገጠህ ሊቃችንን ተናገርክ ነው የናንተ መሪና አቀንቃኝ የነበረውንም ሟቹን አባ ዲያቢሎስንም እኮ አባ ዲያቢሎስ ብዬዋለሁ የክህደት መሪና አቀንቃኝን የማክበር ግዴታ የለብኝም አንተ ከፈለክ ይሁዳንም ማክበር ማንገስ ትችላለህ ፣ ሲጀመር እኔ ለናንተ መልስ አልሰጥም ብዬ ነበር ነገር ግን ስሜን ጠቅሰህ ስለመጣህ ግድ ሆነብኝ እንጂ ያንተ ቢጤ መናፍቅ በየ ጉራንጉሩና በየ ስርቻው እንዳሸን ፈልቶ የለ እንዴ ፣ ልክ ሌሎች የኦርቶዶክስ መምህራን ንቀው እንደተዋችሁ ሁሉ እኔም ንቄ መተው እችል ነበር ግን እናንተ ሲንቋችሁ የተፈራችሁ ስለሚመስላችሁ እኔንም በግል ስሜን ስለጠቀስክ ያ እንዳልሆነ እንድታውቁት እንጂ የውሃ መውቀጥ አባዜ የለኝም ።

 8. ጥበቡ ሞላልኝ says:

  ለዝብርቅርቅ(ለታዛቢው)

  ሰላም ጤና ይስጥልኝ እያልኩ በመቀጠልም አስተያየትዎን ሳይ ምንም እንኳ መመላለሱን ባልፈልገውም በድጋሚ መልስ እንድሰጥዎ ተገድጃለሁ፤
  እርስዎ እየደጋገሙ ማንነት ማንነት ማንነት ይላሉ ማንነቴን እኮ እርስዎ የሰጡኝ ወይም የሚሰጡኝ ሳይሆን ልዑል አምላክ ገና ሲፈጥረኝ በራሱ አምሳል አርጎ የሰራኝ፣ ማንነቱን በውስጤ አስቀምጦ የፈጠረኝ ስለሆንኩ ስለማንነቴ እርስዎ እንዲነግሩኝ አያስፈልገኝም፤ ምክርም አልጠየኮትምና በመጀመሪያ እራስዎን ጠንቅቀው ይወቁ እላለሁ፤
  ሌላው ደግሞ አይገባችሁም አይገባችሁም እያሉ ብዙ ጊዜ ይጮሃሉ “ያብዬን ወደ እምዬ” አሉ፤ የማይገባኝ እኔ ወይስ እርስዎ??? ይመስለኛል የማይገባቹህ የሚለው ቃል እንደ ገደል ማሚቶ እየነጠረ ወደ እርስዎ እየተመላለሰ ሳይሆን አይቀርም እየደጋገሙ ያንኑ ጩኽትዎን በሃይል የሚያስተጋቡብን፤ መጽሐፍ “ሰው እንደ ሚያስበው እንደዛው ነው”፤ እንደሚል! ከጹሁፎ እንደተረዳሁት ምን አይነት ሰው ሊሆኑ እንደሚችሉ መገመት አያቅተኝም፤ ሰው ያለውን ነውና የሚሰጠው ያሎት ይሄ ብቻ ስለሆነ የሚሉትም ያንኑ ነው፤ በተጨማሪም ለኔ መልስ መስጠት የሰለቸዎት ነው የሚመስሉት ልክ ብዙ ጊዜ እንደጻፍኩልዎ ያህል፣ እኔ ብዙ የ(Social Media) ተጠቃሚ አይደለሁም፤ ይህም ሶሻል ሚድያ ጥሩ ስላልሆነ ሳይሆን እኔ ካለብኝ ብዙ ሃላፊነትና ጫና የተነሳ ጊዜ ስለሚያጥረኝ ነው፤ እናም በህይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ፣ አሁን ደግሞ ለሁለተኝ ጊዜ አስተያየት መስጠቴ ነው አመኑም አላመኑም አንዳችሁንም አላውቅም እርስዎም እኔን አያውቁኝም፤ ይሄንንም ቢሆን አንድ ወዳጄ ነው ሊንኩን ልኮልኝ እስቲ ግባና ተመልከት ብሎ ጎልጉሎችን ያስተዋወቀኝ፤ ጎልጉሎችን በዚህ አጋጣሚ ለማመስገን እወዳለሁ፤ ጥሩ ጥሩ ጹሑፉችን አይቻለሁ ደንበኛችሁ ሳልሆን አልቀርም፤ እናም በሊንኩ መሠረት ገብቼ ሲዘባርቁ ሳይ አላስችል ብሎኝ ነው የጻፍኩልዎ፣ በመሠረቱ በመጽሐፈ ምሳሌ ላይ “ሰነፍን አትገስጸው ይሰድብሃል፣ ጠቢብን ግን ምከረው ምክርን ገንዘቡ ያደርጋል” እንደሚል እያወኩ ነበር እስቲ ምንአልባት ከሰሙ በሚል ቅን ሃሳብ ተነስቼ ምክሬን የለገስኩዎት፤ እናም አቶ ዝብርቅርቅ በግድ ጻፉ ያለዎት ደግሞ የለም፤ “ሲጀመር ለናንተ መልስ አልሰጥም ነበር” ላሉት ደግሞ መልስዎንማ አየነው እኮ!ምንም ፍሬ ነገር የሌለበት ከንቱ ጩኽት! ውስጡ የሞላው ሰው ጻፍ ባይባልም እንኳ ውስጡ ጭራሽ አያስቀምጠውምና መጻፉን አይተውም፤ ሰለዚህ ላለመጻፍዎ እንኔ ወይም ሌላውን ምክንያት ማድረግ አይችሉም፤

  በተጨማሪ ደግሞ በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረውን ሰውን አይናቁ፤ “እናንተን ሲንቋቹህ የተፈራቹህ ይመስላችሗል፣ ምናምን ብለዋል” ለመከበር መርሁ (The Principle) ሌላውን መናቅ ሳይሆን ራስን ዝቅ ማድረግ ነው፤ እኔ ጨርሻለሁ ከእርስዎ ጋር እሰጥ አገባ ሙግት የምገባበት ጊዜ የለኝም፤ ባለፈው እንዳልኩዎ ቢያስተውሉ ኖሮ ያለፈው አስተያየቴ ብቻ ይበቃዎት ነበር፤ ነገር ግን ከእርስዎ ጋር መነጋገር ማለት ድንጋይ ላይ ውሃ እንደማፍሰስ መስሎ ነው የታየኝ፤ ውድ ጊዜዬን በንትርክ አላጠፋም።

  በመጨረሻም ያሳቀኝ ነገር ቢኖር እኔ እያወራሁ የነበርኩት ስለ አለቃ ታዬ፣ እርስዎ የሚያወሩት ስለ አባ ዲያብሎስ ምናምን ነበር፤ ምንም የማይገናኝ ነገር፡ “ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ” አሉ! ይሄ መቼም ጤነኝነት አይመስለኝም፤ ከዚህ በላይ የምልዎ የለኝም እግዚአብሔር ንፁህ ልብና ተሳዳቢ ያልሆነ አንደበት ይስጥዎ ከማለት በስተቀር፣ እኔ ጨርሻለሁ፤ እርስዎ እንደለመዱት መዘባረቁን መቀጠል ይችላሉ።

  “ስምን መልአክ ያወጣዋል” እንዲሉ፣ እውነትም ዝብርቅርቅ!!!

  ጥበቡ ሞላልኝ

Speak Your Mind

*